Back to Front Page


Share This Article!
Share
የግጭት ተዋናዮች ይንጓለሉ

የግጭት ተዋናዮች ይንጓለሉ

ኢብሳ ነመራ 07-27-18

ባለፉ ሁለት ዓመታት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል፣ ቁጥራቸው በውል ለማይታወቅ ዜጎች ሞትና የአካል ጉዳት ምክንያት የሆኑ ግጭቶች አጋጥመዋል። ግጭት ከሰው ጋር የኖረና ለወደፊትም የሚኖር ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያጋጥሙ ግጭቶች ግን የተለየ ባህሪ አላቸው። ግጭቶቹ ውስጣዊና የህዝብ ለህዝብ ሳይሆኑ በአመዛኙ ውጭያዊና በሌላ ሶስተኛ ወገን ህቡዕ ተዋናይነት የሚከናወኑ መሆናቸው ነው ልዩ የሚያደርጋቸው። የግጭቶቹን ባህሪ ለመረዳት ካጋጠሙ ግጭቶች መሃከል የተወሰኑትን - በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ በኦሮሚያና አንዳንድ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም ሰሞኑን በጎባ ከተማ ያገጠሙ ግጭቶችን እንመልከት።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲያጋጥሙ የቆዩና አንድ ሚሊየን ያህል ለሚሆኑ ዜጎች ከኑሮ መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግጭቶች አሁንም ጊዜ እየጠበቁ እያገረሹ ነው። በኦሮሚያ ጉጂ ዞንና ደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን አዋሳኝ አካባቢ በቅርቡ ባጋጠመ ግጭት በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ ከመኖሪያው ተፈናቅሏል። ሰሞኑን በኦሮሚያ ባሌ ዞን ጎባ ከተማ ታዋቂ የኦሮሞ ነጻነት ታጋይ ለነበሩት ሃጂ አደም ሳዶ መታሰቢያ ሃውልት ለማቆም የቀረበን ሃሳብ መነሻ በማድረግ የሃይማኖት ገጽታ ያለው ግጭት አጋጥሟል።

እርግጥ ነው፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት እንግዳ ነገር አይደለም። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦች አርብቶ አደሮች ናቸው። የአርብቶ አደር ማህበረሰቦች ለከብቶች የግጦሽ ሳርና ውሃ ፈለጋ ከስፍራ ስፍራ ስለሚንቀሳቀሱ፣ በዚህ እንቅስቃሴ አንዱ የሌላው ወሰን ውስጥ የሚገባበት አጋጣሚ ስለሚፈጠር፣ የሳርና ውሃ ሽሚያ ስለሚያጋጥም ግጭት የተለመደ ሁኔታ ነው።

Videos From Around The World

ይሁን እንጂ ግጭት የኑሯቸው አካል የሆኑት የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሱማሌ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ግጭቶችን የሚፈቱባቸው ባህላዊ የእርቅ ስርአቶች አላቸው። ለምሳሌ በቦረና ኦሮሞና በአዋሳኝ የኢትዮጵያ ሱማሌ ማህበረሰቦች መሃከል የሚያጋጥሙ ግጭቶች የሚፈታ ገዳ ቦረና የተባለ ቋሚ የእርቅ ሸንጎ አለ። ግጭቶች ሲያጋጥሙ ይህ ጋዳ ቦረና የተባለ ሸንጎ ግጭቶች ተባብሰው በሁለቱም ወገን በሰው ህይወት ላይና የእንስሳ ሃብት ላይ የከፋ ኩዳት ሳያስከትሉ፣ ወደ ቋሚ ግጭትነት አድገው ዘላቂ የኑሮ ስጋት ሳይሆኑ ይቅርታና ምህረት ላይ የተመሰረተ እርቅ ያወርዳል።

ሁለቱ ህዝቦች ግጭቶች ሲያጋጥማቸው በእርቅ የሚፈቱበት ስርአት ከማበጀታቸው በተጨማሪ በጋብቻ ተሳስረዋል። አንድ ገበያ ይውላሉ፤ የጋራ ባህልና ወግ አላቸው። ይህ መስተጋብር የፈጠረው ዝምድና ግጭቶች እንዳይቀሰቀሱ፣ ቢቀሰቀሱም ደም ሳያቃቡ እንዲበርዱ ማድረግ የሚያስችል ማህበራዊ መሰረት ፈጥሯል።

