Back to Front Page


Share This Article!
Share
ህዝቡ የለውጡ ባለቤትና አራማጅ ሆኗል

     ህዝቡ የለውጡ ባለቤትና አራማጅ ሆኗል

ዓለምአየሁ አ 06-29-18

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ የህዝብን ይሁንታ ያገኙ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶች መመዝገባቸው እውነት ነው። ኢትዮጵያ የብሄር ብዝሃነት ያላት ሀገር ሆና ሳለች ለዚህ ብዝሃነት እውቅና በመንፈግ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የተካሄደው የመጨፍለቅ ዘመቻ ቋጠሮ ውሉ ተፈተቶ ብሄሮች መብቶቻቸውንና ነጻነታቸውን የተጎናጸፉት ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ነው። አሁን በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ የቆጠራል እንደሚሉት ሆኖ አዲሱ ትውልድ ለዚህ ድል ሲዘምርለት ባይታይም፤ በጭቆናው ውስጥ ላለፍን ግን በልባችን ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይዞ የሚኖር ድል ነው።

በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና መሰረተ ልማት ዘርፎችም ጉልህ ስኬቶች ተመዝግበዋል። ኢኮኖሚው ለይህን ዓመታት በይህን ያህል በመቶ አደገ የሚለውን የሰለቸ የእድገት ገለጻ ከመጠቀም ይልቅ የሚታይ ተጨባጭ አመላካቾችን ላንሳ። ከሃያ ሰባት ዓመታት በፊት አርሶ አደሩ የመሬት ባለይዞታነት መብቱ ቢረጋገጥም፣ ከፊውዳላዊው ገባር ስርአት ብዙም ባልተለየ ሁኔታ ምርቱ ላይ የባለቤትነት መብት አልነበረውም። አርሶ አደሩ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመሬቱን ለምነትና መሬቱ የሚሰጠውን የምርት አይነት፣ የማምረት አቅም ወዘተ ባለገናዘበ ሁኔታ ምርቱን ለመንግስት በዝቅተኛ ገበያ እንዲያቀርብ በአይነትና በመጠን ኮታ ተቆርጦ ግዴታ ይጣልበት ነበር። ግማሽ ያህል የሚሆኑ የአገሪቱ አርሶ አደሮች የቤተሰባቸውን ፍጆታ ሸፍነው በአይነትና በመጠን የተጣለባቸውን ኮታ ማቅረብ አይችሉም ነበር።  በዚህ ሁኔታ ለልብስ፣ ለጋዝ፣ ጨው ወዘተ ፍጆታ ወጪያቸውን ለመሸፈን ከግብርናው ጎን የሚያረቧቸውን ከብቶች ሸጠው እህል በውድ ዋጋ ከገበያ ገዝተው በዝቅተኛ ዋጋ ለመንግስት በማቅረብ የተጣለባቸው ኮታ የሚያሟሉ አርሶ አደሮች ቁጥር ቀላል አልነበረም።

ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የሞያ፣ የግብአትና የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኝበት ስርአት አልነበረም። እናም የግብርናን ያህል ባረጀ ቴኮኖሎጂና የአመራረት እውቀት የሚካሄደው ግብርና ካስከተለው በወጉ ከእጅ ወደአፍ እንኳን መሆን የማይችለው የአርሶ አደሩ ምርት፣ የመንግስት ኮታ ተደምሮበት አርሶ አደሩን በቀን ሶስቴ መመገብ እንዳይችል አድርጎት ቆይቷል።

Videos From Around The World

አሁን ይህ ሁኔታ በአመዛኙ ተቀይሯል። አርሶ አደሩ ምርቱ ላይ የማዘዝ ሙሉ መብት አለው። ምርታማነቱን ማሳደግ የሚያስችለው የሞያ፣ የግብአትና የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለታል። ይህ ሁኔታ ምርታማነቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት አስችሏል። የምርታማነቱ መጨመር ገቢውን በማሳደግ ኑሮው ቀደም ሲል ከነበረው በጉልህ እንዲሻሻል አድርጓል። ባለጸጋ ለመሆን የበቁ አርሶ አደሮችም አሉ። በዚህ ዙሪያ ከዚህ በላይ ማተት አልፈልግም። በተጨባጭ ያለ እውነት ስለሆነ የአርሶ አደሩን ኑሮ መመልከት በቂ አሰረጂ ነው።

አጠቃላይ የሃገሪቱን ህዝብ 85 በመቶ ገደማ የሚሸፍነው አርሶ አደር፣ መጠኑ ይለያይ እንጂ ገቢው ማደጉ በሃገሪቱ ትልጥ የገበያ አቅም ፈጥሯል። ይህ ትልጥ የገበያ አቅም የነጋዴዎችና አምራቾች ትርፍ እንዲያድግ አድርጓል። ይህ ደግሞ የሃገሪቱን አጠቃላይ የካፒታል ክምችት በማሳደግ የኮንስትራክሽን፣ የአገልግሎትና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአምራች ዘርፉ እንዲፈጠርና እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል። በሁሉም የሃገሪቱ ከተሞች የታየው እድገት የዚህ ወጤት ነው።

