Back to Front Page


Share This Article!
Share
የድንበር ጉዳዮችዕረፍት ይነሳሉ፤ማሰብ ይፈልጋሉክፍል አንድ

የድንበር ጉዳዮች

ዕረፍት ይነሳሉ፤ማሰብ ይፈልጋሉ

ክፍል አንድ

አሜን ተፈሪ 07-11-18

የድንበር ነገር ከህገ ወጥ ንግድ፣ ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ከጸጥታ ወዘተ ጋር የሚያያዝ ብቻ ሳይሆን፤ ሥር የሰደደ ከታሪክ ጋር የተያያዘ ችግር የሚታይበት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በወዲያኛው ሣምንት መጨረሻ (ሰኔ 23 እና 24) ይህኑን የድንበር አካባቢ ጉዳይ የሚፈትሽ አንድ አውደ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ አውደ ጥናት በርካታ የጥናት ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የተለያዩ ወገኖች በመጋበዝ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ የድንበር ጉዳይ የጽጥታ መዋቅሩን ብቻ የሚመለከት አጀንዳ ተደርጎ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ አመለካከት ሊቀየር እንደሚገባ እና የድንበር ጉዳዮችን ቀለል አድርጎ በማየት መወያየት እና ከድንበር ጋር ተያያዥ ለሆኑ የተለያዩ ችግሮች መፍትሔ ማፈላለግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዚህ አውደ ጥናት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ የፌዴራል ጉዳዮች እና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር፣ ኢሚግሬሽን፣ አራ (AARA)፣ የስደተኞች እና የስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የተወከሉ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ዋና ባለጉዳዮች የሆኑት የጠረፍ ከተማ ነዋሪዎችም በአውደ ጥናቱ ተካፋይ ሆነዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ከኩርሙክ፣ ከመተማ፣ ከሞያሌ እና ከሽሬ የመጡ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የዞን ወይም የወረዳ መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል፡፡ በተጨማሪም፤ ለጠረፍ ከተሞቹ ቅርብ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአውደ ጥናቱ ተሳታፊ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ፤ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ወደፊት ጥናት ያደርጋሉ በሚል እምነት፤ ከጎንደር፣ ከአሶሳ እና ከቡሌሆራ ዩኒቨርስቲዎች የተጋበዙ ምሁራንም በአውደ ጥናቱ እንዲሳተፉ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ከዩጋንዳ ማካሬሬ ዩኒቨርስቲ፣ ከሱዳኑ ካርቱም ዩኒቨርስቲ እና ከኖርዌ ዩኒቨርስቲ የተወከሉ ምሁራን በአውደ ጥናቱ ተካፋይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በድንበር አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦችን ህይወት ለማሻሻል፤ እንዲሁም ከጽጥታ፣ ከስደት፣ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ ከህገ ወጥ ንግድ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ የተለያዩ ጥናቶች፤ በኢትዮ-ኬንያ ድንበር በምትገኘው ሞያሌ እና በኢትዮ- ሱዳን ድንበር አካባቢ ባለችው ኩርሙክ ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ከዚህ ቀደም መካሄዳቸውን የጠቀሱት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ፍቃዱ፤ የጠረፍ ከተሞች የህይወት እንቅስቃሴ በምሥራቅ አፍሪካ (Borederland Dynamics in East Africa) በሚል ርዕስ፤ በክፍለ አህጉሩ በሚገኙ የተለያዩ የጠረፍ አካባቢዎች ጥናት መነሻ በማድረግ የፖለሲ ምክረ ሐሳብ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የተላከላቸውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ተመልክተው ግብረ ምላሽ የሰጡ የሥራ ኃላፊዎች ባለመኖራቸው ቅር መሰኘታቸውን፤ የኡጋንዳ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑ የሥራ ባልደረባቸው ከፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት የላካችሁልን የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ደርሶናል፡፡ ኑና እንነጋገር በሚል የደረሳቸውን ፈጣን ምላሽ በምሳሌ በመጥቀስ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የድንበር ጉዳይን ከማዕከል ለይቶ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ ድንበር የማዕከሉ መስታወት ነው፡፡ የድንበር ጉዳይ ከጸጥታ ሥራ ጋር ብቻ ተቆራኝቶ መታየት አይኖርበትም ያሉት ዶ/ር ፍቃዱ፤ የድንበር አካባቢ ታሪካዊ እና ማህበረሰባዊ ሁኔታዎች፤ የክፍለ አህጉሩ ምንግስታት ላላ ያለ ድንበር ፖሊሲ እንዲቀርጹ የሚያስገድድ መሆኑን እና ድንበርን የሚጠብቀው ወታደር ሳይሆን ህዝብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጥብቅ የሆነ ድንበር መፍጠር በጠረፍ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ በእጁ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ህይወቱን ማሻሻል የሚችልበትን ዕድል እንዳያገኝ ያደርጋል ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር፤ የማያፈናፍኑ የጉምሩክ ህጎች ዜጎች በጠረፍ ንግድ ሥራ ህይወታቸውን ለመምራት የሚችሉበትን ዕድል ይዘጋባቸዋል ይላሉ፡፡

