Back to Front Page


Share This Article!
Share
የልዕለ-ሃያሉ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ የ120 ቀናት ህፀፆች

የልዕለ-ሃያሉ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ የ120 ቀናት ህፀፆች

ከፍትህ ይንገስ 08-05-18

ሁላችንም እንደምናቀው ኢህአዴግ ባለፉት ህያ ሰባት አመታት ለፈፀማቸው ጥፋቶች ሁሉ ግልፅ በሆነ መንገድ ይቅርታ ጠይቆ በአዲስ መንፈስ ለመንቀሳቀስ ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ካሳወቀ ወራት ተቆጥረዋል። እንቅስቃሴውን የመምራት ሃላፊነትም የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ለሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ አስረክቧል። ዶ/ር አብይም ሃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ ምንም እንኳ እየተካሄደ ያለው ለውጥ እመራዋለሁ በሚሉት ፓርቲ ሳይሆን በርሳቸው ተሰጥዖ፣ ልህቀትና  በጎ ፈቃድ እንደሆነ በሚያመላክት ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ቢሆንም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያግዛሉ ያሏቸውን በጎ የሚመስሉ ግን ገና ያልተፈተኑ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ እርምጃዎች በስፋት ተዝምሮላቸዋል፤ አሁንም እየተዘመረላቸው መሆኑን ሁላችንም እንገነዘባለን። በመሆኑም ይህ ፅሁፍ በነዚህ በጎ በሚመስሉ የዶ/ር አብይ ርምጃዎች ዙሪያ አይሽከረከርም። ከዚህ ይልቅ የዚህ ፅሁፍ አላማ አሁን ያለው መነሳሳት ግለቱን ጠብቆና መስመሩን ሳይስት ሊቀጥል እንዲችል ለማገዝ በሚረዳ መልኩ ሊታረሙ ይገባቸዋል በሚባሉ ቁምነገሮች ላይ ሃሳቦችን መሰንዘር ይሆናል። በዚም መሰረት አንኳር አንኳር ሊባሉ የሚችሉ ህፀፆችን እንደሚከተለው ለማምብራራት እሞክራለሁ።

ኢህአዴግን በተመለከተ፡

አሁን በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ኢህአዴግ አቅጣጫ የጠፋበት ድርጅት/ግንባር ሆኗል ። ኢህአዴግ ገና ሲፀነስ ጀምሮ  በሳይንሳዊ መንገድ አጥንቶ የስርዓቱ አደጋዎች ናቸው ብሎ የለያቸው ትምክህትና ጠባብነት ምንም እንኳን በስግብግብ፣ አልጠግብ ባይና ማናለብኝነት በተሞሉ መሪዎቹ  ምክንያት ሳይንሱ ፈሩን ለቆ ማጥቂያና አንገት ማስደፊያ እንዲሆን ተደርጎ የቆየ ቢሆንም አሁን ደግሞ እነዚህ የማይታረቁና አድህሪ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ አንድነት ጠንቅ የሆኑ አመለካከቶች የበላይነቱን ይዘው ላዩ ላይ  እየጨፈሩበትና ጠልፈው ሊጥሉትም ጫፍ ላይ የደረሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዚህም ይመስላል "ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ" ይሉ የነበሩ ጠባቦች ባንድ በኩል "ሰው የፈጠረውን አምላክ እንደሚያመልከው ሁሉ ኢትዮጵያም የፈጠራትን አማራ ማምለክ አለባት" ብለው የሚሰብኩ  ትምክህተኞች አሁን ባለው መድረክ ዋና ተዋንዮች ሆነው የቀረቡት። ከዚህ በመነሳት በአንክሮ ለተመለከተው ሰው ኢህአዴግ እጅግ በተወሳሰበ ችግር ውስጥ እየዳከረ እንዳለ መገንዘብ አያቅተውም።

የኢህአዴግ ችግር በውስጡ ባለው ተቋማዊ ክፍፍል፣ የስልጣን ሽኩቻ፣ አለመተማመን፣ ክህደትና የእርስ በርስ መጠላለፍ ብቻ የተወሰነ  ሳይሆን በርዕዮተ-ዓለም ደረጃም ቢሆን የት ላይ እንደቆመ ለማወቅ የተቸገረበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለዚህም ነው ሁሉም ነገር ዶ/ር አብይ ላይ ተንጠልትሎ የሚገኘው። በመሆኑም ዶ/ር አብይ አንድም ሶስትም (ህግ አውጭ፣ ህግ አስፈፃሚና  ህግ ተርጓሚ) ሆነው እየተንቀሳቀኡ ይገኛሉ። ሲፈልጉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትን ተግባራት ያከናውናሉ፤ በል ሲላቸው ደግም የፍትህ አካላቱን ስራዎች ጠቅልለው ይሰራሉ፤ ከነዘህ ባሻገር የካቢኔ አባላቶቻቸውን የስራ ሃላፊነቶች ለመወጣት በመዳከር ላይ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ዶ/ር አብይ አሁንም ሲሻቸው የኢህአዴግ መሪ ይሆናሉ፤ ሲያስፈልጋቸው ደግሞ የተቀዋሚው ጎራ መሪ ሆነው ይገኛሉ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ የኢህአዴግና የተቀዋሚው ጎራ ጣምራ መሪ ሆነው መታየት ይፈልጋሉ። ከዚህ ጉዳይ ጋ በተያያዘ  ዶ/ር አብይ በደንብ ሊረዱት የሚገባቸው አንኳር ነጥብ ግን አለ። ይህም አንድ የፖለቲካ መሪ የተለያየ ርዕዮተ-ዓለም የሚከተሉ ዜጎች መሪ ሊሆን የማይችል መሆኑን ነው። እንዲህ አይነት ሁኔታ የዴሞክራሲ ተምሳሌት ተደርጋ የምትወሰደውን አመሪካን ጨምሮ በየትኛውም የአለም ክፍል ታይቶ አይታወቅም። ይህ ያልጠራና መርህ የሌለው አካሄድ ሳይታረም ከቀጠለ ደግሞ ዶ/ር አብይና ተከታዮቻቸው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሃገሪቱ እና ህዝቦቿ እንዲበታተኑ እየሞሸሯቸው እንደሆነ ሊገንዘቡት ግድ ይላል።።

