Back to Front Page


Share This Article!
Share
ፍቅር ያሸንፋል አዎ ያሸንፋል ግን እንዴት

ፍቅር ያሸንፋል አዎ ያሸንፋል ግን እንዴት

ማህፍቅ ከብሄረ ኢ/ያ 06-28-18

 

ጠቅላይ ሚኒስተር ደ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለህዝቡ ከፍተኛ ተስፋ በመስጣት ላይ የሚገኙ ሲሆን ብዞዎቹን ተቃዋሚ የሚባሉት ሰዎች በመፍታት እንዲሁም ወንጀል የሰሩትንም በመፍታት የሁሉም ተቃዋሚ ወገን እና ለአብዛህኛው ህዝብ በሚመስል መልኩ መልካምነታቸውን ተቀባይነት አስገኝቶላቸዋል፡፡

ይህ መልካም ነገር እንዳለው ሁሉ የራሱ የሆነ መጥፎ ነገር አለው፡፡

መቸም በዚህ ግዜ ስለ ጠቅላይ ሚስተሩ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች መናገር በእውነቱ በርከት ያለ ሰው ባያስደስትም ህዝብ እንደ ማዕበል ነውና እውነታውን መፃፍ በተዘዋሪ ለሁሉም ጠቃሚ ስለሆነ አይሄው የተሰማኝን ልገልፅ ወድጃለሁ፡፡

እንደሚታወቀው ደ/ር አብይ አህመድ በተክለ ሰውነት መልከመልካም የሚባል ፈገግታው አስደሳች ንግግሩ ጣፋጭ የሆነ በወሳኝ ግዜ ወደ ኢትዮጵያ መሪነት የመጣ በትምህርቱም ራሱን እያሻሻለ አሁን ላለበት ደረጃ የደረሰ ለብዙዎቻችን አርአያ የሚሆን ግለሰብ ነው፡፡

ደ/ር አብይ ሀገሩን በወታደርነት ያገለገለ ፣ ወታደራዊ ዲስፒልን ታንፆ ያደገ እና በጦርነትም ተሳትፎ አድርጎ የተዋጋ እና ያዋጋ በሂደትም በአፈፃፀሙ ራሱን እያሳደገ ለዚህ የደረሰ ግለሰብ ነው፡፡

Videos From Around The World

አገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት 3 ዓመታት በተለይም በኦሮሚያ ክልል በውል ባልታወቀ ምክንያት ረብሻው ግጭቱ ተበራክቶ እንደነበር እሙን ነው፡፡

ያለፉት አመታት የግጭቶቹ ምክንያቶች ባይረጋገጥም በተለያዩ ሶሻል ሚድያ ይነሱ የነበሩ ነገሮች ለማስታወስ ያክል የታሰሩ የኦሮሞ ክልል ተወላጆች እና ፖለቲከኞች ይፈቱልን፣እኛ ሰርተን ባንለወጥበትም የሌላ ብሔር ተወላጅ በአከባቢያችን ሰርቶ ማደግ አይችልም በሚል ሰውን ማፈናቀል ብሎም ጉዳት ማድረሰ እንዲሁም ህወሓት ከመጥላት የተነሳ የትግራይ ሰውን መጥላት በአጠቃላይ የስልጣን ጥያቄ በሚመስል መልክ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የብሄሩ ተወላጆች የሚመራ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ተቃውሞ አድርገዋል ውድመት እስከትሏል፡፡ እንዲሁም በህዝቦች መካከል አልመተማመን ፈጥሯል፡፡የሚገርመው የተቃውሞው አስተባባሪ እና አስፈፃሚ ከሆኑት ቄሮ ተብሎ ከሚጠራው ባሻገር ኦፒዲኦ በሚሰጣቸው መግለጫ እና ሀሳቦች አንዱ እንደነበር መገመት አያዳግትም ነበር፡፡

የኢህአደግ ግንባርም ከፍተኛ ውይይት እና ግምገማ በማድረግ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ሃይለማርያም ከስልጣን በራሴ ፈቃድ ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርባለሁ ከለ በኋላ ከፍተኛ የሆነ የሶሻል ሚድያ ድጋፍ ለለማ ነገርሳ መንሸራሸር ጀመረ፡፡

በሂደት ግን አቶ ለማ ነገርሳ የፓርላማ አባል ባለመሆኑ መመረጥ እንደማይችል ሲረጋገጥ የነበረው ቲፎዞ ወድያው ተገልብጦ ደ/ር አብይ አህመድ ጋር ሆነ፡፡

