Back to Front Page


Share This Article!
Share
እጥፋቶቹ

እጥፋቶቹ

አሸናፊ 08-07-18

 

ኢህአዴግ ሆይ፣ የራሴ ሰው እምትለው ዓቢይ አጋድሞ እያረደህ ነው፡፡ ራስህ ያመጣኸው ነውና፡እማዝነው ላገሬ ነው።

 

ነበር፣ ነበር…

ኢህአዴግ ላይ ያለኝ ስሜት የለየለት ተቃዉሞም ድጋፍም አልነበረም። ቅልቅል ነገር ነበር። እምደግፈው የተሻለ አመራር አይገኝም ወይም ለኢትዮጵያ አያሻትም ከሚል አልነበረም፡፡ ግን ኢትዮጵያ በብዙ አቅጣጫ የመሻገርያውን መስመር ላይ ለመድረስ እየተቃረበች ስለመሆኑ ግልፅ ስለነበር እንጂ፡፡ ወንዙ መሃል ላይ ፈረስ አይቀየርም፣ እንዲሉ።

ለምሳሌ የልማት ሽግግሩ አፋፍ ላይ ነበር፡፡ የተጀመሩት ሜጋ ፐሮጀክቶች ፍፃሜ ላይ በማድረስ ብቻ የኢትዮጵያን ግስጋሴና ህዳሴ ላይመለስ የማብሰሪያ ደወሉ ሊደወል መቃረቡን ፍንትው ብሎይታይ ነበር፡፡ የዲፕሎማሲ ልዕልናው ደርግ እንደተቀየረ ብዙም ሳየቆይ ነበር የተቀየረው። የራሱ ፈተናዎች እየተሻገረ መጥቶ ወደሰገነት ከፍ ከፍ እያለ ነበር፡፡

ፈደራሊዝም ለአገራችንም ለፖለቲካዊ ባህላችንም አዲስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህም፣ እየወደቅን እየተነሳን እያሻሻልነውና አስተማማኝ መሰረት ላይ እየገነባነው እምንሄድ እንጂ ከመጀመርያውም አልጋባልጋ ይሆናል ተብሎ አልተጠበቀም፡፡ እግሩ ሥር ሰዶ አካሉ ደልድሎ ገና አልጠናም እንጂ ብዙ ርቀት እየሄደ ነበር።

ፈቅ ማለት ያቃተውና አንዳንዴም እየባሰበት የታየው ዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደሩ ጉዳይ ነው፡፡ የሁለቱ ችግሮች ቀጥተኛው ምንጭ የፖለቲካ አመራሩ ብልሽት ነበር፡፡ በተለይም የመልካም አስተዳደሩ ችግር ህግንና ፍትህን ጨምሮ ሁሉንም የስርዓቱ ገፅታዎች በፍጥነት እየበከለ ሄዶ ደህና ደረጃ ላይ የነበሩትንም ውጤቶች ያበላሽ ገባ፡፡ ሁኔታውም ለአሉባልተኞችና አክቲቪስቶች የተመቸ ሆነ፡፡

በእነደዚህ ዓይነት መድረክ አስመሳዮችና ህዝበኞች ሙሴን ተመስለው፣ “ህዝቡን ባህር ለማሻገር የመጣን መሲሆች ነን”እያሉ ተጎዘጎዙት፡፡ ህዝቡም በተሰፋ መቁርጥ ውስጥ ተስፈኛሆኖ እነሱ እሚነግሩትን እንጂ ሌላን አያምንም። በደህና ጊዜ ቢሆን ’’በ7 ዓመቴ ንጉስ እንደምሆን ተነገሮኛል’’ እሚለንን ሰው ማየት ያቅለሸልሸን ነበር፡፡ ይቅርና ኢህአዴግን እሚመራ የመጨረሻው ሰው፣ ተራ የኢህአዴግ አባል እንኳ የዚህ ዓይነት ንግግር ቢወጣው ወዲያው እሚባረር ነበር እሚመስለን፡፡ ኧረ’ቴ! እየዬም ሲደላ ነው፤ ድርጅቱ ሳናውቀው ብዙ ተቀይሯልና፡፡

Videos From Around The World

 

 

ከወደ መተማ እምትጤሰው ጢስ…

ይህ እንግዲህ በአንድ አዋቂ ለአፄ ዮሃንስ የተገጠመ ማስጠንቀቂያ ነበር፡፡ አፄ ዮሃንስ ጣልያን በሰሜን፣ ድርቡሽ በምዕራብ፣ ምኒሊክ በሸዋ ሶስቱም ባንዴ አስጨነቁዋቸው፡፡ ያኔ ጣሊያንን ለመደምሰስ ከተው የነበረበት ጊዜ ቢሆንም የትኛውን ማስቀደም እንዳለባቸው ማውጣት ማውረዳቸው አልቀረም፡፡ ምኒሊክ የስልጣን ጉዳይ ነው፣ ግድ የለም ይቆይ፣ በኋላ ይታሰብበታል፡፡ ጣልያንና ደርቡሽ ግን የአገር ጉዳይ ነው፣ የደርቡሹ ደግሞ ይብሳል፣ የክርስትናና የእምነት ጉዳይም ስላለበት… ሲሉ ያሰቡበት ይመስለኛል፡፡ግን ደግሞ አዋቂው በትክክል ተንብዮላቸው ነበር፡፡

’’ከወደ መተማ እምትጤሰው ጢስ

እምታስነባ ናት እምታስነጢስ

እምብዛም አትበጀው ላፄ ዮሃንስ’’

ተመሳሰለ?! ኢህአዴግ ለኤርትራ ጉዳይ የሰጠው ትኩረት “ሂሳብ አልወድም” እንደሚለው ሰነፍ ተማሪ ዓይነት ሆኖ ነው የቆየው። ወይ ደፍሮ አልተጋፈጣት ወይ አልተፋታት።

