Back to Front Page


Share This Article!
Share
የጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድና አጋሮቻቸው የቂም በቀል ድርጊት

የጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድና አጋሮቻቸው የቂም በቀል ድርጊት ቁጥር . ።

ከፍትህ ይንገስ 08-08-18

እንደሚታወቀው በተለያዩ ጊዚያት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልሎች መካካል የድንበር ወሰንን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ግጭቶች ተከስተዋል። በነዚህ ግጭቶች የተነሳ ከሁለቱም ወገኖች በኩል በርካታ ህይወቶች ተቀጥፈዋል፣ ቀላል የማይባሉ የአካል ጉዳቶች ደርሰዋል፣ በመቶ ሽህዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ተፈናቅለዋል እንዲሁም ለቁጥርና ለአይነት የሚያታክቱ ንብረቶች ወድመዋል። ይህን ተከትሎም በሁለቱ ክልሎች ባሉ ባለስላጣናትም ይሁን የፖለቲካ አቀንቃኞች (Political Activists) መካከል ቂምና ቁርሾ ተፈጥሯል። በተለይም እነ ጃዋር መሃመድ፣ ዶ/ር ፀጋየ ረጋሳ፣ ሃጫሉ ሁንዴሳና ሌሎችም "ዘመንኛ" ፅንፈኞችና እብሪተኞች ልክ የእነሱ ወገን ብቻ እንደተነካ አድርገው በመቁጠር ለነበረው ችግር ሁሉ ተጠያቂወቹ የሶማሊ ክልል ባለስልጣናት በተለይም የክልሉ ፕሬዚደንት የሆኑት አብዲ ኢሌና የክልሉ ልዩ ፖሊስ እንደሆኑ ለማሳየት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ይሰማሉ። የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ፅንፈኞች ፌዴራል መንግስቱን የሚያሽከረክሩት እነሱ እንደሆኑ በሚያስመስል ሁኔታ ትዕዛዝ ሲሰጡም ይሰማሉ። ከዚህ ጋ ተያይዞ ሃጫሉ ሁንዴሳ በቅርቡ በሚሊንየም አዳራሽ ተደርጎ በነበረ ዝግጅት ላይ ዶ/ር አብይ የሶማሊ ክልል ባለስላጣናትንና ልዩ ፖሊስን እንዲጨፈልቁ ካልሆነም ለቄሮ ስሞታ እንደሚያቀብ በዘፈን መልክ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። ጃዋር መሃመድም ባንድ ወቅት ባደረገው ንግግር ላይ አብዲ ኢሌ መሄድ አለበት (Abdi Iley must go)፤ እሱ ካልሄደ ኢትዮጰያ ሶማሊ የሚባል ክልልን አልረግጥም ሲል ተደምጧል። ዶ/ር ፀጋየም እንዲሁ ተመሳሳይ የሆኑ አጉራ ዘለል ንግግሮችን በተደጋጋሚ ሲያሰማ ይደመጣል። ሌሎችም አሉ።

እጅግ በጣም የሚያሳዝነውና የሚገርመው ብሎም ኢትዮጵያ በንፁሃን ልጆቿ ተጋድሎ ከደረሰችበት የክብር ደረጃ ምን ያህል እየወረደች እንዳለች የሚያሳየው ጉዳይ ግን ዶ/ር አብይም ራሳቸው ከላይ እንደተገለፀው በፅንፈኞቹ በተደረገባቸው ጫና ምክንያትና ራስቸውም በያዙት ቂምና ቁርሾ የተነሳ በሚመስል አኳኋን በፌዴራል መንግስት ደረጃ ያላቸውን ስልጣን ተጠቅመው እንደለመዱት ህገመንግስቱን በጣሰ መንገድ የፌደራል የፀጥታ አካላት ኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ዉስጥ እንዲገቡ ማድረጋቸው ነው። እዚህ ላይ ግልፅ እንዲሆን የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር የሶማሊ ክልል አመራሮች ፕረዚደንቱን ጨምሮ ችግሮች አልነበሩባቸውም ወይም የሉባቸውም የሚል አቋም የሌለኝ መሆኑን ነው። እነዚህ የሶማሊ ክልል አመራሮች በሚያስተዳድሩት የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ዉስጥ ልክ በማንኛውም ሌላ የኢትዮጵያ ክልልስጥ ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ሊኖር እንደሚችል መገንዘብ የሚከብድ አይደለም። አይደለም "አጋር ድርጅት" ተብሎ በሚታወቅ የፖለቲካ ፓርቲ በሚመራው የሶማሊ ክልል ቀርቶ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሚመሯቸው ክልሎች ሳይቀር የሙስና፣ ብልሹ አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደነበሩ ኢህአዴግ በግልፅ ያመነው ጉዳይ ነው። ከዚህ አልፎ ዶ/ር አብይ ራሳቸው እንደአሻንጉሊት እየተጫወቱበት ያለው ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት አሸባሪ" እንደነበር በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርበው በይፋ መስክረዋል። ለነገሩ አለመታደል ሆኖ እንጅ በመሪው "አሸባሪ" የተባለ ድርጅት የያዘውን ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ ነበረበት እንጅ ይቅርታ ጠይቄያለሁ በሚል ሰበብ መርህ አልባ፣ ስሜት ቀስቃሽ፣ ህዝበኛ እና ዘላቂነት የሌላቸውን መፈክሮች አንግቦ ህዝቡን ግራ በማጋባት ስልጣን ላይ መቆየት አይገባውም ነበር። ሁሉም ባለፉት 27 አመታት ሃላፊነት ላይ የነበሩ የቀድሞ ሚንስትር ዶ/ር አብይን ጨምሮ ስልጣን መልቀቅ ነበረባቸው።