ደ/ር አብይ አህመድ ስብዕናውን የሚገነቡለትን ነገሮች በቀጥታ ተሳተፎበት ይሁን ሳይሳተፍበት በሚድያዎች ቅብብል በዛ፣ በረከተ፤ ብሄርተኝነቱ መሰረት በማድረግ ቅስቀሳው ቀጠለ፡፡ከዛ በኋላ የኢህአደግ ውስጣቸውን ባናቅም ከፍተኛ ሽኩቻ እና አንድ መሆን ከብዳቸው የእነሱ ነፀብራቅ ህዝቡም ላይ ከፍተኛ ክፍፍል ፈጠረ፡፡

በወቅቱ ሲወራ የነበረው ብአደን እና ኦሄደድ አንድ እንደሆነ የነበረውን ጥላቻ ሊያጠፉ ፖለቲካዊ ስራ ተሰራ፣ ፕሬዝደንቶች ክልል ድረስ በመሄድ የአንድነት ጉባኤ አደረጉ ተስማማን ተብሎ ታወጀ፡፡

የደቡቡ ደግሞ ከህወሓት ጋር አንድ ነው የሚል ወሬ ይወራ ስለነበር የድርጅቱ ሊቀመንበር ምን እንደሚሆን ለመገመት አዳጋች አድርጎት ነበር፡፡

በዋናኝነት የደቡቡ ተወካይ እና የኦሮሞው ተወዳዳሪ ባደረጉት ፉክክር ሚዛኑ ደ/ር አብይ ጋር ሆነ እና ሊቀመንበር ሆነ ቀጥሎም የሀገሪቱ መሪ ሆኑ፡፡

ደ/ር አብይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሁነው ሲሾሙ ፓርላማ ላይ ያቀረቡት ልብ የሚነካ ንግግር በእውነቱ የህዘዝብን ልብ ለመያዝ ያደረጉት ጥበብ ስለነበር ወድያውን ተሳክቶላቸዋል፡፡

ደ/ሩ ፍቅርን እየሰበኩበት ያለው መንገድ በመሰረቱ ሁለት ስትራቴጂ መሰረት በማድረግ ነው፡፡

  ብዛት ያለው ህብረተሰብ የትግራይ ህዝብ ከስርዓቱ ልዩ ተጠቃሚ እየመሰለው ከፍተኛ ጥላቻ በፅንፎኞች፣በተቃውሚዎች ዘመቻ ስለተፈጠረ መተማመን አጥቷል፡፡

ይህን ማራገብ በአሁኑ ግዜ መልካም ተቀባይነትን ለማግኘት ያስችላል፡፡ስለዚህ ደ/ር አብይ በንግግራቸው ውስጥ ፍቅር ይሰብካሉ በተዘዋሪ ህወሓትን ይነቅፋሉ፣በተዘዋሪ ህዝቡ ለይ ያለው አመለካከት ኋላ ቀር በመሆኑ በጠቅላይ ሚኒሰተሩ የአሽሙር ንግግሮች ህዝቡ የትግራይን ህዝብን ጨምሮ ይጨፈልቃሉ፡፡

እንደሚታወቀው የሁሉም ፅንፈኞች እና ተቃውሚዎች ማጠንጠኛ ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ ስለሆነ ደ/ር አብይ በንግግራቸው ማህል ህወሓትን ሲዘልፉ ሰው ደግሞ ህዝብን ይዘልፋሉ፡፡

ስለዚህ ይህ ስትራቴጂ ከፍተኛ የተቀባይነት ለደ/ር አብይ አህመድ በንግግሩ ታውረው ለወደዱት ነገርን አገናዝበው እና መርምረው ውሳኔ ላይ በማይደርሱ ሰው ተቀባይነትን አስገኝቶላቸዋል፡፡

እዚህኛው የፍቅር ስትራቴጂ የይቅርታ ስትራቴጂም አለው፤ይቅር እንባባል በሚል ታላቅ እና ትልቅ ቃል ጠቅላይ ሚኒስተሩ በተገኙበት መድረክ ይናገራሉ ይሰብካሉ ነገረ ግን ትግራይ ህዝብ ላይ ያለው የሌላው አመለካከት ለመቀየር የሰሩት ስራ ብዙም አይደለም፡፡

