Back to Front Page


Share This Article!
Share
የህዳሴው ግድብ ይጠናቀቃል

የህዳሴው ግድብ ይጠናቀቃል

ሰዒድ ከሊፋ 08-28-18

ሰፊ ለም መሬት እና የውሃ ሐብት ይዘን፤ በተደጋጋሚ በረሃብ ማለቃችን እና በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች እየተራቡ በዓለም ህዝብ ፊት ለልመና በመቆማችን የመንፈስ ስብራት ደርሶብናል፡፡ ስለዚህ የመቻል ሳይሆን ያለመቻል መንፈስ ነግሶብን፤ ድህነት እንደ በሬ ቀንበር ጭኖ፣ እንደ ባሪያ ቋንጃ ሰብሮ ሲገዛን ኖሯል፡፡

እንደኛ ያለ ታሪክ ላለው ህዝብ፤ እንደ ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት በራስ አቅም ለመስራት መነሳት የሚኖረው ትርጉም ትልቅ ነው፡፡ እኛ ታላቁ የህዳሴን ግድብ ለመገንባት መነሳታችን፤ የበራ ሻማን እፍ ብሎ ማጥፋት ይሳነው የነበረ ሰው፤ ተራራን ገፍቶ ለመጣል ሲነሳ ከማየት ጋር ሊነፃፀር የሚችል ለውጥ ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት እንደ አውድማ በሬ በዝማም ሸብቦ ከያዘን የአይቻልም መንፈስ መፈታት ነው፡፡ ስለዚህ፤ የህዳሴውን ግድብ ያለ ውጭ ዕርዳታ ሰርቶ ከማጠናቀቅ የሚልቅ እና እንደ ዋና ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ፕሮጀክት የለም፡፡ እንደኔ ሐሳብ፤ የህዳሴው ግድብ ለአፍሪካውያን የመንፈስ ብርሃንም ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ድንበር እና ከአሁኑ ዘመን ተሻግሮ፤ በመጪዎቹ በተከታታይ ብዙ ትውልዶች ልብ ውስጥ ሊያበራ የሚችል እና የአፍሪካ ህዳሴ ፋና ለመሆን የሚችል አህጉራዊ ክስተትም ነው፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን፤ ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጠቅሰዋል፡፡

Videos From Around The World

የህዳሴው ግድብ፤ አፍሪካን በበታችነት መንፈስ ቀይዶ ለማኖር፣ ቀፍድዶ ለመያዝ ሲባል በመሰሪ ጥበብ ከተሸረበው ሰንሰለት በማውጣት እግረ-መንፈሳችንን ከእግረ ሙቅ የሚያላቅቅ እና ካቴናን አውልቆ የሚጥል የአርነት መንፈስ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ለአፍሪካውያን የሚሰጣቸው ትርጉም ምን እንደሆነ ለመረዳት፤ ጉባ በመሄድ ግድቡን የጎብኙ አፍሪካውያንን ቃል ልብ ብሎ ማድመጥ ብቻ በቂ ነው፡፡

ምናልባት ከስድስት ዓመታት በፊት፤ ለጉብኝት ወደ ጉባ የሄዱት የአፍሪካ ሐገራት ወታደራዊ መኮንኖች፤ እንደ ማንኛውም ጎብኚ ያለውን ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ፤ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ጥሩ ሥራ ሠርታችኋል፡፡ ከገመትኩት በላይ ነው በማለት ነገር አዳንቆ ከመመለስ አለፍ ብለው፤ ለሟቹ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ለኢንጅነር ስመኘው ሽልማት ሲያበረክቱ አይተናል፡፡ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ወታደራዊ መኮንኖች መካከል፤ አንድ የዛምቢያ ወታደራዊ መኮንን፤ ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ፤ አፍሪካ ያለ ውጭ ዕርዳታ በራሳቸው አቅም ምን መስራት እንደሚችሉ አሳይቶናል ሲሉ የተናገሩት ቃል፤ ግድቡ ለአፍሪካውያን የሚሰጣቸውን ትርጉም በትክክል የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡

አፍሪካውያን ከምዕራብ የዕርዳታ አንቀልባ ወርደው በራሳቸው እግር ለመቆም ሲሞክሩ የታየበት፤ የቅኝ ግዛት ኮተት እና ግሳንግስ ተሽቀንጥሮ ሲጣል ያየንበት፣ የኢ-ፍትሃዊ ሰንኮፍ በፍትህ እጅ የተነቀለበት፣ ክፍለ - አህጉራዊ የትብብር ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ግድብ መሆኑን እያየን ነው፡፡ የሱዳኑ አምባሳደር ግድቡን ከጎበኙ በኋላ፤ ይህ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ የአፍሪካ አህጉር ግድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ፤ ለዓለም ጭምር የሚጠቅም ሥራ እየሰራች ነው ሲሉ መናገራቸው ለዚህ አብነት ነው፡፡

ባለሙያዎች እንደሚናነገሩት፤ የሕዳሴው ግድብ፤ በአባይ ተፋሰስ ሊገነቡ ከሚችሉት ግድቦች ውስጥ ትልቁ እና ለመጪዎቹ 400 ዓመታት ሊያገለግል የሚችል ግድብ ነው፡፡ ወደፊት የሚመጡ ተከታታይ ትውልዶች በልዩ አድናቆት የሚመለከቱትን ሥራ እየሰራ ያለው ይህ የኛ ትውልድ፤ ሐገሪቱን ከአንድ ሺህ ለሚበለጥ ዓመታት ቁልቁል እያወረዳት፤ እንደ ሲዖል አዘቅት ያለ ማቋረጥ እየዋጣት፣ ከተስፋ መቁረጥ ጠርዝ ከጣላት፣ የተሸናፊነት መንፈስ ያከናነባት የውርደት ጉዞ እንድትወጣ ማድረግ የቻለው ትውልድ የጀመረውን ፕሮጀክት መጨረስ አለበት፡፡ ስለዚህ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፕሮጀክቱን ሲያጓትቱ የቆዩ ችግሮችን በመለየት ፈጣን እርምጃ መወሰዳቸውን መስማታችን ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው፡፡

የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ ያቺ ድንጋይ ለእኔ፤ የውርደት ካባን ማራገፍ የጀምርንባት ድንጋይ ነች ሲሉ የገለጧት፤ እዚያ ጉባ በክብር ተቀመጠችው ድንጋይ፤ ተራ የፕሮቶኮል ወይም የማስታወሻ ድንጋይ አይደለችም፡፡ ለአንድ የታሪክ ምዕራፍ፤ እልባት ሆና የተቀመጠች ልዩ እና ክቡር ድንጋይ ነች፡፡ ከዚያች ድንጋይ በይፋ መቀመጥ በፊት እና በኋላ ነገሮች በእጅጉ ተቀያይረዋል፡፡ እኛ ስለራሳችን ያለን ግምት ብቻ ሣይሆን ዓለም ስለኛ ያለው ግምትም ተለውተጧል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየተሰራ ያለው፤ የውርደትን መራራ ጽዋ ሲጨልጥ በቆየው፤ ረሃብን፣ ድህነትን፣ ስደትን እስኪያንገሸግሽ በተጋተው፤ በመጥፎ የታሪክ ሸክም ጎብጦ እና ቅስሙ ተሰብሮ በደቀቀው፤ በዚህ በኛው ትውልድ መሆኑ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ በዚህ ረገድ ዕድለኛ ትውልድ ሊባል ይችላል፡፡ ከመከራ አዘቅት ወጥቶ ይህን ገድል መሥራት፤ በመጠኑም ቢሆን ኑሮው በሞላለት ወይም በልቶ በተረፈው ትውልድ ሳይሆን፤ ገና በልቶ መጥገብ ባልጀመረው በዚህ ትውልድ መገንባቱ ልዩ ትርጉም ይሰጣል፡፡

ይህ ትውልድ፤ ከፊተኛው ትውልድ ድህነትን ተቀብሎ፤ ከእርሱ በኋላ ለሚመጡ ትውልዶች ብልፅግናን አውርሶ ላለማለፍ ልዩ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ጠላቱን ለይቶ አውቋል፡፡ ዋነኛ ጠላቴ ድህነት ነው ብሏል፡፡ ሌሎች ጠላቶች ሁሉ፤ ከድህነት የሚበልጡ ጠላቶች እንዳልሆኑ ተረድቷል፡፡ ድህነትን እና የድህነት ሙሽራ ወይም ሚዜ የሆነውን ኋላ ቀርነትን ከማስወገድ በቀር ሌላ የላቀ ግብ የለኝም ይላል፡፡

