Back to Front Page


Share This Article!
Share
በሸለላና ቀረርቶ የሚፈርስ አገር ፣የሚበተን ህዝብ የለም ።

በሸለላና ቀረርቶ የሚፈርስ አገር ፣የሚበተን ህዝብ የለም ።

አርታኢ ፣ ልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ )

ቀን ፣ ህዳር 20/2011.

 

ኢትዮጵያዊያን ብዙ የጋራ መልካም አብነቶች እንዳሉን ሁሉ የጋራ ችግሮችም አሉን ።በመልካምነት ከሚታወቁ አብነቶች አንዱና ዋናው ተመሳሳይ ባህልና የብሔር ብዙሃነት ሲሆን አብይ ችግራችን ደግሞ የመቻቻልና የሀሳብ ልህቀት አድማሳችን ሰንካሎት የበዛበት ነው ። ኢትዮጵያ ያላት የሰው ፀጋ ፣የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የሀብት ምንጮች በሚገባ መጠቀም ላይ ያሉት ክፍተቶች (Gaps of unutilizedSocial Capital )አያሌ ናቸው ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የሁሉም መሳሪያና ማሳለጫ የሆነው የፖለቲካ ጥበብ(Art of Politics ) ቁልቁል እንጂ ሸቅብ የማይራመድ በመሆኑ ኢትዮጵያና ህዝቧ አድሮ ጥጃ ሆነዋል ። የኢትዮጵያ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ብስለት ብቻ ሳይሆን ቅንነትም (Honesty ) የተላበሱ አይደሉም ። በኢትዮጵያ የተለመደ የፖለቲካ አሰራር በተንኮልና መጠላለፍ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ለአገር እድገትና ለዲሞክራሲ ግንባታ ችግር ሆኖ ብዙ ዘመናት ዘልቀዋል ።ይህ ጥራት የጎደለው የፖለቲካ አሰተዳደርና አሰተሳሰብ ዘመን ተሻጋሪ ብሔራዊ ችግሮች ማስከተሉ አልቀረም ።

የፖለቲካ አሻጥር የደንቆሮዎች አሰተሳሰብ ከመሆኑም በላይ የአንድ አገር ህዝብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሴቶች ያናጋል ። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ዲሞክራሲ የራቃቸው አገሮች በተዛባ ፖለቲካ የመበታተን አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል ። በዲሞክራሲ ተግባራዊ መርህ ላይ ያልተከሸነ ፖለቲካ ፈፅሞ ለህዝብ አይጠቅምም ። በተመሳሳይም በብሄር ላይ የተቃኘ የፖለቲካ መሰመር የህዝብ ጠንቅ ነው ። ለማንም አይበጅም ። በተመሳሳይም ህዝብ የማይቆጣጠረው የፖለቲካ አሰተዳደር ለአገር እድገት ነቀርሳ ነው ። በኢትዮጵያ ህዝብ የሚቆጣጠረው እንዲሁም ለህዝብ ጥቅም የተመሰረተ የፖለቲካ አሰተዳደር የለውም ብሎ አፍ ሞልቶ መተቸት ይቻላል ። ብዙ ተሰፋ የተቻረው የኢህአዴግ ፖለቲካ አሰተዳደርም አምዱ ነቅዘዋል፣ ፖለቲካዊ መስመሩ አደጋ ላይ ወድቋል ።

Videos From Around The World

በኢህአዴግ ሰርአት የተወለደው የብሔር ፖለቲካ ሙሉ ለሙሉ የችግሮች ምንጭ ተደርጎ ባይወሰድም ያስከተለው ማህበራዊ መዛባት ግን ከፍተኛ ነው ። ተጠራጣሪና ብሔር ተኮር ማህበረሰብ እንዲፈጠር የኢህአዴግ መር ስርአት አሰተዋጽኦ አድርጓል ። ብሔር ተኮር ሰርአት ደግሞ ዘላቂነት እንደሌለው በተግባር ታይተዋል። ስርአቱ እየተፍረከረከ በሂደት ወደ ሸለላና ቀረርቶ መሄዱ እንደማይቀር ሁኔታዎች ይጠቁማሉ ። ለአብነት ፣- የአማራ ክልልና የትግራይ ክልል የፖለቲካ መሪዎች በየቅያቸወ ዘራፍ እያሉ ይገኛሉ ። ይህ በጣም የሚያስገርም እንዲሁም የሚበሳጭ የቁልቁለት ፖለቲካ መዘዝ አጥቢ ላይ ናቸው ። የሚያወጧቸው የድርጅት ጋሬጣዎች እጅጉን የወረዱ ናቸው ። በአንድ አገር የሚኖሩ መሪዎች አይመስሉም ። መሪ የመሆን ብቃቱ ያላቸውም አይመስልም ። በጥቅሉ የሁለቱ ክልል መሪዎች በመንግሥት ሀላፊነት የመጠየቅ አዝማሚያዎች ይታያሉ ። ለችግሮች በመወያየትና መነጋገር መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ በሸለላና ህዝባዊ ሰልፎች ክልላቸው ያስተዳድራሉ ።

