Back to Front Page


Share This Article!
Share
የታንዲካ ሰዓት ደርሰች'ንዴ?

የታንዲካ ሰዓት ደርሰች'ንዴ?

 

ተኸለ መልኪን: July 22 -2018

 

ዓመተ ምህረቱ፤ በፈርንጆች ኣቆጣጠር 1994-5 ገደማ፤ ኣገሩ ስዊድን፤ ከተማው ሉንድ፤ ቦታው የሶስዮሎጂ ዲፓርትመንት ነው። ኣንድ ተመራማሪ ጋብዘናል ስለ ኣሉ ኣንድ ክብ ጠረጴዛ ያህል ኣስተማሪዎችና ተማሪዎች (15 ገደማ) ነበርን። እንግዳው ታንዲካ ምካንዳዊረ ይባላል (ኣፍሪቃዊ)፤ የመጣው፥ ዴንማርክ ከሚገኝ ሰንተር ፎር ደቨሎፕመንት ሪሰርች(የምዕባሌ ጥናት ማእከል) ነበረ።ኣሁን የፕሮፈሰርነት መዓርግ ተሰጥቶት ሌላ ኣገር ውስጥ የሚሰራ ያለ ሰው ነው።

Videos From Around The World

 

ስለእድገት የተናገረው፤ ኣሁን ብዙም ትዝ የማይለኝ ቢኖርም፤ ቀልቤን የሳበው ከተባበሩት መንግስታት ኣካሎች ለዓለም የሚላከው ኢንፎርሜሽን ምን ያህል ኣሳሳችና ሆን ብሎ የሚሰራጭ መሆኑን፤ እንዲሁም በጣም ችሎታ ያላቸውና: በጣም የተማሩ ኣፍርቃውያን እራሳቸው ተመራምረው፥ ደምረውና ቀንሰው የሚያገኙትን ትክክለኛውን ውጤት ሳይቀር የተባበሩት መንግስታት እንደማይቀበለው የሚገልጽ እስከነምስክርነቱ ኣቀረበ። በጣም የሚያስደነግጠው ግን፥ ጥሩ መበልጸግ የጀመሩትን የሶስተኛ ዓለም ኣገሮችና ህዝቦች በሚመለከት የተናገረው ንው። ይህ ኣሁን የምጽፈው ያለሁትም ከሁሉ በላይ ያችን መልእክት (ብትጠቅም) ለማስተላለፍ ብቻ ነው። ታንዲካ (የዝያን ጊዜ የትምህርት ደረጃውን ኣልውቅም) እንዲህ ኣለ፤ የኣንደኛው ዓለም ኣገሮች ሶስተኛው ዓለም እንዲበለጽጉ ፍጹም ኣይፈልጉም።ብልጽግናው ገና እግር መትከል ሲጀምር: ምልክት የሚሰጠው የተባበሩት መንግስታት ነው። በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት መሰረት ኣንዲት የሶስተኛ ዓለም ኣገር ጥሩ እየሀደች ነው፤ ጂ::ፒ (ጠቅላላ ያገሪቷ ፍርያምነት) ከተወሰነ መቶኛ (ፐርሰንት) በላይደርሷል ብሎ ካወጀ፤ የኣገሪቷ የብልጽግና ዕድሜ ቢበዛ 2 ወይም 3 ዓመታት ነው፤ ከዝያ በኋላ የሚታየው የሰላም መደፍረስ፥ ጦርነት፥ የርስበርስ መጋጨት የመሳሰሉ ጸረ ምዕባሌ የሆኑ ስነምግባሮች ናቸው ብሎ ሲያበቃ: በተርታ ኣገሮችን እንደ ምሳሌ በመስጠት ደመደመ።

ይህ ኣባባል ኣዲስ ነገር በመሆኑ ሳይሆን፤ በሙሉ በራስ ተማማኝነትና ተጨባጭ በሆኑ መረጃዎች ማቅረቡ ነው የሳበኝ ለማለት እደፍራለሁ። በበኩሌ ነጋም ጠባም የትኛዋ ሃገር ወደፊት ገሰገሰች እያልኩ የምዳስስ፤ ጥሩ ስሰማ የምደሰት፥ መጥፎ ስሰማ ደግሞ የማዝን(እንደ ብዙዎች ያፍሪቃ ተወላጆች) በመሆኔ የታንዲካ ኣባባል ከኣንጎሌ ሊወጣ ኣልቻለም፥ ድሮ ከማደርገው በላይ እንድከታተልም ኣድርጎኝ ቆይቷል።

 

