Back to Front Page


Share This Article!
Share
አንዴ ሳያይ ሌላ ጊዜ ሲያሳይ

አንዴ ሳያይ ሌላ ጊዜ ሲያሳይ

ወንድይራድ ኃብተየስ 06-27-18

አዲሱ መንግስት ህዝቦችን ለማቀራረብ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከላይ ታች ሲል እየተመለከትን ነው። አንድ እንጨት አይነድም አንድ ሰው አይፈርድም እንደሚባለው አንድ ሺህ ችግር ያለባትን አገር ለአንድ ሰው አሸክመን መፍትሄ መጠበቅ የዋህነት ነው። ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጊጤ እንዲሉ ሁላችንም የሚገባንን ማድረግ ከቻልን አገራችንን ወደተሻለ ደረጃ እንደምናሳድጋት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። አገራችን የፌዴራል ስርዓት ተከታይ አገር ናት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ይህ ስርዓት አጠቃላይ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ትልልቅ ግጭቶችን ያስወግዳለ እንጂ ትናንሽ ችግሮችን ሁሉ ያስወግዳል ማለት እንዳልሆነ ከግንዛቤ ሊገባ ይገባል። በርካታ ልዩነቶች ለሚስተዋሉባት አገራችን የፌዴራል ስርዓት ከአህዳዊ ስርዓት እጅጉን የተሻለ መሆኑን በተግባር ማየት ይቻላል። ባለፉት 27 ዓመታት በፌዴራል ስርዓት በርካት ስኬቶችን እንዳገኘን ሁሉ አንዳንድ ያስተዋልናቸውም ክፍተቶች እንዳሉ አምኖ መቀበል በቀጣይ ስህተት እንዳንሰራ የሚያድነን ነው። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ልዩነት እጅጉን ተሰብኳል፤ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ መንግስት ህዝቦችን ሊያቀራርብ የሚችሉ አንድነቶችን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ድልድዮችን ከመስራት ይልቅ ልዩነቶችን የሚያጎሉ ግድግዳዎችን ሲገነባ ቆይቷል።

እንደእኔ እነደኔ መንግስት በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ አካሄድን ባለመከተሉ በህዝቦች የተሳሳተ አስተሳሰብ አንተ ከእኔ ነህ አንተ ደግሞ ከእኔ አይደለህም፣ ውጣልኝ፣ ሂድልኝ የሚል እጅግ ጽንፍ የወጣ የተሳሳተ እንዲፈጠር አድርጓል። ይህን አይነት አስተሳሰብ የፌዴራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ በደንብ አለመገንዘብ እንጂ የስርዓቱ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። አንዳንዶች አገራችን በቅርቡ ገጥሟት የነበረው ችግርን ከፌዴራል ስርዓቱ ጋር ለማያያዝ እና ይህ የአስተዳደር ዘይቤ መለወጥ አለበትየሚል የግል አስተሳሰባቸውን ሲያራምዱ ይስተዋላሉ።

Videos From Around The World

በዕውኑ የአገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አወቃቀር ለቀውስ ዳርጓታል ስል ሁሌም ራሴን እጠይቃለሁ? ነገሮችንም በጥሞና ለመመርመር ጥረት አደርጋለሁ። እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የአገራችን ስኬቶች ሁሉ መሰረታቸቸው የፌዴራሉ ስርዓት ነው፤ ይህ ሲባል ግን ይህ ያልተማከለ ስርዓት ምንም ችግር የለበትም ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅልኝ ይገባል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የፌዴራል ስርዓት ትላልቅ ችግሮችን ይፈታል እንጂ ትንንሽ ችግሮች እዚህም እዚያም መኖራቸው መቼም አይቀርም። እነዚህ ሊወገዱ የሚችሉት የዴሞክራሲ ስርዓታችንን ስናጎለብተው ብቻ ነው። አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የፈጠረው ትናንሽ የመንደር ጥቅመኛ የሚያደርገው አምባጓሮ ሁሉ ከፌዴራል ስርዓቱ ጋር ማገናኘት ተገቢ አይደለም።

