Back to Front Page


Share This Article!
Share
"ለውጡ" ያስከተለው መልካም ዕድሎች እና አሉታዊ ውጤቶቹ (አባይን በጭልፋ)

"ለውጡ" ያስከተለው መልካም ዕድሎች እና አሉታዊ ውጤቶቹ (አባይን በጭልፋ)

ከማህተመ ፍቅረስላሴ 11-24-18

እንደመታወቀው የአገራችን ሆኔታ ሁሉም ሰው በሚባል መልኩ የፓለቲካ ተንተኝ አድርጎታል :: ይህ ትውልድ በሀገሩ ነገር ያገባኛል ፣ ይሰማኛል በማለቱ የመጣ አስተሳሰብ ነው፡፡የራሱ የሆነ መልካም ነገር አንዳለው ሁሉ በሌላ በኩል የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤትም አለው፡፡በአሁኑ ጊዜ በአብዛህኛው ህብረተሰብ የሀገሩ ጉዳይ ሳይሆን እያንገበገበው ያለው የብሄሩ እና የመሬት ጉዳይ ነው፡፡

ታድያ ይህ ለምን ሆነ ካላችሁ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል፡፡የመጀመሪያው የሀገሪቱ አከላለል ያስከተለው ውጤት ነው፡፡ይህም ተበታትነው የነበሩ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ የአገሪቱ ህዝቦች በሚመሳሰሏቸው ሰዎች ወደ አንድ የታቀፉ ሲሆን በሂደት እነዚህ ህዝቦች የራሳቸውን ነገር እያጠናከሩ ሲመጡ ኢትዮጵያዊነት እየተዘነጋ እንደመጣ አስባለው፡፡ይህ ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ መንግስታት በሀገሪቱ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

Videos From Around The World

ሁለተኛው ነገር ደግሞ የብሄር አቀንቃኞች የፈጠሩት ችግር ነው፡፤ይህም የእኛ ብሄር አልተጠቀመም ፣ ተጎድቷል፣በሀፍት ክፍፍሉ እየተጎዳ ነው ወዘተ የሚል ነገር በማጤንጠን የሰዎች አስተሳሰብ በአጥር ውስጥ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

እንግዲሀ ከላይ ያሉ እውነታዎች ሁሉም ሰው ቢገነዘባቸውም ነገር ግን ከነበረበት አመለካከት ሊወጣ አልቻለም፡፡በቅርቡ የመጣ ለውጥ "መሰረቱ የተለያየ ቢሆኑም አስከተሎ የመጣው መልካም ነገር እንዳለ ሆኖ አሉታዊ ተፅዕኖም እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

በመሰረቱ ለውጥ ማለት ምን ማለት ነው ?

በእኔ አረዳድ ለውጥ ሽግግርን እንጂ ሂደትን አይወክልም፡፡በሂደት ውስጥ ማሻሻል ያካትታል ፤ ከነበረው ወደ ላይ ወይ ወደ ታች መሰረቱን ሳይለቅ ሂደቶች ይቀጥላሉ፡፡በሽግግር ጊዜ ግን ከሆነ ነገር ወደ ሌላ አዲስ ነገር ይለወጣል ማለት ነው፡፡በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ የአሰራር ስርዓት መለወጥ ነው እንጂ ያለው የመንግስት ለውጥ የለም፡፡ይህ ሁሉም ህብረተሰብ ሆነ በራሱ መንግስት ሊረዳው እና ሊያውቀው ይገባል፡፡እስኪ ባለፉት የአሰራር ለውጥ ሂደቶች የታዩ ስትራቴጂያዊ እንቅስቃሴ እንመልከት፣

1.  የመንግስት ሚና ከኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ወደ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች በስፋት ተንሰራፍቷል፣

