Back to Front Page


Share This Article!
Share
የፓለቲካ ስልጣን ጵጵስናዊ ስልጣን አይደለም።

    የፓለቲካ ስልጣን ጵጵስናዊ ስልጣን አይደለም።

 

ልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ) መስከረም 17/2011።

 

   የነፃነት መለኪያ ምንድነው? የዲሞክራሲስ?

ነፃነት አንፃራዊና ከእንቅስቃሴ ጋር የተዛመደ ነው። የስው ልጅ ሲፈጠርም ሆነሲኖር ነፃ አይደለም።እድገቱና አኗኗሩ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አጥሮች የተከበበ ነው። ያሻውን፣ የፈለገውን ማድረግ አይችልም።ውስንነት አለበት። አንድም በባህል ሌላው ደግሞ በስው ሰራሽ ህግጋት ተፅእኖ ስር ነው።በደል ፈፅሞ በነፃነት መኖር ከቶ አይቻልም።የመኖር መለኪያ ደግሞነፃነት ነው።የመስራት ፣ የመዳር፣ የማደግ ዋልታ ደግሞ ስምምነት ነው። ምድር የሁም ቤት ናት።ሰውም ምድርን በጊዚያዊነት ይገለገልባታል።አርሶ፣ ዘርቶ፣አጭዶ ፣ ወቅቶ ይተቀምባታል።  አምርቶ፣ፈብርኮ፣ ለብሶ ፣አጊጦ ይታይባታል። ተወልዶ፣አድጎ፣አግብቶ ፣ ወልዶ ዘምዶ ይኖርባታል። ግን በነፃነት አይኖርም። ምክንያቱም ነፃነት በተፈጥሮ ሳይሆን በፍላጋ የሚገኝ በመሆኑ ነው።ነፃነት ያለ ተጠቃሚነት ባርነት ነው።በድህነት ስር የሚዳዳ ሰው ነፃ ይሁን አይሁን ትርጉም አይስጠውም። ለምን የቅድሚ ቅድሚያ ተጠቃሚ አይደለምና ።የነፃነት መለኪያ በስምምነት ላይ የተተከለ ተጭባጭነቱ የተረጋገጠ የተጠቃሚነት ውህደት ድምር ውጤት ነው። ሰው በተፈጥሮና በስው አእምራዊ ውጤት የሚገኝ ጥቅም ተጠቃሚ ካልሆነ ነፃነት አልባ ከመሆኑም በላይ የዲሞክራሲ መርተኦም የለውም።ተጠቃሚነት ባልስፈነበት ዲሞክራሲ ይጎረብጣል።ዲሞክራሲ ከፍላጎት ጋር ካልተጣጣመ ጉዳት ነው። ምክንያቱም ዲሞክራሲ የነፃነት ጥቅም ማስከበርያ መሳሪያበመሆኑ ከማህበረስብ ፍላጎት ጋር መጣጣም ይኖርበታል ።ፍትሀዊ ጥቅምና ለውጥ ያለፍትሀዊ ነፃነት ዋጋ ቢስ ከመሆነም በላይ የጋርዮሽ ስምምነት መርሆች ያፈርሳል። በጋራ ለመኖርና ለመበልፀግ የጋራ መርሆ ያስፈልጋል።የመርሆች ተፈፃሚነት ማሳያ አንዱ ሰብአዊ ብልፅግና ነው።

