Back to Front Page


Share This Article!
Share
ፌንጣ ቢቆጣ ክንፉን ጥሎ መጣ

ፌንጣ ቢቆጣ ክንፉን ጥሎ መጣ

ይቤ አብርሃ ከውቤ በረሃ 10-06-18

በአንድ የገጠር መንደር ውስጥ በምሽት እሳት ተነሳና የተወሰኑ ቤቶችን ማቀጣጠል ጀመረ ፡፡ በዚህም ምክንያት ነዋሪዎቹ (አርሶ አደር ይሁኑ አርብቶ አደር አላጠራሁም)ታወኩ፣ ኡኡታው ቀለጠ፣ተራወጡ በሀዘኔታ እንባ ተራጩ፡፡እሳቱ ተያይዞ ንብረቶቻቸውን፣ ከብቶቻቸውን፣ በጎተራ ያለ ምርታቸውንና ለአጨዳ የደረሰ ሰብላቸውን እንዳያወድምባቸው ስጋት ገባቸው፡፡

ከመኖሪያ ቤቶቹ በርቀት ላይ በሚገኝ ምንጭ የሚኖሩ እንቁራሪቶች እሳቱን በማየት ተነጋገሩ ፡፡ ከፊሎቹ በነበልባል እሳቱ ውብትና ድምቀት ሲስቅቁ ገሚሶቹ በሀዘንና በድንጋጤ ተውጠው ተሳቀቁ፡፡ከእንቁራሪቶቹ መካከል የተወሰኑት እሳቱን ለመሸሽ ከውሃ ምንጩ እንወጣልን ሲሉ እሳቱን ዐይተው ሲስቁ የነበሩት ደግሞ የበለጠ ሳቁባቸው። ፈሪዎች እያሉም አላገጡባቸው።ከምንጩ የሚወጡትን እንቁራሪቶች ለምንድነው የምትወጡት ብለው ጠየቋቸው። እነሱም እሳቱ እኛ ጋር ሊደርስ ይችላል ብለው መለሱላቸው። እነዚያም ውሃ ውስጥ እያለን እንዴት ነው እሳት እዚህ የሚመጣው?እሳቱ ቢመጣም እንኳ ውሃ ውስጥ ስላለን አንቃጠልም፤ እንደውም እሳቱ ምንጫችን ጋር ከደረሰ ይጠፋል ብለው ከምንጩ እንዳይወጡ መከሯቸው ።እንወጣለን ያሉት እንቁራሪቶች ግን እሳቱ ቢመጣም ባይመጣም ከምንጩ ወጥተን ዐለቶች ሥር ተሸሽገን የሚሆነውን እናያለን አሉ።

ቢሆንም ከምንጩ እንወጣለን ያሉት እንቁራሪቶች አንወጣም ያሉትን እንቁራሪቶች ምክንያት አጣጥለው ከምንጩ ወጡ።በጓደኞቻቸውም ፈሪዎች ቦቅቧቆች ተብለው ተዘለፉ።

Videos From Around The World

በመንደሩ የሚኖሩት ሰዎች እሳቱ እየባሰባቸው ስለሄደ ውሃ ፈልገው ወደ ምንጩ ግር ብለው መጥተው በጣሳ እየቀዱ በእንስራ እየሞሉ እሳቱን ለማጥፋት ውሃውን እየተቀባበሉ ወደ ተያያዙት ቤቶች መርጨት ጀመሩ።በዚህ መሃል ከምንጩ አንወጣም ያሉት እንቁራሪቶች በውሃ ቀጂዎቹ ከውሃ ጋር ተቀድተው የእሳት ራት ሆኑ። ከምንጩ ሸሽተው የነበሩት ግን ሕይወታቸውን አዳኑ።

