Back to Front Page


Share This Article!
Share
የትግራይ ህዝብ ወንድም ከሆነ የአማራ ሕዝብ ጋር አንድነትና ፍቅር እንጂ ፀብ አይሻም ።

የትግራይ ህዝብ ወንድም ከሆነ የአማራ ሕዝብ ጋር አንድነትና ፍቅር እንጂ ፀብ አይሻም ።

 

ልኡል ገብረመድህን (አሜሪካ)

 

ጥቅምት 23/2011

    ህዝብ ከታሪክ ይቀድማል። ታሪክ የማህበረሰብ ክሰተት ወይም ክንውን ማሕደር ነው። ህዝብና ታሪክ ደግሞ ስፍራ ያስፈልገዋል። የስፍራው ስያሜ ደግሞ አገር ነው ። አገር ታላቅ ነው ።አገር ታላቅ የሚያደርገው አብይ ጉዳይ የሕዝቦች መለያና መጠሪያ መሆኑ ነው።  አገር ያለ ህዝብ ፣ እንዲሁም  ህዝብ ያለ አገር መኖር ታሪክ አልባ ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረውም ። ሰለ አገር ማሰብ ሰናቆም ነባራዊ ታሪክም እየረሳን መሆኑን መታወቅ አለበት ። ዘመን

 ታረኮቻችን ያለ አገር አንድነት ዋጋና ሰፍራ የላቸውም ።አገር ሲፈርስ ታረክም ይፈርሳል ።የአክሱም፣ የአድዋ ፣ የመተማ ፣ የውጫሌ ፣ የጎንደር ፣ የሐረር ፣ የሱማሌ ፣ የደቡብ ፣የምዕራብ ፣ የምስራቅ ጥንታዊ እንዲሁም ዘመናዊ አገራዊ ታሪኮቻችን ያለ ሕዝቦች ውስጣዊ አንድነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እርባና የላቸውም ።

    ኢትዮጵያ የታሪክ ባለርስት ብቻ ሳትሆን የሰው ልጅ መገናኛ አገር እንደሆነችም የተለያዩ ድርሳነ መረጃዎች ይገልጻሉ ። ለአብነት በምርምር ሰሟ ሉሲ ወይም ድንቅነሽ ኢትዮጵያዊ ሰው ናት ። ኢትዮጵያ ሌላ ፀጋም አላት ።ይህውም የተለያዩ ብሔረሰቦች እናት ነች ።የዳበረ ባህልና ታሪክ ያላት አገር የመንግስት አሰተዳደር ባህል ችግር ሰለባ ነች ። የመሬት ፣ የግብር ፣ የፍትህ ፣ የስርአት ፣የባህል ፣ የፖለቲካ ፣ የአገልግሎት ፣ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ጎታች ችግሮች የኢትዮጵያ እድገትና ህልውና የሚፈታተኑ ሆኖ ቆይተዋል። እንደ ታላቅነታችን የፖለቲካ ባህላችን ኋላ ቀር ነው ። የፍትህና የፖለቲካ መዋቅሮች ምሶሶ ጎባጣነት ምክንያት ኢትዮጵያውያን አሰፈላጊ ያልነበረ መሰዋእትነት ሲከፍሉ ኖረዋል ። በብሔር ጭቆና ምከንያት ብረት አንግቦ እርስ በእርስ ሲፋጅ ከርመናል ። የብሔር ጭቆና ለማስቀረት የታገሉ ታጋዮች ተፈላጊ የስርአት ለውጥ አልተከሉም። ፖለቲካ የለውጥ መሳሪያ ከመሆን ይልቅ ወገን መጉጃና መጨቆኛ እየሆነ በመምጣቱ የአገር አንድነት ስሜት እንዲቀዛቀዝ አይነተኛ ምከንያት ሆነዋል ። ተጠራጣሪ ህብረተሰብ እንዲፈጠር ቀዳዳ አበጅተዋል ።

