Back to Front Page


Share This Article!
Share
ምህዳሩና የመንግስት ሚና

ምህዳሩና የመንግስት ሚና

ዋሪ አባፊጣ 08-28-18

በውጭ ሀገር ሆነው በትጥቅ ትግልም ይሁን በፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲሳተፉ የነበሩ ኃይሎች ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከፍተኛ ተግባራትን ከውኗል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዓለ ሲመታቸውን ከፈፀሙበት ዕለት ጀምሮ፤ እነዚህ አካላት ወደ ሀገራቸው መጥተው በፖለቲካው ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር። ይህ የሀገራችንን ምህዳር ለማስፋት የተደረገው መንግስታዊ ቁርጠኝነት እስካሁን ድረስ በትጥቅ ትግልና በፖለቲካዊ እንቅቃሴዎች ሲሳተፉ የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶችንና አክቲቪስቶችን ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ያደረገ ነው። ወደፊትም ወደ ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ ሁኔታ ትግላቸውን ለማካሄድ የሚሹ ኢትዮጵያዊያን በዝግጅት ላይ ናቸው።

Videos From Around The World

ታዲያ ይህን ሁኔታ በጥቅሉ ስንመለከተው፤ የኢፌዴሪ መንግስት የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት ያለውን ቁርጠኝነትና ይህንንም ለመተግበር እየተጫወተ ያለው ሚና ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ምን ያህል በፅናት እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድምተግባሩ ራሱ የሚናገር ነውና።

አዲሲቷ ኢትዮጵያና የለውጥ አመራሯ የተያያዙትን የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ እንዲሁም በሀገሪቱ እየመጣ ባለው ለውጥ የመንግስት ድርሻ ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ ያረጋግጣል። በዚህም የሀገራችን የወደፊት ብሩህ ተስፋ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ለመገመት ነብይ መሆንን የሚጠይቅ አይደለም።

ርግጥ በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ አመራር እንዲህ ዓይነት ጠንካራ አቋም የያዘው በሁለት ምክንያቶች ይመስለኛል። አንደኛው፤ በትግል ወደ አመራርነት የመጣው የለውጥ አመራር አስቀድሞ የታገለው ለዴሞክራሲያዊ ነፃነት በመሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፤ ይህ በህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ወደ አመራርነት የመጣው የለውጥ አመራር በመጪው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በሀገራቸው ውስጥ ሆነው የሚሳተፉበትን ነፃ መደላድል ከወዲሁ እየፈጠረ በመሆኑ ነው። ሁለቱንም ምክንያቶቼን ዘርዘር አድርጌ ባቀርባቸው፤ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ምን ያህል በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ለውድ አንባቢዎቼ ያስረዱልኛል ብዬ አምናለሁ። እስቲ በቅድሚያ መነሻዬን ከመጀመሪያው ምክንያቴ ላድርግ።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው ባለፉት ዓመታት ቲም ለማ በመባል የሚታወቀው የሀገራችን የለውጥ ቡድን የታገለለት አንዱ ጉዳይ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ ተነፍጎ የቆየውን ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ለመላው የሀገራችን ህዝብ ለማጎናፀፍ ነው። ይህን ነፃነት ለማምጣት በርካታ ወጣቶች ሞተዋል፤ አካላቸውንና ንብረታቸውንም ከፍለዋል።

ዴሞክራሲያዊ ነፃነት በህገ መንግስቱ ላይ ሰፍሮ ቢገኝም፤ አፈፃፀሙ ግን ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ እንደሚባው ዓይነት ነበር። የዜጎች የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች ሰበብ አስባብ እየተፈለገላቸው ይታገዱ ነበር። ዜጎች የአንድ ፖለቲካ ድርጅት አባል በመሆናቸው ምክንያት ለመስማት የሚዘገንኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈፀምባቸው ነበር። በዚህም ሳቢያ ዜጎች በውጭ ሆነው ገሚሱ በትጥቅ ትግል ሌላው ደግሞ በተደራጀ ፖለቲከኛነት እንዲሁም በአክቲቪስትነት ለመንቀሳቀስ ተገደዋል።

ታዲያ በውጭ ይታይ የነበረው የተደራጀና የተናጠል ትግል ሀገር ውስጥ ያለው ችግር የወለደው ለመሆኑ እማኝ መጥራት የሚያስፈልግ አይመስለኝም ራሳቸው ሃይሎቹ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የሚናገሩት እውነታ ነውና። እነዚህ ጉዳዩች በሀገር ውስጥም ህዝቡን በእጅጉ ያስመረሩት ነበሩ። በዚህም ሳቢያ የጭቆናን ቀንበር አንቀበልም ያሉ የኦሮሚያ ወጣቶች የጀመሩት ትግል ወደ ሌሎች አካባቢዎች ስር ሰድዶ ተቀጣጥሎ ዛሬ ነፃነትን ማጣጣም ችለናል።

