Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሰላም፣ ኢንቨስትመንትና ልማት

ሰላም፣ ኢንቨስትመንትና ልማት

ዓለምአየሁ አ 07-28-18

ካፒታል ረቢ ሃብት ነው። ባለሃብቶች ይህን ረቢ ሃብት ስራ ላይ የሚያውሉት ወይም ኢንቨስት የሚያደርጉት ለአንድ ግብ ነው፣ ትርፋማ ሆነው ሃብታቸው እንዲያድግ፤ በቃ። የስራ እድል መፍጠር፣ የአካባቢ ማህበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ሃገርን ማሳደግ ወዘተ ለባለሃብቱ ተጓዳኝ ጉዳዮች ናቸው። የባለሃብቶች ሃብት ሲረባ፣ እነዚህ ተጓዳኝ ፋይዳዎች መገኘታቸው ግን አይቀሬ ነው። 

በሌላ በኩል እንደሃገር ሲታሰብ  የስራ እድል ፈጠራ፣ አካባቢያዊ ልማት፣ አጠቃላይ የሃገር እድገት ወዘተ የኢንቨስትመንት ቀዳሚ ፋይዳዎች ናቸው። እነዚህ ግቦች ለባለሃብቱ ቀዳሚ ባይሆኑም ለሃገርና ህዝብ ግን ቀዳሚ ናቸው። መንግስታት ትርፍ ፈላጊውን ባለሃብት የሚያበረታቱት፣ የኢንቨስትመንት መደላድል የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ የሚጠበቅበት ለዚህ ነው። ቀዳሚው የኢንቨስትመንት መደላድል ደግሞ ሰላም ነው። ሰላም በሌለበት፤ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተገታበት፣ ብቃት ያለው የሰው ሃይል በማይገኝበት፣ ሃብት በሚዘረፍበትና በማንኛውም አጋጣሚ ሊወድም በሚችልበት ሁኔታ ሃብት አይረባም። እናም ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንት አይኖርም። መንግስት ለሰላም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የሚያደርገው አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

ከ2008 ዓ/ም መግቢያ ጀምሮ ኢትዮጵያ ሳለም ረቋት ቆይታለች። በኦሮሚያ፣ በአንዳንድ የአማራና የደቡብ ክልል አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ነበሩ ሰላሙን ያራቁት። የህዝባዊ ተቃውሞዎቹ መነሻ በመንግስት ችግር ምክንያት የተፈጠረ የህዝብ ብሶት ነው። ህዝባዊ ተቃውሞው የህዝብ ብሶት የወለደው ቢሆንም፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የግልና የህዝብ ሃብት ውድመት ምክንያት ሆኗል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ገትቷል፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን አሰተጓጉሏል። መስከረም 2009 ዓ/ም ላይ ብቻ በኦሮሚያ በመቶ የሚቆጠሩ የግል ኢንቨስትመንት ተቋማት መውደማቸው ይታወሳል።

ይህ ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስትና በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ (ኢህአዴግ) እመርታዊ የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስዱ ያስገደደ ሁኔታን አስከትሏል። አሁን ያለውን የለውጥ አመራርና የለውጥ እንቅሰቃሴ የወለደው ከሁለት ዓመታት በላይ የተካሄደ ህዝባዊ ተቃውሞ ነው። ይህ ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስትን ከነአካቴው አስወግዶ ቢሆን ኖሮ፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴው በወጉ ያልተደራጀ ስለነበረ፣ ውጤቱም ግብታዊ መሆኑ ስለማይቀር  ሃገሪቱ ምናልባት ዳግም ተመልሳ ልትገነባ የማትችልበት ቀውስ ውስጥ ትገባ ነበር። ከዚህ ቀውስ ማንም አያተርፍም ነበር፤ የለውጡ ዋነኛ ሃይል የነበረው ወጣትም (ቄሮ)፣ ተቃዋሚ ቡድኖችም አያተርፉም ነበር።  በመሆኑም ህገመንግስታዊ ስርአቱ እንደተጠበቀ እመርታዊ የለውጥ እርምጃዎች መወሰድ የሚያስችል የስልጣን ሽግግር መደረጉና የለውጥ አመራር ወደስልጣን መምጣቱ ሃገሪቱን ከጥፋት ታድጓታል።

Videos From Around The World

አሁን ሃገሪቱን እየመራ የሚገኘው የለውጥ አመራር በሃገሪቱ አንጻራዊ ሰላም አስፍኗል። በየአካባቢው ቦግ፤ እልም እያሉ የሚያጋጥሙ ግኝቶች መኖራቸው ባይካድም፣ በ2008 እና 2009 ዓ/ም ከነበረው ጋር በንጽጽር ሲታይ የተሻለና ተስፋ ሰጪ የሰላም ሁኔታ አለ። አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም የተገኘው የለውጥ አመራሩ በወሰዳቸው ፖለቲካዊ እርምጃዎች ነው።

