Back to Front Page


Share This Article!
Share
ባለህበት እርገጥ ባለህበት ውደቅ

ባለህበት እርገጥ ባለህበት ውደቅ

ይቤ ከደጃች. ውቤ 09-14-18

 

 ሰሞኑን በመዲናችን በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች በሰንደቅ ዓላማ ምክንያት ሁከትና ግርግር ለመፍጠር ሙከራ ተደርጎ ነበር።ነገር ግን ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሙከራ ማድረግ እንጂ ሁከትና ግርግር መፍጠር ለማንም አይበጅም።ወጣቶች ድጋፋቸውንም ሆነ ነቀፋቸውን የመግለፅ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው።ይህን ሲገልፁ ግን ከወገኖቻቸው ጋር በመነጋገር በሰላማዊ መንገድ ነው እንጂ ሁከትና ግርግር በመፍጠር መሆን የለበትም።

መብታችን ነው የሚሉትን ነገር ለማስከበር የሚፈልጉ አካላትና ወጣቶች የሌላውን መብት በመርገጥና በመደፍጠጥ መሆን እንደሌለበት መገንዘብ ያሻቸዋል። በአንድ ጀምበር የሀገሪቱ መለያ ካለተቀየረ ሞቼ እገኛለሁ ማለት የአምባገነንነትን ጦር መታጠቅ ማለት ነው።ባለንበት ዘመን ልዩነትን ለመግለፅ ቀስት መገተር ጦር መወርወር አስፈላጊ አይደለም ።ልዩነትን ለመፍታት የዘመናችን የሰለጠነው መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየትና መነጋገር እንጂ ድንጋይ በመወርወር ሁከትና ግርግር መፍጠር ጊዜው ያለፈበት ፋሽን ነው።

Videos From Around The World

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር ከቀዳሚዎቹ ረድፍ ነች። በሠለጠነ መንገድ ከተጓዝን ልዩነታችን ውበታችን ነው። ከ86 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ላላት ኢትየጵያ ልዩነት የግጭትና የሁከት ምንጭ ሳይሆን ከሠራንበት የሀብትና የዕውቀት ምንጭ ነው።ጠንክረን ብንሠራ ልዩነታችን የቱሪዝም መስህብ ሆኖ ገፅታችንን እንገነባበታለን ፣ ብሔራዊ መግባባት እንፈጥርበታለን፣ጥሪት እንቋጥርበታለን፣ ከድህነት የምንወጣበትን መንገድ እንዘረጋበታለን እንጂ ልዩነታችንን ልንሻኮትበትና ልንጋጭበት ምክንያት አይሆንም። እርስ በርስ ብንጋጭ ደግሞ ከሕዝብ ብዘታችን አንፃር ችግሩ ወደ ጎረቤት ሀገራትም የሚያንዣብብ ይሆናል።

ግጭቶቹ በተለይ በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ቀናት በፓስተር ጳውሎስ፣ በኳስ ሜዳ ፣በአውቶቡስ ተራ መናኸሪያ እንዲሁም በሰባተኛ አካባቢ በተወሰነ መልኩ ታይተው ነበር ። የግጭት መንስኤ የኦነግን አመራሮች ለመቀበል በሚደረግ ዝግጅት የራሳችንን መለያ እንሰቅላለን በሚሉና በሌሎች ወጣቶች መካከል የተፈጠረ አለመግባባትና ስሜታዊነት ነው።የፀጥታ አካላትና ፖሊስ የተፈጠረውን ሁከት ለመበተንና ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመዋል።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ባንዲራን ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አርማን መስቀል ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት አካል ከመሆኑ አንፃር የሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕገ መንግሥታችን ጋር የሚፃረር አይደለም። ስለዚህ ዜጎች አርማቸውን ሲሰቅሉ የሌላውን አርማ በማውረድ መሆን የለበትም።የራሳችን የሚለውን መብት የምናስከብረው የሌላውን መብት በመፃረር ወይም በመዳፈር ሊሆን አይገባም። የተሰቀለን አርማ መለያ አውርጄ የራሴን እሰቅላለሁ ብሎ መጣር ከሌሎች ጋር ለመጋጨት በር መክፈት ይመስለኛል። በተለያዩ ቦታዎች የሀገሮች ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ ባላንጣ የሆኑ ሀገሮች መለያ ጎን ለጎን የመውለብለብ ዕድሉ ሠፊ ነው።ይህ ደግሞ ሀገሮችን ለግጭት ሊያነሳሳ የሚችል አይደለም።

ይህን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ችግሮቻችንን በመደማመጥ በፍቅር መፍታት አለብን እንጂ በኃይልና በጉልበት ለማሸነፍ መጣር አዋጪ አለመሆኑን ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።በሃሳብ ገበያ ውስጥ ተወዳድሮ ሃሳብን ከመግለጫ መንገዶች አንዱ ባንዲራ እንደመሆኑ ችግሮችን ሥርዓት ባለው መልኩ ለመፍታት ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሽማግሌዎች ይጠበቃል።ችግሮች ሲፈጠሩ የመገናኛ ብዙሃን የመንግሥት አመራሮችን የፖሊስ አካላትን ማነጋገራቸው ተገቢ ነው።ይሄ ወደፊት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በኃይል ለማሸነፍ መሞከር በየትኛው መልኩ አዋጪም አትራፊም አይደለም። በኃይል እናሸንፋለን ብለው ካሸነፉ እንደ ደርግ አገዛዝ የሌላውን ፍላጎት መደፍጠጣቸውና መርገጣቸው አይቀርም።ደርግ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እያለን ትምህርት ከመግባታችን በፊት እያሰለፈን ባለህበት እርገጥ እያለ እንደወታደር ያስረግጠን ነበር።ዕድሜያችን ሲደርስ ለወታደርነት ሊመለምለን ማለት ነው።ኢህአዴግ መጣና ከዚህ ጣጣ ነፃ አወጣን እንጂ፤ወታደራዊው ደርግ ባለህበት እርገጥ ሲል ባለበት ወደቀ።ባለህበት እርገጥ ውጤቱ ባለህበት ውደቅ ማለት ይመስለኛል።

