Back to Front Page


Share This Article!
Share
ለውጡን የሚያናውጡ ይውጡ

ለውጡን የሚያናውጡ ይውጡ

ይቤ አብርሃ ከውቤ በረሃ

09-26-18

ለውጥ ባለበት ቦታ ነውጥም ይኖራል። ስለዚህ ለውጥና ነውጥ የጎሪጥ እየተያዩም አንዳቸው አሸናፊ ሆነው እስኪወጡ ጎን ለጎን ይጓዛሉ። የኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛው የሚያሳየን ሥልጣን የሚገኘው በጠብመንጃ አፈሙዝ ወይም በጦርነት እንጂ በጠረጴዛ ውይይት አለመሆኑን ነው።የኢህአዴግ ምክር ቤት ይሄንን የዘልማድ የሥልጣን ተሞክሮ በመስበር ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በመቀየር አሳይቶናል። ርምጃው ዘወትር በሥልጣን ለሚሻኮቱና ህዝባቸውን በስደትና ጠኔ ለሚያንገላቱ ለአፍሪካውያን መሪዎች ምሳሌ የሚሆን ነው። ይህም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደናቂነት አስገኝቷል። ለሀገራችንም ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ከመስጠቱ በተጨማሪ ገፅታችንን የሚገነባ ነው።

ላለፉት ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ ለተከሰቱት ቀውሶችና ሁከቶች እልባት ለመስጠት የገዢው ፓርቲ ምክር ቤት ዶክተር ዐቢይ አህመድን በፓርቲው ሊቀመንበርነት በመምረጥ በኢፌዴሪ ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲሾሙ ካስደረገ ግማሽ መንፈቀ ዓመት ሆኗቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ሀገር አመራር ባለፉት ስድስት ወራት ላሳዩት ጅምር ክንውኖች ኢህአዴግ የጅምር ለውጡ ተዋናይ፣ ሠሪና ቀማሪ በመሆን የተጫወተውን ጉልህ ሚና የሚያስረዱ ናቸው። የተሠሩት ጅምር የለውጥ ሥራዎች አመርቂዎች ናቸው። በተለይ በውጭ ዲፕሎማሲው ሥራ ድልን ያጎናፀፉ በመሆናቸው እንኮራለን።

Videos From Around The World

በውጭ ሀገራት በተለያዩ ሰበብ አስባቦች የታሠሩ ዜጎች እንዲፈቱ የተሄደበት ርቀትና የተገኘው ውጤት የሚደነቅ ነው።ለሀገሩ ባዳ ለሰው እንግዳ ሆኖ በስደት በሚኖርበት ሀገር የፌዴራል መንግሥቱን ሲንቅና ተቃዋሚነትን ሲያቀነቅን የነበረው ዲያስፖራ ገዢውን ፓርቲ ከመንቀፍ ወደ መደገፍ ተሸጋግሯል ማለት ይቻላል።በዚህም የለውጡን ጅምር ሥራዎች ያደነቁ አያሌዎች ናቸው።

ነገር ግን አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ዜጎች የለውጡን ጅማሬ አደነቁ እንጂ የለውጡን ጅማሬ ፍሬ ለማጣጣም አልታደሉም። አበባው አበበ እንጂ ፍሬ አላፈራም። ስለዚህ ለውጡ ያማረ ነው ወይም የመረረ ነው ለማለት ገና ማጣጣም አለብን። በለውጥ መንገድ ላይ እንደሆንን ሁላችን እናውቃለን። በአንድ ጀንበር ለውጥ ሊመጣ አይችልም።መረጋጋት ያስፈልጋል።

ጅማሬውን ስናየው ግን የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እመው (እናቶች) እንዲሉ ለውጡ ተስፋ የሚያጭር እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። ዜጎች አዲሱን ዓመት የተቀበሉት ብሩህ ርዕይን ጠብቀው በጎ ተስፋን ሰንቀው ነው ማለት ይቻላል።