Videos From Around The World

     ኢትዮጵያ አያሌ ባህላዊ ሆነ ዘመናዊ ትምህርት ቀመስ ዜጐች ያጎለበተች አገር ናት ። የአጠቃቀም ጉድለት ካልሆነ ዳሩ ኢትዮጵያ በሁሌም አቀጣጫዎች የዳበሩ ልዩ ልዩ የባህል ሰነዶችም አሏት ። ግን የዳበሩ የፖለቲካም ሆነ የመንግሥት አሰተዳደራዊ ተቋማት የላትም ። አሁን ያለው ያልተማከለ የመንግስት ሰልጣን በጎ መርሆች ቢኖሩም ከችግር የፀዳ ሊሆን አልቻለም ። አገር በቀል ዜጎች በማንነትና በመሬት አዋሳኝ ምከንያት ግጭቶች ተከስተዋል ፣ የሰው ህይወትም ቀጥፈዋል። በኢትዮጵያ ለሚነሡ አገራዊ ችግሮች መነሻ ምከንያት የተዛባ የፖለቲካ አሰተሳሰብ ችግር ነው ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ መነጋገርም ሆነ መደማመጥ አልባ በመሆኑ ለችግሮች መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ መቃቃርና መጠላለፍ የሰፈነበት የስርአት ብኩንነት በመስፈኑ ነው። አገሩ አልጠበበ፣ መሬትም አልታጣም ታድያ ለምን ችግር እያጣን ? ። ፖለቲካ የአስተሳሰብ ውልደት በመሆኑ የችግሮች መፍቻ ከመሆን የችግሮች መነሻ ምከንያት መሆን አልነበረበትም ። በአንድ ወቀት የስልጣኔ ባለቤት የነበረች አገር ቁልቁል የመውረድ አባዜ የተጠናወታት በሌላ ሳይሆን ለኢትዮጵያ አሳቢ ነን ከሚሉ ቁልቁል የወረዱና ያልዘመኑ ሸራቢ ፖለቲከኞች አመለካከት የመነጨ ነው ። ቂም በቀል መነሻ ያደረገ ስርአት ዘላቂነት የለውም ብቻ ሳይሆን ማህበረሰብ በታኝና አውዳሚ ነው ።

     በኢትዮጵያ  የብሔር ወይም የማንነት ጥያቄ ሕገ መንግሰታዊ ነው። ከፍ ሲልም ብሔራዊ መብት ነው ።ሲቀጥልም የሕልውና ጥያቄና መብት ተደርጎ ይወስዳል ። የማንነት ጥያቄ ማንሳት መልካም እንጂ ጎጂ አይደለም ።ችግሩ ማንነትን የሚስተናገድበት አመለካከትና ዕይታ የተዛባ መሆኑ ነው ። ብሐረሰቦች ማንነታቸው ተከብሮ ፣ ተከባብሮ ለመኖር የሚያነሷቸው መብት ነክ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ ማግኘት ይገባቸዋል ። እኔ ማን ነኝ ብሎ ለሚጠይቅ ዜጋ ጥያቄው ከማጥላላት ይልቅ ሰብዓዊ መብቱ መሆኑ ታውቆለት ቀልጣፋ አሰተዳደራዊ መልስ ያሻል ። የማንነት ጥያቄ በማንም ይነሳ በማ ጉዳዩ መብታዊ በመሆኑ በጥንቃቄ መፍትሔ መሻት አለበት ። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የማንነት ጉዳይ አፈታት በአንቀጽ ተደንግጎ ይገኛል ። ችግሩ ግን ጉዳዩ ከመብት አንፃር ከማየት ይልቅ ልላ ያልተፈለገ ቅጥያ በማበጃጀት ለማድበስበስ መፈለጉ ተጨማሪ ችግር ያስከትላል ።