የአማራም ሆነ የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ክልሎች ናቸው ። ክልል መሪዎችም ኢትዮጵያዊያን ናቸው ። ታድያ የሚያጋጫቸው ምንድን ነው ? መቸም የሚፋጠጡበት ችግር የህዝብ ጥቅም እንዳልሆነ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው ።ህዝብ ለህዝብ ምንም የሚቃቅር ክስተት የተለመደ አይደለም ። የትግራይ ተወላጆች በአማራ ክልል የመኖር መብት ለምን ይነፈጋል? ለምን ክልሉን እንዲለቁ ይገደዳሉ ? ክልሉ እንዲለቁ የሚደረጉበት ምክንያትስ ምንድነው ?የክልሉ መስተዳድር ለዜጎች መፈናቀል በህግ ተጠያቂ አይደለም ወይ?።የሁለቱ ክልል ህዝቦች መሐል የጠነከረ ዝምድና ካልሆነ ሌላ በጋህድ የሚታወቅ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም ። የሁለቱም ክልል መስተዳድሮች ከህዝብ ፍላጎት ውጭ ክልላዊ አሰተዳደር እየመሩ መሆናቸው በቅጡ የሚያውቁት አይመስልም ። በሁለቱም ክልል የሚነሱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች እንጂ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች አይደሉም ። ህዝቡ የሰላምና መረጋጋት ጠየቀ እንጂ አማራ ወይም ትግራይ አይደለሁም አላለም ። በኢትዮጵያ የክልል አስተዳደሮች ለሚነሱ ሁለ ገብ የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ የሚገነዘብና መልስ የሚሰጥ አሰተዳደር ያስፈልግ ነበር ። ክልል መሪዎች ችግር ፈጣሪ እንጂ ችግር ፈቺ እንዳልሆኑ በተጨባጭ ታይተዋል።

በትግራይ ክልል የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በክልሉ የመኖር መብት እንዳላቸው ታውቆ እንደክልሉ ነዋሪ እንጂ እንደመጤ መታየት አይኖርባቸውም ። የትግራይ አስተዳደራዊ ክልል ክልላቸውና አገራቸው ነው ። አማራ ከትግራይ ፣ትግራይ ከአማራ ክልል እንዲፈናቀል አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው ? ህዝቡ ለምን የፖለቲካ ቁማር ሳጥን ውስጥ ይጨመራል ?። ለህዝብና አገር ልዕልና ቁመናል የሚሉ የፖለቲካ መሪዎች አስተዳደራዊ ስህተት ሊፈፅሙ ይችል ይሆናል እንጂ እንዴት በህዝብ ላይ አሳፋሪና ኢ ህገ መንግሰታዊ ስህተቶች በፖለቲካ መሪዎች ሊፈፀም ይችላል ? ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች በፀጥታ ምክንያት ከአማራ ክልል ሲፈናቀሉ አንድም የክልሉ ሀላፊ ተጠያቂ አለመደረጉ በእጅጉ ያሳዝናል ። በተመሳሳይ ከደቡብ የኢትዮጵያ ክልል የአማራ ተወላጆች በግፍ ሲፈናቀሉ አንድም የክልሉ ሀላፊ ተጠያቂ አልሆነም። ይህም አሳዛኝ ክሰተት ነው ።

