Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጃዋር አደብ መግዛት አለበት!

ጃዋር አደብ መግዛት አለበት!

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል 09-28-18

መቐለ

 

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ቀርቤ በሰጠኋቸው ቃለ መጠይቆችና በጻፍኳቸው አርቲክሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ በአገራችን በኢትዮጵያ የመጣውና ገና አሁንም ቢሆን በጅምር ያለውን የለውጥ አየር በመደገፍ ብቻ ሳይሆን ለውጡን ሊያደናቅፉ ይችላሉ ብዬ የማምንባቸው የተለያዩ ሃይሎችና አመለካከቶች ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ስተች፣ ስጋቴን ሳስቀምጥ፣ ስገልጽና ስጠቁም መቆየቴን የሚታወቅ ነው።

 

የትግራይ ህዝብ ነባራዊ ሁኔታ ከህወሓት መሪዎች መንኮታኮት ጋር ተያይዞ የመመዘን ነገር፤ ይህንም ተከትሎ እጅግኑ ሚዛናቸው የሳቱ የሚሰነዘሩ አስተያየቶችና አመለካከቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራከቱ መጥተዋል። አቶ ጀዋር መሓመድ ከአቶ ዳዊት ከበደ (አውራምባ ታይምስ) ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ለጽሑፌ መነሻ ሆነኛል። አቶ ጃዋር ከዳዊት ከበደ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ዋና ይዘት ጃዋር ከህወሓት መሪዎች ጋር ግኑኝነት ለመፈጸም እንደሚሻ፤ ምክንያቱም አቶ ጃዋር የትግራይ ህዝብ እንደተሸነፈና እሱ ራሱ በሁኔታው ብቸኛ የመፍትሔ አምጪ ነኝ ብሎ ስላመነና ስለሚያምን ነው። አቶ ጃዋር መሓመድ ከአቶ ዳዊት የቀረበለትን ጥያቄዎች ተከትሎ የሰጠው መልስ ከሞላ ጎደል አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት መጽሐፉን አጠበች በሚገባ የሚገልጸው ሆኖ ነው ያገኘሁት። ስለ ግለሰቡ ማንነትና ያለፉት ስራዎች መተረክ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለምና በቀጥታ ወደ ርእሰ ጉዳዬን ልግባ።

Videos From Around The World

 

አቶ ጃዋር ራሱን የፖለቲካ ሳይንቲስት አድርጎ መሾሙ፣ መቀባቱ፣ ማቅረቡና መጥራቱ በብዙሐኑ ኢትዮጵያን ሙሑራን ዘንድ ትዕዝብትን አትርፈዋል። ግለሰቡ ራሱ የፖለቲካ ሳይንቲስት አድርጎ መቁጠሩንና መጥራቱን በግሌ አይሞቀኝም አይበርደኝም። ግለሰቡ ለራሱ ያለው አመለካከትም ይጠቅመኛል ብሎ እስካመነ ድረስ የፖለቲካ ሳይንቲስት ነኝ ከማለት አልፎ ይመጣል ተብሎ በቅድሳት መጻህፍት የተጻፈ መሲህ እኔ ነኝ ቢልም የእኔ ጭንቀት አይደለም። አቶ ጃዋር አገራችን ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን ችግር በተመለከተ ራሱን እንደ ብቸኛ አዋቂ፣ እንከን የለሹ የተዋጣለት የመፍትሔ ሰው ብቻም ሳይሆን በሕዝቦች የውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ገብቶ ለመፈትፈት ያሳየው ፍላጎትና ምኞት ግን በቀላሉ የሚታለፍ ሆኖ አላገኘሁትም።

 

በእውነቱ ነገር፥ አቶ ጃዋር ስራ ራሱ ያለው እምነትና አመለካከት በእኔ ቤት ቦታ የለውም። በመሆኑም፥ ግለሰቡ የትግራይን ህዝብ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ያስተላለፋቸው መልእክቶች እንደተጠበቀ ሆኖ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ለሚሰጠው ማንኛውም ዓይነት ሃሳብ እንዲሁም ለሚያንጸባርቀው አመለካከት ልኩን አውቆ በልኩ ይመላለስና አድብ መግዛት ይገባው ዘንድም ይህችን መጣጥፍ ለማዘጋጀት ተገድቻለሁ።