    በኢትዮጵያ ለሃያ ሰባት አመታት የዘለቀው ፖለቲካዊ ስርአት ብሔር ተኮር ስለነበር ስርአቱ ከፌዴራል የመንግስት አሰተዳደርና አፈጻጸም ጋር የመጋጨትና የአፈፃፀም መዛባት ሲታይበት ቆይተዋል። በብሔር የተቃኘ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ለአገር አይደለም ለራሱ ለብሔረሰቡ ጠቃሚነትና ዘላቂነት የለውም ። የአማራ ፖለቲካና የአማራ ኢኮኖሚ የሚባል ፖለቲካዊ መርህ የለም ።የትግራይም በተመሳሳይ ። ደቡብ ጋርም የለም ። ፖለቲካና ኢኮኖሚ በብሔር አይቃኝም ። በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የዘር ግጭቶች በአብዛኛው መነሻቸው የብሔር ፖለቲካና ኢኮኖሚ ነው ። ለዘመናት በአብሮነት የዘለቀ ሕዝብ ያለምንም በቂ ምከንያት የዘር ግጭት ውስጥ አይገባም ፣ አይጠፋፋም ፣ አይጎዳዳም ። ሕዝብ አይሳሳትም ።ሕዝብ አይበዳደልም። ሕዝብ አይገዳደልም። ሕዝብ ምክንያታዊ ነው ።ሕዝብ ብልሐተኛ ነው ። የችግር መነሻ ሕዝብ ሳይሆን ሕዝብ የሚያስተዳድር መንግሰታዊ መዋቅር ነው ። ሕግን መሰረት አድርጐ የዜጎች መብትና ጥቅም የማያስጠብቅ የፌዴራል ስርአት የግጭቶች መንስኤ ከመሆን አያልፍም ። በኢትዮጵያ የታየውም ይህ ሀቅ ነው ።

   በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክልል የሚኖሩ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ዘመናት የተሻገረና የዳበረ የጋራ ታሪክና አኩሪ ባህል ያላቸው ታላቅ ሕዝቦች ናቸው ።ለመንግስታዊ ስልጣንም አዲሶች አይደሉም ። የዘመናዊ ስልጣኔ ባለቤቶች ናቸው ። አክሱምና ላሊበላ ፣ጎንደርን የሐ የጋራ መገለጫዎቻቸው ናቸዉ ። በቋንቋም ቢሆን የተራራቁ አይደሉም ። ሑለቱም ህዝቦች አዋሳኝ ሳይሆኑ ቤተሰብ ናቸው ። በጋብቻና በደም የተሳሰሩ መልካም ግንኙነት ያዳበሩ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሸ ምከንያቶች ከቶ የማይለያዩ ድንቅና ብርቅ ህዝብ ለመሆናቸው ብዙ መተንተን የሚያሰፈልግ አይመስለኝም ። እኝህ ሁለቱም ህዝቦች የኢትዮጵያ ደህንነት ምሰሶዎች ናቸው ። አገር ወራሪ ጠላት መግቢያ በር የሚዘጉ ብቻ ሳይሆን ባለድሎችም ጭምር ናቸው ። ቴድሮሰና ዮሐንስ ጀግንነትና መልካምነት አሳይቶን አልፈዋል ።የአገርና የወገን ክብርም አሰሰክቦናል።

   የአማራና የትግራይ ህዝብ ጨቋኙን የደርግ አሰተዳደር ለመቀየር የከፈሉት መሰዋእትነት ከግምት በላይ ነው ። ከሰንደቅ እሰከ ትጥቅ ያበረከቱት ሲመዘን ድንቅ ነው ። የሁለቱም ህዝብ አኗኗርም ተመሳሳይ ነው ። መሬት አልምቶ የሚኖር ህዝብ ነው ። ያለ ተጨማሪ ሰልጠና ብረት አንግቦ መተኮስ የሚያዉቅ ህዝብም ነው ። አብዛኛውም ብረት የታጠቀ ህዝብ ነው ። ቢሆንም ለግጭት የቀረበ ህዝብ አይደለም ። አሁን አሁን የዘፈን ዳር ዳሩ እሰክሰታ ነው እንዲሉ ሁለቱም ህዝቦች የሚያቃቅሩ ስርአት ወለድ ችግሮች በመታየት ላይ ናቸው ። መነሻ ምከንያት ማንነት የሚል ቅጥያ ሰም እየተበጀለት የፖለቲካ ቁማርተኞች ትዕይንት መሰማት የተለመደ መምጣቱ ለብዙዎቻችን አሳዛኝ እየሆነ ነው ። በመሬት ማሰፋፋት ወይም ወረራ ግጭት ግብቶ የማያውቁ ህዝቦች ለምን ማንነት የግጭት መንሴ ይሆናል ?። በአንድ አገር እየኖሩ በመሬትና በማንነት ፀብ መጫጫር ለምን አስፈለገ ?። በትክክል የግጭቶች መነሻ የግዛት ማስፋፋትና የማንነት ጥያቄዎች ናቸው ?።  

