Back to Front Page


Share This Article!
Share
የህዝቦችን የትግል ውጤት ያንኳሰሰ ተግባር ህዝቦችን ኣይደምርም

የህዝቦችን የትግል ውጤት ያንኳሰሰ ተግባር ህዝቦችን ኣይደምርም

ከኣሉላ የውሃንስ  መቐለ  28 ሰኔ 2010 ዓ/ም

የኢትዮጵያ ህዝቦች በቅድመ ኢህኣዴግ በነበሩት ዘመናትበጨካኝና ሰው በላ ስርዓቶች የደረሰበት ኣሰቃቂ ተግባር ተዘርዝሮ የሚያልቅ ኣይደለም፡፡ ዓለምን ጉድ ያሰኘ እልቂት ያውም ኣምራች ሃይልና ሙሁሩን እንደ እብድ ውሻ በጠራራ ፀሃይ በድብቅ ብቻ ሳይሆን በመሃል ከተማ በሚገኙ ኣውራ መንገዶች ጭንቅላታቸውን ፈርሶ ለሌላው መቀጣጫ በሚል ያለቁት ቤታቸው ይቁጠረው፡፡ በጣም የወላጆችን ልብ የሰበረ፣ ጧሪ ይሆኑኛል ብለው ያሳደጉዋቸውና በሌለ ኣቅማቸው ያስተማሯቸን ልጆቻቸው በየጎዳናው ተጥለው ሲያገኙዋቸው ለኣእምሮ ቀውስ፣ ለእድሜ ልክ በሽታ፣ ለኣካላ ስንኩልነትና ለሞት የተዳረጉ ወላጆች በጣም በርካታ ናቸው፡፡ እስከኣሁንም ቢሆን በሂወት ያሉ ጥቁር ልብሳቸው ያላወለቁና ከቁስላቸው ያላገገሙ በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ስለነዚህ ሰለባዎች ሳስብና ለመፃፍ ስሞክር በራሱ ልቤ እየተነካና እምባየ እየተናነቀኝ ስለሆነ ሙሉውን መግለፅ ተስኖኝ ነው፡፡ 

የኣሁኑ ኣያርገውና ጎንደር ውስጥ በተፈራ መላኩ ዘመን ወላጆች መላኩ ተፈራ የእግዚኣብሄር ታናሽ ወንድም የዛሬን ማርልኝ ከእንግዲህ ኣልወልድም ያስባላቸው መሆኑን የትናንትናው ትውስታችን ነው፡፡ ኣገላለፁ ይለያይ እንደሆነ እንጂ በዚህ ሰው በላው ዘመን በኣራቱም የሃገሪቱ መዓዝናት ወላጆች ከለቅሶ ባሻገር ኣንጎርጉረውበታል፡፡

Videos From Around The World

ይህንን ስርኣት ያንገሸገሸው የኢትዮጵያ ህዝቦች በኢህኣዴግ መሪነት ክቡር ሂወታቸውን ገብረው ስርኣቱ ላይመለስ ቀብረውት ነበር፡፡ ለ27 ዓመታትም የሰላም ኣየር መተንፈስ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ስርኣታት ያሳልፉት ከነበረው መራራ እና ስር የሰደደ ድህነት ከነበረው ጋር ሲወዳደር እምርታ ኣሳይተዋል፡፡ ኣገሪቱን ለዘመናት ይግጥዋት ከነበሩ ገዢዎች በመቶ ዓመት ውስጥ ከኣንድ ለናቱ የነበረው የኣዲስ ኣበባ ዩኒቨርሲቲ በዘመነ ኢህኣዴግ 42 ተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎችን በመላ ሃገሪቱ ተከፍቷል፡፡ በመሰረተ ልማትም ካለመገናኘት ወይንም በጣም ብዙ ቀናትን በኣስቸጋሪ መንገድ ተሰቃይቶ ይደረስ የነበረው በዘመነ ኢህኣዴግ ካለው ስር ሰዶ የቆየው ችግር በቂ ባይሆንም ዓለም የመሰከረለት እምርታ ተመዝግበዋል፡፡ በኣስፋልትና ደረጃውን በጠበቀ ጠጠር መንገድ ክረምት ከበጋ መገናኘት የተቻለበት ግዜ ደርሰናል፡፡ ምንም እንኳ በኢህኣዴግ ውስጥ ባለው ስር የሰደደ ሙስና ደረጃውን በጠበቀና የታለመለትን እድሜ ማገልገል በሚችልበት ተደርጎ የተሰራ ኣለመሆኑ የሚሰማኝ ቢሆንም፡፡ በኣየር መንገድ፣ በመብራት፣ በተሌ፣ በጤናና በትምህርትቤቶች መስፋፋትና ሁሉም ጤናውን እንዲጠበቅና የትምህርት እድል ማግኘት እንዲችልና በመሳሰሉት ዓለም የመሰከረለት እምርታ የተመዘገበ መሆኑ የሚካደ ኣይደለም፡፡ 