በዚህ ረገድ ኮንትሮባንድ የሚል አስደንጋጭ ቃል መጠቀሙን ትተን፤ ኢ-መደበኛ ድንበር ተሸጋሪ ንግድ የሚል ለዘብ ያለ ስያሜ በመስጠት፤ የጠረፍ አካባቢ ህዝብ ለኑሮውን ለመደገፍ በሚያስችል የንግድ ሥራ እንዲሰማራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ ተናግረዋል፡፡

Videos From Around The World

ይህን ሐሳብ መነሻ በማድረግ አስተያየት የሰጡ አንድ የስራ ኃላፊ፤ ከድንበር ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ ያለው አማራጭ የኢኮኖሚ ውህደት መፍጠር መሆኑን እና በአሁኑ ጊዜ ድንበርን ሙሉ በሙሉ ለማስከበር የሚያስችል ቁመና እንደሌለን ጠቅሰው፤ ድንበርን ላላ የማድረግ ሐሳብ፤ አሁን ያለው መንግስት ከሚያራምደው አቋም አንጻር የተቃኘ እንዲሆን ከተደረገ ተደማጭነት ለማግኘት እንደሚቻል እና ይህም አቋም የበርካታ የአፍሪካ ሐገራት አቋም እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የጉባዔው ተሳታፊዎች የተለያዩ የድንበር አካባቢ ችግሮችን እየጠቀሱ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ከኢሚግሬሽ የተወከሉ አንድ ተሳታፊ በበኩላቸው፤ በድንበር አካባቢ ነጻ ቀጣና (በፈር ዞን) አለመኖሩን እንደ ችግር ጠቅሰው፤ አብዛኞቹ የጠረፍ ከተሞች ቀደም ሲል ኬላ የነበሩ እና ከድንበሩ ስር ተጠግተው የተቆረቆሩ፤ እንዲሁም በዕቅድ ያልተገነቡ ከተሞች በመሆናቸው የተሟላ ማዘጋጀቤታዊ አግልግሎት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህም የድንበር ከተሞች አመሰራረት ያለውን ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል ብለዋል፡፡

በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ ድንበር እንዲሁም በሱማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያሉት እንደ ቀብሪበያህ እና ተፈሪ በር የመሳሰሉ፤ እንዲሁም በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያሉት ከተሞች ወደ ከተማነት የተየሩት ከኬላነት ተነስተው ነው ያሉት እኒሁ ተሳታፊ፤ የእነዚህን ከተሞች ሁኔታ ለማሻሻል እና ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ የማስተር ፕላን ዝግጅት ቢጀመር፤ የጎረቤት ሐገራት እንቅስቃሴአችንን በበጎ አይመለከቱትም፡፡ ይህም ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል በማለት መንግስት ግልጽ የድንበር አስተዳደር ፖሊሲ ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት እንደታየው ችግሩን አሳንሰን ከተመለከትነው እና በድንበር አካባቢ መስራት ያለብንን ሥራ ለሌላ መቶ ዓመት እንዳናሳድረው ያሰጋል ብለዋል፡፡ ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ካልሰጠን፤ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ለመፍታት የሚያስቸግር ውስብስብ ችግር ሆኖ ይመጣል ያሉት ተሳታፊ፤ ወደ ፊት ትልቅ እሣት የሚጭር ችግር እንዳይፈጠር ያላቸውን ስጋት አንጸባርቀዋል፡፡

