Back to Front Page


Share This Article!
Share
የሰላምና የልማት ቀጠና

የሰላምና የልማት ቀጠና

አዲስ ቶልቻ 09-10-18

ኢትዮጵያ ባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት በቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን ትጠቀሳለች። በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም እንዲሰፍን፣ በቀጠናው ሃገራቱ መሃከል መጠቃቀም ላይ የተመሰረተ ትስስር እንዲኖር የያዘቻቸው አቋሞችና ያከናወነቻቸው ተግባራት ውጤታማ ናቸው ማለት ይቻላል። በቀጠናው ሃገራት መሃከል የመንገድ፣ የባቡርና  የሃይል መሰረተ ልማት ትስስር እንዲኖር ያደረገችው ጥረት በተወሰነ ደረጃ ውጤታማ ሆኗል። በዚህ ረገድ ለቀጣይ ስራዎች መነሻ የሚሆን መሰረት ተጥሏል።

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍንና የሶማሊያ መንግስት ዳግም እንዲቆም በማድረግ ረገድ ቀዳሚውን ሚና ተጫውታለች። ምንም እንኳን እስካሁን ፍሬ ባያፈራም፣ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ቡድኖችን ለማግባበት ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መሃከል በአብዬ ግዛት የተፈጠረው አለመግባበት  ወደከፋ ግጭት እንዳያመራ፣ ሁለቱም ሃገራት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል በአወዛጋቢው አካባቢ እንዲሰማራ መሰማማታቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት  ከኤርትራ በስተቀር ከተቀሩት አጎራባች ሃገራት ጋር ቀደም ሲል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከጥርጣሬ የጸዳ ግንኙነት መመስረት ችላለች። ይህ ሁኔታ የግጭት ስጋት በሚያንዣብብበት ቀጠና አንጻራዊ ሰላም ማስፈን አስችሏል።

Videos From Around The World

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበራትንም ግንኙነት እንደተቀሩት አጎራባች ሃገራት ሰላማዊና የትብብር እንዲሆን ፍላጎቷን ስትገልጽ መቆየቷ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበራት ግንኙነት የጸብአጫሪነት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በሁለቱ ሃገራት መሃከል ያለው ግንኙነት አንድ ቀን ሰላማዊ ይሆናል የሚል ተስፋ ያረገዘ ነበር። ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች የደምና የባህል ትስስር የሚመጥን እንዲሆን ስትሰራ መቆየቷ ለዚህ አስረጂ ነው።

ኢትዮጵያ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞችን ስትቀበል ቆይታለች። በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ መሃከል ያለው ግንኙነት ከሌሎች አጎራባች ሃገራት በተለየ በደምና በባህል የተሳሰረ ስለሆነ፣ ኤርትራውያን ስደተኞች በኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት ስደተኞች የተለየ መብት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ተደርገዋል። የኤርትራ ስደተኞች በስደተኞች መጠለያ ውስጥ ለመኖር አይገደዱም፤ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ዘመዶቻቸው ጋር መኖር ይችላሉ፤ ይህ በህግ ነው የተፈቀደው። በርካታ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የነጻ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ሲደረግ ቆይቷል። አሁንም በርካቶች በትምህርት ላይ ይገኛሉ። ይህ እውነታ ኢትዮጵያ የሁለቱ ሃገራት መጻኢ ግኝኙነት መልካም እንዲሆን የነበራትን ፍላጎትና ተስፋ ያሳያል። የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በ2010 ዓ/ም አጋማሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ከኤርትራ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል መወሰኑም ይታወሳል።

ያም ሆነ ይህ፣ ጠቅላይ መኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ለማመን በሚያስቸግር ፍጥነት መታደስ ችሏል። በጥርጣሬ ሲተያዩ የነበሩትና አልፎ አልፎም ሲኮረኳከሙ የነበሩት ሁለቱ መንግስታት፣ ይህን ገጽታ ፍጹም ቀይረው የአንዱ መሪ በሌላው ሃገር ጉብኝት ለማድረግ በቅተዋል። በዚህ ጉብኝት ለአንደኛው ሃገር መሪ በሌላሻው ሃገር የተደረገው አቀባባል የሁለቱ ሃገር መንግስታትና ህዝቦች ተነጣጥለው የቆዩባቸውን አመታት የሚያካክስ በሚመስል ሁኔታ እጅግ የሞቀ እንደነበረ እናስታውሳለን።

ሁለቱ መንግስታት ግንኙነታቸውን ለማደስ መወሰናቸውን ተከትሎ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመጀመር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በኤርትራ ወደቦች ልትጠቀም የምትችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ተስማምተው እንደነበረ የታወሳል። በዚህ መሰረት የሁለቱም ሃገራት አየር መንገዶች፣ አንዱ ወደሌላው ሃገር በረራ ጀምረዋል። የየብስ ትራንስፖርት ለመጀመርም የመንገድ እድሳት ስራ ጀምረዋል።