ታድያ እንደዚህ ስል ኢህኣዴግ የተዋጣለት ድርጅት ነው፣ ድርጅት ነው ለማለት ከጅሎኝ ኣይደለም፡፡ መልካም ኣስተዳደርንና ፍትህን ያለህ በሚያስብል በከፍተኛ ደረጃ ችግሮችን ሲከሰቱና እነዚህ ሰዎች እያስቸገሩን ነው ሲባል ከኣንድ ቦታ ወደሌላ በማዛወር በህዝቡ ላይ ስቃዩን እንዲቀጥሉበት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ኢህኣዴግ ያን ሁሉ ጥረቱ መና ከሚያስቀሩለት ሰዎች መቆራረጥ ባለመቻሉ እነሆ ለከባድ የህዝብ ብሶት ተዳርጎ በኣሁኑ ሰዓት በሞትና በሂወት መካከል

ለመኖር ተገድዶ ታይተዋል፡፡ በፖለቲካው ምህዳሩም ስንመለከት በጣም የጠበበ፣ ስልጣኑን የተቆናጠጡት የኢህኣዴግ ኣመራሮች ከነሱ በስተቀር ሌላ ማስተዳደር እንደማይችል ኣስበው እስከመጨረሻው በወጣቶች መተካትን ሳይመርጡ በመቆየታቻው ኣሁን ለደረስንበት ደርሰናል፡፡

ታድያ እንዲህ ሆኖ ሳለ በውጭ ሃይሎች ዙርያ መለሽ ጫናና በሁኔታዎች ኣስገዳጅነት የኣመራር ለውጥ፣ ያውም ወጣት ኣመራር መምጣቱ በጣም በርካታ የሃገሪቱ ህዝቦች ያስደሰተ ነበር፡፡ ከኣዲሱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ይወጡ የነበሩ ቃላትም ማርማር የሚሉና ኣሁንም እንዳሉ በእውን ቢተገበሩ ለውጥ ፈላጊው ህብረተሰብ የሚያስደስቱ ናቸው፡፡ ድሮ ድሮ ሰው ማመን ቀብሮ ነው የሚለውን ተረት ግን እውን እየሆነ፣ የህዝቡ ትግል የሚያሽመደምዱ ሁኔታዎች መከሰት መጀመራቸው ኣደብ ካልተበጀለት ሃገራችን ኣይታው ወደማታውቀው ቀውስ የሚያስገባን ይመስለኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወደ በትረ ስልጣን የወጡበት መሰላል ምን ይሁን ምን ለጊዜውም ቢሄን እፎይታና መረጋጋት በመፈጠሩ ህዝቡ ሰላም ፈላጊ በመሆኑ ምስጋናና አድናቆት ችሮኣቸው ነበር፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ   ሁለት ወራት ሳይሞላቸው፣ የዘመሩለትን የመደመር፣ መፋቀርና ይቅር መባባል ሳይደርቅ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ከማይዋጥላቸውን የትምክህተኞች የበላይነት እንዲሁም የግዛት ተስፋፊነት ከተጠናወታቸው ሃይሎች ጋር መጋባት የጀመሩና የመጡበትን ብሄር የረሱ ይመስላሉ፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በብሄር ብሄረሰቦች መራራ ትግል ከፍለው እውን ያደረጉትን ራስን በራስ የማስተዳደር መታቸውና በህዝቦች ይሁንታ ፀድቆ በመተግበር ላይ የነበረውን ህገመንግስት በፍጥነት የሚንዱ ሃይሎች መጠቀምያ መሳርያ ህየሆኑ እያየን ነው፡፡ ለማሳያ ያክልም፡ ያለውን ህግና ሳያሻሽሉና ከፓርላማው ይሁንታ ሳያገኙ በከፍተኛ ወንጀልና ሙስና በህግ ጥላ ስር የዋሉትን መፍታት ብቻ ሳይሆን እንደተፈቱም የጀግና ኣቀባበል እንዲደdረግላቸው ማድረግ፣ ፀረሽብር ህጉ በኣግባቡ ሳይሻሻል ኣሸባሪዎችን መፍታትና እንደ ኣንድ ጀግና በቤተመንግስት ኣስገብቶ ማወያየት በይቅርታ ተፈትተዋል ከሚለው ጋር የሚጣረስ ነው፡፡

