Back to Front Page


Share This Article!
Share
ፀጉረ ልውጥ የህግ ትርጉም ይሰጠው!

ፀጉረ ልውጥ የህግ ትርጉም ይሰጠው!

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 09-25-18

ላያት ሁሉ አይነ ግቡ የሆነችው ውብና ፅዱዋ ሃዋሳ ከተማ ለታሪካዊው የኢህአዲግ ጉባኤ መሰየሚያ ሆና ተመርጣለች፤ ይገባታል። ለዚህ ጉባኤ የሚደረገው ዝግጅት አካል የሆነው የደህንነት ጥበቃ መግለጫ በተከበሩ የክልሉ ፓሊስ ኮሚሽነር ተከናውኗል። የጉባኤው በሰላም መጠናቀቅ ለሃዋሳ ከተማ ህዝብ እጅግ ወሳኝ ነውና ፓሊስ ብቻውን ሳይሆን ህዝቡም እንደራሱ ጉዳይ አይቶ አብሮ መስራት ይኖርበታል። ይህን ካልኩኝ በኋላ ይህን አስተያየት ለመፃፍ ወደ አስገሳደኝ የፓሊስ ኮሚሽነሩ መግለጫ ልለፍ።

Videos From Around The World

ማንን ማለታቸው እንደሆነ ከመገመት በስተቀር፣ ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው ይባላልና፣ እርግጠኛ መሆን የማይቻልበት የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአደባባይ ላይ "ስያሜ" ሰው ሁሉ የየራሱ መዝገበ ቃላት ይዞ ሲተረጉመውና ሲተገብረው ከረመ። ይህ ሃረግ "ፀጉረ ልውጥ" የተሰኘው ሲሆን ዘመናት የቆጠረ የአማርኛ ቃል/ሃረግ ነው። ይህ ቃል/ሃረግ ነባር ቢሆንም አተገባበሩ ላይ የጎላ ችግር አልነበረበትም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ገጠር ይሁን ከተማ መሄድም፣ መኖርም፣ መዘዋወርም፣ የሚከለክለው ነገር ስላልነበረ፤ እንዲያውም እንግዳ ሲሆንማ እንክብካቤው ሌላ ነበር። "የስው አገር ሰው" ተብሎ ያላቸውን ያቀርቡለታል።

ባለንበት አስቸጋሪ ጊዜ ሰው በማያውቀው ሰው ይቅርና የራሱ ጥላ ሲከተለው መደናገጥ ጀምሯል። በኢትዮጵያ ውስጥ ለአፈፃፀም አስቸጋሪ የሆኑና ራሳችንን የማንወጣው ችግር ውስጥ የከተቱን ቃላትና ፍረጃዎች መጠቀም ከጀመርን ቆይተናል። "ብሄር" ብለን አንዳንዱን ሰው የትኛው ሳጥን ውስጥ እንደምንከተው በትክክል የማናውቅበት ሁኔታ እየተፈጠረ የግምትና የግብታዊነት ስራ ስንሰራና ህብረተሰቡን በእጅጉ ስንጎዳ እንገኛለን። "ፀጉረ ልውጥ" የሚለው ቃል የሃገሪቱ "ቀዳማዊ ጌታ" ስለተናገሩት በጎጂ ባህላችን መሠረት "ምን ማለትዎ ነው?" ብሎ ማብራርያ መጠየቅ የለም።

"ጦር አውርድ" በሚለው የበእውቀቱ ስዩም ልብ የሚነካ ትረካ ላይ ንጉሱ "የመንን እንውጋት ሲሉ" መኳንንቱ ለማንሰላሰል ጊዜ ሳይሰጡ "እንበላት" ብለው ተነሱ። መሪ የሚናገራት እያንዳንዷ ቃል የህግና የፓለቲካ ትርጉም ያላት ፓሊሲም ስትራተጂም ናት። አምላኩን፣ ዙፋኑንና ህዝብን የሚያከብር መሪ በስሜት መናገር አይኖርበትም፤ "ከአፍ ከወጣ አፋፍ" ይሆናልና።

