Back to Front Page


Share This Article!
Share
የትግራይ ህዝብና ዶ/ ር አብይ አህመድ

የትግራይ ህዝብና ዶ/ ር አብይ አህመድ

ይዲድያ ብጹእ 08-23-18

አባይ (እምቢተኛ) በሬ በጫንቃው ቀንበር ተጥሎበት መፎሩን አልጎትት ብሎ ሲለግም፤ ትጉሁ ገበሬ ዘንጉን ለቀቅ አድርጎ ጎንተል ሲያደርገው ወደፊት ነቃ ብሎ እንደሚውተረተር፤ ብእሬንና ወረቀቴን ለማነካካት የምንደረደረው አንዳንዶቹ በመገናኛ ብዙሃን በሆነ ነገር ጎንትልና ወጋ አድርገውኝ ከተኛሁበት ሲያባኑንኝ ነው።

ከሰሞኑ አንዱ በፌስ ቡክ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለትግራይ ህዝብ በጣም ጥሩ እንደ ሆኑና፤ ህዝቡም ይህን ተገንዝቦ ይደግፋቸው ዘንድ እንደሚገባ ሰፋ ያለ ሐተታ አቅርቦ፤ መልእክቱ በጽሞና ተመልክቸዋለሁ። በመልእክቱ ከተነጸባረቁት ነጥቦች ባንዳንዶቹ ብስማማም፤ ከፊሎቹ ግን ወደ አንድ ጽንፍ የዘመሙና ሚዛናቸው በተገቢ ትንተናና አመክንዩ ያልታጀቡ በመሆናቸው ሂስ መሰንዘር ያስፈልጋል ከሚል እምነት ይህን ጹሁፍ አቅርቤለሁ።

የጸሐፊው ዋና ወይም መካከለኛ ሃሳብ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለትግራይ ህዝብ መሉ በሙሉ በጎ የሚያስቡና የሚጠቅሙት ናቸው የሚል አንደምታ ያዘለ ነው። ዶ/ር አብይ እንደ አንድ ግለ ሰብ ለሁሉም የሰው ልጅ ተጋሩን ጨምሮ ሊወዱና ሊያፍቅሩ ይችላሉ። ስለ ትግራይ ህዝብም ከልምዳቸው ተነስተው በጣም ማራኪ የፍቅር ቃላት በአደባባይ አዥጎድግዷል። ለዚህ የፍቅር ቃላቸውም ህዝቡ ደስታውንና ፍቅሩን ሞቅ ባለ ጭብጨባ አጸፋውን መልሷል።

Videos From Around The World

ከዚህ በተጨማሪም በድርጅታቸው ሆነ በቅርበት አብሮአቸው ከሚሰሩት ጋር ስለ ትግራይ በጎ እንጂ ክፉ ያስባሉ ብየ አልገምትም፤ ስለዚህ ህዝብ ሌት ተቀን እንደሚያስቡና የሚያስቡቱም በጎ እንጂ ከፉ እንደማይሆን አምናለሁ። ይሁንና ፍቅሩና ምሕረቱ እንዳለ ሆኖ፤ ህዝቡ በዘመነ ሥልጣናቸው፤ በተለይም በሁለቱ ክልሎች፤ ነብር አባርሮና አንቆ እንደሚገድላት ሚዳቋ ከመሆን አልዳነም።

ዶ/ር አብይ የትግራይን ሕዝብ ይወዱታልን? ድብን አድርገው! እየወደዱት ግን ከአሰቃቂ ግድያና መፈናቀል ሊታደጉት አልቻሉም። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? መሆንስ ሆኖ አይኖቻችን ፈጥጠው አይተዋል፤ ጆሮዎቻችንም ስለ ወገኖቻችን አሰቃቂ ሞት በመስማት ተሞልቷል። ከፍቅራቸውና ከምሕረታቸው ማዶ አሻግረው ማየትና መርገጥ የተሳናቸው ወሰኝ ነገር ነበር፤ አሁንም አለ። ያን አጮልቆው ማየት ካልቻሉና ያንን ደሴት ካልረገጡ፤ በያዙትና በጨበጡት የፍቅርና የይቅርታ መስተጋብር ብቻ ተግዳሮቱን ፈጽመው ሊያስወግዱት ሊፈቱት አይችሉም።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለትግራይ ሕዝብ ወይም ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ ናቸው ወይም አይደሉም ብሎ ሥራችውን ለመመዘን ብቃት ያለው የመመዘኛ መሣሪያ፤ በአገሪቱ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትና በምድርቱ ገዥና ልዑለ የሆነው ሕግ እንዴት እየተረጎሙትና እየተገበሩት እንዳሉ በመቃኘት ነው። ይህ ቀና ህሊና ያለው ዜጋ በቀላሉ መዝኖ ሊደርሰበት የሚችል ነው። በአገሪቱ በየነጥብ ጣቢያው የሚከሰት ግጭትና ግድያም በዚህ ዙሩያ የሚውጠነጠንና የሚሽከረከር ነው።