  ህጎችን በመጣስ በይቅርታ ስም እሰረኞችን መፍታት ፣ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁትን ነፃ ማውጣት እና የትግራይ ተወላጆች በአብዛህኛው የሚመሯቸውን ድርጅቶች በኦሮሞ ተወላጅ መተካት ነው፡፡

ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ለፓርማ የመጀመሪያ ወቅታዊ ንግግር ሲያደርጉ ለፓርላማው እኛ ህግ አልጣስንም ከጣስንም ጠይቁን ስልጣኑ የእናተ ነው ብለዋል፡፡

ፓርላማው አሸባሪ ያለውን ድርጅት ፓርላማው አይ ከአሸባሪ መዝገብ ሰርዠዋለው ብሎ ህግ እስኪያወጣ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የእንደራሴውን ውሳኔ ማስፈፀም እንጂ መሆን የነበረበት ህግን በራሱ መጣስ አልነበረበትም፡፡

ግን ምን ማድረግ ይቻል ነበር ካለችሁኝ ፍቅር እና ይቅርታ ያሸንፋል ተብሎ መነሳት ጥሩ ሆኖ ውሳኔውን ግን ፓርላማ ተወያይቶበት ህጎቹን እንዳሻሻል በማድረግ ተፅዕኖ በመፍጠር ስራውን አላማውን ማስፈፀም ቢችል የህግ የበላይነትን ጎን ለጎን ማስክበር ይቻል ነበር፡፡

ሌላው በትግራይ ተወላጆች የሚመሩ ድርጅቶች ሙሉ ለሙሉ የማንሳት ስትራቴጂ መከተል ሌላኛው ስትራቴጂ ሲሆን በኦሮሞ ተወላጅ ሲተካ ለግዜው ከኦሮሞ ህዝብ በዘለለ ሌላው ሊያስደስተው ይችላል፡፡ግን ወደ ፊት የዚህ ብሄር ተወላጅ በተራው በሌላው ብሄር አሁን በተሳሳተ አረዳድ ትግራይ ላይ እየደረሰ እንዳለው ማግለል እና አድሎ ስራ ለእነሱም ይደርስባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ የስልጣኑም አሰራር ግንቡ አሁንም ቢሆን አልፈረሰም ፤ ነገር ግን ግንቡ ላይ የነበረው ቀለም ብቻ በኦሮሞ ብሄር ቀለም የመቀባት እና የመቀየር ስራ ነው ደ/ር አብይ አህመድ እየሰሩ ያሉት፡፡የእውነት በፍቅር የታወረ አይን ስለሚበድለው ሰውም ቢሆን በፍቅር አይን ነው የሚመለከተው፡፡

የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ቃላት ብዙውን ሰው በፍቅር አይናቸው ስለጋረደው እየሆነ ያለውን ነገር የሚያስከትለው ተፅዕኖ እና ውጤቱን በደንብ እየተገነዘብነው አይደለም፡፡

እንዲሁ ሳሰበው ደ/ር አብይ አህመድ የትግራይ ህዝብን እንደሚወዱ ለመረዳት ብዙ ችግር የለብንም፤ምክንያቱ በንግግራቸው ማህል ስለ ህዝቡ መልክም ነገር እና የትም ሀገር ሂደው መስራት ብቻ እንደሚፈልጉ በሚል በተደጋጋሚ በተለያየ ቦታ አንስተዋል፡፡

ይህ መልካም ነገር እያለ አሁንም የሌላው ብሄር ተወላጅ ህዝብ ጥላቸው ገና አለቀቀውም፡፡

ስለዚህ የፍቅር እና የይቅርታ ጉዞው በትግራይ ህዘብ ላይ በሌሎች ብሄሮች ያለው መጥፎ አመለካከት ፣ በአጠቃላይ የማያገናዘበው የህብረተሰቡ ክፍል ክልቡ መቀየር አለበት፡፡በዚህ ስለ ፍቅር እንቆማለን በዛ ደግሞ መልሰን ጥላቻችን አናሳያለን፡፡

እውነት አንድ አንድ ጊዜ ሰው ዝም ብሎ ነው እንዴ እሚነዳው ያስብላል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስተሩ ፍላጎት ወይም ንግግር የእውነት የፍቅር አመለካከት ከገባን ብሄር መሰረት አድርገን የምናደርገው የቂም የጥላቻ መንገድ እንደ ህዝብ ማቆም አለብን፡፡

የእውነት የደ/ር አብይ አህመድ ንግግር እና ድርጊት የየቅሉ በመሆናቸው ምክንያት አሁንም የጥላቻ መንፈሱ በየአከባቢው ገኗል፣ ጨምሯል፡፡

