Back to Front Page


Share This Article!
Share
ግልጽ ደብዳቤ ለትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚደንትአቶ ደብረጺዮን ገብረሚካኤል

 

ግልጽ ደብዳቤ ለትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት

አቶ ደብረጺዮን ገብረሚካኤል

 

አብርሃም ከአዲስ አበባ፣ 07-09-18

 

 

ክቡር ምክትል ፕሬዚደንት፣

 

ይህን መልዕክት እንድጽፍልዎ ያነሳሳኝ ለህወሓት ያለኝ አክብሮት እና አድናቆት ነው፡፡ የህወሓት ትግል በኢትዮጵያ ታሪክ ከተመዘገቡ የነጻነት እና የእኩልነት ትግሎች ምን አልባት ታላቁ ወይም ከታላላቆቹ አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የህወሓት ትግል ለመላው ኢትዮጵያዊ የነጻነት እና የእኩልነት ፈር ቀዳጅ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ በየመጽሔቱ እና ጋዜጣው፡- ህወሓት ወይም ወያኔ አገር ሊበጣጥስ ነው፣ አገር ሊያፈርስ ነው፣ የአገሪቱን ሃብት ሊዘርፍ ነው ወዘተ ይባል ነበር፡፡ ህወሓት የትኛውን አገር እንደበጣጠሰ እና እንደዘረፈ እኔ አላውቅም፡፡ በእውነቱ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የሚዘረፍ ሃብት ነበር? የአገሪቱ ካዝና በጦርነት የተራቆተ አልነበረም? እንዴትስ ለእንደዚህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር አንድ ድርጅት እና ታጋዮቹ መቼ እንደሚያባራ በማያውቁት ጦርነት ራሳቸውንም፣ ሕዝባቸውንም ይማግዳሉ? የህወሓት ዓላማ ግልጽ ነበር፤ ሕዝብን ማስቀደም፡፡ እንደ ግለሰብ እጅግ ከማደንቃቸው እና ሚያስቀኑኝም ነገሮች መካከል የህወሓት ትግል ዋናው ነው፤ በህወሓት የትጥቅ ትግል ውስጥ ጽናት ነበር፣ ዓላማ ነበር፤ መስዋዕትነት ነበር፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕዝባዊነት ነበር፡፡

 

አሁን አሁን በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ወደ መልካም አቅጣጫ ይወስዳል ወይስ አይወስድም ለሚለው ጥያቄ እንደ እኔ ጊዜ የሚመልሰው ነው፡፡ መልካም ጅምሮች አሉ፡፡ መስመር የሳቱ የሚመስሉም ነገሮች አሉ፡፡ የአገሪቱ አንጡራ ሃብቶች በውጭ ዜጎች መያዝ የለባቸውም፤ ያ ከሆነ ሃብት አይኖረንም፣ አገራችን በሌሎች ቁጥጥር ስር ትወድቃለች የሚል አቋም ሕዝባዊ እና ጸረ ሕዝብ አቋም ነው ብዬ ለማሰብ ይከብደኛል፡፡ አንጡራ ሃብታችንን ለራሳችን እናቆይ የሚል መሪ፣ እነዚህን ሃብቶች ለባዕድ አገር ባለገንዘቦች መሸጥ ገንዘብ እንደሚያስገኝ ጠፍቶት ወይም ሳያውቅ ቀርቶ ነው አልልም፡፡ እኔ አሁን ይህን መልዕክት ለመጻፍ የፈለግሁት፣ ህወሓት በመላ አገሪቱ ላለው ችግር መንስኤ እና ተጠያቂ ተደርጎ የሚነገረውን በማስመልከት ነው፡፡ አሁን እየሆነ ካለው ስሜት የተቀላቀለበት ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለሕዝብ ቅርብ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን ሊሆኑ ይችሉ ነበር፤ ምን አልባት ቀረብ ያላሉት አገሪቱ ጠንካራ መንግሥት ያስፈልጋታል፣ አመራሩም ጠንከር፣ ኮስተር ያለ መሆን አለበት ብለው ስላመኑ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አመራር ያስፈለገበት ምክንያት ደግሞ የአገሪቱ ስር የሰደደ እና የበዛ ችግር ሳይሆን አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ አቶ መለስ በስቴዲየም እና በአደባባይ ሕዝብ ሰብስበው ስሜት የሚኮረኩሩ ንግግሮች ማድረግ የሚያቅታቸው አልነበረም፤ ችግር ፈቺ አድርገው ስላላዩት ይሆናል እንጂ፡፡ ይህ ማለት ግን ያንን ያህል ሩቅ ሆነው መቆየታቸው ሊተች አይገባም ለማለት አይደለም፡፡

Videos From Around The World

 