ለትግራይ ሆነ ለሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትናው፤መተማመኛው፤ጋሻውና መልህቁ ሕገ መንግሥቱና በምድሪቱ ላይ ገዥ የሆነው ሕግ ብቻና ብቻ ናቸው። መሪዎች ተግተውና ጠንክረው ሕገ መንግሥቱና ሕጉ ተግብራዊ ካደረጉ የህዝቡ አጠቃላይ ሰላምና ደህንነት የሚያጎናጽፉ ከመሆናቸው ባሻገር፤ በምልአተ ህዝቡ ሊሞጎሱና ሊከበሩም የተገባቸው ናቸው።

የአገሬ ሰው በጨው ደንደስ በርበሬ ይወደስ እንደሚል፤ በርበሬ በጨው ጠንቅ እንደሚወደስ መሪዎች የሚከበሩትና የሚሞጎሱት በሕገ መንግሥቱና በሕጉ ተገቢ አተገባበር ደንደስ ላይ እንደሆነ ሊሰመርበት የተገባ ነው። ስለዚህ አንዱ የሕገ መንግሥቱና የሕጉ ፋይዳና ወሳኝነት ከዚህ በሚገባ ማሰተዋልና መገንዘብ ይኖርበታል።

ከዚህ አንጻር የትግራይ ተወላጆች ባኦሮሚያና በአማራ በማንነታቸውና በዘራቸው ጠንቅ በጠራራ ፀሐይ ሰዎች በነቂስ ወጥተው በድንጋይ ወግረውና ጭንቅላታቸው ከአንገቶቻቸው ቀልተውና ቀንጥሰው ለትእይንት ሲያቀርብዋቸውና ሲያይና ሲሰማ፤ ሕዝቡ በሰልፍ ወጥቶ የሕግ ያለህ! ብሎ የሙጥኝ ያለውና ከለላ እንዲሆነው የተጠጋው ሕገ መንግሥቱና ሕጉን ነው።

ዶ/ር አብይ የህዝብ ዋስትናና አለኝታ ሕገ መንግሥቱና ሕጉ እንደ ሆነ የተገነዘቡት ገና አሁን ከአራት ወር የሥልጣን ጊዜአቸው በሃላ ይመስላል። በዚህ ጊዜ ጠ/ሩ ይቅርና ሕገ መንግሥቱና ሕጉን ሊተገብሩ በቃልም አንድም ዘላለ ሃረግ ትንፍሽ አላሉም። አሁን ለጉዳዩ ትኩረት መስጠታቸው እሰዩው የሚያሰኝ ቢሆንም፤ በዚህ ወቅት ግን የበረካታ ንጹሐን ዘጎች ሕይወት የሕግ ከለላና ዋስትና በማጣት አልፏል።

ዾ/ር አብይ ፍቅርና ይቅርታ ግንባር ቀደም ማድረጋቸው የተገባ ነው። ከፍቅር በላይ አምላክን ሊገልጽ የሚችል ባህሪ የለምና። ዳሩ ግን ከፍቅርና ከምሕረት በተጨማሪ ሌሎች መስተጋብሮች እንዳሉ ማጤን ደግሞ ያስፈልጋል። ፍቅር ብቻውን ፀንቶ መኖር የሚችል ስላይደለ፤ፍርድና ሌሎች መስተጋብሮችም መታከል አለባቸው። እግዚአብሔር አፍቃሪ አምላክ እንደ ሆነ ሁሉ፤ በጽድቅ የሚፈርድ አምላክ መሆኑን ማወቅ ደግሞ ያስፈልጋል።