ሌሎቹ ደግሞ የናይልና የቀይ ባህር ጉዳዮች ናቸው። የናይል ጉዳይ የሚፈታው በግድቡ በኩል መሆኑ ግልጽ ነበር። ይህን ፈጽሞ መጠራጠር አያስፈልግም። ቁልፉ ያለው ጨርሶ ከመገላገል ላይ ነው። ግንባታው አለመጀመርም፣ መጀመርም፣ ማገባደድም… ሁሉም ልዩነት የላቸውም። ፈረንጆች እንደሚሉት የመጨረሻው ዙር (ቪክትሪ ላፕ) ላይ መልፈስፈስ የበለጠ ያስጠቃ እንደሆነ እንጂ ጥቅም-የለሽ ነው። ትኩስ ድንች ለዘላለሙ ጨብጠው እያረሩ ለመኖር ፈቃደኛ እንደመሆን ይቆጠራል። እቅጩን ለመናገር ግድቡ የኃይል ማምረቻ ፕሮጀክት አይደለም፣ የመከላከያ ኃይል ማስታጠቂያ እንጂ።ዘላለም እሚተናኮልህን ኑክሌር የታጠቀን ጠላት ማርከሻውን እንደማበጀት ማለት ነው፡፡

ቀይ ባህር የበለጠ እየቀላ ነው የመጣው። ነባሮቹም አዲሶቹም ኃያላን ይጋፉበታል። አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድ፣ ኢትዮጵያም ቀይ ባህርን ከንግድ መተላለፍያነት ውጭ አይተውት አያውቁም። አንደኛ፣ ኩታ ገጠም ድንበራቸው ስለመሆኑ ዘንግተዋል። ሁለተኛ፣ በህልውናቸው ላይ ቀጥተኛ ወሳኝነት ያለው ስትራተጂካዊ የጸጥታ ቀጠናነቱን ችላ ብለውታል። ከዚያ ማዶ ያሉት አገራት ግን ይህን አውቀው ቀይባህርን እንደ ቀይ ምንጣፍ ከሥር እየጎተቱ ሲወስዱት በዚህ በኩል ያለችው ኢትዮጵያ እንቅልፍ አይነሳትም። ኢህአዴግን የብዙ ኢትዮጰያውያን ምሁራን ስጋትና ጉትጎታ ፈፅሞ አላነቃውም።

ቻይና ትኩረቷን አፍሪካ ላይ ያደረገችው ጥሩ ሰዓት ላይ ነው። ለምዕራቡ ዓለም አፍሪካ የልማት ቀጠና ሆና አትታየውም። ስለዚህም ስደትና ብጥብጥ ከልክ እንዳያልፍ ያህል እሚልኩት የእርዳታ ገንዘብና ቁሳቁስ ካልሆነ በቀር ለኢንቭስትመንት አያስቧትም። አሁን ድረስ። ቻይና ግን በዚሁ ክፍለዘመን መባቻ ላይ ይህንን አስተሳሰብ ገለበጠችው። ሊታመን እማይችል መዋእለ ንዋይ እያፈሰሰች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ኢንቨስትመንት ላይ በግዝፉ ገባች። በኢህአዴግ አመራር ስር የነበረችው ኢትዮጵያ ከቻይናጋር የመሰረተችው ቅርበትና ትብብር ጉልህ ማሳያ ነበር። ኢትዮጵያ፣ ለቻይናና አፍሪካ የጠነከረ ግንኙነትም እንደመረማመጃ በር ታይታለች።

በዚህ ጊዜ አሜሪካ “አፍሪካ ሙሉ ለሙሉ በቻይና ተጽእኖ ሥር ልትገባ ነው” እሚል ስጋቷ እያየለ መጣ። እናም፣ ይህንን የቻይና ተጽእኖ ለመግታት ብሎም በራሷ ተጽእኖ ለመተካት መርሃ ግብር ነድፋ ተንቀሳቀሰች። ይህ የአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት ሴክሬቴሪ የነበሩት ሬክስ ቲለርሰን የካቲት ወር መጨረሻ ላይ ወደ ኢትዮጰያ ሊመጡ ሲሉ በአንድ የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ያሰሙት ንግግር “ቻይና አፍሪካን ስትጠቀልል እንዳለፈው እጃችንን አጣጥፈን አናይም” ነበር ያሉት። ከዚያ በኋላ ዶ/ር ዓቢይ ተመረጡ፣ ያማማቶ መጡ፣ ዓቢይና ኢሳያስ ኤሜሬትስና ሳውዲ ተገናኙ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ታረቁ…

 

አዲስ ንጉሥ

የዘንድሮ መጋቢት ጉደኛ ነበረች፡፡ ዓቢይ አጼውና ዓቢይ ጾም አንድ ላይ ነበር የመጡት።

የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት ለስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ የስብሰባውም ዓላማ የአባል ድርጅቶቹ ግምገማዎች ፈትሾ ለመወሰን፣ ሂያጅ ሊቀመንበሩን በይፋ ለማሰናበትና አዲስ ሊቀመንበር ለመምረጥ ነበር፡፡ አገሪቷ ውጥረት ሰፍኖባት ስለነበርና ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆኛ መንገዱም መጀመርያ የገዠው ፓርቲ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ስለነበረ ስብስባው እጀጉን የዜጎች ትኩረት ስቦ ሰነበተ፡፡ እጮዎቹ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቃነመናብርት እንደሆኑ ከግንባሩ የቆየ ልምድና ህገ ደንብ ይታወቃል፡፡ ከአራቱ ብዙም ለመሪነት እሚያጓጓ እጩ አልነበረም። ‘ያ ቢሆን’ ከሚባል ‘ያ ባይሆን’ ማለት የቀለለ ይመስል ነበር።

ያኔ ዶ/ር ዓቢይን እንዳሁኑ በደንብ አላውቃቸውም፡፡ ይሁንና፣ ኦሮምያ ውስጥ ከነበረው ከፍተኛ አለመረጋጋትና የመልካም አስተዳደር መጓደል አንፃር ያሳዩት የአመራር ብቃት ማነስ፣ በተጨማሪም በንግግሮቻቸው ውስጥ ባስተዋልኩዋቸው የማስመሰልና የታይታ ድራማዎቸ እንዲሁም የሌሎች ሰዎች ንግግሮቹን ሙሉ ይዘት በግልፅ ኮርጀው የራሳቸው አስመስለው የማቅረብ ከፍተኛ የስብእና ጎዶለነት በማንጸባረቃቸውና ከመሳሰሉት ሁኔታዎች ተነስቼ፣ እሳቸውን እንዳይመረጥ ኢህአዴግን ለማግባባት ሞክሬ ነበር፡፡ እንዲሁ ያልታሰበ ስህተት እንዳይፈፀም ሰግቼ እንጂ የምር የኢህአዴግ አመራር ዘንግ ከሳቸው ዘንድ ይወድቃል የሚል ጥርጣሬ ኖሮኝ አልነበረም፡፡

