Back to Front Page


Share This Article!
Share
‘አንድ ህዝብ አንድ አገር’ እርባና ቢስ መፈክር!

 ‘አንድ ህዝብ አንድ አገር’ እርባና ቢስ መፈክር!

ሄኖስ አቤል

ጳጉሜ ፪ ቀን ፪፻፲ ዓ.ም

ምዕራፍ ፩

ክፍል ፩

ለአንድነት፣ ለፍቅር ለጋራ ብልጽግና የጋራ ጠንካራ አገር እንዲኖር ተብሎ እንጂ የአማራ ልሂቃን የየትኛውም ብሔር ወዳጅ ሆነው አያውቁም፡፡ በእርግጥ እንዲሆኑም አይገደዱም፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የአማራ ልሂቃን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ሲያፈርሷት ሌሎች ሲጠግኗት የኖረች አገር ናት፡፡ አሁን ኢትዮጵያን ለማዳን ተብሎ የሚከፈል መስዋእት አክትሟል፡፡

“አንድ ህዝብ አንድ ሀገር” የሚለው መፈክር በርካታ ዓመታት ወደ ኋላ መልሶ እ.አ.አ 1930ዎቹ በጀርመን ምድር አዶልፍ ሂትለር ናዚን በሚመራበት ወቅት “Ein Volk, Ein Reich, Ein Fuhrer” በእንግሊዘኛው “One people, One Nation, One Leader” የሚለው መፈክር ያስታውሰናል፡፡

በዚህ መፈክር አገሮች ተወረዋል፤ ንፁሃን ሰዎች ተገድለዋል፤ በእስራኤላውያን ላይ የዘር ማጥፋት አሰቃቂ ግፍ ተፈጽሟል፡፡ አንድ ህዝብ አንድ አገር በሚለው መፈክር ውስጥ “አንድ ህዝብ” የሚል መርዛማ ቃል ብዙሀነትን የማስተናገድ ባህሪም ሆነ መርህ የለውም፡፡ በህበረ ብሔራዊ አገር ውስጥ የትኛው ህዝብ ነው? አንድ ህዝብ ለሚለው ጥያቄም ምላሽ የለውም፡፡

Videos From Around The World

በዚህ አስተሳሰብ ሳቢያ ጀርመን በአጎራባች አገሮች ያሉ ‘ጀርመናውያን’ ወደ አንድ ለመሰብሰብ፤ ‘በደም’ ጀርመናውያን ያልሆኑ እስራኤላውያን አገር እንዲለቁ፣ ካምፕ ውስጥ እንዲከለሉ፣ እንዲታፈኑና እንዲገደሉ አደረገች፡፡ ይህ ‘አንድ ህዝብ’ የሚለው መፈክር ብዘሀነትን ያለማስተናገድ አንድ ባህሪው ነው፡፡ በህብረ ብሔራዊ ሀገር ‘አንድ ህዝብ’ የሚል አስተሳሰብ አፋኝ፣ ጨቋኝ፣ አግላይና ወራሪ አስተሳሰብ ነው፡፡ በዚህ መፈክር ምክንያት ጀርመን አገራትን ወራለች፡፡

‘አንድ ህዝብ አንድ ሀገር’ በተለይም ‘አንድ ህዝብ’ የሚለው መፈክር ባለንበት ዘመን በጀርመን ምድር ሽብርን ማነሳሳት ተደርጎ ስለሚቆጠር የሚያስወነጅል አፀያፊ ዓረፍተ-ነገር ነው፡፡ ምክንያቱ አንድ ህዝብ የሚለው አግላይና ብዝሀነትን የማይቀበል ብቻ ሳይሆን ከአንድ ህዝብ ውጪ ያሉ ህዝቦች አደጋ ላይ የሚጥል፤ ማንነቶችንና ልዩነቶችን የሚጨፈልቅ አንድ ብሔር የሌላን ማንነት እንዲለብስ የሚያስገድድ አረሜናዊ ሀሳብ ነው፡፡

በ’አንድ ህዝብ’ መፈክር የጀርመን ናዚ (ሂትለር) በእስራኤላውያን ላይ የፈፀመው ግፍ ለአብነት ለማንሳት ያህል እንጂ “አንድ ህዝብ” የሚለው ዓረፍተ-ነገር በራሱ አደገኛ እና አፍራሽ ነው፡፡ “አንድ ህዝብ” የሚል ፈሊጥ ብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የማያቅፍ፤ ማንነቶችን የሚያንኳስስ፤ አንድ መለዮ እንዲኖር የሚታትርና ለየት ያሉ አስተሳሰቦችና ማንነቶች የሚጠየፍ አምካኝ አስተሳሰብ ነው፡፡  

