Back to Front Page


Share This Article!
Share
ግልፅ ደብዳቤ ለተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ኣብይ ኣሕመድ

ግልፅ ደብዳቤ ለተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ኣብይ ኣሕመድ

ክብርነትዎ፣

እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ በጣም ከተደሰቱና ከደግፉዎት ኢትዮጵያዊያን አንዱ ነኝ። ገና ታዳጊ ወጣት ሁኜ አገሬን ትቼ አሜሪካን ሃገር የምኖር ዜጋ ነኝ። ኢህአዴግ ለውጥ እንዲያመጣ ስጠባበቅ ስለነበርኩኝም የርስዎ ማለትም ወጣትና የተማሩ መሪ መምጣት ለውጥ ይመጣ ይሆን ወይ እያልኩኝ በተስፋ ጠብቄ ብቻ ሳይሆን በርስዎ ላጥርጣሬ ለነበራቸው ጓደኞቼም ስከራከራቸው ነበረ። አሁንም በርስዎና እርስዎን በመሰሉ አዲስ አስተሳሰብ ሰንቀው ኢትዮጵያን በሰላምና ብልፅግና ጎዳና የምትመሯት የኢህአዴግ መሪዎች ተስፋዬ እንደተጠበቀ ነው።

ክቡር ሆይ፣ ይህን ካልኩኝ በኋላ ግን ት በጣም የሚያሳስቡኝ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጌ ትንሽ ልበልና እባክዎት ትንሽ ጊዜ ሰጥተው ያንብቡትና ያስቡበት። ምክንያቱም ሃገራችን ሁላችንም በምንመኘው መንገድ ትጓዝ ዘንድ ታሪካዊ ሃላፊነት ስላለብዎት ይህም ለማድረግም የህዝብዎን ስሜት ማዳመጥ ተገቢና አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁኝ። እዚሁ ላይ በግል የሚደግፍዎት ኢትዮጵያዊ በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን ብዙዎቹ ግን በድርጅትዎ የተማረሩ በመሆናቸው ዋናው መፍትሄም አማራጭ ድርጅቶች እንዲኖሩና እኩል ቦታ ኖሯቸው የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዋር እንዲፈጠር ማድረግ ሆኖ እያለ በመታየት ያለው ድግሞ እጅግ የተደበላለቀ ጉዳይ ስለሆነ ውጤቱም እንደዛው የተፈለገውን ሰላምና እርቅ ከማምጣት ይልቅ የተደበላለቀ እንዳይሆን ዝግ ብለው እንዲያስቡበት ለማለት ነው።

Videos From Around The World

1ኛኢህአዴግን ከማጠናከር አኳያ፣ ኢህአዴግ ከነብዙ ችግሮቹ እስካሁን ድረስ አገርን በማስተዳደር የሚገኝ አማራጭ ገና ያልተገኘለት የፖለቲካ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ይገኛል የሚል እምነት ቢኖረኝም ለውጡ ግን ድርጅቱን ሙሉ በሙሉ ያካተተና የድርጅቱ ጥንካሬ የሚያመጣ ሳይሆን ድርጅቱ በሁለት ጎራዎች የከፈለና አባላቱን እርስ በርሳቸው የሚያጋጭ አዲስ አስተሳሰብ አራማጆችና ኋላ ቀር አስተሳሰብ አራማጆች በሚል እርስ በርስ የማይገናኙ በሃስብ ግጭት ብቻ ሳይሆን መተማመንን በማስቀረት ጥርጣሬን ያነገሰ ሆኖ ያ ጠንካራና ብቸኛ የሆነው ኢህአዴግ ዲሞክራሲ ከመፍጠሩና ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ሳይፈጠር የአልጋ ቁራኛ እንዳይሆን እሰጋለሁኝ። ምክንያቱም እርስዎ የርስዎ አይነት አስተሳሰብ የሚያራምዱ ጓዶችዎን ይዘው እየነጎዱ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን ወደ ኋላ በመተው አንዳንዴም አስፈላጊ እንዳልሆኑ በመቁጠር በድርጁቱ ውስጥ ክፍፍል እየተፈጠረ መሆኑና ክፍፍሉም በድርጅቱ ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ አደጋ የሚያመጣ እንዳይሆን እያሳሰበኝ ነው። በተለይም እርስዎን ለዚሁ ስልጣን እንዲበቁ መንገድ ለጠረጉ ወይም እድሉን ላመቻቹ ብዙ አባሎቻቸው አሰውተው የመጡትን የድሮው መሪዎች ክብራቸው በሚነካ መንገድ ከስራ ሃላፊነታቸው በጡረታ ስም ሲሰናበቱየቀን ጅቦች እየተባሉ ሲሰደቡና ሲዋረዱ እያየን ነው። ይህ ድርጊት በብዙ የድርጅታቹህ አባላትና በህዝቡ ዘንድ ጥሩ ስሜት አይፈጥርም ብቻ ሳይሆን ድርጅቱን በጠላትነት በሚተያዩ አባላት የውስጥ ሁከት ወደ ውድቀት ሊያደርሰው ይችላልና እንዲታሰብበት። ድርጅታቹህን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለማስታረቅ በውስጣቹህ ጠብና ብጥብጥ እንዲነሳ ማድረግ የራስህ ህይወት በራስ እንደ ማ እንዳይሆን። የክብርነትዎ መልእክትም ፍቅርም ጥላቻንም እየጋበዘ ያለና ድብልቅልቅ ያለ ስለሆነ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ወደ ፍቅር ቢጋብዙ ተመራጭ ይሆናል።