ስለሆነም ፍርድንና ፍቅርን አጣምሮና አጣጥሞ ሕዝብን በሰላም እንዲኖር መሪ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ይጠበቅበታል። ብልህ መሪ ተቃራኒ የሚመስሉና እንደ ዋልታዎች የተራራቁ የሚመስሉቱን መሥተጋብሮች ማለትም ፍቅርና ፍርድን አቀናጅቶ፤ ሸምኖና ቀምሞ ህዝቡን በእፎይታና በሰላም እንዲኖር የሚያደርግ ጥበብ የተሞላው መሪ ነው። እነዚህ ሚዛናቸው ጠብቀው ካልተከናውኑ ሕዝብ ችግር ላይ መውደቁ የማይቀር ነው። እየተከሰተ ያለው ነገርም በዚህ የጥበብ ጉድለት ሳቢያ ነው።

ወደ ግል የሕይወቴ ልምምድ እገባና ከጠቀመች የህግ ልዕልናን ከዚህ በማስተያየት ለማቅረብ እሞክራለሁ።

በወጣትነት እድሜየ ካንዱ ጓደኛዩ ጋር በሆነ ነገር ተጨቃጨቅንና፤ ተነስቼ ግንባሩን በድንጋይ እፍነክተዋለሁ፤ እንደ ውሃ በፊቱ የሚፈሰው ደሙን በጨርቁ እየጠረገ አንተ ሰውዩ በህገ- አምላክ ከዚህ ቦታ እንዳትንቀሳቀስ! ብሎ ጮኾብኝ። እኔም ባለሁበት ግትር ብዩ ቀምኩኝ። በዚህ መካከል በስፍራው የሚተላለፉ ሰዎች ደርሰው ልጁን አጣጥበው ወደ ቤቱ አጽናንተው ሲወስዱት፤ እኔን በጣም ከተቆጡኝ በሃላ አባቴን እንደሚነግሩት ነግረውኝ ለቀቁኝ። ይህች ነገር አባቴ ዘንድ ከደረሰች እንደምትከርብኝና አበሣዋ የበዛ እንደ ሆነ ተረድቼለሁ። ከዚህ በላይ ያስጨነቀኝ ደግሞ የአካባቢው ዳኛ አባቴ መሆኑ ነው።

አባቴ በሕግ ፊት ዳኛ ሆኖ ሲቀርብ የማያመቻምችና ፍርድን ማጣመም የማይወድ ሰው ነበር። የተፈነከተው ጓደኛዩ ከወለጆች ሳይውሉ ሳያድሩ የልጁ ጉድ ያላወቀው አባቴ ጋር አቤቱታቸውን ይዘው ቀረቡ። አባቴ ወዲያውኑ ካለሁበት ቦታ ተፈልጌ እንድመጣ አደረገ። ድርጊቱ ወይም ወንጀሉ እንደ ፈጸምኩ ጠየቀኝ፤ እኔም አልቅሼ አዎን አልኩ። አባዩ እኔን በእነዚህ ሦሦት ቀናት ከቤት እንዳትወጣ ካለኝ በሃላ፤ ለተበዳዩ ልጅ ቤተሰብ ፈንጠርና ፈርጠም ብሎ ከሦስት ቀን በሃላ ልጃችሁ ይዛችሁ እንድትቀርቡ አላቸው።

በሦሦተኛው ቀን በግዞት የቆየሁት ተከሳሹ እኔና የተፈነከተው ጓደኛዩ ከወለጆቹ ጋር ዳኛው አባቴ ፊት ለፍርድ ቀረብን። በፍርድ ወንበሩ የተሰየመው የአባቴ ዓይኖች ከዚህ በፊት በፍቅር የሚመለከቱኝ ዓይኖች ከቶ አልነበሩም ። ግራ ቀኙ ከተመለከተና ካጠና በሃላ በዚያ ጊዜ የወንጀለኛው መቅጫ በሚያዘው መሰረት ለተወሰኑ ቀናት እስር ቤት እንድቆይ ተወሰነብኝ። አባት ምንም ያክል ልጁን ይውደደው እንጂ፤ ልጁ ሕግ ተላልፏልና በገዛ ልጁ ላይ ጨክኖ ይፈርድ ዘንድ ተገድደዋል።