Videos From Around The World

ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ ዶ/ር አብይ ወደ አቅላቸው ተመልሰው በመርህ ላይ በመመስረት ፕሮግራማቸውንና ደንባቸውን ግልፅ ያድርጉ። አንድም እስከአሁን እንደነበረው ኢህአዴግ ግራ ዘመም (Left Wing)  ነው ይበሉን፤ ካልሆነም ወደመሃል (Centre) መጥቷል ብለው ያሳውቁን፤ ካለበለዚያ ደግሞ ቀኝ ዘመም (Right Wing) ሆኗል ይበሉና ይንገሩን። በሌላ በኩልም ከህዝቡም ይሁን ከተቃዋሚዎች ብሎም በራሳቸው ድርጅት ውስጥ ያላቸውን መርህ የሌለው (Unprincipled) የሆነ ግንኙነታቸውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ፈር ያስይዙት።  ዶ/ር አብይ ይህን ማድረግ ከቻሉ የፈለገ ድርጅት ከኢህአዴግ ጋ ይቀጥላል ያልፈለገ ደግሞ ትቶ ይወጣል ማለት ነው። ሂደቱ በዚህ መልክ ጠርቶ ከቀጠለና ከሁለት አመት በኋላ  የሚካሄደው ምርጫ እውነተኛ፣ ገለለተኛ፣ ነፃና ደሞክራስኪያዊ ሊሆን ከቻለ ህዝቡ በሚፈልገው መንግስት የመተዳደር እድሉ የሰፋ ይሆናል።

ሃገሪቱ ውስጥ ያሉ እንቅስቃሴዎች የግለሰብ ለዕልና ግንባታ ላይ ያነጣጠሩ መሆኑ፡

በሃገራችን አሁን እያየን ያለነው የህግና የተቋማት ሳይሆን የግለሰብ ልዕልና ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ላይ መሆናችን ነው። ይህም ማለት ዶ/ር አብይ የፈለጉትን ተግባር በፈለጉት ቦታ፣ ጊዜና መጠን መስራት የሚችሉ መሆኑን እንጅ የህግ ገደብ እንዳለባቸው እንኳን የተረዱ የማይመስሉበት ደረጃ ተደርሷል። ለማሳያ ያህል የተወሰኑ ጉዳዮችን እንደሚከተለው መጥቀስ ይቻላል።

·       ኢትዮ-ኤሪትያን የተመለከተው የአልጀርሱ ስምምንት:

 

እንደሚታወቀው ይህ ስምምነት በ1993 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በፀደቀበት ወቅት "ከአምስቱ  የሰላም ቅድመ ሁኔታዎች" ጋ ነበር። አሁን በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ የሚያሳየው ግን "አምስቱን የሰላም ቅድመ ሁኔታዎች" ሳያካትት የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንደተቀበለው ነው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ይህ አሁን በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስምምነት ላይ ተደረሰበት የተባለው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ 1993 ዓ.ም ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካፀደቀው ውሳኔ ጋር ይለያያል። ይህ በመሆኑም ሂደቱ በህግ አግባብ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ1983 ዓ.ም ያፀደቀውን ውሳኔ እንዲሽርና አዲሱን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያፀድቅ ይጠበቅበት ነበር። ይህን ጉዳይ በተመለከተ የተሄደበት አግባብ ግን መሰረታዊ የህግ ጥሰት ያለበት መሆኑን መረዳት ይቻላል። ምክንያቶቹ ደግሞ ሶስት ናቸው። አንደኛው ምክንያት የውሳኔ ሃሳቡ የቀረበው በፖለቲካ ፓርቲ እንጅ አግባብ ባለው የመንግስት አካል ፀድቆ አይደለም። የተወካዮች ም/ቤት ይቅርና የሚንስትሮች ም/ቤትም የተወያየበት አይመስልም። ሁላተኛው ምክንያት ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ1993 አ.ም ያጸደቀውን ውሳኔ አልሻረም። ሶስተኛ  የተወካዮች ም/ቤት በቅርቡ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስምምነት የተደረሰበት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ያሳለፈው ውሴኔ አልነበረም ብቻ ሳይሆን ውይይትም አላደረገበትም።

 

ከለአይ የተገለፀው የህግ ዝንፈት ሳይስተካከል ዶ/ር አብይ ያደረጉት ግን በቅርብ ጊዜ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያስቀመጠውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንደ መጨረሻ የሃገሪቱ  መንግስት ውስኔ በመቁጠር ለህዝብ መግለፃቸውና ወደ ተግባርም መግባታቸው  ነበር። ከዚህ አልፎም የህዝብ ተወካዮች  ም/ቤት ዶ/ር አብይን ጠርቶ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ በጠየቀበት ወቅት የሰጡት መልስ በማን አለብኝነት የተሞላና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላትን የናቀ በሚመስል ሁኔታ ነበር። እንደ ዶ/ር አብይ መልስ አሁን እያስፈፀሙት ያለው ውሳኔ በ1993 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፀደቀውን የመንግስት ውሳኔ ነው። ይህ ግን ከላይ በዚህ ፅሁፍ ከተገለፁት ምክንያቶች አንፃር ሲታይ  መሰረት የሌለውና ከእውነታ የራቀ መልስ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ  በአጭሩ የ1993 ዓ/ም የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውሳኔ ካሁኑ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ የሚለይ በመሆኑ ነው። የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላትም ጠቅላይ ሚንስትሩ የተሳከረ መልስ በመስጠታቸው ምክንያት ተጠያቂ በማድረግ ይቅርታ እንዲጠይቁ ከመጋፈጥ ይልቅ ጠቅላይ ሚ/ሩ ያቀረቡትን ሃሳብ ተቀብሎ በጭብጨባ መሸኘት ነበር።። ይህ ሂደት ያሳየን ነገር ቢኖር የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ምን ያህል ልዕልናውን በሃላፊነት ተዋረድ  ከበታቹ ላለ ግለሰብ አሳልፎ የሰጠ እንደነበረ ነው። እንዴው ከበቅሎ ልጅ የመጠበቅ ያህል ይሆናል እንጅ የተዎካዮች ም/ቤት የጠቅላይ ሚንስትሩን አካሄድ ባይቀበለው ኖሮ ምን ይውጣቸው ነበር???