ግን ተመረጡ፡፡

ያኔ ከውጭ ላያቸው መላው የኢህአዴግ አመራር ዶ/ር ዓቢይበመመረጣቸው ደስተኞች ይመስሉ ነበሩ፡፡ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ በብርሃን ፍጥነት ሂደቱ “ዲሞከራሲያዊና ጓዳዊ” እንደነበረ የኢህአዴግን ጽ/ቤት ወክለው መግለጫ ሰጡ፡፡ በምርጫው ማግስት ዶ/ር ደበረፅዮን ከዚያ በፊት በማይታወቁበት ስሜት መቀሌ ላይ በኦሮምኛ ዘፈን እንደጉድ ሲጨፈሩ ላያቸው ’አረ ጉድ!’ ያሰኝ ነበር፡፡ አቶ ደመቀ ደግሞ ምርጫው ያንን ውጤት ይዞ ይወጣ ዘንድ ከትግል ጓዶቻቸው ጀርባ ’ውስጠ ወይራዊ ድብብቆሽ’ እንደተጫወቱ እንድናውቅላቸው (እንዲሁም አዲሱ ንጉሥ እንዲያውቁላቸው) በግላጭ ለሆሳስ ሲነግሩን፣ ’እኔኮ ነኝ’ በሚል ዓይነት ለሚዲያዎች ሹክ አሉ፡፡

አሁን አሁን ሁሉም ኢህአጎች ደስተኛ አይደሉም፡፡ ይህ መሆኑ እሚደንቅ አይደለም፡፡ የ27 ዓመታት ስኬቶች በሙሉ ’’ቆሻሻ ብቻ’’ እያለ ድርጅታዊ ሌጋሲን ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ላይ በሚወረውር መሪ ሁሉም ደስተኛ ሊሆኑአይጠበቁም! በተለይም ለህወሓት ታጋዮች ግልፅ መራራ ፀሃይ ተከሰተች፡፡ “60 ሺ ጓዶቻችን አስውተን፣ ከኦሮሞና ሌሎች ውድ ታጋዮች ጋር ሆነን ይህን ፈደራል ስርዓት ለመገንባት በቅተናል’’ በሚል እሚፅናናውን ነባር ታጋይ ላይ ’’ደርግ የወደቀው ራሱ ነው’’ እያሉ ስሜቱ ላይ እንደበረዶ የቀዘቀዘ ውሃ ደጋግመው ቸለሱበት፡፡

ከተማሩትና ከተመራመሩትም ዉስጥ፣ ከተቃዊሚ ፖለቲከኞቹም ውስጥ፣አጠቃላይ አኳኃኑና አካሄዱ ስጋት ያሳደረባቸው እየበዙ መጥተዋል፡፡ዶ/ር ዓቢይ ኢህአዴግ እንዳልሆኑ ብዙ ሰው እያመነ ቢመጣም፣ “ታዲያ ከየት ናቸው?” ለሚለው ጥያቄ ግን ግልፅ መልስ አጥቶ ግራ ተጋብቷል። ዶ/ር ዓቢይ አሁን አሁን “ተቃዋሚው ጠቅላይ ሚኒስትር” በሚል የሚገለፁ ሆነዋል። አንድ አዛውንት የፖለቲካ ሰው “እኔ ጠቅላይ ሚኒስትር አላየሁም” ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተውኛል። አንድ ሌላ እማውቃቸው ላገራቸው ብዙ ሥራ ያበረከቱና የተከበሩ ፕሮፌሰር ጠ/ሚኒስትር ዓቢይ በጠሩት የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ያሳተፈ ስብሰባ ላይ ተገኝው ነበር፣ ሲባል ሰማሁእናም ጠ/ሚ/ሩ ’’ፑሽ አፕ’’ እንስራ ሲሉ ወዲያው የስብሰባውን ቦታ ለቀው ወጡ፣ ተባለ። በኋላ ላይ እዛው የነበሩ ሰዎች ’’ምነው’’ሲሉ ጠየቅኳቸው፡፡

“እንዲህ ዓይነት የጎረምሳ ሥራ ኮ ከተማሪዎቻችንም አናጣውም ነበር”ብለው እንደመለሱ ሰማን፡፡

ለስልጣን ኮረቻ ያበቃው ጎረምሳ ትውልድም ከስድብና ተግሳፅ አልተረፈም፡፡ በተደጋጋሚ፣ ”ይህ የናቱን መቀነት እሚፈታ ትውልድ“ ሲባል አድምጧል፡፡ ወጣቱ ’የስራ ዕድልና የተጠቃሚነት መብት’ ሲል የተዋደቀላቸው ጥያቄዎች በጣቶች መካከል አንድባንድ ሾልከው እየወደቁ አሁን በፍቅርና መደመር አረሞች ተወረው ተረስተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ህዝብ ሲደመር ቢከርም እኔን አያክልም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አንድንዴ ራሳቸውን እሚያዩት እንደንጉሥ ነው፡፡ ይህንን ራሳቸው ነግረውናል። እንደውምእንደማንኛውም ንጉሥ ሳይሆን ለተለየ ተልዕኮ እንደተጠሩ ዓይነት ነው። አልፎ አልፎ ከአንደበታቸው አምልጦ ከሚሰማው አነጋገር መገንዘብ እሚቻለው ምናልባት ከአገር በላይም እንደሆኑ ይሰማቸው ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ያለፈው ሰሙን በአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ጊዜያቸውንና ቀልባቸውን በውል መድበው ሳይሆን እንደነገሩ፣ እንደተራ ፍፃሜ ያነሱት የኢንጅነር ስመኘውን የመገደል ዜና በዚህ መልክ ነበር፤ “ሰው በጠራራ ፀሃይ የሚገደልባት አገር መሪ እንደመሆን እሚያሳፍር ነገር የለም፡፡”