አባቴ ይወደኛል፤ነገር ግን አጥፍቼለሁና እንደ ማንኛውም ሰው ቀጥቶኛል። ይህ አግባብነት ያለው ሥራ ነው። እዚህ ላይ ፍቅር የሕግን ልዕልና ሲቀማና ሲደመስስ አይታይም። ፍርድም ቢሆን ፍቅርን አያጠፋም። እንድታሰር በፈረደብኝ ጊዜ አባቴ ፍቅሩ ከድሮው ቅንጣት አልቀነሰም ነበር። በታሰርኩበት ቦታ ቀድሞ መጥቶ የጠየቀኝና ስቅስቅ ብሎ በማልቀስ አቅፎ የሳመኝ እርሱ ነበርና። ከዚህ ከትንሹ የፍርድ አደባባይ ትእይንት ለታላቋ አገራችን ሊተርፉ የሚችሉ ልንማርባቸውና ልንቀስማቸው የተገቡ አያሌ ነገሮች አሉ ብዩ አስባለሁ።

በተወለድኩበት አካባቢና ትውልድ የተበደለ ሰው በዳዩን፤ በሕገ-አምላክ ወይም በሃይለሥላሴ አምላክ ካለው በዳዩ ካለበት ቦታ ንቅንቅ አይልም። በዳዩ በሕገ-አምላክ ተብሎ ካልቆመ ሲያዝ ወንጀሉ እንደሚከርበትና እንደሚጠነክርበት ስለሚያውቅ መቆምን የሚመርጥ ሲሆን፤ከዚህ በላይ ግን በውስጥ ያለው ፈሪሃ እግዚአብሔር ነው። የእግዚአብሔር ሕግ ጥሶና ረግጦ መሄድ ህሊናው አይፈቅድለትምና።

ጠንካራ አገር ፅኑና እውነተኛ ሕግ የተደነገገባትና የሚተገበርባት አገር ናት። ሕግ አንድ ማሕበረ ሰብ ውስጥ፤ሰው ሳይበደልና ሳይበድል እንዲኖር የሚያደርግ አስተማማኝ መሣርያ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት መተግበር ሁለተኛ የለሌው የመጀመሪያ ምርጫ ነው። መንግሥት ለዚህ አስፈላጊ የሆኑ መዋቅሮችና ሥርአቶች ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራበት የተገባ ነው።

ሕግ በማሰከበር ሥራ ላይ ተዋናይ የሆኑ አያሌ ግብአቶች ያሉ መሆናቸው ቢታወቅም፤ በግንባር ቀደም የሚጠቀሱት ግን ሕግ አስፈጻሚዎቹ ዳኞችና ሕግ አስከባሪዎቹ ፖሊሶች ናቸው። ስለ ዳኖች በዚህ ጹሑፍ የምለው ባይኖረኝም፤ ስለ ፖሊስ ሰራዊቱ አስመልክቶ ግን ጥቂት ልሰነዝር እፈልጋለሁ።

ጤናማ የፖሊስ ሰራዊት ቁመና ሕግን በማስከበር ተግባር ላይ ወሳኝ ነው። ፖሊሰ የሠላምና የደህንነት አርማና ፈርጥ ነው። ሰላማዊ አገር ካለ ጠንካራና ሙያውን ከሚያከበር ፖሊስ ውጭ ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም። ታማኝና ቆፍጣና ፖሊስ ባለባት አገር የሚኖር ዜጋ ያለ ስጋት ይወጣል ይገባል፤ ይገዛል ይሸጣል፤ ይማራል ያስተምራል፤ ያርሳል ይነግዳል። ኢትዮጵያ ለፖሊስ ሰራዊቷ ከተቋም ጀምሮ እስከ ግል ሕዋስ ወይም ነጥብ ጣቢያ ልዩ ትኩረት ልትሰጥ ይገባታል።

የወቅቱ የፖሊስ ሰራዊት ቁመናና ሥራው በድፍኑ ሲገለጽ በኔ ግምገማ በጣም ደካማ ነው። ለዚህ ጠንቅ የሆኑ አያሌ ምክንያቶች መዘርዘር ቢቻልም፤ ዋና ዋናዎቹ ገርፍ ገርፍ አድርገን ለማየት እንሞክራለን።

ሲጀምር ፖሊሶቹ ተገቢ የሞያ ብቃት የሌላቸውና ሞያው ለሚጠይቀው ግዴታ (code of conduct) ተገዥ የማይሆኑ ናቸው። ይህ ተገቢ ምልመላና ስልጠና በመሰጠት ማሻሻል የሚቻል ሲሆን፤ ስልጠናው ተከታታይ ማድረግና ሥራቸውም ሁሉጊዜ በተገቢው መንገድ መቆጣጠርና መገምገም አስፈላጊ ነው።

