Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጥላቻ የዘለቀው ህዝብ ሃገር አይገነባም

ጥላቻ የዘለቀው ህዝብ ሃገር አይገነባም

ኢብሳ ነመራ 06-24-18

አሁን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ ነች። ይህ የለውጥ ሂደት በተለይ ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ በኦሮሚያና በሌሎችም የሃገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ህዝባዊ የተቃውሞ ንቅናቄዎች ውጤት ነው። ህዝባዊ የተቃውሞ ንቅናቄዎቹን የፈጠረው በመንግስት ውስጥ የነበረ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግር ነው። በሃገሪቱ ሁሉም የመንግስት መዋቅር እርከኖች የመልካም አስተዳደር ችግር፣ አስከፊ መሆን የሚችለውን ያህል ከፍቶ ቆይቷል። በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ተገቢ አገልግሎት አግኝቶ ጉዳይ ማስፈጸም የዘውትር ጉዳይ ሳይሆን ጥቂት እድለኞች የሚያገኙት የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ዜጎች አገልግሎት ፍለጋ ወደመንግስት ተቋማት ሲሄዱ በስጋትና በመሳቀቅ ነው። በተለይ ማዘጋጃ ቤት፣ ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት፣ የወረዳ አስተዳደርና የቀበሌ ጽህፈት ቤቶች፣ የመሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ወዘተ የጊቢያቸው ድባብ የሚከብድ፣ ከጥበቃ ጀምሮ ያሉት ሰራተኞችና ሃላፊዎች ድምጽ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል።

የፍትህ ስርአቱ ህዝቡ በሃገሪቱ ፍትህ ላገኝ አልችልም ብሎ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረገ ነበር። ፍርድ ቤቶች የሚፈርዱት በፍትህ ሚዛን ሳይሆን በገንዘብ ሚዛን ሆኖ ቆይቷል። ያለው ይፈረድለታል፤ የሌለው ደግሞ ይፈረድበታል። ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች የነበሩ ግለሰቦች የተከሰሱባቸው የሙስና ጉዳዮች ጭምር እልባት ሳያገኙ ዓመታትን ያስቆጥራሉ። ተከሳሾቹ ወይ ተፈርዶባቸው ታራሚዎች አይባሉም፣ ወይ በዋስ ተለቀቀው እንዲሟገቱ አይወሰንም፣ ወይ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ነጻ ተብለው አይለቀቁም። እንዲሁ ጉዳያቸው እልባት ሳያገኝ እየተንከባለለ፤ አንዱ ሲወሰን ሌላው እየተንጠለጠለ ዓመታት ይንገላታሉ። በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንደተመሰረተ ጉዳዩ ቀልብ ሳቢ ሆኖ፣ ያገኝ የነበረው የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን የዜና ሽፋን ቀርቶ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ህዝብ ጉዳዩን የሚረሳበት ሁኔታ የተለመደ ነው። ይህ የፍትህ መዛባት ውጤት ነው። የዘገየ ፍትህ እንደተከለከለ ይቆጠራል።

በሌላ በኩል የመንግስትና የህዝብ ሃብት ዘረፋ በአዋጅ የተፈቀደ የሚመስልበት ሁኔታ ታይቷል። ከአነስተኛና መካከለኛ የመስኖና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች፣ ሆስፒታሎች ግንባታ ጀምሮ በቢሊየን የሚለካ ሃብት እስከተመደበላቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ያሉ የልማት ስራዎች ይጀመራሉ እንጂ አይጠናቀቁም። አብዛኞቹ የልማት ፕሮጀክቶች የተመደበላቸውን በጀት ጨርሰው በግማሽ እንኳን የማይጠናቀቁበት ሁኔታ የተለመደ ነው። ገንዘባቸው አልቆ በጅምር የሚቀሩትም በርካቶች ናቸው። የብቃትና የአቅም እጥረት የዚህ ችግር አንዱ ምክንያት ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ግን ዘረፋ ነው።