ይህ አባባል በጣም ሲበዛ ነውር ነው፡፡ የኢንጅነሩ መገደል እንደተራ የህልፈት ፍፃሜ እሚታይ ሳይሆን ትልቅ አገራዊ አንድምታ ያለው ክስተት ነው፡፡ በመሪ አንደበት መነገር ያለበትም በሚመጥነው አገራዊ ሚዛን ብቻ ነው፡፡ ይኸኛው ግን ከዛም ይከፋል፡፡ ጠ/ሚ/ር ዓቢይ የታያቸው እሳቸው እሚመሩዋት አገር አንሳ መገኘቷ እንዴት እንዳሳፈራቸው ነው፡፡ በአባባላቸው ቃና ውስጥ ያለው እምነት “ይህች አገር ማፈርያ ናት፣ አትመጥነኝም” እሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሳቸው ማፈር ሲኖርባት እሳቸው በኢትዮጵያ የማፈራቸው ነገር “እኔ ካገር በላይ ነኝ” የሚል የውስጥ ግለ-ምስል ብዥታ የፈጠረው ይሆናል፡፡

 

የሁለት ሰዎች ሽንገላ

ይህ ህዝብ ሁለት መሪዎች ’’ወርቅ ነህ’’ ሲሉ ነግረውታል፡፡ ትግራይ ግን አሁን ከኢትዮጵያ በሃብት ድልድል እምትበልጠው ሶስት ክልሎችን ብቻ ነው። በድህነት ከአገራዊ አማካይ መቶኛ ወደ አምስት ነጥብ በታች ናት። ትግራይ በ1953 በቀንድና የጋማ ከብት ሃብት ከኢትዮጵያ አንደና ነበረች። በነነጋድራሥ ገብረህይወት ባይከዳኝ አጼ ምኒሊክና ኢትዮጵያ በሚል መጽሃፋቸው የኢትዮጰያውያን ግብር አከፋፈል እንዳሃብታቸው መጠን እንጂ ለሁሉም እኩል አይሁን በሚል ምክራቸው እንዲህ እሚል ይገኝበታል፡ “አሁን በጌምድር፣ ጎጃም፣ ወሎ… ብዙ ብር አይገኝበትም። ስለዚህ እንደሃብታሞቹ ሸዋና ትግሬ ሊገብሩ አይቻላቸውም።”ከዛ ወዲህ ግን ቁልቁል ሄደች። የጠመኔ በጀት እንኳ አትሸፍንም እምትባል ክፍለ ሀገር ሆነች።

በህወሓት-ኢህአዴግ ኢትዮጰያ ረዥሙ ያልተቋረጠ ሰላም እንዲሁም ያልተቋረጠ እድገት ያገኘችበት ዘመን ነው። የኢትዮጵያ ድህነት መቶኛ ስሌት በከፍተኛ መጠን ቀንሷል። ኢኮኖሚው ደግሞ ከምስራቅ አፍሪካ ትልቁ፣ ከሰሃራ በታች ካሉት የአፍሪካ አገራትም አራተኛ ተቀምጧል። ይህ ትልቅ ውጤት ነው። ትግራይግን በንፅፅር ከኢትዮጵያ ክልሎችም ከግርጌ ናት። ህወሓት፣መሃል አገር በመገንባት ለሁሉም እሚዳረስ የልማት ትሩፋት አመጣለሁ በሚል ትግራይ ላይ ያተኮረ ትልቅ ሥራ አልሰራም። ስልጣን ተቆጣጥሮ ሲያበቃ ግን ፖለቲካውን (ትርክቱን) ሳይቆጣጠር ቀረና አሁን የከፈለው መስዋእትነት ሁሉ፣ የሰራው ቁምነገር በሙሉ በአደባባይ “የ27 ዓመታት ቆሻሻ” የሚልታግ ተለጥፎበት አየን።

 

ዓቢይና ’’ጅቦቹ’’!

ጠ/ሚ/ር መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ያልተመጣጠነ ስልጣን በህወሓት እጅ ነው ሲባል ነበር። ነገሩም ያሰኛል። ምክንያቱም ቁልፍ ስልጣኖች በጠ/ሚ/ሩ ስር ስለሆኑና ጠ/ሚ/ር መለስ ደግሞ ከህወሓት ስለነበሩ። እሳቸው ከሞቱና ቦታው በደኢህዴኑ ኃይለማርያም ከተያዘ በኋላም ሃሜቱ ቀጠለ። ይህም ምክንያት ነበረው። የደህንነቱና የመከለከያው የበላይ ሹመኞች ከህወሓት ወይም ከትግራይ ስለነበሩ። ጠ/ሚ/ር ዓቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ “በፍፁም አያሰሩትም” እሚል አስተያየት በዛ። ይህ ማለት ስልጣን መልቀቅ አይታሰብም፣ ስልጣናቸው ሳይለቁም ቢሆን “አይተባበሩትም፣ አያግዙትም” ወይም ደግሞ ጭራሽ “ዕንቅፋት ይሆናሉ” የሚል ነጥብ አለው።

አዲሱ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዓቢይ የህወሓትን ሰዎች አንድባንድ ሲያባርሯቸው ግን አንድም የተሰማ ኮሽታ አልነበረም። ህወሓት ፍጹም የበላይነቱን ያለማንገራገር ለቋል። ይህ እምብዛም የተለመደ ነገር አይደለም። ፍጹም የበላይነት ነበረው እየተባለ የነበረውን ድርጅት የአዲስ መሪ ትእዛዞችንና ውሳኔዎችን በማክበር ራሱን ለማሳነስ ተባባሪ ሆኖ መገኘት አዲስ ነገር ነው። ይሁንና ስልጣን በመጥቅለሉ በብዙ የሃሜት ዱላዎች ሲመታ የነበረው ህወሓት፣ ስልጣኖቹን ያለማንገራገርና ያለማቅማማት አንድባንድ ሲያስረክብም “የቀን ጅቦች” በሚል የማጥላላት ዱላ መመታቱን ቀጠለ እንጂ ህግ አክባሪነቱን ወይም ለአገር አሳቢነቱን አልታየለትም።

ሰኔ 16 የ”እንድመርና ዓቢይን እንደግፍ” ሰልፍ ተጠራ። ሰልፉ የተጠነሰሰውም የተደራጀውም ህወሓትን በሚጠሉ ግለሰቦችና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ሰዎች ነበር። በሰልፉ ዕለት የቦንቡ አደጋ አጋጥሞ ሰዎች ተጎዱ። ጠ/ሚ/ሩ የተጣራ መረጃ ሳይዙ “የቀን ጅቦች ሞያን ተገን አድርገው” በማለት ጣታቸውን ወደ አንድ በመቀሰርተከታዮቻቸውንአቅጣጫ ጠቆሙ። ወዲያውም በወልዲያ፣ በባቲና በሌሎች አካባቢዎች በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር ጥቃቶች ደረሱ። እንጅነር ስመኘው ላይ በተፈጸመው ግዲያ ሳቢያም፣ “የቀን ጅቦች ናቸው የሚል ወሬ በመነዛቱ” ከዚያ ተከትሎ ጣና በለስ ላይ ሶስት የትግራይ ተወላጆች በድንጋይ ተቀጥቅጠው ተገደሉ። “ለምን የመስቀል አደባባዩ የፍንዳታው ማጣራት ውጤት ተሎ ለህዝብ አይገለፅም” ተብለው የተጠየቁት ጠ/ሚ/ር ዓቢይ፣ “ከደሙ ንጹህ ነን ብላቹህ፣ እፎይ ለማለት ከሆነ አይቻልም” ብለው እርፍ!

