Back to Front Page


Share This Article!
Share
የለውጡ አደናቃፊዎች

የለውጡ አደናቃፊዎች

ዳዊት ምትኩ 06-30-18

ሰላምን ስለተመኘነው ብቻ ልናገኘው አንችልም። ህብረተሰቡ የአካባቢው ሰላም ዋስ ጠበቃ መሆን አለበት። በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ኃይሎች ህዝብን በማሸበር የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴን ለመግታት የሚያደርጉት ጥረት ከቀቢፀ ተስፋ የመነጨ ድርጊት መሆኑን ህዝቡ ይገነዘባል። ከህዝብ የሚሰወር ምንም ነገር ባለመኖሩ፣ የእነዚህ ሃይሎች አሳፋሪ ተግባር ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዳሻቸው መዝረፍ ለምደው ዛሬ በለውጥ ሀደቱ ያ ስለቀረባቸው የገዛ ዜጋቸው ላይ ቦንብ የሚያፈነዱ ናቸው።

እርግጥ ከየትኛውም ወገን ይሁን በህዝብ ላይ ቦምብ የሚያፈነዳ ወይም ሽብር የሚነዛ አካል እርሱ አሸባሪ መሆኑ ግልፅ ነው። ያም ሆኖ ህብረተሰቡ እነዚህ በከሰረ ፖለቲካ ስሌት የሚንቀሳቀሱና ተስፋ የቆረጡ አካላት ለውጡን ለማደናቀፍ ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ ጥረት ማድረጋቸው እንደማይቀር ማወቅ አለበት። በመሆኑም የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ በመጠበቅና ፀጉር ልውጦች ሲገጥሙት ለአካባቢው ፀጥታ ሃይል ተገቢውን መረጃ በወቅቱ መስጠት ይኖርበታል።

Videos From Around The World

እዚህ ላይ ህብረተሰቡ የቀን ጅቦች የሚለወንም አገላለጽ መገንዘብ ይኖርበታል። ይህ አገላለጽ የህዝብን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማፈን፣ የቀድሞውን እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል ስግብግብ አስተሳሰብና ድርጊት የሚወክል እንጂ ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል የተሰጠ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል። ይሁን እንጂ ማንም ሰው ከየትኛውም ህብረተሰብ ክፍል ይሁን፤ የህዝብን የለውጥ ፍላጎት ለማኮላሸት ማናቸውንም ዓይነት እንቅስቃሴዎችን ካደረገ እርሱ የቀን ጅብ መሆኑን መረዳት ይገባል።

ህብረተሰቡ የኢፌዴሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ በአገሪቱ ውስጥ እየመጡ ያሉ ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተፈፀሙ ያሉ ሴራዎችን የሚመረምሩ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን መገንዘብ አለበት። እነዚህ ኮሚቴዎች እየተፈፀሙ ያሉ ሴራዎችን በማጣራት ለህግ የሚያቀርቡ ናቸው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ሰኔ 16 ቀን 2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ እውቅና ለመስጠት እንዲሁም አገራዊ አንድነትን ለመገንባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ለመደገፍ በአዲ አበባ በወጣው ህዝብ ላይ ቦምብ ተወርውሯል፤ ሂደቱ እንዲስተጓጎልም ተደርጓል።

በወቅቱም ሰላማዊ ሰልፉን ለማደናቀፍ ቦምብ ከመወርወር ጀምሮ ሂደቱ እንዲስተጓጎል በወቅቱ መብራት የማጥፋት እና የቴሌኮም ኔትወርክ የማቋረጥ ተግባር ተከናውኗል። በተጨማሪም የኢኮኖሚ አሻጥር በተደራጀ አኳኋን በመስራት የኑሮ ውድነት እንዲባባስና የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋሙ ተቋማት አስፈላጊውን አገልግሎት እንዳይሰጡ እየተደረገም ነው። ይህ እጅግ አሳፋሪና እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚደረግ ጥረት መሆኑ ግልፅ ነው።

ይሁን እንጂ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች እነዚህን ህገ ወጥ ተግባራት አጣርቶ ለህግ ለማቅረብ ከተለያዩ አካላት ጋር ስራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። የማጣራቱንና የምርመራውን ውጤት በወቅቱ ለህዝቡ ያቀርባሉ።