    በጎንደር ወልቃይት በወሎ ራያና አላማጣ የማንነት ጥያቄ የሁለቱ ወንድም ህዝቦች ግኑኝነት የሚያሻክር መሆን የለበትም ።ሁለቱም ህዝቦች በሁሉም ክልላዊ አስተዳደሮች የመኖር ህገመንግስታዊ መብት ብቻ ሳይሆን ወንደማዊነትም ጭምር ነው ። በሚኖሩበት ክልልም በቋንቋቸው የመማርና የመዳኘት ሙሉ መብት እንዲኖራቸው አሰፈላጊ ነው ። በሚኖሩበት ክልል የመንግሥት ሥራ የመቀጠርና የማገልገል መብትም ጭምር እንዲኖራቸው ያሰፈልጋል ። የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸዉም ፍትሀዊነት የተላበሰ መሆን ይኖርበታል ። ወልቃይትም ሆነ ራያ የኢትዮጵያ ቦታዎች ናቸው ። አማራም ሆነ ትግራይ የኢትዮጵያ ክልሎች ናቸው ። መሬቱም የኢትዮጵያ ነው ።ህዝቦችም ኢትዮጵያውያን ናቸው ። ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት የህዝብና የመንግሥት ነው ። ኢትዮጵያ ውሰጥ ክልላዊ መሬት የለም ። የክልል መሬትም የለም ። የወልቃይትም ሆነ የራያ ጉዳይ የማንነት እንዲሁም  የተጠቃሚነት ጉዳይ ነው ።ይህ ደግሞ ውስብስብነት የለውም። ጉዳዩን የሚያወሳሰቡ የሁለቱ ክልል መሪዎች ከስልጣናቸው ባሻገር የህዝባቸው መብት፣ ተጠቃሚነት፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ሥርየት ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል ። ህዝብ የፖለቲካ መሰመር ዘዋሪ እንጂ ተዘዋሪ መሆን የለበትም ። የማንነት ጥያቄ ህግና ስርአትን የተከተለ መሆን ይኖርበታል ። በሀይልና በፖለቲካዊ መግለጫዎች የሚፈታ የህዝብ ጥያቄ የለም ።

    በወልቃይትና ራያ ለሚነሱ ማናቸውም የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡና ህዝብን ያማከለ ህገ መንግሥታዊ ውሳኔዎች መወሰን ይኖርባቸዋል ። የክልል መስተዳደሮች አቅም ውስንነትም ሆነ የፖለቲካ አቋም ምከንያት በሁለቱ ክልሎች ለሚነሱ የማንነት ሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ጉዳይ የአንድም ዜጐች ሕይወት ማለፍ የለበትም ። የሁለቱ ክልል መስተዳድሮች ከእልህና መናናቅ ደካማ የፖለቲካ አሰተሳሰብ ወጥቶ የህዝባቸውን መብትና ጥቅም ማስፈፀም ይኖርባቸዋል ። በሰለጠነ የዲሞክራሲ ሰጥቶ መቀበል መርህ የሁለቱ ክልል መሪዎች የህዝቡን ነባራዊ አንድነትና መከባበር ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ።ወልቃይት ሆነ ራያ የኢትዮጵያ ቦታዎችና መሬቶች ናቸው ። የአማራም የትግራይም አይደሉም ። የትግራይ ሆነ የአማራ የሚባል መሬት የለም ። ሰለሆነም የአማራና የትግራይ ህዝብ ፀብና ግጭት ውስጥ የሚገባበት አንዳች በቂ ምከንያት የለውም ። ችግሩ የህዝብ ሳይሆን የፖለቲካ ቁማርተኞችና የተዛባ የታሪክ አረዳድ ነው ። ሁለቱም ህዝቦች መቼም ቢሆን ተጋጭቶ ፣ ተጣልቶና ተለያይቶ አያውቁም ፣ ለማለያየት አይቻልም ብቻ ሳይሆን በብዙ በቂ ምክንያቶች የሚታሰብ አይሆንም ።

 

 

Videos From Around The World