እንግዲህ የቀድሞ ኢህአደግ ውሳኔዎች በአብዛህኛው ኢኮኖሚክ ውሳኔ መሰረት በማድረግ በስፋት መሰረት ልማት በተለይም ፣ የሰው ሃይል ልማት የጥራቱ ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ፣ የብሄረሰቦች ልማት እና የግንበታ ሴክተር የመሳሰሉት ላይ በስፋት ሰርቷል፡፡እነዚህ ነገሮች ባይሰሩ ንሮ ኢትዮጵያ አሁን ከላችበት የድህነት ሁኔታ ወደ አስኪፊ የሚባል ደረጃ ትደርስ ነበር፡፡

ይህን በቅጡ ለመረዳት አዳጋች የሆነበት ምክንያት አሁን ያለው ትውልድ ራሱን የሚያነፃፅረው ቤተሰቡ ካሳለፉት የሂወት ጊዜ ጋር ሳይሆን በአንድ ጊዜ ካደጉ አገሮች ጋር በመሆኑ ነው፡፡

አዲሱ አመራር ደግሞ የቀድሞ አመራር የረሳቸው ላይ ቁልፍ ስትራቴጂ ውሳኔዎች ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡እንደሚታወቀው ጥላትህን ለመውጋት ርቆ ከመዋጋት አቅርቦ ጓደኛ አድርጎ መውጋት የተዋጣለት ስትራቴጂ ነው፡፡

እርግጥ ነው አዲሱ አመራር የእውነተኛው ስትራቴጂው ምን እንደሆነ ማወቅ ቢያዳግትም የብዙ ተቃዋሚ እና ፅንፈኞች ሃይል አላማ በአንድ ግዜ ንዶታል፡፡ምክንያቱም እነሱ የሚያወሩትን አዲሱ አመራር ከተናገረ ልዩነቱ ዜሮ ሆነ ማለት ነው፡፡

እንግዲህ እውነታው ባናቅም የሚመስለንን ግን እንፀፋለን እና መንግስት የእውነት የቱን መንገድ እየተከተለ እንደሆነ ወይም ትክክለኛው ዓላማው ወደፊት ጊዜ የሚያወጣው ነገር ቢሆንም ነግር ግን የቀድሞ መንግስት ያፍናቸው የነበሩትን ጋዜጤኖች ፣ መንግስቱን ይቃወሙት የነበሩትን ተቃዎሚዎች ነፃ በማድረግ በዋነኝነት በተቃራኒ ጎራ ቁመው ከነበሩት ሃይሎች ጋር እንዲሁም የእነሱን ሀሳብ ከሚደግፉ ህብረተሰብ ጋር በቀላሉ ለመግባባት እና ልባቸውን ለማሸነፍ ተችሏል፡፡

2.  የዝምታ ፖለቲካ ተንሰራርቷል፡

በዚህ ጊዜ በሁለት ነገር ሚድያዎች እንደተከፈሉ መረዳት ይቻላል፡፡ይህም የሚነሱ ጥቃቶች እና ችግሮች ባለው ደረጃ ለህዝብ ለማድረስ እየተሰራ ያለው ሚና እየነፈሰ ባለው ነፋስ አብዛህኛው ሚድያዎች እየተጓዙ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡

እርግጥ ነው የፖለቲካ ነፋሱ ከልማታዊ አስተሳሰብ ወደ ፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳ እንደተለወጠ አስባለሁ፡፡እንግዲህ ፖለቲካዊ ፕሮፖጋንዳ ስል ለማለት የፈለኩት የቀድመዎቹ ሚድያዎች እና ፖለቲካኞች በተለይም የአገር ውስጥ ንግግራቸው ስራቸው ሁሉም ነገራቸው ልማታዊ መንግስት ከሚለው አስተሳሰብ የመነጨ ነበር፡፡

የአሁኖቹ ፖለቲከኖች እና ሚድያዎች ንግግራቸው ሆነ አረማመዳቸው ኢኮኖሚካል መሰረት ያደረገም ሳይሆን ፖለቲካ መሰረት አድርጎ የራሱ የሆነ አጀንዳ በመያዝ ነገር ግን ነፋሱን ለመከተል ወይም ለመምራት ፕሮፖጋንዳ መሰረት በማድረግ እየተሰራ ያለ ስራ ለማለት ነው፡፡