Videos From Around The World

       የዲሞክራሲ መስረቱ ነፃነት ነው። በፍትሀዊነት ለመኖር ሰው ማክበር ሲጠይቅ ፣ለመብት መከበር ደግሞ ፍትሀዊ ዳኝነት ያስፈልጋል።በነፃነት የዳበር ህዝብ ዲሞክራሲን ለመስራት አይታደግም።ሰለዚህ ዲሞክራሲ የጥቅም ማስጠበቅያ ማሳሪያ መሆኑ ነው።የስው ጥቅም ስንል ማህበራዊና ኑሮ ያቀፈ መስተጋብር ለማለት ነው። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመከላከል ህዝብ አገልጋይ መርህ መኖር የግድ ሆኖ በመገኘቱ ከውጥረት ለመላቀቅ ማህበራዊ ፍትህ መመስረት ነበረበት።ሰው በሚያመቸው ስልትና ዘይ በእኩልነት ለመኖር የነፃነት ስምምነት መፍጠር ነበረበት። በመሆኑም ስምምነት ላይ ያተኮረ ስርአተ -ደንብ ቀርጾና ደንግጎ ለመኖር በጊዜ የተገደበ ተቋም ያስፈልገዋል።ይህ ተቋም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋም ነው። የተቋሙ ልዕልናም ተወራራሽና ተለዋዋጭ ባህሪ ያለው መሆን አለበት።ማህበራዊ መርሆ የጊዜና ለውጥ ውጤት ነው። ለውጥ ደግሞ የእንቅስቃሴ ውልደት ነው። ማህበራዊ እንቅስቃሴ መገደብ አይቻልም። ምክንያቱም ሰው ተንቀሳቃሽ ነው። በእንድ ቦታ ተገድቦና ተከልሎ አይኖርም። በመሬት ላይ የበላይነት አለው።በፈላገው ጊዜና ቦታ የመኖር መብት የተላበስ ነው። ግን ደግሞ የሂደት ጉዞ አለው። በስምምነት የተከለውን ስርአትና ደንብ መቀበልና ማክበር አለበት። በፍላጎት መኖር እንጂ መለውጥ አዳጋች ነው። ለውጥ ሰፋ ያለ ትንተናዊ ዳስስ ቢኖረውም ዋናው ሥሩ ግን አስተሳስባዊ ልህቀት ነው። ፍትሀዊ አስተሳስብ(rational thinking) የማህበራዊ እድገት መገለጫ አይነተኛ መርህ ነው።ይህ አስተሳሰብ ባልስፈነበት ማህበረሰብ የበላይነት ወይም ጠቅላይነት ስሜትይጎለብታል።ጥቅም ተኮር (የእኔነት) አመለካከት ይዳብራል።በሂደትም ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ ቅርፅ ይይዛል። የድህነት መንስኤም እስከ መሆን ይዘልቃል።ድህነት ደግሞ ተዋራራሽነት ባህሪ ያለው የስው ልጅ ፈታኝ ግን የሚበጠስ ሰንሰለት ነው። በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኣኗኗር ከድህነት ጋር ስምምነት የላቸውም ።የአስተሳሰብና አመለካከት ፅርየት(ንፅህና) የድህነት በሽታ ፈዋሽ መድሀኒቶች ናቸው።

የሃሳብ ልዕልነት ባልስፈነበት አገር የስው ዋጋ ከእቃ ሸያጭ ያነስ ይሆናል።ክብሩና ማንነቱ በነፋስ ይወስዳል። ባህሉና ወጉ ይናጣል፣ይቅጭጫል፣ ይዋጣል፣ይሞታል ፣ በማንነቱ ይጎዳል።ሰብአዊ ልዕልነት እንዲገነባ የማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝነት አለው። ጥቅሙንና ባህሉን የሚያስጠብቅ ህብረተስብ እንዲኖር ደግሞ የህግ ከለላ ያስፈልገዋል። የህገ መንግስት ስርአት (መንግስት የሚመራበት ስርአት) ገደባዊ ስርአት ከሌለ ለመተማመን ይጠፋል፣ጭቆና ይነግሳል፣ ስርአት ይጣሳል፣ ሌብነት ይስፋፋል፣ ድህነት ስር ይስዳል ፣ እድገት ይኮላሻል፣ ነፃነት ይሞታል፣ ዲሞክራሲ ይተናል፣ ግጭት ያገረሻል፣ ስደትና ረሀብ ይስፋፋል፣በመጨረሻም አገር ይፈርሳል። በአንድ አገር የተረጋጋ ስርአት አለ ለማለት የሚያስችል መመዘኛ መኖር አለበት። አንዱ መመዘኛ ደግሞ የምርጫ ሂደት ነው። ምርጫ አማራጭ ነው። የለውጥ መነሻም ነው። ህገ መንግስታዊ ግዴታም ነው። የመጪው ትውልድ ነፀብራቅም ነው። የአንድ አገር ህዝብ መሪውን ለመስየም የሚያስችሉት ማስፈፀምያ ነፃ ተቋሞች እንዲኖሩት ይፈለጋል።የለማ አገር፣የተረጋጋ ዜጋ ፣ ጥቅሙን ያወቀ ህዝብ ለመገንባት የመንግስትና የስልጣን ገደብ መኖር አለበት።