ህዝበኛ ካልሆነ በስተቀር ኣንድ ለሃገሩ የሚሰራ መሪ እኔ ነኝ እንዲህ ያደረግኩኝ እንዲህ የሚለውን ፊልም የፃፍኩኝ እናም ኣመስግኑኝ ይላል ብየ ባላምንም ኣዲስ ኣበባ ለተካሄደው የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ኣዘጋጆች በሰሩት ወንጀል ብህግ ጥላስር የነበሩና በኢህኣዴግ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው መሆናቸው ሳያንስ በዚሁ ሰልፍ ላይ የተስተጋቡት መፈክሮች፣ የተውለበለቡ ባንዴራዎች ከምስጋና ያፈነገጠና ለሌላ ኣላማ ማስፈፀምያ  ማለትም ህገመንግስቱን በጠራራ ፀሃይ የናደ ሆኖ ሳለ ለዚህ ፀረ ህገመንግስታዊ ሰልፍ ሽፋን ኣልሰጣችሁም ብሎ መክሰስና እስከኣሁንም ኢኤን ኤንን መዝጋት እሳትና ሌሎች የነውጥና የጥላቻ ሚድያዎች ግን ከውጭ ኣገርቤት ገብተው እንዲሰሩ መፍቀድ የማናለብኝነትነት የተቃርኖ ውሳኔ ነው፡፡ ነገ ዛሬ ኣይደለምና ይህንን እርምጃ የወሰዱ ሰዎች ታሪክ ይቅር እንደማይላቸው ልብ ያለው ልብ ሊል ይገባል፡፡ በተመሳሳይ ሙሉ በሙሉ የመደመር፣ ኣንድ ህዝብ፣ ኣንድ ባንዴራና ኣንድ ህዝብ ብቻ የመሆንን ፌደራል ስርዓቱ መፍረሱ የተበሰረበት ሰልፍ በባህርዳር ተካሂዴዋል መሪዎችም በእጅጉ ደንፍተዋል፡፡ እነዚህ መሪዎች የኣምሃራ ህዝብ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲያጣ ሲደረግ በባዶ እግሩ ሲደኸይ ኣመራር ሲሰጡ የነበሩ መሆናቸው ግልፅ ሆኖ ሳለ ኣሁን ከ 27 ዓመታት በሃላ እንዲህ ኣይነት የህዝብን ቀልብ ለማማለል የተጠቀሙበት ንግግር ከሲኣይኤና በውጭ ሃገር ከሚኖሩ ትምክህተኞች በሚሰጣቸው ትእዛዝ ነፍጠኝነት ለማስፈንና ያረጀውን ስርዓት እንዲያስንሰራራ ለማድረግ እንዲያግዛቸው በህዝቡ ጉያ ለመሸሸግ ያስችላቸው ዘንዳ ብቻ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በሰፊው የኣምሃራ ህዝብ ቁማር በመጫወት ሚስኪኑን እንደገና ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ለመማገድ እየሞከሩ ያሉት ሚስቶቻቸውንና ልጀቻቸውን ኣሜሪካ ውስጥ ኣስቀምጠው በሰላምና በምቾት ያለምንም ስጋት

እየተማሩና እየኖሩ ያለት ከጌቶቻቸው በሚከፈላቸው ገንዘብ መሆኑ እውነተኛው የኣምሃራ ህዝብ ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል፡፡

