Back to Front Page


Share This Article!
Share
መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ

መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ

ይልቃል ፍርዱ 07-31-18

የለውጥ መኖር ፣ የለውጥ መፈጠር፣ የለውጡ መቀጠል በሕግ የበላይነት እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን ከማክበርና ከማስከበር ጋር ተጣምሮ ካልሄደ ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ የሕግና ሥርዓት መከበር ለአንድ ሀገር ሀገርነት ለመንግሥትም መኖር መሠረታዊ መለያው ነው፡፡ሕግ የፀናበት የተከበረበት ሀገር የመልማት የማደግ ሕልሙም ዕውን ይሆናል፡፡ ሕግና ሥርዓት ከሌለ ሀገርና ሕዝብ ሊኖር ሊቀጥልም አይችልም፡፡

የዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት በያሉበት ስፍራ በሰላም መኖር መሥራት ወዘተ እጅግ ወሳኝና መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡በየአካባቢው ግጭትና ሁከት ለመፍጠር ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ እየሞከሩና እየጣሩ ያሉት ክፍሎች የሀገርንና የሕዝብን ሰላም እያደፈረሱ ይገኛሉ፡፡የጅምላ ትርምስ ከመፍጠር ወደ ነፍስ ግድያ የመሸጋገራቸውን ሂደት እያየን ነው፡፡ይሄ ዓይነቱ ሁኔታ ለሰላም የማይበጅ ስለሆነ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ቆመው ሊከላከሉት ይገባል፡፡ሰላምና ልማት ናፋቂው ሕዝብ ዕኩይ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ለፍትህ ማቅረብ አለበት፡፡

ሀገርና ሕዝብ ሰላም ካጣ ተረጋግቶ ለመሥራት ስለሚሳነው ስለልማት ስለዕድገት ማሰብ አይቻልም፡፡በሀገሪቱ የተፈጠረውን ለውጥ ለማሰናከልና ወደ ኋላ ለመጎተት የሚጥሩት ክፍሎች ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም ይህንን የማክሸፍ ዋነኛው ሥራ የሕዝቡ የራሱ ነው የሚሆነው፡፡ ሰላም ሽቶ ፣ ለውጡን ተግቶ የመጠበቅ ግዴታውን ለፖሊሶችና ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

Videos From Around The World

ብጥብጥና ሁከትን ለማረጋጋት ሲባል ብቻ የሚሠራ ሥራ ጊዜን ይበላል፡፡ብዙ ሀገራዊ ሥራ ሊሠራ የሚችልበትን ዕድል ይነጥቃል፡፡በሕዝብም ውስጥ መሰላቸትን ይፈጥራል፡፡መንግሥት እንደ መንግሥት በሙሉ ዐቅሙ ለልማትና ለዕድገት ሊያውለው የሚገባውን ጊዜ የሰላምና መረጋጋት ሥራ ብቻ በመሥራት ተጠምዶ ያሳልፋል ማለት ነው፡፡እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚፈጠረው ጠንካራ ውሳኔዎችን ለማሳለፍና በተግባር ላይ ለማዋል ካለመቻል የተነሳ ነው፡፡የዳንጎቴ ሲምንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ በመንገድ ላይ ሳሉ በመኪናቸው በተተከሰ ተኩስ ተገደሉ ፣ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በመስቀል አደባባይ የግድያ ሙከራ ተደረገ ለእሳቸው በተጠመደው ቦንብ ሌሎች ንፁሃን ዜጎች ሕይወታቸው አለፈ ፣ ከፊሎቹም የአካል ጉዳት ደረሰባቸው፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለም በመስቀል አደባባይ በመኪናቸው ሞተው ተገኙ፡፡ፖሊስ የግድያዎቹን ሁኔታ አጣርቶ መረጃ ሳይሰጥ በግድያ ላይ ግድያ እየተጨመረ ነው፡፡ሌሎች ሁከቶች እንዳይፈፀሙ ፖሊስ ነቅቶና ተግቶ የመጠበቅ ኃላፊነቱ መወጣት አለበት፡፡ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም የሚገቡት አስተማማኝ ጥበቃ ሲኖር ነውና፡፡