አገራችንን ጨምሮ በዓለማችን የተከሰቱ አሰቃቂ ድርጊቶች በድጋሚ በአገራችን እንዲከወኑ የሚሰብኩ በርካታ የአማራ ልሂቃን መኖራቸው ግልጽ በመሆኑ ጉዳዩ በንቃት ሊታይ የሚገባው ነጥብ ነው፡፡ የአማራ ልሂቃን ዘር ማጥፋት ዘመቻቸውን ጀመሩት እና ተገበሩት በቅማንት ላይ አይደለም፡፡ የአማራ ልሂቃን የዘር ጭፍቸፋ የፈፀሙት በትግራይ ህዝብ ላይ አይደለም፡፡ ከሁሉም በፊት የአማራ ልሂቃን በአንድ ዘር ላይ አሰቃሲ ተግባር የፈጸሙት በኦሮሞዎች ላይ ነው፡፡

ከዚህ በመቀጠል በትግራይ ህዝብ ላይ ዘመቱ፡፡ አቆሳቆሉ፣ ለስደት ዳረጉት፣ ለረሀብና ለእርዛት አጋለጡት፣ ከእንግሊዝ ጋር በማበርም አጋዩት፤ በአውሮፕላን በቦምብ ናዳ አቃጠሉት፤ ደሙን አፈሰሱት፡፡ በይቅርታ ታለፉ፡፡ የአማራ ልሂቃን ግን የደም ሰው ማፍሰስ ሱስ ስላለባቸው አሁንም ሁሉም ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የሚተዳደሩበትን ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማፍረስና ዳግም በደም ለመራቸት አጀንዳ ቀርፀው በሂደት ላይ ናቸው፡፡  

ባለፉት 27 ዓመታት ዕድሉ አላገኙም እንጂ ዕድሉ ቢገኝ ኖሮ የአማራ ልሂቃን የጥቃት ሰለባ የሚያደርጉት ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቢሆንም ቀዳሚ ትኩረታቸው የትግራይ ብሄር ላይ መሆኑ ገሀድ ነው፡፡ በእነሱ እሳቤ የትግራይ ህዝብ በሆነ ምክንያት አንገቱን የሚደፋ ህዝብ አይደለም፤ ብለው ስለሚያምኑና እውነትም ስለሆነና የትግራይ ህዝብ ፋሺስታዊ ተግባራቸውን ስላስውረደባቸው (Abort ስላደረገባቸው) የትግራይ ህዝብ ቀና እንዳይል ማድረግ ከቻሉ ሌሎች ከትግራይ ህዝብ ይማራሉ በሚል ብኩን ክርክር የትግራይ ህዝብ ለማጥፋት ሌት ተቀን ሲለፉ ይታያሉ፡፡ አሁን ይንን ስሌት አይሰራም፡፡ እንኳን አሁን ያኔ ድሮ ድሮም የትግራይ ህዝብ አልጠፋም፡፡ አሁን የትግራይ ህዝብ ብቻውን አይደለም፡፡ ሌሎች ጭቁን ህዝቦች እራሳቸውን ቀና አድርገው በማንነታቸው ኮርተው እየኖሩ ነው፡፡ ኦሮሞ፣ ቅማንት፣ አገው፣ ጋፋት፣ አርጎባ፣ ዓፋር እና ሌሎችም ነቅተው የሚሆነውን እየተከታተሉ ነው፡፡  

በአማራ ልሂቃን ትምክህት ምክንያት በአገራችን ታሪክ የማይረሳው፣ መቼም ቢሆን ከኦሮሞዎች ህሊና ሊወጣ የማይችል በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመ ግፍ ከአውደ መዛግብት  መገንዘብ ይቻላል፡፡ አጼ ምንሊክ በኦሮሞዎች ላይ የፈፀመው ዘር የማጥፋት ጥቃት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊያወግዙት የሚገባ ድርጊት መሆኑ ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ የሚገባው አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ አንዱ ጨላማ ገጽታችን ነውና፡፡ አሁን ዳግማዊ አጼ ምንሊክ በህይወት የለም፡፡ የአጼ ምንሊክ ርዝራዥ ግን መርዙ ከደማቸው ባለመውጣቱ ምክንያት አሁንም ድረስ ሰላማችንና አንድነታችንን ሲያደፈርስ ይታያል፡፡