ነገሩ እጅግ ገራሚ ነው። የኦሮሞያ ሰው ሆኖ ኦሮሚያን በማንደድና በማውደም በብጥብጥ መሰላል ወደ ስልጣን የመጣ ሰው፣ የኦህዴድ ታጋይና አመራር ሆኖ ሳለ የኦህዴድ መርሆችን ቅርጥፍጥፍ አድርጎ የበላ ሰው፣ በኢህአዴግ አመራሮች ተመርጦ የኢህአዴግ ሊቀመንበር የሆነ ሰው ኢህአዴግን የራሱን ግንባር ሲያፈርስ፣ ስለኢትዮጵያ ፍቅርና መደመር አውርቶ እማያባራ ጠ/ሚ/ር፣ የኢትዮጵያ ትልቁ አሰባሳቢና እንቁ ፕሮጀክት የሆነውን የህዳሴን ግድብ በአንደበቱ ለማንሳት እሚጠየፍ፣ በውሸት መረጃ ጉዳት እየደረሰብን ነውነ እውነቱ ይነገር ለሚል አቤቱታም “አታስቡት” የሚል ምላሽ እሚሰጥ መሪ ሲኖረን ከግርምት በላይም የምጽአት ምልክት ነው።

 

ዓቢይና ዓባይ

ጠ/ሚ/ር ዓቢይ ስለ ዓቢይ እንጂ ስለዓባይ ሲያወሩ አንድም ቀን አልተደመጡም። ከቀረጻ ውጭ በሆነው ዝግ ስብሰባ ላይ እዛው በተሳተፉ ሰዎች ጠ/ሚ/ሩ አሉት እየተባለ የተነገረው፣ “ግድቡ በ10 ዓመትም አያልቅም” የሚል ቀፋፊ አነጋገር ነው። እውነት ብለውት ከሆነ፣ 65% ላይ የደረሰ፣ መላእ ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት መንፈስ እየተረባረቡበት ያለን እጅግ ውድ አገራዊ ፕሮጅክት ላይ እንዲህ ዓይነት የጠላት ዓይነት አነጋገር ከአገር መሪ የማይጠበቅ በመሆኑ እንግዳ ነገር ነው።

የእንቁ ኢትዮጵያዊ እንጅነር ስመኘው አሟሟት በጣም ያበሳጫል። በአንድ ሰው ላይ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ የተተኮሰ ጥይት ነው። ግድያው ጂኦፖለቲካዊ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ከጥቂት ቀናት በፊት ስለጉዳዩ አየርላንዳዊውና ታዋቂው የአለም አቀፍ ፖለቲካ ተንታኝ ፊንያን ካኒንግሃም “Politics Shadow Ethiopia’s Foul Murder’’ ሲል ባስነበበው ፅሁፉ ከኢንጅነሩ መገደል በስተጀርባ እሚጠረጠሩት ህቡአን እጆች እነማን እንደሆኑ ያመላክታል። ግድያው እንደተሰማ ጠ/ሚ/ር ዓቢይ ለጉብኝት አሜሪካን አገር እየደረሱ ነበር። ስለሁኔታው እንደሰሙ በረዳታቸው በአቶ ፍጹም አረጋ “ጠ/ሚ/ሩ ማዘናቸውን ገለፁ” ከሚል አጭር የትዊተር መልእክት በቀር ያሉት ነገር የለም። አንዳንዶቹ ደጎች ጠ/ሚ/ሩ ጉዟቸውን አቋርጠው ህዝባቸውን ለማጽናናት ይመለሳሉ ብለው ገምተው ነበር። የሃዘን ቀን ይታወጅ ይሆናልም ብለው አስበው ነበር። ብዙ የተደከመበትና እሳቸው ጠ/ሚ/ራችንም አብዝተው የጓጉለት ጉብኝትና ድግስ፣ አገር ብትጠቃም ባትጠቃም፣ ብታዝንም ባታዝንም መቀጠል ነበረበት። ቀጠለ።

ከኃይማኖት አባቶች የእርቅ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ባሰሙበት ጊዜ ሃዘናቸው በመግለጽ ይጀምሩና በጉዳዩ ዙርያ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያበረታ ቃል ይናገራሉ ብለን ጠብቀን ነበር። ጭራሽ ሳያነሱት ቀሩ። ቀጥሎ በሁለተኛው ቀን ከፖለቲካ ሰዎች ጋር ሌላ መድረክ ነበራቸው። በንግግር የከፈቱትም ራሳቸው ናቸው። ስለ እንጅነሩ ግድያና ስላጋጠመው ሃገራዊ ሃዘን ምንም ሳይሉ አለፉት። በጥያቄና መልስ ጊዜ “ዛሬ አንድ እንጅነር ስመኘው የተባለ…“ በሚል ሟቹ በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ያሉ ሰው ሳይሆኑ ተራ ዜጋ እንደሆኑ አድርገው ፍጻሜው በአንዲት ዓረፍተ ነገር ጨርፈውት አለፉ። በሌላ ቀጣይ እስላሞ ወገኖቻችን ባዘጋጁትና እስልምናን አረቦች ስለማስተማር በደሰኮሩበት መድረክ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መሪ መሆን እንደሚያሳፍራቸው ለመግለፅ ያህል ጉዳዩን አነሱት። የእንጅነሩ ግድያ ከግድቡ ጋር የተያያዘ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች የግድቡን እጣ ፈንታ ለመወሰን በአደባባይ የግድቡን ስራ አስፈፃሚ እስከመግደል የመሰላቸውን የማኮላሻ እርምጃ ሲወስዱ ኢንጅነርዋን የተገደለባት አገር መሪ ደግሞ “የኢትዮጵያ መሪ መሆን ያሳፍራል” ማለታቸው እሚሰጠው አንድምታ ምን ይሆን?!