ሀገራችን ከፊቷ ትልቅ የልማት፣የዶሞክራሲና የሰላም ሥራ ይጠብቃታል።የልማት ሥራዎቿን ማስፋፋት፣የውጪ ባለሀብቶችን መሳብ፣ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የምንችለው ምቹና ተመራጭ የምንሆነው እኛ ሰላም ሆነን ስንገኝ ነው።ወልዶ መሳም ዘርቶ መቃም የሚቻለው ሰላም ሲኖር ነው።ዜጋው ልጁን ማስተማር፣ የሞተበትን መቅበር የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። የምድር እንስሳት የሰማይ አዕዋፋት በልተው ጠጥተው የሚቦርቁት ሰላም ሲኖረን ብቻ ነው።ሰላማችን ከእኛ አልፎ ለአራዊትና ለአዕዋፋት መሠረታዊ ነገር ነው።ድህነትን የምንዋጋው ሰላምና ፀጥታ ሲረጋገጥ ነው።ሁከትና ግጭት ድህነታችንን ተከናንበን ተመፅዋች ያደርገናል እንጂ የሚያመጣልን ፋይዳ የለም።

መንግሥት ሰላም ማስከበር ዴሞክራሲ ማስፈን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታው እንደመሆኑ ዜጎችም ሃሳባቸውን ሲገልፁ የማይቀበሉትን መለያ እያወረዱ የራሳቸውን እየሰቀሉ መሆን የለበትም።ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ በሄዱበት ወቅት በሚኒሶታ ዲያስጶራዎችን በተሰበሰቡበት ሲገኙ ዜጋው ከፊሉ ሌላ አርማ (ባንዲራ)፣ከፊሉ ሕገመንግሥታዊ አርማ የሌለበት ባንዲራ የቀረው ደግሞ የፌዴራል መንግሥት አርማ ያለበትን ባንዲራ ይዞ ጎን ለጎን ቆሞ ሲያውለበልብና ስሜቱን ሲገልፅ በመከባበር መንፈስ በመሆኑ ሁከትና ግርግር እንዳልተፈጠረ በሚዲያዎቻችን ዐይተናል።

ሰሞኑን በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሰላም ደመና እያንዣበበ ባለበት በዚህ ወቅት የሰላም ተምሳሌት እየሆነች ባለችው ሀገራችን ሁከት መፍጠሩ ተገቢ አይደለም።ለረጅም ጊዜ በርስ በርስ ጦርነት ሲታመሱ የነበረ የደቡብ ሱዳን ዜጎች የሰላምን ፍሬ ለማጣጣም ተቃርበዋል።የሀገሪቱ መሪዎችና ባላንጣዎች ባለፈው መስከረም ሦስት ቀን በአዲስ አበባ የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች በተገኙበት በመፈራረም ለሰላም ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

መስከረም 3 ቀን 2011 ዓም በአዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በደቡብ ሱዳን አመራሮችና ተፋላሚዎች መካከል የተካሄደውን ትልቅ የሰላም ስምምነት ከመሆኑ አንፃር ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተቀባብለው ዘግበውታል።ለዚህ ስምምነት ሀገራችን ከታላቁ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ ጀምሮ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን፣ ያላሰለሱ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች።ይህም ሀገራችን ለሰላም የምትሰጠውን ዋጋ የሚያሳይ ነው።የጎረቤት ሀገር ችግር የራሴ ችግር ነው በማለት ተደጋጋሚ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ስታደርገ የነበረችው ሀገራችን ጥረትዋ በከንቱ አልቀረም።ይህም የሀገራችንን ገፅታ የበለጠ የሚገነባ ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነትን የበለጠ የሚፈጥር ተግባር ነው።

ለረጅም ጊዜ በርስ በርስ ጦርነትና በአሸባሪዎች ግጭት ስትታመስ በነበረችው ሶማሊያ የሰፈነው አንፃራዊ ሰላም፣ በኢትዮ ኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የቆየው ግጭት ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በራስ ተነሳሽነት መፈታቱ በጦር ዐውድማዎች አካባቢ የነበሩ ምሽጎች ተደርምሰው በአዲሱ ዓመት መባቻ ከሁለቱም ሀገራት ያሉ ወገኖች የሚገናኙበት መንገድ መመቻቸቱና ለሰላም ያላቸውን ዋጋ በፍቅር በናፍቆት በዘፈንና በእንባ መግለፃቸው የሰላምን ዋጋ አጉልቶ ያሳየናል።በሁለቱ ሀገራት የሰፈነው ሰላም ሁለቱም አትራፊ ሊሆኑ የሚችሉበትን የምፅዋና የአሰብ ወደቦችን ለመጠቀም ተነሳኝነት የፈጠረ ነው።ይህም የሁለቱ ሀገራትን ሕዝቦች የበለጠ የሚያቀራርብ ሀገራችንም አማራጭ ወደቦችን በማየትና በማወዳደር እንደ አካባቢው ርቀት ለመጠቀም የሚያስችላት ነው።

 

Back to Front Page