እንደእኔ እንደኔ የአገራችን የፌዴራል ስርዓት የታሰበለትን ግብ መቷል ባይ ነኝ። ይህ ስርዓት የአገሪቱን ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ቢያንስ ሁለት መሰረታዊ ችግሮችን መቅረፍ ችሏል። የመጀመሪያው ለዘመናት የአገራችን ችግር ሆኖ የኖረውን የፖለቲካ ችግር ማለትም የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነት ጥያቄዎች፣ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋነቋንና ባህልን የመጠቀምና የማሳደግ መብትን መመለስ አስችሏል። ይህ በተጨባጭ የተረጋገጠ እውነታ ነው። ዛሬ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማነነታቸው እንዲኮሩ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል ስርዓቱም ከሌሎች ጋር እኩል መወሰን እንዲችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል። ሌላው ደግሞ የአገሪቱ የልማት ፍላጎት መመለስ የሚያስችል አሰራርን ዘርግቷል። የፌዴራል ስርዓቱ ፍተሃዊ ልማትን በማስፈንና ድኅነትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። ዛሬ ላይ በሁሉም አካባቢዎች እኩል ባይባልም ፍትሃዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይስተዋላል። ለዚህ ነው ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የፌዴራል ስርዓታችን የሚስተዋሉ ችግሮች ቢኖሩበትም በእነዚህ መስፈርት መሰረት ከገመገምነው የታለመለትን ግብ መቷል ስኬታማም ሆኗል ለማለት የደፈርኩት።

የፌዴራላዊ አስተዳደር እንደ እኛ ላሉ ብዝሃነት ለሚስተዋልባቸው አገራት አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው። በተግባርም ተረጋግጧል። በእርግጥ መስተካከል ያለባቸው የአስተሳሰብ ችግሮች የሉም ባይባልም፤ ይህን ስርዓት ማስተካከል እንጂ ለመለወጥ መሞከሩ ተገቢ አስተሳሰብ አይመስለኝም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ክልሎች ወሰን እንጂ ድንበር የላቸውም። ድንበራቸው ኢትዮጵያ ነች። በመሆኑም ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመንግስት ሃላፊዎች ጭምር ክልሎች ወሰን እንጂ ድንበር እንደሌላቸው በደንብ ሊያውቁ ይገባል።

ክልሎች ህገመንግስትንና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ መቻል አለባቸው። እንደእኔ አተያይ በቅርብ ለታየው ቀውስ የዳረገን ህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን አመራሩ ጭምር ወሰንንና ድንበርን የተረዱበት ሁኔታ የተሳሳተ በመሆኑ ይመስለኛል። አንተ ከዚህ አይደለህም ውጣ፣ ወደመጣህበት ሂድ፣ ከዚህ ያፈራኸው ንብረትም የእኛ ነው፣ ወዘተ በማለት ዜጎችን በማፈናቀል ለችግር ሲዳርጉን የነበሩት አካሎች ራሳቸውን በደንብ መፈተሽ ህገመንግስትን በደንብ መረዳት መቻል አለባቸው። ይህን አይነት አስተሳሰብና ተግባር ጣጣው ለሁላችንም የሚተርፍ በመሆኑ በእንጭጩ መቀረፍ መቻል አለበት።

የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ድክመቶቹንም ራሱን በራሱ ማረም የሚያስችል መንገድ ያለው ስርዓት ነው። ምንም ነገር ዘላለማዊ አይደለም። ከጊዜ ጋር ማሻሻያዎች ይፈልጋል። መንግስትም ከባቢያዊ ሁኔታውን በየጊዜው እየፈተሸ ማስተካከል የሚፈልጉ ነገሮችን ማስተካከል ይገባዋል። ቁራሽ መሬት ወደዚህ ወይም ወደዚያ ሄደብኝ በማለት አጠቃላይ ስርዓቱን ሊያፈርስ የሚችል አደገኛ ነገር ውስጥ መዘፈቅ አደጋው የከፋ ይመስለኛል። በፌዴራል ወይም በማዕከላዊ መንግስቱና በክልል መንግስታት መካከል ያለውን የስልጣን ክፍፍል በሕገ መንግስቱ በግልፅ የተለየ በመሆኑ ሁሉም ድርሻ ድርሻውን መወጣት ከቻለ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ያገኛሉ። ህገመንግስታችን ለችግሮቻችን ሁሉ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ ሰነድ መሆኑን በመረዳት የመፍትሄ ምንጭ ማድረግ ተገቢ ነው።

