Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጎልያድና ዳዊት፤ ሃይል ከእግዚአብሄር እንጂ ከግዝፈት አይመጣም

ጎልያድና ዳዊት፤ ሃይል ከእግዚአብሄር እንጂ ከግዝፈት አይመጣም

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 12-30-18

1980 ዓ.ም. ህወሓት አብዛኛዎቹን የትግራይ ከተሞች የተቆጣጠረበት አመት ነበረ። የቤተሰቤ በጣም የቅርብ ወዳጅ የነበረችው የጎንደር ተወላጅ ሴት በዚህ የህወሓት ድርጊት ከመበሳጨቷ የተነሳ አንድ እድሜ ልኬን ልረሳው የማልችል አስደንጋጭ ነገር ተናገረች፦ "ህዝቡን ጋዝ አርከፍክፈው ለምን አያቃጥሉትም"። በሆዴ "ሳሃሊተነ ቅድስት" ከማለት በስተቀር ትንፋሽ አልወጣኝም። እንዴት አድርጌ ልተንፍስ? ወላጅ አባቴን ጨምሮ መቐለ ከተማው መሃል የሚኖሩት እህቶቼ፣ በየደብሩ አፅማቸው ያረፈው እናቶቼ፣  አያቶቼና ቅድመ አያቶቼ በእሳት ሞገድ ሲጋዩ በአይነህሊና ስለታየኝ። ድንጋጤ ብቻ አልነበረም ዝም ያሰኘኝ። ምንም እንኳ የትውልድ ቦታችን እጅግ የተራራቀ ቢሆንም ዝምድናና ወዳጅነት በሱ እንደማይወሰን ከልቤ አምን ስለነበር የሷን ያህል የሚቀርበኝ የትግራይ ተወላጅ የሆነ ሰውም አልነበረኝም። የእድሜየ ግማሹን ያህል ጎንደርና ጎጃም ስኖር "አገሬ እንጀራየ ነው" ባይ ነበርኩ። ለካ ጓደኝነቱ በሷ ህግና አመቺነት እንጂ በጋራ መተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አልነበረም። ስለዚህ በኔ ስሜት መጎዳት አልተጨነቀችም። "ወያኔ ነህ፣ ባትሆንም ትግሬ ነህ ተብየ ማእከላዊ ምርመራ ውስጥ የአራት አመት እስር በጠጣሁበት በመከራየ ጊዜ ተመላልሳ ስለጠየቀችኝ አሁንም ወዳጅነታችን የፀና ነው።

Videos From Around The World

ያ አመት በህወሓት ድል ያልተናደደ ሰው አልነበረም። ከዚህም የተነሳ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎችና መምህራን ስጋት ውስጥ ገብተው ነበር። ከሁሉም በላቀ የተበሳጩት ግን የኢሠፓው ግንባር ቀደም ካድሬ አቶ ሽመልስ ማዘንግያ ነበሩ። "የውክልና ጦርነት ነው የሚካሄድብን" አሉ የልደት አዳራሽ በተማሪ ጢም ብሎ በሞላበት። ህወሓት የማን ቅጥር ወታደር ሆና ጦርነት እንደከፈተችባቸው ከራሳቸው በስተቀር ለማንም ግልፅ ባይኖርም በጭፍን ጥላቻ ምክንያት በህወሃትና በትግራይ ህዝብ ላይ ስድብ መሆኑ ከተረጋገጠ ይጨበጨባል። በዛ ስብሰባ ላይ የሆነውም ይኸው ነበር። አዳራሹ እስኪነጋነግ ድረስ ተጨበጨበ። ወደውም ጠልተውም ስብሰባው ውስጥ የተገኙት የትግራይ ተወላጆች ተማሪው ተነስቶ ቅርጫ እንዳያደርጋቸው በመስጋት አብረው ጭብጨባውን አቀለጡት። ወይ አገሬ ማለት! እኩል ተወላጅ እኩል ዜጋ ሆኖ አንዱ ፊሪ ሌላው ተፈሪ፤ አንዱ ሰዳቢ ሌላው ተሰዳቢ የሚሆንበት ፍትህ የተዛነፈበት አገር!