የሚገርመው አንድ ህዝብ አንድ አገር የሚለው ቀረርቶ ከ27 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አማራ እንዲሆኑ ይገደዱበት የነበረ መፈክር ከመቃብር ሥር አንሰራርቶ ብቅ ሲል ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የአንድነት፣ የይቅርታ እና የመደመር እሳቤ ሽፋን አድርጎ ትምክህተኛው ኃይል ህዝቦችን በግፍ ለገደሉና ትምክህተኞች ሀውልት እንዲቆምላቸው ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ በተፃራሪው በትምክህተኛው ኃይል በግፍ የተጨፈጨፉ ኦሮሞዎች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በልጅ ልጆቻቸው የቆመው የአኖሌ ሀውልት እንዲፈርስ ይጠይቃሉ፡፡ ተአምረኛዋ አገር፡፡ የትምክህተኛው ኃይል እምነት “ የእኔ ታሪክ የጋራ ነው፤ ያንተ ታሪክ የለም” የሚል ነው፡፡ የአማራ ትምክህተኛው ልሂቅ እምነት “የእኔ ሀብት የእኔ ነው፤ የአንተም ሀብት የእኔ ነው” የሚል ወራሪ እምነት ነው፡፡ ሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸው ታሪክ ያላቸው አይመስለውም፡፡

በኢትዮጵያ ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የታየው ድራማዊ ትዕይንት አማራ ክልል ለአማራዎች ብቻ በሚል ድርሰት ብዙ ህዝብ ተገድሏል፤ ብዙ ህዝብ ተፈናቅሏል፤ የብዙ ህዝብ ንብረት ተዘርፏል፡፡ ብዙ ብሄር ላይ ያነጣጠረ ዘረኛ እርምጃ ተወስዷል፡፡ በመሆኑም በሺዎች የሚቆጠሩ የቅማንት ብሄረሰብ፣ በመቶዎች ሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ግፍ ተፈጽሟል፡፡ ይህ ግፍ ሲፈጸም በክልሉ መንግስት እየተመራ እንደተካሄደ የሚያረጋግጡ መረጃዎችና ማስረጃዎች በርካታ ናቸው፡፡

የአማራ ትምክህተኛ ልሂቃን በትዕቢት ተወጥረው የአማራ ህዝቦች የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የማህበራዊ ፍትሕ ጥያቄዎችን ከመፍታት ፈንታ ሚስኪኑ የአማራ ህዝብ ከሁሉም ብሄሮች ጋር ለማባላት አጀንዳ ቀርጸው ወደ ጥፋት እየመሩት ይገኛሉ፡፡ በክልሉ የሚገኙ የአገው፣ የቅማንት፣ የጋፋት፣ የኦሮሞ፣ የአርጎባ፣ የትግራይና ሌሎችም ላይ የዘር ፍጅት እየሰበኩና እኩይ ዓላማቸው እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡

ይህ ከመጀመሪያው ዙር የዘር ማጽዳት ተግባር የመጨረሻ ነው፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያ ሥራዎች በተገቢና ስኬታማ በሆነ መንገድ አከናውነዋልና፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሥራዎች ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ አንድ አስተሳሰብ መፍጠር ነው፡፡ በህወሓት ስም የትግራይ ህዝብ ላይ ጥላቻ እንዲነግስ ማስቻል፡፡ ተሳክቷል፡፡ ሂትለር በጀርመናውያን ጭንቅላት ውስጥ እስራኤላውያን ላይ የነዛው ጥላቻ እንደማለት ነው፡፡ ስኬታማ የጥፋት መንገድ እንደመራ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያ ስራዎች የጥላቻ ንግግሮችና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳዎች በአማራ ልሒዋቃን ተደርሰው፣ በአማራ ልሒቃን ተተውነው፣ ለአድማጭ ተመልካች ሲተላለፉና ሲዘመሩ ቆይተዋል፡፡

ከዚህ በመቀጠል በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶር. አብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍ በሚል ሽፋን በተካሄደ ፈንጠዚያ ላይ መሬት የመውረርና የመስፋፋት ህልም ያላቸው መፈክሮች ተንፀባርቀዋል፡፡ ለአብነትም የአማራ ድንበር ተከዜ ነው! ራያ የአማራ ነው! ወልቃይት የአማራ ነው! መተከል የአማራ ነው! ወለጋ የአማራ ነው! ሸዋ የአማራ ነው! የሚሉ መፈክሮች ተበራክተው ተንፀባርቀዋል፡፡ እነዚህ መፈክሮች በክልሉ የመንግስትና የፖለቲካ ክንፎች ቁንጮ አመራሮች ድጋፍ እና አይዞን ባይነት የተከወኑ ናቸው፡፡ የአማራ ልሂቃን ይህንን አጀንዳ የቀረፁትና በተደራጀ አኳሃን የመሩት ስለመሆናቸው በመድረክ ንግግሮቻቸው አመላክተዋል፡፡ በመገናኛ ብዙሀን ላይ ቀርበውም ሲያስተባብሉ አይታይም፡፡ ከዚህ ባሻገር በመድረኮቹ ላይ ውስጥ አላስፈላጊ ስሜት ኮርኳሪ የፕሮፖጋንዳ ንግግሮች በገዱ አንዳርጋቸውና በደመቀ መኮንን ተላልፈዋል፡፡