አርሶ አደሩ በከተሞች መስፋፋትና በልማት ሰበብ መሬቱን ሲቀማ ዘላቂ ህይወቱን ታሳቢ ያደረገ ካሳ አይከፈለውም። በከተሞች ዙሪያ የነበሩ አርሶ አደሮች በካሬ ሜትር በሳንቲሞች ቢበዛ 3 ብር ካሳ ተከፍሏቸው ነበር መሬታቸው የሚወሰደው። ይህ አንድ አባወራን ከአንድና ከሁለት ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ ብቻ መኖር የሚያስችል ካሳ አርሶ አደሩን ለልመና የዳረገበት ሁኔታ ታይቷል። በሌባ በኩል የቀበሌና የማዘጋጃ ቤት ሹመኞችና ደላሎች የአርሶ አደሩን መሬት በመቸብቸብና ለዘመዶቻቸው በመሸለም የማይገባቸውን ከፍተኛ ጥቅም አግኝተዋል። በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ዞን አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ መመልከት ለዚህ በቂ አስረጂ ነው። ጥቂቶች በመንግስትና በህዝብ ሃብት ዘረፋ ሚሊየነር ባለሃብት ሲሆኑ በርካቶች ሃብታቸውን አጥተው በስራ አጥነት ለአስከፊ ድህነት ተዳርገዋል። ይህ ፍትሃዊ ያልሆነ ሃገራዊ ሀብት ክፍፍል ህዝቡን አስቀይሞታል፤ አስቆጥቶታልም።

Videos From Around The World

ወደፖለቲካው ስንመጣ፤ ሃገሪቱ የተለያዩ አመለካከት አራማጅ ፖለቲከኞች/የፖለቲካ ፓርቲዎች ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱባት ብትሆንም፣ በፌደራልና በክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የህዝብ ውክልና አግኝቶ የሚንቀሳቀሰው ግን የአራት ብሄራዊ ድጅቶች ግንባር የሆነው ኢህአዴግና አጋሮቹ ብቻ ናቸው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶቹ የሃገሪቱን የፖለቲካ አመለካካት ብዝሃነት የሚያንጸባርቁ አይደሉም። ይህ አነሰም በዛም ደጋፊዎች ያላቸው አመለካከቶች በምክር ቤት ውስጥ የሚደመጡበትን እድል የነፈገ ሁኔታ በፖለቲካ ምህዳር ጥበት ተገልጿል። ሁኔታው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ህገወጥ አካሄዶችን እንዲከተሉ አስገድዷል። በሌላ በኩል መንግስት ከተቃውሞ ሰልፍ ጀምሮ በተለያየ መንገድ የተገለጹ ህገወጥ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተሳታፊዎችን፣ መሪዎችንና እነዚህ እንቅስቃሴዎች ላይ አተኩረው የሚሰሩ ጋዜጠኞችን የሚያስርበትን ሁኔታ አስከትሏል።

እነዚህ ከላይ የተገለጹ ችግሮች በሃገሪቱ የሰፈነውን ይብሄሮች ነጻነትና እኩልነት፣ የተመዘገበውን ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት፣ ማህበራዊ ልማት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ፍሰት እድገትና ከዚህ የተገኙ ጥቅሞችን ደፍቀው ጎለተው በመውጣት የሃገሪቱ መገለጫዎች ለመሆን በቅተዋል። እነዚህን ስኬቶችን ደፍቀው የወጡ ችግሮች በጽሁፉ መግቢያ ላይ የተጠቀሰውን ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴን አነሳስተዋል።

የተቃውሞ እንቅስቃሴዎቹ በተለይ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የታችኞቹ የመንግስት መዋቅሮች እንዳይሰሩ እስከማድረግ የደረሱ ሃያል ነበሩ። ይህ ሁኔታ መንግስትና በፍጹም ብቸኝነት የሃገሪቱን ስልጣን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ ራሱን ፈትሾ ከማስተካከል ውጭ አማራጭ እንዳይኖረው ያደረገ አጣብቂኝ ውስጥ ከተተው። ይህ በጥልቀት መታደስ በተሰኘ ዘመቻ መሰል እንቅስቃሴ የተካሄደ ራስን ፈትሾ የማስተካከል ርምጃ በግንባሩ ውስጥ ተራማጅ አመለካካት የነበራቸውን ግለሰቦችን የያዘ የአመራር ቡድን ወደሃላፊነት እንዲመጣ አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጨምሮ አሁን በስልጣን ላይ ያለው አመራር ይህ ኢህአዴግ ውስጥ የነበረ ተራማጅ ቡድን ነው።