        የፓለቲካ ስልጣን በደጉማና ቀኖና አይመራም። የፓለቲካ ስልጣን ገደብ ባበጁ የአለም አገሮችና ያልተገደበ ስልጣን ባላቸው አገሮች መሀል ያለው የእድገትና ብልፅግና ልዩነት ተቀራራቢ አይደለም። በአንድ ፓርቲ ወይም መንግስታዊ አገዛዝ (አስተዳደር) ያለስልጣን ገደብ የሚተዳደሩ አገሮች(ያልበለፀጉ) በውስጣዊ የተናወጡ ናቸው። የሀብት ብክነትና ሌብነት በስፋት ይታይባቸዋል።መሪዎችም አምባገነን ናቸው። ሰብአዊ መብት ያልገደብ ይጣሳል።እንደ ጵጵስና ያለገደብ የሚመራ ፓርቲ ወይም መንግስት ፈፅሞ የዲሞክራሲ መርሆች አያከብርም። በግላጩ ዘራፉና ህግ ገምዳጅ ይሆናል።የህዝቡ እምነት ያጣል። በመሞገስ ፈንታ ሌባ መንግስት ለመባል ይበቃል።የፓለቲካ መርህ ህግን መስረት ተደርጎ የሚስራ የመንግስት ስርአት ነው።

        የፓለቲካ መሪዎች ስብከትና የሚናገሩት ቃል ለጊዜው መልካም ቢመስልም ተግባር ላይ ብዙ ጊዜ የሚሳካ አይሆንም።ለሚመሩት ህዝብ የማይናገሩት የተስፋ ቃል ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል። ትግበራ ላይ ግን ይሽመደመዳሉ። ለዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ የብቃትና የግልፅነት መጔደል ችግር ነው። በመስረቱ ስልጣን መልካምም ነው አይደለምም።እንደአጠቃቀሙና አመራሩ ነው።የህዝብ መሪዎች አሉ። የህዝብ ያልሆኑ መሪዎችም አሉ።በህዝብ ስም የሚነግዱ አስመሳይ የፓለቲካ ነጋዴዎች ለህዝብ ውግንና የቆሙ መስሎ ችግር የሚፈጥሩ፣ ህግ የሚያዛቡ፣ ውንጅልና የሚያስፋፉ፣ ለስፊው ህዝብ ዴንታ የሌላቸው፣ በነቅዕ መስመር የስፈሩ ሌቦች ናቸው።የኋላ ታሪካቸውም ችግር ያለበት ነው። በአንድ ወቅት ሌባ የነበረ ሰው ልማዱ ሁሌም ይከተለዋል። ስልጣን ላይ ሲቆናጠጥ ደግሞ የበለጠ ሌባ ይሆናል ።መቸም አገር በሌቦች ስትመራ ህውከት እንጂ ሰላምና ልማት አይስፍንም ። ህዝብ የሚበድልና የሚስርቅ መሪ የሚጠየቅበት ስርአት ማበጀት ተገቢ ነው። ችግሩ ግን ሁሉም ሌባ ከሆነ ጠያቂም ተጠያቂም አይኖርም። አማራጩ ሁሉም አስታቅፎ ገደል መጣል ነው።ሌባ መሪ በህግ መጠየቅ እንጂ በምክርና ግምገማ የሚስተካከል አይሆንም።ቀጣፊ መንግስት ወይም መሪ ወይም ፓርቲ በድያለሁ ስለሆነም ህዝቤ ለመካስ እፈልጋለሁ ሲል ይደመጣል። ይህ ህዝብ መናቅና ማፌዝ ነው። ወንጀልም ነው።መሪ ከተሳሳተ መቀየር ወይም መጣል ነው ያለበት። በፓለቲካ ሂሳብ ይስተካከላል የሚባል ፅንስ ሀሳብ የለም።የፓለቲካ መርህ የተለየ ነው። ፓለቲካ የስልጣን ማግኛ ሃሳባዊ መንገድ ነው።በዚህ መርህ ስህተት መፈፀም የለበትም።ምክንያቱ ስህተት ለማረም ያለው እድል እጅግ ጠባብ ነው።የፓለቲካ ስህተት የሚያስከፍለው ዋጋ መተመን ያዳግታል።