በእርግጥ አንድ እጅግ ያሳዘነኝ ነገር አለ፡፡ እርሱም በመገናኛ ብዙሃን እየተነገረ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ነው፡፡ መቼስ ይህ ሁሉ አቶ መለስ ወይም አቶ ኃይለማሪያም ወይም በጠቅላላው የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር እያወቀው የተደረገ ከነበረ እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡ ደርግ ሰው የሚበላ የሕዝብ ጠላት መንግሥት ነበር የሚባለው እንዲህ ዓይነቱን ሰይጣናዊ ተግባር ከቤተ መንግሥት እስከ ቀበሌ በተደራጀ መዋቅር ይፈጽም ስለነበር አይደለም? ፈጻሚው ደርግ ሆነ ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት ሆነ ለውጥ ያመጣል?

 

ክቡር ምክትል ፕሬዚደንት፣ እኔ የትግራይ ተወላጅ አይደለሁም፡፡ ስለዚህ ህወሓት መለወጥ አለበት ብል ድፍረት አድርገው አይውሰዱብኝ፡፡ እኔ እስከማውቀው እና እንደማምነውም ህወሓት ትናንት የሕዝብ ግምባር-ቀደም ተሟጋችና ታጋይ ነበር፤ አሁን ደግሞ ወደ ቀድሞ ማንነቱ መመለስ አለበት፡፡ አዳዲስ መሪዎችን ወደ ፊት ማምጣት አለበት፡፡ ነባር መሪዎች ለአዲስ ትውልድ መሪዎች ቦታ መልቀቅ አለባቸው፡፡ ህወሓት ብቻውን ሊጠየቅበት የሚገባ ነገር አለ ባልልም፣ ተራ ዜጋ ነኝና እኔ የማላውቀው ነገር ግን ህወሓት ብቻውን የሚጠየቅበት ነገር ካለ ኃላፊነት ወስዶ፣ የትግራይን እና የኢትዮጵያን ሕዝቦች ይቅርታ ጠይቆ ቀድሞ ወደ ነበረው የሕዝብ አለኝታነት አቋም መመለስ አለበት፡፡ ወደ ቀድሞ አቋሙ ስል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ በህወሓት አባል መያዝ አለበት ማለቴ አይደለም፡፡ ያ ፓርቲው የሚወስነው እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ሊሆን የሚገባው እንደሆነ አውቃለሁ፡፡

 

ህወሓት ድንቅ ታሪክ ያለው ድርጅት ነው፤ በቀጣይ ትውልዶች ድርጅቱ መታወስ ያለበት በዚህ አስደናቂ ታሪኩ ነው፡፡ እኔ እንደማውቀው ህወሓት ለሕዝብ ታግሏል፣ ዋጋ ከፍሏል፤ ይህ ሆኖ እያለ ግን አሁን ስሙ ጠልሽቷል፡፡ ለስሙ መጠልሸት ምክንያት የሆኑትን በመለየትና በማስተካከል የድሮውን አቋም መልሶ መያዝ አለበት፡፡ ወገቡን አስሮ ለነጻነት የታገለ፣ የተዋደቀ፣ የቆሰለና የተሰዋ የትግራይ ሕዝብ ካሣ ያስፈልገዋል፡፡ ካሣ ስል ገንዘብ ነክ ካሣ አይደለም፡፡ ካሣ ሊሆነው የሚችለው የመሪ ድርጅቱ ህወሓት መቃናት እና ወደ ቀድሞ ሕዝባዊነቱ መመለስ ነው፡፡ ህወሓት በእውነት እና በሃቅ ላይ የተመሠረቱ አቋሞች ይዞ ተጉዟል ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁንም መታደስ ያለበትን፣ መለወጥ ያለበትን፣ መቀየር ያለበትን ለይቶ አዲስ ህወሓት ሆኖ መውጣት ይችላል፡፡ ክቡር ምክትል ፕሬዚደንት፣ ህወሓት የማይቻል የሚመስለውን ግብ በግምባር ቀደምትነት ያሳካ ድርጅት ነው፡፡ ህወሓት በእርስዎ አመራር ታሪኩ ሁሉ ተረስቶ ወደ መገፋት የሚሄድበት ዘመን መሆን የለበትም፡፡ ሕዝባዊነቱን መልሶ ማምጣት ከቻለ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲል መከለስ የሚገባውን መከለስ አይከብደውም፡፡ ክቡር ምክትል ፕሬዚደንት ዛሬ እንደሚባለው ህወሓት ጸረ ሕዝብ ሳይሆን የሕዝብ አለኝታ መሆኑን በተግባር ሊያሳይ ይገባዋል፡፡

 

ከአክብሮት ሰላምታ ጋር፣

አብርሃም

Back to Front Page