Share This Article!
Share

Back to Front Page

ሐገር ጫታ ይሆናል

ሐገር ጫታ ይሆናል

አሜን ተፈሪ 08-22-18

አሁን ሐገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ መጥፎ የማሽቆልቆል ሁኔታ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ሰፊ የጋራ መግባባት የተያዘበት ተቃራኒ አስተያየት አለ - የተስፋ መንገድ ጀመረች እንጂ በማሽቆልቆል ጎዳና እየተራመደች አይደለም የሚል፡፡ ይህንም ጉዳይ ከምሁራን እና ከፖለቲከኞች አንደበት ሲነገር እንሰማዋለን፡፡ በሚዲያዎችም እናየዋለን፡፡ ታዲያ የእኔ እይታ ሁለቱንም ቀላቆሎ ያሳየኛል - ተስፋ እና ስጋቱን፡፡ እንዲህ ያለ ድምዳሜ ለመያዝ የሚያበቁ በቂ ምክንያቶችም አሉኝ፡፡

ነገር ግን፤ መጥፎ የማሽቆልቆል ሁኔታ የተፈጠረው የለውጥ አመራሩ በመምጣቱ፤ ወይም አዲሱ የኢህአዴግ አመራር ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር በማፈንገጡ አይደለም የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ትክክል ሆኖ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ ነገሩን በልቤም (on intuitive level) ሆነ በአዕምሮዬ ስገመግመው፤ ይህን አስተያየት መቀበሉ ያስቸግረኛል፡፡ ይልቅስ የለውጥ ኃይሉ የተፈጠረው፤ ከተዘፈቅንበት ችግር ለመውጣት በተደረገ ትግል ነው፡፡ ይልቅስ የለውጥ ኃይሉ በፍጥነት ወደ አደጋ ታመራ የነበረችን ሐገር በመጠኑም ለማረጋጋት የቻለ ኃይል ነው፡፡ ይልቅስ የለውጥ ኃይሉ በአብዛኛው የሚንገላታው በተወረሰ ችግር እንጂ በእርሱ አካሄድ በተፈጠረ ችግር አይደለም፡፡ ይልቅስ አሁን ሐገሪቱን ቀጥ አድርጎ ያቆማት፤ የለውጥ ኃይሉ የረጨው ተስፋ ነው፡፡ ይህም ብዙ ሰዎች የሚጋሩት ስሜት እና አስተያየት ነው፡፡

Videos From Around The World

‹‹አዲሱ አመራር ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር በመውጣቱ ሐገሪቱን ወደ ቀውስ አስገባት›› ብሎ ማለት የለውጥ ኃይሉ ከመምጣቱ በፊት ሐገሪቱ ሰላም ነበረች የሚል ክህደት ይሆናል፡፡ ይህ ሐሳብ የተሳሳተ ሐሳብ ነው፡፡ ለልቤም ሆነ ለአዕምሮዬ እውነት ተጻራሪ የሆነ ምስክርነት ነው፡፡ ተጨባጭ መሠረት የሌለው ትንተና ነው፡፡ 

የተለያዩ ሐገራት መውጫ የሌለው ከሚመስል ችግር ውስጥ ሲገቡ አይተናል፡፡ ለምሣሌ፤ ሙስና -በሲንጋፖር፤ የከፋ ድህነት -በብራዚል፤ የስደተኞች ጉዳይ - በካናዳ መውጫ የሌለው መስሎ ታይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የተጠቀሱት ሦስቱም ሐገሮች ከዚያ መውጫ የሌለው ከሚመስል ከባድ ችግር መውጣት ችለዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሐገሮች ከዚያ መውጫ የሌለው ከሚመስል ችግር ለመውጣት የቻሉት፤ ችግሩ የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኖ የታያቸው መሪዎች፤ ፖለቲካዊ አደጋን ሊጋብዝ የሚችል ደፋር የተሐድሶ እርምጃ በመውሰዳቸው ነው፡፡

