Back to Front Page


Share This Article!
Share
አንድ ሆነን እንነሳ፣ ነገን እንገንባ

አንድ ሆነን እንነሳ፣ ነገን እንገንባ

ይቤ ከደጃች ውቤ 11-2-18

 

ረቡዕ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም 12 ሰዐት አካባቢ ቡና ለመጠጣትና አረፍ ለማለት ወደ አንድ ቤት ጎራ ብዬ ነበር። በወቅቱ ቤቱ በሰዎች ተሞልቶ በፀጥታና በርጋታ የቴሊቪዥን ሥርጭት እየተከታተሉ እንደሆነ ተረዳሁ፤ ለእኔ መዝናኛ ወይም እግር ኳስ አልያም ሌላ ትዕይንት ሊሆን ይችላል ብዬ ገምቼ ነበር።ወደ ጀርመን በሚደረገው ጉብኝት ዙሪያ ግንዛቤ ቢኖረኝም ሰዐቱን ማወቅ አልቻልኩም ፤ ግምቴ ግን ትክክል አልነበረም ከጀርመን ፍራንክፈርት በፋና ቴሌቪን በቀጥታ የሚተላለፈውን የኢትዮያውያንና ትውልደ ኢትዮያውያን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እየቀረቡ ያሉ ጥያቄዎችን እና በማጠቃለያም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጡ ምላሾችን የሚከታታተሉ ታዳሚዎች በብዛት ነበሩ። ይህም መንግሥት የዜጎቹን የልብ ትርታ ካዳመጠ ዜጎችም መንግሥት የሚሰጠውን ምላሽ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆናቸውን ማሳያ ይሆናል።

እንኳን በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎች በጀርመን ፍራንክፈርት የተሰበሰቡት ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያደርጉት ንግግር መሀል ደስታቸውን ለመግለፅ ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ፣ በጭብጨባ፣ በሆታና በፉጨት ሲገልፁ እንደነበር ታዝቤያለሁ።ይህም በስፖርት ሜዳ ውስጥ ተወዳዳሪዎች መሀል አንደኛው አካል ጎል ሲያገባ ደጋፊዎች የሚሰሙት የደስታና የርካታ ድምፅ ይመስል ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም።ተመልካቾችም ትዕይንቱ በጉጉት መከታተላቸው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

Videos From Around The World

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ በትረ ሥልጠናቸውን ከያዙ ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን የአውሮፓ ጉብኝታቸውን አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጉብኝታቸውን ያካሄዱት፤ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮንና የጀርመኗ መራሄ መንግሥት አንጌላ መርክል ባደረጉላቸው ጥሪ መሠረት ነበር። የመጀመሪያውን የአውሮፓ ጉብኝታቸውንም ባለፈው ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከተማ አካሂደዋል። በፓሪስ ከተማም ፤ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዩች ዙሪያ መክረዋል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በፓሪስ ኤልሴ ቤተ መንግሥት ተገናኝተው የሁለቱን ሀገሮች ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙርያ ተወያይተዋል።