ችግሮች በተፈጠሩበት ቦታ ሁሉ በአግባቡ አንብቦ ተንትኖ በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዞ እርምጃ አለመውሰድ ሀገርና ሕዝብን ዋጋ ያስከፍላል፡፡እየታየ ያለውም ይኸው ነው፡፡የኢንጂነር ስመኘው ሞት ድፍን ሀገርን ዜጋ በዕንባ ያራሰ፣ የሀዘን ማቅ ያለበሰ ነው፡፡ሕዝብን ቁጣና ብስጭት ውስጥ የቀሰቀሰ ነው፡፡ለሀገር የደከመ የተንከራተተ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክትን ይዞ ለዓመታት በአባይ ንዳድ በረሀ በቃጠሎ ውስጥ ከዜጎቹ ጋር ሆኖ ሲለፋ ሲደክም ሲወጣ ሲወርድ የነበረን በርካታ የግድብ ፕሮጀክቶችን የሠራ የመራ በዚህም ሂደት ጥልቅ ልምድ ያዳበረን ሰው መንግሥትና ሕግ ባለበት ሀገር በአደባባይ ገሎ ጥሎ መሄድ እንደ ሀገር ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛል፡፡የህዝብንም እምነት ይሸረሽራል፡፡

ለሀገር ሌት ከቀን ለለፋ ሰው ዋጋው ይሄ ከሆነ ዜጎች መንግሥት ሆይ ምን እየሠራህ ነው ዋናው ስራህ የሀገርንና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ አይደለምን ምንስ እየሠራህ ነው፤ጥበቃህስ የታለ ብለው ይጠይቃሉ፡፡በሀገሪቱ ውስጥ ሕግና ሥርዓትን በመጣስም ላይ የሚገኝ ሥርዓተ አልበኝት እየነገሠ መሆኑን ሕዝብ እያስተዋለ ነው ይህ ማለት ዕኩይ ተግባር እየፈፀሙ ላሉት ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን መናድ ብቻ ሳይሆን በኔ ቋንቋ አሸባሪነት ነው፡፡ከአደባባይ ግድያ ጀምሮ በየቦታው አሳቻ ቦታ በመጠበቅ ዝርፊያ ፣ንጥቂያና ድብደባ በብዛት እየታየ ይገኛል፡፡ይህ የሥርዓተ አልበኝነት ምልክት በግልጽ እየተስፋፋ በመሆኑ ቆም ብለን በእርጋታ እናስብ ዘንድ ግድ ነው፡፡

የአንዳንዶች ደካማ የመከራከሪያ ነጥብ እንዲህ አይነቱ ነገር በሽግግር ጊዜ ይከሰታል የሚል ነው፡፡ሽግግር ማለቱን ምን አመጣው ? በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥ በተካሄደ የተሀድሶ እመርታዊ ለውጥ (radical change) መነሻነት የተካሄደ ለውጥ ነው እየታየ ያለው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ስልጣን ያመጣው ራሱ ኢሕአዴግ ነው፡፡በሀገሪቱ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አመራር በመተካት ያመጣው ለውጥ ነው፡፡ሀገሪቱን እየመራም ያለው ኢህአዴግ ነው፡፡

የድርጅቱን መሠረት ይዞ ነው የሚታረመውን በማረም የሚሻሻለውን ለማሻሻል የሚስተካከለውን ለማስተካከል የአመራርና የአሠራር ለውጥ ያስፈለገው፡፡አብዛኛዎቹ ወደ ተግባር የተለወጡት ውሳኔዎች ቀደም ሲል ድርጅቱ የወሰናቸው ነገር ግን ወደ ተግባር ሊለውጣቸው ያልቻላቸው የነበሩ ናቸው፡፡ዛሬ ወደተግባር ተሸጋግረዋል፡፡

በአጭሩ ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የሕግ የበላይነት መከበር የዜጎች ሰላም ከምንም ነገር በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ስለዚህም መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ቁርጠኛ የሆነ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡መንግሥት ለጉዳዩ እልባት ሰጥቶ ለሕዝብ ያሳውቅ ዘንድ ሕዝብ ውጤቱን ከመንግሥት ለመስማት ይጠብቃል፡፡