ህዝብ እንክሳለን የሚሉ ሞላጫና አትላይ መሪዎችና የፓለቲካ ድርጅቶች መገደብና መቀጣት ይኖርባቸዋል ።የፓለቲካ ጌጋ(ስህተት) እየታረመ የሚሄድ አሰራር አይደለም ። ምክንያቱም ህግና ስርአት ተበጅቶለት የሚጀመር ስራ በመሆኑ አስተዳደራዊ ስህተት አይከስትም። ከተከስተም የስሪው እንጂ የህግ ስህተት አይሆንም። ሰለዚህ የማስተካከያ እርምጃ መውስድ በፓለቲካ ስርአት የግድ ነው።ህግና ስርአት ሲጣስ መታለፍ አይቻልም ።ለምን ቢባል የፓለቲካ ስርአት ባህሪ ስላልሆነ ጭምር ነው።ስለሆነም ከመርህ በማፈንገጥ አይቻልም። የፓለቲካ ስልጣን በባህሪው አጔጊ ነው።በመሆኑም ለስህተትና አምባገነናዊ አሰራር ተገላጭ ነው። መሪዎች ዝነኛና ተወዳጅ የህዝብ አገልጋይ ከመሆን ይልቅ ሲልከስከሱና ሲማግጡ ይታያሉ።ሲስርቁና የህዝብ ሀብት ሲያባክኑ ይታያሉ።ሲጨቁኑና ሲያስሩ ይታያሉ። ነፃ እንዳልነበሩ ነፃነት አልባ ህይወት ይኖራሉ። በፈፀሙት ስህትትም ሲንከራተቱ ይኖራሉ። የህዝብ ያልሆነ መሪ ወይም የፓለቲካ ድርጅት ወይም መንግስት ጊዜና እድል ሊሰጠዉ አይገባም።የፓለቲካ ስርአት የለውጥ ጥንስስ መሆን አለበት። የፓለቲካ ስርአት ተለዋዋጭነት ባህሪ አለው። ከነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የሚዘምምና የሚዘምን ፓለቲካዊ ስርአት ወሳኝ ነው። ህዝብ እስኪስለቸውና ቋቅ እስኪለው መጠበቅ የፓለቲካ ብልሀትና ብስለት አይደለም። ፈጣና ተራማጅ ፓለቲከኛና የፓለቲካ ስርአት ያስፈልጋል።

       የፓለቲካ ስልጣን የኮንትራት ስራ ውል ነው። በዚህ መስረት ውል ያፈረስ ይቀጣል።የፓለቲካ ስልጣን ውል ማደስ ይቻላል ።ለማደስ ደግሞ ውፅኢታዊ (ውጤታማ) መሆን ይጠይቃል።የፓለቲካ ኮንትራት ውል ለማደስ ደግሞ ውድድርና አማራጭ መኖር አለበት።አማራጭነትና ተዋዳዳሪነት የሌለበት የፓለቲካ ስርአት አምባገነን (totalitarian) ስርአት ነው። መብት ጨፍላቂ ስርአት ከሆነ ደግሞ ነፃነትና ዲሞክራሲ ማሳ ለማሳ መስጎም(መጣጣምና መጓዝ) አይችሉም ። በፓለቲካ መርህ የተፈረቀ መብት የለም። ከፊል ዲሞክራሲም የለም። አማራጩ መሆን ወይም ያለመሆን ነው። ማንም ፓለቲከኛ ወይም የፓለቲካ ድርጅት ስብከተ ቃል ህዝብን ያማከለ ነው። የገጠርና የከተማ ህዝባችን ጥቅም ለማስከበር የሚል ተስፋ ከፓለተካ ድርጅቶችና መሪዎች መስማት የተለመደ ነው። ህዝብም በታላቅ ተስፋ ይስማቸዋል፣ ይከተላቸዋል፣ ይስይማቸዋል። ነገር ግን ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ባህሉ ውስንነት ይታይበታል።መሪውን የሚከታታል፣የሚሰቀል ፣የሚያወርድ ማህበረሰብ መገንባት አለበት።ጊዜያዊ ወይም የስሜት ፓለቲካ መጨረሻው ውርደትና ውድመት ነው። በተሳሳተ የፓለቲካ መስመር መዋዣቅ(nasticsim) የፓለቲካ ልህቅነት ወይም ብስለት ክስረት ነው። የምክንያታዊ የፓለቲካ ስርአት መነሻው ከጭፍን አስተሳስብ የተላቀቀ ፍትሀዊ አስተሳስብ መከተል ነው። በፍትሀዊ አስተሳስብ(rationalism) የተቃኘ ህዝብ በሁሉም መስክና ዘርፍ ውጤታማ ነው።የሀሳብ ልህቀት ለዘላቂ እድገትና ስላም አይነተኛ ምክንያት ነው።