በዚህ ጊዜ፤ መሪው በአንድ በኩል የቴክኖክራት ባህርይ፤ በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ሂደቱን ይዞት ለተነሳው ዓላማ ተፈጻሚነት የመጠቀም ጥበብ ሊኖረው ይገባል፡፡ አንድ መሪ የፖለቲካ ሂደቱን ለዓላማው ተፈጻሚነት ምቹ እንዲሆን የማድረግ ብቃት ሳይኖረው፤ ቴክኖክራት የመሆን ብቃት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህን ለማድረግ የሚችለው የፈላስፋን ብቃት የታደለ የፖለቲካ ሰው ብቻ ነው፡፡ አንድ መሪ ርዕዮተ ዓለማዊ ንጽህናውን ለመጠበቅ ከሚጣጣር ይልቅ፤ ጊዜው ምን እንደሚጠይቅ አውቆ እና ተረድቶ፤ ከእውነታው ጋር የተጣጣመ የአፈጻጸም ብቃት መያዝ እና ለማመቻመች (compromise) ዝግጁ መሆን፤ እንዲሁም ቴክኖክራቲክ ጥበብ የታደለ ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡

መንግስታት ችግር ፈቺ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉት ህልውናቸውን የሚፈታተን አደገኛ ችግር ውስጥ ሲገቡ ነው፡፡ መንግስታት ድርስ ከሆነ አደጋ ጋር ሲጋፈጡ፤ በአዘቦቱ ይደረጋሉ ተብለው የማይታሰቡ የለውጥ እርምጃዎችን ይወሰዳሉ፡፡ በአንድ በኩል፤ እነዚህ ህልውናን የሚፈታተኑ አደጋዎች፤ ችግሮችን በከፍተኛ የትኩረት ኃይል ለማሰብ፣ ዳተኝነትን ለማስወገድ እና በእውነተኛ ስሜት መፍትሔ ለመፈለግ የሚያነሳሱን ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የችግሩ አደገኛነት የተሐድሶ ጥረት እንዳናደርግ መሰናክል የሚሆኑ ችግሮችን ሁሉ ጠራርጎ በመጣል፤ ለእውነተኛ ተሐድሶ ጎዳና ያመቻቻል፡፡ በመሆኑም፤ በደህናው ጊዜ ወይም በአገር አማን ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እና የርዕዮተ ዓለም አጥርን  ጥሶ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛነት የሚጎድላቸው ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ሌላው ቀርቶ ህዝብ ራሱ)፤ በተስፋ መቁረጥ ጫና ዳተኝነትን በማስወገድ ትክክለኛ ሆኖ የተገኘን ማናቸውንም ውሳኔ ለመወሰን ያደፋፍራሉ፡፡ ስለዚህ እንደ ቴፐርማን ያሉ ምሁራን፤ ‹‹የእውነተኛ መፍትሔዎች ምንጭ ቀውስ (crisis ) ነው›› ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ሌሎች ሐገራት ተስለው የማያገኙት በርካታ አጓጊ እሴቶች ያላት ሐገር ነች፡፡ ግን በዚያው አንጻር ኢትዮጵያ በመጥፎ ቀጣና የምትገኝ ሐገር ነች፡፡ እንደ አሜሪካ በጣም የተማረ ህዝብ፤ በዓለም ምርጥ የሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች፤ እንዲሁም ከማንኛውም የዓለም ሐገር የላቀ በፈጠራ የተደራጀ (innovative ) ኢኮኖሚ ያለው እና የጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ባለቤት ለሆነ ሐገር ጭምር ፈታኝ ሊሆን በሚችል ክፍለ አህጉር የተቀመጠች ሐገር ነች፡፡