ወደ ኢትዮጵያ መለስ ብዬ ሳይ፥ ከደርግ በኋላ ብዙ ኣዎንታዊ ለውጥ ኣየሁ: ሰማሁም። የፖለቲካውን ጉዳይ ወደጎን ትቼ፤ በትምህርት፥ ብሕክምና፥ በኤኮኖሚ ወዘተ.. ተስፋ የሚሰጥ ሲታይ ቆዬ ነው የምለው፤ ሁል ጊዜ ግን ያቺ የታንዲካ ሰዓት መች ነው የምትሞላው ብዬ ከመቸገር ኣቋርጬ ኣላውቅም። ኣሁን ቅርብ የኣዲስ መሪ መምጣትና፤ ብዙ ቃል ኪዳኖችና ፈጣን ውሳኔዎች ሲወሰዱ ስሰማ፤ መጀመርያ ወደ ጥሩ ብቻ የሚያመራ ሆኖ ነበር የተሰማኝ፤ኢትዮጵያ ክኣደጋው ልታመልጥ ነው መሰልኝ ኣልኩኝ፥ ሊሆንም ተስፋ ኣደርጋለሁ። ሆኖም በዚ ኣጭር ጊዜ የሚሸተው የሚያስተማምን ሆኖ ኣልተሰማኝም፤ እንድያውም ያቺ ታንዲካ ያላት (በጣም የዘገየቹ) ሰዓት ወደ መድርሷ ገደማ መሰለቺኝ።

ምክሬ፤

እኔ ኤሪትዊ ነኝ፤ ሆኖም ኢትዮጵያ ትሁን ሌላ: በተለይም የኣፍሪቃ ኣገር: ብልጽግና ማየት፥ የሚያስደስተኝና ተስፋ የሚሰጠኝ ሰው ነኝ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በብልጽግና`ና በሰላም እንዲቀጥል፤ ለሌሎችም ኣርኣያ እንዲሆን ከተፈለገ፤ የውጭ እጅ ሳይገባበት ጉዳዮቹን ራሱ ፈት`ቶ ህዝቡ በተሻለ የሚኖርበትን መፍትሔ እንድያገኝ ነው የምመክረው። ኣገሬም ከእንደዚህ ያለ ጎረበት (መላኪውን ስርዓት ኣስወግዳ) በሰላምና በብልጽግና እንድትኖር የኣብዛኛው ህዝቦቻችን ፍላጎት መሆኑ ኣያጠራጥረኝም። የደረሳችሁበትን ደረጃ ጠብቃችሁ ጨምሩበት፤ ኋላ የሌሎች ማስ`ሳቅያና መሳለቅያ እንዳትሆኑ፥ ኣርኣያ ልትሆኑት ይጥብቃችሁ የነበረውን የኣፍሪቃ ህዝብ ኣታሳፍሩት፥ ተስፋ ኣታስቆርጡት። ፖለቲካችሁን በብልሃት ፍቱ፤ የማይፈታ ነገር የለምና።

 

መደመር፤

 

ይህ ቃል በመሰረቱ ፖለቲካዊ ትርጉም ሊሰጠው ከሆነ ጥንቃቄ የሚሻ ነው እላለሁ። ምክንያቱም እንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ችግሮች በዚሁ በመደመር ምክንያት የመጣ ይመስለኛል። የኡጋዴንና የኦሮሞ ጥያቄዎችን ብንወስድ፤ ካለፍላጎታችን የተደመርን (የተገዛን/የተወረርን) ህዝቦች ነን ነው የሚሉት። እና ይህ በፍቅር እንደመር የሚለው ኣባባል ልባቸውን ያርስላቸው ይሆን? ለትውልዶች ሲተላለፍ የቆየ ጸረ መደመር የሆነ ኣስተሳሰብ ብስመ ፍቅር ሊቀየር ይችል ይሆን? በተግባር ልባቸውን የሚያርስ ስነምግባሮች ሳይወሰኑና ተግባራዊነታቸው ታይቶ ሳይመዘን: ኣብሮ በፍቅር መኖር በሚል ደግና ጥሩ መርሆ` ሃሳባቸውን ይቀይሩ ይሆን?

 

ኤርትራ፤

 

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ዓመታት የሄደ፥ ኣስፈላጊ ያልነበረ፥ ውግያ በማካሄድ ናጽነቷን የተጎናጸፈች ኣገር ናት። ኣስፈላጊ ያልነበረ ማለቴ፥ በኤርትራ ህዝብ ፍላጎትና፤ የተባበሩት መንግስታት በፈቀደላት መሰረት፤ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀጥል ወይም ናጽነቷን እንድታውጅ ዕድል ሳይሰጣት በዝያን ጊዜ የነበረው መንግስት በሃይል ገብቶ ኣገሪቷን ኢትዮጵያዊት እንድትሆን በማስገደዱ ምክንያት የተጫረ ኣሰቃቂና ኣክሳሪ ውግያ በመሆኑ ነው። ዛሬበኢትዮጵያም በኤርትራም በኩል የሚካሄደው ያለው; 56 ዓመታት በፊት ሊደረግ ይገባው የነበረውን ነው። ኣሁንም ከኢትዮጵያም ይሁን ከኤርትራ፤ ከህዝብ ፍላጎትና ቡራኬ ውጭ የሚወሰድ የሆነ ውሳኔ፤ ተመልሶ ወደ ቀድሞው ችግራችን እንደሚመልሰን ኣትጠራጠሩ፤ የኦጋዴንና የኦሮሞ ጥያቄዎች ኣብነት ይሁናችሁ፤ ከኤርትራው ጦርነት ጋር ጎን ለጎን ሲሄድ የቆየና ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉትን ሰላምና ኣንድነት ያላረጋገጠ ሆኖ ነው የቆየው። ጉዳዩ በልክ እስካልተፈታ ድረስ፤ የምብራቅና ምዕራብን ሓያላን መንግስታት ድጋፍ ኣግኝቶ እንኳን ሰላምን ሊያረጋግጥ ኣይችልም።