ይህ በግንባሩ ውስጥ የነበረ ተዳማጅ አመለካካት ያለው የአመራር ቡድን በድርጅቱ የመታደስ ርምጃ ወደስልጣን የመጣ ቢሆንም፣ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን የሃገሪቱን አስተዳደራዊ፣ የፍትህና ፖለቲካዊ ችግሮች ለማስተካከል የወሰደው ርምጃ በህዝቡ ውስጥ በሃገሪቱ አብዮት የተካሄደ ያህል ትልቅ መነቃቃትና ተስፋ ፈጠረ። ይህ በህዝብ ውስጥ የተፈጠረ መነቃቃትና ተስፋ ተመልሶ ለአዲሱ ተራማጅ አመራር ጉልበት ሰጠው። በዚህ ሁኔታ ተራማጅ አመራሩ ሃገራዊ መግባባት መፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የሚያስችሉ ታራሚዎችን በይቅርታ በነጻ የመልቀቅና የእርቅ ርምጃዎች ወሰደ። ይህ ሁኔታ በውጭ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ተቃዋሚዎችን ወደሰላም እንዲመጡ አነሳሳ። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተሰኘው በአንጋፋ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚመራው ቡድን ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ለመሆን ወደሃገር ቤት መመለሱን ልብ ይሏል። ግንቦት 7 የተባለው ቡድን ማንኛውንም የአመጽ እንቅስቃሴ ለማቆም ወስኗል፤ ለጊዜውም ቢሆን።

አዲሱ ተራማጅ አመራር ከአጎራባችና ከመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት ጋር ያደሳቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች፣ ጉልበቱን እየጨረሰ ለመቆም የተቃረበውን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠልና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ላማቃለል ያቀረባቸው የኢኮኖሚ እርምጃ አማራጭ ሃሳቦች፣ ዘረፋን ለመከላከል ያሳየው ቁርጠኛ አቋም፣ እንዲሁም ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ጦርነትም ሰላምም ያልሆነ ሁኔታ (ሞት አልባ ጦርነት) ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ለማስቀረት ያቀረበው ሃሳብ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።

እነዚህ ከላይ የተገለጹ ተራማጅ አመራሩ የወሰዳቸው ርምጃዎች ወደአስከፊ ደረጃ እየተሸጋገረ የነበረውን የሃገሪቱን የሰላም ሁኔታ ማረጋጋት አስችሏል። ህዝብ በቀጣይ ችግሮቹ አቅምና ሁኔታዎች በፈቀዱት ልክ ይስተካከላሉ የሚል ተስፋ እንዲያድርበት አድርገዋል። እነዚህ ሁኔታዎች መልካምና በህዝብ የተወደዱ ቢሆኑም፣ ያስከፋቸው አካላት ግን አሉ። የተራማጅ አመራሩ ርምጃዎችና በህዝቡ ላይ የተፈጠረው ተሰፋና መነቃቃት ያስፈራቸው አካላት፣ ተበላሽቶ በነበረው የኢህአዴግና የመንግስት አመራር ውስጥ የፖለቲካና ተያያዥ ስልጣንን ተሞርኩዘው ከጥገኞች ጋር በመመሳጠር የህዝብና የመንግስት ሃብት ሲዘርፉ የነበሩ ቀማኞችና ግብረ-አበሮቻቸው ናቸው።