በኢህአዴግ ሰርአት ሰር ተጣምሮ የቆዩ ሁለቱ የሰሜን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ማለትም የአሁኑ አዴፖና ሕ.ወ.ሓ.ት በትብብር ወዳጅነት ረዘም ላሉ አመታት በአጋርነት ሰርተዋል እንዲሁም ሀብት መዝብረዋል ፣ዘርፈዋል ፣ ሁለቱም በሙስና ሳሙና ታጥበዋል። ጥረትና ኤፈርት በመባል የሚታወቁ የንግድ ደርጅቶች አሏቸው ። ዘናጭ ሀብታም የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው ። ሕ.ወ.ሓ.ት. አዴፖ የሚያስተዳድረው ጥረት የንግድ ደርጅት ማቋቋሚያ ገንዘብ የለገሰ የዋህ ድርጅት ነው ። ሁለት ሌቦች ሲካፈሉ እንጂ ሲሰርቁ አይጣሉም እንደሚባለው ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እነኝህ ነባር የፖለቲካ ድርጅቶች ሰጣ ገባ ላይ ናቸው ። የየክልላቸው ህዝብም የፖለቲካ አጋፋሪ እንዲሆን የድጋፍና የተቃውሞ ትዕይንቶች ሲፈፀሙ ማየት አስደሳች አይደለም ። የሁለቱም ክልል ህዝብ አስተዳዳሪ መረጃዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ በሀላፊነት መርህ ላይ የተመሰረተ አመራር መሰጠት በቀጠሮ የሚቆይ ጉዳይ አይደለም ። ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ መምከርና መወያየት ጠቃሚነቱ የጎላ ከመሆኑም በላይ የህዝብ ለህዝብ ሰላማዊና ማህበራዊ ትስስር ያሰፍናል ።

በኢትዮጵያ እንደባህል እየተወሰደ የመጣ ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች በአግባቡ ያለመተግበር ችግር ለፖለቲካ መሪዎች ዋልጌነት መሠረት ሆነዋል ። ኢህአዴግ ራሱ ያፀደቀው ህገ መንግስት በተደጋጋሚ ህገ መንግሰታዊ ጥሰቶች ሲፈጸም ነበር ። ለምሳሌ ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች በመረጡት ቦታ የመኖር ህገ መንግሰታዊ መብታቸው ሆኖ ሳለ ግልፃዊ ግፍና መፈናቀል ሲፈፀምባቸው ህዝብ የሚመራ ኢህአዴግ መር መንግስት ፋይዳ ያለው የማስተካከያና የእርምት እርምጃዎች አልወሰደም ። አሁንም ቢሆን ቀኑ ሳይመሸ ንፁሃን ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሲያፈናቅሉ ፣ ንብረት ሲዘርፉ ፣ ሲገድሉ የነበሩ የመንግስት ሀላፊዎች ለፍትህ መቅረብ ይኖርባቸዋል ።የዜጎች ህገ መንግሰታዊ መብት ሲጣስ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቁጥር አንድ በሀላፊነት መጠየቅ ይኖርበታል ። የአገርን የህዝብ ሀብት በመንግሥት ሹማምንቶች ሲባክንና ሲመዘበር ፣ የዜጎች ህገ መንግሰታዊ መብቶች ሲጣሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያውቁም ነበር ማለት የሚያሳምን ጉዳይ ፈፅሞ ሊሆን አይችልም ።

በኢትዮጵያ እርቀ ሰላም እንዲሰፍን የተጎዱ ዜጎች ሲካሱ ፣ በደል የፈፀሙ የመንግስት ሀላፊዎች በፍርድ ሲጠየቁ ፣ የፍትህ ልዕልና ሲከበር ብቻ ነው ። በመቋቋም ላይ የሚገኘው የሰላምና እርቅ ኮሚሽን አንዱ የሥራ ተግባርም ይሆናል ብየ እገምታለሁ ።አሳዛኝ ድርጊቶች በመንግሥት ሀላፊዎች ሲፈፀሙ በመቆየታቸው የሰላምና እርቅ ኮሚሽን በርካታ ውስብስብ ችግሮች እንደሚያጋጥሙት የሚጠበቅ ቢሆንም ፍትሀዊነትና ሚዛናዊነት የጠበቀ ተግባር እንደሚያከናውን የብዙዎች ፍላጎት ነው ።በአግባቡ ባልተፈተሸ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሰርአት ሲላሸቅና ሲጋጭ የቆየ የኢትዮጵያ ህዝብ በእርቀ ሰላሙ መንፈስ ዳግም ይፈወሳል የሚል እምነት አለኝ ። የኢትዮጵያ ዜጎች በአገራቸው በሰላምና በመተሳሰብ ለመኖር የሚያስችል ዲሞክራሲያዊ ሰርአት ይገባል የሚል እምነት አለኝ ። በኢትዮጵያ ሰርቶ እንጂ ሰርቆ ለመኖር የማያስችል ስርአት ይገነባል የሚል የፀና እምነት አለኝ ። በኢትዮጵያ ህዝብ አገልጋይ መንግስት ይኖራል የሚል አብይ ተሰፋ አለኝ ።