ትርጉም በሌለበት ትርጉም ከራስ የሆነ ስራ ቀጠለና " አትግደል" የሚለው የአስርቱ ትእዛዛት ቃል ማደሪያ ከሆነው ደብር ውስጥ "ፀጉረ ልውጥ" በደቦ በግፍ ተገደለ። እብደት ነው አይደለም? ነው እንጂ፣ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ከ"ፀጉረ ልውጥ" ተጠንቀቁ ሲባል የህግ ትርጉሙ አብሮ ካልተሰጠ ሆድ ለባሰው ማጭድ ከማዋስ የሚተናነስ አይደለም። ይህ ብቻ አይደለም። ወደ አካባቢው "የሱ ዘር ያልሆነ" ሰው እንዳይመጣበት የሚፈልግ ሰውም ይህንን "መመሪያ" በ"ህጋዊ" መሣሪያነት ይጠቀምበታል።

አዋጆችና ፓሊሲዎች ሲወጡ በመጀመሪያ ገፃቸው ላይ በሰነዶቹ ለሰፈሩ ቃላትና ሃረጎች ትርጉም ይሰጣል። ይህ የሚደረገው ቃላት እንደየአገባባቸው የተለያየ ትርጉም ስለሚኖራቸው የህግ አንቀፅ ተጠቅሶ ቅጣት በሚወሰንበት የህግና ፓሊሲ አተገባበር አለም ውስጥ የትርጉም አሻሚነት መኖሩ ፍትህ የሚያጓድል አደገኛ ነገር በመሆኑ ነው። በሳይንሳዊ ምርምርም ቢሆን አንድ "ቫርያብል" (ትክክለኛ የአማርኛ ቃል አላገኘሁለትም) በዛው ምርምር ውስጥ እንዲይዝ የተፈለገው ትርጉም መገለፁ የግድ ነው። የምርምር መረጃ መሰብሰቢያ ቅፃቅፆች የሚዘጋጁትም "ቫርያብሎች" ከምርምሩ አላማ ጋር የተገናዘበ የማያወላዳ ትርጉም ከተሰጣቸው በኋላ ነው። አለበለዚያማ የምንሰበስበው መረጃ ከምርምሩ ዋናና ዝርዝር አላማ ጋር "አራምባና ቆቦ ሆኖ ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ይባክናል። ይህን ትርጉም "ኦፐሬሽናል ዴፊኒሽን" ይሉታል በልሳነ እንግሊዝ። ለአፈፃፀም የሚመች ትርጉም እንደ ማለት ነው።

ህዝብን በማይወክሉና በአስር ሺዎች የተሰውለትን ህዝባዊ አላማ በሸጡ ጥቂት አግበስባሽ ግለሰቦች ሰዉ ሁሉ በደረሰበት በደል ከመከፋቱ የተነሳ ቀጥሎ የማነሳውን ጉዳይ የማነሳው ብዙ ካመነታሁ በኋላ መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁ። የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሌላው በአደባባይ የተወሰኑ ህዝብን ጎድተዋል ያሏቸውን ለመግለፅ የተጠቀሙበት ቃል/ሃረግ "የቀን ጅቦች" የሚል ነው። ይህ በአሁኑ ዘመነኛ ቋንቋ "ቫይራል" የሆነው የፍረጃ ቃል/ሃረግ እመልካች ጣቶን በጠንካራው ቀስረው የሚመለከታቸውን በስም እየጠሩ ሐቁን እንደ ቲማቲም ቢያፈርጡት ኖሮ "የቀን ጅቦች" ሳይሆን የ"ጁራሲክ ስጋ በል ዳይኖሶሮች" ቢሏቸውም ሲያንሳቸው ነበር። ተመቺው ማን እንደሆነ ሳይታወቅ አየር ላይ የዋለው ቅዝምዝም ሁሉም ወደፈለገበት አቅጣጫ ቀልብሶ ሊማታበት ሲሞክር ይስተዋላል።

አንዱ ጦማሪም "የአመቱ ታላቅ ቀልድ" ብሎ አንዱ ድረገፅ ላይ መርጎታል። ቃሉ/ሃረጉ አቅጣጫውና ግቡ ግልፅ ቢደረግ ኖሮ ግን "የአመቱ ታላቅ ቀልድ" ሳይሆን "የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ቁምነገር" ይሆን ነበር። ነገሩ "ክፍት የሥራ/የቀልድ ቦታ" ሆነና በረንዳ ላይ የተኛ ከጎጃም የመጣው ለምኖ አደር ኣብሮት እዛው በረንዳ ላይ የወደቀውን ከትግራይ የመጣውን "የኔ ብጤ" አንት የቀን ጅብ" ቢለው መቸም ከምሩ አይደለም ብሎ ያሰበው "ተሰዳቢ" "አሁን እኮ ቀን አይደለም" ብሎ ቢመልስለት ሳይርባቸው የሚያድሩበት ጥሩ እራት አይሆንም ትላላችሁ?