ቴፐርማን፤ ‹‹አሜሪካ በግራ በቀኝ በውቂያኖስ የተከበበች እና የሰላም ጠንቅ የማይሆኑ ጥሩ ጎረቤቶች ያላት ሐገር ናት -በሰሜን ካናዳ በደቡብ የሜክሲኮ-›› ይላል፡፡ የጀርመኑ ቢስ ማርክ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ለሰካራሞች እና ለአሜሪካኖች ይስቅላቸዋል›› (God smiles on drunkards and Americans) የሚል ዝነኛ አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስብስብ የሆነ የውስጥ ችግሯን መፍታት ብትችል እንኳን የሰላም ጠንቅ የሚሆን ችግሮች ባላቸው ጎረቤቶች የተከበበች ሐገር ናት፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የጀርመኑ ቢስ ማርክ አባባል ለኢትዮጵያም የሚሰራ የሚሰራ ይመስለኛል፡፡ ከአምስት ወራት በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ከምትገኝበት ሁኔታ ውስጥ ለመገኘት የበቃችው ‹‹እግዚአብሔር ቢስቅላት››  መሆን አለበት፡፡

ሆኖም አንዳንድ ፀሐፊዎች፤ ‹‹በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ መንግስት ዓለምን ሁሉ የሚያስቀኑ ድንቅ እሴቶቻችን ሁሉ ለማውደም የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል›› ሲሉ እንደሚከሱት፤ ብዙ ሐገራትን የሚያስቀና የለውጥ ዕድል በተደጋጋሚ እያገኘን፤ ዕድሉን ለማጥፋት የምንችለውን ሁሉ እያደረግን የምንገኘውን ኢትዮጵያውያን ለመክሰስ እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ዝም ብሎ ዳር ሆኖ ለሚመለከተን ሰው በጣም አስጨናቂ የሚሆንበት ጉዳይ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረውን መልካም ዕድል የሚያጠቡ ተግባር እና አሰተሳሰቦችን ከአንዳንድ የፖለቲካ አመራሮች ዘንድ ማየቱ ነው፡፡ ትክክለኛ የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመለየት እና መፍትሔዎችንም በትክክል ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ ዕድል ያገኘችውን ሐገር መልሶ ቅርቃር ውስጥ እንድትገባ የሚያደርግ የፖለቲካ ቁማር መጫወት የሚፈልጉ እና ‹‹አንድ ነገር ሲኖር እና ሲሞት መለየት የሚቃታቸው›› የፖለቲካ ነጋዴዎች ማየት በእርግጥም ያስጨንቃል፡፡

የሐገራችንን ታሪክ በደንብ የሚያውቁ የውጭ ሐገር ሰዎች፤ ከወራት በፊት ሐገሪቱ ከነበረችበት አሳሳቢ የህልውና ሁኔታ ወጥታ የተስፋ መንገድ ውስጥ መግባቷ ላይገርማቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም፤ ይህች ሐገር እስከ ዛሬ በመጣችበት የታሪክ ጎዳና ብዙ ጊዜ ጠፋች የሚያሰኝ አሰቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትወድቅና የፖለቲካ ትንበያዎችን ሁሉ ፉርሽ በሚያደርግ አኳኋን አፈር ልሳ ትነሳለች፡፡ ታዲያ በገጠሟት የውስጥ እና የውጭ ከባባድ ፈተናዎች ሳትረታ የሐገሪቱ ህልውናም ሳይከስም ተጠብቆ ሺህ ዘመናት ለመዝለቅ ቢችልም፤ ህዝቦችዋ የለውጥ ዕድሎችን በአግባቡ የመጠቀም ችግር የሚታይባቸው በመሆኑ፤ ከሩቅ የሚመለከቱን አንዳንድ የውጭ ሐገር ሰዎች ‹‹ኢትዮጵያውያን አሁን ያገኙትን ዕድል እንደለመዱት ያባክኑት ይሆን? ወይስ ካለፈ ስህተታቸው ተምረው ወደ ተሻለ ደረጃ ሁኔታ ለመሸጋገር ይጠቀሙበት ይሆን?›› በሚል በጉጉት እየተመለከቱን ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም፤ በስኬት ጎዳና ለመራመድ የምትችል ሐገር በመፍጠር፤ በገዛ እጃችን ራሳችንን የማቁሰሉን ተግባር ማቆም ይኖርብናል፡፡