በኢትዮጵያ ሲነሱ ለቆዩት ሰብአዊና ማህበራዊ እንዲሁም የዲሞክራሲ ጋሬጣዎችየኢህአዴግ ያህል ችግር ባይፈፅሙም ለኢትዮጵያ ችግር ሆኖ ቆይተዋል ። ሰማንያ ቦታ ተበጣጥሶ በየጉራንጉሩ የተቋዋሚ ስያሜ አንግቦ ፣ በእርባና ቢሰነት ፍሸካ ሲነፉ ነበር ። አንዳንዶቹ ደግሞ አገር በመበተን ተግባር ላይ ነበሩ ። አንዳንዶቹ ደግሞ በኢህአዴግ ሳንባ ሲተነፍሱ ቆይተዋል። በጣት የሚገመቱ ግን የኢህአዴግ ሰርአት በፅናት ሲፋለሙ ነበሩ ። በኢትዮጵያ ሰላማዊ የመንግሥት የስልጣን ሽግግር እንዳይኖር በኢትዮጵያ የመንግስት ተቋዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰላምና ዲሞክራሲ እንቅፋት ሆኖ ዘልቀዋል ። በመሆኑም በኢትዮጵያ ለተፈፀሙት የወንጀልም ሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከተጠያቂነት ውጭ አይሆኑም ።ምክንያቱም በቀጥታም ሆነ በሌላ መንግስት ሲፈፅማቸው ለቆየው ወንጀሎችና የህዝብ ሀብት ምዝበራዎች ተባባሪ ነበሩ ። የተቋዋሚ የፖለቲካ ደርጅቶች ብዛት ለኢህአዴግ መር መንግስት አብይ መሳሪያ ሆኖ ለ30 አመታት ቆይተዋል። ፈርጣማ ተቋዋሚ ድርጅት በኢትዮጵያ እንዳይኖር የኢህአዴግ ስርአት በርከት ያሉ ፖለቲካዊ አሻጥሮች (Political Conspiracies )ሲያከናውን ኖሯል ።

ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀው የሚሸልልና የሚያቅራራ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን የሰከነና የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁለንታዊ ጥቅሞች ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን የግድ ነው ። ለኢትዮጵያ ሰማንያ የፖለቲካ ድርጅት አያስፈልጋትም ። ለኢትዮጵያ ህገመንግስት የሚጥስ ሰርአት አያስፈልጋትም ። ለኢትዮጵያ ጎራ ለይቶ የሚሸልል ሰላም አደፍራሽ የፖለቲካ ድርጅት አያስፈልጋትም ። ለኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ሁለንተናዊ መብት የማያስከብር ሰርአት አያስፈልጋትም ። ለኢትዮጵያ አንድነት እንቅፋት የሚሆን ሰርአት ፈፅሞ አይመጥናትም። ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ንግድ የሚያፋፍም የኮንትሮባንድ ሰርአት ፈፅሞ አያስፈልጋትም ።

እንደ እኔ እምነት በአማራና ትግራይ ክልሎች ያለው ውጥረት እርባናየለሽ ክልላዊ የማናናቅ ፖለቲካዊ ቅሌት እንጂ ህዝባዊ መሠረት የለውም ። በመሆኑም የሁለቱም ክልል ፖለቲከኞች አርቆ ማሰበን መለማመድ ይኖርባቸዋል ። ህዝብ አስተዳዳሪዎች በመሆናቸው ድርብ ድርብርብ ሀላፊነት እንደተሸከሙ በሰከነ ዲሞክራሲያዊ አሰተሳሰብ ራሳቸው መገምገም ይኖርባቸዋል ። የፖለቲካ ልዩነት ችግር የህዝብ ችግር አድርጎ ማቅረብ ወንጀል መሆኑን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል ። የህዝቦች መፃኢ ተስፋና ሰላም ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል ።ህዝብ ከህዝብ ጋር ሁለንተናዊ ትስስሮች የሚሸረሽሩ ፖለቲካዊ ሴራዎች ከመፈጸም መቆጠብ ይኖርባቸዋል ።የህዝብ ለህዝብ የትስስር ምግባሮች ተግባራዊ ቢሆኑ ተመራጭ ነው እላለሁ ። የንግድ መሰመር መገናኛ መንገዶች መዝጋት ሀላፊነት የጎደላቸው መሪዎች ተግባር ነው ። በዚህም ብልሹ አመራር የህዝብ ጉዳት ጊዜያዊ ቢሆንም ለፖለቲከኞች ግን የዘላለም የሞራል ስብራት ሆኖ ይኖራል ። ህዝቦች ምንጊዜም ቢሆን አይለያዩም ። ህዝብ የፖለቲከኞች ሸቀጥ ማራገፊያ ወደብ ፈፅሞ ሊሆን አይችልም ።

 

 

Back to Front Page