 

ኤርትራን የሚመራ ያለው ሰው ፈላጭ ቆራጭ የሆነ ዲክተተር መሆኑን ዓለም የመሰከረው ነው። ስለሆነም፤ ከዚህ ሰው ጋር የሚደረግ ስምምነት: ከሱ ጋር ብቻ የሚደረግ እንጂ ከኤርትራ ህዝብ ጋር እንዳልሆነ ማወቁ ደግ ይመስለኛል። በተጨማሪም ዲክተተሩ የስልጣንን ጣዕምና ኣጠቃቀም ለብዙ ዓሰርታት ዓመታት (ዲኬድስ) ያህል ያወቀው ስለሆነ፤ የሆነ ኣዲስ መሪ ሊወዳደረውና ወደፈለገው ሊጠመዝዘው የሚቻል ኣይደለም፤ በኣንጻሩ ኣደጋ ሊሆን ነው የሚችለው። የኤርትራ ህዝብ ከጎረበቶቹ ጋር በሰላም ሊኖር ፍላጎቱ ስለሆነ፤ ተከባብሮ ሊጠቃቀምና ሊተጋገዝ ዝግጁ ነው፤ ዝምድናዎቻችን ጥሩ እና ዘላቂነት ያላቸው እንዲሆኑም ህዝብ ከሚወክል መንግስት ወይም መሪ ጋር መስማማት ብቻ ሲሆን መሆኑንም ለህዝብም ፖለቲከኞችን ማስታወስ እወዳለሁ።

 

የኤርትራው መሪ የኢትዮጵያውንን መሪ እንዴት መምራት እንዳለበት ሊያስተምረው ካልሆነበስተቀር፥ በጤና እንዲህ ባልቀረበ ነበር። ብልሃቱ ደግሞ እንዴት ኣንዲትን ኣገር ከተቃዋሚዎች ነጻ እንድትሆን ማድረግ ነው (ልክ እንደ ኤርትራ)። ይህን ለማድረግ ደግሞ ብዙ ልፋት የሚያስፈልገው ኣይደለም፤ ገንዘብና ሓይል (ስልጣን) ይበቃል። በገንዘብ ታማኝ የሆነ ሓይል መዘርጋት፤ ህዝብ እርስበራሱ እንዳይተማመን ማድረግ፤ የሚያሰጉትን ይቅርና፥ የተቃውሞ ኣዝማምያ የሚያሳዩትን ሁሉ ያለ ምሕረት ማጥፋት፥ የተቃውሞ መሪዎችን: በተለይም ህዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያላቸውን: መሰወርን የመሳሰሉ ናቸው። እንግዲህ እንዲህ ያለ እርምጃ ሲጀመር; መሪው (ተማሪው) የቤት ስራውን ማከናወን ላይ እንዳለ ማስተዋል ጥሩ ነው።

 

ከሁሉ የሚያሰጋውና የሚያሳዝነው፤ ሰላም ሲጠፋ የኣገሮቻችን የወደፊት ግስጋሴና እርምጃ/እድገት ይኮላሻል፤ ወደፊት እንደመገስገስ ወደኋላ ይቀለበሳል፤ ህዝብ፥ በተለይም ኣዲሶች ትውልዶች በመጥፎ ኣርኣያነትና የተደናቀፈ ኣስተዳደግና ኣስተሳሰብ ያድጋሉ።

 

ምኞቴ፤ ባገሬና በጎረቤት ኣገሮች ኣንዲሁም በኣፍሪቃ ቀንድና በመላው ኣፍሪቃ ሰላምና ብልጽግና ተረጋግጦ ማየት ነው። ዛሬ፥ ዕድሜ ለ በታሪክ ያለፉና ያሉ ጨኳኝ ኣስተዳደሮች ያስከተሉት ስደት፤ የኣፍሪቃ ቀንድ ህዝቦች ተዋውቀዋል፥ ተጋግዘዋል፤ ተደጋግፈዋል እንዲሁም ተዋልደዋል፤ ስለዚህም መንግስታት ለወደፊት የሚያዋጣና የሚያስማማ የችግሮች ኣፈታትና የሚያከባብር ጥሩ ስምምነቶች ለመወሰን ቢበቁ፤ ህዝብ በእልልታ የሚቀበለው መሆኑ ኣያጠራጥረኝም። ይህ እስካልተፈጸመ ድረስ ግን ያ የታንዲካ ኣባባል በኣገሮቻችንና ህዝቦቻችን ላይ እያንጃበበ መሆኑን ኣንርሳ በማለት ደግሜ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።

 

የታንዲካ ሰዓት ደርሰች`ንዴ?

ኣፍሪቃን የልጆቿ ልቦና ያድናት።

Back to Front Page