 

 

 

·       የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት፡

 

መንግስት የመደበኛውን የህግ ስራዓት ተጠቅሜ ህግና ስራዓትን ማስከበር እችላለሁ የሚል አቋም እስከወሰደ ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳቱ  በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች መከበር ረገድ ካለው አሉታዊ ተፅዕኖ አንፃር ሲታይ ሊደገፍ እንጅ ሊነቀፍ የሚገባው አልክነበረም፤ ምንም እንኳን መተቸት መብት ቢሆንም። ችግሩ የነበረው ጠቅላይ ሚ/ሩ አዋጁ መነሳቱን ያሳወቁበት መንገድ ነበር። እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚ/ሩ አዋጁ እንደተነሳ አድርገው ለህዝብ የገለፁት የሚንስትሮች ም/ቤት ውሳኔን ብቻ መሰረት አድርገው ነበር። በህገመንግስቱ መሰረት ደግሞ የሚንስትሮች ም/ቤት የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል እንጅ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የተወካዮች ም/ቤት ነው። ይህን ሂደት ስንመለከት ጠቅላይ ሚ/ሩ ህገመንግስቱን እንደጣሱ በግልፅ መመልከት ይቻላል። ምክንያቱም የሚንስትሮች ም/ቤት ውሳኔን ለህዝብ ከመግለፃቸው በፊት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እስኪያፀድቀው ድረሥ አልጠበቁምና። ይህ ሂደት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ የተወካዮች ምክርቤትን ልዕልና በማናለብኝነት እንደነጠቁ የሚያሳይ ሌላው ድርጊት ነው።

 

ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚንስትሮች ም/ቤትን ውሳኔ እንደመጨረሻ ውሳኔ አድርገው ለህዝብ የገለፁበት ምክንያት ግልፅነትን ለማስፈን ነው ተብሎ ክርክር ቢነሳ እንኳን የሚያስኬድ አይደለም። ይህ ሊሆን ይችል የነበረው ጠቅላይ ሚ/ሩ ለህዝብ የገለፁት የሚንስትሮች ም/ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ ይችል ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል በሚል ቢሆን ነበር። ከዚህ ስንነሳ አሁንም አልፈጠረበትም እንጅ የትወካዮች ም/ቤት የሚንስትሮች ም/ቤትን የውሳኔ ሃሳብ ባይቀበለው ኖሮ ጠቅላይ ምንስትሩ ምን ሊሉ ይችሉ ነበር፤ ሌላ ስህተት ከመደረብ በስተቀር።

 

·       ምህረትና ይቅርታ፡

 

ሁላችንም እንደምናቀው የዶ/ር አብይ አስተዳደር በወንጀል ድርጊት ለተጠረጠሩም ይሁን ለፍርደኞች ይቅርታና ምህረት አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። ይህ በራሱ ሲታይ በጎ ተግባር እንጅ መጥፎ ሊሆን አይችልም። ይሁን እንጅ ድርጊቱ እየተፈፀመ ያለበት አግባብ ህግን በተከተለ መንገድ አይመስልም።  በነገራችን ላይ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ራሱ ምህረትና ይቅርታን የሚመለከት የተሟላ ህግ አለመኖሩን አምኖ አዲስ ህግ እንዲወጣ እንዳደረገ ይታወቃል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ገና ህጉ ሳይፀድቅ ዶ/ር አብይ በራሳቸው መንገድ ሄደው  ይቅርታና ምህረት ያደረጉላቸው ሰዎች እንደነበሩ በተለያየ መንገድ ሰምተናል። በዚህ ረገድ እንደምሳሌ መጥቀስ የሚቻለው አንዱ የዶ/ር  አብይ  ድርጊት የመከላከያ ሰራዊቱን ብሎም ሃገርን በመክዳት ወንጀል ይጠረጠር  የነበረን ሰው በራሳቸው ኤሮፕሌን አሳፍረው ምህረት እንዲደረግለት ማድረጋቸው ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ዶ/ር አብይ ምን ያህል በህግ የበላይነትና በተቋማት አስፈላጊነት ላይ እንደማያምኑና እንቅስቃሲያቸው ሁሉ የራሳቸውን ልዕልና የመፍጠር ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያሳያል። ለነገሩ ንጉስ የመሆን ፍላጎት ያለው ሰው ከዚህ አሻግሮ መመልከት ይችላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ሊሆን ይችላል።

 

·       "ሽብርተኛ" ተብለው ተፈርጀው የነበሩ ድርጅቶች፡

 

እነዚህ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸውድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ መሰረዛቸው የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት እድል ይኖረው እንደሆነ እንጅ ጎጅ ጎኑ እምብዛም ነው፤ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እስከወሰኑ ድረስ። አሁንም በዚህ ረገድ ሊነሳ የሚችለው ችግር በተግባራዊ እንቅስቃሴው ዙሪያ ነው። እነዚህ ድርጅቶች አሸባሪ ተብለው የተፈረጁት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው። አሸባሪ አይደሉም ብሎ መሻር የነበረበትም ተቋም  ራሱ የተወካዮች ም/ቤት ነው። ይህ ሁሉ ሳይሆን ዶ/ር አብይ ራሳቸው ከምክር ቤቱ ውሳኔ በፊት ም/ቤቱ ውስጥም ሳይቀር እነዚህ "አሸባሪ" ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶች አገር ውስጥ ገብተው እንዲነቀሳቀሱ ጥሪ ያስተላለፉበት አጋጣሚዎች ነበሩ። አያደርጉትም እንጂ የተተወካዮች ም/ቤት አባላት የዶ/ር አብይን ድርጊት (ማለትም) ጥሪ ቢቃወሙትስ ኖሮ? ከኛ ውሳኔ በፊት ጥሪ ማድረገዎ ህገወጥ ነው ብለው ዶ/ር አብይን ተጠያቂ ቢያደርጓቸውስ ምን ሊሉ ነበር? ምናልባትም እኮ እንደዚህ አይነት ስህተቶች ስልጣን ሊያስለቅቁ የሚችሉ ናቸው። ደግነቱ ም/ቤቱ የሚተነፍሰው ከበታቹ ባለው የጠቅላይ ሚ/ሩ ሳንባ እንደሆነ ካረጋገጥን ከርማናል፤ እንዴው በአሁኑ ወቅት መሰረታዊ ለውጥ መጥቷል እየተባለ በሚደሰኮርበት ወቅት መሆኑ ግራ እያጋባን ነው እንጅ።

