Back to Front Page


Share This Article!
Share
ታጋይ እንጂ ትግልና ለውጥ አይሞቱም

ታጋይ እንጂ ትግልና ለውጥ አይሞቱም

አባ-ዲዱ ቢሊሳ 07-06-18

በኢትዮጵያ እመርታዊ የፖለቲካ መሻሻል እየተካሄደ ይገኛል። ይህ የለውጥ ሂደት ድንገት እንመብረቅ የወረደ ሳይሆን ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት የተፈጠሩና እየተካረሩ የሄዱ ቅራኔዎች ውጤት ነው። ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አብዮታዊ ለውጦችና ድሎች መገኘታቸው ታሪክ ሲያወሳው የሚኖረው ድል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኢፌዴሪ መንግስት ከአፈጻጸም የመነጩ ጉልህ ውስንነቶች የነበሩበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው።

በኢኮኖሚው ዘርፍ ከአንድ አስርት ተኩል ዓመታት በላይ ተከታታይ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል። ይሁን እንጂ ይህን እድገት ሁሉም ዜጎች ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳይ ክፍተት ታይቷል። የኢኮኖሚ እድገቱ በልማት የተደገፈ አልነበረም። በእድገቱ የተፈጠረው ሃብት የአንበሳ ድርሻ ለጥቂቶች ሲደርስ የተቀረው ህዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል ማለት ይቻላል። ይህም በተለይ በገጠርና በከተሞች በተንሰራፋ የስራ አጥነት ችግር በይፋ ታይቷል። ይህ ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል በይፋ የተፈቀደ ከሚመስለው የህዝብና የመንግስት ሃብት ዘረፋ፣ ሃይ ባይ ካጣ የመልካም አስተዳደር መጓደል ጋር ተዳምሮ የህዝብና የመንግስትን ግንኙነት አሻክሮታል።

Videos From Around The World

ከፖለቲካ አኳያ፣ ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ታሪካዊ ድሎች ቢመዘገቡም ጉድለቶች ግን አልጠፉም። በኢትዮጵያ የአመለካካት ነጻነት የተከበረው ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው። ከዚያ ቀደም ዜጎች የፈቀዱትን አመለካካት የመያዝ፣ የመግለጽና የማራመድ መብት አልነበራቸውም። ይህ በህግ ነበር የተከለከለው። ከደርግ ውድቀት በኋላ የአመለካከት ነጻነት በህገ መንግስት በመረጋገጡ በተለያየ አመለካካት የተደራጁና አመለካከታቸውን በይፋ የሚያራምዱ፣ በህዝብ ውክልና የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል።

በሃገሪቱ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ዋነኛ መገለጫ የሆነው የፕሬስ ነፃነትም የተረጋገጠው ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ነው። ከዚያ ቀድም ነጻ ፕሬስ አልነበረም። ሃሳብን የመግለጽ መብት ቀዳዳዎች የነበሩት መፅሃፍት፣ ተውኔት፣ ዘፈን ወዘተ ቢሆኑም በጥብቅ ቅድመ ምርመራ ውስጥ እንዲያልፉ ይደረግ ነበር። ከደርግ ውድቀት በኋላ ይህ ተሽሯል። አሁን የአመለካካትና አመለካከትን የመግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች በህገመንግስት ተረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ፣ ይህ ፖለቲካዊ ስኬት ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ እየፋፋ ከመሄድ ይልቅ እይቀጨጨ ሄዶ የመቀንጨር አደጋ ተጋርጦበታል። በሃገሪቱ ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዊች ቢኖሩም፣ የሃገሪቱ ትልቁ የፖለቲካ ስልጣን አካል በሆኑ የክልልና የፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች መቀመጫ የማግኘት እድላቸው ግን ወደመዘጋቱ ተቃርቧል። በ1987፣ 1992፣ 1997 ዓ/ም በተካሄዱ ምርጫዎች ከገዢው ፓርቲ ውጭ የሆኑ ግለሰቦችና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤቶች ውስጥ አነሰም በዛ ተሳትፎ ነበራቸው። ከዚህ በኋላ በተካሄደው በ2002 ዓ/ም አራተኛ ዙር ምርጫ ይህ ውክልና ወደ ሁለት ወረደ፤ አንድ የግል፣ አንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ ነበር መቀመጫ የማግኘት እድል የገጠማቸው። በ2007 ምርጫ ደግሞ የግል እጩዎችና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውክልና ምንም ሆነ። ይህ ከጊዜ ወደጊዜ እየጠበበ የሄደ የተለየ አመለካከት ውክልና የማጣት እድል በምንም መስፈርት  ጤናማ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም።