በዚህም መሰረት እየደረሱ ያሉ ብሄር ተኮር ግጭቶች እና መፈናቀሎች በተለየም በተገለለው ወገን በዝምታ ማለፍን የመረጠ ይመስለኛል፡፡ዝምታ የራሱ ጥሩ ነገር ያለው ቢሆነም ዝምታ ሲበዛ ግን ተጎጂው ራሱ ዝም ያለው ስለሚሆን መንግስት መጠንቀቅ አለበት፡፡

 

3.  የሹም ሽረት ሂደቶች

እንግዲህ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ወደ ስልጣን ሲመጡ የነበሩ አመራሮች ከጠቂቶቹ በስተቀር በአብዛህኛው ወይ ተለውጠዋል አልያም ተሸረዋል፡፡

አንድ መሪ ከጎኑ በማድረግ አብረውት የሚሰሩትን መርጦ ሽመተ ሲሰጥ እውነትም በአብዛህኛው ነገር የመሪው ሀሳብ እየተቀበሉ መመሪያ የሚሰጡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡በዚህ መሃል ግን አንድ አንድ ጠንከር ያለ ሀሳብ የሚያነሰ ግለሰቦች መኖራቸው የግድ ይላል፡፡

እንግዲህ የሹመት ነገር ከተነሳ ዋናው ነገር የህዝብ ሮሮት ያለው ወረዳ አከባቢ በመሆኑ የወረዳው የአሰራር ሁኔታ ተፈትሾ አስቸኳይ ውሳኔ የሚያስፈልገው ሲሆን ከዚህ ውጭ ያለው ደግሞ የመንግስት ሰራተኛው ሮሮት ነው፡፡

የመንግስት ሰራተኛው ከፍተኛ የሆነ ችግር እንዳለበት ሁሉም አመራር የሚገነዘበው አይመስለኝም ፡፡ እርግጥ ነው አዲሱ ካቢኔ ሲሾሙ ደ/ር አብይ ያስተላለፉፈት መልዕከት በጣም ጥሩ የሚባል ነበር ፤ ነገር ግን ያን ያህል ዋጋ የለውም፡፡ ሁሉም የመንግስት ሃላፊዎች ባለቸው ስልጣን ሰራተኛን ያንገላታሉ፣ ያበሳጫሉ ይበድላሉ፡፡አሁንም ቢሆን መልካም መሪ የለም እያልኩ አደለም በአብዛህኛው ዝቅተኛ አመራሮች በተለይም የቡድን መሪዎች ፣ የመመሪያ ኃላፊዎች /ዳይሬክቶሮች ከበታች ያሉ ሰራተኞች በጣም ከሚገባው በላይ እያሰቃዩት ይገኛሉ፡፡

የመንግስት ሰራተኛው ከመንግስት ሃላፊው ጋር መንግስት ቀጥሮ ሲያሰራቸው ሁሉም ለአንድ አላማ ነው ፤ እሱም መንግስት ለዜጎች እሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ በየደረጃው ተልዕኮውን ለማስፈፀም እና ለመፈፀም የተቀጠሩ ሰራተኞች ናቸው፡፡ይህ መሆኑ እየታወቀ በአብዛህኛው አሰራሩ የአሽከር እና ጌታ ስርዓት ሁኗል፡፡

የመንግስት አመራሮች በተለይም ሲቪል ሰርቪሱ እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ስር የሚገኙ ትዕዛዝ ሰጪ ሳይሆን መከተል ያለባቸው አቅጣጫ ተቋሚዎች ፣ መመሪያ ሰጪዎች እንዲሁም ውሳኔ ሰጪዎች መሆን አለባቸው፡፡ፕሮፊሽናሉ ሰራተኛ ደግሞ ስራውን ሳይነሳዊ አድርጎ በሚሰጠው መመሪያ እና ውሳኔ መሰረት ተገቢውን ስነ ምግባር ተላብሶ አገልግሎቱን መስጠት ነው፡፡