ኦሮሚያ ከደቡብ ማህበረሰቦች ጋር በሚዋሰኑባቸው ለምሳሌ በጉጂ ዞንና ጌዲዮ አካባቢም ግጭቶች ፍጹም እንግዳ አይደሉም። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እንደማንኛውም አዋሳኝ አካባቢ ጌዲዮዎች በኦሮሚያ ጉጂ ዞን ውስጥ፣ ኦሮሞዎች በጌዲዮ ዞን ውስጥ ይኖራሉ። በዚህ ምክንያት አብረው በሚኖሩባቸው አካባቢዎችና በወሰን አካባቢዎች ግጭቶች ያጋጥማሉ። እነዚህ ግጭቶች ግን አስከፊ ጉዳት አድርሰው አያውቁም። ቋሚ የኑሮ ስጋትም ሆነው አያውቁም። ሁለቱ ማህበረሰቦች ጎንዶሮ የተሰኘ የይቅርታና ምህረት የእርቅ ስርአት አላቸው።

የጉጂ ጎሳ ኦሮሞዎችና ጌዲዮዎችም በጋብቻ፣ በጉዲፈቻና ሞጋሳ ዝምድና መስርተዋል። በኢኮኖሚ ተሳስረዋል። ባህልና ወግ ተጋርተዋል። ጌዲዮዎች ከኦሮሞ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጋዳ አስተዳደር ስርአት አላቸው። በዚህ ምክንያት ግጭቶችን ማስቀረትና ሲያጋጥምም ተጽእኖውን መቀነስ የሚያስችል ማህበራዊ መሰረት ዘርግተዋል።

በኦሮሚያ ጎባ ዞን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት፣ የጎባ ከተማ ከአብዛኞቹ የባሌ ዞን ከተሞች በተለየ ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ብሄሮችና ሃይማኖቶች ተከታዮች መኖሪያ ነች። ጎባ የራሷ የሆነ የከተሜነት (metropolitan) ባህል ያዳበረች ከተማ ነች። የተለያዩ ባህሎችና ሃይማኖቶች ክልስ የሆነው ይህ  የከተሜ ባህል ለልዩነት ቦታ አይሰጥም። የመቻቻልና የመከባበር እሴት አፍርቷል። በዚህ ባህል ውስጥ የእርስ በርስ ግጭቶች የመቀስቀስ እድላቸው እጅግ አነሰተኛ ነው።

ልብ በሉ፤ አሁን ግጭቶች የተነሱትና አስከፊ ጉዳት ያደረሱት በእነዚህ ግጭቶችን የመከላከል፣ ከተከሰቱም በኋላ ተጽእኗቸውን በእጅጉ መቀነስ የሚያስችል ማህበረሰባዊ መሰረት ባባቸው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ የኦሮሚያና ደቡብ አካባቢዎች፣ እንዲሁም የከተሜነት ባህል በዳበረባት የጎባ ከተማ ነው።

እንግዲህ፣ ከላይ የተጠቀሱት ግጭቶች ቀድሞውኑም መነሳት በሌለባቸው አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ናቸው። ከተቀሰቀሱም በኋላ ወትሮ በነበረው የእርቅ ስርአት በቀላሉ ሊበርዱ አልቻሉም። ለምሳሌ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ወሰንን መነሻ ያደረገ እንደሆነ ቢነገርም፣ ቀድሞ እርቅ ይወርድባቸው በነበሩ ስርቶች እንዲሁም የመንግስት እርምጃዎች መብረድ አልቻለም። የግጭቱ ምክንያት ወሰን መሆኑ ቢነገርም፣ ከወሰን  በራቁ አካባቢዎችም ማንነትን መሰረት ባደረገ ግጭት ሲገለጽ አስተውለናል። በያዝነው ዓመት መግቢያ ላይ ግጭቱ ተጋግሎ በነበረበት ወቅት ከኢትዮጵያም አልፎ በሶማሌ ላንድ አካባቢ ጭምር ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭት ለመቀሰቀስ ተሞክሮ እንደነበረ እናስታውሳለን።

የኦሮሚያ ጉጂ ዞንና ጌዲዮ ግጭት መቀሰቀስን ተከትሎ ወትሮ ግጭቶች በእርቅ መፍትሄ በሚያገኙበት የጎንዶሮ ስርአት ለመፍታት ተደጋጋሚ ሙከራዎች ተደርገዋል። የግጭቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች እንደገለጹት በተደጋጋሚ ጎንዶሮ ተቀምጠዋል። ይሁን እንጂ ግጭቱ እንደወትሮው በጎንዶሮ እልባት ሊያገኝ አልቻለም። አስከፊነቱም በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ቀደም ሲል ካጋጠሙ ግጭቶች ሁሉ የከፋ ነው። በዚህ ግጭት አንድ ሚሊየን ያህል ሰዎች መፈናቀላቸውን ልብ ይሏል።

