Back to Front Page


Share This Article!
Share
የርእዮተ አለም ለውጥ አልተደረገም

                              የርእዮተ አለም ለውጥ አልተደረገም

ስሜነህ 08-27-18

 

ሃገራዊ ቀውሱ ተባብሶ በነበረበት ወቅት ወይም የዛሬ ሁለት ሁለት አመት ነሃሴ 15 2008  የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ መገምገሙ ይታወሳል። በግምገማው ይፋ እንዳደረገውም በአንድ በኩል የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ችግሮችን በመቅረፍ የህዝብ መብትና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በድርጅቱ የቀረበውን የአስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ሂደት የሚመለከት የግምገማ ሃሳብ መነሻ በማድረግ በዚህ ሂደት በአገራችን የተመዘገቡ አዎንታዊ ለውጦችና በተጨባጭ የሚታዩ ድክመቶችን በዝርዝር ስለመገምገሙም ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

አገራችን የተያያዘችው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግቦች በተሃድሶ የመጀመሪያ ዓመታት በግልፅ እንደተቀመጠው ፈጣንና ህዝብ የሚጠቀምበት ዕድገት ለማምጣት የሚያልሙ ናቸው ያለው ግምባር፤ ከዚህም ዕድገት ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ያላሰለሰ ትግል ማካሄዱን አስታውሷል፡፡  

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይህን መነሻ በማድረግ ባካሄደው ግምገማ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት በመወሰን፤ ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅቱ ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንደሚወሰድም አስታውቆ  ነበር፡፡  

Videos From Around The World

በዚሁ መሰረት ለዚህ ለውጥ የሚበጅ የአመራር ለውጥ ያደረገው ግምባር ዶክተር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀ መንበር አድርጎ ከመረጠ ከአራት ወራት በላይ ተቆጥረዋል። የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር አብይ በመንግስት አመራር ጠቅላይ ሚንስትር እንደመሆናቸው በእነዚህ አራት ወራት ውስጥ በርካታ መንግስታዊ እርምጃዎች በመውሰድ ያለተጠበቁና ምናልባትም በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ አምጥተዋል።በዚህ ጊዜ ታዲያ እንደ ድርጅት በኢህአዴግ በኩል የታዩ እንቅስቃሴዎች በመቀዛቀዛቸው የዶክተር አብይን እርምጃ ከርእዮተ አለም ለውጥ ጋር አያይዘው የተመለከቱ በርካታዎች ናቸው።ይህ መወናበድ  ከተርታው ህዝብ ጀምሮ በፖለቲካ ልሂቃኑ ዘንድም የተስተዋለ ነው።ከዛ ሁሉ ውጥንቅጥ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የግንባሩ ሊቀመንበርና የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድም ሆኑ ስራ አስፈጻሚው በሰጠው መግለጫ የርእዮተ አለም ለውጥ እንደሌለ እና ግምባሩና የሚመራው መንግስት ግና በተሃድሶ ሂደት ላይ ስለመሆናቸው አረጋግጠዋል።በእርግጥ እነርሱ ባያረጋግጡም የርእዮተ አለም ለውጥ እንዳልተደረገ የሚያጠይቁ በርካታ አስረጂዎች ስለመኖራቸው መጥቀስ ቢቻልም በእነርሱ ያምራልና የእነርሱው ማረጋገጫ ላይ ተንተርሶ መወያየት የፖለቲካ እይታችንን ያሰፋልና በዚሁ አግባብ አንዳንድ ጉዳዮችን እናንሳ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ጓድ ዶ/ር አቢይ አህመድ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢህአዴግ እስካሁን የርዕዮተ ዓለም ለውጥ አለማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ በሂደት ራሱን እያሻሻለና ተሃድሶ እያደረገ እዚህ መድረሱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአዳዲስ ሃሳቦች የሚስተዋለውን ፍላጎት ለመመለስ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ድርጅቱ በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ በተወያየባቸው አጀንዳዎች በመግባባት መጠናቀቁን ጠቅሰው፤በኢህአዴግ ልዩነት አለ በሚል የሚናፈሰው ወሬ መሰረት የለውም ብለዋል። በሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አሁን የመጣውን ለውጥ ሙሉ በሙሉ የተቀበሉና ያልተቀበሉ ግለሰቦች እንጅ እንደ ድርጅት ልዩነት እንደሌለም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለውጡን አልተቀበለም በሚል የሚቀርበው ወቀሳ አግባብ አለመሆኑንም አንስተዋል። በህወሓት ውስጥ ለውጡን ደግፈው ለህዝቡ ሰላምና ብልጽግና የሚሰሩ አመራሮች የመኖራቸውን ያክል ለውጡን ያልደገፉ እንዳሉም አስረድተዋል። ይህ ለውጥን ያለመቀበል ጉዳይ ግን በአራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የሚታይ መሆኑንም ነው የገለጹት፤ በጉዳዩ ላይ ህወሓት ብቻውን ሊወቀስ እንደማይገባ በመጥቀስ። ኢህአዴግ ግንባር ከመሆኑ አንጻር አራቱ ድርጅቶች በእኩል ድምጽና በመግባባት ተስማምተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ስለሆነም የለውጡ አካል መረዳት ካለበት ይህን እውነታ ነው።በዶክተር አብይ አመራር ላይ ከተስማማን እርሳቸው የሚመሯቸውን ብሄራዊ ድርጅቶችና ግምባር አንዱን እያነሱ ሌላኛውን መጣል በተዘዋዋሪ ለውጡን መቃወም ነው። ዶክተር አብይ ይህን ስላሉ አይደለም። የአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች እኩል የሚወከሉበት የግምባሩ ስራ አስፈጻሚ ከሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች እንደግለሰብ ለውጥ አደናቀፊዎች ቢኖሩ እንጂ እንደ ግምባር እና እንደ አባል ድርጅት የተናጋ አንዳች ነገር እንደሌለና የዛሬ ሁለት አመት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ግንባሩ ስራውን እየሰራ መሆኑን አረጋግጧል።

