Back to Front Page


Share This Article!
Share
ይድረስ በተለይ ለዶ/ር ብሩክ ሀይሉ

ይድረስ በተለይ ለዶ/ር ብሩክ ሀይሉ

 

ከበደ ዮሃንስ 10-28-18

“Voice of Assenna” የተሰኘ ጣቢያ ዶ/ር ብሩክ ሀይሉ ከአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም ጋር በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ላይ ያደረጉትን ቃለምልልስ ወደትግርኛ ተርጉሞ ያቀረበዉን አዳምጫለሁ። ዶ/ር ብሩክ በቃለምልልሱ የሰጡት ሀሳብ በዚህ ጉዳይ ላይ ከ18 ዓመት በፊት ሰጥተዉት ከነበረዉ ሀገራዊ ጥቅምና ፋይዳ አንፃር ስመዝነዉ ለእርሳቸዉም ሆነ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ለሚተጋ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚከተለዉን ጥያቄ አዘል አስተያየት መጫር አስፈላጊ ሆኖ ስለተሰማኝ ላኩላችሁ

 

Videos From Around The World

የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ስለጉዳዩ እና ሊወሰድ ስለሚገባዉ እርምጃ ምሁራዊ አስተያየት ከሰጡት ቀዳሚ ምሁራን መካከል ዶ/ር ብሩክ ሀይሉ አንዱ እንደነበሩ አስታዉሳለሁ። በወቅቱ ዶ/ር ብሩክ  የህንድን እና የፓኪስታንን ለዘመናት ያልተፈታ የድንበር ግጭት በማስታወስ ጉዳዩ ለሀገራቱ ነቀርሳ ሆኖ መቀጠሉን ጠቁመዋል። ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ተገዳ ወደጦርነት ከገባች ጡርነቱን በማያዳግም ሁኔታ አጠናቃ በታሪክም ሆነ በህግ የሚገባትን መብት ማረጋገጥ እንደሚገባት አስረግጠዉ ተናግረዉ ነበር። ይህን ማድረግ ካልቻለች ወረራዉና ዉጤቱ ኢትዮጵያን ልክ እንደነቀርሳ በሽታ ሲያመነምናት ሊኖር እንደሚችል ስጋታቸዉን አስረድተዋል። በእርግጥም የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከደፈረበት ጊዜ ጀምሮ ያሳለፍናቸዉ 20 ዓመታት በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበረዉ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ምክንያት ዶ/ር ብሩክ እንዳሉት ለሀገራችን ከፍተኛ ነቀርሳ ሆኖ ሰብአዊ ፍጥራችንን እና ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን አመንምኖታል። ማለትም ወደን ሳይሆን ተገደን በገባንበት ግጭት ምክንያት ነቀርሳ ሆኖን ቆይቷል። በወቅቱ ዶ/ር ብሩክ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሰጡት ምሁራዊ ማብራሪያ ኢትዮጵያ ጡርነት ዉስጥ ከገባች በአጭር ጊዜ ዉስጥ ማጠናቀቅ እንዳለባት ሲመክሩም በታሪክም ሆነ በህግ የሚገባትን የግዛት አካል በዚሁ አግባብ ማረጋገጥ ይኖርባታል የሚል አንደምታ ነበረዉ። ከዚህ አኳያ ዶ/ር ብሩክ ከ18 ዓመት በፊት ጉዳዩ ነቀርሳ ሆኖብን እንዳይዘልቅ  እና በህግም ሆነ በታሪክ የሚገባንን ግዛት በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲረጋገጥ ከጠቆሙት አኳያ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተጀመረዉ የኖርማላይዜሽን ሂደት ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳያጋጥም ምን መደረግ አለበት ብለዉ ይመክራሉ?

በዓለምአቀፍ ህግ መሰረት አንድ ቡድን ወይንም ሀገር ባካሄዱት ጦርነት ምክንያት በሀይል የተቆጣጠሩትን አካባቢ ከሌላኛዉ ወገን ጋር ድንበራቸዉ ከየት ወዴት እንደሆነ በመስማማት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፋይል(ዲፖዚት) ባላደረጉበት ሁኔታ ሀይል የነበረዉ አካል ለጊዜዉ አካባቢዉን በመቆጣጠሩ ብቻ “…የተቆጣጠርከዉ ቦታ በሙሉ ያንተ ነዉ…” ማለት ይቻላል? ማለትም ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላ በአሸናፊዉ እና ተሸናፊዉ መካከል ስምምነት ላይ የተደረሰበትና በዓለምአቀፍ ደረጃ እዉቅና ያገኘ የተካለለ ድንበር በሌለበት ሁኔታ የአንድ ሀገር ክልል በጦርነት ምክንያት/በሀይል/ ስለተገነጠለና ተገንጣዩ አካል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደሀገር እዉቅና ስላገኘ ብቻ የጦርነቱ አሸናፊ በመሆኑ በሀይል የተቆጣጠረዉ ክፍል በሙሉ የራሱ ግዛት ነዉ ማለት ይቻላል? እንደሀገር እዉቅና ማግኘት ብቻዉን(ለምሳሌ በኤርትራ ኬዝ) የግዛት ሉአላዊነትን ያረጋግጣል? በዚህ መሰረተሀሳብ ኤርትራ የአሰብ እና የምፅዋ ግዛቶች ባለቤት የምትሆንባቸዉ አመክንዮዎች ምንድን ናቸዉ? ከጦርነቱ መጠናቀቅ እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኤርትራ እንደሀገር እዉቁና ከሰጠ በኋላ የአፋር ህዝብ ወይንም የኤርትራ መንግስት ከደርግ ዉድቀት በኋላ ያስተዳድራቸዉ የነበሩ ሌሎች የድንበር አካባቢዎችና ህዝቦች የኤርትራ አካል ሳይሆኑ የኢትዮጵያ አካል ናቸዉ የሚል የህግም ሆነ የታሪክ መከራከሪያ ላለማቅረብ ምን ይከለክላል? የኤርትራ መንግስት የዛሬ 20 ዓመት በኢትዮጵያ አስተዳደር ስር የነበረዉንና በአሜሪካና በሩዋንዳ መንግስታት ተወካዮች በአስተዳደራችን ስር እንደነበር ያረጋገጡትን ባድመን እና አካባቢዉን የይገባኛል ጥያቄ እንዳነሳበት(ወረራ መፈፀምን ጨምሮ) ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ በጦርነት ሀይል ከተገነጠለች በኋላ በምታስተዳድረዉ አካባቡ ያሉ የወደብም ሆነ ሌሎች አካባቢዎችን በታሪክና በህግ ላይ ተመስርተን የግዛት ይገባኛል ጥቄ ከማቅረብ ምን ይከለክለናል?

 

Back to Front Page