በጎባ ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት መነሻ የሃጂ አደም ሳዶን መታሰቢያ ሃውልት ማቆም እንደሆነ ነው የሰማነው። የመታሰቢያ ሃውልቱን መቆም በሚደግፉት ወገን ሃውልቱ የሚቆምበት ስፍራ ቀደም ሲል የአከባቢው መለያ የሆነው፣ ለሃገሪቱም ብርቅዬ የሆነው የቀይ ቀበሩ ምስል የያዘ ሃውልት የቆመበት ስፍራ ነው። ሃውለቱ እዚህ ስፍራ ላይ ይቁም፣ የለም በሌላ ስፍራ ይቁም በሚሉት ጎራዎች መሃከል የተነሳው አለመግባባት ምንም ሃይማኖታዊ ምክንያት የለውም። ይሁን እንጂ ግጭቱ ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዲኖረው ተደረጓል። በከተማዋ መናልባት ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል የዘለቀው የሃይማኖት መቻቻል ባህል የአሁኑን የግጭት ቅስቀሳ ሊቋቋም አልቻለም።

እነዚህ ከላይ የተገለጹ ሁኔታዎች በሃገሪቱ የተቀሰቀሱት ግጭቶች ሊፈጠሩ በማይችሉበትና ግጭቶችን መቋቋም የሚችል ባህል በጎለበተባቸው አካባቢዎች ያጋጠሙ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል። ለማሳያነት በተጠቀሱት ሶስቱ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምስክርነት የአካባቢው ህዝብ አንዱ ሌላው ላይ ተነስቶ አልተጋጩም። ግጭቶቹ የተቀሰቀሱት ከውጭ የመጡ ሶስተኛ ወገን የግጭት ተዋናዮች በሚሰነዝሩት ጥቃት ነው። ይህ የሚያሳየው ግጭቶቹ የህዝብ ለህዝብ አለመሆናቸውን ነው። ለእርቅ ያስቸገሩትም በህዝብ መሃከል የተፈጠሩ ባለመሆናቸው ነው።

እዚህ ላይ ግጭትን መቋቋም የሚያስችልና ከተፈጠረም በኋላ መፍታት የሚያስችል የዳበረ ባህል ያለባቸው አካባቢዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደረጉት ሶስተኛ ወገኖች እነማን ናቸው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ምላሹ ግን ሩቅ አይደለም።

ሃገሪቱ አሁን እመርታዊ ለውጥ ያመጣ የለውጥ ሂደት ላይ ተገኛለች። ይህ ለውጥ ቀደም ሲል በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ በፖለቲከኞችና በጥገኞቻቸው መሃከል በተዘረጋ የጥቅም ትስስር የመንግስተና የህዝብ ሃብት በመዝረፍ፣ በኮንትሮባንድ ንግድ ይገኝ የነበረውን ተገቢ ያልሆነ ጥቅምና ብልጽግና አስቀርቶታል፤ የጥቅም ትስስሩን መረብ በመበጣጠስ። ጥቅሙን ከማስቀረት በተጨማሪ፣ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ሲያጋብሱ የነበሩ ግለሰቦችና ከለላዎቻቸውን ለህግ ተጠያቂነት አጋልጧል።

እነዚህ አካላት ጥቅማቸውን ማስጠበቅና ከህግ ተጠያቂነት ማመለጥ የሚችሉት የህግ የበላይነት ሲጠፋ ብቻ መሆኑን ያውቃሉ። የህግ የበላይነት ደግሞ ከምንም በላይ አሰተማማኝ ሰላም ያለበትንና የመንግስት መዋቅሮች ሃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ የሚወጡበትን ሁኔታ ይሻል። ግጭትና ረብሻ ይህን ሁኔታ ያጠፋል። ዘራፊዎቹና ከለላዎቻቸው እዚያም እዚህም ውዥንብር በመንዛትና ሰዎችን በገንዘብ በመደለል ግጭት የሚቀሰቅሱት ሰላምን በማደፍረስ፣ የመንግስት መዋቅሮች ስራ እንዳይሰሩ በማድረግ የህግ የበላይነትን ለማጥፋት ነው።

በመሆኑም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ወጣቶች የተለያየ ተቀጣጣይ አጀንዳ በማቀበል ግጭት ለመቀስቀስ በማህበራዊ ሚዲያና በአሉባልታ ከሚነዙ ውዥንብሮች ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው። ህዝቡ ግጭቱ ውስጥ ካልገባ የግጭት ተዋናዮቹ ተንጓለው ሰለሚወጡ በቀላሉ አደብ ማስያዝ ይቻላል።    

Back to Front Page