ልክ በሁለተኛው አመት ዋዜማ ላይ ተጀምሮ በአመቱ ማግስት በተጠናቀቀው ወይም የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ከነሀሴ 14 እስከ 16/2010 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የጥልቅ ተሃድሶውን አፈፃፀምና ያስገኘውን ውጤት በተለመደው ድርጅታዊ ባህል፣ ዴሞክራሲያዊነትን በተላበሰ እና በሰከነ አግባብ በጥልቀት መገምገሙን አስታውቋል፡፡

ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የጥልቅ ተሃድሶውን ተከትሎ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች የአመራር ፈጠራ ታክሎባቸው የለውጡ ቱርፋት የሆኑ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ማረጋገጡንም በሰጠው መግለጫ አመልክቷል፡፡ ከአሁን በፊት ውሳኔዎች እየተወሰኑ እና አቅጣጫዎች እየተቀመጡ በአፈፃፀም ድክመት ይታይባቸው የነበሩ ጉዳዮች በፍጥነት መፈፀም በመጀመራቸው በዚህ አጭር ጊዜ ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብለው የማይታሰቡ ድሎች ተመዝግበዋል፤ ሲል ማመልከቱም በግምባሩ አባል ድርጅቶች መሃል ጠፍቶ የነበረው ወይም መስሎን የነበረው የተግባር አንድነት ወደ ቦታው መመለሱን ወይም ደግሞ ለመናጋት ሁነኛ መነሻ የሚሆነው የርእዮተ አለም ለውጥ አለመደረጉን የሚያጠይቅ ነው፡፡  

በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች መመዝገብ የጀመሩ ለውጦች ጉልህና ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባችው መሆኑንም ገምግሜያለሁ የሚለው ስራ አስፈጻሚ፤ በፖለቲካው መስክ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ታራሚዎችን ከእስር ከመፍታት ጀምሮ፣ የትጥቅ ትግል ያካሂዱ የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶች የትጥቅ ትግላቸውን በማቆም በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በውይይትና በድርድር መተማመን በመፍጠር ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የተሰሩ ሥራዎች፣ ህዝቡ ያለምንም መሸማቀቅ ሀሳቡን በተለያየ መንገድ በነፃነት ማራመድ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ የመንግስትን ሚዲያን ጨምሮ በሌሎች ሚዲያዎችም የተለያዩ ሀሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ሁኔታ መጀመሩ፣ ተዘግተው የነበሩ ድረ-ገፆች መከፈታቸው የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት አይነተኛ ሚና መጫወታቸውን ማረጋገጡንም ማመልከቱ፤ ባሳለፍናቸው አራት ወራት ያየናቸው እና የፈነጠዝንባቸው ለውጦች በዶክተር አብይ አመራር ሰጪነት የመጡ የግምባሩ ርእዮተ አለማዊ ድሎች ስለመሆናቸው የሚያረጋግጥ እንጂ ስናነሳና ስንጥላቸው በነበረው አግባብ የመጣ አለመሆኑን ነው፡፡

ለዜጎች ዋጋና ክብር በመስጠት ከሀገር ውስጥ ባሻገር በጎረቤት ሀገራትና በመካከለኛው ምስራቅ ዜጎቻችን ከእስር እንዲፈቱና የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ መደረጉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብበዋል በሚል በተደጋጋሚ ከህዝብ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ህጎች ህዝብንና የመስኩን ሙያተኞች ባሳተፈ መልኩ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ስኬቶች መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚው ካያቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑም በመግለጫው መመልከቱ የብሄራዊ ድርጅቶቹን በተግባር አንድነት መንሰላሰልና የርእዮተ አለም ውግንናቸውን የሚያረጋግጥ አስረጅ ነው፡፡

በሰብአዊ መብት አያያዝ አስከፊ ችግር የነበረባቸው የማረሚያ ቤቶች እና ሌሎች የፀጥታና ህግ አስከባሪ ተቋማት ሪፎርም ለማድረግ አመራሮቹን ከመለወጥ ጀምሮ እየተሰራ ያለው ሥራ እንዲሁም ህዝብ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ተቋማት ኃላፊዎችን በማንሳት የተጀመረው የአመራር ሪፎርም የተቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል የተፈፀሙ እና ውጤትም ያመጡ መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚው አረጋግጧል፡፡በተለይ በዚህ ረገድ ግምባሩ መፈረካከሱን ሲያወሱ የነበሩ ሰዎች ከዚህ በላይ የድርጅቱን ጥንካሬ እና ርእዮተ አለማዊ ቅኝት ሊያጠይቅበት የሚያስችል አስረጅ የለም።የተፈቱ እና የተሰናበቱ የማረሚያ ቤቶች የስራ ሃላፊዎችን ብሄር እየቆጠርን ብሄራቸውን ለሚወክለው የግምባሩ አባል ድርጅት በመለጠፍ አበቃ አለቀ ስንል የነበርን ሁሉ የኢህአዴግ ነገር እድሳት ላይ እና ግለሰብ ሌቦች ላይ እንጂ እንደ አባል ፓርቲ የተለወጠ ርእዮተ አለማዊ መከፋፈል እንደሌለም የሚያሳየን ሁነኛ አስረጅ ነው።

እነኝህ እርምጃዎች የህዝቡን ድጋፍ ያገኙ፣ እንደ ሀገር የመቀጠል ስጋት ውስጥ ገብተን ከነበረበት ተጨባጭ አደጋ በመውጣት አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣ ያስቻሉ መሆኑን በአዎንታ መገምገሙ ድርጅቱ አሁንም ያለህዝብ ተሳትፎ ባዶ እንደሆነ የሚያመላክትና የህዝብ ምልከታም በዚህ ቅኝት እንጂ በቀኝ እጅ ደግፎ በግራ እጅ ያልሆነውን ማራገብ መልሶ እንቅፋት መሆን እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በነፃነት በሀገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ ያስቻለ ውጤታማ ሥራ መከናወኑንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ተቀምጧል፡፡ይህ ደግሞ ከላይ በተመለከተው ከግንባሩ አቋም ውጪ የመጣ አለመሆኑን ያልተገነዘበ ከውጭ የሚመጣ አካል እንደገና ሌላ መናቆር ውስጥ እንዳይገባ ስለሚያሰጋ ቅኝታችን ቢስተካከል የተሻለ ይሆናል።