አቶ ሽመልስ በህወሓት ጉዳይ ላይ ብቻ ተናግረው ቢያቆሙ ኖሮ በፓለቲካዊ ንዴትነቱ ብቻ ታይቶ ሊታለፍ ይችል ነበር። ለቀቧት ጥላሸት እንደ ድርጅት መልስ መስጠት ሃላፊነቱም የህወሃት ይሆን ነበር። የሰውየው ዋና አላማ ግን የህወሓትን ድል ከውጭ ሃይል ጋር ማገናኘቱ ብቻ አልነበረም። ዋናው አላማቸው ህዝቡ ነበር።  የጀመሩት በአገር ማዳን ጦርነት ላይ የአገር ረዳት አጥተው፣ ከሶስት የውጭ ወራሪ ሃይሎች ጋር ሲፋለሙ፣ ዘውዳቸውን ሳያጌጡበት ሳጥን ውስጥ እንደተዘጋበት፣ በታላቅ ጅግንነት ያለፉትን አሳዛኙን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስትን በመዝለፍ ነበር። በ1980 እንኳና ንጉሱን    ህወሓትን ለመዝለፍ በቂ ምክንያት አልነበረም ። ጥፋት ያላጠፋ ንጉስ ነግሦ አያውቅም ኢትዮጵያ ውስጥ። ነገስታቱን የምናስታውሳቸው ግማሽ ይሁን ሩብ ይሁን በፈፀሙት በጎ ተግባር ነው።

አፄ ሚኒሊክን በአድዋ ድል እናሞግሳቸዋለን ቀሪውን ግን ለአንባቢ ልተወው። ኢትዮጵያን አንድ ያደረጉ ታላቅ ባለውለታ አፄ ቴዎድሮስን  የጎንደር ህዝብ በሠሯቸው ግፎች በእጅጉ ከመቀየሙ የተነሳ ሳሩ ቅጠሉ በንጉስ ፋሲል ተሰይሞ እያለ ጎንደር ከተማ ውስጥ ከአንዲት አነስተኛ ሆቴል በስተቀር በኒህ ታላቅ ንጉስ የተሰየመ ነገር አልነበረም። ያች ሆቴልም ድርጅቶች በባለቤቱ ስም ይጠሩ ብሎ ደርግ መመሪያ ሲያወጣ "ቴዎድሮስ ሆቴል" ስሟ ወደባለቤቱ ስም ተቀየረች። ከኢህአዴግ ስልጣን መያዝ ወዲህ ስለቴድሮስ የማይዘፍን የለም፣ ሃውልትም ተሰርቷል፤ ከፍ ይበልም ይጨመርም እየተባለ ነው። ይህ ተገቢ ነው። ለኒህ ታላቅ ሰው ከዚህ በላይም ይገባቸዋል።

ከሁሉም የኢትዮጵያ ነገስታት በላቀ ከውጭ ወራሪዎች ጋር የተጋፈጡት አፄ ዮሃንስን ግን ከማንም የበለጠ ጥፋት ሳያጠፉ ለምን አፍ ያለው ሁሉ እንደሚቀጠቅጣቸው አገር መስጠት የማይቻልበት እንቆቅልሽ ነው። አቶ ሽመልስ ማዘንጊያ እንዲህ አሉ፦ "አፄ ዮሃንስ መተማ ሄደው የሞቱት ለሃይማኖታቸው ብለው ነው።" እንደልቡ እንዲናገር የተፈቀደለት ሰው ከሰው ሁሉ የበለጠ አዋቂ ይመስለዋል፤ ደፍሮ አፉን የሚያስይዘው ሰው ስለማይኖር። እኒህ ተናጋሪ እንዲህ የሚዘልፏቸው ሰው ከጭንቅላታቸው አቅም በላይ ናቸው። በነገራችን ላይ ሽመልስ ማዘንጊያ ከተስፋየ ወልደስላሴና ለማ ጉተማ ጋር በ1976 የተደረገው የትግራይ ተወላጆች አገር አቀፍ አፈሳ አስተባባሪ ነበሩ።