 

የህወሓት መሪዎች ትልቁ በሽታ፤ ከምንም በላይም ለዚህ ሁሉ ውድቀትና ኪሳራ የማገዳቸው ሌላ ምንም ሳይሆን ግለሰቦቹ ለራሳቸው የነበራቸው እጅግ የተጋነነ ምስል፤ በተጨማሪም የተሳሳተ ግምትና እምነት ነበር። የህወሓት መሪዎች የሌላውን ሰው አስተሳሰብ አመለካከትና ሃሳብ የሚያደምጡበት

ልብም ሆነ ጆሮ አልነበራቸውም። ከእነሱ ውጭ ሌላ አዋቂ፣ ከእነሱ ውጭ ሌላ አሳቢ ሰው ያለ አይመስላቸውም ነበር። በጥቅሉ የህወሓት መሪዎች እኛ ብቻ ነን አዋቂዋች ባዮች የነበሩ ልባቸው በትዕቢት ያበጠባቸው ዓይነት ሰዎች ነበር የነበሩ።

 

አቶ ጃዋር የተጸናወተው በሽታም መጨረሻቸው ያላማረ የህወሓት መሪዎች የተለየ አይደለም። አቶ ጃዋር ቀደም ሲል ከናሁ ቴሌቪዥን በቅርቡ ደግሞ ከአውራምባ ታይምስ ጋር በነበረው ቆይታ የኢትዮጵያ ህዝብ በአቶ ጃዋር ምህረት፣ ፈቃድና መልካም ምኞት እየኖረ እንዳለ ነው የነገረን። አቶ ጃዋር በኢትዮጵያ ህዝቦች ደስ ያልተሰኘ፣ ያኮረፈና ቅር ያለው እንደሆነ መንግስታትን እየገለባበጠ ሊያተረማምሰንና ደም ሊያቃባን፤ የራራልን፣ የወደደንና ደግነትና ቸርነትን የተሰማው እንደሆነ ደግሞ ሰላምንና ፍቅርን ሊሰጠን እንደሚችል ሲነግረንም ችንሽ ሰው ምን ይለኛል አላለም።

 

አቶ ጃዋር ይህን ማወቅ ይጠበቅበታል፥

 

አንድ፥ ኢትዮጵያ ከማህጸንዋ በወጡ በልጆችዋ ተጠቃሚ ለመሆን ባትታደልም እንደ ሀገር ግን ራሳቸውን የማይክቡና በታላቅ ትህትናቸው የሚታወቁ ብዙ ምሁራን፣ አዋቂዎች፣ አስተዋዮችና ጭምት የሃይማኖት መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተማጓቾችና ጠበቆች፣ ፖለቲከኞች ያየችና ያሳለፈች አገር ናት። ስለሆነም ይህ በማን አለብኝነትና አጉል ድፍረት የምታደርገው አገርንና ህዝብን የማያንጽ ሃላፊነት የጎደለበት ንግግር ማቆም አለብህ።

 

አንተ ስለ/ለ ራህስ ያለህና የምትሰጠው ግምት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በእርግጠኝነት የምነግርህ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ህዝብ አታውቀውም። አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ የነገሰ ንጉስ ሳዖል በእግዚአብሔር ፊት ለሁለት ዓመታት ብቻ ነበር በመጎስ የተመላለሰ የተቀረው ሰላሳ ስምንት ዓመታት እግዚአብሔር የማያውቀው ሰው ነበር። አቶ ጃዋር፥ አጋጣሚውን ስታገኝ አጋጣሚውን ተጠቅመህ ያለፈውን ህጸጸችህ ወደኋላ ትተህ አዲሱን ምዕራፍ ለመልካም ነገር መጠቀም ሲገባህ ራስህን ከሰው ዘር በሙሉ በላይ አድርገህ በማስቀመጥ በትዕቢት አፍህን የከፈትክ ያህል እንዲሁ ዓይንህ እያየ ጆሮህ እየሰመህ ስኳርነቱ አልቆ ወደ ቆሻሻ እንደሚጣል መስቲካ ከኢትዮጵያውያን ልብ የምትወጣበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ከዚያ በኋላ የሚኖርህ ዘመንንም ቢሆን የመቅበዝበዝ ህይወት እንጅ የስራ ዘመን አይሆንልህም። ልደቱን ያላየ ተመለስ!

