Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሰሚ ካለ አሁንም አልረፈደም(ጥሪ ለቲም-ለማ)

ሰሚ ካለ አሁንም አልረፈደም

(ጥሪ ለቲም-ለማ)

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ታሕሳስ 14፣ 2011 ዓ.ም.

አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ ስናይ ኢትዮጵያን የመምራት ስልጣን ተቆጣጥሮ የሚገኘው በኢህአዴግ ስም ቲም-ለማ ተብሎ እየተወደሰ የሚገኝ ቡድን ነው፡፡ ይሁን እና ይህ ቡድን አገር ወይም ክልል መምራት አልቻሉም፡፡ ዶ/ር አብይ እና ኦቦ ለማ አገር ወይም ክልላቸውን መምራት ስላልቻሉ፣ ኦሮሞ አገር ወይም ክልል መምራት አይችልም የሚል ካለ እሱ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው አይደለም፡፡ በተመሳሳይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አማራ ክልልን ማረጋጋት ካልቻለ የአማራ ተወላጅ ክልል መምራት አይችልም ወይም ዶ/ር ደብረፂዮን የትግራይ ክልል መምራት ካልቻለ ትግሬ ክልል መምራት አይችልም የሚል ካለ እሱም ጤነኛ ሰው አይደለም፡፡ በአንድ የአመራር እርከን የብሄር ውክልና እንዲደረግ ማድረግ ማለት ያየተወከለ ተወካይ ብቃት የብሄሩ ብቃት ይወክላል ማለት አይደለም፡፡ ያተወካይ የሚወክለው ነገር ካለ የብሄሩ ጥያቄ፣ ፍላጎት ማንፀባረቅ ነው፡፡ የአመራር ብቃት በትውልድ ቦታ፣ በብሄር፣ በቋንቋ መቻል እና አለመቻል የሚወሰን አይደለም፡፡ የአመራር ብቃት የሚወሰነው በትምህርት፣ በስልጠና፣ በአደረጃጀት፣ በአመለካከት እና በተሞክሮ እንዲሁም በግል ተሰጦው ነው፡፡ 

Videos From Around The World

አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ ስናይ፣ አገርራችን ኢትዮጵያ መንግስት እና ሕገመንግስት እያላት እየተበጠበጠች ነው፤ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በገዛአገሩ ሰላም እና መረጋጋት አጥቶ እየተሰደደ እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ይህ ችግር የአመራሮቹ /ቲም-ለማ/ የግል ብቃት ችግር እንጂ አንዳችም ከመጡበት ብሄር የሚያያዝ ችግር የለበትም፡፡ ይህ የአመራር ችግር ገሚሱ ስልጣን ለማራዘም ከብሄሩ ጋር በማያያዝ ትርፍ ለማግኘት ሲሞክር ገሚሱ ደግሞ ያለውን የብሄር ጥላቻ ለማንፀባረቅ ድሮውም አይችሉም የሚል ድምዳሜ ሲሰጥ ይታያል፡፡ ይህ የብቃት ችግር በፈለገው መልክ ይገለጥ ከብሄር ጋር ለማያያዝ እየሞከረ ያለው ጥገኛ (ጠባቡ እና የትምክህት) አመለካከት የተጠናወተባቸው ሀይሎች ብቻ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ቲም-ለማ እየተባለ የሚወደሰው በኢህአዴግ ውስጥ ሆኖ ጋብቻ የፈፀመው የትምክህት እና የጠባብ ህቡእ ቡድን የኢህአዴግ ስራአስፈፃሚ ቦታ በስውር ሴራ ተቆጣጥሮ፣ ህጋዊው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሽባ በማድረጉ፤ ኢህአዴግ አገርን መምራት አቅቶት አገራችን ኢትዮጵያ በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ የህይወት ሲቃ ትንቅንቅ ትገኛለች፡፡ አሁን በኢህአዴግ ውስጥ የተከሰተው የአመራር ክፍተት ለማንም ሳይደበቅ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ይህ የአመራር ክፍተት በኢህአዴግ ኮር አመራር ደረጃ በመፈጠሩ የኢህአዴግ መዋቅር መቋጠሪያው ተፈቶ የታችኛው የአመራር እርከኖች እንደ የጆንያ ድንች በመበታተኑ ቲም-ለማ ራሱ የበተነው መሰብሰብ አቅቶት ለችግሩ የውጭ ምክንያት እያጣቀሰ ሌላ ችግር በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡

አንድን የፖለቲካ ድርጅት ጥንካሬ የሚወሰነው በፈጠረው አደረጃጀት ነው፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ሊህቃን እንደሚሉት የድርጅት ሃይልና ጥንካሬ ለመግለፅ በጆንያ ከታሰረ ድንች ወይም ሽንጉርት ያመሳስሉታል፡፡ ፖለቲካ ድርጅት ማለት ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ዜጎች በአንድ ላይ ተሰባስበው ወይም ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ሀይል ይፈጥራሉ ይላሉ፡፡ እነዚ የተሰባሰቡ ሃይሎች ያሰባሰባቸውን ወይም እርስ በርስ ያስተሳሰራቸውን ፖለቲካዊ አመለካከት ከላላ ወይም ቋጠሮው ከተፈታ ልክ የታሰረ ጆንያ ሙሉ ድንች ሲፈታ እንደሚበተን ይበተናል፡፡ ከተበተነ ደግሞ ሀይሉ ይጠፋል ይባላል፡፡ አሁን በኢህአዴግ ላይ ያጋጠመው ነገር ይህ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች /ቋጠሮዎች/ ስብስብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢህአዴግ ሀይል በቋጦረው ላይ ነው፡፡ ቋጦሮው ከተፈታ ግን ኢህአዴግ ተበተነ፣ ሀይል አጣ ማለት ነው፡፡ አሁን እያየነው ያለው ነገር ይህ ነው፡፡ ኢህአዴግ በመለስ ዜናዊ ንድፍ መሰረት ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር በፈጠሩ አራት ድርጅቶች /ቋጦሮዎች ወይም የታሰሩ ጆንያዎች/ ማለትም ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን የተመሰረተ ድርጅት ነው፡፡ እነዚህ አራት የተደራጁ ድርጅቶች በአንድ ሌላ ጠንካራ አደረጃጀት /ቋጦሮ ወይም ጆንያ/ ማለትም በኢህአዴግ ተጠርንፈው አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ነበሩ፡፡

ይሁንና ባለፉት 4-5 ዓመታት በኢህአዴግ ውስጥ ባጋጠመው የመበስበስ አደጋ፣ እንደ ታሪኩ ከገባበት ዝቅጠት መውጣት አቅቶት እነሆ በመለስ የታሰረ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ቋጠሮ በሀ/ማርያም ደሳለኝ የኢህአዴግ ቋጠሮ ተፈቶ፣ አራቱ ድርጅቶች ለየብቻቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2008 ዓ.ም. - 2009 ዓ.ም. በየድርጅታቸው ታጥረው የየድርጅቶቻቸው ቋጠሮ በማላላት ተጠምዶ /በመበስበስ ጉዞ ለማለት ነው/ ከሰነበቱ ቦሀላ ሶስቱም ድርጅቶች /ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን/ በ2010 ዓ.ም. ቋጠሮቻቸው ፈትተው እንደ የተፈታ ጆንያ ድንች ተበትነው ቀሩ /ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጆንያ በመውጣት/ ፡፡ አራተኛው ድርጅት ማለትም ህወሓት እንደ ሌሎች እህት ድርጅቶች ለመበታተን፣ በአቶ አባይ ወልዱ መሪነት ቋጦሮውን በማላላት ተጠምዶ ከቆየ ቦሀላ /በመበስበስ ጉዞ ለማለት ነው/፤ የሰማእታት አደራ እና የህዝቡ እሮሮ አመራሩ ከእንቅልፉ እንዲባንን ስላደረገው ቋጦረው ቢላላም ሳይፈታ ለጥቂት በመትረፉ ድርጅቱን ከብተና ድኗል፡፡