መንግስት ችግር በተከሰተ ቁጥር የተሰማንን ጥልቅ ኃዘን እንገልፃን አጥፊዎቹን አጣርተን ለፍርድ እናቀርባለን ከሚለው የተለመደና የሰለቸ አባባል ወጥቶ አመራሩ ለሕዝብ በገባው ቃል መሠረት መፍትሄ ማምጣት መንግሥታዊ ግዴታው ነው፡፡

አጥፊዎችን ለፍርድ ማቅረብ የሕዝብን ብሶትና ችግር መፍታት በየቦታው የሚታየውን ሥርዓተ አልበኝነት ከሕዝብ ጋር በመሆን ሙሉ በሙሉ ማስቆም ይጠበቅበታል፡፡መንግሥታዊ አመራሩ በውስጡ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን በገሀድ እያስተዋለ ያለ ችግር በውይይት በመፍታት ከቀድሞው በፀና መልኩ በመገኘት የበለጸገች ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊና ሰብዐዊ መብት የተከበረባት ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ማፋጠን ቀዳሚ ሥራው መሆን አለበት ፡፡

በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ ለማየት እንደተቻለው በለውጡ የተነሳ ጥቅማችን ተነክቷል ብለው የሚያስቡ ጥቂት ወገኖች በአራቱም ማእዘናት ዜጎችን በገንዘብ በመደለል በማሰልጠንና በማሰማራት ብጥብጥ፣ ሁከትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡እያደረጉም ይገኛሉ፡፡

በዚህም ሳይወሰኑ ብሔርን ከብሔር፣ ጎሳን ከጎሳ ለማባላትና ለማናከስ እንዲሁም ግጭቱን ወደከፋ ደረጃ ለማሸጋገር በሺዎች የሚቆጠሩ ሐሰተኛ የመረጃ ድር ማኅበራዊ ገጾችን ከፍተው ሕዝብ የማሸበር የስነልቦና ጦርነት ከፍተዋል፡፡በዚህም የሀሰት ዜናዎችን ፈጥረው ያሠራጫሉ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ችግሮችን ከልክ አሳልፎ በመለጠጥ አግዝፈው ለማሳየት እየጣሩ ይገኛሉ፡፡በማጋነን የተዛባና የማይገናኝ ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ከሌሎች ሀገራት ያገኟቸውን ምስሎች በፎቶሾፕ በማቀናበር ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት መደበኛ ሥራ አድርገው ይዘውታል፡፡በስፋት እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡ህዝቡ በአሉባልታ ወሬዎች ሳይደናገጥ ለሰላምና ለልማት ዘብ መቆም አለበት፡፡

በተጠቃሽ ምሳሌነት በባሌ ጎባ የነበረውን ግጭት ለማባባስ በማቀድ ሴራሊዮን ውስጥ ከዓመታት በፊት የነበረን አስከፊ ጭፍጨፋ የሚያሳይ ምስል በፎቶሾፕ በማቀናበር ኢትዮጵያዊ እንዲመስል በማድረግ ሕዝብን ለጦርነት ሲቀሰቅሱበት ከርመዋል፡፡በዚህ የሚገኝ ስኬት የለም፡፡ከሕዝብ እልቂት እናተርፋለን በሚል አቅደው ከሆነም ዋጋ የለውም፡፡የተዛባና ሁከት ቀስቃሽ የሀሰት መረጃዎችን ለማሠራጨት እስከ 100 ሺህ ሊደርሱ የሚችሉ ሐሰተኛ የፌስቡክ አካውንቶች ተከፍተው የጥላቻ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡የዒላማቸው ግብ ሀገሪቱን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ መክተትና መበታተን ነው፡፡ኅብረተሰቡ ራሱን ከእነዚህ ዕኩይ ዓላማ አራማጆች መጠበቅ የችግሩን ጥልቀትም ለልጆቹ ማሳወቅ እንዲጠነቀቁም ማድረግ ይገባዋል፡፡

Back to Front Page