ከዚህ አለፍ ብሎ ደግሞ አሁን በግላጭ የወራሪና የአስፋፊነት ዘመቻውን ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የኤርትራን ሉአላዊ አገርነት ገደል በመክተት፤ በኤርትራ ውድ ልጆች የተገኘን የነፃነት ድል ወደ ኋላ ለመመለስ ለአንዴና ለመጨረሻ የተጣለው ኤርትራን ያካተተ የድሮ ካርታ ተሸክመው በየአደባባዩ መዞር ጀምሯል፡፡ የአማራ ልሂቃን የማይቀይሱት የጥፋት መንገድ ምን አለ? እነዚህ ልሂቃን የአማራ ህዝብ፣ የአማራ ወጣት፣ የአማራ አርሶ አደር ከጎረቤት አገር ሱዳን ለማጋጨትና ማገዶ ውስጥ ለመጨመር የተንኮል ሴራቸውን ቀጥለውበት አርሶ አደሮችን በማስታጠቅ አጥፊ አጀንዳ ላይ ተጠምደዋል፡፡

የራሷ አሮባት….! እንዲሉ የአማራ ልሂቃን በአማራ ክልል ውስጥ ያለው ሁሉን አቀፍ ቀውስ ማብረድ አቅቶዋቸው የጎረቤት ህዝቦች ወደ እነሱ ዳንኬራ በአባልነት ለመመልመል ሲደክሙ ይታያሉ፡፡ በደቡብ ወሎ በወረ ኢሉ ያለው የእሳት ሰደድ ወይም ቃጠሎ ወይም የህዝብ ናዳ ማብረድ አልቻሉም፡፡ የቅማንት ሕገ-መንግስታዊ መብት መመለስ አልቻሉም፡፡ የአገው ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ ሊያስተናግዱ አልቻሉም፡፡

ይህንን የውስጥ ትኩሳት ለማስፈንጠር የሚደረግ መወራጨት እራሳቸውን እንደሚበላቸው እሙን ነው፡፡  በቅርቡ ብሔረ አማራ ‘ዴሞክራሲያዊ’ ንቅናቄ (ብአዴን) ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አካሂዶ ካስተላለፋቸው የአቋም መግለጫ ነጥቦች አንዱ አሁን በሕገ-መንግስቱ መሠረት የተደረገው የክልሎች አከላለል እንደገና እንዲታይ የሚል ነበር፡፡ የዚህ የአቋም መግለጫ ዓላማው አሁን የተፈጠረው ሁከት የፌዴራል ሥርዓት የፈጠረው ነው ለማለት ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ሁለንተናዊ ቀውስ እንደ መልካም ዕድል ተጠቅሞ አጠቃላይ ሸዋ፣ ፊንፊኔና ከሚሴን ከኦሮሚያ፣ ወልቃይት፣ ራያ፣ ሁመራ እና ተከዘ ከትግራይ፣ መተከልን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ በመውረር ብሄር ብሄረሰቦችን በማንበርከክ ከዚህ ቀደም የነበረው ያረጀና ያፈጀ አሀዳዊት ኢትዮጵያ በላያችን ላይ ለመጫን ያለመ ቅዠት ነው፡፡ ኢትዮጵያውነት እምነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በተራ ስብከትና በተራ የአንድነት መዝሙር የሚገለጽ አይደለም፡፡ ብሔር ብሄረሰብና ህዝብ በእኩል ያማታስተናግድ ኢትዮጵያ የማንንም ሀገር ልትሆን አትችልም፡፡