ጠቅላይ መኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰሞኑን በአፍሪካ ቻይና የጋራ የትብብር መድረክ ላይ ተሳትፈው ሲመለሱ ወደኤርትራ ጎራ ብለው ነበር። ጠቅላይ ምኒስትሩ መጀመሪያ ያረፉት ከአካባቢው ወደቦች በሙሉ ለኢትዮጵያ ቅርብ ወደሆነው የኤርትራ የአሰብ ወደብ ነበር። በመቀጠል ወደምጽዋ ወደብ ነበር ያቀኑት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሰብ ወደብንና ከአሰብ ወደብ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ያለውን 71 ኪሎ ሜትር መንገድ ጎብኝተዋል። መንገዱ አገልግሎት ለመስጠት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ገምግመዋል። የአሰብ ወደብን በተመለከተ ወደቡ ላይ የተወሰኑ የማስተካከያ ስራዎች ከተከናወኑ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቅላይ ምኒስትሩ ገልጸዋል። ከአሰብ በኋላም ወደ ምጽዋ በማቅናት ወደቡን ጎብኝተዋል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ምጽዋ ሳሉ፣ መቀለ የተሰኘችው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብም ምጽዋ ወደብ ደርሳ የመጀመሪያውን የኤርትራ የወጪ ንግድ ሸቀጥ ጭና ወደ ቻይና ቀዝፋለች። የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ አገልግሎት በኤርትራ መጀመሩ፣ ሃገራቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያጡትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች መልሶ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ገልጸዋል።

ኤርትራ ከፍተኛ የሆነ የአሳ ምርት እንዳላት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የአሳ ምርት ከሩቅ ሃገራት እንደምታስገባ የገለጹት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ የንግድ ግንኙነት መጀመር ኢትዮጵያ ከኤርትራ የአሳ ምርት ማስገባት እንደሚያስችላት አመልክተዋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶቿን ወደ ኤርትራ መላክ እንደምትችል አመልክተዋል። በዚህ አኳኋን በአነስተኛ መጠን የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ  የንግድ ልውውጥ እንደሚጀምሩም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ለማደስ ሲወስኑ ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መሃከል አንዱ ኤምባሲዎቻቸውን መክፈት እንደነበረ ይታወሳል። በዚህ መሰረት የሃገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ የኤርትራ ኤምባሲ ጽህፈት በይፋ መከፈቱ ይታወቃል። ኤርትራ አምባሰደሯንም ሾማ ኤምባሲው ስራ ጀምሯል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሰደሯን የሾመች ቢሆንም፣ የኤምባሲው ጽህፈት ቤት ግን በይፋ ስራ መጀመሩ አልተበሰረም ነበር። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አስመራ በሄዱበት ወቅት የኤምባሲ ጽህፈት ቤቱን በይፋ ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአስመራ በነበራቸው ቆይታ ከኤርትራ በተጨማሪ   ሶማሊያን ጨምረው የሶስትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያስቻለ የመሪዎች ውይይት አድርገዋል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ፣ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ የሶስቱን ሃገራት ህዘቦች የበለጠ ለማቀራረብና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።

ሶሰቱ መሪዎች የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና ከጦርነትና እርስ በርስ መጠፋፋት በማላቀቅ ሰላማዊ ቀጠና ለማድረግም መስማማታቸውን ጠቅላይ ምኒስትር ዶ/ር አብይ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሶሰቱን ሃገራት የውጭ ጉዳይየ ምኒስትሮች ያካተተ የልኡካን ቡድን ወደ ጅቡቲ ተጉዞ ነበር። የልኡካን ቡድኑ በተለይ በኤርትራና በጂቡቲ መሃከል የቆየውን ድንበርን መነሻ ያደረገ አለመግባባት መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረ ነበር።

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኢል ኡመር ጊሌ ሃገራቸው ከኤርትራ ጋር የገባችበትን አለመግባባት መፍታትና በአራቱ ሃገራት ቀጠናዊ ትብብር ለመፍጠር ዓላማ የሄደውን የልኡካን ቡድን በደስታ ነበር የተቀበሉት። የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የጅቡቲና የሱማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጅቡቲ ባካሄዱት ስብሰባ፣ በሃገራቱ መሃከል ሰላምና መረጋጋትን ለማሰፈን ተስማምተዋል። በአራቱ የቀጠናው ሃገራት መሃከል ሰላም ማረጋገጥ ከተቻለ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ሃገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል።

በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ ካለምንም የውጭ ሸምጋይ ከኤርትራ ጋር የነበራትን ለሁለት አስርት ዓመታት የሻከረ ግንኙነት ማደሷን ተከትሎ፣ በተቀሩት የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት መሃከል የነበረው  የትብብር ተነሳሽነት ጎልብቷል። በኤርትራና በሶማሊያ መሃከል መልካም ግንኙነት ተፈጥሯል። አሁን ደግሞ ከድንበር ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሻከረ ግንኙነት በነበራቸው ኤርትራና ጅቡቲ መሃከል የሰላምና የትብብር መሰረት ተጥሏል። ይህ በዋናነት በኢትዮጵያ የተጀመረው የሰላምና የትብብር ተነሳሽነት፣ ቀጠናውን ሙሉ በሙሉ ከግጭት የጸዳ በማድረግ ቀጠናዊ ሰላምና ትብብር መፍጠር የሚያስችል መደላድል አስቀምጧል።  

 

 

 

 

Back to Front Page