Back to Front Page


Share This Article!
Share
የሕግ ልጓም ጫፉ እስከየት ይሆን?!

         የሕግ ልጓም ጫፉ እስከየት ይሆን?!

                                  (በሙሐመድ ሁሴን)

09-21-18

 

የኢትዮጵያ ክብርም ሆነ ውርደት ያለው በዜጎቿ መዳፍ ውስጥ ነው፡፡ ትናንት ሀሳብን በነጻነት  መግለጽ ተሳነን፤ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጠፋ፤ የመልካም አስተዳደር ችግር በየዘርፉ ገነገነ፤ ሌብነት አሳፋሪነቱ ቀረ፤ ፍትሀዊ ዳኝነት ጠፋ እና መሰል ጥያቄዎች የአገሪቱ ዜጋ የብሶት ምንጭ ሆነው በአደባባይ ገንፍለዋል፡፡ በዚህም የሕግ የበላይነት ይከበር፤ ከዜጎች ላይ የጭቆና ቀንበር ይነሳ፤ ኢትዮጵያ በርካሾች አትረክስም፤ ታላቅ ህዝቦች ነን አንበታተንም፤ ልዩነቶቻችን ውበት ናቸው እና ሌላም ሌላም መፈክሮች ተይዘው ላንቃ እስኪነቃ ተዘምረዋል፡፡ ከዚህም በላይ ለዝናብ ውኃ የታሰቡት ቦዮች የበርካታ አፍላ ወጣት ደም አስርገዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ አበሳዎች ተከፍለው መንታ ተስፋን አምጠው መውለድ ችለዋል፡፡ በቆራጥ መሪ የለውጥ ጭላንጭል መታየት ይዘዋል፡፡ የሕግ የበላይነትና ሠላም ግን አሁንም በቀን ጅቦች ተበልተዋል፡፡

Videos From Around The World

የሕግ የበላይነት በዚች አገር ከምንም በፊት በቀዳሚነት ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ይህ መሠረት ባልያዘበት ሂደት ውስጥ ቀሪዎቹ ጅምር ተስፋዎች ጉም የመጨበጥ ያህል እምነት ያሳጣሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዙሪያና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ለዚህ አስረጂ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የለውጥ ጭላንጭሎቹ ባለቤት ህዝብ እንደሆነ ሁሉ የዚች አገር ሠላም እንዲረጋገጥም ባለቤቱ ህዝቡ ነው፡፡ መንግስትም የመሪነት ሚናውን መወጣት ግዴታው ነው፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የሚገኝ ወጣት ደሙን በየጎዳናው ረጭቶ ያመጣውን የለውጥ ተስፋ ውስኪ እየረጨ፣ ዶላር እየረጨ፣ አሉባልታ እየረጨ እናት አገሩን በማፍረስ ለተሰገሰገ ባንዳ በፍጹም አሳልፎ መስጠት የለበትም፡፡ ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ የአካባቢውን ሠላም ብቻም ሳይሆን ህይወቱን ከፍሎ ያመጣውን የዚች አገር የለውጥ መሪ ጭምር ቆቅ ሆኖ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡

በመላው አገሪቱ መነቃቃትን የፈጠሩት ትግሉ የወለዳቸው የለውጥ ተስፋዎች እንደተፈሉ የችግኝ ቡቃያዎች የሚታዩ ናቸው፡፡ የመለምለም አለያም የመክሰም እኩል ዕድል ባለቤቶች፡፡ በመሆኑም የአገራዊ ለውጡ ቀያሽና ባለቤት ህዝብ ነው፡፡ ባለቤቱ ህዝብ የሆነ ታላቅ አገራዊ የይቅርታ፣ የለውጥና በአንድነት ተደምሮ የመሻገር ራዕይ ደግሞ በምንም ተዓምር ሊገታ አይችልም፡፡ አልጋ በአልጋ ሊሆን እንደማይችልም እሙን ነው፡፡ ለውጥ በቀላሉ የሚቆናጠጡት ድል አይደለም፡፡ በአገሪቱ የሚስተዋሉት ደም አፋሳሽ ሴራዎች በህዝብና መንግስት ውህደት መታረም ካልቻሉ አላስፈላጊ ዋጋ ማስከፈለቸው አይቀርም፡፡  ጥቅማቸው የጨነገፈባቸውና በህዝብ ስም መመዝበሩ የነጠፈባቸው ጥቂት ኃይሎች ቀን ከሌት የሚጎነጉኑት ትርምስና ብጥብጥ የመፍጠር እኩይ ሴራ ከፖሊስና ከፀጥታ አካላት ዓይን ለጊዜው ሊደበቅ ይችል ይሆናል፡፡ ከህዝብ ዓይን ግን ለሰከንድ ተደብቆ የመቆየት አቅም የለውም፤ አይችልም። ምክንያቱም ህዝብ ሆደ ሰፊም፣ የነስር ዓይንም፣ የቆቅ ጆሮም ባለቤት ነውና፡፡