ለዚህ ነው የአማራ ልሂቃን በአመዛኙ የየትኛውም ብሔር ወዳጅ ሆነው አያውቁም፡፡ በእርግጥ ወዳጅ እንዲሆኑም አይገደዱም፡፡ ነገር ግን ለዚህ ነው የአማራ ልሂቃን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው የሚባለው፡፡ ከአናሳው የአማራ ብሔር ወይም የአማራ ትምክህተኛ ልሂቅ በስተቀር በዚህ ሀሳብ የማይስማማ ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለአንድነት፣ ተከባብሮ አብሮ ለመኖር ካለው ጽኑ ፍላጎት፣ ይቅር ባይ በመሆኑና የወደፊቷ የበለጸገች ኢትዮጵያ አማትሮ በማየት እንጂ የአማራ ልሂቃን አይደለም በአንድ አገር አብሮ ለመኖር ለጉርብትናም እጅግ አስቸጋሪና መሰሪ መሆናቸው ያውቃሉ፡፡

አንድ ህዝብ! አንድ ሃይማኖት! አንድ ሀገር የሚለው መፈክር መዘዙ ብዙ ነው፡፡ አንድ ህዝብ አንድ ሀገር የሚለው መፈክር ከዚህ ቀደም ተሞክሮ ህዝቦችን የበላ፣ የህዝቦችን ደም ፉት ብሎ የመጠጣ፣ ህዝቦችን በቂም በቀል በጎሪጥ ያስተያየ፣ ቁርሾ የዘራ፣ ሞትንና መፈረካከስን የሚጋብዝ የአጋንንት ጥሪ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚያውቁት ሀቅ ነው፡፡ በመሆኑም በተራዘመ የትጥቅ ትግል ድባቅ መተውታል፡፡ ይሁን እንጂ በአማራ ልሂቃን ዘንድ ይህ አስተሳሰብ እንደ አዲስ አገርሽቷል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሊተገበር ቀርቶ ሊታሰብ የማይገባው፤ ሊወገዝ ሚገባው የከሰረ አስተሳሰብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ብዙ ህዝቦች አንድ አገር እንጂ ያ ኋላ ቀር አምካኝ አስተሳሰብ ከቶውንም ሊሳካ የማይችል ቅዠት ነው፡፡ ነገር ግን ይህን አይተገበርም ማለት በኃይል ለመተግበር የሚሞክር ኃይል አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ አይተገበርም የምንልበት ምክንያት ግን አላስፈላጊ መስዋእት ተከፍሎ  ኢትዮጵያ የምትባል አገር ግብአተ መሬቷ እውን ይሆናል፡፡ ስለሆነም አስተሳሰቡ አፍራሽ ነው፡፡

የሆኖ ሆኖ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያለፈውን በደል፣ ያለፈውን ጭቆና፣ ያለፈውን ግፍ አልፈው፣ ይቅር ብለው አሁን አንዲት ጠንካራ፣ የኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በጥናትና ምርምር የበለጸገች፣ ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩል የምታስተናግድ ቤት የምትሆን፣ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁለተኛ ተፈጥሮ የሆነባት የተከበረች አገር ባለቤት እንዲሆኑ ይመኛሉ፡፡ የኢትዮጵ ህዝቦች አንዲት የበለጸገች የጋራ ቤት ኢትዮጵያ ከመመኘት አልፈው በቃል-ኪዳናቸው

እኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን በነፃ ፍላጎታችን፣ በህግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤ ይህ ዓላማ ከግብ ለማድረስ፣ … ኢትዮጵያ ሀገራችን የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት ሀገር በመሆንዋ፣ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፣ መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፣ ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነፃነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ አስፈላጊነት በማመን፣ በትግላችንና በከፈልነው መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ

ባለፉት ሃያ ሰባት (27) ዓመታት ከፍተኛ ርብርብ በማካሄድ ኢትዮጵያ በታሪኳ ያላየችውን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፈ ብዙ ለውጥ ሀዲድ ውስጥ እንድትገባ ማድረግ ችለዋል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ረገድም ቢሆን ከፍተኛ ርቀት መጓዝና ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ እነዚህ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህልውናቸውን በትግላቸው ባያረጋግጡ ኖሮ የተገኙ አኩሪ ውጤቶች ማስመዝገብ ቀርቶ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከመፅሐፍ ቅዱስ በስተቀር ከታሪክ መዛግብት ትሰረዝ ነበር፡፡

ይህ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለውጥ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝቦች የነቃ ተሳትፎ ባያክሉበት ሊሳካ አይችልም፡፡ እንዲሁም ይህንን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የነቃ ተሳትፎ ከሚመራ ትክክለኛ የፖለቲካ ኃይል ውጪ እውን ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደር የለሽ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስለመሆኑ አስመስክሯል፡፡ በኢትዮጵያ የተመዘገቡት ዘርፈ ብዙ ለውጦች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ረገድም በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ላይ ከተመዘገቡት ድሎች ያልተናነሰ ድል ተመዝግቧል፡፡ በኢትዮጵያ የተመዘገበው ዘርፈ ብዙ ልማት መልካም እንደሆነ ከሞላ ጎደል ምልዓተ ህዝቡ የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡

ይሁንና የአማራ ልሂቃን ጥላሸት ሲቀቡት ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት አገሪቱ በአማራ ልሂቃን በተመራችባቸው ጊዜያቶች ሁሉ አገሪቱ ቁልቁል የምትሄድ አገር አሁን ወያኔ የሚባል ተአምረኛ እንዴት ተአምር ይፈጥራል በሚል ምቀኛ አመለካከት የተፈጠረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳሆን የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነት ሕገ-መንግስታዊ መብቶቻቸው መታፈን ጀምሯል፡፡ በመደመርና አንድነት ሥም ብሔሮች፣ ብሐረሰቦችና ህዝቦች አንገታቸው ቀና እንዳይሉ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እራስ በራስ የማስተዳደር፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ህገ-መንግስታዊ ሥልጣን በአደባባይ ሲነጠቁ ማየት የዕለት ተዕለት ክዋኔ ሁኗል፡፡ ይህ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡

በዚህ ምክንያት አሁን ባለንበት አገራዊ ቀውስ በርካታ ፖለቲከኞች፣ በርካታ ሙሁራን፣ በርካታ ተንታኞችና በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢትዮጵያ በመስቀላዊ መንገድ ላይ ትገኛለች ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ከመስቀላዊ መንገድ አልፋ ገደል አፋፍ ላይ ትገናለች ይላሉ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ኢትዮጵያ ያበቃላት አገር ተስፋዋ የተሟጠጠ አገር ሲሉ ይገልጿታል፡፡ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ አስተያቶች ደግሞ ኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግስት የሌለባት፣ የዜጎች ደህንነት የማይጠበቅባት፣ ሰዎች በጠራራ ጸሐይ የሚገደሉባት፣ ለዜጎቿ የእግር እሳት የሆነች፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ለውጭ ኃይሎች አሳልፋ የሰጠች ክብሯን ያስደፈረች አገር በሚልም ያስቀምጧታል፡፡ 

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ

1.   አንድ ህዝብ አንድ አገር!

2.   ብዙ ህዝቦች ብዙ አገሮች!

3.   ብዙ ህዝቦች አንድ አገር! የሚሉ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ጉዳዮች ከፊት ለፊታችን ተቀምጠዋል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ እንደ አዲስ መሠራት ያለባት አገር ናትን?  

 

1.  አንድ ህዝብ አንድ አገር!

የ‘አንድ ህዝብ አንድ አገር’ አስተሳሰብ መነሻ ሀሳብ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ጠንካራና የምትከበር አገር ልትሆን የምትችለው የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የባህል ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው አንድ ህዝብ በመሆን እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት አይቀበልም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ደካማ ሀገር ፈጥሯል ብሎ ያምናል፡፡

ይሁን እንጂ ከፌዴራላዊ ሥርዓት ውጭ ያሉ ሁሉም ዓይነት የመንግስት አስተዳደሮች ተሞክረው ከስረዋል፡፡ ከፊውዳላዊ እስከ አምባገነናዊ ወታደራዊ መንግስት ተሞክረዋል፡፡ ሁሉም ከሽፈዋል፡፡ አሃዳዊ ስርዓት በባህሪው ብዙሀነትን አይቀበልም፡፡ ብሁሀነት እንደ ስጋተ የሚመለከት ነው፡፡ ከ27 ዓመታት በፊት በነበሩ ስርዓተ መንግስታት በተግባር ተሞክሮ ኢትዮጵያ በመፍረስ አፋፍ ላይ የጣላት የመንግስት አስተዳደር ዓይነት ነው፡፡ አስተሳሰቡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በክንዳቸው ገርስሰውታል፡፡

