Back to Front Page


Share This Article!
Share
ከሰላም ውጪ አቋራጭም ሆነ አማራጭ የለም

ከሰላም ውጪ አቋራጭም ሆነ አማራጭ የለም

                                            ይቤ ከደጃች ውቤ 10-26-18

 የያዝነው  ጥቅምት ወር ለኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ወር ነው ማለት ይቻላል ። በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ አሥር የሴት ሚኒስትሮች (ሃምሳ በመቶ) በአንድ ጊዜ የተሾሙት በያዝነው ወር ጥቅምት 6 ቀን 2011 እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ በዚህም በታሪካችን  ለመጀመርያ ጊዜ አሥር የሴት ሚኒስትሮች (ሃምሳ በመቶ) በአንድ ጊዜ መሾማቸው የአሁኑን ካቢኔ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ አድርጎታል፡፡

ይህም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አመራር ዐብይ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ሊሆን የሚችልና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ያለ ፋና ወጊ ተግባር ነው ፡፡  በወቅቱ ከተሿሚዎቹ ሚኒስትሮች መካከል ከአፈ ጉባዔነታቸው መነሳት እንደሚፈልጉ በማስታወቅ በፓርላማው መልቀቂያቸውን ያቀረቡት ክብርት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የአፈ ጉባዔ ኃላፊነታቸውን የሥራ መልቀቂያ በተቀበለው የተወካዮች ምክር ቤት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ወይዘሮ ሙፈሪያት  የመጀመሪያው የሰላም ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል። የሰላም ሚኒስትር የሆኑት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ለሀገሪቱ የተለያዩ የደኅንነት ተቋማትና ለፌዴራል ፖሊስ አመራር ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡በተመሳሳይ ኢንጅነር አይሻ መሃመድ ደግሞ የሃገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን በኢትዮጵያም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰየሙ እንስት የመከላከያ ሚኒስትር መሆናቸው የሚታወስ ነው።

Videos From Around The World

 የሚኒስትሮቹ ሹመት ከተሰጠ ከአስር ቀናት በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ ክብርት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ወይም ፕሬዝዳንት  ሆነው  ተመርጠዋል። ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት  ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  ሓላፊነታቸውን ለመልቀቅ ያቀረቡትን ጥያቄ ሁለቱ ምክር ቤቶች  ከተቀበሉ በኋላ ነው።ይህም ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴን በኢትዮጵያ  ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት  የተመረጡ እንስት ርዕሰ ብሔር ያደርጋቸዋል ።ከአስር ቀናት በፊት የተሾሙትን አስር ሚኒስትሮችን ጨምሮ  ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ. ም በፕሬዚዳንትነት የተመረጡት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የመደመርን ጉዞ ለመሳካት፣  ብሔራዊ መግባባትን  ለማምጣት፣  የገፅታ ግንባታን ለመፍጠር አመርቂ ሥራ ይሠራሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ለጋራ ስብሰባው ባቀረቡት መልቀቂያ ላለፉት አምስት ዓመታት ሀገራቸውን በቅንነት ማገልገላቸውንና ይህም የሚኮሩበት የታሪካቸው አካል እንደሆነ በማስታወስ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትን አመስግነዋል፡፡ ሦስቱ ዓመታት ለሀገሪቱ ፈታኝ እንደነበሩ ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ሙላቱ  ፣ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ግን በመጣው ለውጥ በርካታ አመርቂ ውጤቶች  መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

 ዶክተር  ሙላቱ ይዘው የቆዩትን የርዕሰ ብሔር ኃላፊነት የሚያስረክቡት በአሁኑ ጊዜ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የሚያስችል አመራር ወደ ኃላፊነት እየመጣ በመሆኑ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ካሁን በኋላ የመንግሥት ሥልጣን ከብሔርና ከፆታ አኳያ ብቻ መታየት እንደሌለበትም ያስገነዘቡት ዶክተር ሙላቱ ያቀረቡት የፕሬዚዳንትነት መልቀቂያም በጋራ ስብሰባው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የሁለቱ ምክር ቤቶችም  አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት አድርገው መርጠዋል፡፡ ዶክተር ሙላቱ ተሾመም ሥልጣናቸውን በይፋ ለአዲሷ ፕሬዚዳንት አስረክበዋል፡፡