ያለፉ አራት መቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክን ተመልክተህ፤ ከቅኝትህ የተገነዘብከውን የታሪክ ሐቅ አስፍር ብባል፤ ኢትዮጵያን እጅ ከወርች አስረው ያሰቃይዋት፣ የግሪንግሪት ጥለው የረጋገጧት ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ተናገር ቢሉኝ፤ የሀገራችን ሁለት ሠይጣን ችግሮች፤ ሐይማኖትን ወይም ጠቅላይ ግዛትን ሰበብ አድረገው የሚለኮሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ወይም ግጭቶች፤ እንዲሁም የውጭ ወራሪ ኃይሎች ቀጥተኛ ጥቃት እና ዘወርዋራ ሸፍጥ ናቸው እላለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ችግሮች፤ ለድህነት እና ለኋላ ቀርነት አሳልፈው ሰጡን፤ ድህነት እና ኋላ ቀርነት ደግሞ መልሰው ለሁለቱ ችግሮች ያቀብሉናል፡፡ ቅብብሎሹ ያለ ማቋረጥ ይቀጥላል፡፡ እንዲህ ሆኖ እዚህ ደርሰናል፡፡

ይህ ትውልድ፤ ያለፉ ተከታታይ ትውልዶች፤ የጠላቶቼ አካል የሚሉትን ነገር ሁሉ ጥላቸው እንጂ አካላቸው አይደለም አለ፡፡ የችግራችን ምንጭ ከውጭ ነው ብለው ወደ ውጭ ሲመለከቱ፤ እርሱ ምንጩ ከውስጥ ነው ብሎ የቤቱን ወለል አደላደለ፡፡ እነርሱ፤ ዕርዳታ የሚሰጠኝ ማነው ብለው፤ የውጭ ዕረዳታ ፍለጋ አይናቸውን ሲያንከራትቱ፤ እርሱ፤ በራሴ ገንዘብ እሰራለሁ አለ፡፡

ደም እና አጥነቱን ገብሮ ያስከበረውን ነፃነት፤ ድህነት እየነጠቀው በውርደት ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ድሃ እና ኋላ ቀር ብትሆንም፤ ነፃነቷ የተከበረ ሐገር ነች፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ፋና፣ የፀረ - ቅኝ አገዛዝ ትግል ቀንዲል እና ለጥቁር ህዝቦች ትግል የመንፈስ ኃይል በመሆን ታላቅ ከበሬታ የሚሰጣት ሀገር ነች፡፡

ታዲያ ኢትዮጵያ፤ ኋላ ቀርነት የተጫናት፣ ድህነት ያደቀቃት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ያደከማት፣ የተረጋጋ የመንግስት አስተዳደር መመስረት የተሳናት ሐገር ነች፡፡ ነገር ግን፤ የቅኝ አገዛዝ ኃይሎች እንደ ተራበ አውሬ በዙሪያዋ ሲያንዣብቡ እና እንደ ተኩላ መንጋ ዘለው ሊሰፍሩባት ሲያደቡ ቢቆዩም ነፃነቷን አስከብራ ኖራለች፡፡

የኛ ትውልድ፤ እንደ ሐገር በሚሊዮኖች ስንዴ ልመና እየወጣን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በአረብ ሐገር ግርድና ፍለጋ እየተሰደዱ ባለበት ሁኔታ፤ በአባቶቻችን ታሪክ ብንኮራ ራስን ማታለል ነው፡፡ ያለ ውጭ ዕርዳታ፤ የማይንቀሳቀስ ኢኮኖሚ ይዘን፣ ዳገት የሚወጣ ነፃነት አለን ማለት አንችልም እያለ፤ ከእውነቱ ጋራ ተጋፈጠ፡፡ ራሱን አልሸነገልም፡፡