ለዘመናት በግጭትና ቀውስ ሳቢያ በከፋ ድህነት ውስጥ ስትዳክር የኖረችው አገራችን ያልተማከለ ስርዓት መከተል በመቻሏ በየዘርፉ በርካታ ስኬቶች ማስመዝገብ ችላለች። ይሁንና መንግስት ሁኔታዎችን መርምሮ ማስተካከል ባለመቻሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ አስፈሪና አሳፋሪ አካሄዶችን ተመልክተናል። ይህን አይነት ድርጊቶች ደቡብ አፍሪካ በዜጎቻችን ላይ አደረሰች ብለን ስንጮህ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ዛሬ ያ ነገር በአገራችን ተከስቷል። ንጹሃን ዜጎቻችን በጠራራ ጸሃይ ተገድለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። ደቡብ አፍሪካ ያሉ ዘረኞች ከዚህ የተለየ ምን አደረጉ? መንግስት ዘግይቶም ቢሆን እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ነው።

አሁንም የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማበላሸት የሚሯሯጡ አካሎችን እየተመለከትን ነው። እነዚህ አካላት ለመግቢያ እየተጠቀሙበት ያለው እንደትላንቱ ሁሉ የፌዴራል ስርዓታችን ውስጥ የሚስተዋለውን ልዩነቶች ነው። እውነታን ቆም ብሎ በማሰብ እነዚህ ሃይሎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ለማንም የሚበጅ ባለመሆኑ ልናወግዛቸው ይብቃችሁ ልንላቸው ይገባል። ሲዳማ የክልል ጥያቄ ለማቅረብ ከዋይታ ጋር መጋጨት ወይም ጉራጌና ቀቤና ይህ የእኔ ነውና ውጣልኝ አልፈልግህም ወዘተ መባባል ለምን አስፈለገ?

ኢትዮጵያ በርካታ ልዩነቶችና ፍላጎቶች የሚስተዋሉባት አገር ከመሆኗ ባሻገር ባልተረጋጋው እና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ በሚታይበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የምትገኝ አገር ናት። ኢትዮጵያችን በዚህ አስቸጋሪ በሚባለው የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የሰላም ደሴት ለመሆን የቻለችው የህዝቦቿን ልዩነቶችና ፍላጎቶች አጣጥማ መኖር የሚያስችላት የፌዴራል ስርዓት መተግበር በመቻሏ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ የህዝቦች የዘመናት ጥያቄዎች የሆኑት እኩልነት፣ ሰላምና ልማት የተረጋገጡት በዚህ የፌዴራል ስርዓት ነው። እንደእኔ እንደኔ ፌዴራሊዝም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የህልውናዋ መሰረት በመሆኑ ምርጫም ብልጫም ነው ባይ ነኝ።

በፌዴራል ስርዓታችን ውስጥ ከሚታዩ ማንነቶች መካከል የክልል ወይም የቡድን ማንነትና ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶች ሳይዛነፉ እኩል ሊዳብሩና ሊተገበሩ ይገባል። ኢትዮጵያዊ ማንነት ሌሎች ማንነቶችን ደፍጥጦ እንዲገኝ አለማድረግ በተመሳሳይ የቡድን ወይም የብሔር ማንነትን ከሌሎች ማንነቶች በተለይ ከኢትዮጵያዊ ማንነት በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሁሉንም በልክ በልክ የማናስኬደው ከሆነ ዋጋ ያስከፍለናል። የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነትም ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ መሆን መቻል ይኖርባቸዋል። በፌዴራል አስተዳደር ክልሎች ያለ መዕከላዊ መንግስት እንዲሁም መዕከላዊ መንግስት ያለ ክልሎች አይኖሩም። አንዱ ክልል ቀውስ ሲገጥመው ችግሩ የዚያ ክልል ብቻ የሚቆም ሳይሆን አገር አቀፍ ችግር ይዞ እንደሚመጣ ተመልክተናል። በመሆኑም እባብ ሞኝን ሁለቴ ነደፈው፤ አንዴ ሳያይ ሌላ ጊዜ ሲያሳይ እንደሚባለው እንዳይሆን ከደረሰብን ችግሮች ጥሩ ትምህርት ልንቀስም ይገባናል።

 

Back to Front Page