ለዚህ ምሳሌ በቅርቡ ከኦሮሞ የተፈናቀሉ አማራዎች ፣ ከአማራ እየተፈናቀሉ ያሉ የትግራይ ሰዎች ፣ በአዋሳ የተፈጠረው ግጭት እና በትግራይ ህዝብ ላይ ሌላው ማህበረሰብ ያለው መጥፎ አመለካከት ከጥላቻ አስተሳሰብ አመለካከት ለያልተቀየረ ህዝብ በፍቅር እና ይቅርታ በሚል ቃላት ልቡ ቢሰለብም የጠቅላይ ሚኒስተሩ ድርጊት ግን ንግግራቸው መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ አሁንም የኦሮሞን ብሄር በማግነን ላይ ስለሚገኙ ሰው ከተሸወደው ሳይኮለጂ በዘለለ ከፍተኛ የጥላቻ ስሜት በትግራይ ህዝብ እንዲሁም በአማራ ህዝብ ከኦሮሞ በኩል የደረሰው ጉዳት በጠቅላይ ሚኒስተሩ ድርጊት መሰረት ያደረገ እና በራሱ ኦሮሞ ከፍተኛ የጥላቻ ስሜት እየሰረፀብን እና እያደገባቸው ይገኛል፡፡

እውነት እንነጋገር ብንል የትግራይ ህዝብ ከማንም በላይ ለፍቅር የሚሞት እና የሞተም ህዝብ መሆኑን እየታወቀ ባህሎ እና ንሮው እመነቱም መሰረት አድርጎ የሚኖር መሆኑን እየታወቀ የጠቅላይ ሚኒስተሩ የፍቅር እና የይቅርታ ንግግሮች መደገፍ ከብዶት አይደለም ግን እውነታው በፍፁም ንግግሩ ወርቅ ነው ተግባሩ ግን ብሄር ተኮር በመሆኑ ነው፡፡

እንግዲህ እቺ አገር ታሪካዊው ዳራዋ ስንመለከት ሁሉም ነገር የተነሳው በትግራይ በኩል ነው፡፡

ሀይማኖት፡-

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ከሚገኙት ሃይማኖቶች ክርስትና እና እስልምን መነሻቸው ትግራይ ነው፡፡

ቋንቋ፡

የኢትዮጵያ ትልቁ ፊደል ቋንቋ መሰረት የሆነው ግዕዝ መነሻው ትግራይ ነው፡፡እውነት ኦሮሞ እና ሌሎች ቢሄሮች አንድነት ፣ ፍቅር ከልብ የገባችሁ ከሆነ የቋንቋችሁ ፊደል ከላትን ወደ ግዕዝ ይለወጥ ቢባል ትቀበላላችሁ ? አይመስለኝም ነገር ግን አንድነት የሚመጣው ከባዕድ ከወሰድናቸው ነገሮች በመውጣት ከሀገር በቀል ነገሮች ወደ ራሳችን በመውሰድ መጀመር ነው፡፡ደ/ር አብይም አህመድም ሌላው የአንድነት መሰረት ቋንቋ ነውና በትንሹም ቢሆን ፊደላችን አንድ ላመድረግ ሌላው ቤት ስራዎት እንዲሆን አበክሬ እጠይቃለሁ፡፡

ባህል፡-

ባህልም ብንመለከት በአብዛህኛው የኢትዮጵያ ሀገር እንደ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰዱ ባህላዊ ድርግቶች መለያዎች መነሻቸው ትግራይ ነው፡፡

ፖለቲካ፡-

ኢትዮጵያዊያን ስለ አስተዳደር በተደራጀ መልኩ መነሻ የሆነው ትግራይ ነው፡፡

ግዛት፡

የቀድሞ የአክሱም ነገስታት አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ይቅርና ከዛም በዘለለ ግዛታቸው በጣም ሲፊ እንደነበር ታሪክ ይናገራል ስለዚህ አሁን ላለችው ኢ/ያ ያለፉት መንግስታት ሸራርፈው እዚህ አደረሷት እንጂ ሰፊወን ግዛት የመሰረቱት አሁንም ከትግራይ የወጡ የሀገሪቱ ነገስታት ናቸው፡፡

ሙዝቃ፡-

የኢትዮጵያ ቅኝቶች ተብለው የሚዘፈኑ የሚዘመሩ በአጠቃላይ ለዘፈን ሆነ መዙሙር መነሻ እና መሰረት የሆነችው ትግራይ ናት ያውም ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ነው፡፡