ከላይ ያነሳነው ተረት አሁን በሀገራችን የምናየውን ሁከት የሚያስረዳ ምሳሌ ነው ማለት ይቻላል። በሀገራችን ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲታዩ የነበሩ ቀውሶችን ለማክሰም ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ በማድረግና ራሱን በማደስ አመርቂ የለውጥ ጅማሬዎችን አሳይቶናል። ነገር ግን በለውጡ የተናወጡና የተደናገጡ ግለሰቦች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ሁከት በመለኮስና በመቀስቀስ ወጣቱ በዘር ተኮር ግጭት ርስ በርስ እንዲጫረስና ደሙ እንዲፈስ እየጣሩ ነው ። በዚህም በየክልሎቹ ግጭቶች እየተቀሰቀሱ ሰዎች የዜግነት መብታቸው ተጥሶ ንብረታቸው ሲዘረፍ ሕይወታቸውን ሲያልፍ እና ራሳቸውን ለማትረፍ ሲሰደዱ ዐይተናል። በዚህም ነውጥ እናቶችና ሕፃናት ፣ ነፍሰጡሮችና አዛውንቶች የችግሩ ተጠቂዎች ሆነዋል።

ግጭቶቹ በየቦታው እየተነሱ መሆኑ እሙን ነው። በዙር ወይም በተራ በሚመስል ሁኔታ እየተነሳ ያለው ሁከት እዚህ ግባ የሚል ምክንያት የሌለውና ችግሩ ዘር ተኮር መሆኑ ነው። የዛሬ መቶ ዓመት ቅድመ አያቴ አጠፉት ለተባለ ጥፋት እኔ መቀጣት የለብኝም።የተወለድኩበት ብሔር ተፈጥሮ የለገሰቺኝ እንጂ መርጬ ያገኘሁት አይደለም። ሁከቶቹ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ብርና ጦር እየሰጡ በወጣቱ ግጭትና ሕልፈት መደሰት የሚፈልጉ የሚተውኑበት ነው ማለት ይቻላል።ይህም በኢፌዴሪ ሕገ በመንግሥት የተደነገገውን ዜጎች ቤተሰብ የመመሥረት፣ ንብረት የማፍራት መብት የሚጥስ ነው ያላቸውን እኩልነትም የሚደመስስ ነው።ከግጭቱ እናተርፋለን የሚሉ አካላት ፌንጣ ቢቆጣ ክንፉን ጥሎ መጣ እንዲሉ ትርፋቸው ኪሳራና ተቀባይነት ማጣት ነው።

በነዚህ ሁከቶች የሚያዝኑ፣ የሚያለቅሱና የሚሳቀቁ የመኖራቸውን ያህል የሚደሰቱና የሚስቁም ይገኛሉ።ከላይ እንዳነሳነው ተረት እነሱም የዘረኝነት እሳት እንዳይፈጃቸውና እንዳያጠፋቸው ሊጠነቀቁ ይገባል።የጨው ገደል ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅሳል እንደሚባለው የሀገራችን ብሂል እነሱም ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች የመፍትሄ አካል ሆነው መገኘትና መታየት አለባቸው እንጂ ለውጡን ለመቀለበስ ከሚጥሩ ጎን መቆም የለባቸውም። ዜጎች ለግጭቶቹ ከፀጥታ አካላት ጎን ቆመው መላ ካልዘየዱ እነሱም ጋር እሳቱ መድረሱና የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው የማይቀር ነውና።በሻሸመኔ ከተማ በአንድ ግለሰብ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ወጣቶች ተሰብስበው ሲመለከቱ እንደነበረው እኛም ችግሮች ሲፈጠሩ በማህበራዊ ሚዲያ በማራገብ ችግሩን በመመልከት ከመመከት ይልቅ እሳት እየለኮስንና እያባባስን ነው።

የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ዜጎች እንዲሁም ወላጆች ወጣቶችን አንተም ተው አንተም ተው ማለት አለባቸው። ወጣት የነብር ጣት የሚባለውን ብሂል የነብር ጣት መሆናችንን ሁከት ከመፍጠር ይልቅ ሥራ በመፍጠር ብናውለው መልካም ነው።መገናኛ ብዙሃንም ከመዝናኛቸው እና መናኛ ፕሮግራማቸው ባለፈ ችግሩን ሊፈቱ የሚችሉ ህዝብን ከማቃቃር ወደ መፋቀር የሚያሸጋግሩ በተለያዩ ቋንቋዎች በአየር ሰዐታቸው በማሰራጨት የመፍትሔው አካል መሆን አለባቸው። ፕሮግራማቸውን ሊያሠራጩ የሚችሉት ተደማጭነትም የሚያገኙት ሀገር ሰላም ስትሆንና ስትረጋጋ ነውና።