እነዚህ አካላት በተራማጁ አመራር ርምጃ ጥቅማቸውን አጥተዋል። ጥቅም ከማጣት ባሻገር በህግ ከመጠየቅ ጋር ተጋፍጠዋል። እናም ይህን ሁኔታ ለመቀየር ቀደም ሲል የዘረጉትን የዘረፋ የትስስር መረብ ተጠቅመው የተራማጅ አመራሩን እርምጃዎች ለማደናቀፍ እየሰሩ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሮሚያ ጭናክሰን፣ በጉጂና ደቡብ ጌዴዮ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በደቡብ ወልቂጤ፣ በሃዋሳና ወላይታ ተልካሻ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ የተቀሰቀሱ ደም አፋሳሽ ግኝቶች ተራማጁን አመራር ለማደናቀፍ ከተደረጉ ሙከራዎች መሃከል ተጠቃሾች ናቸው። ቅዳሜ ሰኔ 16፣ በአዲስ አበባ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና አብረዋቸው ለሚሰሩት የተራማጅ አመራር አባላት ቡድን የእስከዛሬ ተስፋ ሰጪ ርምጃ እውቅና ለመስጠትና ለማመስገን በመስቀል አደባባይ በተጠራው ህዝባዊ ትዕይንት ላይ የተወሰደው የቦምብ ጥቃትም የዚሁ ተራማጁን አመራር የማደናቀፍ ሙከራ አካል ነው። በመስቀል አደባባይ የተፈጸመው የቦብም ጥቃት መድረሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና በአጠቃላይ ተራማጅ አመራሩ ላይ ጉዳት በማደረስ የህዝብ ለህዝብ ግጭት መፍጠር ነው።

የእርስ በርስ ግጭቶች ሃገራዊ አንድነትንና ብሄራዊ መግባባትን ያላላሉ። የሃገራዊ አንድንትና መግባበት መላላት ተራማጁ አመራር ለህዝቡ አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት አቅሙን በማዳከም፣ በሂደት አሁን በህዝብ ያገኘውን አመኔታ የመሸርሸር አቅም አላቸው። ይህ ሰነባብቶ፤ ከራርሞ ለተቃውሞ ያጋልጠዋል። ጥቅማቸው የቀረባቸውና በህግ ለመጠየቅ ስጋት የተጋለጡት ዘራፊዎች ቀድመው የዘረጉትን መረብ ተጠቅመው ሁከትና ግጭት ለመቀሰቀስ በመራወጥ ላይ የሚገኙት ለዚህ ነው።

እነዚህ አካላት የእርስ በርስ ግጭት ለመለኮስና ለማቀጣጣል፣ ህዝቦች በጥርጣሬ እንዲተያዩና ለጥቃት እንዲከጃጀሉ ለማደረግ የጥላቻ መርዝ ነው የሚነዙት። የጥላቻ መርዝ የዘለቀው ህዝብ አቀጣጣይ አጋጣሚ ሲያገኝ ግጭት ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው። ግጭቶች ደግሞ ሃገራዊ አንድነትንና መግባባትን በማጥፋት ተራማጅ አመራሩን ሊያስናክሉ ይችላሉ።

ጥላቻ የገባው ህዝብ ጥንጣን እንደበላው የበሰበሰ እንጨት ነው። ጥንጣን በልቶት የበሰበሰ እንጨት የሚጸና ቤት አይሰራም። ጥላቻ የዘለቀውም ህዝብ ጠንካራ አንድነት ያላት ሃገር መገንባት አይችልም፤ አንድነትን ማጽናትና ብሄራዊ መግባባት መፍጠር አይችልም። እናም የኢትዮጵያ ህዝብ የጥላቻ መርዝ ዘልቆት ጥንጣን እንደበላው እንጨት የሚጸና ሀገር መመስረት እንዳይሳነው ሊጠነቀቅ ይገባል። ተቆርቋሪ መስለው የሚቀርቡት በሙሉ መልካም አይደሉም። እንደተበደለ ነግረው፣ በዳዩንም ሹክ ብለው የጥላቻ መርዝ በመከተብ ለግጭት የሚያነሳሱት መልካሞች እንዳልሆኑ መገንዘብ አለበት። እንኳን አብሯቸው ተሳስሮ የኖረው ቀርቶ፣ በተለያየ አጋጣሚ ቅሬታ ያሳደሩበትንም ይቅር ብሎ ወገኑ እንዲያደርግ የሚነግሩት ደግሞ ደጎቹ ናቸው። የጥላቻ መርዝ ዘልቆት በገዛ እጅ አንድነቱን እየፈለሰ ተስፋውን እንዳያጨልም መጠንቀቅ አለበት።

Back to Front Page