ኢኮኖሚው፡

ኢኮኖሚውም ቢሆን አብዛህኛው ህብረተሰብ በአንድ አከባቢ ተወስኖ ባልኖረበት ዘመን የትግራይ ቀደምት ሰዎች ግን አንድ አከባቢ ሰፍረው ግብርና በማካሄድ እንዲሁም ንግድን አለማቀፋዊ በማድረግ ለሀገሪቱ ህዝብ መሰረት ሁነዋል፡፡

ዲፕሎማሲው፡

ቀደምት የአክሱም መንግስታት ጠንካራ እና የሰለጠኑ ስለነበር ከራሳቸው አልፈው ጠንካራ ከሚባሉት የአለም መንግስታት የዲፕሎማሲ ግኝኑነት ነበራቸው ፤ ስለዚህ በዚህም ረገድ ትግራይ ናት መሰረቷ፡፡

በአጠቃላይ አሁን ላለው ኢትዮጵያ በፖለቲካው ፣በኢኮኖሚው እና በማህበረሰባዊ ሁለተናዊ ሁኔታ ዕድገት መሰረት የሆነው ትግራይ ናት ፣የትግራይ ህዝብ ነው፡፡

እውነታው ይህ ሁኖ እያለ ሰዉ ግን ለትግራይ ህዝብ ያለው የወረደ አመለካከት በጣም ያሳዝናል፡፡አሁን ብዙ ሰው ለትግራይ ህዝብ እየነከሰው ይገኛል፡፡የትግራይ ህዝብ ለሌላው ቀሪ ህዝብ ባጎረሰው እየተነከሰ ይገኛል፡፡

ስለዚህ አገሪቱ ብትፈርስ የትግራይ ህዘብ መጀመሪያውንም ኢትዮጵያን ፈጥሯታል አሁንም ቢሆን ታሪኩ ፣ባህሉ፣ሃይማኖቱ እዛው ትግራይ ላይ ስለሚቀር ምንም የሚያደግተው የሚከብደው ፈተና የለም፡፡ግን ይህ አይጠቅምም አሙን ነው ለምን ካልን ህዝብ ለህዝቡ ተዋልዷል ፣ ህዝብ ለህዝብ ከብዷል፡፡በአጠቃላይ ያለ ትግራይ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችምም አትኖርምም፡፡

እናም ደ/ር አብይ አህመድ ስርዓት መቀየር ከፈለጉ ምንም ችግር የለም፤ ህዝብን ያነጋግሩ ፣ ህዝቡ ይወሰን በዛ መሰረት የተሻለ ብለው የሚያሙኑበትን ስርዓት ይመስርቱ፡፡

ነገር ግን ደ/ር አብይ አህመድ

  ንግግሮ ፍቅር ድርጊቶ ብሄር ተኮር እየሆነ ነው እና ለዚህ መገለጫ በሙሉ አመራሩን የኦሮሞ ተወላጆች እያስያዙት በመሆኑ፣

  በፍቅር ስብከቶ ውስጥ ሰው ስለ ትግራይ ያለው አመለካከት በጥላቻ የተሞላ በመሆኑ የሰሩት ስራ ቀርቶ ከፍቅር አንፃር ከሀገር መሪ አንፃር አናሳ በመሆኑ፣

  ህዝቡም በተለይም ኦሮሞ ፍቅር ገብቶት ሳይሆን ስልጣን በቢሄር ተወላጅ ስለተያዘ የሚሰጠው ድጋፍ ህዝቡ ላይ ያለው ሀገራዊ አመለካከት እና ስሜት በሰፊው ያልተሰራ በመሆኑ፣

  በይቅርታ ሰበብ ህጎች ስራ ላይ እየዋሉ ባለመሆኑ (ይቀርታ አይሰጥ ማለቴ አይደለም ግን ህግን እያስቀደምን መሰረቱ ህግ እያደረግን በፍቅር ይቅርታ ቢሰጥ መልካም ነው)

በከፍተኛ ትኩረት እና ጥንቃቄ ንግግሮዎን እና አረማሞደን እንደገና ሊመለከቱት ይገባል፡፡

በግሌ ደ/ር አብይ አህመድ እዚህ ደረጃ ለመድረስ የሄዱበት መንገድ ፣ በትምህርት ራሳቸውን ያሻሻሉበት ሂደት ለብዙ ሰው አርዓየ የሚሆን ተግባር ነው፡፡