 

·       ሃይማኖትና መንግስት፡

በህገመንግስቱ አንቀፅ 11 መሰረት ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው። መንግስት በሃይማኖት፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት አይችሉም። ዶ/ር አብይ ግን ከዚህ ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ያፈነገጠ ንግግር ከአንደበታቸው ሰምተናል። በዚህ ረገድ ዶ/ር አብይ በአንድ ወቅት ለተባበሩት አረብ ኢመሬቶች አልጋ ወራሽ የእስልምና ተቋም እንዲገነቡላቸው እንደጠየቋቸው በአደባባይ መናገራቸውን ልብ ይሏል። በህገ መንግስቱ መሰረት ይህ ተግባር የሃይማኖቱ ተከታዮችና መሪዎች እንጅ የዶ/ር አብይ ጉዳይ አይደለም። በዚህ ዙሪያም ዶ/ር አብይ ሊያስቡበት ይገባል እንላለን።

የተለያዩ ሃላፊነት የጎደላቸው አረፍተ ነገሮች፣ ሃረጎችና ቃላቶች ጥቅም  ላይ እየዋሉ መሆኑ፡

ሁላችንም እንደሰማነው ዶ/ር አብይ ወደሃላፊነት ከመጡ ጀምሮ  በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በርካታ ንግግሮችን አድርገዋል። የሚበዙት ገንቢ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥላቻን፣ በቀልንና ጥቃትን ያረገዙ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ "ጸጉረ ልውጥ" የሚለው ሃረግ የመጀመሪያው ነው። ለሁላችንም ግልፅ እንደሚሆነው የኢፌድሪ ህገመንግስት አንቀፅ 32 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ/ት በፈለገው/ችው የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በነፃ የመንቀሳቀስና የመስራት ብቻም ሳይሆን የመኖር መብትም እንዳለው/ላት ግልፅ በሆነ መንገድ አስቀምጧል። ይህ ሆኖ እያለ ዶ/ር አብይ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ያሳካልኛል ብለው ስላመኑ ብቻ ፀጉረ ልውጦችን ነቅታችሁ ጠብቁ በሚል ለህዝቡ በተለይም ለወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል መልዕክት ማስተላለፍ ህጋዊ መንገድን በመፃረር ስልጣንን ለማስጠበቅ ከተደረገ ንግግር ውጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል አይደለም። ምክኒያቱም ከመነሻው መልእክቱ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው። ከዚህ አልፎም ወጣቱን ለወንጀል ድርጊት የሚያነሳሳ ነው። በውጤቱም ወደ ስርዓት  አልበኝንነት የሚያመራ ተግባር ነው። መልዕክቱን ለማስተላለፍ የተፈለገው በቅን ልቦና ቢሆን ኖሮ መገለፅ የነበረበት በየአከባቢው ሰላምን ሊያውኩ የሚችሉ ሰዎች ስለሚኖሩ ሁላችሁም አከባቢያችሁን በመጠበቅ የተለየ እንቅስቃሴ ሲያጋጥማችሁ ለፀጥታ አካላት አሳውቁ በሚል መንገድ መሆን ነበረበት።

ሌላው መስቀል  አደባባይ በተደረገው ሰልፍ ላይ ተፈፅሞ በነበረው አሳፋሪና ፀያፍ የሆነ የቦምብ ጥቃትን ተከትሎ ዶ/ር አብይ የሰጡት መግለጫ እንዲሁ መጥፎ መልዕክትን ያዘለ ነበር። በወቅቱ የተፈፀምውን የቦምብ ጥቃት ትክክለኛ አዕምሮ ያለው ሰው ይደግፈዋል ተብሎ አይታሰብም። ይሁንና ዶ/ር አብይ "ጥቃቱ በደንብ የተጠናና ሙያቸውንና ችሎታቸውን ተጠቅመው ያደረጉት" ነው ብለው ሲናገሩ ጣታቸውን  ማን ላይ እንደቀሰሩና ህዝቡም ጣቶቹን ማን ላይ ሊቀስር እንደ ሚገባ ያመላከቱበት መግለጫ ነበር። በተመሳሳይ መንገድም አሁን በቅርቡ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋ ባደረጉት ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበሩ የርሳቸው ደጋፊ እንደሆኑ የሚታወቁ  መምህራን ዶ/ር አብይ ተናግረውታል ብለው ያቀረቡት  ጉዳይ አደገኛነቱ በቀላሉ  ሊታይ የሚችል አይደለም። እነዚህ ደጋፊ ነን የሚሉ ሰዎች እንዳሉት  ዶ/ር አቢይ አቶ እሳያስን መቀሌ መውሰድ ፈልገው እንደነብረ ግን እንደ አዲስ አባባ አይነት የቦምብ ጥቃት ቢደርስ የሁለቱ ሃገራት  ህዝቦች ግንኙነት ይሻክራል ብለው ሰግተው እንደትውት ተረድተናል ።