አሁን እንደገና ማንሰራራቱ ኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ እንድትፈርስ የሚያደርግ ነው፡፡ በአጉል መፈክር አንድ የምትሆን አገር የለችምና፡፡ አስተሳሰቡ በየትኛውም መስፈርት ሊሳካ የማይችል ይልቁንም ህዝቦች እርስ በራሳቸው የሚያባላ አደገኛና መርዛማ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ አደገኛና መርዛማ የመሆኑ ማረጋገጫ በአንድ ምዕራፍ ተሞክሮ ህዝቦች የተሰቃዩበት፣ በማንነታቸው፣ በባህላቸው፣ በቋንቋቸው የተዋረዱበት፣ ቆርሾ፣ ቂምና በቀል የያዙበት አስተሳሰብ ነው፡፡ በመሆኑም ዳግም እንዳያንሰራራ በርትተው ስለሚፋለሙትና ፍልሚያው በሀሳብ ብቻ ሳይሆን በጦር መሳሪያ የታገዘ ስለሚሆን ህዝብ የሚጨርስ በደም የሚያራጭ አስተሳሰብ ነው፡፡ በመሆኑም ነው በየአካባቢው አሁንም ነፍጥ የሚያነሱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብቅ ብቅ እያሉ ያሉት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ይህ አስተሳሰብ ከአንድ አካባቢ ወይም ከአንድ አካባቢ በተወለዱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የአንድ ብሔር ተወላጆች ነን ባይ ልሒቃን የሚቀነቀን አፍራሽ ምልከታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ በጋራ መኖር ግን ይችልበታል፡፡ ይህም ቢሆን በተለመደው አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሆነው ለመኖር ከቶውንም ፍቃደኛ አይደሉም፡፡  ይልቁንስ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሁለተኛው አማራጭ እንዲያዩ ያደርጋቸዋል፡፡

2.  ብዙ ህዝቦች ብዙ አገሮች!

የዚህ አስተሳሰብ መነሻ ሀሳብ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድ ህዝብ አንድ ሀገር በሚለው መፈክር በኢትዮጵያ ምድር በማንነታቸው ያፈሩበት፣ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የታዩበት፣ በቋንቋቸው እንዲናገሩ የተከለከሉበት፣ ከሰው በታች የሆኑበት፣ የተጨቆኑበት ብሔራዊና የመደብ ጭቆና ያዩበት በመሆኑ አምርረው የሚጠየፉት አስተሳሰብ በመሆኑ የራሳቸው ዕድል በራሳቸው መወሰን ስለሚፈልጉና ስለሚያምኑበት መገንጠልን ማዕከል አድርጎ ሚቀነቀን አስተሳሰብ ነው፡፡ መነሻው ታሪካዊ ቁርሾና በደል ነው፡፡

ይህ አስተሳሰብ በየትኛውም መለኪያ ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡ ትክክለኛና መስዋእት ያስከፍል ይሆናል እንጂ ጊዜ ይወስድ ይሆን እንጂ በተግባር በዓለም አገራት የታየ የዓለም ታሪክ አካል ነው፡፡ አንድ ህዝብ አንድ አገር የሚለው አስተሳሰብ ለዚህኛው አስተሳሰብ መሰረት ነው፡፡ በአንድ ህዝብ አንድ ሀገር ዲስኩር የተገነባች አገርም የለችም፡፡ ብዙ ህዝቦች ብዙ አገሮች የሚለው አስተሳሰብ በእኩልነት የሚያምን አስተሳሰብ ነው፡፡ በእኩልነት አብሮ መኖር ይቻላል የሚል እሳቤ አለው፡፡ በእኩልነት አንድ ጠንካራ አገር መመስረት ይቻላል የሚል ነው፡፡

የብዙ ህዝቦች ብዙ አገሮች አስተሳሰብ ሌላኛው ገፅታው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከአመሰራረቷ ጀምሮ ችግር ያለባት፣ የአንዱ ብሔር ልሂቃን በሌሎች ብሔር ብሔረሰብና ህዝብ ላይ በታሪክ አጋጣሚ በተቀዳጁት የበላይነት በወረራ፣ በቅኝ ግዥ የተመሰረተች አገር ከመሆኗ አልፎ የኢትዮጵያ ትርጉም አከራካሪ ነው የሚል አስተሳሰብም አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ማለት አማራ ማለት ነው የሚለው ቀረርቶና ሽለላ ለዘመናት የቆየ አውዳሚ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ትርጉም እንደገና ሊታይ ይገባል፤ እንደ አዲስ ሊቀየስ ይገባል ብሎ ያስባል፡፡

ስለሆነም ይላሉ የዚህ አስተሳሰብ አቀንቃኞች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት ተጠቅመው የየራሳቸው አገር መስርተው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሥልጣናቸውን በማያወላዳ መልኩ አሳይተው የኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት (United States of Ethiopia/ USE) መመስረት ይቻላል የሚሉ ናቸው፡፡ 

ይህ አስተሳሰብ የሚያጓጓና ሄዶ ሄዶም ውጤታማ የሚሆን አስተሳሰብ ነው፡፡ በእኩልነት ተከባበሮ አብሮ መኖር ካልተቻለ የየራስ አገር መስርቶ ማየት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በእርግጥ መገንጠል አማራጭ አይደለም፡፡ መገንጠል አማራጭ ሳይሆን ህዝቦች ተገደው የሚገቡበት መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳን ተብሎ የሚከፈል መስዋእት አክትሟል፡፡

  1. ብዙ ህዝቦች አንድ አገር!