አህአዴግ የወሰዳቸውን የለውጥ ርምጃዎች በጉጉትና በናፈቆት የሚጠብቁ አካላት የመኖራቸውን ያህል በለውጡ የሚናጡና የሚደናገጡ ይኖራሉ። በጅምር ለውጡ የሚደናገጡ የነውጥ ማዕበል ማነሳሳታቸው የማይቀር ነው።የለውጥ ደመናን ሲጠብቁ የነውጥ ማዕበልን ማወቁና መጠንቀቁ ተገቢ ነው። በለውጡ የተገፉ የሚመስላቸው የተከፉ እና ያኮረፉ አይጠፉም።

እነዚህ ሰዎች የነውጥ ማዕበል ለማነሳሳት እጃቸው ቢያጥር እንኳ መፍጨርጨራቸው እይቀርም።ቀደም ሲል በሶማሌ፣ በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እና በድሬዳዋ ከተማ በሰሞኑን ደግሞ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች በተነሱት ሁከቶችና ግጭቶች፣ የሞቱ ዜጎች፣ የጠፉና የተዘረፉ ንብረቶች በለውጡ በተደናገጡ አንጃዎች የመጣ ነውጥ ነው ማለት ይቻላል። በለውጡ ጮቤ የረገጡ (የተደሰቱ) አልያም ጩቤ የጨበጡ (የተበሳጩ) መኖራቸው የማይቀር ነው።ሁሉንም ዜጋ ሊያሰደስት የሚችል አመራር በየትም ሀገር ሊኖር አይችልም። ኅብረተሰቡ ለውጡን የሚያናውጡ ይውጡ ማለትም ይጋለጡ ብሎ መጠየቅ፣አካባቢውንም ከፖሊሶች ጋር ተባብሮ መጠበቅ አለበት።

ኢህአዴግ የሀገሪቱ አውራ ፓርቲ ሆኖ ብዙ በጎ ሥራዎችን ቢሰራም የፈፀመው የአሠራር እንከኖችና ያላለፈው ተግዳሮት አለ። ፓርቲው የሰዎች ስብስብ ነው። በሥራ ላይ እያለ ያውም ሀገርን በመምራት ላይ ሆኖ ስህተቶች ይፈፀማሉ። ፈረንጆች እንደሚሉት የሚሠራ ሰው ይሳሳታል ትልቁ ስህተት ግን አለመሥራት ነው። ነገር ግን ለህዝብ እንሠራለን ብለው ለራሳቸው ጥቅም ሲሠሩ የነበሩ እንዳሉ ይታወቃል።

በስህተት የሚሳሳቱ የመኖራቸውን ያህል ሆን ብለው ስህተት የሚፈፅሙም ይኖራሉ። ገሚሶቹ የአመራር አካል ሆነው በማንአለብኝነት የፈፀሙት ስህተት ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ዋና ዋና አመራሮችን በማየት በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና የተዘፈቁና የተጨማለቁ ናቸው።ፓርቲው የሰዎች ስብስብ እንጂ የመላዕክት ስብስብ አይደለምና ስህተቶችን መፈፀሙ የማይቀር ነው። ነገር ግን በይቅርታ የሚታለፉ እንከኖች የመኖራቸውን ያህል የማይታለፉ ጥፋቶችም ይኖራሉ። በስህተቱ ስንተቸውም በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት መሆን አለበት። በየአካባቢው የሚነሳው ነውጥ እዚህ ግባ የሚባል ምክንያት የሌለው ነው።

ተምረናል የሚሉት ዜጎቻችን ጥላቻንና መቃቃርን ሲሰብኩ ያልተማረው ማኅበረሰብ መደመርንና ፍቅርን እያስተማረ ሁከትና ግርግርን ለማብረድ እርቅን ለማውረድ ሲጥር ይስተዋላል። የመለያየትን ጦስ ከጎረቤታችን ሶማሊያ ማየት እንችላለን። ሶማሊያ አንድ ሀገር፣ አንድ ቋንቋ እና እምነት ተከታይ ሀገር ሆና ላለፉት ሃያ ዓመታት በጎሳ ጦርነትና ግጭት ስትታመስ ቆይታለች። በዚህም የብዙ ዜጎቿ ሕይወት ሲያልፍ፣ ንብረት ሲዘረፍ ቆይቷል። ሀገሪቱም የአሸባሪዎችና የዘራፊዎች መፈንጫ መሆኗ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