ከዚህ ሁሉ ስንነሳ ዶ/ር አብይ እነዚህን አረፍተ ነገሮች፣ ሃረጎች ወይም ቃላቶች እየተጠቀሙ ያሉት ህወሓትንና ከሱ ጋ የተያያዘውን የማህበረሰብ ክፍል አጣብቂኝ (Corner) ውስጥ ለማስገባት እንደሆነ ለመረዳት አዳጋች አይደለም። ዋናው ጥያቄ ያለው የህወሓት አብዛኞቹ አመራሮች በራሳቸው ስግብግብነትና አልጠግብ  ባይነት ራሳቸውን ጠልፈው በጣሉበት ወቅት ዶ/ር አብይ በተለይ  በአጠቃላይም ደግሞ ኦህዴድ(OPDO) ለምን ይህን ማድረግ ፈለጉ የሚለው ላይ ነው። በኔ አስተሳሰብ ምክኒያቶቹ ሁለት ናቸው ብየ እገምታለሁ። አንደኛው ኦሮሚኛን የፌደራል ቋንቋ ከማረግ ጋ የተያያዘዘው ጉዳይ ነው። በማህበራዊ መዲያም ይሁን በተለያየ መንገድ ከህወሃት ሰዎች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች  እንደሚጠቁሙት  ህወሃት የኦሮሚኛ ቋንቋ በሌላው ላይ መጫን የለበትም የሚል አስተሳሰብ እንዳለውና ይህንንም ያለማወላወል እየታገለው እንደሆነም ነው።  ሁለተኛው ጉዳይ  ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ አለው ከሚባለው ህገመንግስታዊ ልዩ ጥቅም ጋ የተሳሰረ ነው። በዚህ ረገድም ቢሆን ህወሃት የኦህዴድን ተስፋፊነት ዝንባሌ ልክ ሊኖረው ይገባል የሚል አቋም እንደያዘ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሄ ደግሞ ኦህዴድን አላስደሰተም። በነዚህ ምክንያቶች መነሻነት ከኢህአዴግ  መርህ ውጭ በሆነ መንገድ ኦህዴድ  ከብአዴን ጋ በመደራጀት ህወሓትን እየገፋው እንደሆነ መረዳት ከባድ አይደለም።

በሌላ በኩል የኦህዴድን ፍላጎት ገፍተን ካየነው ደግሞ ሌላ ምንጭ ላይ ሊያደርሰን ይችላል። ይኀውም ኦህዴድ የኦሮሞን የህዝብ ቁጥርና ያለበትን የቦታ አቀማመጥ እንደዋነኛ መሳሪያዎች ተጠቅሞ ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን በሌሎች ብሄር ብሀረሰቦችና ህዝቦች ላይ የበላይነቱን ለመጫን ያለመ የሚመስል አካሄድ እየተከተለ መሆኑ ነው። ይህ የኦህዴድ የኦሮሞን ተስፋፊነትና የበላይነት የመፍጠር ቅዠት ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ቅርፅና ማንነት ይዛ አትቀጥልም ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለኦሮሞ ህዝብ የህልውና ጉዳይም አደገኛ ጋሬጣ ሊሆን እንደሚችል መገመት ካባድ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚችልበት ምክንያት ደግሞ ዙሪያው በሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተከበበ በመሆኑ ነው።  ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ወገኖች የኢትዮጵያን ዋና ከተማ ወደ ሌላ ቦታ በማዛወር የኦህዴድን ተፅዕኖ መቀነስ ይቻላል ብለው የሚከራከሩት።

የአስራር ግልፀኝነት፡

ዶ/ር አብይ በብዓለ-ሲመታቸው ላይ በግልፅ ያስቀመጡት  አንዱ ዋነኛ ነጥብ መንግስታቸው የአሰራር ግልፅነትን የተላበሰ እንደሚሆን ነበር። ሌላው ቀርቶ በሌላው አለም ተሰምቶ እንኳን በማይታወቅ ደረጃ ኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛና ቁልፍ የሆኑ ውሳኔዎች የሚያሳልፈውን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ሳይቀር ለህዝብ ቀጥታ እንደሚተላለፉ ገልፀዋል። የዚህ አይነት አሰራር ሙያዊና ስነምግባር የተላበሰ መሆን አለመሆኑን ወደጎን ትተን ማለታቸውን ብቻ ለግልፀኝነት ያላቸውን ፍላጎት እንደማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ይሁንና እርሳቸው ሃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ ህዝብ ሊያቃቸው የሚገቡ ሂደቶች ሲገለፁ አላየንም። እንደማሳያ ያህል ለመጥቀስ መስቀል አደባባይ ስለተፈፀመው አስነዋሪ ፍንዳታ አጣርተን ጠንሳሾች (እንደነሱ አገላለፅ “የቀን ጅቦቹ” ) እነማን እንደሆኑ በየደረጃው ለህዝብ እንገልፃለን ተብሎ እሳክሁን የተገለፀ ነገር አላየንም። ሲዳማና ወላይታ ውስጥ የነበረውን ግጭት በተመለከተም እንዲሁ በተመሳሳይ መንገድ አጣርተን ለህዝብ እንገልፃለን ተብሎ እስካሁን የተሰማ ነገር የለም። ቤንሻንጉል ጉሙዝ ስለነበረውም ሁኔታ አንድም ነገር አልተባለም። ሌሎችም አሉ። ሌላው ቀርቶ የመንግስት መዲያዎች እንዳይገቡና እንዳይዘግቡ  የተደረጉበት አጋጣሚዎች እንኳን ጥቂት አይባሉም። በቅርቡ ዶ/ር አብይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን ጋ ባደርጉት ውይይት ላይ ሚዲያዎች ገብተው እንዲዘግቡ እንዳልተፈቀዳለቸው ከተለያዩ ምንጮች ተረድተናል። ይባስ ብሎም የውይይቱ ዘገባ ተዘጋጅቶ ለሚዲያዎች የተላከው በጠቅላይ  ሚ/ር ፅ/ቤት እንደሆነ ሰምተናል። ተጨባጭ ሁኔታው የሚያሳየው ይህን ከሆነ እንዴት አድርገን ነው ታዲያ  የዶ/ር አብይ አስተዳደር አሰራር ግልፅነት የሰፈንበት ነው ልንል የምንችለው፤ ያው እንደተለመደው አይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ ካላሉን በስተቀር።