ሁለተኛው የፖሊስ ሥራ በጣም ወሳኝ፤ ሥራውም ውስብስብና ተግዳሮት የሞላበት ሲሆን፤ደሞዛቸው ግን አንሰተኛ መሆኑ ነው። የአገሪቱ የኤኮኖሚ አቅም ለሁሉም የመንግሥት ሰራተኛ ደሞዝ መጨመር የሚፍቅድ ባይሆንም፤ ካለው ችግር አኳያ የፖሊስ ደሞዝ ማሻሻል ቅድሚያ ቢሰጠው የመፍትሔው አንዱ ዘርፍ ሊሆን ይችላል።

በጨቋኝና ዴሞክራሲ በሌለበት አገር ፖሊስ ሕዝቡን ገትቶና አስሮ የሚይዝ የመንግሥት መጠቀሚያ መሣሪያ ነው። በዚህ መንግሥት ሥር የሚሰራ ፖሊስ በህዝብ ቁቡልነት የሌለውና የሚጠላ ነው። በአሁን ጊዜ ያለው የኢትዮጵያ ፖሊስ የዚህ ተቃራኒ በሆነ ጽንፍ የተሸነፈ ነው። ሕዝብን እንወክላለን ብለው ያመጹ ለምሣሌ ቄሮና ፋኖ መንግሥትን በሃይል ተጋፍጠውታል። ከዚህ በሃላ እነዚህ ሃይሎች ራሳቸው እንደ መንግሥት ለዋጮች (King makers) አድርገው ስለቆጠሩ፤ራሰቸው ከፖሊስና ከሕግ በላይ አድርገው መቁጠር ይዘዋል። ፖሊስም መንግሥት ተገን ስለማይሆንለትና እነዚህ ቡድኖችም ስለሚያዋክቡትና ስለሚያስፈራሩት፤የሞያ ግዴታው በፍርሃት ምክንያት እንዳይወጣ አድርጎታል። አንድ የታወቀ ኢትዮጵያዊ ባኦሮሚያ ክልል አንዲት ከተማ አንድ የፖሊስ ቡድን በርከት ያሉ ቄሬዎችን አይቶ መንገዱ ቀይሮና ሰብሮ በፍርሃት ሲሄድ ተመልክቻለሁ ብሏል። ይህ አደገኛና በአፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት የተገባ አዝማሚያ ነው። ቄሮ ይሁን ፋኖ ለሕግ ተገዝዎች እንደ ሆኑ አገሪቱ አስረግጣ ማሳወቅና ህጋዊ እርምጃም መውሰድ የተገባት ነው። ማንም ከሕግ በላይ የለምና!

ፖሊስ በዘረኝነት ቁርቁሱና ፍትጊው ለሕግ እንደ መቆም በዘሩ ስለ ተሰለፈ ዜጎች ያላግባብ ሲገደሉና ሲታሰሩ እንዲሁም ሲንገላቱ ይታያሉ። ለምሣሌ በሻሻመኔ በጠራራ ፀሐይ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ፖሊስ እያየ ተዘቅዝቆ የተሰቀለው ሰው ድርጊት የፖሊስን ሞያ የሚያጎድፍ ነው። በኦሮሚያና በአማራ በተጋሩ ላይ ፖሊስ ሊከታተለውና ሊያቆመው እየቻለ የተደረጉ የዘር ጥቃቶችና ግድያዎችም ይህን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።

ሌላው ትልቁ የወቅቱ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ችግር ሙሰኝነትና የራስን ጥቅም ማገበስበስና ማሳደድ ነው። ራሴ ከገጠመኝ ልጀምር፤ ከሁለት ዓመት በፊት ቦሌ ደርሼ ሚኒባስ ይዞ ይጠብቅ የነበረው ወንድሜ ጋር እቃችንን ጭነን እየተጫወትን ወደ ምናርፍበት ቤት አቀናን። የሾፌሩ ረዳት ከሻንጣዩ ብዙ ፋይሎች ይዛ የነበረችው ላፕ ቶፔ አውጥቶ ይመዘብራል። ይህን ያወቅነው ቤት ከገባን በሃላ ነበርና ታኪስዋን ልንደርስባት አልቻልንም። የነበረን ምርጫ ፖሊስ ጋር ማመለከት ነበርና ወዲያዉኑ በአካባቢው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን ሪፖርት አደረግን። አጋጣሚ የባለ ታኪሲው ሞባይል ቁጥር ስለ ነበረን ፖሊስ በወቅቱ ደውሎ የሰረቀውን ሰው አነጋግሯል። እንዲህም ሆኖ ጉዳዩን የያዘው ፖሊስ ተከታትሎ ለመያዝ ምንም ፍላጎት አልነበረውም፤ በዚህ ሳቢያም ውድ እቃዩ ቀልጬ ቀርቻለሁ።