Videos From Around The World

ኢህአዴግና አመራሩ በዚህ መንገድ ስልጣን ተቆናጥጠው እየቀጠሉ ባሉበት ሁኔታ በምን ስሌት ነው የሶማሊ ክልል አመራሮች ተለይተው የፌዴራል መንግስት ተጠቂ (Victim) እንዲሆኑ የተመረጡት? እነዚህ የሶማሊ ክልል አመራሮች ከኢህአዴግ አመራሮች የከፋ ""አሸባሪነት"" ፈፅመዋል በሚል ተገደን እንድናምን ቢደረግ እንኳን የፌደራል መንግስት ጣልቃ የገባበት ሂደት ፍፁም ኢ-ህገመንግስታዊ መሆኑን መካድ ግን አይቻልም። ለምን ቢባል በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 51 ንዑስ አንቀፅ (14) መሰረት የፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ጉዳይ ዉስጥ ጣልቃ መግባት የሚችለው በሚመለከተው የክልሉ መንግስት ጠያቂነት ነው ብሎ በማያሻማ ሁኔታ ስለሚደነግግ ነው።

በተግባር የታየው የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ገብነት ግን ከዚህ መሰረታዊ የህገመንግስት ድንጋጌ ጋር የተጣረሰ ነው። በተለያዩ ሚዲያወች እንደተዘገበው የፌዴራል መንግስቱ የፀጥታ አካላት ሶማሊ ክልል ዉስጥ የገቡት አርብ ማለትም ሃምሌ 27/2010 ዓ.ም ነው። በዚህ ወቅት የክልሉ መንግስት ጥያቄ እንዳላቀረበ ተረድተናል። የፌዴራል መንግስቱ የፀጥታ ሃይል የክልሉን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ሰላም፣ ደህንነትንና ፀጥታን ለማስከበር ሶማሊ ክልል ዉስጥ እንዲገባ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል ተብሎ በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ፅ/ቤት ሃላፊ ሚንስትር የተገለፀው ደግሞ ሰኞ ሓምሌ 30 /2010 ዓ.ም ነው። በዚህ ቀንም ቢሆን የትኛው የሶማሊ ክልል መንግስት አካል ጥያቄውን እንዳቀረበ የተሰጠ በቂ ማብራሪያ አልነበረም። በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉድዮች ፅ/ቤት እንደተገለፀው ሰኞ ሓምሌ 30 /2010 የተደረገ የክልሉ መንግስት ጥያቄ አለ ብለን አሁንም ተገደን ብናምን እንኳን በመጀመሪያ ማለትም አርብ ሃምሌ 27/20110 የተደረገውን የፌዴራል መንግስት ኢ-ህገመንግስታዊ ጣልቃ ገብነት አያስተባብለውም። ምክንያቱም የአርቡ የፌደራል መንግስት በፀጥታ ህይሉ አማካኝነት ያደርገው ጣልቃ ገብነት ከፈረሱ ጋሪው እንዲሉ ከሶማሊ ክልል መንግስት ጥያቄ ሳይቀርብ ነው። በነገራችን ላይ ሶማሊ ክልል ዉስጥ ለተፈጠረው ትርምስና ፍጅት ዋነናው መነሻም ይሄው አርብ ምሽት የተደረገው የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብነት መሆኑን መካድ አይቻልም።