ያለው ሆኔታ ግን ኃላፊ ያዛል ፈፃሚ ይፈፅማል ካልመሰለውም ይፈፅማል ምንያቱም ትክክለኛ የምዘና ስርዓት ስለማይተገበር ፈፃሚን ለመጉዳት ፣ በሞራሉ ለመጫወት ኃላፊዎቹ ጋር ሃይሉ ስላለ ነው፡፡

ፈፃሚዎችም ቢሆን የተማሩትን ከመተግበር ትዕዛዝ ተቀባዮች ሁነው እና ሌላ ያልተገባ ባህረ ለምደው ይወጣሉ ፡፡

በመሆኑም የሹም ሽረቱ በመንግሰት መስሪያቤቶች ከዝቅተኛ አመራር እስከ ከፍተኛ አመራር መቀጠል አለበት፡፡

4.  የማግለል እና የመገለለ ፖለቲካ

መገለል ማግለል በህዝቦች መካከል እጅግ በረቀቀ መንገድ እና ሁኔታ የሚሰራ ሲሆን ይህም ጥበባዊ መንገድ ተከትሎ እየተፈፀመ ያለ ነገር ነው፡፡እውነታው በእርግጥ ማወቅ ባይቻለም ወደ እውነታው የተጠጋ እና ድርጊቶችን ግን ገምግሞ የሆነ ሀሳብ ላይ መድረስ ይታያል፡፡

ህወሓት አሁን ያለበት ደረጃ ትክክለኛ አቅሙ በሚወራው ሆነ በእውነታው ማወቅ አደጋች ቢሆንም በተለያዩ መንገድ ግን የመገለለ ፖለቲካው ተጠቂ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የተቋዋሚ ሚድያዎች ሆኑ ቡድኖች ዋንኛ የህልውናቸው መሰረት ህወሓት ላይ ያለ እና የለለ ሃይላቸው ተጠቅመው እንዲጠላ ማድረግ እና እንዲወገድ ማስቻል ነው፡፡ይህም ላለፉት ዓመታት የተሰራው ስራ በሚገባ ሰምሮ ከህወሓት አልፎ የህወሓት መሰረት ለነበረው የትግራይ ህዝብም ተርፋል፡፡

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ትልቁ ችግር ፤

ህወሓት የሚወቀስበት ብዙ ነገሮች እንዳለ ሆኖ የሚወደስበት ሌሎች ነገሮችም አሉት ፡ እርግጥ ነው ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሉም የኢህአደግ እናት ድርጅቶች በየክልላቸው ለተፈፀመው ኢሰብአዊ ጉዳት ተጠያቂ ሲሆኑ በፌደራል ደረጃ ለተፈጠሩ ችግሮች ደግሞ በጋራ ተጠያቂ ናቸው፡፡

ታድያ ለምን ህወሓት ለብቻው ተጠላ ለሚለው ጥያቄ ቀላል ነው መልሱ ፤

የመጀመሪያው ይዞት የነበረው ስልጣን ምናልባችም ተገቢ ነበር አልነበረም ለሚለው ጥያቄ ሌላ ራሱን የቻለ ማብራሪያ የሚያሰፈልገው ሲሆን እንዲሁ በደፈናው ግን አብዛህኛው የመከላከያ ዋና ዋና ቦታዎች በትግራይ ባለስልጣናት ቁጥጥር ስለ ነበር በቀላሉ ጥላ ሸት ለመቀባት አመቺ በመሆኑ፣የሚገርመው ግን ከፍተኛውን የሚኒስተር ቦታ የያዙት ደግሞ ኦሮሞ እና አማራ ነበር ፤ አሁንም ነው፡፡

