Back to Front Page


Share This Article!
Share
የሚዲያው ትኩረትና የዘንድሮው የመኽር ወቅት

የሚዲያው ትኩረትና የዘንድሮው የመኽር ወቅት

                                     እቴጌ ዳጊ 08-03-18

ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ባለው ፈጣን እድገት ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የግብርናው ዘርፍ የሚጫወተው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ ግብርናው የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ኋላቀር አሠራሮቹን በማዘመን ምርታማነትን ማሳደግ ግድ ይለዋል፡፡ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችውን ግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በማሸጋገር በአገራችን እየተገነቡ ላሉት ኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ግብዓቶችን የማቅረብ አቅም ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ሰሞኑን የ2011 ዓ.ም በጀት ዓመትን ባጸደቁበት ወቅት እንደተናገሩት ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ መሬቶቻችንን በማረስ የምግብ ዋስትናችንን ከማረጋገጥ በዘለለ ለገበያ የሚተርፍ በቂ ምርት ለማምረት ግብርና ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አበክረው ተናግረዋል፡፡ በይበልጥም በአፋርና ሶማሌ ክልልሎች የተንጣለሉትን ሰፋፊ መሬቶች ከመኽር የዝናብ ወቅት በተጨማሪ በመስኖ በማልማት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ዜጎቻችን እንደ ከዚህ ቀደሙ የውሐ፣ የመብራትና የመንገድ  መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ አልሆንም የሚሉ ጥያቄዎችን  ከማንሳት ይልቅ በአካባቢያችን  ባሉ ወንዞች የመስኖ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ይኖርባቸዋል በማለት የግብርናው ዘርፍ ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

Videos From Around The World

ያለንበት ወራት  የክረምት ወቅት ነው፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ አብዛኛው የሀገራችን ክፍል ዝናብ የሚያገኝበት ነው፡፡ ገበሬው የመኽሩ ምርት ያማረ ፍሬ እንዲኖረው ላቡን ጠብ አድርጎ የሚሰራበት የእርሻ፣ የዘር፣ ጉልጓሎ፣ የአረም ወቅቱ አሁን ነው፡፡ ልክ እንደ ገበሬው ሁሉ መንግሥትም የክረምቱ ወራት ከመግባቱ በፊት ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳሉ ያላቸውን ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና አረም ማጥፊያ የመሳሰሉ ግብዓቶችን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ የግብርና ባለሙያዎችም እንዲሁ ገበሬው ዘመናዊ የአስተራረስና የአዘራር ዘዴዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግ እስር አስር በማለት ሙያዊ እገዛ የሚሰጡበት ወቅት ነው፡፡

 

የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ በ2010/11 ምርት ዘመን በመኸር እርሻ ከ375 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ከ14 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ለመሸፈን ዕቅድ ተይዟል። የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሀኑ በምርት ዘመኑ በሰብል ይሸፈናል ተብሎ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ ከ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል መሸፈኑን ጠቁመዋል።

ለምርት ዘመኑ የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት እንዲገዛ ከታቀደው ከ1 ነጥብ 39 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ውስጥ 1 ነጥብ 35 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የተገዛ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።

በማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ላይ በተደረገው ክትትል እስከ አሁን በአጠቃላይ 868 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መድረሱን አቶ አለማየሁ  ተናግረዋል፡፡ ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር ተያይዞ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አርሶ አደሩ አልደረሰንም የሚል ጥያቄ እንደሚያነሳ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ "የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ምንም ችግር የለም" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ከስርጭት ጋር ተያይዞ ችግር ሊኖር እንደሚችል ተናግረው ይህንንም ከክልሎች ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ አጠንክረው እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በተመለከተ በምርት ዘመኑ ለማቅረብ ከተዘጋጀ 1 ነጥብ 58 ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ ከ 757 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ መቅረቡን ጠቁመዋል።

በመኸር ወቅት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በቆሎና በማሽላ ሰብል ከተሸፈነው 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ከ488 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች ለመከላከል መሰራቱን ተናግረዋል። በተሰራው ሥራ ከ386 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ በኬሚካልና በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል። በዚህም ከ92 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተውን በአርሶ አደሮች መከላከል ስራ መሰራቱን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።

የግብርናው ዘርፍ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ግን አሁንም እየተሰጠው ያለው ትኩረት በቂ ነው ማለት አይቻልም ፡፡ በተለይ ገበሬው ግብርናውን ለማዘመን እንዲረዳው መንግስት የሚነድፋቸውን አዳዲስ አሠራሮች ከማስተዋወቅ፣ ከማንቃትና ወቅታዊ የዝናብና የአየር ጸባይ መረጃዎችን ለገበሬው ከማድረስ አጻር ሚዲያዎቻችን የዘንድሮውን የመኽር ወቅት አስመልክቶ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነበር ለማለት ያስቸግራል፡፡

እንደሚታወቀው በሰሞኑ ዋና መነጋገሪያ የሆነው የፖለቲካው ሁኔታ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ሚዲያዎችም የእለት ተእለት ርዕሶቻቸው የሚያነጣጥሩት በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በኢትዮ- ኤርትራ ስምምነት ፣ በግጭቶች እና በሚፈፀሙ የግድያ ወንጀሎች ላይ ነው፡፡ በዚህም የመኽር ወቅቱና የግብርናው ጉዳይ ትኩረት ሳያገኙ መቅረታቸውን ለመታዘብ ችለናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከፍተኛ ምርትን ማስገኘት ይችላሉ የተባሉ አዳዲስ የምርምር ውጤቶችን የማስተዋወቁ ሥራ እንኳን እምብዛም ሽፋን ሳይሰጠው ቀርቷል፡፡  

መረሳት የሌለበት አብይ ጉዳይ ለውጡ ያስፈለገበት ምክንያት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር በማለምና የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትራችንም ራዕይ ይህን መሰረት ያደረገ ሆኖ በይበልጥም ግብርና ላይ ጠንክሮ በመሥራት የሀገሪቱን እድገት ማረጋገጥና  ገጽታዋንም  በመገንባትን ያለመ ነው፡፡

ሚዲያዎቻችን ከሰሞኑ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅመው  አይነኬ የነበሩ የፖለቲካ ጉዳዮችንንና ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ የመብት ጥሰቶችን አስመልክተው ብዙ ነገር እያሉን ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ይህ አቀራረባቸው ዲሞክራሲን ከማስፈን አንጻር ትልቅ ዋጋ እንዳለው ይታመናል ፡፡ ለዚህም አድናቆት መስጠት ያስፈልጋል፡፡  ነገር ግን ትኩረታቸውን በፖለቲካው ላይ ብቻ ማድረጋቸው ሌሎች ልማታዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ሊያስረሳቸው ስለሚችል መረሀ-ግብራቸውን ሚዛናዊ በማድረግ ሁሉንም ጉዳይ ጠቃሚነቱን እያስተዋሉ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

ይህ የመኸር ወቅትም አንድ ትልቅ ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳይ በመሆኑና በይበልጥም የመጪውን ዓመት የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥና ካለማረጋገጥ አንጻር ወሳኝ አጀንዳ መሆኑ ከግምት ገብቶ ገበሬው የሚፈልገውን መረጃ እንዲያገኝ ማድረግ  መንግሥትም አስፈላጊ ግብኣቶችን እንዲያሟላና ባለሙያውም ድጋፉን እንዲሰጥ የተለያዩ አካባቢዎችን እየቃኙ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት መፍትሔና ውጤቶችን ማሳየት ሚዲያዎቻችን ትኩረት ሊሰጡት ከሚገባ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡         

 

 

Back to Front Page