የፕሬስ ነጻነት፡

ዶ/ር አብይ ለፕሬስ ነፃነት መከበር የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ በተለያየ መንገድ ሲገልፁ ይሰማሉ። በዚህ ዙሪያ በርግጥ የተለያዩ በጎ እርምጃዎችን ወስደዋል። ለምሳሌ ያህል ታግደው ምናልባትም በወንጀል ይፈለጉ የነበሩ የሚዲያ ተቋማትን ነፃ እንዲሆኑ አድርገዋል። ከዚሁ ጋ ተያይዞም አሁንም ታግደው የነበሩ በርካታ ድህረ ገፆች እንዲከፈቱ አድርገዋል። የመንግስት ሚዲያዎችም ነፃነታቸውን ያወጁ የሚያስመስሏቸው መርሃግብሮችን ማስተላለፍ ጀምረዋል። ከነዚህ የመንግስት ሚዲያ ተቋማት ዘገባዎች ውስጥ ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ በእስረኞች ላይ ይፈፅሙ የነበሩ  ኢ-ሰብዓዊና ዘግናኝ የሆኑ ድርጊቶች ይገኙበታል።

ይሁን እንጂ እነዚህ የመንግስት ሚዲያዎች አሁንም ከልብ ተቀይረዋል ወይ የሚለው ጉዳይ እጅግ በጣም አነጋጋሪ ነው። የዚህ ምክንያት ደግሞ ሚድያዎቹ  እያቀረቡ ያሏቸው ዘገባዎች ሲታዩ ሁሉም ተፈፀሙ እየተባሉ እየቀረቡ ያሉት መጥፎ ድርጊቶች ዶ/ር አብይ የጠቅላይ ሚንስትርነት ቦታውን ከመረከባቸው በፊት የነበሩ  ናቸው። እርሳቸው ወደሃላፊነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ያሉ ችግሮችን ሲዘግቡ ያየሁበትና የሰማሁበት አጋጣሚ አልነበረም ማለት እችላለሁ። እንደውም እነዚህ ሚዲያዎች  ልክ ቀድሞ ለተለያዩ መሪዎች  ያደርጉት እንደነብረው ሁሉ ዶ/ር አብይን ማሞገስና ማንቆለጳጰስ ምናልባትም እንደፈጣሪና አዳኝ (Savior) ተደርገው እንዲታዩ ማድረግ ላይ ያተኮሩ ይመስላሉ።

ያለፈን ስርዓት መተቸትና መቃወም ደግሞ ለኛዎቹ  የመንግስት ሚዲያዎች ችግር ሆኖ አያቅም። በደርግ ጊዜ የአፄውን፤ በኢህአዴግ ጊዜ ደግሞ የደርግን “ሰይጣንነት“ ሳይሰብኩ ያለፉበት ጊዜ ነበረ ብሎ ደፍሮ ለመናገር አይቻልም። እንዲያውም  እንደባዘቶ ነበር ሲያብጠለጥሏቸው ይሰሙ የነበሩት። አሁንም እነዚህ ሚዲያዎች የሚያብጠለጥሉትና "አንበሳነታቸውን" እያሳዩ ያሉት ከሶስት ወራት በፊት በነበሩት የኢህአዴግና የመንግስት አመራሮች ላይ እንጅ አሁን ሃላፊነት ላይ ያሉት አመራሮች እየፈፀሟቸው ባሉ ስህተቶች ላይ አይደለም። ያሁኖቹ አመራሮችማ በነዚህ የመንግስት  ሚዲያዎች ዘንድ እንደ ፈጣሪ ነው እየታዩ ያሉት። ለነገሩ ምንጊዜም የኒዚህ ሚዲያዎች መርህ "ያሁኖቹ" አይሳሳቱም ቢሳሳቱም መነቀፍ የለባቸውም የሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው የሚመስለው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እነዚህ የመንግስት ሚዲያዎች እንዲዘግቡ የማይፈቀድላቸው ሁኔታ እንዳለም በቅርቡ በጠቅላይ ሚ/ሩና በምሁራን ተደርጎ የነበረውን ውይይት ያስታውሷል።

ሌላው ከሚዲያ ነፃነት ጋ ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው የዶ/ር አብይ ዝንፈት ደግሞ ከኢኤንኤን (ENN) ጋ ተያይዞ ያለው ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ገና ዶ/ር አብይ የጠቅላይ ሚንስትርነት ሃላፊነቱን በያዙ ማግስት በENN  ላይ ደስተኛ እንዳልነበሩ የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ። ዋነናው ምልክት ዶ/ር አብይ በአንድ መድረክ ENNን የሚቆጣጠረው አካል ጠፍቷል በሚል ያስተላለፉትን የቂም በቀል የሚመስል መልእክት ማስታወስ ብቻ በቂ ነው። ይህን ያሉበት ምክንያት ደግሞ ይህ ሚድያ "ሰውየው" ብሎ ጠርቶኛል በሚል ነበር። ከዚህ በኋላ የመንግስት መረጃዎችን መከልከልና ከሚሰጡ መግለጫዎች ማግለልን ጨምሮ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር ENNን ከገበያ እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የዶ/ር አብይ እጅ ያለበት መሆኑን ደፍሮ መናገር ይቻላል።

ከመንግስት ሚድያዎችም ሆነ ከENNን ሁኔታዎች ስንነሳ ዶ/ር አብይ ሚድያው ነፃ እንዲሆን አደርጋለሁ ሲሉ እርሳቸውንና አስተዳደራቸውን የሚደግፈውን  ወይም አያውክም ብለው የሚያስቡትን ብቻ እንዳይሆን ስጋት አለኝ። የሚዲያ ነፃነት እንዲያ ቢሆንማ ኤሪትሪያና ሰሜን ኮሪያም የሚያደርጉት እኮ ከሱ የተለየ አልነበረም። በእውነተኛ ሚዲያ ነፃነት ማመን ሲባል ሬት ሬት የሚሉ ዘገባዎች ሲቀርቡም መቻልና መቀበልንም ያካትታል። ያም ሆነ ይህ  ሚድያዎች በሚያቀርቡት ዘገባዎች ተመስርቶ አንዱን ልጅ ሌላውን ደግሞ የእንጀራ ልጅ አድርጎ የሚቆጥር አካሄድ አምባገነናዊና ጨቋኝ ከመሆን አይዘልም።

