Back to Front Page


Share This Article!
Share
የፕሮፌሰር መስፍን ቅኝትና የዶክተር መረራ ጉዲና ምኞት

የፕሮፌሰር መስፍን ቅኝትና የዶክተር መረራ ጉዲና ምኞት

ይቤ ከደጃች ውቤ 11-06-18

ሰሞኑን በወጡ የግል ጋዜጠች ላይ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን ቅኝት ተኮር ትችትና የዶክተር መረራ ጉዲናን ምኞት ወይም ናፍቆት በወፍ በረርም ቢሆን ለማየት ሞክሬያለሁ ፡፡ ሁለቱም ምሁራን ሃሳብን የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በጋዜጦቹ ላይ አስተያየታቸውን ገልፀው አንብቤያለሁ፡፡ሁለቱም ግለሰቦች በመምህርነት ሙያቸው ለሀገሪቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሲያበረክቱ የቆዩ ኢትዮጵያ አለኝ ከምትላቸው ምሁራን ተርታ የሚጠቀሱ የካበተ ልምድ ያላቸው ሲሆኑ፤ የፕሮፌሰር መስፍን ሆነ ረዳት ፕሮፌሰር መረራ በዕድሜያቸው ብቻ ሳይሆን በሙያቸው አንቱ የተሰኙ ልሂቃን ናቸው፡፡

Videos From Around The World

ምሁራኑ በዕድሜና በቁመና ይበልጡኛል ከእነሱ ቁመናና ዕውቅና አንፃር እኔ ብላቴና ነኝ በዕውቀትም ሆነ በታዋቂነት አጠገባቸው አልደርስም ፡፡ፕሮፌሰር መስፍን ቅኝታቸውን (ትችታችውን) ሲጀምሩ ፤የክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሹመት በማጣጣል የሦስቱም ሥርዓት አገልጋይ ነበረች በሚል ነቀፌታ ነው ፡፡

እኔ ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የሦስቱም ሥርዓት አገልጋይ ሆነው ማለትም በመምህርነት ለህዝብና መንግሥት እንደሠሩ እንደነበር ነው የምረዳው፤ ዕድሜያቸው እየበረረ ይሁን አለቃቸው እያባረረ ባላቅም ከመምህርነት ተሰናብተዋል፡፡ ስለዚህ ፕሮፌሰሩም የሦስቱም ሥርዓት አገልጋይ ነበሩ ለእርሳቸው ሲሆን ልክ ለሌላው ሲሆን ስህተት ሊሆን የሚችልበት መንገድ አልታይህ አለኝ ፡፡

ከመምህርነት ሲለቁ የሰብዓዊ መብት ተጋች ድርጅት መሥርተው ሲንቀሳቀሱ ቀጥሎም በቅንጅት ፓርቲ ምሥረታ ወቅት ዋና ተዋናይና አቀንቃኝ የነበሩ ናቸው፡፡ ይህንንም ያደረጉት ከዩኒቨርሲቲ ሲለቁ እንደነበር ተረድቻለሁ፡፡ ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሹመቱን ሲያገኙ ደስታው የጋራችን ነው፤ ለሌሎች ሴቶች ተምሳሌት ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ሊያስነቅፋቸው የሚችል ነገር ካለ በአገልግሎት ዘመናቸው የሰው ሕይወት ሲያጠፉ፣ ሀብት ንብረት ሲዘርፉ ከተገኙ ወይም ከተዋናዮቹ መካከል የሚጠቀሱ ቢሆን ነበር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አስተያየት ሲሰጡ የምንጠቅመውም የምንሰጡት ሂስ አልሚ ሲሆን እንጂ አውዳሚ ሲሆን አይደለም፤ እናም ፕሮፌሰሩ በሙያቸውም በዕድሜያቸውም አንጋፋ ሆነው ሳለ ቀርፋፋ አስተያየት ሲሰጡ መታየት አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ መንቀፍንም ብቻ ሳይሆን የመደገፍ ሞራል የመስጠት ባህልን ማዳበር አለባቸውም፡፡ ባለንባት ምድር ላይ ምሉዕ በኩልሄ የሆነ ስብዕና ያለው አመራር ደግሞ ማግኘትም የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ሰሞኑን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተመድን ጨምሮ እንደ አፍሪካ ብረት የመሳሰሉ አህጉራዊ ተማት እና ሌሎችም ክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዕውቅናና አድናቆት የሰጡትን የክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሹመት ሲያጣጥሉና ሲያብጠለጥሉ አንብቤያለሁ፡፡ ለነገሩ ፕሮፌሰር መስፍን ሲያናንቁ ነው እንጂ ሲያደንቁ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን በሴትነታቸው ለዚህ ታላቅ ሓላፊነት ዕውቅና ቢሰዋቸው ወጣት ሴቶቻችንም ለዚህ ሓላፊነት መድረስ የሚችሉበትን ጎዳና የሚያሳዩ ይሆናሉ፡፡