በቲም-ለማ ተበትኖ የቀሩት ብአዴን እና ኦህዴድ ከገቡበት የመበስበስ እንቅልፍ ሊቧኑኑ ስላልቻሉ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርቀው በመሄድ ከጥገኞች እርቅ ፈፅመው እስከ መዋሀድ ብሎም የድርጅት ስም እና የሰማእታት አሻራዎች እስከ ማጥፋት ደርሷል፡፡ ይህ ቡድን እዚህ ሳይቆም በመጨረሻው ጉባኤ ኢህአዴግ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ "ይፋዊ/ኦፊሻላዊ ፍት" ለማድረግ ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡

ኮር አመራሩ የአገራችን ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን አቅቶት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሰላም እንድታጣ፣ መፈቃቀር እና መቻቻል በአገራችን ማቆጥቆጥ ጀምሮ የነበረው እንደገና ወደ እርስ በርስ መጠራጠር፤ አንዱን ህዝብ የሌላው ህዝብ ጠላት እንደ ሆነ፤ አንዱን ህዝብ ተሰራቂ ሌላው ህዝብ ሰራቂ እንደ ሆነ፤ አንዱን ህዝብ አዳኝ ሌላው ህዝብ ታዳኝ፤ አንዱን ህዝብ ሌባ አሳዳጅ ሌላው ህዝብ በሌባ ደባቂነት እየተፈረጀ ይገኛል፡፡ መንግስት ይህን ከማስተካከል ይልቅ በሚያወጣቸው መግለጫዎች እነዚህ ነገሮችን የሚያባብስ ሆኖ ቀጥሎበታል፡፡ ይህ በኮር አመራሩ የነበረውን የመበስበስ በሽታ ወደ መንግስት መዋቅር እየተዛመተ በመምጣቱ ችግሩን እያባባሰው ይገኛል፡፡ የዚህ መገለጫ አንዱ በታህሳስ 11፣ 2011 ዓ.ም. በተወካዮች ምክርቤት የፀደቀው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሸን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፡፡

ይህ አዋጅ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ስለመሆኑና በተለይ በትግራይ ህዝብ በስፋት ቅሬታውን ሲያቀርብ እና ሲጠይቅ ሰንብቷል፡፡ በመገናኛ ብዙሀንም ሲሰራጭ ሰንብቷል፡፡ የትግራይ ህዝብ ያለውን ስጋት በሰላማዊ ሰልፍና በተለያዩ ሚድያዎች ሲያቀርብ፣ መንግስት ወይም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይህን የህዝብ ቅሬታ ወይም ስጋት ተገንዝቦ እንዲቀርፍለት እና እንዲያስወግድለት በማሰብ ነበር፡፡ ነገር ግን የቲም-ለማ መንግስት ይሁን የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይህን የትግራይ ህዝብ ጥያቄ እንደ የህዝብ ጥያቄ ወስዶ መልስ ከመስጠት እና ብዥታዉን ግልፅ ከማድረግ ይልቅ በማናለብኝነት ስሜት በትእቢት በመወጠር የህዝቡን ድምፅ ወደ ጎን በመተው ህጉ በድምፀ ብልጫ እንዲፀድቅ በማድረግ ጥቁር ጠባሳ ለታሪክ ትቶ አልፏል፡፡

አሁን በአገራችን ያለው ችግር ዋናው መንስኤ የኢህአዴግ ኮር የአመራር መበስበስ ነው፡፡ ይህ አመራር ቋጦሮውን በመፍታት ድርጅቱን በመበተኑ በኦሮምያ እና በአማራ ክልል መንግስት የሌለ እስኪመስል ህገመንግስት እየተጣሰ በመንጋ የሚተዳደር አከባቢ ቀላል አይደለም፡፡ በነዚህ አከባቢ ህዝቡና ድርጅቶቹ ሆድና ጀርባ ሆኖው፣ ህዝቡ የመንግስት ያለ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ በትግራይ ክልል ህወሓት ወደ ትክክለኛው አብዮታዊ ዴሞክራሲ በመመለሱ በህዝቡ እና ድርጅቱ ተፈጥሮ የነበረውን ክፍተት እየጠበበ የላላውን ቋጦሮው እየጠበቀ ህዝብና ድርጅት ከመቸውም በላይ አንድነታቸው እያጠበቁ ይገኛል፡፡ የዚህ ሁሉ ምሽጥር ህወሓት ከዝቅጠት መንገድ በመውጣት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ መያዝ በመጀመሩ ነው፡፡