ሁለተኛው የእውነት የተጎዱት እንደተጠበቀ ሆኖ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣ መሳሪያ አንስተው የምታገሉ የፖለቲካ አላማቸው በህወሓት ጥላቻ ላይ ተመሰረቱ ነገር ግን ህወሓትን እንደ ስትራቴጂ የጥላቻ ማዕከል አድርጎ የወሰዱበት ምንያት የእውነትም በደሉ ታይቷቸው ሆነ አልያም ለግል ጥቅማቸው ብቻ በፈለጉት ምክንያት ሆነ በህዝብ አለማ ስም ትግሉን የሚመሩ በሙሉ የፕሮፖጋዳቸው መነሻ እና መድረሻ ህወሓት ላይ በመሆኑ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ድርጅቱ በሌሎች ሰዎች የደረሰበት መጠላት ከእሱ አልፎ ወደ ህብረተሰቡ በመውረዱ በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ተወላጆች በተለያዩ ቦታዎች እየተፈናቀሉ እና ጥቃት እየደረሰባቸው ቢሆንም የመገለል ፖለቲካ ዕጣ ፋንታ የደረሰበት በህወሓት ምክንያት ምንም ትኩረት እየተሰጠው አይደለም፡፡

በበኩሌ አገራችን ኢትዮጵያ የሁሉም አገር እንደመሆኖ መጠን ባልጠበበ መሬት ምንም በማይከፈልበት ፍቅር አሁን ጊዜው የፍቅር ነው እና የሌላው ብሄር ተወላጅ ከምንም በላይ በፍቅር በመንከባከብ መያዝ ማቀፍ ነው እንጅ በማግለል ፣ በማፈናቀል ፣ በማጥቃት ምንም የሚተርፍ ነገር የለም፡፡

ከዚህ ቀደም ድሬ የፍቅር አገር ፣ አዋሳ፣ ናዝሬት ፣ ደብረ ዘይት ፣ ባህር ዳር ፣ መቀሌ ወዘተ የህዝቡ እና የሚድያው ወሬ የፍቅር ህዝብ ፍቅር አገር እንደነበር የቅርብ ትውስታ ነበር፤ አሁን ግን ተገልብጦ ቀርቶ የፍቅር ህዝብ እና አገር ብለን ልናወራ ተከባብረን ለመኖር በአንድ አንድ ቦታ አደጋች እየሆነ መጥታል፡፡

መሬቴ መሬትህ ወዘተ እተባለ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን የምንዘምር በዙ ሰዎች ከእንዲዚህ አይነት አስነዋሪ ድርጊት በፍጥነት ወጥተን ወደ ፍቅር መለወጥ አለብን፡፡

መንግስት በተለይም የሁኑ አዲሱ አመራር የአመራር ሆኔታ አሁንም በሌላ አንድ ብሄር በሚመስል መልኩ እየተተካ እየመጣ የሚመስል ነገር አለና መጠንቀቁ አይከፋም፡፡

እንግዲህ ከላይ ከዋና ዋናዎቹ ለዛሬ ሀሳቤን ላካፍልብት የወደድካቸው የጠቀስኩ ሲሆን በአብዛህኛው ሀገር ወደ ፊት እንዲቀጥል ሆነ እንዳይቀጥል ማድረግ የሚችሉ ነገሮች ናቸው፡፡

አገራችን ላይ ለሚነሱ ችግሮች በዋነኝነት መነሻቸው ሁለት ነገር ናቸው እነሱም

  የብሄር ጉዳይ እና

  የመሬት የባለቤትነት ጥያቄ ናቸው፡፡

የብሄር ጉዳይ

ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር ገኖ እና ጣራ ላይ በመውጣት ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ ገኖ እና ከብሮ ይገኛል፡፡እንግዲህ አንድ ህዝብ በብሄር ሲታቀፍ ጠናካራ ሆኖ ለመሄድ ካለው ፋይዳ በዘለለ ያለውን በህል እና ልማድ ለማስፋፋት ፣ ለመጠበቅ ይጠቅማል፡፡በእኔ አመለካከት የቀድሞ መንግስታት የሚመስላቸውን የቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች የጥንካራያቸው መሰረት ያድርጉ እንደነበር ታሪክ ያሳውቀናል፡፡