በመሰረተ ልማት፣ በትምህርትና ጤና አገልግሎትም አጅግ ከፍተኛ እድገት ታይቷል። የአገልግሎት አሰጣጥና የጥራት ችግር መኖሩ ሳይዘነጋ በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች አርሶ አደሩ በቅርብ ርቀት የጤናና የትምህርት አገልግሎት ማግኘት ይችላል። በንጹህ መጠጥ ወሃ አቅርቦትም ቢሆን ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ድንቅ እድገት ተመዝግቧል።

እንግዲህ፤ እነዚህ ከላይ ውስብስብ ሞያዊ ትንታኔንና አሃዝን ወደጎን በማድረግ በማንኛውም ተራ ሰው ማስተዋል ሊታወቁ የሚችሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች በተለይ አርሶ አደሩ ማህበረሰብ በመንግስት ላይ እምነት እንዲኖረውና ተስፋ እንዲያድርበት አድርጎ መቆየቱ እውነት ነው። ነገር ግን ከተጨባጭ እድገትና ለውጥ ባሻገር ከርእዮተ ዓለም ልዩነት የመነጨ የፖለቲካ ፍትጊያ ባለባቸው ከተሞች፣ በተለይ ትላልቅ የሃገሪቱ ከተሞች በመንግስት ላይ ያለው እምነት እንደገጠሩ አልነበረም። ከዚህ በተጨማሪ ከተሜው እንደ አርሶ አደሩ ከመሬትና ማምረቻ መሳሪያ ጋር የተቆራኘ ባለመሆኑ፣ የስራ እድል አግኝቶ ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረጉ ተግባር ቀላል አልነበረም። ይህ ሁኔታ ወደከተማ ከሚደረግ ፍልሰትና አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተዳምሮ በሃገሪቱ ሲመዘገብ በቆየው እድገት ጉልህ መሻሻል ማሳየት ያልቻለ የስራ አጥነት ችግር ታይቷል።

የሃገሪቱ መሰረታዊ የፖለቲካ ሃይል የብሄሮች ብሄረሰቦች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ፖለቲካዊ አመለካቶችም በመሆናቸው እነዚህን አመለካከቶች ማስተናገድ የሚያስችል ዴሞክራሲን ከመገንባት አኳያ በተፈጠረው ሰፊ ክፍተት ሳቢያም የፖለቲካ ተቃውሞዎች ተቀስቅሰዋል። በዚህ ሁኔታ ዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ ጥያቄ ተጋግሎ መቅረብ ጀመረ።  የልማት ፍላጎት ቀደም ሲል ከነበረው መሻሻል በማሳየት ብቻ የሚረካ ሳይሆን ተጨማሪ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ከከተማ ባሻገር ከፍተኛ አንጻራዊ የኑሮ መሻሻል በታየባቸው የገጠር አካባቢዎችም ቢሆን ተጨማሪ የልማት ጥያቄዎች ማነሳታቸው አልቀረም።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ በተደጋጋሚ ገዢ ሆነው መቀጠላቸው ገዢነቱን እንደርስት የወሰዱ ሃላፊዎችን ሳይፈጥር አልቀረም። እነዚህ ገዢነትን እንደርስት የተመለከቱ በየደረጃው ያሉ የስራ ሃላፊዎች፣ ስልጣናቸውን የግል ፍላጎትን ማሳኪያ መሳሪያ አድርገው መጠቀምን ተለማምደዋል። ይህ ህዝቡን ያማረረ የመልካም አስተዳደር መጓድል ምክንያት ሆኗል። ስልጣንን ለግል መጠቀሚያ ማዋል በከራይ ሰብሳሰቢነት የሚገለጽ በመሆኑ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን አዛብቷል። የተወሰኑ የማይገባቸውን ሃብት አጋብሰው ሲበለጽጉ፣ በርካቶች የሚገባቸውን አጥተው፣ ይዘው የነበረውንም ተነጥቀው ለድህነት ተዳርገዋል።

እነዚህ ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ሃገሪቱን ያስተዳደረው ኢህአዴግ ላይ የታዩ ጉድለቶቹ ከስኬቶቹ ልቀው ታይተዋል። ይህ ሁኔታ የፈጠረው ቅሬታ ወደህዝባዊ አመጽነት ለመቀየር በቅቷል። ህዝባዊ ተቃውሞው የብዙዎችን ህይወት አስከፍሎ፣ በመጨረሻ ፍሬ አፍርቶ መንግስት ራሱን ለማሻሻል እንዲወስን አድርጎታል። አነሆ በህዝባዊ ተቃውሞ ወደሃላፊነት የመጣው የለውጥ አመራር በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ተጨባጭ የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።