ፈጣን ዕድገት ካላረጋገጥን እንደ ሀገር ህልውናችን አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል መነሻ ይዞ፤ ከድህነት ናዳ ለማምለጥ እንደሚሮጥ ሰው መስራት አለብን ብሎ ተረባረበ፡፡ የሀገሪቱን ልማት የሚያግዝ የኤሌክትሪክ ኃይል መፍጠር እንደሚገባ ተረድቶ፤ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ፈለገ፡፡ በታላቅ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነገሮችን መልክ ካስያዘ በኋላ፤ የግድቡ ግንባታ ዲዛይን ጥናት ሲጠናቀቅ፤ አበዳሪ ፈልገን እንሰራዋለን ማለት እንደማይቻል አውቆ፤ ምንም ድሃ ብንሆን ግድቡን እንደምንም እንሰራዋለን ብሎ ተነሳ፡፡ ይህ እርምጃ፤ በድህነት እየማቀቀ ቢኖርም ነጻነቱን አስጠብቆ ለዘለቀ ህዝብ ታላቅ ኩራት ነው፡፡ እስከዛሬ ያጣነውን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ነፃነት የተቀዳጀንበት ልዩ ታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ የመሆን ታሪካችን ሌላ ገጽታ ነው፡፡ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፤ ኢትዮጵያውያን ያለ ውጭ እርዳታ ምን መስራት እንደሚቻል አሳይተውናል በሚል ዳግመኛ የነፃነት አብነት አድርገው እየተመለከቱን ነው፡፡ የህዳሴው ትውልድ፤ ሐገራችን ለብዙ ዘመናት የማይፈታ እንቆቅልሽ ሆኖ የተቸገረችባቸውን ነገሮች እየፈታ በድል እየተረማመደ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ፤ የጦርነት ቀጠና ለሆነው የአፍሪካ ቀንድ የውሃ ማማ እና የኤሌትሪክ ኃይል ጎተራ ብቻ ሳይሆን፤ የሰላም ካስማ እና ዋልታ በመሆን ስሟ የሚጠራበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ የቀጠናው የዳቦ ቅርጫት ለመሆን የምትችልበትም ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር የሆኑት ዶ/ር ኒኮሳዛኒ ዲላሚኒ ዙማ፤ በአንድ ወቅት ከሚት ኢቴቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤

እንደ ህዝብ ወደፊት ተመልካች መሆን አስፈላጊ ነው፡፡ ለምናባችን ወይም ለራዕያችን ሰፊ ሜዳ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ወደፊት ተመልካች የመሆን የአዕምሮ አዝማሚያ፤ ለራዕያችን ተፈፃሚነት ሊያግዘን የሚችል አዲስ ጎዳና ይከፍታል፡፡ ራዕይህን መንከላወሻ ሜዳ አትንፈገው፡፡ አስቀድመህ፤ የትም አልደርስም ብለህ አትነሳ፡፡ የትም አልደርስም የሚል ሐሳብ ሲገዛህ፤ ይኸው ሐሳብህ ተጨባጭ እና እውን ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ ሐሳብህ፤ ራሱን ለማስፈፀም የሚችል ትንቢት (self- fulfilling prophecy) ይሆናል፡፡

ሁሌም ችግሮች መኖራቸው አይቀርም፡፡ ዋናው ነገር እነኚህን ችግሮች እንዴት ልናስወግዳቸው እንችላለን ብሎ፤ አቅጣጫ ተልሞ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ከዚያም አልፈህ፤ የዛሬ ሃያ፣ ሠላሣ ወይም ሃምሳ ዓመት የት መድረስ እንደምትፈልግ ማሰብ ይኖርብሃል፡፡ አዕምሮህ ዛሬ በተዘፈቅህበት ችግር ተወስኖ ሲቀር፤ ትኩረትህ እሱ ብቻ ሲሆን፤ ችግርህ ራሱን መላልሶ የሚወልድበትን ዕድል ትሰጠዋለህ፡፡ በጠላኸው ነገር ትወረሳለህ፡፡ የለውጥ የመጀመሪያ እምራፍ፤ ይኸ ነገር እንዲህ መሆን የለበትም፡፡ የኔ ህይወት ከዚህ የተለየ መሆን አለበት የሚል ቁርጠኛ ሐሳብ መያዝ ነው፡፡ ይህን ቁርጠኝነት ይዘህ ነገን ማለም አለብህ፡፡ ትኩረትህ ዛሬ በምትገኝበት መጥፎ ሁኔታ ብቻ መቀንበብ እና መወሰን የለበትም፡፡ ይኸ ነገር መቀየር አለበት ብለን፤ ነገ ሆኖ ማየት የምንፈልገውን ጉዳይ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ወደፊት ተመልካች ሆነን፤ ዛሬ ያለውን ችግር ለመፍታት መጣጣር ይገባናል፡፡ የህዳሴው ግድብ ይጠናቀቃል፡፡ ኢትዮጵያም የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ትሆናለች፡፡

 

Back to Front Page