ዳሩ ግን ጫዋታው ሌላ ነበርና፤በርካታ ሰዎች ተሳስተሃል፤ፖሊስ ጋር መሄድ አልነበረብህም፤ ሌቦቹ ተደራጅተው ስለሚሰርቁ የእነርሱ አስተባበሪ አግኝተህ በሱ በኩል የሚከፈለው ከፍለህ ማስመለስ ትችል ነበር አሉኝ። ፖሊሶችም ከሎቦቹ ጋር ግኑኝነትና ትስስር እንዳላቸው ተማርኩኝ፤ ነገር ግን ሁሉም ፖሊሶች አይደሉም።

አንድ ጓደኛዩም ከውጭ ሄዶ ስለነበረው ጓደኛው እንዲህ አጫውቶኛል፦

ጓደኛው አዲስ አበባ እንደ ገባ ወንድሙ እንዲንሸራሸርባት መኪናወን ይሰጠዋል። እንግዳው መኪናውን አንድ ጥግ ላይ አሰቀምጦ ሲጠጣ አድሮ በጧቱ ሲመጣ የመኪናዋ ሁሉም ብልት(Body) ተወስዶ ቆፎዋ ብቻ ቀርተዋል። እንግዳው በሁኔታው በጣም ተደናግጦ ወንድሙ ዘንድ ሲፈራ ሲቸር ደውሎ ነገረው። ወንድሙ ግን በተረጋጋ መንፈስ እስቲ ከአንድ ስዓት በሃላ እደውልልሃለሁ አስከዚያው ግን ተረጋጋ አለው ከአንድ ስዓት በሃላ ወንድሙ ደውሎ፤ አትጨነቅ፤ ብቻ ጧት ወደ መኪናዋ ሂድ አለው። እንግዳው ወንድሙ እንዳለው በጥዋቱ ሲሄድ መኪናዋ እስከነ ሙሉ ነፍስዋና ብልቶቿ አገኛትና እፎይ! አለ። ለካስ ወንድሙ ባገሪቱ ያለው የፈረጠመው የሌቦች ሕገ ወጥ ኔት ዎርክ ያውቅ ኑሮ ዋናዎቹን አግኝቶ የሚከፈለውን ከፍሎ ነው መኪናዋ በሌሊት የተገጣጠመችው። በሃገራችን እንዲህና እንዲያ ያሉ አሳዛኝ ድራማዎች በየቀኑ የሚተወኑ ናቸው።

መንግሥት ይህን አሳዛኝ ድርጊት ሳያውቀው ቀርቶ አይደለም፤ ይሁንና በዚህ ዘርፍ መንግሥት ቀዳሚና ከባድ የቤት ሥራ እንዳለው ሳስገነዝብ፤ ነገሬን የምደመድመው፤ ከአረብ አገር የሚመጡ ወንድሞቻችንና በተለይም ምስኪን እህቶቻችን በስንት ጭንቅ ጥረው ግረው ያመጧት ቤስታ ቤስቲን ሳትቀር ቦሌ ላይ መዘረፏ ነው። ውይ ቦሌ! ስንቱ ባንቺ አለቀሰ? ስንቱስ በዓመታት ጥሮ ግሮ ያከማቸውን በናጣቂ ተኩሎች በጥቂት ሰዓታት አጣ ነጣ! መንግሥት ሆይ! ስለ ድሃ አደጉና ስለሚስኪኑ ግድ ብሎህ ትጋና ሕዝብህን ታደግ!!

በቦሌ ጠንከር ያለ የፖሊስ ጣቢያና የደህንነት ቁጥጥር ማድረግ ለምን አልተቻለም? እንባውና ዎዮታው እስከ መቼ ይቀጥል? በመጨረሻ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ይኖር ዘንድ ቁልፉና ወሳኙ ሕገ መንግሥቱና ምድሪቱን የሚገዛ ሕጉ ነውና በዚህ ዙሩያ አበክራችሁና ጠንክራችሁ ስለምድሪቱ ሰላም፤ብልጽገናና ደህንነት ስትሉ ሥሩ ብዩ እማጠናችሁለሁ!!!

ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

አሜንና አሜን!!

 

Back to Front Page