ታድያ ነገስታት በቋንቋ እና ባህል የሚመስላቸውን ህዝቦች አስከትለው መልካም ነገር ሰርተዋል በተቃራኒውም እንደዛ፡፡

በታሪክ መዛባት ይሁን እውነታው እርግጠኛ መሆን ቢያደግትም ቀደም ሲል የነበሩ ቁርሾዎች የተወሰነ ማህበረሰብ አነሳስቶ ታግለው እና ኣታግለው አሁን ለደረሰችው ኢትዮጵያ እንድናይ ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው የቀሩ ቁርሾዎችም ቢኖሩም፡፡

ስለዚህ ብሄር የጥንካሬ መገለጫ እየሆነ ሲመጣ የእኔ ብሄር የእኔ ዘር ወደ ሚል አመለካከት እየገነነ በመምጣቱ አሁን ብሄር ከሃይማኖት እና አገር በልጦ ኢትዮጵያዊ ውስጥ ነግሷል፡፡

አንድ ህዝብ በብሄር ማንነት ሲደራጅ የሚያየውም ፣ የሚመለከተውም ፣ የሚሰማውም እንዲሁም የሚወስነውም በብሄር መነፃር በመሆኑ ሲያዝንልህም እንደዘው በሙሉ ልብ ነው ሲጠላህም በጭካኔ ይሆናል፡፡

ከብሄር መገለጫዎች መካከል አንዱ እና ዋንኛው ቋንቋ ሲሆን ቋንቋ ለአድነት ሆነ ለመለያየት ከፍተኛ መሰረት አለው፡፡

እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ቋንቋዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡እነዚህ ቋንቋዎች ሁሉም ብሄርሰብ የራሱን ቋንቋ እንድያድግለት እና እንዲነገርለት ስለሚፈልግ ሁሉም ለዚህ ይታገላል፡፡

በመሰረቱ የአገሪቱ የስራ ቋንቋ ምንም እንኳን አማርኛ ቢሆንም የአገር ቋንቋ ግን ተብሎ አይጠራም፡፡ አሁን ቅኝታችን በብሄር በመሆኑ አንድ በሁሉም ዘንድ የሚነገር በቀላሉ ህዘብ ሊያውቀው የሚችል እናዳርግ ቢባል ሌላ ግጭት ያስነሳል፡፡በሀገራዊ ፋይዳው እንደ ኢትዮጵያ ማሰብ ከተቻለ እንዲሁም ቋንቋ በመሰረቱ ለመግባቢያ ነው የተፈጠረው በሚለው አመለካከት ብንቃኝ ንሮ አንድ ቋንቋ የሚያግባባ መምረጥ ያን ያክል አይከብድም ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን የስራ ቋንቋ ብዙ ህዝብ ተናጋራ ባለው ሳይሆን የሚመረጠው በብዙ አከባቢ ተናጋሪ ባለው እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ምክንያቱም የቻይና ቋንቋ ከአለም ህዝብ በህዝብ ከፍተኛ ተናጋሪ ያለው ቢሆንም እንደ ኢንግሊዘኛ ግን አለመን አይሸፍንም፡፡በዚህም ምክንያት በቀላሉ የአለም ቋንቋ ሊሆን አልቻለም፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ ወስጥ ኢትዮጵያውነት ማስቀደም ካለብን አንድ የስራ ሆነ አገራዊ ቋንቋ ይዘን መሄድ አለብን ነገር ግን በብሄር ወይም በዘረኝነት የታጠርን ከሆነ ግን አገሪቷ በቋንቋ ምክንያት ሰላሟን ከምታጣ ሌላ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ቢጨመር ያው የህልውና ጉዳይ ስለሆነ እደግፋለሁ፡፡