        ለዘላቂ የህዝብ ጥቅም ዘላቂነት ያለው አስተሳሰብ መወረስና መጠናከር አለበት።ለዚህ ደግሞ በነፃነት ማሰብ ያስፈልጋል።በነፃነት ማሰብና መንቀሳቀስ የመጀመሪያ የነፃነትና የዲሞክራሲ መብት መገለጫ ነው።የሃሳብ ነፃነት የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው የትውልድ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ መብት ወፍሪ(ግብአት)ነው። የተለያየ የሃሳብ አመለካከት ያዳበረ ማህበረሰብ በዘላቂ ረብሓ(ጥቅሙ) አይደራደርም። በፍታሃታዊ አስተሳሰብ የዳበረ ማህበረሰብ የፓለቲካ ሚዛን ለማስተካከል ብቃትና ክህሎት ይኖረዋል።በፓለቲካ በመቀያየርና መለዋወጥ ስጋት ውስጥ አይገባም። የፓለቲካ ስራ እንደ ገበያ ነው። አዋጭነቱና ጠቀሜታው በሚገባ መተንተና መጠናት ይኖርበታል። አዋጭነቱ በማህበረስቡ መመዘን አለበት። የፓለቲካ ወገንተኝነት አያስፈልግም ። ማንም ይሁን ምን መመዘንና መታየት ያለበት ከህዝብ ጥቅም ጋር በተያያዘ መሆን ይገበዋል። ጥሩ ለስራ አድናቆት ላጠፋ ደግሞ ውግደት መለመድ ያስፈልጋል ። የፓለቲካ ሚዛኑ ውጤቱ እንጂ ቁመናው አይደለም። የፓለቲካ ድርጅት የተለያዩ ሃሳቦች በግልፅና በነፃነት የሚመረቱበት ስብስብ እንጂ የአፄዎች አመለካከት የስፈነበት ድርጅት መሆን የለበትም። ስልጣን ከአንድ የፓለቲካ ስልጣን ወደ አንዱ የፓለፓቲካ ስልጣን መቀያየር መቻል የፓለቲካ መርህ ከመሆኑም ባሻገር የህብረተስብ የአስተሳስብ ነፃነትና ዲሞክራሲ መበልፀጉ ማሳያ መርሆ ነው። የፓለቲካ ስልጣን ባለቤቱ ህዝብ ነው። የፓለቲካ ስርአትና ስልጣን መቀየርና አማራጭ መተካት የፓለቲካ ማህበረስብ ብስለት መለከያ ሚዛን ነው። የፓለቲካ ድርጅት የማህበረስቡ ፍላጎት ያማከለ ድርጅታዊ ተግባሮች የማያከናውን ድርጅት ከሆነ የፓለቲካ ድርጅት ሳይሆን የፓለቲካ ነጋዴ ነው። መወገድና መቀየር አለበት። በህዝብ ስም መሽቀጥና መሸሸግ ህድብ ያለማክበርና ወንጀል ነው። ቅጥፈትና ተንኮል ነው። ሌብነትና ስንፈት ነው። የአንፃራዊ የህዝብ ነፃነትና ዲሞክራሲ አንፃር ነው።

 

 

 

 

 

 

Back to Front Page