በጣም የሚደንቀውና ኣደናጋሪ የሆነ ውሳኔም ከበስተጀርባ እሚገፋቸው ሃይል እንዳለ ግልፅ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግላቸው ወስደዋል፡፡ ይኸውም በህዝብና በሃገር ግፍ የሰሩና በዚሁ ተግባራቸው እንዳይጠየቁ ላለፉት 27 ዓመታት ኮብልለው የነበሩ የደርግ ባለስልጣናት ያለመጠየቅ መብታቸው ተከብሮላቸው እንዲገቡ ማድረጉ ሳያንስ በነደመቀ መኮነን የጀግና ኣቀባበል ተደርጎላቸው እብደት ወይንስ የህዝቡን ንቀት ብቻ የጎንደሯ እናት እርግማን ይድረሳቸው፣ የመላው ኢትዮጵያ በነዚህ ሰዎች ልጀጆቻቸውን የተነጠቁ እናቶች እርግማን በቅርቡ እንደሚደርሳቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ በዚህ ኣካሄድ የስርዓቱ ስያሜ ምን ሊባል እንደሚችል ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ኣሁን በነበረው የኢህኣደግ ስርዓት ስር የሰደደ ቂም በቀል ያላቸው የተለያዩ በተለይ ደግሞ የትምክህት ሃይላት ኣገር ውስጥ ገብተው ሊታገሉ ነው ወይንስ ሊበጠብጡ በቀጣይ የሚታይ ቢሆንም እኔ እስከኣሁን በዓለም ለይ እማውቀው ይቅርታ ጠይቆ በሰለም ለመኖር የሚደረጉ ሂደቶች እንጂ ድንፋታምና ተሸናፊ ከኣሸናፊው ጋር በሰላማዊ መንገድ የሚታገልበት ሁኔታ የለም ኣይኖርምም፡፡ለዚሁ ቀላል ማሳያ በኣምሃራና በኦሮምያ እንዲሁም በተለያዩ ኣካባቢዎች በስመ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲበጣበጥ እያደረጉ ያሉት በስመ ይቅርታ የተፈቱት ወንጀለኞች መሆናቸው የኣደባባይ ምስጢር ነው ምንም እንካን በመንግስት እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎች የኣብየን ወደእምየ ቢሆንም፡፡ 

በቅርቡ ደግሞ በጣም የወረደ፣ ጥላቻን የሚቀሰቅስና የማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሃገሪቱ የመዘዋወርና ሰርቶ የመኖርን ዕድል በሚያሽመደምድ ኣኳሃን ፀጉረ ለወጥ ሲመጡባችሁ ተከታተሉዋቸው መንግስት በራሱ ግዜም እየተከታተላቸው ነው ብለውን እርፍ ኣሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይህንን ሲሉ ኤርትራዊ፣ ሱዳናዊ፣ ሶማልያዊ፣ ኬንያዊ ወይንም ግብፃዊ ማለታቸው እንዳልሆነ፡፡   ኣሁንም ግዜ ኣልመሸም ዶ/ር ዓብዪ ወደ ሂሊናቸው ተመልሰው የኢህኣዴግ ኣካሄድ በተሻሻለ መልኩ ያሉትን ችግሮች ኣስተካክሎ፣ ጀሮውን ለህዝብ የሰጠ በውስጡ ያሉ ኣመራሮችም ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ለሊበራል ስርዓት እጅዋን ያልሰጠች፣ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት የመሰለውን የሚደግፍና የሚቃወም እንዲሁም የነፃ ሚድያ በጥላቻና ቂም የማይዘጋበት ወይንም የማይስፈራራበት፣ ህገመንግስቱን ያሉትን ጥሩ ጎናች የሚቀጥሉበትና መሻሻል የሚገባቸውን በህዝቡ ይሁንታ የሚሻሻሉበት፣ በተለይ ደግሞ የፀረ ብሄር ብሄረሰብ ኣቀንቃኞች በትረት የሚቃወሙበት ኣካሄዶችን መከተል ኣንቱ ከማሰኘት ባሻገር እቺ ሃገር እንደሃገር የሚያስቀጥልና ኣገራችን የምንመኝላት ማማ እምትደርስበት ሁኔታ እውን ሊሆን ይችላል፡፡ በዚሁ ወቅት ግዜ ያለፈበትና የተቀበረ የትምክህተኞች የበላይነት በመመለስ፣ የግዛት ተስፋፊነትና በኣንድ ቋንቋና ባንዴራ ስር ኣንበርክኮ ለመግዛት የሚደረግ ከንቱ ሙከራ ግን መላው ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታግለው ያሽመደሙድታል ኣልያም ሃገሪትዋ የመሰነጣጠቅ ኣደጋ ይደርሳታል፡፡ እናም ይታሰብበት፡፡ መልካሙን ሁሉ ለሃገራችን፡፡ ቸር እንሰንብት

Back to Front Page