ዶክተር ዐብይ አህመድ ውይቱን አስመልክቶ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ፈረንሳይ እንደ ትናንትናው ዛሬም ለታሪክ፣ ለቅርስና ለእምነት ያላቸውን ወዳጅነት እንዲያሳዩ እንደሆነ ጠቁመው በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት ለፕሬዚዳንቱ ጥያቄ አቅርበውላቸው መልካም ምላሽ እንደሰጧቸው አስታወቀዋል።የፈረንሳይ መንግሥት ለአብያተ ክርስቲያናቱ ጥገና የሚውል 300 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥና በባለሙያዎች ለማሰጠገን ቃል የገባ ሲሆን ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፕሬዚዳንቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ የዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ፈረንሳይ ተስማምታለች በዚህም እስከ 2ሺህ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከፕሬዚዳንቱ ጋር በሰላም፣ በዴሞክራሲና በልማት ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ውይይት እንዳደረጉና የሀገር መከላከያ ሠራዊትንም ለማዘመንና የሰው ኃይል ለማሰልጠን ከስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል። በምጣኔ ሀብት ረገድ በአየር መንገድ ሀገራቱ ያላቸውን ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ አውጥተው የአዲስ አበባ ኤርፖርትን ለማዘመን እንደሚሠሩም ማክሮን ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚው ማሻሻያ ከዓለም ባንክ ከምታገኘው የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ ፈረንሳይም የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነችም ነው ዶክተር አብይ ያወሱት። ፈረንሳይ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት በመሆኗ ከኢትዮጵያ ጋር በባህል፣ በእምነትና በቋንቋ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይም መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ዶክተር ዐብይ እያደረጉት ያለውን ማሻሻያዎችና የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አድንቀው ሀገራቸው ለዚሁ ማሻሻያ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ፈረንሳይ እንደምታደንቅ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ ሀገራቱ በቀጠናው ብልፅግናና ሰላም እንዲኖር ለሚደረገው ጥረት አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።ዶክተር ዐብይ የሚያደርጓቸው ማሻሻያዎች በቀላሉ የማይታዩና ብዙ ፈተና የገጠማቸው እንደሆነ፤ እንደሁም ማሻሻያዎቹን ለማድረግ ምን ያህል ከባድ እንደሆነም እረዳለሁ ሲሉ ፕሬዚዳንት ኢማኖኤል ማክሮን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብርታት የሚጠይቀውን ጎዳና መርጠዋል እኛም ከጎናቸው እንቆማለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊና የባህል ዘርፎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ እንዲመጣ ያሳዩት ቁርጠኝነትና ያደረጉት ማሻሻያ በሀገሪቷ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ዶክተር ዐብይ ከፈረንሳይ ጉብኝት ከሁለት ቀን በኋላም ማክሰኞ ጥቅምት 20 ቀን ወደ ጀርመን በርሊን በማምራትም ከጀርመን መራሂተ-መንግሥት አንጌላ መርከልና ከሌሎች የጀርመን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።በጉብኝቱም የጀርመን መራሄተ መንግሥት አንጌላ መርክል በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እንደሚደግፉ ጠቁመዋል፤ጀርመን በቀጥታ ይሁን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅት ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል መራሄተ መንግሥት አንጌላ መርክል ገልፀዋል። ፤

በጀርመን በተካሄደው የቡድን 20 ሀገራት ስብሰባም ኢትዮጵያም ተሳታፊ የነበረች እንደመሆኗ ኮምፓት አፍሪካ በሚል በአፍሪካ የልማት ፋይናንስ እንዲፈስና የአፍሪካ መሠረተ ልማት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።ኢትዮጵያን ጨምሮ ቤኒን፣ ኮትዲቯር፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ እና ቱኒዚያ የክንፉ ማለትም የቡድን ሃያ ኮምፓክት አፍሪካ የመጀመሪያ አባልነት መታወቂያ የተሰጣቸው ሃገራት ናቸው። የጀርመን መንግሥት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ፈንድ አቋቁሞ አፍሪካን ለመደገፍ የሚያስችል አዲስ አሠራር አውጇል፤ በዚህ አሠራር መሠረት ትኩረት ያገኘችው ኢትዮጵያ ስትሆን የጀርመን መካከለኛና አነስተኛ ኩባንያዎች ሀገራች መጥተው በስፋት ኢንቨስት ያደርጋሉ ።

በጀርመን በርሊን አቅንተው ካካሄዱት ጉብኝትና ከቡድን ሃያ ሀገሮች ጉባዔ በኋላም ፍራንክፈርት ውስጥ ከ20 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያ ዜጎች ጋር ተገናኝተው ታላቅ ውይይት አድርገዋል። አንድ ሆነን እንነሳ፣ ነገን እንገንባ በሚል መሪ ቃል ከዲያስፖራዎች ጋር የተካሄደው ውይይት ያማረና የሰመረ ነበር ማለት ይቻላል። በአውሮፓ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያካሄዱት ጉዞአቸው በስኬትና በውጤት ታጅቦ ጥቅምት 22 ቀን አዲስ አበባ ተመልሰዋል።

ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች የተወከሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በጀርመን ፍራንክፈርት ያደርጉት ውይይት፤ ዜጎች ስለ ሀገራቸው መፃዒ ዕጣ ፈንታ፣ ስለ መንግሥታቸው ዕቅድና ክንውን እንዲሁም አሁን በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለሚኖራቸው አስተዋፅዖ፤ ያላቸውን ጥያቄዎች፣ ፍላጎታቸውንና ራዕያቸውን አቅርበው ፊት ለፊት ሃሳብ በመለዋወጥና ጥያቄ በመጠየቅ ተካሂዷል። ዶክተር ዐብይ አህመድ ለሁሉም የአውሮፓ ቆንስላዎች አማካይ በሆነችውና በርካታ ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚገኙባት በፍራንክፈርት ከተማ፤ አንድ ሆነን እንነሳ፣ ነገን እንገንባ በሚል ቃል ከዳያስፖራው ጋር ያደርጉት ውይይት፤ በኢትዮጵያዊ አንድነት መንፈስ ነገን ብሩህ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ የታመነበት ነው።

በጀርመን ፍራንክፈርት ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የካሄደው ውይይት ዶክተር ዐብይ አህመድ ቀደም ሲል በአሜሪካ ከዳያስፖራው ጋር ግንቡን እናፍርስ፣ ድልድዩን እንገንባ በሚል መሪ ቃል ከኒውዮርክ እስከ ሚኒሶታ ባደረጉት ጉብኝት፤ በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ የሀገሩ የለውጥ ሂደት ባለቤት እንዲሆን እንዳደረጉትና ስኬታማ እንዳደረጉት ሁሉ፤ በፍራንክፈርት የተካሄደው ውይይትም

የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ

የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ ያስታውቃል

እንደሚባለው ሀገራቸውን ለሚናፍቁና ሙያዊ አስተዋፅዖ ማበርከት ለሚፈልጉ ዜጎች ብሩህ ተስፋን የፈጠረና፣ ደስታንና ርካታን የጫረ ነበር ።

ከአውሮፓ ግዙፍ ስቴዲዮሞች አንዱ በሆነው የፍራንክፈርቱ ኮሜርዝባንክ አሬና ረቡዕ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከሃያ ሺ የሚልቁ ኢትዮጵያውያን የሀገር ናፍቆት በሚኮረኩሩ የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎች ታጅቦና ተውቦ ዜጎች ከርዕሰ መንግሥታቸው ጋር ውይይት አድርገውበታል ፡፡ በናፍቆት ሲጠበቅ ከነበረው መርሃ ግብር በፊት የተለያዩ ሀይማኖት አባቶች ስለሀገራቸው አንድነት ጥሪ አቅርበዋል፤ ባርከዋል፤ መርቀዋልም፡፡ በስቴዲየሙ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያንም መድረኩን በግጥም በባህላዊ ዘፈኖች አጅበዋል፡፡