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበልና በማስጠለል ከጥንት ጀምሮ የተመሰከረላት ኩሩ ሀገር ነች።አይሁዳውያን ከሀገራቸው ሲሰደዱ ለመጀመሪያ ጊዜ መጠለያና መጠጊያ በመሆን ሸሽጋለች፣በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ከኬልቄዶን ጉባዔ በኋላ ወደ ሀገራችን የተሰደዱት የክርስትና አባቶችም ተሸሽገውባታል። ከእነዚህም መካከል ዘጠኙ ቅዱሳን በሀገራችን ኖረው ሲያርፉ (አባ ጴንጤሎዎን አባ አረጋዊ የመሳሰሉት) በትግራይ በስማቸው ገዳማት ተገድሟል።የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በቁረይሾች ጥቃት ሲደርስባቸው በነቢዩ መሐመድ ፍትሕ ወደ አለባት ሀገር ኢትዮጵያ ሂዱ ብለው ሸኝተዋቸዋል።

ዛሬ ግን ዜጎች በመንደር ማለትም በወንዝና በጅረት እየተሠፈረ፣ በዘር ማለትም አጥንትና ጅማት እየተቆጠረ እትብታቸው በተቀበረበት ሀገር የሚቀበሩበት ቦታ እየተከለከለ እየተገደሉና እየተሰደዱ ይገኛሉ። ቀደም ሲል በሶማሌ፣በድሬዳዋና በአዲስ አበባ የታየው ግርግር ሰሞኑን ደግሞ በቤንሻንጉል ካማሼ ዞንና በደቡብ ክልል ካፋና ሸካ ዞኖች ያጋጠመውን የዜጎች መፈናቀል በጋምቤላም እያየነው ነው።አዝማማያውን ስናየው ችግሩ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም የሚደርስ ይመስላል።የመከላከያና የፀጥታ አካላት የለውጥ ሂደቱን ለመቀልበስ፤ ኢፍትሐዊነትን እና ሥርዓተ አልበኝነትን ለማንገሥ የሚፍጨረጨሩትን መቆጣጠር ይጠበቅባቸዋል። ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ከመድረስ የችግሮቹን አዝማሚያዎች በመቃኘትና በመገመት ግርግርና ሁከትን መመከት፤ የዜጎችን ሕይወት ከስጋት መታደግ አለባቸው።በየቦታው እየተፈጠረ ላለው ሁከት ምላሽ ለመስጠት አንድ ጥይት በቂ ነው።ነገር ግን መንግሥት ትዕግስት ያሳየው ፈርቶ አይደለም።ሁከት ሊያስነሳ የሚችል አሳማኝ ምክንያት የለም።ጥያቄዎችን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቀን መብታችንን መጠየቅ እንችላለን።መብታችንን ለማስከበር የዜጎችን መብት መርገጥ የለብንም ።

ለውጡን ተከትሎ መንግሥት በወሰደው ርምጃ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያስችሉ ዐውዶችን ፈጥሯል።በዚህም ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል።ከነዚህ አንዱ ኢህአፓ አመራሮች ሲገቡ በቀይ ሽብር መታሰቢያ ቤተመዘክር ተገኝተው ለሞቱ ዜጎች የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።ከዚሁ ጎን ለጎን እነርሱ በነጭ ሽብር ስም ስላጠፉት ሕይወት የተነፈሱት ነገር አልነበረም።ዘጋቢዎችም ይሄን መጠየቅ አልቻሉም።እነርሱ ከሰለጠነ ሀገር መጥተው ለቀይሽብር ሰማዕታት ሀዘናቸውን ሲያሳዩ በነጭ ሽብር ስለሞቱት ደግሞ ይቅርታ መጠየቅ ነበረባቸው።በመደብ ግጭት ያፈሰሱት የሰው ደም እንጂ የበግ ደም አይደለም ።ዴሞክራሲ የሚጀምረው ከዚህ ነው ማለት እችላለሁ።