የተለያዩ አመለካከቶችን ማስተናገድ የሚያስችል የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር፣ እንዲሁም በተካረረ የአመለካካት ልዩነት የተፈጠረውን የሃገራዊ አንድነት መላላት ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከተወሰዱት እርምጃዎች መሃከል በእስር ላይ የነበሩ ፍርደኛና በክስ ሂደት ላይ የነበሩ የወንጀል ተጠርጣሪ ፖለቲከኞችን በይቅርታና ክስ በማቋረጥ በነጻ እንዲሰናበቱ ማድረግ ተጠቃሽ ነው። በውጭ ሃገራት ይንቀሳቀሱ ለነበሩ ፖለቲከኞች የተላለፈው የሰላም ጥሪ፣ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች በምህረት ወደሃገር ቤት የሚመለሱበትን እድል ለመፍጠር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምህረት አዋጅ መጽደቁም የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት፣ ሃገራዊ መግባበትን የመፍጠርና የማጠናከር እርምጃ አካል ነው።

እስካሁን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማደረግ ወደሃገር ቤት ተመልሷል።  ለትጥቅ ትግል በውጭ ሃገር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦችም ወደሃገር ቤት ተመልሰዋል። ወደሃገር ቤት ለመመለስ በዝግጅት ላይ ያሉም አሉ። በሜጀር ጄነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ አንድነት ሃርነት ግንባር ወደሃገር ቤት ለመመለስ የልኡካን ቡድን ልኮ በመንግስት አቀባበል ተደርጎለታል። ጄነራል ከማል በቅርቡ ወደሃገር ቤት የመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። አርቦች ግንቦት 7 የተባለው ንቅናቄ በኢትዮጵያ ውስጥ  ሲያካሂድ የቆየውን የአመጽ እንቅስቃሴ ለጊዜው ማቆሙን አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከአጎራባችና ከመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት ጋር ያለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር የወሰዷቸው ርምጃዎች፣ በተለይ በእነዚህ ሃገራት በእስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በነጻ ተለቀው ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸው በህዝቡ ዘንድ እንደትልቅ ስኬት ተወስዷል። ከኤርትራ ጋር ያለውን የሰላም ችግር ለመፍታት የተጀመረው ጠረትም በበጎ ጎኑ ነው የታየው። በአጠቃላይ የለውጥ አመራሩ የሚከተለው የእርቅ፣ የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር (አንድነት) መንፈስ በህዝቡ ላይ ሰፍኖ ትልቅ ሃገራዊ መግባበትና መነቃቃት ተፈጥሯል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደው ምናልባት በሃገሪቱ ታሪክ ባልታየ ሁኔታ 4 ሚሊየን ገደማ ህዝብ የተሳተፈበት የእውቅናና የምስጋና ሰልፍ የዚህ በህዝብ ላይ ያደረ ተስፋና መነቃቃት፤ የእርቅ፣ ይቅርታና አንድነት መንፈስ መገለጫ ነው። ሰልፉ ልዩነቶች በአንድ ላይ የተስተናገዱበት ነበር። በጅግጅጋ፣ በጎንደር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በወልቂጤ ተመሳሳይ የምስጋና የእውቅና የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል።  የድጋፍ ሰልፉ በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎችም የቀጥላል ተብሎ ይጠብቃል።

እነዚህ ሁኔታዎች ህዝቡ ለለውጡ ሂደት የሰጠውን ይሁንታ ያረጋግጣሉ። ለውጡ በህዝቡ ይሁንታ የተሰጠው ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል እንደገለጽኩት በህዝቡ ገፊነት የተገኘም ነው። በህዝቡ የተገኘና በህዝቡ ይሁንታ የተሰጠው መሆኑ የሚፈለገውን ውጤት የማስገኘት አቅም እንዲኖረው ያደርጋል።

እነዚህ ህዝቡ ከለውጥ አመራሩ ጋር መሆኑን ለመግለጽ በራሱ ተነሳሸነትና አደራጅነት ያዘጋጃቸው በሃገሪቱ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ ህዝባዊ ሰልፎች ለውጡን የማስቀጠል ጉልበት የሚሰጡ መሆናቸው ሳይዘነጋ፣ በተለይ በአዲስ አበባው ሰልፍ ላይ ያጋጠመው የቦምብ ጥቃት ህዝቡን አሳዝኗል። የቦብምብ ጥቃቱ ዓላማ የለውጡን ሂደት ማደናቀፍ ነው። በምልዓተ ህዝቡ ድጋፍ ያገኘውን ለውጥ የማደናቀፍ አቅም እንደማይኖረው ግን ግልጽ ነው። የቦምብ ጥቃቱ የለውጡን ሂደት ከማደናቀፍ ይልቅ ህዝቡን እልህ ውስጥ በማስገባት የሚያጠናክር ሆኗል።

ሆኖም በቦምብ ጥቃቱ የሁለት ንጹሃን ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። እነዚህ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ዜጎች ላይ ይነበብ የነበረው ጥንካሬና ለውጡን ለማስቀጠል መስዋዕትነትን ለመቀበል ያላቸው ዝግጁነት፣ ለውጡን ለማደናቀፍ ለሚሯሯጡ ቡድኖች ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል። ከዚህ በተጨማሪ ተጎጂዎቹን ለመደገፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ10 ሚሊየን ብር፣ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልላዊ መንግስት የ15 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማደረግ መወሰናቸው በመደመር ለውጡን ለማሳካት ያለው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል። አሁን ህዝቡ የለውጡ ባለቤትና አራማጅ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል።  

  

 

Back to Front Page