ይህ ሁኔታ ከሰላማዊ አማራጭ ውጭ የሆኑት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጉልበት እንዲያገኙ አድርጓል። ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከተፎካካሪነት ይልቅ ወደጽንፈኛ ተቃዋሚነት ገፍቷል። ከሰላማዊ መንገድ ውጭ የሆኑ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች፣ የመወከል እድል ያጡ በርካታ ዜጎችን ድጋፍ አገኙ። ህጋዊ የሆነ መደመጫ መንገድ ያጡት የተቃውሞ ድምጾች በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር በሚገኙ የግል ሚዲያዎች፣ እንዲሁም በውጭ ሃገራት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚያስተዳድሯቸው የመንግስታት ሚዲያዎች መደመጥ ጀመሩ። በኋላም ማንም ሃሳቡን በሚያቀርብባቸውና ሰፊ ተደራሽነት ባላቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች ይሰራጩ ያዙ። ህጋዊ መንገድ ያጡት እነዚህ ድምጾች ጣፍጠው ይደመጡ ጀመር። ይህ ለተቃውሞው እንቅስቃሴ ጉልበት ሰጠው። ከዚሁ ጋር ሰላማዊ ያልሆነ የተቃውሞ መንገድን የመረጡ ፖለቲከኞች፣ ደጋፊዎቻቸውና ሃሳባቸውን እንደወረደ ያስተጋቡ ሚዲያዎች ጋዜጠኞች በወንጀለኝነት እየተጠየቁ በገፍ እስር ቤት የሚገቡበት ሁኔታ ተፈጠረ።

እነዚህ ከላይ የተነሱት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች፣ ህዝቡና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአንድ ወገን፤ የኢፌዴሪ መንግስት፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና አጋሮቹ ደግሞ በሌላ ወገን ተሰልፈው እየተካረረ የሄደ ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል ። ይህ ቅራኔ መንግስትና ገዢው ፓርቲ በየወቅቱ በሚወስዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ሊረግብ ይችል የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ ይህ ባለመደረጉ በድንገት በህዝባዊ ተቃውሞነት ፈንድቶ ወጣ፤ በ2008 ዓ/ም መግቢያ ላይ። ይህ በኦሮሚያ በኋላም በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተቀጣጠለው የአደባባይ ተቃውሞ በቂና አሳማኝ ምክንያት ስለነበረው፤ እንዲሁም ቅራኔዎቹ ተብላለተው ከበሰሉ በኋላ የፈነዳ በመሆኑ ከዚያ ቀደም እንደነበረው በተለመደው ህግን የማስከበር የሃይል እርምጃ ሊበርድ አልቻለም።

ህዝባዊ ተቃውሞውን ለመቀልበስ የተወሰደው የሃይል እርምጃ የበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋቱ፣ አካል መጉደሉ ተቃውሞውን ከማብረድ ይልቅ ለተቃውሞ የሚያነሳሳ ምክንያት ሆኗል። ህጋዊው የፖለቲካ ሜዳ አላንቀሳቅስ ያላቸውና ሊያንቀሳቅስ አይችልም ብለው ያመኑ ፖለቲከኞች ይህን ህዝባዊ ተቃውሞ በተለያየ መንገድ በተለይ በማህበራዊ ኪዲያ ይመሩ ስለነበረ ትግሉን በሃይል እርምጃ መግታት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጠረ። በአጠቃላይ የሃይል እርምጃው ሰዎችን ከመግደልና ከማሰር ያለፈ የለውጥ ፍላጎቱንና ወደለውጥ የሚደረገውን ጉዞ ሊገታው አልቻለም። ሃይል ታጋይን እንጂ ትግልን ሊገድል አይችልምና።