 

ሁለት፥ በአንተ ምህረት የቆመች አገር ሆነ በእንተ መልካም ፈቃድ ብቻ ለመኖር የታደለ ህዝብ የለምና ማስፈራራትህን አቁም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈራ ግለሰብም ሆነ ቡድን የለም። አንዱ እንዳሻው ሲሆን ሌላው በዝምታ ሲመለከት ዝምታን በፍርሃት ጋጠ-ወጥነትን እንደ ጀግንነት መቆጠር አዳልጦ ይጥልሃልና። ደግሞም አንድ ሰው ይህን ማድረግ እችላለሁ ካልክ ታሪክ ያለው ስድስት ሚልዮን ህዝብ ደግሞ ምን ማድረግ እንደሚችል ግምት ውስጥ ብታስገባ የመጀመሪያ ተጠቃሚ አንተ ነህ።

 

ሶስት፥ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተከትሎ አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይ ህዝብ ጥቅምና መብት አንስቶ የመመጎት ሆነ የመታገል ስራ የማን ድርሻ እንደሆነ አቶ ጃዋር ለትግራይ ህዝብ የመናገር መብትም ሆነ ስልጣን የለህም። አዛውንቶቹ ያለህን ፍቅር የምትገልጸው ደግሞ የአዛውንቶቹ የሁከትና የብጥብጥ አጅንዳ ይዘህ ወደ ቀድሞ ስራህን በመመለሰ እንጅ የትግራይን ህዝብ ለማነጋገር ባሳየኸው ፍላጎትና ባቀረብከው ጥሪ አይደለም።

 

አራት፥ የትግራይ ህዝብ ውስጣዊ ችግር የሚፈታው በትግራይ ክልል ተወላጆች ብቻ መሆኑን ልታውቅ ይገባሃል። የትግራይ ክልል የውስጥ ችግር በተመለከተ የትግራይ ክልል ልጆች ብቻ ይመለከታል። እኛ የትግራይ ክልል ተወላጆች የውስጣችን ችግር መፍታት አቅቶናል/አልቻልንምና አገሌ ሆይ እገሊት ሆይ እርዳን፣ እርጅን፣ እርዱን ብለን ያስገባነው ማመልከቻም የለም ያቀረብነው ጥሪ የለም። እርዳታን ፍለጋ ያስገባነው ማመልከቻም ሆነ ያቀረብነው ጥሪ እስከሌለ ድረስ ደግሞ ምን ይሁን ማንም በጉዳያች ላይ ጣልቃ ገብቶ እንዳሻው ይመላለስና በህዝባችን ፊትም ይሻገር ዘንድ አንፈቅድም። የትግራይ ልጆች የአከባቢያቸውና የህዝባቸው ማንኛውም ችግር አጥንተው መፍትሔ ለማበጃጀት ሆነ ለመስጠት የአንተ የአቶ ጃዋር እርዳታ እንደማይሹ ግልጽ ሊሆንልህ ይገባል።

 

አምስት፥ የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ምንም ዓይነት ስጋት የለውም፤ እንደ ሌለውም አቶ ጃዋር የተሰወረብህ ይመስላል። ስጋት ከፍርሃት የሚመነጭ ነውና። የትግራይ ህዝብ ደግሞ የሚፈራው ግለሰብ ሊኖር ቀርቶ የሚፈራው ቡድን የለም። ለመሆኑ የትግራይ ህዝብ የሚፈራው ማንን ነው? የሚፈራ ግለሰብ ሆነ ቡድን አለ ከተባለስ የሚፈራው ምን ስለ ሆነ ነው? ለመሆኑ ህግና ስርዓት ባለባት አገር አቶ ጃዋር በትግራይ ህዝብ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት የፈቀደልህ ማን ነው? በበኩሌ እንዲህ ዓይነቱ አቶ ጃዋር ዳያስፖራ ላይ የለመደው የፖለቲካ ሸቀጥ በቃ! ተብሎ ልኩን አውቆ እንዲመላለስ ካልተደረገ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የሚመራ መንግስት የመደመር ፍልስፍና የሚያኮስስ፣ የሚያፋልስ፣ የሚያድክም፣ ውሃ የሚቸልስ ነው የሚሆነውና ጥንቃቄ ቢደረግ እመክራለሁ።