የዚህ ምልከታ መነሻ ሀሳብ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ችግሮችን፣ ግፎችን፣ ጭቆናዎችን፣ በደልን፣ አንዱ የበላይ ሌላኛው የበታች መኖሩን እውቅና በመስጠት በታሪክ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ምድር የተፈፀሙ ስህተቶችን እንዳይደገሙ በመከላከል ከላይ የተቀመጡትን ክርክሮች የሚያስታርቅ አስታራቂ ምልከታ ነው፡፡ ይህ ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ተሞክሮ ተነፃፃሪ ሰላም (Relative Peace)፣ ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድም ብዙ ርቀት መጓዝ ችሏል፡፡

ይሁንና ብዙ ህዝቦች አንድ አገር የሚለው ጥልቅና አገርን የመገንባት (Nation Building) ፍልስፍና በአሁኑ ወቅት ከባድ ፈተና ላይ ወድቋል፡፡ አንድ ህዝብ አንድ አገር የሚለው መሰሪ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ያደረጋቸው ይመስላል፡፡ አንዳንዱ ብሄሮች ደግሞ የነፃነት እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡

የሶማሊ ክልል ህዝብ በወታደራዊ ኃይል ታፍኖ ተይዟል፡፡ ለጊዜው የተረጋጋ ይመስላል፡፡ ነገር ግን የተቀበረ ፈንጅ ነው፡፡ ከፊት ለፊታችን የሚፈነዳ ቦምብ! የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ህዝብ በወታደራዊ ኃይል ማንበርከክ አይቻልም፡፡ ማእከላዊ መንግስት በክልል ስልጣን ሕገ-መንግስቱን ተላልፎ ጣልቃ መግባትና ክልሎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ  የማስተዳደር ተግባር ጀምሮታል፡፡    

አማራ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው ቀውስ የሚያቧራ አይመስልም፡፡ የአማራ ልሂቃን ይንህንን ቀውስ ከማርገብ ፈንታ ወጣቱ ወደ እሳት መማገድ ምርጫቸው ሁኗል፡፡ አመጹ ተጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል፡፡ የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሀንም ሆነ ጋዜጠኞቹ ከጎረቤት ክልል ህዝብ ለማጋጨት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ የአገሪቱ ልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሀንም እንደዛው፡፡

ኢትዮጵያ መንግስት አልባ እየሆነች መትታለች፡፡ አብዛኛዎቹ ክልሎች አመፆችን መቆጣጠር ተስኖዋቸዋል፡፡ የአንድነት ሰባክያን ለውጥ ማምጣት አልቻሉም፡፡ ሕግና ሥርዓት እየተከበረ አይደለም፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ደጃፉን በጥንቃቄ ሊጠብቅ ይገባል፡፡ የሚደርስለት መንግስት የለም፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት አስጊ ሁኔታ መውጣት የምትችለው

1.   ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በተሟላ ስነ-ምግባር (discipline) ሲተገበር፤

2.   ከፌዴራል ከአንዳን የክልል መንግስታት ጋር ያለው ሴረኛ (conspiring) ግንኙነት ነፃ በሆነ መንገድ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጀመር

3.   አሁን ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በየትኛውም መልኩ የማይነካ መሆኑን በሚመለከተው አካል ማስተማመኛ መስጠትና በጥብቅ ስነ-ምግባር ሲተገበር፡፡ የፌድራል መንግስት በክልሎች የሚያደርገው ኢ-ሕገ-መንገስታዊ ጣልቃ ገብነት ሲያቆምና በወታደራዊ ኃል አገርን አቆያለሁ ከሚል እብሪተኛ አስተሳሰብ ነጻ ሲሆን፤

4.   የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትና ስልጣን በአስቸኳይ መተግበር ሲጀምሩና

5.   መንግስት አገሪቱ የምትመራበት አቅጣጫ ምልዓተ-ህዝቡ፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በግልጽ እንዲያውቁት  ማድረግ ሲችል ነው፡፡      

ክፍል ፪ ይቀጥላል

 

Back to Front Page