በወጣቶች መስዋዕትነት የተገኘው ይህ ነፃነት፤ መነሻው ጭቆናን ማስወገድ በመሆኑ ጭቆናን ለማስወገድ ሲታገሉ የነበሩ ሃይሎችን ሁሉ ማቀፍ ይኖርበታል። ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ይጠቅማል የሚሉትን ሃሳቦች ለህዝባቸው ማቅረብ አለባቸው።

ይህ እንዲሆንም በውጭ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ለማግባባትና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ አሜሪካ በማምራት ታለቅ ድል አስመዝግበዋል። እውነተኛው የዴሞክራሲ ነፃነት በሀገራችን ውስጥ እውን መሆኑንም አስረድተዋል። ይህን ተከትሎም ወደ ሀገር ቤት ያልመጡ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሀገራቸው ገብተው ለእውነተኛው የዴሞክራሲ ነፃነት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ተስማምተዋል። እነዚህ እውነታዎች የለውጥ አመራሩ በትግሉ ወቅት ይዞት የተነሳውን እውነተኛ የዴሞክራሲ ነፃነት መንገድን በማሳለጥ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን በሀገራችን ለማስፋት ምን ያህል በፅናት እየሰራ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። የመጀመሪያው ምክንያቴ ከእነዚህ ሃቆች አኳያ መታየት ይኖርባቸዋል።

ወደ ሁለተኛው ምክንያቴ ስመለስ ደግሞ፤ የለውጥ አመራሩ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ በሁሉም ዘንድ ተዓማኒ እንደሆን የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም የምርጫውን ተዓማኒነት የሚያረጋግጡ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን የሚጠቀምና በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ መንገድን ለመከተል አስቧል።

ይህን ዓላማ በመያዝ በቁርጠኝነት እየሰሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ መጪው ምርጫ በሁሉም ዘንድ የሚታመን እንዲሆን ከዚህ በፊት ይሰራበት የነበረውን የኮሮጆ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት ወደ ኤሌክትሮኒክስ አሰራር በመቀየር ምርጫው በሁሉም ዘንድ እምነት የተጣለበት እንዲሆን ለማድረግ መንግስት ይሰራል ብለዋል።

በአንድ በኩል፤ ይህች ሀገር የሁላችንም በመሆኗ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ እኩል ተሳታፊ መሆን እንዲችል ኑ አብረን እንስራ በማለት በተከታታይ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ በምርጫ ወቅት ሳይቀር ለጥርጣሬ የሚጋብዙ ማናቸውንም ነገር በመዝጋት መወዳደሪያ ቦታውን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ የገለፁት የዘመናዊ አሰራር እርሳቸውና መንግስታቸው እዚህ ሀገር ውስጥ አውነተኛው ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን ምን ያህል ፍላጎት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነው።

እውነተኛ ዴሞክራሲን ሀገራችን ውስጥ ለማምጣት በዶክተር አብይና በመንግስታቸው እየተከናወነ ያለውና የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ የሆነው የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ተግባር ማሳያ ነው ብዬ አምናለሁ።

የሁሉም ዜጎች በፈለጉት የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ታቅፈው ያለ አድልኦ የመንቀሳቀስ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው የመከበር እንዲሁም በሁሉም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ በእኩልነት የመዳኘት መብታቸው እንዲረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባው ጉዳይ ነው። ታዲያ መንግስት ይህን የሚያደርገው ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ምክንያቶች በመነሳት እዚህ ሀገር ውስጥ ከፅሑፍ ባለፈ ዴሞክራሲው በተግባር መገለፅ እንዳለበት ስለሚያምን ነው። እናም ይህ የመንግስት ሚና በሀገራችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ የፖለቲካ ምህዳርን እየከሰተ ያለና ወደፊትም የሚከስት ስለሆነ፤ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተቀራርበው በመስራት የምህዳሩ ማዕድ ተቋዳ መሆን ይኖርባቸዋል እላለሁ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ላይ የሚገኙትና ወደፊትም የሚገቡት የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች ይሁኑ አክቲቪስቶች የዚህች ሀገር ተደማሪ አቅም መሆናቸውን በማስረዳት፤ መንግስት እነዚህ አካላት ወደ ተጨባጭ ስራ ገብተው የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ በማስፋት ለሚተገብሯቸው የህግ የበላይነትን ያከበሩ ማናቸውንም ተግባራቸውን እንዲከውኑ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚወጣ የሚተነትን ፅሑፍ ነው።

Back to Front Page