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በዕለቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት በመሆን በተሾሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ታላቅ ሀገር የመገንባት ህልምን ዕውን ለማድረግ ከሰላም ውጪ አቋራጭም ሆነ አማራጭ መንገድ እንደሌለ ገልፀዋል።ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በንግግራቸው፥ የኢትዮጵያ እና የህዝቦቿ ርእሰ ብሔር በመሆን ለማገልገል በመመረጣቸው ደስታና ክብር እንደተሰማቸው ገልፀዋል።አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ የበኩላቸውን ሲወጡ ለነበሩትና  በገዛ ፍቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለለቀቁት ለኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የሚወዷትን ሀገራቸውን ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩ ትልቅ የሀገር ባለውለታ ናቸው፤ በዛሬው እለትም ባደረጉት ተግባር በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ከተለመደው ውጪ በገዛ ፍቃድ ስልጣን በመልቀቅ ለለውጥ እድል መስጠት መጀመሩን ልንማር ይገባል።

 

ይህ ተግባር በክልሎች፣ በየደረጃው በሚገኙ የአስተዳደር አካላት፣ በመንግሥትና በግል ተቋማትም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ ተቋማት ጭምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

፥ በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በሴቶችም ሆነ በወንዶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ከተመራ ኢትዮጵያ ከድህነት እና ኋላቀርነት ተላቃ ወደ ብልጽግና ጎዳና የምታመራበትና ዜጎቿን ከመድሎዎ በፀዳ መልኩ በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር እውን እንደሚያደርግ እተማመናለሁ ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ። የለውጥ ጉዞው ውስብሰብ እና በርካታ ፈተናዎች ያሉቡት እንደሚሆን ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ እነዚህን ፈተናዎች መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች የጋራ ቤት እንደሚገነባ ቤተሰብ እርስ በአርስ በመደማመጥ፣ በመፈቃቀድና በመተሳሰብ አንድነትን በማጠናከር መሻገር እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በንግግራቸው ታላቅ ሀገር የመገንባት ህልምን ዕውን ለማድረግ ከሰላም ውጪ ምንም አቋራጭም ሆነ አማራጭ መንገድ የለም ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ስለዚህ ሁላችንም ሰላማችንን አጥብቀን እንድንጠብቅ ከሁሉ በላይ ሰላም ሲታወክ በምትጎዳዋ እናት ሰም እጠይቃለሁ ሲሉ ተማፅነዋል።ኢትዮጵያዊነትን ከሰላም ጋር አንድ ለማድረግ እንሥራ ያሉት ፕሬዚዳንቷ  ባቀረቡት ጥሪ ሰላምና ጤና ሰላምና ሥራ የልማት መሠረት መሆናቸውን ጠቁመዋል።ሰላም የልማትና ብልጽግና ምልክት በመሆኑ፤ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሴቶችም ሆነ ወጣቶች እንዲሁም ሁሉም የሀገረቱ ህዝቦች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንዱረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

አያይዘውም የሰላም እጦት ዋነኛ ተጠቂዎች ሴቶች በመሆናቸው፥ በስልጣን ቆይታቸው ዋነኛው ትኩረታቸው መላው ኢትዮጵያን ሴቶችና ሰላም ወዳድ ወንዶችን እንዲሁም በመላው ዓለም የሚገኙ ሰላም ወዳዶችን ሁሉ ከጎናችው በማሰለፍ ሰላም በማስፈን ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።በዚህም የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።

የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና የስልጣኔ ምልክት የሆነቸው ኢትዮጵያ ድህነትና ኋላ ቀርነት ውስጥ እንደትቆይ ያደረጋት የሰላም እጦት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ የሰላም ጠንቅ የሆኑትን በማስወገድ የሀገሪቱ እድገትና ብልጽግናን አይቀሬነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አንስተዋል።ስለ ዕድገትና ብልጽግና ሲወሳ የሴቶችና ወጣቶች እኩል ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት መላው የሀገሪቱ ሴቶች እና ወጣቶች በርትተው በሀገሪቱ ልማት ተሳታፊ በመሆን ድህነትን በጋራ እንዲያስወግዱም አደራ ብለዋል።

ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ወሳኝ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራሲ ሥር እንዲሰድ በማድረግ በሐላፊነት መንገድ እንዲሰሩም ነው ያሳሰቡት።ህዝቡም የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ለውጡን ለሚመራው የፖለቲካ ሀይል የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ሴቶች ከወንዶች በተሰማሩበት ማለትም በቤት ውስጥ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው ኑሮን ለማሸነፍ ሌት ተቀን የሚተጉ ለእኔ ባያልፍልኝ ለልጆቼ ለሀገሬ ያልፋል በሚል ትግል የሚያደርጉ ሴቶች ከጥረታቸው ወደ ኋላ እንዳይሉ አደራ ብለዋል።በወንዶች ጥረት ብቻ የተገነባ ሀገርም ሆነ ቤተሰብ የለም ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ሴቶች የቤትም የሀገርም ምሰሶ ናቸው፤ ሴቶች ከተጎዱ ቤተስብ ይጎዳል ሀገር ይጎዳል፤ ስለዚህ ሴት ሀገር ነች፤ ሀገርን ደግሞ ወንዱ ሊንከባከብ ይገባል ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ20 የካቢኔ አባላት 10 ሴቶች እንዲሆኑ መደረጉ እና እሳቸውም ለዚህ እንዲበቁ መሆኑ በአሁኑ ወቅት እየመጣ ካለው ለውጥ ተጠቃሽ ነው መሆኖን በአፅንዖት ተናግረዋል።የእስካሁኑ የሴቶች የትግል ጉዞ ዕውን እንዲሆን ሀላፊነት ከተረከቡ አንስቶ እስከ ዛሬዋ ድረስ ከፍተኛ ሥራ በመሥራት ላይ ለሚገኙት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሁን የጀመሩት አካታች ፖሊሲ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶች ብሎም ለቤተሰብ እና ለሀገር መልካም በመሆኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉበት አደራ ብለዋል።

የክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቀ ዘውዴን መመረጥ አስመልክቶ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሠፊ ሽፋን በመሥጠት ዘግበዋል ።  የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ ሓላፊዎች ለኢትዮጵያ  መንግሥትና ሕዝብ የደስታ መግለጫ አስተላልፈዋል።

 ለኢትዮጵያ በዲፕሎማትነት ለረጅም ጊዜ በተለያዩ ሀገሮች በአምባሳደርነት ያገለገሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በክፍለ አህጉራዊና አህጉራዊ ድርጅቶች ከመሥራታቸው በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ተመርጠው በተለያዩ ሥፍራዎች አገልግልዋል። የካበተ የዲፕሎማሲ ልምድ ያላቸው አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት  ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ሀገራችን ከተለያዮ ሀገራትና ከዓለም አቀፍ ተማት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት በውጤት እና በስኬት የታጀበ ያደርገዋል።እንዲሁም ሀገራችን የተያያዘችውን የለውጥ ጎዳና ያማረና የሰመረ ያደርገዋል።

ሌላው ከዚሁ ጎን ለጎን መታየት ያለበት ከሹመት በሁዋላ የሚጠበቅባቸውን ሓላፊነት አገልግለው ሥልጣንን ለተከታይ አለመልቀቅና ተተኪ ዜጋን አለማዘጋጀት ነው።

 ዜጎች ከፍተኛ ሓላፊነት ከተመረጡ በሁዋላ ሥልጣን የሚለቁት ወይ በሞት አሊያም በብረት ማለትም በጦር መሣርያ ነው።ሥልጣን በቃኝ የሚል አመለካከት መጨበጥ አለብን።በሹመት የወጣ ሓላፊ የሚጠበቅበትን ብሔራዊ ግዴታ በተገቢው መልኩ ከተወጣ ሥልጣኑን ለመልቀቅ አያንገራግርም። በሹመት የወጣ በሽረት እንዳይወርድ በተገቢው ማገልገል ከቻለ ከሓላፊነት ሲወርድ በሀገሩ ጎዳናዎች ነፃና ሰላም ሆኖ ይዘዋወራል የህዝብ ፍቅር ያገኛል ።

በሹመቱ ወቅት ግዴታውን መወጣት ካልቻለ፣ በሌብነት ከተጨማለቀ አማራጩ መደበቅ ብቻ ነው። ነፃ ሆኖ ለመዘዋወር ወዳጅ ዘመዶቹን ለመጠየቅ ወይም ለመዝናናት ቢፈልግም ቅሉ የሠራው ሸፍጥ አናቱን ይበጠብጠዋል። ስለዚህ አማራጩ ሌሌት መጉዋዝ ብቻ ይሆናል።ሥልጣንን እንደርስት ጉልት አድርጎ መመልከት ሓላፊነትን በሚገባ በመወጣት ተተኪዎችን አፍርቶ በመተካት መታጀብ አለበት።

በሀገር ውስጥ ሐላፊነታቸውን በጥሩ ሁኔታ የተወጡ ዜጎች ሓላፊነታቸውን ሲለቁ ወደ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተማት ገብተው ለመቀጠር ይችላሉ።የተሻለ ሥራ ሠርተው ካለፉ ለሌሎች ተተኪዎችም ምሳሌ ይሆናሉ። በመሆኑም ሥልጣንን በሞት ወይ በብረት (በጦር መሣርያ) ከማጣት በክብር ሓላፊነትን አስረክቦ መልቀቅ በሀገራችን ሊለመድ ይገባል። የሰላም አንዱ መሣርያ ሓላፊነትን በአግባቡ ተወጥቶ ሥልጣንን ማስረከብ ነዋና።ይህ ሲሆን ደግሞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሥልጣን ሽኩቻዎችን መክታትና መግራት ይቻላል።

Back to Front Page