ነገር ግን በቅርቡ ሐገራችን ከኤርትራ ጋር ያለውን የድንበር ችግር ለመፍታት የወሰደችው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪ፤ አሁን ትኩረታችን የተሳበው በውስጥ ጉዳዮች ነው፡፡ የአስተዳደር ወሰንን እንደ ድንበር የመቁጠር አዝማሚያ እየተበራከተ፤ ይታያል፡፡ ከጎረቤት ሐገራት ጋር ካለው ድንበር ይልቅ በክክሎች መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ትልቅ አጀንዳ ሆኗል ብለዋል፡፡

በመተማ አካባቢ የሚታየው ሁኔታ ሁለት መልክ ያለው ነው፡፡ በአንድ በኩል፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ህዝቦች መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ሰላማዊ የወንድማማችነት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ሲሆን፤ በሌላ በኩል በየጊዜው ድንገት ቦግ የሚል የግጭት እሣት ይታያል፡፡ ይህ ጉባዔ እንደተጠናቀቀ በመተማ የተከሰተው ግጭት ለሰው ህይወት መጥፋት፤ ለአካል ጉዳት እና ለንብረት ውድመት ያዳረገ ችግር ፈጥሯል፡፡ ከመተማ ከተማ የሚጡ አንድ አዛውንት እንደ ገለፁት፤ በከተማ ነዋሪዎች መካካል የሚታይ ግጭት የለም፡፡ በሱዳን ጋላባት እና በኢትዮጵያ መተማ የከተማ ነዋሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት በጣም የሚያስደስት ሆኖ ሳለ በአርሦ አደሮች በኩል ግን አሳዛኝ ግጭት ይታያል ብለዋል፡፡

እኛ እና ሱዳን ሰላም ነነ፤ እኛ እና ሱዳን ጠቦች ነነ የሚለው ሁለት አፍ ሆነ ተብሏል በሚል አስተያየት መስጠት የጀመሩት አዛውንት፤ አዎ፤ የሱዳን ጋላባት ከተማ እና የሐበሻ መተማ ከተማ ነዋሪዎች በመካከላችን ድንበር ሆኖ የሚገኘው አንድ ድልድይ ነው፡፡ እኛ ሰላም ነነ፤ ተቃቅፋን፣ ተዋደን እንኖራለን፡፡ ቋንቋም እንወራረሳለን፡፡ አሁን የእኛ ችግር የእርሻ መሬት ላይ ነው፡፡ ድንበሩ ከዚህ እስከዚህ የሱዳን ነው፡፡ ከእዚህ እስከ እዚህ የሐበሻ ነው ተብሎ የተከለለ መሬት የለም፡፡ ከዚህ ቀደም በመፈራራት እንኖር ነበር፡፡ አሁን በመደፋፈር ነው፡፡ መጥተው ክምር ያቃጥላሉ፡፡ አሁን ሰኔ የሰሊጥ ወቅት ነው፡፡ እነሱ 75 በሬ ነድተው ወስደዋል በማለት ያለውን ችግር አብራርተዋል፡፡

ከፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ የተወከሉት የጉባዔው ተሳታፊ የድንበር እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት ለማጥናት የተደረገውን ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ሰፊ ጥናት መሆኑን ጠቅሰው በማድነቅ፤ የፕሮጀክቱን አስተባባሪዎች በማመስገን ጥያቄ አንስተዋል፡፡