ታድያ ሁለተኛ የስራ ቋንቋ ሲጨመር ሌላው በተነፃፃሪ የተናጋሪ ብዛት ያላቸው ብሄሮች የእኛም ቋንቋ የስራ ቋንቋ ይሁን ማለታቸው ስለማየቀር እሱንም የሚያስተናግድ የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀት አለበት፡፡

የመሬት ባለቤትነት፡

የመሬት ጉዳይ እዚህ አገር ህዝቦችን እያባላ፣ እያፈናቀለ እና ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ ዋንኛው ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ስለ መሬት ባለቤትነት ሲነሳ ቀደም ሲል የነገሱ ነገስታት የአገሪቱ ወይም በግዛታቸው የሚገኘው መሬት ባለቤት ናቸው ፡፡ በሂደት በተለያዩ አስገዳጅ ሁኔታዎች የመሬት ባለቤትነት ከነገስታት የተረፈው ለመሳፍንታት እንዲሁም ከእነሱ የተረፈው የሽማምቶች እያለ በየደረጃው ይወርዳል፡፡

በሂደት መሬት የመንግስት ሆኖ ቢታወጅም በተጨባጭ መሬት በአሁኑ ጊዜ የብሄር ሆኗል፡፡

በሂደት መሬት የህዝብ ነው ቢባልም ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ መሬት የክልል ሆኗል፡፡

ስለዚህ በተጨባጭ መሬት የብሄር ከሆነ ግፋ ቢል መሬት የክልል ከሆነ ከብሄር ውጭ ወይም ከክልል ውጭ የሆነ ሰው የመኖር መብቱ በመሬት ባለቤቱ ፈቃድ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ የሰው መፈናቀል ዋንኛ ምክንያት ከሆኑት መካከል መሬት አንዱ ከሆነ ባለቤትነቱን ማስተካከል ይበጃል ማለት ነው፡፡

በእኔ አመለካከት የዚህ ነገር መፍትሄው የሚሆነው የአመለካከት ለውጥ ቢመጣና ሁሉም የአገሬ ዜጋ ተንቀሳቅሶ የፈለገበት ቢሰራ እና ይህ ቦታ የእኔ ነው የሚል ሽሚያ መግባት ባንችል አሁን ባለንብት የድህነት ሆኔታ አንፃር መሬት የመንግስት ቢሆን እና ቢቀጥል ደስ ባለኝ ፤ ነገር ግን በተጨባጭ ያለው በተቃራኒው በመሆኑ መሬት ባለቤትነት ወደ ግለሰብ መዞር አለበት፡፡መሬት የሚሸጥ የሚለወጥ ከሆነ ማንም ሰው በገዛው ዕቃ የመጣላት ሆኔታው ይቀንሳል እንዲሁም የክልሎች ጣልቃ ገብነት ይጠፋል ስለዚህ ይህን መንግስት ቢያጥነው መልካም ነው፡፡

በአጠቃላይ ከቀድሞ አመራሮች መልካሙን አስቀደመን ከፋቱን ማስተማሪያ አድርገን ቀጣያን ኢትዮጵያ የፍቅር አገር እንድናደርጋት የእውነት ከገባንበት ጠባብ አስተሳሰብ መውጣት አለብ፡፡

በእውነት በብሄር የሚደበቁ አክቲቭስቶች መምከር እና መገፀፅ አለብን፤

በእውነት ለውጡ" የሚባለው የአማርኛ ቃል እስካአሁን ለቆየንበት አመስግነን ለቀጣይ ግን ወደ መደበኛ ስራ እና ኢትዮጵያውነትን መሰረት አድርገን ወደ ምንሄድበት ቁልፍ ስራዎች መሄድ አለብን፡፡

ለአስተያየት mahteme100@gmail.com

 

Back to Front Page