 

ስድስት፥ የደብረጽዮን ድክመት፣ የደብረጽዮን የአቅም ማነስ፣ የደብረጽዮን የአቋም መዋዥቅ፣ የትግራይ ህዝብ አቅም ማነስ ሆነ ድክመት እንደማያመላክት በዚህ አጋጣሚ ለአቶ ጃዋር ግልጽ ላደርግለት እወዳለሁ። የህወሓት መሪዎች ከፌደራል ስልጣን መወገድ ማለት ደግሞ የትግራይ ህዝብ ከስልጣን መወገድ ማለት አይደለም። የህወሓት መሪዎች ከፌደራል ስልጣን መቀነስና መንሳፈፍ ማለት የትግራይ ህዝብ እንደ አንድ ህዝብ ህገ መንግስት ያጎናጸፈውን መብትና ጥቅም ያጣል፣ ይቀርበታል፣ ይነጠቃል ወይም ይቀነሳል ማለት አይደለም።

 

የህወሓት መሪዎች መዳከምና ከስልጣን መወገድ የትግራይ ህዝብ መዳከም ነው ብሎ የሚያምን ግለሰብ ሆነ ቡድን ያለ እንደሆነም ስሌቱ የተሳሳተ መሆኑ በዚህ አጋጣሚ ለመጠቆም እወዳለሁ። የተሳሳተ ስሌት፣ የተሳሳተ እምነትና አመለካከት፣ የተሳሳተ ዕይታ - የተሳሳተ ውሳኔ ላይ ያደርሳልና። የተሳሳተ ውሳኔ ደግሞ ፍጻሜው ሊያምር እንደማይችል ባለ አእምሮ የሚስተው እውነታ አይደለም።

ስለሆነም አቶ ጃዋር የበላይነት እየተሰማው ባለው በአሁኑ ወቅት የህወሓት መሪዎች ቁልቁል ቢወርዱም በትግራይ ህዝብ ዘንድ ምንም የተፈጠረ አዲስ ነገር እንደሌለ ልብ ቢል ይበጀዋል።

 

ሰባት፥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሸነፈ ሆነ የተዳከመ ሕዝብ እንደ ሌለ በአንጻሩ የተሸነፈና የተዳከመ አብዮታዊ ዲሞክራሲና አቀንቃኞቹ ብቻ እንደሆነ በሚገባ ያስተዋልክ አይመስለኝም። ግልጽ በሆነ አማርኛ፥ የተሸነፈው የህወሓት መሪዎች እንጅ የትግራይ ህዝብ አይደለም። የከሰረው የህወሓት መሪዎች እንጅ የትግራይ ህዝብ አይደለምና በተሳሳተ ስሌት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዳትደርስ ላሳስብህ እወዳለሁ።

 

የማስታረቅን ስራ መስራት እፈልጋለሁ ያለ ሁሉ አስታራቂ አይደለም!

 

አስታራቂ ማን ነው?" የሚለው ጥያቄ ለመመለስ ብዙም የሚከብድ አይመስለኝም። አስታራቂ ከምንም በላይ ከራሱ ጋር የታረቀ ሰው ነው። አቶ ጃዋር የማስታረቅን ስራ መስራት እፈልጋለሁ ሲል ተደምጠዋል። ምኞች አይከለከልምና። ለመሆኑ የህወሓት መሪዎች የትግራይ ምሁራንን መስማት ትተው አቶ ጃዋር የሚሰሙበት ምክንያት ምንድ ነው? የህወሓት መሪዎች ከግለ ሰቦችና በግለ ሰቦች የሚመመሩ ቡዱኖች ጋር ሌላ የጓዳ ዝምድና መመስረትና መፍጠር የፈለጉበት ምክንያት ምንድ ነው? የራሳቸው ህልውና ለማስጠበቅ ወይስ የትግራይ ህዝብ ጥቅም ግድ ስለሚላቸው? ያልተገባ ግኑኝነት ሞት እንጅ ህይወት አይሆንም። ስለሆነም ይህ በቀላሉ የሚታለፍ ጥያቄ አይሆንም።