ምንም እንኳን እነዚህ ሀገ ወጥ ተግባሮች ሚሊዩኖች የሚፈልጉትን አገራዊ ለውጥ የማስቆም ቅንጣት ያህል አቅም ባይኖራቸውም፤ ህብረተሰቡ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት እነዚህን ሃይሎች በማጋለጥና ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ እንደ ሁልጊዜው ከመንግስት ጎን ቆሞ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ፅሀፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፤ ተስፋ የቆረጡና ጥቅማቸው የተነካባቸው ሃይሎች እንደ ሰኔ 16ቱ ዓይነት በህዝብ ላይ ጥቃት ሊፈፅሙ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ሰላሙን መጠበቅ እንደሚኖርበት አሳሰበዋል።

እርግጥም በየትኛውም አገር ውስጥ የሰላም ጠባቂ ህዝብ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት የታወከው ሰላማችን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና መንግስታቸው በከወኑት ስራ በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ የሰላማችን ባለቤት መሆን ችለናል። ይህ የሆነውም ህዝቡ ለውጡን ደግፎ ከመንግስት ጎን በመቀሙ ነው። ዛሬም ሰላሙን የለውጡ አደናቃፊዎች እንዳያደፈርሱበት መጠንቀቅ አለበት። ይህን በማድረግ የአገሩን አንድነትና ዕድገት መጠበቅ ይኖርበታል።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚዋ እየሆነች ነው። ለዚህም ምስክሮቹ የቀጠናው አገራትና ዓለም አቀፉ ማሀበረሰብ ነው። ይህን ቀዳሚነታችንን የህበረተሰቡን ሰላም በማወክ ለማደናቀፍ የሚሹ ጥቅማቸው የተነካባቸው ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ ነው። ይሁን እንጂ ከህዝብ የለውጥ ፍላጎት ፊት ሊቆም የሚችል አንዳችም ሃይል አይኖርም። ለአገሩ ሰላምና ዕድገት ዋነኛው ሃይል ህዝብ እንጂ እኔ ብቻ ልብላ የሚሉ ስግብግቦች ስላልሆኑ ነው። እናም ህብረተሰቡ ለሰላሙ ቅድሚያ መስጠት አለበት።

እርግጥ ሰላም ከሌለ ህግን ማስከበር አይቻልም። መብትም አይከበርም። መብትን በፈቃዳችን ሳይሆን በህገ ወጦች ችሮታ ብቻ ለማግኘት እንገደዳለን። ህገ ወጦች ህዝቡ በትግሉ ያገኘውን መብት ሲሻቸው ይነፍጉታል። የህግ አስፈፃሚም ይሆናሉ። ሌላው ቀርቶ የህዝቡ በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይም አሳሳቢ ይሆናል።

የሰላም እጦት ፈተናን እንኳንስ በተግባር የተፈተነው የአገራችን ህዝብ ቀርቶ ሌላውም ቢሆን ያውቀዋል። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም አገር ህዝብ ይገነዘባል። በመሆኑም ለሰላሙ ዘብ በመቆም የለውጡን አደናቃፊዎች አምርሮ ሊታገላቸው ይገባል።

ህዝቡ በለውጡ ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ የተፈጠረውን አስተማማኝ ሰላም ተገንዝቧል። የለውጡ ባለቤትም እርሱ ነው። እርግጥም የህዝብንለውጥ ፍላጎትን ማንም ሊያቆመው አይችልም። አገራችን የህዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የጀመረችው ፈጣንለውጥ ጉዞ ተጨባጭ ስኬቶችን እያስመዘገበ ነው።

ህዝቦች መስዋዕት ጭምር የሆኑዐት ይህ ለውጥ በአሁኑ ሰዓት ማንም ሊያቆመው የማይችልት ደረጃ የደረሰ ነው። መንግስትአገር ውስጥ ያከናወናቸው ተግባሮች እንዲሁም አካባቢውን ከማስተሳሰር አኳያ ያደረጋቸው ጥረቶች በስኬት የታጀቡ ናቸው።

ይሁን እንጂ ፈጣኑ ለውጥ ከስጋት ላይ የጣሏቸው አንዳንድ አካላት ተፈጥረዋል። እነዚህ አካላት የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ በርካታ እንቅፋቶችን አዘጋጅተው ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት እንዲሁም ህዝብን በጠራራ ፀሐይ ለመግደል እያሴሩ ናቸው። ይህን ሴራ ማውገዝና መታገል የህዝቡ ድርሻ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ምክንያቱም ከህዝብ የሚሰወር ነገር ባለመኖሩ እነዚህን አደናቃፊዎች ለህግ አሳልፎ በመስጠት ሰላምን መጠበቅ ስለሚቻል ነው። የሰላሙ ዋስ ጠበቃና ባለቤት ህዝቡ በመሆኑ አደናቃፊዎችን መታገል የእርሱው ተግባር ነው።

 

 

 

 

Back to Front Page