የወይራ ዘለላ የሚዘረጋለት የትናንትናው ጠላት እንዳለ ሆኖ እርዎን እዚህ ቦታ ላይ እንዲደርሱ እድል የሰጠውና ቀን የጣለው ወገንዎ ደግሞ ጅብ የሚባልበት፣ የይቅርታና የጥላቻ ጥሪ ለኢትዮጵያ አያስፈልጉም። ትናንትና ወያነ ተብለው እንደጠላት እየታዩ ከኖሩበት የኢትዮጵያ ምድር በወገኖቻቸው የተጨፈጨፉ፣ የተገደሉና የተባረሩ የትግራይ ልጆች ዛሬ ደግሞ እርስዎ ባወጡት አዲስ ስም የቀን ጅብ እየተባሉ መከራቸው እያዩ ነው። በደቡብ ህዝቦች፣ በኦሮሚያና በአማራ ህዝቦች መካከል እያየለ እየመጣ ያለው ግጭትም የርስዎ የሰላምና የይቅርታ መንገድ የሚያደናቅፉ ስለሆነ ከቁጥጥር ሳይወጣ መፍትሄ ይፈለግለት።

2ኛዲሞክራሲ ምህዳርን በተመለከተ፣ ዲሞክራሲያዊ ምህዳር ለማስፋት ኢህአዴግ የራሱን ውስጣዊ ጥንካሬ ካለው ብቻ ከሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶች ጋር የሚኖረው ድርድር ውጤቱ የሚፈልገው እንዲሆን ማድረግ የሚችለው። ካልሆነ ግን አንዳንድ ተቃዋሚ ሃይሎች የተዳከመ ኢህአዴግን ገፍትሮ ከመጣል ሌላ የማይፈልጉ እንዳሉ መረዳቱ አስፈላጊ ነው። ስለሆነም ውስጣዊ ጥንካሬውን የጠበቀ ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ሃይሎች ጋር ሁሉም በሚስማሙበት መንገድ ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ፣ የህግ አስከባሪ ሃይልና ሌሎች ኣስፈላጊ ተቋማት ማቋቋም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊ መከባበርና ወንድማማችነት ያማከለ የተፎካካሪ አማራጭ ሃይሎች መኖር ለሃገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለኢህአዴግ ህልውና ወሳኝ ነው እና እርቅና ሰላም ለማምጣት በቅንነት መስራት ያስፈልጋል።

ሃገራችን ውስጥ ፍፁም ሰላም እንዲኖር፣ እድገትና ስልጣኔ ቀጣይ እንዲሆን የሃገራችን አንድነቷንና ክብሯን ጠብቆ መሄድ ወሳኝ ነው።ስለሆነም ከማንኛውም ነገር በላይና በፊት ኢህአዴግ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ማረጋገጥ ይኖርበታል። በአሁኑ ጊዜ ብሄር በብሄር ላይ የሚያነሳሱ የተለያዩ ክስተቶች እየተፈጠሩ ናቸው። አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችም ኢትዮጵያዊያንን በብሄር ደረጃ ጥላቻና ግጭት ወደሚፈጥሩበት መንገድ እየመሯቸው ይገኛሉ። እንዚሁ ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ቁጭ ብለው በመወያየትና በመግባባት መፍት መፈለጉ ለነገ የማይባል አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን እርስዎና ፓርቲዎ ቅድሚያ እንድትሰጡበት በማክበር አሳስባለሁኝ። እን እኔ እምነት የእርስዎ መንግስት ፍቅርና የኢትዮጵያ አንድነትን ስለሰበከ ብቻውን የሚያመጣው ሰላም ይሁን አንድነት አይሮርም።

3ኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ማካለል በተመለከተ፣ ኢህአዴግ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት እንዳበቃ በብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች የይህወት መስዋእትነት የተገኘውን ወታደራዊ ድል ምክንያቱ እስካሁን ድረስ ለህዝቡ ባልተገለፀለት መንገድ የአልጄርስ ስምምነት ተብሎ በሚታወቀው የውርደትና ሽንፈት ቀይሮት እነሆ ይግባኝ በማይባልለት ብይን ያን የክቡራን ወንድሞቻችን አፅም የወደቀበት ባድመን ጨምሮ ለኤርትራ አሳልፎ እንዲሰጥ አድርጓል። የድንበር ማካለሉ በውሳኔው መሰረት ተግባራዊ ያልሆነበት ምክንያትም አንዴ የአልጀርስ ውሳኔ ሻዕብያ የአለም ሰላም አስከባሪዎች በማባረሩ ምክንያት ውሉ ውድቅ ሆኗል፣ አንዴም ባለ አምስት ነጥብ መደራደሪያ ይዘናል፣ ከኤርትራ ወደኛ የተሰጠ ስላለ ባድመና ሌሎች ለኤርትራ የተሰጡ ኢትዮጵያዊ መሬቶችን ሰጥቶ በመቀበል ግዛታችን እናስከብራለን በማለት ሰንካላ ምክንያቶች ሲቀርቡ ቆይቷል። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ሳይሆን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሆነ ክብርነትዎ አውጇል።

ከላይ እንደጠቀስኩት የድርጅትዎ ውስጣዊ ጥንካሬ ተናግቶ፣ ወዳጅና ጠላት አፍርተው፣ ህዝቡ በተስፋና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከተው፣ ተፎካካሪ፣ ተቃዋሚ፣ አሸባሪ የተባሉ ሃይሎችም ኢህአዴግ በጣረሞት ላይ ያለ ድርጅት ነውና መቃብሩ ውስጥ እንክተተው እያሉ ባሉበት ወቅት፣ እርስዎም የዘመቱበትና ኢትዮጵያዊ ወጣት ከጫፍ እስከ ጫፍ ሉአላዊነትህ ተደፈረ ተብሎ በቁጣ በመዝመት ህይወቱ የገበረበት፣ ኢትዮጵያዊ እየኖረበት ያለው ኢትዮጵያዊ ምድር ለኤርትራ ለመስጠት ልክ ድንበር ጥሶ የመጣ እንስሳ እንደመመለስ አድርገው ሙሉ በሙሉ ተቀብለን ተግባራዊ እናደርጓለን ሲሉ የኢትዮጵያዊያን ስሜት በጣም ጎድቷል። ያገር ጉዳይ እኮ የሁሉም ዜጋ እንጂ የጥቂት ባለስልጣናት አይደለም። በዚሁ ጉዳይ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ከሚያዋርዱን ህዝቡ እንዲዘምት በየቀበሌው በመሄድ እንደተደሰኮረለት በዚያ መጠን ልጁ የገበረለትን ጉዳይና የልጁ አፅም ያረፈበትን ኢትዮጵያዊ ምድር አንዴ ተሳስታቹህ በአልጄርሱ ውል መሰረት በህግ የተፈረደ ስለሆነና ለስህተታቹህም ህዝቡን ይቅርታ ጠይቃቹህ ማማከር ያስፈልጋል። ኢህአዴግ በንቀት እንደዚሁ ያገር ጉዳይ እንደፈለገ ማድረግ አይገባውም። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር በታሪክም ተጠያቂ የመሆን ጉዳይም ከግምት በማስገባት የተከፈለው መስዋእትነትና የህዝቡን ክብር ቢጠበቅለት ይሻላል። ስለዚሁ ከኤርትራ ጋር ሰላም ያስፈልገናል፣ ፍርዱም አሁን ይሁን ወደፊቱ መተገበሩ አይቀርም። ነገር ግን ኢህአዴግ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ባገር ሉአላዊነት መጫወቱን አቁሞ ከህዝቡ ጋር እንዳይጣላና እጣ ፈንታው እንዳያበላሽ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጓል። ክብርነትዎም ከዚሁ ሃላፊነት ማምለጥ አይችሉምና በዚሁ ፈታኝ ወቅት የውጭ ዓለሙን ከማዳረስ ይልቅ ባገር ውስጥ ሙሉ ሰላም የሚረጋገጥበት መንገድ እንዲፈጠር ቢጥሩ ይሻላል።