የኦነግ ሠራዊት አባላት ከነ ትጥቃቸው በትግራይ በኩል ሲገቡ በነዋሪዎች አቀባበል ተደርጎላቸዋል።የሠራዊቱ አባላት ከነትጥቃቸው ሲገቡ የተወሰነ ማረፊያ መንግሥት አመቻችቶ፣ ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ ሰጥቶ፣ ችግር እንዳይፈጥሩ አረጋግቶ ማሰናበት ተገቢ ነበር።በአንዳንድ አካባቢዎች ለተፈጠሩ ሁከቶች የኦነግ ሠራዊት እጅ ነበረበት ከተባለ ሲገቡ መሣሪያቸውን ለሁከት እንዳየጠቀሙበት መደረግ ነበረበት።በኦነግ ስም ያለግንባሩ እውቅና ዝርፊያና ህገ ወጥ ተግባራት ተከናወኗል። በቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ካሉም እልባት መስጠት ያስፈልጋል።

ከብቶች እንኳ ካደሩበት በረት ጠዋት ለግጦሽ ሲሰማሩ እንዲሁ አይለቀቁም።ቢለቀቁ ደግሞ ለአጨዳ የደረሱ ሰብሎችን ያወድማሉ፣ የሰው ማሳ ይግጣሉ ፤ስለዚህ አብሯቸው እረኛ እንዲሰማራ ይደረጋል።እረኛው ከብቶቹን በለመለመ መስክ ያሰማራቸዋል፣ወደ ምንጭ ውሃ ይወስዳቸዋል።ስለዚህ ከአውሬዎች ጥቃት ይጠብቃቸዋል፣የሰው ማሳና ሰብል እንዳይነኩ ይከላከላቸዋል።የኦነግ ሠራዊት አባላት ሀገር ቤት ሲገቡ ትጥቃቸውን ማስረከብ አልያም የሚኖሩባቸውን አድራሻ ማስመዝገብ በመንግሥትና በፀጥታ አባላት በኩል አደጋ እንዳይደርስ መቆጣጠር ግዴታ ነው።በቤንሻንጉል በደረሱት ግጭቶች የኦነግ ታጣቂዎች አሉበት መባሉ በራሱ ያሳዝናል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰሞኑን በሠጡት መግለጫ ባለፉት ሦስት ዓመታት በነበረው ሁከትና ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቄያቸው መፈናቀላቸውንና ያፈሩትን ንብረት ማጣታቸውን በምርመራ ማረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡ውጤቱን ለሚመለከተው አካል ይፋ በማድረግ ተጠያቂ ያደረጋቸው አካላት መኖራቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ለውጡን ተከትሎበአካባቢዎች አለመረጋጋት ምክንያት የዜጎች በነፃነት የመዘዋወር፣ንብረት የማፍራትና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እየተሸረሸሩ በመሆናቸው መንግሥት በፍጥነት ሊያስቆመው ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ ሳምንታት ዩኒቨርሲቲዎች የሚከፈቱበት ጊዜ በመሆኑ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ጥረት መደረግ አለበት።የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር ዐብይ አህመድ በሐዋሳ ከተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛው ጉባዔ ጎን ለጎን በየዩኒቨርሲቲ ትምህርት ፍጹም ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን በሚቻልበት ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንቶች እና ከክልል አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።በዚህ ወቅት የትምህርት ዘመኑ ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን የተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ የትምህርት ማኅበረሰብ አባላት፣የክልል አመራሮችና የፀጥታ አካላት ሓላፊነት እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ከመስከረም 23 እስከ 26 በሐዋሳ የተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ከላይ ያነሳናቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።በዚህም የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የማንነት ጥያቄዎችም በሕግ አግባብ እንዲፈቱ ማድረግ፤የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጠናከር ፣የተሃድሶ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ማስቀጠልና ሀገራዊ ለውጡን ወደፊት ማስኬድ መቻል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 

 

 

Back to Front Page