ነገር ግን ፕሮፌሰር መስፍን የሰጡት ሂስ ወይም አስተያየት ፋይዳውን ልረዳው አልቻልኩም፡፡ ሂስ አልሚ እንጂ አውዳሚ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ከላይ እንደ ጠቀስኩት ፕሮፌሰሩ ሹመቱን ያጣጣሉትና ያብጠለጠሉት ፕሬዚዳን የሦስቱም ሥርዓት ማለትም ለንጉሣዊው ለወታደራዊውና ለፌዴራላዊ ሥርዓቶች ስታገለግለ የቆየች ናት በሚል አመለካከት ነው፡፡

ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባላቸው የካበተ የዲፕሎማሲ ሙያ ከሀገራቸው አልፈው በክፍለ አህጉራዊና አህጉራዊ ተማትን ጨምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለያዩ ቦታዎች ተመድበው አገልግለዋል፤ ይህም በዓለም አቀፍ ማበረሰብ ዘንድ ያላቸውን ዕውቅናና ተቀባይነት የሚያሳይ ነው የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጎቴሬዝ ሹመታቸውን አስመልክቶ ለኢትዮ መንግሥትና ሕዝብ አድናቆታቸውን በመግለፅ የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ክብርት ፕሬዝዳንትዋን በሴትነታቸው በእናትነታቸው ለዚህ ሀገራዊ ሓላፊነት በመብቃታቸው አመራራቸው የተሳካ እንዲሆን በሀገሪቱም የሚታዩ የጎሳ ሽኩቻዎች ተወግደው ሰላም እንዲሰፍን በማሰብና በማሳሰብ ዕውቅናና ልዕልና ቢሰጡዋቸው የተሻለ ነበር፡፡

በሀገራችን ባህል ለሴቶች የምንሰጠው ክብር ከወንዶች ያነሰ ነው በአንዳንድ አካባቢዎች ትልልቅ ሰዎች እንን ሲጣሉ የሴት ልጅ እያሉ አፋቸውን መክፈት ይቀናቸዋል፡፡ ለነርሱ ዘለፋ ቢሆንም ከሴት ያልተወለደ ደግሞ የለም ሴቶቻችንም ጥሩ ሥራ የሠራች ሴትን አትገርምም ወንድ እኮ ናት እያሉ ይገልፃሉ፡፡ ይሄ የሚያሳየው ትልልቅ ሥራ የሚሠራው በወንዶች ብቻ ነው የሚል ዕሳቤ በውስጣቸው እንደተቀረፀ መሆኑን ነው፡፡

ስለዚህ ፕሮፌሰር ለአንበሳ አይመትሩም ለብልህ አይመክሩም እንደሚባለው ርስዎ መምከር አልችልም፡፡ ሲያኮስሱ እንጂ ሲያወድሱ፣ ሲንቁ እንጂ ሲያደንቁ ስለማልሰማ መደነቅ ያለበትን እያደነቁ ቢተቹ የሚያምር ይመስለኛል፡፡ ምሁር ደግሞ ሁሌ ማማረር የለበትም ብዬ አስባለሁ፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናም የጥምር መንግሥት ቢቋቋም የተሻለ ነው የሚል ምሁራዊ አስተያየት ሰጥተዋል ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ አምጥቶ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳውን ጠብቆ ምርጫ ለማካሄድ እየተንደረደረ ይገኛል የምርጫ ወቅቱም ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ የሚቀረው ነው ፡፡