ከዚህ በኋላ ባለፉ ሃያ ሰባት ዓመታት ሃገሪቱን ሲያስተዳደር የቆየው ኢህአዴግና የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞው ሃገሪቱን ለከፋ አደጋ ከማጋለጡ በፊት ጉልህና ተጨባጭ ለውጥ ማሳየት የሚችል እርምጃ ለመውሰድ ወሰኑ። ኢህአዴግ ራሱንና መንግስትን በጥልቀት መርምሮ ለማደስ የወሰነው ይሄኔ ነበር። ከተሃድሶው በኋላ መንግስትና ገዢው ፓርቲ የሚሰጡት ምላሽ ጉልህና ተጨባጭ መሆን ብቻ ሳይሆን በአዲስ አመራር የሚሰጥም መሆን ነበረበት። ገጽታው የተበላሸው የቀድሞ አመራር የሚሰጣቸው ምላሾች ተቀባይነት የማግኘት እድል አልነበራቸውም። እነዚህ ሁኔታዎች አዲስ የኢህአዴግና የመንግስት አመራሮች፣ ከጉልህና ተጨባጭ የለውጥ እርምጃዎች ጋር ወደሃላፊነት እንዲመጡ አድርጓል። አሁን ሃገሪቱን የሚመሩት የኢህአዴግ ሊቀመነበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከእነአመራር ቡድናቸው ወደስልጣን የመጡት በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ነው። በዶ/ር አብይ የሚመራው የተሃድሶ ውጤት የሆነው የፌደራልና የክልል አመራር ጉልህና ተጨባጭ የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።

በተለይ ከፖለቲካ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸውንና በክስ ሂደት ላይ የነበሩ ዜጎችን በይቅርታና በክስ ማቋረጥ እንዲለቀቁ ማድረግ ቀዳሚው ጉልህ እርምጃ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ በውጭ ሃገራት በተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ለሚገኙ ተቃዋሚ ሃይሎችና ሚዲያዎች የሰላም ጥሪ ተላልፏል ። በዚህ ጥሪ መሰረት በአንጋፋ የኦሮሞ ነጻነት ታጋዮች የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲ ግንባር (ኦዴግ) ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ ወደሃገርቤት በመመለስ ቀዳሚ ሆኗል። ከዚህ በኋላ በወታደራዊው ደርግ ኢሰፓ የስልጣን ዘመን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን የነበሩት ዶ/ር አምባሳደር ካሳ ከበደ፣ ሞረሽ ለወገኔ ድርጅት መሪ አቶ ተክሌ የሻው፣ የተባበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን የሚመሩት ጄነራል ሃይሉ ጎንፋና አባ-ናጋ ጃራ፣ በጄነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ አርነት ነጻነት ግንባር ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ለመቀላቀል ወደሃገር ቤት ገንብተዋል። መቀመጫውን በአሜሪካ አድርጎ የነበረው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ የተሰኘው መገናኛ ብዙሃንም በሃገር ቤት ቅርንጫፉን ከፍቷል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ ግንቦት 7 ከሰባት ዓመት በፊት የተወሰነባቸው የአሸባሪነት ፍርጃ እንዲነሳላቸው ወስኗል። ይህ ድርጅቶቹና አመራሮቹ በሃገር ቤት ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ምህረት የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል። የምህረት አሰጣጥና አፈጻጸም አዋጅም በመጽደቅ ሂደት ላይ ይገኛል። የህዝብ ሚዲያዎችም የመንግስት ቃል አቀባይነታቸውን ትተው ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ለህዝብ ማቅረብን እየተለማመዱ ነው።