መደበኛ (ህጋዊ) ያልሆነ የድንበር ንግድ እንዲኖር መፍቀድ ያስፈልጋል የሚል የተነሳውን ሐሳብ ተንተርሰው፤ ለመሆኑ ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ሲባል ምን ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ንግድ እንዲኖር መፍቀድ የሚጠቅመው ማንን ነው? የሚጎዳው ማንን ነው? ሐገራዊ አንድምታውስ ምንድነው? የሚል ጥያቄ መነሳት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡ ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ስንል ምን ማለታችን ነው? የሚል ጉዳይ መነሳት አለበት፡፡ ሌሎች ያደጉ ሐገራት ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ሲሉ፤ የህግ ገደብ ያልተደረገባቸውን ቀረጥ እና ታክስ ያልተከፈለባቸውን ሸቀጣሸቀጥ ወይም ዕቃ ለመጥቀስ መሆኑን፤ በተቃራኒው ኮንትሮባንድ ሲባል፤ የሕግ ገደብ የተደረገባቸውን እና የተከለከሉ እንደ ጦር መሣሪያ፣ አደንዛዥ ዕጽ እና መድኃኒትን የሚመለከት እንደሆነ ጠቅሰው፤ እነዚህ ሐገራት ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ሥራ ምንድነው የሚለውን በድንጋጌ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡

የተጠቀሱት ሐገራት ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ጠቃሚ መሆኑን ይቀበላሉ፡፡ ኮንትሮባድን ደግሞ በጥብቅ ይከላከላሉ ያሉት የጉምሩክ ተወካይ፤ ሐገራቱ ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ፤ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተቀብለው ከራሳቸው ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ህግ አውጥተው እንደሚሰሩ እና የጠረፍ ንግድን የሚቆጣጠሩበት በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራ ስርዓትም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ታዲያ ይህን ነገር ወደኛ ሁኔታ ስናመጣው፤ ኮንትሮባንድ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ያጠቃልላል፡፡ በኢትዮጵያ የጉምሩክ አዋጅ፤ ኮንትሮባንድ ማለት የተከለከለ፣ ገደብ የተደረገበት እና ቀረጥ እና ታክስ ያልተከፈለበት ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ የሚባለውን ኮንትሮባንድ እያልን የምጠራው በዚህ የተነሳ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነገር ግን ጉዳዩ መታየት ያለበት በተወሰነ የድንበር አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎች አንጻር ብቻ ሳይሆን በሐገር አቀፍ ደረጃ ካው አንድምታ አንጻር ነው፡፡ ይህን ስንል በአሁኑ ጊዜ በጉምሩክ አሰራር ወይም የቁጥጥር ስርዓት ላይ በጣም ከፍተኛ ችግሮች መኖራቸው የታወቀ ነው ያሉት ተወካዩ፤ በጠረፍ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ ኑሮውን በንግድ ሥራ ለመምራት የሚችልበት ዕድል በመነፈጉ ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥመውም እናውቃለን፡፡ ሆኖም፤ ኢንፎርማል ክሮስ ቦርደር ትሬዲንግ ለዚህ ህብረተሰብ ችግር ማቃለያ እንዲሆን ምክረ ሐሳብ ስናቀርብ፤ መፍትሔው ዘላቂ ነው ወይ የሚለውን ከግምት ማስገባት ይኖርብናል በማለት፤ ጥናቱ ትንሽ ጠለቅ ብሎ ሊመለከታቸው የሚገቡ ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም፤ እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በየዓመቱ በአማካይ ከ200 እስከ 300 ሚሊየን ብር የሚገመት የበኮንትሮባንድ ዕቃ ይያዛል የጉምሩኩ ተወካይ፤ ይህ አሃዝ ባለው ከቁጥጥር ስርዓታችን ብልሹነት የተነሳ የሚያልፈውን ዕቃ ሳይጨምር ነው፡፡ ከተጠቀሰው አሃዝ በብዙ እጥፍ የሚልቅ ዕቃም በኮንትሮባንድ ወደ ሐገር ቤት የሚገባበት ሁኔታ እያለ፤ በየዓመቱ በአማካይ ከ200 እስከ 300 ሚሊየን ብር የሚገመት የበኮንትሮባንድ ዕቃ ይያዛል ብለዋል፡፡