ወጣም ወረደ ግን በሶማሊ ክልል ውስጥ ያለው ሙስናም ይሁን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲሁም ብልሹ አሰራር ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች በከፋ መንገድ እየተፈፀመ እንደሆነ የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ አልቀረበም። ለነበሩት ችግሮችም የክልሉ አመራር በፕረዚደንቱ በኩል ኢህአዴግ እንዳደረገው ሁሉ ግልፅ ይቅርታ ጠይቋል። ይህ በሆነበት ሁኔታ የፌደራል መንግስቱ ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ሶማሊ ክልል ዉስጥ ዘው ብሎ መግባቱ የሚያሳየው "ዘመኑ የኛ ስለሆነ" የፈለግግነውን የበቀል እርምጃ መውሰድ እንችላለን ከሚል ጀብደኛ የሆነ መነሻ የመነጨ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በእግረ መንገድም የነጅዋርን፣ ዶ/ር ፀጋየን፣ ሃጫሉንና መሰል ጀብደኛ " ባለጊዜወችን" ፍላጎት ማርካት እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ዶ/ር አብይና በል የሚሏቸው አጋሮቻቸው የቂምና የበቀል ስሜት ባይቋጥሩ ኖሮ የተፈፀመው ጣልቃ ገብነት እንዲደረግ በፍፁም አይፈቅዱም ነበር። ይልቁንም ልክ ኦሮሚያ ዉስጥ ያለው ችግር መፈታት ያለበት ያለምንም ጣልቃ ገብነት በኦሮሞ ህዝብ ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ እንደነበረው ሁሉ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ውስጥ እየታየ ያለው ችግርም መፈታት ያለበት ያለምንም ጣልቃ ገብነት በሶማሊ ክልል ህዝብ መሆን ይገባዋል የሚል አቋም ይይዙ ነበር። ይህ የቂምና የበቀል ቁርሾ "የሰውየው ለቅሶ ከፍየሏ በላይ ነው" እንዲሉ ሆኖ ዶ/ር አብይና ሌሎች ዶ/ር አብይ ሽምጥ እንዲጋልቡ የሚገፋፏቸው ሰዎች በቂም ላይ የተመሰረተ የበቀል ጥቃታቸውን በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ላይ እንዲሰነዝሩ ገፋቸው።። ይህ ጥቃት ሲታይ ከዶ/ር አብይና አጋሮቻቸው የመደመር፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የመቻቻል ዲስኩሮች ጋር የሚፋለስ ብቻ ሳይሆን አልፎ ተርፎም የቂምና የበቀል እርምጃ ቁጥር አንዱ" ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። እንደዚህ አይነት ፍፁም ኢ-ህገመንግስታዊ የሆነ የቂምና የበቀል እርምጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ህዝብን ልብ ያሻክራል፣ ያቆስላልና ያደማል ብቻ ሳይሆን ለመውጣት የሚያስቸግር አረንቋ ውስጥ እንደመግባት ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል። ምናልባትም እነዚህ መተኪያ የሌላቸው ብርቅየ የኢትዮጵያ ሶማሊ ህዝቦች እየተፈፀመባቸው ባለው ግፍና በደል ተገፍተው ሌሎች አማራጮችን እንዲያማትሩ መግፋትም ሊሆን ይችላል። ከዚህ ስንነሳ ዶ/ር አብይ "ቅዱስና ንጉስ ነኝ" ብለው እያሰቡ ባሉበት ባሁኑ ወቅት እንዲህ አይነትና መሰል የህገመንግስት ጥሰቶችና ንቀቶች ካሳዩ ወደፊት ወደማይቀር በሚመስለው የለየለት አምባገነንነት ሲቀየሩ ምን ሊፈፅሙ እንደሚችሉ መገመት ከባድ አይሆንም። ስለዚህ ሃላፊነት የሚሰማውና የሚያመዛዝን ዜጋ ሁሉ ከመንጋ አስተሳሰብ (Herd/Mob Thinking/Mentality)) ተላቅቆ ዶ/ር አብይን አደብ ይግዙ ሊል የሚገባበት ወቅት አሁንና አሁን ብቻ ነው፤ ኢትዮጵያችን የሁላችንም ናትና።

Back to Front Page