በዲፕሎማሲው መስክ የተሰራው አኩሪ ሥራ የሀገራችንን ተቀባይነትና ተደማጭነት ያሳደገ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ገምግሟል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት የህዝብ ለህዝብ እና የጋራ ጥቅሞች ላይ በመመስረት ህዝባዊነትን ተላብሶ በፍጥነት እንዲሻሻል ለማድረግ መሰራቱ ውጤታማ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት በዘላቂ የጋራ ጥቅሞች ላይ ተመስርቶ እንዲጠናከር የተደረገው ጥረትና ያስገኘው ውጤት እንዲሁም ደግሞ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የተደረጉ ግንኙነቶች እና በሀገራችን እየመጣ ያለውን ለውጥ ተከትሎ ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እየተገኘ ያለው ድጋፍ በአለም አቀፍ ደረጃም ኢትዮጵያ ያላትን ተሰሚነት ያሳደገ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ገምግሟል፡፡

በማህበራዊ ዘርፍ ለበርካታ አመታት በሁለት ሲኖዶሶች ተከፍላ የቆየችው የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የእስልምና እምነት ተከታዮችን መከፋፈል በማስቀረት ወደ አንድነት ለማምጣት የተደረገው ጥረት በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነትን ለማጠናከር ያስቻሉ ጅምር ሥራዎች መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በኢኮኖሚው መስክ በተከናወኑ ሥራዎች የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ በመጀመራቸው ችግሩን ለማስታገስ ያስቻሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን በማየት ጥረቱ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ አስምሮበታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመሰረታዊነት ለማቃለል የሚያስችለውን የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ስራ ላይ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የዋጋ ንረት እያሳየ የነበረው ዕድገት እንዲገታ በማድረግ ረገድ መምጣት የጀመረውን ውጤት በአዎንታ ወስዶ ወደ ነጠላ አሀዝ እንዲወርድ ተጨማሪ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉንም የመፍትሄ አማራጮች በመጠቀም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ገምግሟል፡፡ በተመሳሳይ ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የተጀመረዉ ስራና አፈፃፀማቸው የተጓተቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያሉባቸው ችግሮች ተቃለው በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ መሆኑን በጥንካሬ ገምግሞ ይሄው መልካም ጅምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ኢትዮጵያዊ ማንነት ተገቢውን ክብር እና ቦታ እንዲያገኝ የተጀመረው ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት ከብሔር ማንነት ጋር ተሰናስሎ እንዲፈፀም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የተጀመረው ለውጥ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ጥልቀት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ለውጡን በሁሉም ደረጃ ከማድረስና ከማስፋት አንፃር የሚታየውን እጥረት በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል። ስለሆነም ባሳለፍናቸው አራት ወራት የመጡት ለውጦች ስንለው በነበረው አግባብ በተፈረካከሰና የርእዮተ አለም ለውጥ ባመጣ ቡድን ሳይሆን በነበረው ርእዮተ አለም ላይ ተንጠልጥሎ የዛሬ ሁለት አመት በግምገማ የለየውን ችግር ለማስወገድ ቆርጦ በተነሳ ግንባርና የለውጥ አመራር ነው።  በዚያው ልክ ደግሞ ርእዮተ አለሙን የሌብነት ዋሻ አድርገው የነበሩ ሃይሎች ከአራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች መራገፋቸውን የሚያጠይቅ የግምገማ ውጤትና ቃለ ምልልስ ነው።ህዝብ ደግሞ ግለሰብ ሌቦችን ከግንባሩ በመለየት ድጋፉን ማጠናከር ከቻለ ብዙም ሳንሄድ በአንድ አመት ብቻ ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ በአራት ወራቱ በማብዛት መገንዘብ የሚቻል ስለሚሆን ቅኝታችን ከሆይ ሆይታ በተጨባጭ መረጃዎችና የስራ ሂደቶች ላይ ቢሆን እንደሃገርም እንደህዝብም ሆነ ግለሰብ ያዋጣናል።

 

 

Back to Front Page