"አፄ ዮሃንስ ለሃይማኖታቸው ሲሉ መተማ ሄደው ሞቱ" የሚለው አራካሽ የሆነ አባባል ሆን ተብሎ የተቀየረው ከየትኛው ሌላ አባባል እንደሆነ ተናጋሪው አሳምረው ያውቁታል። ጎንደሮች ውለታቸውን በልተው የአፄውና መተማ ላይ ደማቸውን ያፈሰሱት ጀግኖች የልጅ ልጆችን እንደአውሬ ማሳደድ ሳይጀምሩ የሰማእቱን ታላቅ ውለታ እንዲህ ገልፀውት ነበር፦ "የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ፤ አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዮሃንስ።"

ህዝብን "የትም አይደርስም፣ አቅም የለውም" ብሎ በመናቅ ተራ ዘለፋ መናገር የሞራል ድቀት ነው። አፄው የተሰውት ህዝባቸው ለሆነው ለጎንደር ህዝብ እንጂ ለራሳቸው ሃይማኖት አልነበረም። ሃቁን ፍርጥ አድርገን እንነጋገር ከተባለ ለጎንደሮች የደረሰላቸው እኮ የትግራይ ንጉስ እንጂ የጎጃምና የሸዋ ነገስታት አልነበሩም። የጎንደር ዋና ከተማው እኮ ገዳሪፍ  ነበር የሚሆነው። "ሚኒሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣ ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ" የተባለው እኮ በምርምር ዘዴ ትምህርት "ካውንተር ፋክችዋል" የተባለውን ሁኔታ ለመግለፅ ነው።  

በነገራችን ላይ የጎንደር ህዝብ የአፄ ዮሃንስ ባለውለታዎች መሆናቸውና በሞታቸው፣ ከዛ በኋም በሆኑት የተሰማውን ቁጭት የገለፀበት ረ ዥም ግጥም ያለበት የኢትዮጵያ ታሪክ መፅሃፍ የፃፉት ሰው እኮ የትግራይ ተወላጅ አለመሆናቸው ሁሉም ያውቃል፤ ምናልባት ከአቶ ሽመልስ በስተቀር።

አሁን ያለው የትግራይን ህዝብ በአንዲት ጉርሻ እንዋጠው እንሰልቅጠው የሚለው እብሪት መነሻው ህወሓት የሃገር ሃብት ዘረፈች በእስረኞች ላይ ሰቆቃ ፈፀመች፤ ህወሓትና ህዝቡ አንድ አይነት ስለሆነ አብሮ ይቀጣ የሚለው አይደለም። ገና ህወሓት ለስልጣን ሳትበቃና ሙስና ውስጥ የመግባት "እድል" ሳታገኝ፣ እንዲያውም በአስር ሺዎች የአማራ ወጣቶችን የፈጀውን ደርግን ለማስወገድ የምትታገል ባለውለታ እያለች ጀምሮ ነበር ጦሩ የተወደረው።

ህወሃት እኮ ገና ሌብነት ሳትጀምር ነበር "ሌባ! ሌባ!" ተብላ በሰልፍ የተሰደበችው። ማክሰኞ ግንቦት 20፣ 1983 ኢህአዲግ ሠራዊት አዲስ አበባ ሲገባ የተቀበለው አዘውትሮ በቴሌቭዥን ሲታይ እንደኖረው ዘንባባና አበባ የሚያቀብለው ብቻ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ በሚያሸብር ሁኔታ የዛፍ ቅርንጫፍ  ይዘው የሚሮጡ ሰልፈኞች በከፍኛ ድምፅ "ወያኔ ሌባ!" እያሉ በጦርነት የዛሉትን ታጋዮች ሲያስጨንቁ ነበር፤ በተለይ አምስት ኪሎ አካባቢ። ልብሳቸው ከላያቸው የረገፈባቸውና እስከዛች ሰአት ድረስ ለወራት ያህል እሳትና ባሩድ ሲያሸቱ የቆዩትን ወጣቶች "ሌባ" ብሎ መሳደብ አሁን የእውነት ሌብነት ከመጣም በኋላ ይኸው የስድብ ቃል ሲደገም ሰው ለካ "ሌባ" የሚባለው ቢሰርቅም ባይሰርቅም ነው ብሎ ለመደምደም የሚያጓጓ ቢሆንም አዙረው ሲያስቡት ደግሞ የሚሰጠው ትርጉም ሰባት ቢልዮን የአለም ህዝብ ሌባ ነው ስለሚያስኝ ያስፈራል። ነገሩ ወዲህ ነው። ከጥላቻው ብዛት የተነሳ ትግሬ ሰረቀም አልሰረቀም ሌባ ነው ተብሎ ይፈረጃል። የዚህ መፍትሄው ምንድነው? የትሪልዮን ዶላር ጥያቄ ነው።

