Back to Front Page


Share This Article!
Share
ታሪክ ቀያሪው ትስስር

ታሪክ ቀያሪው ትስስር

እምአዕላፍ ህሩይ 07-29-18

ትናንት እንዲህ አልነበረም። በሁለቱ ሀገራት መካከል በተፈጠረው ሞት አልባ ጦርነት ሳቢያ ውጥረት ነግሶ ነበር። ውጥረቱ በሀገራቱ ውስጥ ብቻ የታጠረ አልነበረም። ከዚያም ተሻግሮ፤ የቀጣናው ሀገራት በአብሮነትና በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ የተፈጥሮ ፀጋዎቻቸውን ለሁሉም ሀገራት በሚበጅ መልኩ መጠቀም እንዳይችሉ ያደረጋቸው ነበር።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ያሳለፉት የባከነ ጊዜ፤ ከራሳቸው አልፎ ምስራቅ አፍሪካ ውስጥም አሉታዊ አሻራ ማሳረፉ ግልፅ ነው። ለምሳሌ ያህል፤ ሶማሊያ ውስጥ ግጭት ሲነሳ፤ የሁለቱ ሀገራት ስም በተዘዋዋሪ ምክንያትነት ሲጠቀስ እንደነበር ማንሳት ይቻላል። ይህም በጉዳዩ ውስጥ ሁለቱ ሀገራት ቢኖሩበትም ባይኖሩበትም፤ ስማቸው እንዲነሳና የክፍለ አህጉሩም ሰላም በሀገራቱ ሰላም መሆንና አለመሆን ላይ ያጠነጠነ መሆኑን እንዲነገር ምክንያት ሆኗል።

Videos From Around The World

በእኔ እምነት ይሁ ሁኔታ ሀገራቱ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ገፅታ ሊኖረው እንደሚችል የሚያመላክት ነው። ስለሆነም ሁለቱም ሀገራት በምስራቅ አፍሪካ የሚኖራቸውን ሚና መለስ ብለው በመቃኘት ለቀጣናው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሲሉ የፈጠሩት የሰላም አውድ ቀጣናውን የተጠቃሚነት ማዕድ የሚያቋድስ ነው።

እናም ሁለቱም ሀገራት በደረሱባቸው የሰላም ስምምነት ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ መነቃቃት ፈጥሯል። የቀጣናው አገራት በጋራ ሰርተው በጋራ ለማደግ ያላቸው ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠናከረ ነው። ትስስራቸውን በማጥበቅ ላይ ይገኛሉ። በሰላም፣ በልማትና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ያላቸውን ግንኙነት ለማጥበቅ በትጋት እየሰሩ ነው። ኢትዮጵያና ኤርትራ በፈጠሩት የሰላም ትስስር፤ ቀጣናውም እየተሳሰረ ያለበትን ክፍለ አህጉራዊ ችግሮች በጋራ ለመፍታት በመስራት ላይ ናቸው።

የቀጣናው አንዱ ሀገር የሌለውን ከሌላው እንዲጠቀም የሚያችሉ የዲፕሎማሲ ድሎች እየፈኩ ነው። እየደመቁም ነው። የፍካትና የድምቀት ድባባቸውም በለውጦች የታጀቡ ናቸው። ከዚህ ቀደም የነበረውን ቀጣናዊ ሁኔታ በመቀየር ለህዝቦቻቸው ታላቅ የምስራችን እያሰማ ነው። ትስስሩ ታሪክ ቀያሪ ሆኗል ማለት ይቻላል። ርግጥም ምስራቅ አፍሪካ በተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለ በመሆኑ፤ በቀጣናው ሀገራት መካከል የሚኖር ጠንካራ ትስስር የህዝቦቻቸውን ዕድገትን በማምጣት ህይወታቸውን በሚፈለገው ደረጃ ለመቀየር የሚያስችል ነው። እናም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት የተቀየደው የሰላም መንገድ፤ የክፍለ አህጉሩን ህዝቦች ቀዳሚ የተጠቃሚነት ህፀፆች የሚያርምና ትስስሩን ወደ መሬት አውርዶ በገሃድ እንዲታይ ያደረገ ነው።

ታዲያ ይህን ትስስር በሚገባ ለመገንዘብ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተቀየረውን ታሪክ መመልከት ይገባል። በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተፈረመው የሰላም ስምምነት ለሀገራቱ ሰላምና ዕድገት ፋይዳው የላቀ ነው።

አንዳንድ አካላት በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች ላይ የሁለቱን ሀገራት ሰላም ፈጥሮ ህዝቦቻቸውን ተጠቃሚ የማድረግ ፍላጎትን በማጠልሸት በህዝቡ ዘንድ ብዥታን ለመፍጠር ቢሞክሩም፤ እነዚህ አካላት ሰላም ለህዝቦች ሁለንተናዊ ጥቅም ማስገኛ መሳሪያ መሆኑን የተገነዘቡ አይደሉም። ወይም ሊያውቁ የሚፈልጉ አይደሉም። ሁሌም በውጥረትና በስጋት ውስጥ መኖርን የሚፈልጉ ናቸው። ዳሩ ግን፤ ውጥረት፣ ስጋትና መሳቀቅ ምን ያህል አስከፊዎች እንዲሁም በህዝቦች የልማት ስራ ውስጥ ምን ያህል ቅስም ሰባሪዎች እንደሆኑ ያለፉት 20 ዓመታት ህያው ምስክሮች ይመስሉኛል።