መንግስት በሺህ የሚቆጠሩ በክስ ሂደት ላይ የነበሩና ፍርደኛ የፖለቲካ እስረኞችን በነጻ ለቋል። በውጭ ሃገራት የተቃውሞ እንቅሰቃሴ ሲያካሂዱ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖችና ግለሰቦች ወደሃገር ቤት ገብተው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አስተላልፎ፣ በዚህ ጥሪ መሰረት የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችና ግለሰቦች ወደሃገር ቤት ተመልሰዋል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያውያን መሃከል ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በይቅርታና እርቅ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል። እነዚህ እርምጃዎች በመንግስትና በህዝብ መሃከል መተማመን አስፍነዋል። ይህ መተማመን ህዝቡ የሃገሪቱ ሰላም ባለቤት መሆኑን ተገንዝቦ ሰላሙን ለእንዲጠብቅ አነሳስቷል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች አሁን የሚታየው አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ያደረጉ ቀዳሚዎቹ ምክንያቶች ናቸው።

መነግስት ከሃገር ውስጥ ባሻገር ከአጎራባችና ከመካከለኛ ምስራቅ ሃገራትም ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያሻሽሉ እርምጃዎች ወስዷል። ከአጎራባችና ከመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት ጋር በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ ግንኙነቱን ለማጠናከር የወሰዳቸው ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች፣ በተለይ በቅርቡ ሞት አልባ ጦርነት ውስጥ ከቆየንባት ኤርትራ ጋር የተመሰረተው የሰላም ስምምነት ወዘተ አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም የፈጠሩ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

በአጠቃላይ በሃገር ውስጥና በአካባቢያዊ ግንኙነት ላይ የተወሰዱ የፖለቲካ እርምጃዎች የሃገሪቱ ሰላም መሰረት እንዲይዝ አድርገዋል። አሁን እዚያም እዚህም የሚያጋጥሙ ግጭቶች ይህን የሰላም መሰረት ሊንዱ ስለማይችሉ በቀጣይ ጊዜያት አስተማማኝ ሰላም እንደሚኖር ይገመታል።

ይህ የሰላም ተስፋ ባለሃብቶች ከስጋት ቆፈን ነጻ የሚሆኑበት ጊዜ እየመጣ መሆኑን አማትረው እንዲመለከቱ አድርጓል። አሁንም በየአካባቢው በሚቀሰቀስ ግጭት የኢንቨስትመንት ስጋት መሆኑ ባይቀርም፣ ከርሞ ከስጋት የጸዳ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሊኖር መቻሉን ተገማች ያደርገዋል። ይህ ሁኔታ ኢኮኖሚው ሊነቃቃ የሚችል መሆኑን ያመለክታል።

የለውጥ አመራሩ ከፖለቲካዊ እርምጃዎች ባሻገር ኢኮኖሚው በጉልህ እንዲነቃቃ ማድረግ ያስቻለ እርምጃዎችንም ወስዷል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ በኢኮኖሚው ዘርፍ እስካሁን በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ ኢትዮ ተሌኮም፣ ይምድር ባቡር፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሳሰሉ የልማት ተቋማት የኢፌዴሪ መንግስት አብላጫ ድርሻ ይዞ በአክስዮን ሽያጭ ወደግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ መወሰኑ ከተወሰዱ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች መሃከል ቀዳሚው ነው። የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ነጻ በማድረግ ረገድ እመርታዊ ተደርጎ ሊወሰድ የመችለው ይህ የማሻሻያ እርምጃ፣ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኩባኒያዎች ትኩረት ውስጥ እንድትገባ አድርጓል።

መንግስት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዱን ተከትሎ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የ2 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ለማከናወን ስምመነታቸውን ገልጸዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ሃገሪቱ ውስጥ በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሳቢያ ተፈጥሮ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት 1 ቢሊየን ዶላር በብሄራዊ ባንክ ክምችት እንዲገባ አድርጓል። በቅርቡ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባለሃብቶች ወደኢትዮጵያ መጠተው በኢንቨስትመንት ጉዳይ ላይ መክረዋል። በተመሳሳይ የቻይና ባለሃብቶች ከዱከም እስከ ቢሾፍቱ ባለው ስፍራ ታላቅ የኢንደስትሪ ፓርክ ለመገንባት ጥያቄ አቅርበው በጉዳዩ ዙሪያ ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር መክረዋል።

ወቅታዊውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል የተወሰዱት እርምጃዎች ውጤት ማሳየት ጀምረዋል። በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት እጅግ አሻቅቦ የነበረው የጥቁር ገበያ የብር የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ሰሞኑን ተስተካክሏል። አሁን በባንክና በጥቁር ገበያ መሃከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባልታየ ሁኔታ ተቀራርቧል። እነዚህ ተጫበጭ ሁኔታዎች ኢኮኖሚው በቀጣይ በጉልህ እንደሚነቃቃ ያመላክታሉ።

በአጠቃላይ፤ መንግስት በወሰዳቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላምና የኢኮኖሚ መነቃቃት እየጠየመ የነበረውን የኢትዮጵያ ገጽታ ማፍካት ጀምሯል። ኢትዮጵያውያን በእርቅና በመደመር አንድነታቸውን ሲያጠናክሩ፣ ሰላም እነደሚኖራቸው የለውጥ አመራሩ የሶስት ወራት እርምጃዎች አረጋግጠዋል። ይህ ሰላም ደግሞ የዜጎች የተሻለ ህይወት መሰረት የሆነውኢንቨስትመንት፣ እድገትና ልማት መደላድል ነው።

 

Back to Front Page