ይህ ለፈገግታ ቢሆንም የሚያቃጥል ገፅታም አለው። "የቀን ጅብ" የሚለው ተናጋሪው ሲናገሩት፣ መቸም በጣም የበሰሉ ሰው ናቸውና፣ ባይተነትኑትም በአይምሯቸው ይዘውት ኖሮ ይሆናል ያልኩት "የአዋቂ ግምት" አለኝ። "የቀን ጅብ" ማለት በጥሬው ሲተረጎም፦ ጅብ በተፈጥሮው ፈሪና አይናፋር ስለሆነ የሚበላው ነገር ለማግኘት በሰው ስፈር የሚዘዋውረው በሌሊት ነው። የቀን ጅብ በእውነታው አለም የተለመደ ክስተት ስላልሆነ ያለምንም ፍርሀትና ይሉኝታ የሚደረግን ዝርፊያ ለመግለፅ የምንጠቀምበት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። "የቀን ጅብ" ከነትርጉሙ ባለመነገሩ ስያሜው የሚመለከታቸው በተንኮል የማይመለከታቸው ደግሞ በየዋህነት ወይንም በመሠረተቢስ ጥላቻ ተነሳስተው የቀስቱን አቅጣጫ ወደ ተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ያዞሩታል። ምንጊዜም ቢሆን በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ አንድ ላይ ተደራጅቶ አይዘርፍም። ዝርፍያ በተፈጥሮው ግለሰባዊና ቡድናዊ እንጂ ህዝባዊ ሆኖ አያውቅም። ዘራፊዎቹ ግን ህዝባዊ ገፅታ ማላበስ አዋጪ ሆኖ ያገኙታል፤ ጥሩ መሸሸጊያ ስለሆነ።

በሌላ በኩልም የዘራፈ ቡድን አባላት ሆነው ከቆዩ በኋላ የፍርድ ቀን ሲመጣ ከመሃላቸው ብዙም ደጋፊ የሌለውና የተጠላውን አሳልፎ በመስጠት ጲላጦስ ሆነው ከአባራሪዎቹ ጋር አብረው "ሌባ ሌባ" እያሉ ይሮጣሉ። አባራሪዎችን እንደ ጋሪ ፈረስ ስሜት በሚነካ ንግግርንና በመፈክር ብዛት ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲያዩ አድርገው ስለለጎሟቸው ከጎናቸውና ከኋላቸው በኩል ያሉትን ዘራፊዎች ማየት ተስኗቸዋል። ስለዚህ እንዱን የአብርሃም በግ አድርጎ ዝርፊያው በ"ህዝብ ድጋፍ" ይቀጥላል።

ይህን እግረመንገዴን ያነሳሁትን ጉዳይ እዚህ ላይ ቋጭቼ ወደ መነሻዪ ልመለስ። የፓሊስ ቋንቋ የህግ ቋንቋ ነው። የፓሊስ ኮሚሽነር ያህል ትልቅ የህግ ባለ ስልጣን "ፀጉረ ልውጥ" ሲል ለፍርድ ቤት/ለአቃቤ ህግ አሠራር በሚመች መንገድ ተርጉሞ ነው ብየ ማሰብን እመርጣለሁ፤ ተቃራኒው ስለሚያስፈራኝ። የህግ ትርጉም ሳይሰጡ እንዲህ ያለ አሻሚ ቃል መጠቀም ንፁሃን "መጤዎች" ተይዘው "ተወላጅ" ወንጀለንኞች ሊሸሸጉ ይችላሉ። ስሜትና ምራቅ ወደ ውስጥ ካልገባ ሰፈር ያበላሻል፤ ምክንያታዊነት፣ ሚዛናዊነትና ህጋዊነት ይንገስ።

Back to Front Page