መለያየትን የሚያራግቡ አካላት አካሄዳቸውን መለስ ብለው መቃኘት አለባቸው። በኢትዮጵያ ነውጥና ብጥብጥ ቢነሳ እንጠቀማለን የሚሉ አካላት የበለጠ ለጉዳት ይጋለጣሉ። ማንም እየመጣ እነሱን ሊያጠቃቸው ስለሚችል አካሄዳቸውን በድጋሚ ቢቃኙ መልካም ነው። መንግሥትም በተለይ የፀጥታ አካላት ካሸለቡበት እንቅልፍ ነቅትው የግብር ከፋዩን ዜጋ ሰላምና ፀጥታ ተግተው ማስከበር ይገባቸዋል። በዋናዋ መዲና አዲስ አበባና ዘሪያዋ ከሃምሳ በላይ ዜጎች በጠራራ ፀሀይ ሲገደሉ ፖሊሶች የት ነበሩ ? ከነዚህ ውስጥ ነውጡን የሚደግፉ ታልፈው ነውጡን የሚነቅፉ ወደ ሰባት ሰዎች መገደላቸው አግባብ አይደለም። ሁከቱ በተነሳበት ጊዜ በእንጭጩ ቢቀጭ ኖሮ የታዘብነው አምባጓሮ ይገታ ነበር።በአዲስ አበባ ግጭቱን ብሔር ተኮር ለማስመሰል ሲጥሩ የነበሩ ከ1ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሓላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገልፀዋል። ይህም ለችግሩ እልባት ለመስጠት የተወሰደ ርምጃ ነው።

የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ፣ በሀገሪቱ ዴሞክራሲ የለም የሚሉ በስደት የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ የሚያቃቅርና የሚያናቁር ሥራ ሲሠሩ ይታያሉ። ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ፓርቲ አመራሮችን ለመቀበል በተጠራ ስብሰባ ፕሮግራሙን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች ከፋፋይነትን የሚያስተጋባ ስሜት ሲያሠራጩ መታዘብ ችያለሁ። አብዛኞቹ ዴሞክራሲ ከሰፈነባቸው ሀገሮች ከረጅም የስደት ዘመን መጥተው ከፋፋይ አጀንዳን ማስተጋባታቸው መቃቃርና መናቆር ያመጣል እንጂ የሚያመጣው ፋይዳ የለም።

ከመንግሥት በተለይ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንና የሚመለከታቸው አካላት ህዝብ በተሰበሰበበት (በተለይ የፓርቲ ደጋፊዎች) ባሉበት መድረኩን የሚመራ ሰው ከራሳቸው መመደብ ነበረባቸው። አልያም መድረኮቹን የሚመራ ሰው ህዝብን ከህዝብ የሚያቃቅር መልዕክት እንዳያስተላልፍ መጣር ግድ ነው።ጋዜጦች እንኳ ብሔርን ከብሔር ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያቃቅር መልዕክት የሚያስተላልፉ ከሆነ ዕገዳ ይጣልባቸዋል።

ምዕራባውያንም የኢትዮጵያን ሰላምና ፀጥታ ይፈልጋሉ።የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም ደህንነት የራቀው፣ ሁከትና ግጭት የቀረበው በመሆኑ ሀገራችን ታውካ በሶማሊያ የታየው ክስተት እንዳይደገም ይሻሉ። በሀገራችን ሁከት ቢነሳ ፀጥ ብለው ሊያዩ የሚችሉበት ነገር የለም።ሀገራችን ከያዘችው የህዝብ ቁጥር ፣ ለቀጣናው ሰላም ከምትወጣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሚና አንፃር ሰላማችንና ፀጥታችን ያሳስባቸዋል። ይህን የፖለቲካ ፓርቲዎች መገንዘብ አለባቸው። የሚሄዱበት የከፋፋይነትና የልዩነት አጀንዳ ለዘመናችን አትራፊ አይሆንም።

 

 

 

 

Back to Front Page