ላለመታማትና ይሉኝታ በሚመስል፣ ብዙ ህዝብ በተገኘበትና ከታማኝ ጋር በረዥሙ በተቃቀፉበት መድረክ ላይ “ኢንጅነር ስመኘውን መግደል ይቻላል፣ የህዳሴን ግድብ ማቆም ግን አይቻልም” የሚል ዓረፍተ ነገር አስገብተው ነበር። በያንዳንዱ ዓረፍተነገር ማሳረጊያ ከፍተኛ ጭብጨባ ሲሰሙ የነበሩት ጠ/ሚ/ር ዓቢይ፣ ይህችኛዋን ሲናገሩ የተለመደው ጭብጨባና ዕልልታ ስላልሰሙ ግራ ገባቸው። እንዴ ጭራሽ! ይደገም ሳይባሉ፣ ደግመው አነበብዋት። ከበፊቱ ትንሽ ሻል ያለ ነገር ሰሙና በዛው አለፍዋት። ጥሩ መገጣጠም ነው። እሳቸውም ለማለት ያህል ነበር ያሉት፣ ታዳሚውም ገብቶታል።

ከዚያ በኋላበሜኔሶታው ስብሰባ ላይ ከሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ “የምርመራው ውጤት ለምን ለህዝብ ግልጽ አይደረግም” ተብለው ሲጠየቁ ነበር ጉዳዩን ያነሱት። እሳቸው ሲመልሱ፣ “እናንተን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ከሆነ እሚነገረው በፍጹም አታስቡት” አሉ። ይህን ካሉ በኋላም፣ “መግደል ማለት ማቀድ፣ ማማከር፣ ፋይናንስ ማድረግ፣ ተስፋ መስጠት ጭምር እንጂ መወርወር ብቻ አይደለም” አሉ። ቀጥለውም፣ “የሰኔ 16ቱስ ነገርናቹህ፣ የእንጅነር ስመኘውስ ምን ልንላቹህ ነው?” ሲሉ በጥያቄ መልክ ደመደሙ።

ህም! ይህ በጣም አስደማሚ ንግግር ነው። “እናንተ” እያሉ እሚገልፅዋቸው ሰዎች ያው ሁሌም የቀን ጅቦች እያሉ እሚገልፅዋቸውን የህወሓት ሰዎችን ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። እሳቸውም ብዙ ለመሸፋፈን አልሞከሩም፤ ጥያቄ ያቀረበችላቸውንም ሰው ከትግራይ መሆንዋን ጠቀሰው ነበር መመለስ የጀመሩት።ስለዚህ ማንን ማለታቸው እንደሆነአያሻማም። “የእንጅነር ስመኘውስ ምን ልንላቹህ ነው?” እምትለዋ አባባል ግን ውስጠ ወይራ ናት። ከሰኔ 16ቱ ነጻ ብትሆኑም፣ ይኸኛው ደሞ አለ፣ እንደማለት።

“መግደል ማለት ማቀድ፣ ማማከር፣ ፋይናንስ ማድረግ፣ ተስፋ መስጠት ጭምር እንጂ መወርወር ብቻ አይደለም” ብለው ካሉት ግን አንዲት እምትረብሽ ሃረግ አለች- “ተስፋ መስጠት” እምትል። ዕቅድ ላይ የተሳተፈ፣ በምክርም በገንዘብም ያገዘ ሰው ወይም አካል ካለ፣ አዎ- በትክክል የድርጊቱም ባለቤት ነው። “ተስፋ መስጠት” የግድያ አካል ስለመደረጉ ወይም ብግብረ-አበርነት ሊታይ ስለመቻሉ ግን ከዚህ በፊት ሰምቼ አላውቅም። የሰኔ 16ቱ ቦምብ ወርዋሪ ግን፣ ያንን ድርጊት እሚያስፈጽም ምን ዓይነት ተስፋ ሊሰጠው ይችላል? ከማን? ከማን እሚለው ለመመለስ የቀለለ ነው፤ ምክንያቱም ከሳሹ ጠ/ሚ/ር ዓቢይ ጥርጣሬያቸውን ስለነገሩን። በሳቸው አተያይ፣ ተስፋ ሰጪው የትግራይ ሰው ወይም ህወሓት ሊሆን ነው። ታድያ ህወሓት ብምርጫና በጓድነት እንደ መሪው የተቀበለውን ሰው ለማስፈራራት ወይም ለማስገደል አስቦ ቦምብ እሚወረውረለትን ሰው “ተስፋ ሰጥቶ ያግባባል” ብሎ ማሰብ የማይመስል ነው። እንዲያው ቢቸግር ብለን እንለፈው።

ነገር ግን ቃሉ ዝም ብሎ የተባለና ትርጉም አልባ ላይሆን ይችላል። አንደበቶች በየትኛውም ደረጃ ተነግረው ስሜት ካልሰጡን ረብ የለሽ ስለሆኑ አይደሉም። ከምን ዓይነት ሁኔታና እውነታ እንደተቀዱ ላናውቅ እንችላለን። የመጡበት ቁምነገር ግን ይኖራል። በስነ ልቦና ጠበብቶች መስፈርት ብዙውን ጊዜ ስለራሳችን ነው እምናወራው። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግብጽ ሄደው በነበረ ጊዜ “ግብጽን አልጎዳም ብለህ ‘ወላሂ ብለህ’ መሃላ ፈጽም” ሲባሉም ሲምሉም አይተናል። ያልሰማነውና ያላየነው ነገርም ይኖራል። አሁን እንጅነሩ ከተገደሉ በኋላ ዝምታ በዝቷል። እንጅነር ስመኘው ጭራሽኑእየተረሱም ይመስላል። አገሪቷ በጉብኝቶች ብዛትና በግንቦች መፍረስ ዜናዎች ተጠምዳለች። ግንቡን ማፍረስ እስከ ግድቡ ማፍረስ አይደርስ እንደሆነ ከዚህ ወዲያ ግልጽ እየሆነ ይሄዳል። የግድያውም ዓላማ ግን ግድቡን ለመግደል ወይም ለማዝግየት ከመሆን አያልፍም። እንጅነሩ ሲገደሉ ፕሮጀክቱን የማስፈፀምና የኢትዮጰያውያን አቅም የማስተባበር በአጠቃላይ የግድቡ እጣ ፈንታና ሙሉ ሃላፊነት በጠ/ሚ/ሩ እጅ መውደቁ ግልጽ ነው። እናማ ይህች “ተስፋ መስጠት” እምትል ቃል ግድያውን እንዲፈጸም ምክንያት ሆና እንዳይሆን እጅጉን እንባንናለን።