ይህ አሃዝ በ2008 ዓ.ም 905 ሚሊየን ብር ደርሷል ካሉ በኋላ፤ በ2009 እና 2010 ዓ.ም ከሞላ ጎደል በዓመት ግምቱ አንድ ቢሊየን ብር የሚደርስ ዕቃ በኮንትሮባንድ ወደ ሐገር ቤት ገብቷል በማለት፤ ከዚህ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ የሚሆኑት የጠረፍ አካባቢ ነዋሪዎች አይደሉም ብለዋል፡፡ ከዚህ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ የሚሆኑት ዕቃውን ወደ መሀል ሐገር የሚያስገቡት ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ኮንትሮባንድ ተጠቃሚ የሆኑት በጠፈር አካባቢ ያሉት አነስተኛ ነጋዴዎች አይደሉም፡፡ በጠፈር አካባቢ ያሉት አነስተኛ ነጋዴዎች ከአንድ የሸቀጥ ልውውጥ መቶ ወይም ሁለት መቶ ብር ለማግኘት ነው የሚሰሩት ብለዋል፡፡ ሆኖም ይህን ያህል ዕቃ ወደ መሐል ሐገር ሲገባ፤ በዝቅተኛ ዋጋ የሚቀርበው ዕቃ ሐገር በቀል ኢንዱስትሪውን ገበያ በማሳጣት ዘርፉን ይዞት ይወድቃል በማለት አስረድተዋል፡፡

ይህ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በማህበራዊ እና በሐገር ደህንነት ላይ የሚያስከትለው አደጋም ከፍተኛ ያሉት የጉምሩክ ተወካይ፤ ወደ ሐገር ቤት ከሚገባው የኮንትሮባንድ ዕቃ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠረው የጦር መሣሪያ፣ አደንዛዥ ዕጽ እና መድኃኒት መሆኑን ነው ያለው መረጃ የሚያመለክተው ብለዋል፡፡ ስለዚህ ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ በጠረፍ አካባቢ ላለው ህብረተሰብ ይጠቅማል ወይ የሚለውን ጉዳይ በደንብ መፈተሽ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የተለያዩ የመንግስት አካላትን አቅም የሚያሳድግ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረው፤ በየሴክተር መሥሪያ ቤቱ ያለውን የሰው ኃይል አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከተቆጣጣሪው ይልቅ ኮንትሮባንዲስቱ የረቀቀ የቴክኖሎጂ አቅም እንዳለውም አመልክተዋል፡፡ ነፍስ ያለው ዶሮ ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ በመደበቅ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ለማስገባት ሲጥሩ ይታያል ብለዋል፡፡

የድንብር ጥበቃ ጉዳይ በተለያየ ጊዜ የተለያየ አመለካከት እንደሚንጸባረቅበት የገለጹት ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ፤ አንዳንድ ጊዜ የማጥበቅ ሌላ ጊዜ የመላላት ሁኔታ እንደሚታይ እና በአሁኑ ወቅት ምዕራባዊ መንግስታት በሰፊው ከፍተውት የነበረውን ድንብር ማጥበቅ መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ የድንበር ጥበቃ ጉዳይ ከሉዓላዊነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጥበቃ የማይቀር ቢሆንም፤ እኛ እንደ ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ የሚቀርበው ላላ ያለ ድንበር (ሶፍት ቦርድር) ነው ብለዋል፡፡

ድንበር ሲታይ ከመሐል ተለይቶ የሚታይ መሆን የለበትም፡፡ ድንበሩ የመሐሉ መገለጫ ነው፡፡ መሐሉ ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ድንበሩ ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ መሐሉ የተሻለ አስተዳደራዊ መዋቅር እና የመልካም አስተዳደር ስርዓት ተጠቃሚ ሳይሆን ድንበሩ ሊያገኝ አይችልም፡፡ እኛ በድንበሩ ነጸብራቅ መሐሉን ለማየት እየሞከረን ነው፡፡ እኛ ከድንበር አንጻር ውስጡን እያየን ነው ያሉት ዶ/ር ፍቃዱ፤ ለዚህ በምሣሌ ያነሱት የኬንያን ሁኔታ ነው፡፡ ኬንያ የተሻለ የዴሞክራሲ ቁመና ያላት በመሆኑ፤ ከኢትዮጵያ ተነስተን ወደ ኬንያ ሞያሌ በመኪና ለመግባት ክልከላ የለም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ይከለክላል፡፡ በአንጻሩ በመተማ በኩል ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ከሱዳን የተሻለ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ያለ በመሆኑ፤ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ያለ ችግር በቀላሉ መሻገር የሚቻልበት ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡

እኛም እንደማንኛውም ሰው ኮንትሮባንድን እንቃወማለን፡፡ ኮንትሮባንዲስቶች በሚሊዮን ሲነግዱ እንቃወማለን፡፡ ሆኖም መታየት ያለባቸው ሌሎች ጉዳዮችም አሉ፡፡ ለምሣሌ፤ የኢትዮጵያ ሞያሌ ነዋሪዎችን ብንወስድ ከድንበር ባሻገር ካሉት ህዝቦች ጋር በአመጋገብ፣ በአለባበስ ባህል እና በአኗኗር ዘዬ ተመሳሳይ በመሆናቸው፤ ማዶ ካለችው ከኬንያ ሞያሌ የሚፈልጉትን ብዙ ነገር ያገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሞያሌ ከአዲስ አበባ 800 ኪሜ ይርቃል፡፡ ከኬንያ ሞያሌ ግን ያለው ርቀት 200 ኪሜ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አካባቢ የኢትዮጵያ ሞያሌ ነዋሪ የሚፈልገው ሩዝ ይገኛል፡፡ አንድ ኪሎ ሩዝ ከኬንያ ሞያሌ ሲመጣ ዋጋው 10 ብር ሊሆን ይችላል፡፡ ከአዲስ አበባ ሲመጣ ዋጋው ይጨምራል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ባለችው ኩርሙክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አለባበሳቸው ከሱዳን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ተመሳሳይ የአለባበስ ባህል ያላቸው በመሆኑ፣ ልብሱም ከአካባቢው የአየር ጸባይ ጋር ተስማሚ በመሆኑ የሚፈልጉትን ልብስ በዝቅተኛ ዋጋ ከሱዳን መግዛት ይችላሉ፡፡ ይህን ሁኔታ በመረዳት የኢጋድ አባል ሐገር መንግስታት የድንበር ንግድ እንዲኖር ውሳኔ አድርገዋል፡፡ በዚህ ስምምነት እስከ 1 ሺህ ዶላር ድረስ የድንበር ንግድ እንዲኖር መፍቀዳቸው ይታወቃል፡፡ በወር ሁለት ጊዜ በዝርዝር የተፈቀደላቸውን ዕቃ ብቻ ይገዛሉ፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹ ዕቃዎች በአካባቢው ተፈላጊ ያልሆኑ እና የተፈቀደው ገንዘብ ትንሽ ከመሆኑም በላይ፤ በዚህ ንግድ ግብር ይከፍላሉ፡፡ ከተፈቀደው ብር መጠን በላይ እንዳይሄዱም ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ በሞያሌ ወደ 40 ሰዎች ፈቃድ አወጡ፡፡ እነዚህ ሰዎች ግብር ሲከፍሉ፤ ሌሎች በህገ ወጥ መንገድ ንግድ ቀጥለዋል፡፡ ስለለዚህ ፈቃድ የወሰዱ ሰዎች በዓመቱ መለሱ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር አለ ብለዋል፡፡

በመጨረሻም፤ ዶ/ር ፍቃዱ ከተሳታፊዎች የቀረቡት አስተያየቶች ለፖሊሲ ምክረ ዝግጅቱ ግብአት እንደሚሆን በመግለጽ፤ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ዲፓርትመንት ሄድ ዶ/ር ተሾመ ኢማና ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር አንዲያደርጉ የጋበዙ ሲሆን፤ ዶ/ር ተሸመም ፕሮጀክቱን በተለያየ አግባብ የደገፉ የተለያዩ ወገኖች እና ተሳታፊዎችን በማመስገን ለሁለት ቀናት የዘለቀው አውደ ጥናት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

 

Back to Front Page