 

አቶ ጃዋር ትግራይ ክልል ድረስ በመሄድ የትግራይ ህዝብ ችግር ለማጤን እያቀረበው ያለው ጥሪና ያሳየው ፍላጎት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ጥያቄ ነው። የዋህ ካልሆነህ በስተቀር አስታራቂ ነኝ ያለ ሁሉ አስታራቂ እንዳይደለ ዜጎች በሚገባ መረዳት መቻል አለባቸው። አቶ ጃዋር የሚወክለው ቡድን አለው። ይህ አቶ ጃዋር በአባልነት የሚገኝበት ቡድን ደግሞ ቀደም ስል እንደጠቀስኩት በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ በስውር ይሁን በግላጭ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አጀንዳ ያለው ግሩፕ ነው። የአቶ ጃዋር ድርሻ አስታራቂ መሆን እፈልጋለሁ በሚል ሽፋን ዲፕሎማቲክ በሆነ መሰሪ አካሄድ የሚወክለውን ቡድን የበላይነት ማስተዋወቅ፣ ማንገስና ማጎልበት ነው። የትግራይ ህዝብ ደግሞ ይህን ሴራ ይስተዋል ብሎ ማሰብ በራሱ ትልቅ ስህተት ነው።

 

አቶ ጃዋር በባህሪው አስታራቂ ሊሆን የሚችል ዓይነት ግለሰብ አይደለም። አስታራቂ መሆን ማለት የፖለቲካ አክሮባቲስት ማለት ነው በሚል አዲስ ትርጉም ካልተስማማን በስተቀር። አቶ ጃዋር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ፍላጎት (Interest) ያለው ሰው ነው። ይህም አሁን አስታራቂ መሆን እፈልጋለሁ ስላለ ሳይሆን ግለሰቡን እንደ አስታራቂ መቀበል ያለብን የግለሰቡ ታሪክ ማጤን ወሳኝነት አለውና። አስታራቂ ነኝ ብሎ የማይታረቅ ጠባሳ ጥለውልን ያለፉ አስታራቂ ነን ባዮች ጥቂቶች አይደሉም፤ አቶ ጃዋርም አንተ የመጀመሪያ ሰው አይደለህምና አካሄድህ ብዙ እንደማያስኬድህ በዚህ አጋጣሚ ወንድማዊ ምክሬን ልለግስልህ እወዳለሁ። ለምን?

 

አንድ፥ የህወሓት መሪዎች ከአዲስ አበባ መንግስት ያለው ግኑኝነት የሚስተካከለው አንተ (አቶ ጃዋር) በምትመክረው ምክር ሳይሆን መጀመሪያ የህወሓት መሪዎች በውስጣቸው ያለውን ችግር መፍታት ሲችሉ ነው። የህወሓት ችግር ደግሞ አንተ (አቶ ጃዋር) የሚመለከት ጉዳይ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ብቻ የሚመለከት ጉዳይ ነው።

 

ሁለት፥ አቶ ጃዋር እውነት ህዝቦችን የሚያቀራርብ፣ በህዝቦች መካከል ሰላማና ፍቅርን ማምጣትና ማንገስ የሚያስችል አቅም፣ እውቀትና ክህሎት ካለህ እየተተራመሰ ያለው ክልልና ህዝብ የትግራይ ክልልና ህዝብ ሳይሆን ኦሮሚያና ሶማሊያ ነው። አቶ ጃዋር ህዝብና ሀገርን የሚጠቅም የሰላም መልዕክት አለኝ ብለህ የምታምን ከሆነ የሰላም መልእክተኛ ያለህ! እያለ እየተማጸነ ያለውና የምስራችን የሚያወራ የሰላም ሓዋሪያ የሚያስፈልገው ህዝብና ክልል ከማንም ክልል በላይ አቶ ጃዋር እትብትህ ተቆርጦ የተቀበረበትና ተወልደህ ያደግክበት ኣከባቢ ነው።

 