በተለያዩ አከባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች፡

በዚህ ረገድ ዶ/ር አብይ እንደጠቅላይ ሚንስትርነታቸውና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥነታቸው በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለማስቆምና እንዳይከሰቱም ለመከላከል  እንዲቻል  ለሃገሪቱ የፀጥታ ተቋማት ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው የሚጠበቅ ነው። ችግሩ ያለው ትዕዛዙን የሰጡበት መንገድ ላይ ነው። ዶ/ር አብይ  ትእዛዙን በሰጡበት ወቅት አንድም ቦታ ላይ "ህገመንግስቱን በማይጥስ ሁኔታ" ሲሉ አልተደመጡም። በነገራችን ላይ ከአራት ወራት በፊት የፌደራል መንግስት የፀጥታ አካላት ሀገመንግስቱን እየጣሱ ክልላችን ውስጥ መግባት የለባቸውም በሚል ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር የነበረው ዶ/ር አብይ የሚመሩት ኦህዴድ ነበር። አሁን ስልጣኑን ራሳቸው ሲይዙት ያንን የተቀደስ ሃሳብ አጠናክረው ሊገፉበት ይገባ ነበር እንጂ ሊያቃልሉት ባልሞከሩም ነበር። ትእዛዙ የተላለፈው እንደ ጃዋር መሃመድ፣ ዶ/ር ፀጋየ ረጋሳና ሃጫሉ ሁንዴሳ አይነት ፅንፈኞችን ለማለዘብና በእግረ መንገድም ስልጣንን ለማደላደል ብሎም የኖቤል ተሸላሚነት ተስፋን እውን ለማድረግ ከሆነ ግን በሌሎች ኢትዮጵያውያን ውስጥ ቁርሾ ከመፍጠር  በዘለለ ሌላ  ፋይዳ ሊኖረው አይችልም።

ከዚህ ባሻገር ግን አሁን አሁን ሃገራችን ውስጥ እየታየ ላለው ስርዓት አልበኝኘት ምክኒያት የሆኑት ራሳቸው ድ/ር አብይ እንደሆኑ ሊገነዘቡት ይገባል። ይህ ስርዓት አልበኝነት እየተስፋፋ ያለው ዶ/ር አብይ የህግንና የተቋማትን ዋጋዎች (Values) በማኮሰስ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ወንጀል ሰርተው የተፈረደባቸውንና ሌሎች  በከፍተኛ ወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎችን ህግንና ተቋማዊ አሰራሮችን ሳይከተሉ ይቅርታና ምህረት እያደረጉ ያለበት ሁነታ ስልተፈጠረ ነው። በነገራችን ላይ  እስካሁን ባየነው ልምድ እንደተረዳነው ህገመንግስትንና ሌሎች ህጎችን የሚጥስ መንግስት ባለበት አገር ተራው ዜጋም ቢሆን ህግ የማይጥስበትና ልቅ የማይሄድበት  ሁኔታ የለም።

የእስረኞች ሁኔታ፡

ዶ/ር አብይ በተደጋጋሚ በርሳቸው አስተዳደር አንድም እስረኛ እንዳይኖር አደርጋለሁ የሚል እንደምታ ያለው ንግግር ሲያደርጉ ይደመጣሉ። ይህ ምን ያህል ይቻላል የሚለውን ረብ የለሽ ሙግት ወደጎን ትተን አሁን በተግባር እየሆነ ያለውን እንመልከት። ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚ/ር ከሆኑ ወዲህ ያለውን ሁኔታ በምናይበት ጊዜ እስር አሁንም እንደሚፈፀምና የእስሩም ሁኔታ ሰብዓዊ መብቶችን በሚጥስ ሁኔታ እንደሆነ ከታሳሪዎችም ሆነ  ከቤተሰቦቻቸው እየሰማን ነው። አሁንም ጨለማ ቤት ውስጥ መታሰር እንዳለ እየተገለፀ ነው። አሁንም የግለሰብ ቤቶች ውስጥ የታሰሩ እንዳሉ እየሳማን ነው። አሁንም አስፈላጊው ማጣራት ሳይደረግ ታስረው የፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ በተደጋጋሚ የሚጠየቅባቸውን እስረኖች እየተመለከትን ነው። እንዲህ አይነት ድርጊቶች እስረኛ እንዳይኖር አደርጋለሁ ከሚል መንግስት አይጠበቅም፤ ምን አልባት የተነገረው ነገር አሉ ለማለት ታስቦ ካልሆነ በስተቀር።  ይህ ጉዳይ ሩቅ ሳይሄድ ከወዲሁ ካልተስተካከለ አሁንም ውሃ ቢውቅጡት እምቦጭ እንዲሉት እንዳይሆን ስጋት አለኝ።

የተለየ ሃሳብ መያዝ፡

ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚ/ር ከሆኑ በኋላ እየነገሩን የመጡት ማንም ሰው የመሰለውን ሃሳብ የመያዝና የማራመድ መብት እንዳለው ነው። በተግባር ግን  ከርሳቸውና ከርሳቸው አስተዳደር  የተለየ ሃሳብ የያዘና የሚያራምድ እንዲሁም የርሳቸውን ሃሳብ የሚተች ሰው እንዲኖር የሚፈቅዱ አይመስሉም። ይህን ለማለት ያነሳሳኝ አንዱ ነገር ዶ/ር አብይ አልታደሱም ብለው የሚያስቧቸውን የትግል አጋሮቻቸውን የሚያዩበት መነፅር ቂምና በቀል ያዘለ እንደሆነ የሚመስሉ ሁኔታዎች መኖራቸው ነው። ይህን ቂምና በቀል ለመረዳት የሚጠቀሙባቸውን እንደ የቀን ጅቦችና ፀጉረ ልውጥ የሚሉ ሃረጎች በማየት ብቻ መገንዘብ ይቻላል። የነገሩን ሁኔታ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ እነዚህን  ሰዎች ያጠመዷቸው ከርሳቸው የተለየ ሃሳብ በመያዛቸው ይሁን እንጅ ሊያጠቋቸው የፈለጉት ደግሞ እየለጠፉባቸው ያሉትን ታፔላዎች ማለትም ሁከት ማነሳሳትና ሰላምን ማደፍረስ የሚሉ ሃረጎችን በመጠቀም ነው።