 

ፍቅርና ጦር

ኢትዮጵያ በጣምአሳዛኝ ወቅት ላይ ነው ያለችው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ባጠቃላይ ግራ በሚያጋባ የደመራ መደናበር ውስጥ ገብተዋል። በአሁኑ ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ ያልገባ የፖለቲካ ደላላ የለም። ኢትዮጵያን እሚዘውራት ማን ለማን ጥቅም እንደሆነ መለየት አልተቻለም። ስርዓት ያለው ነገር ጠፍቷል። ህገ መንግስቱ በራሳቸው በጠ/ሚ/ሩም፣ የልብ ልብ በተሰማቸው ሌሎች ኃይሎችም ግራና ቀኝ እየተጣሰ ነው። የአሁኑ በሶማሊብሄራዊ ክልል ላይ የተፈጸመው የጀብድ እርምጃ እጅግአሳዛኝ ኑባሬ ነው።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የተፈፀመው ወንጀል በሁለቱ በኩል ነው፡፡ መጤዎች በሚልና ተነክተናል በሚል በሰው፣ በንብረትና በአብያተ እምነቶች ላይ የተፈፀመው ጥፋት አሳፋሪና ፈፅሞ እሚስተባበል አይደለም፡፡ የክልሉ ፕረዚዳንትም ከዚሁ ጥፋት ነጻ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ነገር ግን በፈደራል መንግስት የተወሰደው እርምጃም አደገኛና ቅሌት ያለበት ነው፡፡ ጉዳዩ ከተራ ቅሌትም በላይ ሊታይ ይገባል። በዚህ ደረጃ ህግ ማፍረስ ማለት አገር ማፍረስ ማለት መሆኑን መታወቅ አለበት፡፡ ይህንን ተግባር፥ የፈደሬሽን ም/ቤት፣ ሁሉም ክልሎች፣ የህገመንግስትና የፈደራል ተቋማት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያወግዙት እሚገባ ጉዳይ ነው። ከዚህ አንጻር የትግራይ መንግስት የሰጠው መግለጫ አበረታችና ለሌሎች በጎ ምሳሌ ነው።ይህን እምንለው ለሰማሌ ወንድሞቻችን እህቶቻችን ከማሰብ ብቻ አይደለም። ወይም ለህግና ህገ መንገስቱ ከመቆርቆር አኳያ አይደለም።የኢትዮጵያንም ህልውና በቀጥታ ሊፈታተን የሚችል አጉል ውሳኔና እርምጃ ስለሚሆን ነው።

ዶ/ር ዓቢይ መታወቅ የጀመሩት አጋሮ አካባቢ የሃይማኖት ግጭት በተነሳ ወቅትና መከከለኛ ካድሬ በነበሩበት ጊዜ ነበር። ኢህአዴግ ሊያስታርቁ እንደላካቸው መልካም ውጤት አስገኙ። ከፍተኛ እውቅናና ምስጋናም ሸመቱበት። ወዲያውም ከበላይ አመራሮች ጋር ጥሩ ትውውቅ ፈጠሩ። ለበለጠ ሃላፊነት የታጩትም ከዚያ በኋላ ነው። ታዲያ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከግጭቶች ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል ያኔ ጀምሮ የተከሰተላቸው ይመስላል። የኦሮሚያውን ለዓመታት የዘለቀ ብጥብጥ ለጠ/ሚ/ርነት አበቃቸው። የደቡቡ የአዋሳ ግጭት የድርጅቱን ሊቀመንበርና የዞኖቹ አመራሮች አባርረው ሌሎች የራሳቸው ሰዎች ለመተካት አስቻላቸው። አፈ ጉባኤ ሙፈርያትም የቲምለማ አባል ለመሆን በቁ። የአዲስ አበባው የቦንብ ፍንዳታ የፖሊስ መዋቅሩ ሙሉለሙሉ ለመቆጣጠር ሰሩበት። የሶምሌውም ተመሳሳይ ነው። ፎረሙላው ግልፅ ይመስላል፤ ስለ መደመር መደስኮር፣ ግጭት መፍጠር፣ ጣልቃ መግባት።

 

እኛም አውቀናል

አሁን ’’የትግራይ ህዝብና ህወሓት ለየቅል ናችው’’ ያሉዋት ተደጋጋሚ መልእክት በገራገር ስትታይ ’’እና ታድያ፣ የት አገር ነው ድርጅትና ህዝብ አንድ ሆነው እሚያውቁት!’’ ታሰኛለች፡፡ ኦህዴድስ እንደዛ አይደለም እንዴ! ብዙ አያጋጥምም እነጂ ድርጅትና ህዝብ አንድ የሆኑ ጊዜማ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ’’ህወሓትን ለመምታት ስትሉ የትግራይን ህዝብን ደርባቹህ አትምቱት’’ ለማለት ያህል ያሉት ይመስላል፡፡ ነገሩም እውነት ነው፤ ህወሓትን ነጥላቹህ ምቱ ለማለት ነው፡፡

ዋናው መልእክት ግን ለመቺዎቹ አልነበርም፣ ለትግራይ ህዝብ እንጂ፡፡ ከህወሓት ጋር ተደርበህ አትገኝ፣ ራስህን ለይ፡ እንደማለት፡፡ አሜሪካን አገር በሄዱ ጊዜ ደግሞ ሙሰሊም ወገኖቻችንን ሰብስበው ’’እየሩሳሌም እንኳን መስጊድ ተሰርቶ እንዴት አክሱም አይሰራም’’ ሲሉ እሳት ቆስቁሰዋል፡፡ ኢስላም ኢንስቲትዩትለማቋቋምና ዲን ለማስፋፋት የኤሜሬቱን አሚር የገንዘብ እርዳታ ጠይቂያለሁም ብለዋል፡፡ እኔ እምለው፣ ህገ መንግስቱ ሃይማኖትና መንግሥት… እሚለው ነገር ቀረ ማለት ነው ወይ?