ኢትዮጵያ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ሁሌም የኢትዮጵያውያን የወል ሀብት ናት፡፡ የበርካታ ውብ ባህልና እሴት፣ ስብጥርና ውህድ፣ ውጤት የሆነው ህዝቦቿም ለእልፍ ዘመናት አብሮ ሲኖር አንዱ ለሌላው አለኝታ እንጂ ጠላት ሆኖ አያውቅም፡፡ ህዝቡ በወዳጅነት የቀረቡትን አሞናሙኖ በጠላትነት ያዩትን ትቢያ አስቅሞ መሸኘት ያውቅበታል፡፡ ለዚህ አስተማሪ አያሻውም፡፡ ወዳጁንም ሆነ ጠላቱን ከሱ በላይ ለይቶ የሚነግረው፣ አውቅልሃለሁ ባይ  የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጽኑ መሠረት ላይ ያረፈ ማንነት ያላቸውን የኢትዮጵያን ህዝቦች አበጣብጦ አገርን በዘላቂነት እበትናለሁ ብሎ ማሰብ ከቅዠት ያለፈ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ዝንፍ የማይል ሚዛን አለው፡፡ አገሩንና ህዝቡን ሥልጣኔ እንዲያቋድሱት፣ ክብርና ሞገስ እንዲያላብሱት በብረት ተፋልሞ በእጁ ያስገባውን ነጻነት ወዶና ፈቅዶ በእጁ የሰጣቸው መሪዎች ምን ያህል ርቀት ህዝቡንም አገሩንም ማራመድ እንደቻሉ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በአገርና በህዝብ ስም ምን ያህል አስከፊ በደልና ዝርፊያ ሲፈፀም እንደቆየ፣ እየተፈፀመ እንዳለ እና በቀጣይ ለመፈፀም የተነደፈን ስትራቴጂ ብቻ ሳይሆን በማን እንደሚከወን ጭምር ነጥሎ የሚያውቅ ነው፡፡ ህዝብ ከፈጣሪ በታች ሆደ ሰፊና ቻይ በመሆኑ እንጂ አገር ለማተራመስ፣ የፈጠራ የውሸት ማንነት በመንዛት ወንድም ከወንድሙ እንዲጋጭ እግራቸው እስኪቀጥን የሚኳትኑትን ጥቂት የጥፋት ተልዕኮ ሥምሪት ሰጭዎች መንጥሮ ማውጣት ይችላል፡፡ የማያዳግም ርምጃ መውሰድም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ህዝብ  ጥፋተኛ ከስህተቱ እንዲማር ዕድል ይሰጣል፡፡ ይህን በሳል እይታ አዕምሯቸው በህዝብ ሀብት የሰከሩ ግፈኛ ሆዳሞች ከአላዋቂነት ይቆጥሩታል፡፡ ከዚያም እልፍ ሲሉ በምን ያመጣል ሚዛን አሳንሰው ያዩታል፡፡ ነገር ግን ህዝብ አላዋቂ አይደለም፤ ፈጽሞ አይሆንምም፡፡ በምንም ዓይነት ሚዛን ቢሆን አንሶ መታየት አይችልም፡፡ በሴራ የተጠመዱ እኩዮች ወንጀል እየፈፀሙ በህዝብ ውስጥ መዋል፣ ማደር አለመታወቅ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ አስተሳሰባቸው ለህዝብ ከሰጡት ያነሰ ሚዛን እና ከግብዝነት የሚመነጭ ነው፡፡ በህዝብ ላይ ንቀት እየፈፀሙ ከህዝብ ጋር አብሮ መኖር የሚቻልበት ጊዜ አልቋል፡፡ ትዕግስት ልክ አለው፤ የሕግ ልጓምም ሊበጅለት ይገባል፡፡

Back to Front Page