ሶስት፥ እውነት አቶ ጃዋር በሀገራችን እየታየ ያለው መተረማመስ የመቅረፍና የማስወግድ በአንጻሩ በህዝቦች መካከል ሰላምንና እርቅን የማስፈንና የማውረድ ልዩ እወቀትና ችሎታ አለኝ ብለህ የምታምን ከሆነ ሰላሙን አጥቶ አየታመሰ ያለው ህዝብና ክልል ከዚህም አልፎ ቆርበቱ ለመግፈፍ የተዘጋጀ በግ ይመስል ክቡር የሰው ልጅ ቁልቁል ተደፍቶ የተንጠለጠለበት አስደንጋጭ ክስተት ያየነው ትግራይ ሳይሆን አቶ ጃዋር ብዙ ደጋፊ አለኝ ብለህ በምትመካበት ቦታ ነው። ስለሆነም አቶ ጀዋር አገርንና ህዝብን የሚበጅ የሰላም አጀንዳ ካለህ ሰላምን መስበክና ማምጣት ከቤት/ከራስ እንደሚጀምር የፖለቲካ ሳይንቲስት ነኝ ብሎ ለሚያምን ግለሰብ መናገር ለቀባሪ መርዳት ስለ ሆነብኝ አቶ ጃዋር የትግራይ ክልል ድረስ ሂደህ የትግራይ ክልል ተወላጆች ሰብስበህ የምታነጋግርበት ሆነ የምታወያይበት ምንም ምክንያት የለህም።

 

የአቶ ጃዋር ፍላጎት ምንድ ነው?

 

አንድ፥ አቶ ጃዋር በዶ/ር አብይና በአቶ ለማ አስተዳደር ሳይደሰት ቀርቶ የህወሓት መሪዎችን ተለጥፎ የገዛ ራሱ ህዝብ በማተረማመስና ደም በማቃበት ወደ ስልጣን የመውጣት ፍላጎት አድሮት ይሆን?

 

ሁለት፥ ህዝብና አገር ገደል ቢገቡ ግድ የማይሰጣቸው ደንታ ቢሶች የህወሓት መሪዎች ጥቅማቸና ክብራቸውን ለማስጠበቅ የማይቆፉሩት ጉድጓድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለምና ምናልባት የህወሓት መሪዎች በአሁን ሰዓት በስትራቴጂ ደረጃ ትምክህተኛ ሃይል በማለት የሚፈርጁት አካል ለመዋጋት ኦሮሞን እንደ የእኩልነት አጋር በመውሰድ ከኦሮሞ ብቻ በመደመር ዘመናቸውን ለማራዘም አቶ ጀዋር የራሱ ሚና ለመጫወት ፍቃዱን የሚያሳይበት ፍንጭ ይሆን?

 

ሶስት፥ 80 በመቶ የፌደራል ስልጣን በኦሮሚያ ክልል ተወላጆች መያዙን ተከትሎ አቶ ጀዋር ዘመኑ (የእኛ) የኦሮሞ ዘመን ነው ብሎ ስለ ሚያምን ይሆን ለትግራይ ህዝብ የሚበጀውንና የማይበጀውን አፉን ከፍቶ ለመናገር የደፈረው? ( በነገራችን ላይ የአቶ ጃዋር እምነት የኦሮሞ ህዝብ ይወክላል የሚል እምነት የለኝም) አቶ ጃዋር የትግራይ ህዝብ ማለት የኢትዮጵያ አንድ አካል መሆኑን፤ ይህ ማለት ደግሞ የትግራይ ህዝብ የማንም ድጋፍና እርዳታ ሳይሻና ሳይፈልግ ለመብቱና ለጥቅሙ መቆም የሚችልና ለክብሩም ዛሬም የማይደራደር ህዝብ መሆኑን የዘነጋኸው ትመስላለህ። በእርግጥ ቀደም ስል ያሰፈርኩት ሐቅ ዘንግተኸው ሳይሆን ማን አባቱ ማድረግ የምፈልገውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስቆመኝ ማንም የለም ብለህ ስለ ምታምን ነው። እንግዲያው ጉዳዩ በሂደት የሚታይና በጊዜ የሚፈታው ስለሆነ ለጊዜው መልስ አይኖረኝም።

 

አራት፥ ወደ ስልጣን የመጣውን የኦሮሞ ሃይል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ነውና የተቆናጠጥነው ስልጣን በአማራ ልሂቃን በቀላሉ ተጠልፈን ላለመውደቅ የህወሃት መሪዎች እርዳታ መሻቱ ይሆን?