ጭራሽ ደግሞ ዋናው የዋሂብሰቶች አክራሪ የጀሃዳዊ ሰይፍ ዋና አቀንቃኝ የሆኑትንና ለ23 ዓመታት ይህንን ሥራቸውን ከዋናዋ አገር ከሳውዲ ዓረቢያ ሆነው ሲከውኑ ነበር፡፡ ሰሙኑን ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ ሼክ ሠይድ ይባላሉ፡፡ አሁን እንግዲህ ደጋፊ ባለበትና ከልካይ በሌለበት ወሃቢዝም የማስፋፋት ቢዝነሳቸውን ያጣጡፋሉ፡፡ ጃዋርም በጀግና አቀባበል አገር ቤት ገብቷል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ጥንቱ የኢማም ግራኝ ጊዜ መልሰን የኩሽና የእስላሞች አገር እንመሰርታለን የሚል እምነት ያራምዳል፡፡ ይህን በግልፅ የተናገረበት ቪድዮ እስከ አሁን ኢንተርኔት ላይ ተለጥፎ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ የምር ወዴት እየሄደች ነው?

 

የተፈራው እርግማን

ጠ/ሚ/ሩ ልደግፋቸው እሚችሉ ዓይነት ሰው ሊሆኑ ይችሉ ነበር። በተለይም ኢህአዴግ ብዙ ነገሮች ማስተካከል አቅተውት እግሩን ማንሳት ባቃተው ጊዜ የመጡ ሰው በመሆናቸው። አንዳንድ ድፍረታቸውም ጥሩ ሊጠቅሙ ይችል ነበር። ግን አመጣጣቸውም አጀንዳቸውም ብዙ የውጭ እጅ እጅ እሚል ነገር ያለበት ነው። ካልሆነም ራሳቸውን ግልጽ ማድረግና እኛን ማረጋጋት አለባቸው። “ቲምለማ” የሚል ዘንቢል እያንጠለጠሉ መዞር ሳይሆን በፍጥነት አግባብ ያለው የወልና ተቋማዊ አሰራር ማበጀት አለባቸው። ምንም የተለየ ብቃትና እውቀት ሳይኖራቸው (እንደውም ከተፈለገው በታች ሆነው ሳለ) “እኔ፣ እኔ” የሚለውን ግለ-ተኮር አካሄዳቸው የሚጠላና ጎጂ ነው። ጠቅላላ የአገሪቱ ተቋሞችና ካቢኔው እንዳለ ወደ “ቲም ለማ”ነት ኮርኩመው በማሳነስራሳቸውን አግዝፈዋል። ሁለተኛም አገሪቱ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ነበረች። ከመቸውም ጊዜ በላይ በብስለት የጎዳላትን እየሞላ አስተካክሎ እሚመራት እንጂ የራሴን ዓለም ልፍጠር በሚል ወደማይታወቅ ትርምስ እሚወስዳት ጀብደኛ እምትፈልግበት ጊዜ አይደለም።

አሁን መልክ ያጣ ነገር በዛ። እስቲ አስቡት፡ ኢህአዴግን አፍርሶ -ግንቦት ሰባትን አወድሶ፤ ኢሳያስን አምኖ - ደበረጽዮንን አግልሎ፤ ታማኝን አቅፎ - እንጅነር ስመኝን ተጠይፎ፤  ጃዋርን በፍቅር፣ አብዲ ኢለን በጦር…ምን እሚሉት ዝብርቅርቅ ያለ ነገር ነው።

አሌክስ ፔሪ የተባለ የታይም መጽሄት ታዋቂ ጋዜጠኛ ከቀድሞ ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር የቃለ መጠይቅ ቆይታ አድርጎ ነበር። አሁን አስር ዓመት ገደማ ሆኖታል። ጋዜጠኛው ሌሊት እንቅፍ እሚከለክልህ ጉዳይ ካለ ምንድነ እሚል ጥያቄ ይሰነዝራል። የሳቸውም መልስ፣

ሁሌም ፍርሃት ነው። ፍርሃቴም ይህች ከሺ ዓመት በፊት ታላቅ አገር የነበረች አገራችን ከዚያ በኋላ በነበሩት አንድ ሺ ዓመታት የቁልቁለት መንገድ ጀመረች። የቁልቁለቱ ውድቀት ማሳረጊያም ህዝቦቿ በሚልዮኖች  ሲራቡና ሲቀጠፉ ማየት ሆነ። ከዚያም በላይ የለየለት መንኮታኮትሊገጥማት በቋፍ ላይ ደርሳ ነበር። የአሁኑ ፍርሃት ግን ስለውድቀትና መንኮታኮት አይደለም። እኔ እማምነው ያንን ስጋት አልፈነዋል እሚል ነው። ፍርሃቴ ይች ከርቀት ጭልጭል ስትል መታየት የጀመረችው ብርሃን፣ የህዳሴ ብርሃን፣ የሆነ ቦታ ላይ በአንድ የተረገመሰውና የተረገመ ስህተት እልም ብላ ትጠፋብን ይሆን ወይ እሚል ፍርሃት ነው። ህዳሴው ገና ጠንቶ የቆመ ነገር አይደለም። ገና ትንሽ ጊዜ እሚፈልግ ተሰባሪ ነው። ስለዚህ በዚህ ጊዜ ያለኝ ፍርሃት የተስፋ ፍርሃት ነው። ይህ ሚልዮኔም እንደሁለተኛው መጥፎ ከሚሆንብን ይልቅ እንደ መጀመርያው ጥሩ እንዲሆንልን ከሚል በጎ ተስፋ የሚወለድ ፍርሃት ነው።

It has always been fear, a fear that this great nation, which was great thousand years ago but embarked a downward spiral for one thousand years, and reached its nadir when millions of people were starving and dying, may be on the verge of total collapse. Now, it is not a fear of collapse. I believe we are beyond that. It is the fear that the light which is beginning to flicker, the light of a renewal, an Ethiopian renaissance, that this light might be deemed by some bloody mistake by someone, somewhere. This (renaissance) is still fragile, a few shoots (which may need time to be more robust.) At the moment it is fear born out of hope that this new millennium will be as good as the first one and not as bad as the second one.

ብቻ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የፈሩት ሰውና ወቅት እያየን እነዳይሆን!

ይቀጥላል…

አሸናፊአ. (ashenafiandarge18@gmail.com)

Back to Front Page