እነዚህ ጉልህና ተጨባጭ የማሻሻያ እርምጃዎች በህዝቡ ዘንድ ተስፋን ፈጥረዋል። ይህ ተስፋ አሁን በህዝቡና በመንግስት መሃከል ለሚታየው መተማመን ምክንያት ሆኗል። ሰሞኑን በየአካባቢው በህዝብ አነሳሽነት የተካሄዱ የድጋፍ ትዕይንቶች የዚህ እውነት አስረጂዎች ናቸው። ይሁን እንጂ አሁን በሂደት ላይ ያለው ለውጥ ለሁሉም ወገን የሚመች ሊሆን አይችልም። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የነበሩና ከእነዚህ ጋር የጥቅም ግንኙነት የመሰረቱ ጥገኞች የማሻሻያ እርምጃው ጥቅማቸውን ከማስቀረት በተጨማሪ ለህግ ተጠያቂነት ስለሚያጋልጣቸው አስደንግጧቸዋል። በሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎችም ለውጡ ስጋት ሆኖባቸዋል።  በሃገሪቱ ያለውን ቅራኔ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በውጭ ሃገራት ፖለቲካ ሲነግዱ የነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦችም በለውጥ እርምጃው ጥቅማቸው ስለሚቀር እንደማይደሰቱ ግልጽ ነው።

እነዚህ ቡድኖችና ዜጎች ለውጡ የሚደናቀፍበትን ሁኔታ የመፍጠር ፍላጎት ያላቸው መሆኑም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ምናልባት በየአካባቢው ከሚነሱ ግጭቶች ጀርባ እጃቸው ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠርም ብልህነት ነው። በቅርቡ በአዲስ አበባ መንግስት ለወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎችና ለተገኙ ውጤቶች እውቅና ለመስጠትና ለማመስገን የተዘጋጀው ህዝባዊ ትዕይንት ላይ የለውጡ መሪ የሆኑት የኢህአዴግ ሊቀመነበርና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲሁም ሌሎች የለውጡ አመራሮች የነበሩበት መድረክ አቅራቢያ የተፈጸመው የቦብም ጥቃትም ለውጡን የማደናቀፍ ዓላማ ያለው መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ይህ የቦብም ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ግድያ የመፈጸም ዓላማ የነበረው ይመስላል።

ይሁን እንጂ ለውጡ ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ስላለው መሪዎችን በመግደል ብቻ ሊቀለበስ አይችልም። የኢህአዴግ ሊቀመነበርና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንና የአመራር ቡድናቸውን የመግደል እርምጃ ቢሳካም ለውጡን አያቆመውም። በህዝብ ተቀባይነት ያለውን የለውጥ ሂደት፣ የአመለካከት አራማጆቹን ወይም ታጋዮቹን በመግደል ብቻ ማደናቀፍ አይቻልም። የዓለምና የሃገራችን ታሪክ ይህን ያሳየናል። የውጭውን ትተን የሃገራችንን ታሪክ እንኳን በአስረጂነት እንመልከት። በ1960 ዎቹ በሃገሪቱ የነበረውን የብሄርና የመደብ ጭቆና በመቃወም ለእኩልነትና ለነጻነት የተደረጉትን ትግሎች ለመግታት በትግሉ መሪዎችና ታጋዮች ላይ የተፈጸሙትን ግድያዎች ትግሉን አልገቱትም፤ ድሉንም አላስቀሩትም።

ዘውዳዊው ስርአት የትግል መሪዎች የነበሩት ጥላሁን ግዛውና ዋለልኝ መኮንን ላይ የፈጸመው ግድያ ትግሉን አልገታውም። ደርግ በበርካታ የነጻነት ትግል መሪዎችና ታጋዮች ላይ የወሰደው የጅምላ ግድያ እርምጃ ትግሉን አልገታውም። አሁን በሃገሪቱ የሰፈነው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብትና ነጻነት የተረጋገጠበትን ፌደራላዊ ስርአት፣ ጉድለት ያለበት ቢሆንም ዴሞክራሲያዊ ስርአት የተሰዉት የትግል መሪዎችና ታጋዮች አመለካከት ወጤት ነው። እናም አሁንም የትግሉን ወይም የተጀመረውን የለውጥ ሂደት፣ መሪዎች በሚፈጸም ግድያ መግታት አይችልም። ታጋይ በአካል ይሞት እንደሆን እንጂ የለውጥ አመለካከት ስለማይሞት ጊዜውን ጠብቆ መሳካቱ አይቀሬ ነው።             

Back to Front Page