4በመንግስት ይዞታ ስላሉና ወደ ግሉ ሴክተር እንዲተላለፉ ስለተባሉ ኩባንያዎች፣ ህይ ጉዳይ በተመለከተ በበኩሌ መንግስት ከንግድ ፍፁ መውጣት አለበት የሚል አቋም አለኝ። ሆኖም ግን በሃገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና ያላቸውና የሃገር ሃብት ተብለው በሚታወቁና ህዝቡ በሚተማመንባቸው እንደእ ቴሌ፣ አየር መንገድና የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦቻችን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት እናደርጋለን መባሉ ታሪካዊ ስህተት ነው። አንዴ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ስለ ቴሌ ወደ ግል ሴክተሩ ማስተላለፍ ሲጠየቁ ገንዘብ የሚትታለብ ላም ነችና አሳልፈን አንሰጥም ብለው ነበር። አዎን እነዚሁ ያገር ልዩ ሃብቶች በከፊል ወደ ግሉ ሰክተር ማለፋቸው ሳይሆን ቅሬታዬ ለውጭ ገበያ ክፍት ይሆናሉ መባሉ ነው።

በኔ እምነት ኢትዮጵያ ከብዙ የአፍሪካ ሃገራት ልዩ ሊያደርጋት የሚችለው ሃብቷ በልጆቿ መያዙ መሆን ሲችል ነው። ሃገራዊ ባለሃብት ማፍራት መቻል ለወደፊቱ ዕጣ ፈንታዋ ወሳኝ መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል። ስለዚህ እነዚሁ ሁሉም ወደ የግሉ ሴክተር ይተላለፋሉ የተባሉ ኩባንያዎች ከትንሹ እስከ ትልቁ ድረስ ባገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በቀር ለውጭ ባለሃብቶች አሳልፈን መስጠቱን ሁሉም ኢትዮጵያዊ መቃወም ያለበት ጉዳይ ነው። በተለይም ቴሌ፣ አየር መንገዱና የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች የሃገራችን ብሄራዊ ጥቅምና ዋስትና ስለሆኑ ከኢትዮጵያዊ በቀር አንድም ሼር እንኳ ለውጭ ተላልፎ እንዳይሸጥ መከላከል አለብን። መንግስትም ይህ ጉዳይ በፓርቲ ስራ አስፈፃሚ በኩል ውሳኔ የሚያሳልፍበት ሳይሆን እንደ መንግስት ህዝባቸን የሚሳተፍበት መድረክ ፈጥሮ ከዛም የህዝቡን ይሁንታ መሰረት ባደረገ መልኩ በህዝብ ተወካዮች በኩል ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል። በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካ መንግስት ባለሃብቶችን ይዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሌሎቹ የሃገር ደህንነት መሰረት የሆኑት መሰረተ ልማቶችን በእጃቸው ለማስገባት የሚያደርጉት ያሉት ሩጫ ሳይዘገይ ሊገታ ይገባዋል። እትዮጵያን 51ኛዋ የዩናትድ ስቴትስ ግዛት ወይም ቅኝ ግዛት እንዳትገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

ባጠቃላይ እርስዎ በዚሁ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ተስፋ ሰጪና ተስፋ አስቆራጭ ነገሮችን እያየን ነው። ስለሆነም ከሁሉም ቦታ ለሚያስተዳድሩት ህዝብ ቅድሚያ እንዲሰጡና ውስጣዊ ሰላማችን አስተማማኝ እንዲሆን ታሪካዊ ሃላፊነት አለብዎት። ስለሆነም ሩጫውን ቀነስ አድርገው ነገ ሊያስደስትዎት ለሚችል ረጋ ብለው ያገራችን ውስጣዊ አደጋ በመረዳት ድርጅትዎን ማጠናከር፣ ተቃዋሚ ሃይሎች የአማራጭ ሃይሎች እንዲሆኑ ፖለቲካዊ ምህዳሩን ማስፋትና ለውስጣዊ ችግራችን ህዝቡን የመፍትሄ አካል እንዲሆን ቢያደርጉ ሻላ

እግዚአብሄር ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ይባርክ!

መለይ ገ/ስላሴ ፣ ሃገረ-አሜሪካ

06-25-18

 

Back to Front Page