ባለንበት ወቅት ጥምር መንግሥት መመሥረት ማለት የምርጫ ጊዜውን ማራዘም ማለት ይመስለኛል፤ ፋይዳውም የጎላ አይመስለኝም የሚሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው ልዩነታቸውን አጥብበው በርግጥም ጠንካራ የተፎካካሪ ፓርቲ ሆነው ወጥተው ራሳቸውን ለምርጫ ማዘጋጀት ነው፡፡

በ1960ዎቹ በመደብ ትግል ሲቆራቆሱ የነበሩ የነበሩ የፓርቲ አመራሮች አሁንም በዛው ጎዳና ሲዳክሩ ነው የምናየው፤ እነሱ አመራር እየሰጡ ወጣቱና ድው ገበሬ በሞትና አካል ጉዳት ሰለባ ይሆናል፡፡ ፓርቲዎቹ ለዚህ ህዝብ ያተረፉለት ነገር ሞትና ዕልቂት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የብሔርን ልዩነት እንደዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ሰላምና ህልውና ቢያስቡ መልካም ነው፡፡ በየቦታው እየተሰማ ባለው ግጭት እየተጎዳ ያለው ድሀው ህዝብ እና ወጣቱ ነው እነርሱ ከረባታቸውን አስረው መግለጫ እየሰጡ ወጣቱን ለእንግልትና ለስቃይ እየዳረጉ እንዲሁም ለሁከትና ለእስር ሊዳርጉት ያስባሉ ፡፡

በወጣቶች ላይ ልዩነትን የሚያሰፋ አመለካከትን እያሰረፁ መንበረ ሥልጣን እንቆጣጠራለን ብለው የሚያስቡም ምኞታቸው የህልም ራት ሆኖ እንደሚቀር ማሰብ አለባቸው፡፡ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቁጥር ብቻ ብዛት ያላቸው ናቸው ሲሆኑ ከፊሎቹ የመገንጠልን ዕሳቤ ያነገቡና ልዩነትን የሚያራግቡ የተወሰኑት ደግሞ ብረ ብሔራዊ አተያይ ያላቸው ናቸው፡፡

ከፓርቲዎቹ ውስጥ አንዳንዶቹ ከአመራሮች በስተቀር አባል የሚባል ያላቸው አይመስልም አባሎቻቸውን ሰብስበው ሲያናግሩ አይሰማም የገንዘብ ምንጫቸውም ምን እንደ ሆነ የሚታወቅ ነገር የለም በግሌ በፓርቲ አመራር ሆነው የሚያገለግሉ ግለሰብ በግለሰቦች ስም እየነገዱ ሀብት እንዳካበቱ ታዝቤያለሁ፡፡ በየቦታው በሚሰማው ግጭት እንዲበርድም ሲጥሩ የመፍትሔ ሃሳብ ሲያቀርቡ አይሰማም ፡፡ጥንካሬያቸው ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው ከአንድ የሠፈር ውስጥ እድር ያነሰ ወይም የላላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም በዚህ ሁኔታ የጥምር መንግሥት እንዲመሠረት ቦታ መስጠቱ ለሀገር የሚሰጠው ፋይዳ አይኖርም ይልቁንም ጠንክረው ወጥተው በምርጫ ውድድሩ ተሳታፊ መሆን ይመረጣል፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚበጀው ፓርቲዎቹ ተሰባስበው ጠንካራ ፓርቲ ሆነው ከአውራው ፓርቲ ጋር ለመፎካከር መጣር ትልቁ ሓላፊነታቸው ነው ይህ ደግሞ ለሀገርም ለህዝብም የሚበጅ ሀሳብ ለማቅረብ ይረዳቸዋል፡፡

 

Back to Front Page