 

ወዴት ሊያመራን ይችል ይሆን?

 

የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያ የምትባል የጋራችን የሆነች አንዲት አገር እስካለች ድረስ የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ማንም ሰለ ወደ ተችሮለት ወይም ስለ ጠላ ደግሞ ያለውን የሚወሰድበት በዘፈቀደ የሚዘወር ህዝብ ሳይሆን ኢትዮጵያ ለህዝቦችዋ በምታበረክተው ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል ኢኮኖሚያዊ ጥቅማ ጥቅሞች እኩል ተካፋይ ነው። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል የመምከር፣ የመቀበልና የመንፈግ፤ የመሻር ሆነ የማጽደቅ ባለ ሙሉ መብትና ስልጣን ያለው ህዝብ ነው።

 

ስለሆነም፥ እኛ የትግራይ ክልል ተወላጆች ከሌሎች ወንድም እህት ኢትዮጵያውን ወገኖቻችን ፍጹም በሆነ፣ ሽንገላ በሌለበት እውነተኛ ፍቅር ተዋደንና ተፋቅረን መኖርን የምንሻ ህዝብ ነን። ይህ ማለት ግን ሌሎች በውስጥ በጉዳያችን ላይ እጃቸው እንዲሰዱ፤ ወጥተው እንዲገቡ፣ ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ በማለት የትግራይ ህዝብ በሚመለከት አጀንዳ ቀርጸው እንዲሰጡንና መግቢያ መውጫችን እንዲያሰምሩል፤ ጣልቃ እንዲገቡ መፍቀድ ማለት አይደለም። የትግራይ ህዝብ ጣልቃ ገብነትን አይፈቅድም። ትናንት ያልጠቀመን የእኔ አውቅልሃለሁ ፖለቲካ በምንም ዓይነት መልኩ ዛሬም ቢሆን አይጠቅመንም። ትናንት ያልበጀንን ጣልቃ ገብነት ዛሬም ቢሆን አይበጀንም። ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱ ስርአት አልበኝነትና መረን የለቀቀ የቲፎዞ ፖለቲካ አገር ይበትን እንደሆነ እንጅ አገር አያቀናምና አደብ መግዛት የሚገባው ሁሉ ከወዲሁ አድብ እንዲይዝ ቢደረግ ይመከራል።

 

በዚህ አጋጣሚ፥ የህወሓት መሪዎች ከአገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን መወገድን ተከትሎ የትግራይ ክልል ተወላጆች ትግራዋይ በመሆናቸው ብቻ እየታደኑ ከስልጣን የሚገለሉበት፣ የሚገፉበት፣ የሚወገዱበትና የሚንሳፈፉበት አሰራር መደመር ከሚለው የክቡር ጠ/ር ዶ/ር ዓብይ አሕመድ የፍቅር

ፍልስፍና እጅግኑ የሚቃረን ነውና ጉዳዩ ሊያስከትለው የሚችል ጠንቅ ከወዲሁ በማየት በአስቸኳይ ልናስቆም ይገባል ለማለት እወዳለሁ።

 

አንድ ሰው ትግራይዋይ ስለ ሆነ ብቻ የህወሓት መሪዎች እምነት/አጀንዳ ይጋራል፤ የጥቅም ተካፋይ ነው ማለት አይደለም። አንድ ሰው እንደ ዜጋ ከማየትና በግላዊ አቋሙ ከመመዘን ይልቅም በስመ ትግራይዋይ ብቻ ወደ መፈረጅ ከተደረሰ፣ ዜጎች የትግራይ ክልል ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ እንዲሸማቀቁ የሚደረግ ከሆነ ነገሩ ፋሽሽትነት ከመሆን አልፎ ሌላ ሊባል አይቻልም። የትግራይ ህዝብ ደግሞ በታሪኩ ፋሽሽታዊ መንግስት ሆነ አሰራር እሽርሩ የሚልበት፣ ወዶና ፍቅዶ የሚቀበልበት፣ አሜን ብሎ የሚገዛበት፣ ባርነትን በይሁንታ የሚያስተናግድበት፣ ራሱን ለውርደትንና ለውድቀትን አሳልፎ የሚሰጥበት፣ ሞትን በትዕግስት የሚሸከምበት ትክሻ የለውም። ዛሬም እንደ ትናንት መብቱንና ጥቅሙን ጠብቆ ለማስጠበቅ የማንም ፈቃድ የማይጠብቅ ህዝብ ነው።

 

ጥያቄ አለኝ!