ስለዚህ የቲም-ለማ ቡድን እየተባለ የሚጠራው አሁን የኢህአዴግ ስልጣን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ቡድን ከገባበት አዘቅት የመወጣጫ ብቸኛው መንገድ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንነት ለቡዱኑ ለመንገር አይደለም፡፡ ቡዱኑ ባለፉት አስራ-ምናምን ዓመታት ለኢህአዴግ አመራር በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ንድፈ-ሀሳብ ምንነት ሲያሰለጥኑ ሲሰለጥኑ የነበሩ ናቸው እና፡፡

"ህዳሴ ኢትዮጵያ" ለቲሙ መስጠት የፈለገው ምክር አሁንም ገና አልረፈደም ለማለት ነው፡፡ ቲም-ለማ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ ላለፉት ሃያ-ምናምን ዓመታት መርቶም ተመርቶም ውጤቱ አይቷል፤ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጭ በሆነ መንገድም ጥቂት ዓመታት ተጉዟል ጥቂት ወራትም በዚህ የጥፋት መንገድ አገራችን ኢትዮጵያ መርቷል፡፡ ውጤቱም እነሆ ባለፉት 27 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የህዝብ ስቃይ እና መፈናቀል የአደባባይ ምሽጥር ሆኖዋል፡፡

ስለዚህ ቲም-ለማ ከገባበት አዘቅት ለመውጣት መንቃት/መቧነን አለበት፣ አሁን ያለንበት ችግር ብቸኛው መፍትሄ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ በጓዷዊ መንገድ እንደ ኢህአዴግ በሰከነ አእምሮ፣ በዴሞክራሲያዊ ውይይት ችግሮቹን መፍታት አለበት፡፡ ሁኔታዎች እንደሚያመላክቱት የአገራችን ህልውና ከኢህአዴግ ህልውና የሚያያዝ ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ እየተዳከመ በሄደ ቁጥር በህዝቦች መካከል ግጭቶች እየተፈጠሩ ነው፣ አዳዲስ የማንነት ጥያቄዎች፣ አዳዲስ የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል፣ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ተነስተው የማያውቁ የሕገመንግስታችን አንቀፆች (ዓንቀፅ 39) አሁን መነሳት ጀምሯል፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ኢህአዴግን ወደ ቦታው መመለስ እና አለመመለስ የአገራችን ሰላም እና መረጋጋት የማስፈንና ያለ ማስፈን ጉዳይ ሆኖዋል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ ውስብስብ ችግሮችን እየፈታ የመጣ አመራር አሁን ይህ ችግር መፍታት አቅቶት ለችግሮቹ ምክንያት እየደረደረ፣ Externalize እያደረገ፣ ለውስጥ ችግር መፍታት ከድርጅቱ ባህል ውጭ የውጭ ድጋፍ (የጠላቴ ጠላት አባባል) ማማተር የሚመስል ማየት የኢትዮጵያዊነት ክብር የሚነካ በመሆኑ ልብ ይሰብራል፡፡ ስለዚ ከእልህ፣ ከቂም በቀል፣ ከተንኮልና ሴራ፣ ከመጠላለፍ ወጥተን ህዝባዊ ወገንተኝነታችንን ለመመለስ በጠረጴዛ ዙርያ መፍታት አለብን፡፡ ባለፉት 7 ወራት የተጓዝንባቸው ልዩነቶቻችንን የሚያሰፉ አካሄዶች ይብቁ፣ ኢህአዴግ አለ እያልን ህዝባችንም ራሳችንም አናሞኝ፣ መሸዋወድ ይብቃ፤ የህዝብ ድምፅ ይሰማ፣ በክልሎች ጣልቃ ገብነት ይቁም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንግዲህ በአመራሩ ላይ ያለውን የጎሪጥ መተያየት ሊታገሰው አይገባም፣ አይችልምም፡፡ ስለዚህ የልጆች የእቃ እቃ ጨዋታ፣ የብሽሽቅ ፖለቲካ ይህቃ፡፡ ስለዚ ከመርፈዱ በፊት ከእንቅልፍ መቧነን ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው፡፡

 

hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com

Back to Front Page