ግን ደ/ር አብይ አህመድ ተዋግተው ሰውን የመግደል ወኔ የነበራቸውም ሰው እንደነበር መረዳቱም ጥሩ እና አስፈላጊ ነው ፣ እንደው ፍፁም አድርገን መውሰዱ ገና አሁን ግዜው አይደለም፡፡

ደ/ር አብይ አህመድ የመደመር ሃሳባቸውም ቢሆን ያን ያክል ህዝብን የሚወክል አይደለም ፡፡ ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ከመደመር በላይ ተባዝተን ተዋልደን እየኖርን ያለን ሰዎች በመሆኑ ነው፡፡መደመር በባህሪው አያዋህድም፣መደመር በባህሪው የተከፋፈለን ነገር እንደለ መሰረቱ ሳይለወጥ ቁጥርን ብቻ ማሳደግ ነው፡፡ለምሳሌ ኦሮሞ እና አማራ ቢደመሩ የሚለወጥ የሚቀየር ነገር የለም በቃ ሁለት ብሄር የሚል የድምር ውጤት ይሰጠናል፡፡ግን አማራ እና ኦሮሞ ቢባዙ ከማህላቸው የሁለቱም ውህደት ውጤት ነው የሚመጣው ፡፡በሌላ አነጋገር አንድ አማራ ሰው + አንድ ኦሮሞ ሰው = 1አማራ እና 1ኦሮሞ በሌላ መልኩ አንድ አማራ እና አንድ ኦሮሞ ቢባዙ ግን ልጅ ይፈጥራሉ፡፡ስለዚህ ብዚት ምንግዜም ቁጥሩ ሲበዛ ውጤቱም ውህደቱም ይበዛል፡፡እርግጥ ነው ደ/ር አብይ ራሳቸው የመደመር ውጤት ሳይሆነ የብዚት ውጤት ናቸው፡፡ስለዚህ እኛ ከመደመርም በላይ ነን፡፡

በመጨረሻም ደ/ር አብይ አህመድ ከቅርብ ያለውን የሀገሩ ህዝብ ማለትም የትግራይ ህዝብን ያለከበረ ፍቅር የትግራይ ህዝብን ያላጠቃለለ ይቅርታ ዘሎ ኤርትራ ጋር ምንም ትርጉም የለውም፡፡

ኦሮሞ ከአመፅ የተረጋጋው የደ/ር አብይ አህመድ የፍቅር ስብከት ተረድቶት ሳይሆን በጠባብ ብሄርተኝነት ተውጦ ከእሱ ክልል የተወለደ ሰው ስልጣን በመያዙ ነው፡፡

መገለጫው አሁንም ለትግራይ ህዝብ ያላቸው ጥላቻ ፣ለአማራ ህዝብ ያላቸው ጥላቻ፣ አሁንም ቀጥሏለወ፤ በተለይም የአማራን ህዝብ አሁንም እያፈናቀሉ ይገኛሉ፡፡

እኔ ትልልቁ ኦሮሞ ዘመንን ያዩ ኦሮሞ ምናልባች ኢትዮጵያውነት ስሜት ይኖራቸዋል ብየ አስባለው ሌላው ግን እውነት ለአፍ ኢትዮጵያ ሊሉ ይችላሉ እንጂ ልባቸው ሌላ ነው፡፡ይህ አመለካከታቸው በራሳቸው ይዘውት ተወለደ አይደለም ፤ ፅንፈኞች ህዝቡ ላይ የተከሉት መጥፎ ጠባሳ ነው፡፡ስለዚህ ጠቅላየ ሚኒስተሩ ይህንን ጠባሳ ሊለውጡት ይገባል፡፡

በመሆኑም ፍቅር ያሸንፋል አዎ ልክ ነው ፤ ነግር ግን በፍቅር የተዋበ እሾው ህዝቡ ላይ እየተዘራ ስለሆነ ወደፊት ሀገራችን አንድ ምትሆንበት ዘመን ሳይሆን ይበልጥ የምትፈርሰበት ጊዜ ሊያመጣ ስለሚችል ደ/ር አረማመዶዎን እና አነጋገርዎን እንደገና ቢያዩት እና ቢገመግሙት ብሎም ቢያስተካክሉት እመክራለሁ፡፡

በመጨረሻም ደ/ር የእውነት ብሄርን መሰረት ያደረገ የመንግስተ መዋቅር አይገንቡ፡፡

 

 

Back to Front Page