በተለይም በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች በሰላም ውስጥ እንዲያልፉ መደረጉ ከጠቀስኳቸው የውጥረት፣ የስጋትና የመሳቀቅ የዕለት ተዕለት ህይወታቸው መላቀቅ ችለዋል። እነዚያ ህዝቦች ከአሁን አሁን ጦርነት ይነሳ ይሆን?፣ ጦርነቱስ ከተነሳ በህይወት እንኖር ይሆን? ዕጣ ፈንታችን ምን ይሆናል?...ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ነበር።

በእንዲህ ዓይነት የስጋትና የሰቀቀን ህይወት ውስጥ ዕለታዊ ኑሮውን የሚገፋ ህዝብ የልማት ሃይል ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ሃሳቡን ወጥሮ የሚይዘው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው። ስለ ልማትና ስለ ዕድገት ሊያስብ አይችልም። ሁሌም መሳሪያ አንግቦ ትንኮሳ እንዳይፈፀምበት ጊዜውን በስጋት ያሳልፋል እንጂ፤ አካፋና ዶማ ይዞ ለልማት የሚነሳሳበት ሞራልና ትጋት አይኖረውም። ይህ ሁኔታ ግን በአዲሱ ትስስር ተሰብሯል። የውጥረት፣ የስጋትና የሰቀቀን ህይወት ከድንበሩ አካባቢ ተወግዶ እፎይታ ሰፍኗል። ነዋሪዎቹ ዛሬ የሚያስቡት እንደምን ከኤርትራ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በአንድነት እንደሚኖሩ፣ የጋራ ንግዳቸውን እንደሚያከናውኑና ተጠቃሚ ሆነው ህይወታቸውን እንደሚቀይሩ ብቻ ነው። ውጥረት፣ ስጋትና ሰቀቀን ደህና ሰንብቱ ተብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች ከድንበር አካባቢዎች እንዲርቁ መደረጋቸው ሌላኛው የህዝቦች የእፎይታ ምንጭ ነው። እንደሚታወቀው ሁለት አገራት የሰላም ስምምነት ሲፈራረሙ፤ ስምምነቱ መሬት ላይ ወርዶ መተግበር ይኖርበታል። ይህን ተከትሎም ሀገራቱ የተስማሙበት ወታደሮችን ከድንበር አካባቢዎች የማንሳት ተግባር ተፈፃሚ በመሆኑ ስጋትንና ሰቀቀንን እንዲሁም ውጥረትን ማስወገድ ተችሏል። በወታደር በመጠበቅ የሚከናወን የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነት አይኖርም።

እናም ይህን ለማድረግ በድንበር አካባቢ የሰፈሩትን የሁለቱንም ወገን ወታደሮች ከቦታው አርቆ የሰላምን ትክክለኛ አየር በድንበር አካባቢዎች ማንፈስ ያስፈልጋል። በድንበር አካባቢዎች የተፈፀመውም ይኸው ነው። ይህ ርምጃም ዛሬ የድንበር አካባቢ ህዝቦችን በንግድ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ተሳስቦ በመኖር ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ በማስተሳሰር፤ ህዝቦች እንደ ሁለት ሳይሆን እንደ አንድ እንዲተያዩ ያደረገ ክስተት ነው።

የስምምነቱ ሌላኛው ማዕቀፍ የጋራ ተጠቃሚነትን በማስፈን ተያይዞ ማደግን መፍጠር ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት በኤርትራዊያን ወንድሞቻችን ዘንድ ሲካሄድ የነበረው የአሰብ ወደብን ስራ የማስጀመር ተግባር ተጠናቋል። የሁለቱም ሀገራት መሪዎች ወደቡ አገልግሎት በአፋጣኝ የሚጀምርበት ሁኔታ እንዲመቻች በቅርቡ መመሪያ በመስጠታቸው በሁለቱም ሀገራት በኩል ዝግጅት ተጀምሯል።

ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ ወደቡን ለመጠቀም የመንገድ ጥገና ስራን እያከናወኑ ናቸው። ሁሉም ነገር አልቆ ወደ ስራው ሲገባ ሁለቱም ሀገራት ከወደቡ ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ለመገመት አይከብድም። ምክንያቱም ወደቡ ኢትዮጵያ ገቢና ወጭ ዕቃዎቿን በአሰብ በኩል ማስገባት የምትችልበትን አማራጭ እንድታገኝ ስለሚያደርጋት ነው።

ይህም በተለይ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለኢኮኖሚ ግንባታ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች በፈጣንና ቀልጣፋ ሁኔታ እንዲያገኝ የሚያስችለው ይመስለኛል። ወደ ወደቡ የሚያስኬዱ ከተሞችም በዚያው ልክ ያድጋሉ። ከተማዎቹ የንግድ ዝውውር ቀጣናዎች ስለሚሆኑ በውስጣቸው ያለው ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን በር ይከፍትለታል። ላለፉት 20 ዓመታት የነበረው የውጥረት፣ የስጋትና የሰቀቀን ታሪክም በህዝቦች ትስስር እየፈካ ተጠቃሚነት እንዲደረጅ ያደርጋል። የትናንት ስጋቶች ወደ ታሪክነት ጎራ ይደባለቃሉ። ታሪክ ቀያሪው ትስስር፤ በቀጣዩቹ ጊዜያት ወደ ላቀ ሰላም፣ ወደ ጠንካራ የህዝቦች አንድነትና ቀረቤታ ምዕራፍ ያመራናል።

 

 

 

 

 

 

Back to Front Page