አሁን እርስ በእርስ የመነጋገር ባህላችን ደካማ በመሆኑ ካልተቸገርን በቀር፤ በመነጋገር መፍትሔ ለማፈላለግ እንችላለን፡፡ ምናልባት በዓለም ታሪክ ከታዩ የተለያዩ ስልጣኔዎች የብዙ መረጃ ሐብት ባለቤት ለመሆን የቻለ እንደኛ ዘመን ሰው ያለ አይገኝም፡፡ የባቡር፣ የአውሮፕላን፣ የራዲዮ፣ የስልክ፣ የቴሌቭዥን፣ የኮምፒዩተር እና የኢንተርኔት መፈጠር፤ የመረጃ ልውውጡን እና ግንኙነቱን አሳልጦታል፡፡  

ታዲያ በfact እና በdata ክምር የተዝበጠበጠው ገበታ ብዙ ክፍያ እየጠየቀን ነው፡፡ የዘመኑ ሥልጣኔ ተነቃናቂነታችንን (Mobility) እና በራሳችን ህይወት ላይ የመወሰን ዕድላችንን አሳድጎታል፡፡ ግላዊ ህይወት (privacy) የመምራት ዕድላችንን አስፍቶታል፡፡ ሆኖም የማህበረሰባዊ ህይወት አመለካከታችንን ሸርሽሮታል፡፡ ለምሣሌ፤ ሌላ ግብ ሳይኖረን ጨዋታን ብቻ በመፈለግ፤ ‹‹በል እስኪ ወግ አምጣ›› በሚል የምናደርጋቸውን መንፈስ አዳሽ ጭውቶችን ረብ አሳጥቷቸዋል፡፡ ጊዜ ውድ እየሆነብን፣ ክህሎታችንን ባልተቋረጠ ሁኔታ የማሻሻል ግፊት ውስጥ የሚያስገባ የኑሮ አዙሪት ይዞን ተቸግረናል፡፡

ነገር ግን ሐሳብ እና መረጃ ለመለዋወጥ በሚያስችል ጥሩ ዘመን መገኘታችን እሙን ነው፡፡ ስለዚህ እርስ በእርስ በመነጋገር ባህላችን ውስጥ ያሉ እንከኖችን አስወግደን መወያየት ከፈለግን የማህበራዊ ሚዲያው ብዙ ሊያግዘን ይችል ነበር፡፡ ሆኖም አሁን ያለን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም አፍራሽ እንጂ አልሚ አይደለም፡፡ ይህን ሁኔታ በአዲሱ ዓመት ለመቀየር መሥራት አለብን፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሮጌውን ዘመን ሸኝቶ አዲሱን ዘመን ሲቀበል፤ መንግስት በከፈተው ሰፊ የይቅርታ እና የምህረት አልፎ በመሆኑ፤ ከነባር የሐገራችን ወግ እና ልማድ የተስማማ በሆነው እርምጃ ታግዘን፤ በአዲሱ ዘመን አዲስ አስተሳሰብ በመገንባት ባለፉት አርባ እና ሐምሳ ዓመታት በሐገራችን የተፈጠረውን ህመም የሚፈውስ ሥራ መስራት እና ‹‹ኢትዮጵያውያን አሁን ያገኙትን ዕድል እንደለመዱት ያባክኑት ይሆን? ወይስ ካለፈ ስህተታቸው ተምረው ወደ ተሻለ ደረጃ ሁኔታ ለመሸጋገር ይጠቀሙበት ይሆን?›› በሚል የሚገምቱንን ሰዎች ማሳፈር ይኖብናል፡፡   

የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆናችንን ረጋ ያለ ሲቪክ ተዋስኦ ለመፍጠር ማዋል ይኖብናል፡፡ የዘመናችን ማህበራዊ ሚዲያ ቀደም ባለው ዘመን ከነበረው በሳሎን (በካፌ) የመሰባሰብ ዕድል ይሰጠው ከነበረው ፋይዳ ጋር ሊነጻጽር ይችላል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ የጋራ ሐሳቦችን የማንጸባረቅ ዕድል ይሰጠናል፡፡ የሌሎችን አመለካከትም ለመረዳት እና እይታቸውን ለማግኘት ያግዘናል፡፡ ይህ ሚዲያ ያገኘነውን የለውጥ ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም በሚያስችለን አግባብ መገልገል ይኖርብናል፡፡

በርግጥ አንድ ማህበራዊ እውነታን ለመቀየር ሚሊዮኖች መንጋጋት አይኖርባቸውም፡፡ ያለፉ ዘመናት ሳሎኖች ታሪክ እንደሚያሳየን፤ መጠነ ሰፊ የሆነ የአወንታዊ ለውጥ ችቦ ለመለኮስ፤ ፈጠራን የታደለ አዕምሮ ያላቸው እና ነገሩ የሚገዳቸው በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸው በቂ ነው፡፡ ባለፈው ዘመናት የታዩ የታላላቅ አሰላሳዮች እና የድርጊት ሰዎች በርካታ ሐሳቦች፤ የእነሱን ሐሳብ ለማዳመጥ እና እውነተኛ ግብረ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ከታደሙባቸው ጉባዔዎች የተወለዱ ናቸው፡፡ የዘመናችን ሳሎኖች የሆኑት የማህበራዊ ሚዲያዎች ተመሳሳይ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

አሁን ሐገራችን ካለችበት ቀውስ ለማውጣት፤ በህገ መንግስቱ የተረጋገጡትን ሰብአዊ እና ፖለቲካዊ መብቶችን ያለ ምንም መሸራረፍ ተግባር ላይ በማዋል ሁሉም ፖለቲካዊ ኃይሎች ያለ ምንም ተፅዕኖ በሰላማዊ ፖለቲካዊ ውድድር የሚሳተፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት መጀመር አለብን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕብረተሰቡ በሲቪክ ማህበራቱ ይሁን በተናጠል ወይም በየግሉ በሚያደርገው ሰፊ ተሳትፎ፤ አሁን ሐገራችን ያለችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ በሚገባ እንዲገነዘብ በማድረግ፤ ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡

በሂደትም ህዝብ በመንግስት አሰራር ላይ ያለውን ተፅዕኖ የሚያሳድግበት፣ በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ በሚመሠረት ፖለቲካዊ ስርዓት ይበልጥ መተማመን የሚፈጠርበት፤ ቅሬታዎቹን እና የሚያያቸውን ጉድለቶች ሳይሸማቀቅ የሚወያይበት፤ ከዚህ እየተነሳም መፍትሄ የሚያቀርብበት ፖለቲካዊ ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ይህን ሁኔታ ለመፍጠር የፖለቲካ ኃይሎች ራሳቸው በሚያደርጉት ምክክር፣ መደራደር፣ ዝርዝር አካሄዱ የሚወሰን ቢሆን ይመረጣል፡፡ በዚህ ረገድ የምርጫ ህግጋትን፣ የሰላማዊ ሰልፍ አፈጻጸምን፣ የሚዲያ አሰራር እና የፓርቲ ምዝገባ ወዘተ ህጎችን ለማሻሻል የሚካሄደው ጥናት ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ በጠቅላላ ህዝቡን አደራጅቶ በነፃ ሃሳቡን ገልፆ የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ ተቀላቅሎ በፍላጎቱ እንዲመርጥ፣ ፖርቲዎቹም ሐሳባቸውን በተገቢው መንገድ (በመንግስት ሚዲያም ጭምር) ያለ አንዳች ተፅዕኖ መግለጽ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ሐገር ጫታ ይሆናል፡፡

Back to Front Page