 

አንድ፥ አቶ ጃዋር ኤስር ጊዜ ሚኒስተርነት አልፈልግም ሲል ይደመጣል። ለመሆኑ ግለሰቡ ሚኒስትር እናደርጋሃለን ተብሎ ተደራድሮ ነው እንዴ የመጣ? ማን ነው ስልጣን እንሰጣሃለን ያለው? አገሪቱ ህግና ስርዓት የላትም ወይ? ወይስ ኢትዮጵያ ማለት ማይክ የጨበጠ ሁሉ ሚኒስትር የሚሆንባት አገር ሆናለች ማለት ነው?

 

ሁለት፥ አቶ ጃዋር ከሚላቸው ነገሮች መካከል አንዱ ሌላ ጠቅላይ ሚንስትሩን እንዲህ አልኩት እንዲህ መከርኩት የሚለውን ነገር ነው። ለመሆኑ አቶ ጃዋር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አማካሪ የሆነው ከመቼ ወዲህ ነው? ግለሰቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲህና እንዲያ የማለት ስልጣኑ የሰጠውስ ማን ነው?

 

ሶስት፥ አቶ ጃዋር ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልዕክት በቀጥታ ከማናገርና ከማስተላለፉ በፊት ሃሳቡን በስዎች አእምሮ የበላይነት ይኖረው ዘንድ ከሚጠቀምባቸው ስልቶች መካከል አንዱ አስቀድሞ የሰዎችን አእምሮ የመያዝ፣ የመስለብ፣ የማዳከምና የማኮላሸት ልማድ አለው። በሰሚዎች ዘንድም ሃሳቡ ተቀባይነት እንዲኖረውና የሰውን አእምሮ ለመያዝ በተደጋጋሚ ባለኝ ልምድና እውቀት ሲል ይደመጣል። ለመሆኑ ይህ ግለሰብ ምን ዓይነት ትምህርት ነው የተማረው? ለምን ያህል ጊዜ በየትኛው ዓለም አቀፍ ድርጅት ተቀጥሮ ወይም ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ተቀምጦ ነበር የሰራው? በነገራችን ላይ ሰው የሚማረው መጀመሪያ ለራሱ ነው።

 

በውስጥም በውጭም ለምትኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተጋሩ በሙሉ፥

 

ትግራይ ዛሬም እንደ ትናንት የህዝባቸውን አጀንዳ አነግበው የህዝባቸውን ጥቅምና መብት በየትኛውም መደረክ ጠብቀው ማስጠበቅ የሚችሉ ልጆች አሏት። ትግራይ የወላድ መሃን አይደለችም። የአቶ ጃዋር በትግራይ የውስጥ ፖለቲካ ገብቶ የመፈትፈትና እንዳሻው ለመሆን ያሳየው ፍላጎትና ያቀረበው ጥሪ ምንም ዓይነት ተቀባይነት እንደ ሌለውና የትግራይን ህዝብ ጥቅም ማዕከል ያደረገ እንዳይደለ በማወቅ አቶ ጃዋር ያቀረበው ጥሪና ያሳየው ፍላጎት በመንፈግ ድርጊቱ በጥብቅ መወገዝ እዳለበትም በጥብቅ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

 

በመጨረሻ፥ ከአቶ ጃዋር ሊኖረን ስለሚችል ፖለቲካዊ እምነትና አስተሳሰብ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተመለከተ የጋራ አጀንዳ ኖሮን አንድ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠን መነጋገር፣ መወያየትና መመካከር ግን አንችልም እያልኩ እንዳልሆነ አንባቢ አይስተውም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

 

Back to Front Page