የህወሓት አባላት ወይንም ደጋፊ ናችሁ እየተባሉ፣ አይደለንም ካሉም "ትግሬ አይደለህም እንዴ እንዴት ህወሓት አትሆንም?" እየተባሉ በማእከላዊ ምርመራ ድርጅትና በመቐለ ህዝብ ድርጅት እስርቤት ውስጥ እግራቸው በ"ወፌ ላላ" እየተተለተለ ከባድ ሰቆቃ ሲፈፀምባቸውና ሲረሸኑ የነበሩት በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች ታሪክ ያሁኑ ትውልድ እንዲያውቀው አልተደረገም። የፍትህ ሰቆቃ ከደርግ ዘመን ማለት ከስሩ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለው (የነበረው?) ማንም ይፈፅመው ማንም ቁጥር 1፣ ቁጥር 2 እየተባለ ቢሠራ አስተማሪ ይሆናል፤ ቁጥር 3 አይኖርም ብለን ተስፋ በማድረግ!

እየተሠራ ያለው ግን መፅሃፍን ከመሃል ገፆች ጀምሮ እንደማንበብ የሚቆጠር ነው። አንድ ድርጊት ሰቆቃ የሚሆነውና የማይሆነው በአድራጊው ማንነት ላይ ተመስርቶ አይደለም። ይህ የአርባ አመት ሰቆቃ ቆርጦ ማቅረቡ በአጋጣሚ አይደለም። ሰቆቃ የሰብአዊነትና የህግ እንጂ የፓለቲካ ጉዳይ አይደለም። የዚህ ብሄር ተወላጅ ይፈፅመው የዛ ሰቆቃ ሰቆቃ ነው። እንዲያውም በደርግ ጊዜ ማእከላዊ ውስጥ በትግራይ ተወላጆች ላይ በመርማሪዎች ሲፈፀም በነበረው ግፍ ተጎጂ የነበሩት እስረኞችን አሁንም ያኔም " ማነው ያሰቃየህ?" ተብለው ቢጠየቁ የምን አካባቢ ተወላጆች እንደሆኑ ሆዳቸው እያወቀ ብሄር ሳይጠቅሱ "የደርግ መርማሪዎች ናቸው" ብለው ነው/ነበር የሚመልሱት። ይህ እኔው ራሴ የማውቀው ጉዳይ ነው።

በኤሪትርያና በትግራይ የሚገኘው ትግርኛ ተናጋሪ ህዝብ ከውጭ የመጣ የአረብ ወራሪ አስመስለው እነ አጥናፉ አባተ የራያና የወሎን ታጣቂ ዛላምበሳና ዓድዋ-እንቲጮ ድረስ አዝምተውት ተዋጊዎቹ አረብ አለመሆናቸውን ሲመለከት የጦር ስልቱ ጠፍቶት መሸሽ ያልቻለው የሻዕቢያና የህወሓት የመትረየስ መኖ ሆኖ ቀረ። የዘመቻው ስያሜ "ራዛ" የሚል ነበር። ራዛ በትግርኛ አንበጣ የምትበላ አሞራ ናት! የኢትዮጵያ ህዝብ ግሩም ህዝብ ነው ፊትም አሁንም የዘረኝነት መርዝ እያጠጡ የሚያሳብዱት ልሂቃኑ ናቸው። ህዝብ ፊቱን ማዞር ያለበት ወደ እርስ በርሱ ሳይሆን ወደነዚህ "ከታመሰ ባህር ውስጥ አሳ ወደ ሚያጠምዱት ጉዶች ነው።

ሰላማዊ መፍትሄ ተረግጦ ትግራይ ህዝብ ላይ ጦር ከተመዘዘ ግን በእግዚአብሄር ሃይል ከጎልያድ ግዝፈት የዳዊት ወንጭፍ እንደሚያሸንፍ ጥርጥር የለውም። ጀግና የሚወጣው በመከላከል ላይ እንጂ በማጥቃት ላይ አይደለም። ተከላካይ እንጂ አጥቂ ጀግና ተብሎ አያውቅም።

Back to Front Page