በዚህ ረገድ የዶ/ር አብይ  ስርዓት ከደርግ መንግስት የሚለይበት ሁኔታ ደርግ ግልፅ በሆነ መንገድ የሚገድል፣ የሚያስርና እንዲሁም አካልን የሚያጎድል ሲሆን ዶ/ር አብይ ደግሞ ተቀናቃኞቻቸውን ለመጉዳት የሚፈልጉት የተለያዩ አደገኛ ቃላትን በመጠቀም እርሳቸውን የሚደግፋቸውን የህብትረተሰብ ክፍል  በስሜት በመንዳት ነው። ለምሳሌ ያህል ደርግ የቀድሞ ሚንስትሮችን የረሸነው ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ሲሆን ዶ/ር አብይ ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ይቀናቀኑኛል የሚሏቸውን ሰዎች ሊያስጠቁ የሚፈልጉት የሚደግፋቸውን የህብረተሰብ ክፍል በስሜት መንዳት የሚችሉበትን አረፍተ ነገሮች፣ ሃረጎችና ቃላትን በመጠቀም ነው። ይህ መንገድ እጅግ አደገኛና ህዝበኛ-አምባገነናዊ-የግለሰብ-ስርዓትን የሚፈጥር አካሄድ ነው። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በስሜት መነዳት የሚለውን ነገር ስናይ  ሃገራችን  ውስጥ በማመዛዘንና በማስተዋል ሳይሆን  በመንጋ ማሰብና በመንጋ መንቀሳቀስ እንደፋሽን የተወሰደበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ራሳችን በልቶ ይጨርሰናል እንጅ አንድ እርምጃ እንኳን ወደፊት አያራምደንም። በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚ/ሩ  ደጋፊያቸው በመንጋ እንዲነዳና ህግን እንዲደፈጥጥ ግፊት ማድረጋቸው ከጥፋቶች ሁሉ ጥፋት የሆነ ድርጊት መሆኑን የተገነዘቡ ወይም ደግሞ ሊገነዘቡ የፈለጉ አይመስሉም።

 

 

የስልጣን ክፍፍል፡

በዶ/ር አብይ አስተዳደር ዘመን ያለውን የሹመነት አሰጣጥ ስናይ አጀማመሩ የሚያስደስት አይመስልም። እየሆነ ያለው ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ ሃገሪቱን እንደተቆጣጠረ ሰሞን በህወሃት ሰዎች ያላግባብ በገፍ ተይዘው የነበሩትን አብዛኛዎቹን ምናልባትም ደግሞ ምክትሎቹን ከጨመርን በከፋ ሁኔታ በኦህዴድ ወይም ከኦህዴድ ጋ ትሥር ባላቸው ሰዎች የተሞሉ የሚመስሉበት ሁኔታዎችን እየታዘብን ነው። በነገራችን ላይ በሹመት አሰጣጡ ረገድ ለምን የኦህዴድ ሰዎች በዙ የሚል ቅሬታ የለኝም። ቁልፉ ችግርና ሊወገድም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ግን  የአንድን መንግስት ቀጣይነት በከፍተኛ ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሃላፊነት ቦታዎች በኦህዴድ ሰዎች እንዲያዙ መደረጉ ላይ ነው። በዚህ ረገድ ፕሬዚደንቱንና ጠቅላይ ሚ/ሩን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚንስተር፣ የመከላከያ ሚንስትር፣ የጠቅላይ አቃቢ ህግ፣ የገቢዎች ሚንስትር ፅ/ቤት፣ የካቢነ ጉዳዮች ሚንስትር፣ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በኦህዴድ ሰዎች የተያዙ መሆኑን ልብ ይሏል። ከዚህ በተጨማሪም ምክትል የኢታማጅር ሹምና የኦፕሬሽን መምሪያ ሃላፊ፣ የደህንነት መስርያ በቱ ምክትል፣ የፖሊስ ኮሚሽን  ምክትል ብሎም የአዲስ አበባ ከንቲባና የፖሊስ አዛዥ የኦህዴድ ሰዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ የት ሊያደርሰን እንደሚችል መረዳት አይከብድም። ይሁንና ኦህዴድ ነበረ የሚለውን የሌሎች የበላይነት አስወግዶ የራሱን የበላይነት ለመፍጠር የሚያስችል ሂሳብ ለመስራት አያስብም ለማለት ባልደፍርም የህዝቡ ነባራዊ ሁኔታ ግን የሚፈቅድለት አይደለም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በኋላ የማንንም የበላይነት ለመቀበል የሚችል ትከሻ ያለው አይመስለኝም።

ማጠቃለያ፡

ለማጠቃለል ያህል ዶ/ር አብይ እያከናወኗቸው ያሉ በጎ የሚመስሉ ተግባራት መኖራቸውን እንገነዘባለን። በአንፃሩ ደግሞ በርካታ ህፅፆች እንዳሉባቸው የሚያመላክቱ ማሳያዎች አሉ። በተለይም ደግሞ የህግ የበላይነትን ከማስከበር፣ ተቋማትን ከማክበርና ከማጠናከር እንዲሁም ስርዓት አልበኝነትን ከመቆጣጠር አኳያ መሰረታዊ መዛነፎች እየታዩ መሆኑን መካድ አይቻልም። ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ ዶ/ር አብይ የራሳቸውን ተወዳጅነት በማሳደድና  በስብዕናቸው ግንባታ ላይ ትኩረት እያያደረጉ መሆናቸው ነው። ምንም ሆነ ምን ግን  ከተቋማትና ከህጋዊ ስርዓት ርቆ የራስን ልዕልና ለመገንባትና ለማስረፅ መሞከር የሃገርንና  የህዝብን ውድቀት፣ መከራና ስቃይ ያበዛ እንደሆነ እንጅ እድገትና ብልፅግናን ማምጣት አይችልም። ይህ አካሄድ ካሁኑ ካልታረመ  ትንሽ ቆይቶ ወደ አምባገነንነት እንደሚያመራ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። ስለዚህ ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ የምንቸገርበት ደረጃ ላይ ሳንደርስ  ዶ/ር አብይ ህፀፆቻቸውን እንዲያስተካክሉ የበኩላችን ጥረት በማድረግ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን የሚጠናከርበትን ሁኔታ መፈለግ ይበጃል የሚል እምነት አለኝ።

 

 

Back to Front Page