አንድ ሆነን እንነሳ፤ ነገን በጋራ እንገንባ በሚል መሪ ቃል የተካሄደው በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የፍራንክፈርት መድረክ መሪ ቃሉን በሚመጥን መልኩ አንድነትን ያረጋገጠና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርጎ ያሳየ ሆኖ አልፎአል፡፡ ከቆይታ በኋላ በከፍተኛ ድምቀት ወደ መድረኩ ብቅ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ ለዚህ እውነታ ምስክርነታቸውን በመስጠት ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡ ሰላምታቸውንም በተለያዩ የሀገራችን ቋንቋዎች ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ሆናችሁ አኩርታችሁኛል፤ አንድነታችሁ እንዳይወሰድ እፀልያለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል ከአውሮፓዊቷ ሀገር ያለፈ ፈተና ጋር እያነፃፀሩ ንግግራቸውን ያካሄዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በብዙ ተስፋና በጥቂት ፈተና መካከል የቆመች ታላቅ ሀገር ብትሆንም ፈተናዎችን በጥንካሬ ተሻግራ ነገንም በታላቅነቷ እንደምትዘልቅ አረጋግጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ የተጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ውጤታማ እንደሚሆኑና ኢትዮጵያም ተለውጣ ለዜጎቿ የምትመች ታላቅ ሀገር እንደምትሆን ያላቸውን እምነትና ተስፋ "አምናለሁ! ተስፋም አደርጋለሁ!" ሲሉ በተደጋጋሚ በጎላ ድምፅ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ካለችበት ሁኔታ እንደትወጣ ሁሉም የበኩሉን በጎ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበው፤ መንግሥታቸውም የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት ተግቶ እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል።ለዚህም በውጪ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዲገልፁ ጠይቀዋል። ጨምረውም ከዚህ በፊት በአሜሪካ እንዳደረጉት ኢትዮጵያዊያኑ በቀን አንድ ዶላር እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል።ከፊታችሁ ስቆም ሀገራችን በኢኮኖሚ በልጽጋ፣ ሰላማችን ሙሉ በሙሉ ተሟልቶ፣ ግጭት ጠፍቶ፣ ዴሞክራሲ ጎልብቶ፣ ሰብዓዊ መብት በላቀ ሁኔታ ተከብሮ ቢሆን ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግን አይደለም ብለዋል፡፡ እናም አሁንም ላይ ሁለት ነገሮች በኢትዮጵያውያን መዳፍ ላይ መኖሩን አስታውሰው፤ ነፃነትና ተስፋን ሰንቆ በትብብርና በአንድነት መስራት ከተቻለ እውን እንድትሆን የምትፈለገውን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሚያግድ ኃይል አይኖርም፡፡ ምክንያቱም አውሮፓውያን ከጦርነቱ ማግስት ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ከመገፋፋት ይልቅ ትብብርን የመረጡት ጥቅሙ ስለገባቸው ነው፡፡ ዘረኝነትን አምርረው የተዋጉትም ጥፋቱን ስለተረዱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ብዙ የለውጥ ጅማሮዎች በመሳሪያና በአመፅ ተጀምረው፣ በማሸነፍና በመሸነፍ፣ በማሳደድና በመሰደድ የተደመደሙ መሆናቸው ለሁሉም ግልጽ መሆኑን ዶክተር ዐቢይ ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ይላሉ፤ የሚመጡት ለውጦች አዲስ የሰላምና የእርቅ ምዕራፍ ከመሆን ይልቅ ሌላ የእጅ ዙር ውጊያና አመፅ መጀመሪያ ሲሆኑ ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን ያልሞከርነውን የምንሞክርበት አዲስ ዘመን ላይ ነን ያሉት ዶክተር ዐቢይ፤ ምቾትን በመተውና መከራን መታገስ ጥርስ ነክሶ ወደ ሥራ መግባት የግድ ይላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የውጪ ምንዛሪ ክምችትን አስመልክቶ በቀረበላቸው የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ከስድስት ወር ወዲህ በ334 በመቶ መጨመሩን ጠቁመዋል፤ ዲያስፖራዎች ወደ ሀገር ለሚልኩት ገንዘብ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ A/C 1000252736725 ሂሳብ መከፈቱ ይታወሳል፡፡ ከዲያስፖራዎች ጋር በተካሄደው ስብሰባ እንደተናገሩት ከዓለም ባንክ ሓላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይትም የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ገልፀዋል፡፡ ድጋፉ የዓለም ባንክ ላለፉት 15 ዓመታት ለሌሎች ሀገሮች ያልተደረገ ድጋፍ መሆኑን በፍራንክፈርት ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር ባደረጉት ንግግር የጠቆሙ ሲሆን የዓለም ባንክ ከዚህ ድጋፉ በተጨማሪ ከሦስት ወራት በኋላ ግማሽ ቢሊየን ብር ለመጨመር ቃል እንደገባ አስታወቀዋል፡፡

ባጠቃላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ያካሄደው ጉብኝት ዜጎች ለሀገራቸው አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ በር የከፈተ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ዲያስፖራዎችን ጨምሮ ከጀርመንና ከፈረንሳይ መንግሥት እንዲሁም ከቡድን ሃያ ሀገሮችና ከአፍሪካ ተሳታፊ ከነበሩ አመራሮች ጋር የተካሄዱ ውይይቶች የሀገራችንን ብሩህ ተስፋ የሚጭሩ ናቸው፡፡

 

 

Back to Front Page