Back to Front Page


Share This Article!
Share
ይድረስ ለትግራይና ለአማራ ክልሎች መንግስታትና የሃይማኖት መሪዎች

ይድረስ ለትግራይና ለአማራ ክልሎች መንግስታትና የሃይማኖት መሪዎች

ተክለሚካኤል ኪ/ማርያም   10-24-18

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ቀና አስተሳሰብ በመጥፋቱና ቁንፅል አመለከካት በመንገሱ የሰው ህይወት መጥፋት ፣ የመፈናቀልና ንብረትን የማውደም አደጋ እየቀጠለ ነው፡፡ችግሩ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ የተከሰተ ሲሆን ኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ የወደፊት ኣቅጣጫ ለህዝቡ ይፋ በሚያደርግበት ጊዜ ብዙ ተስፋ ሰጪ ጉዳዮችን በኣራቱ የኢሕአዴግ ኣባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ሲገለፅ የሰላም ምልክት የታየበት ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም፡፡በተለይ በሙስና ፣ በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ፣ በፍትህ ፣ በመልካም ኣስተዳደርና በዴሞክራሲ ምህዳር ላይ ህዝቡ የነበረውን ጥያቄ ለመመለስ ትግል እንደ ሚካሄድና ለዚህም የኣመራር ለውጥ እንደ ሚደረግ በማያሻማ መገለፁ ህዝቡን ያስደሰተ ነበር፡፡

በመቀጠል ኣዲሱ ጠቅላይ ሚንስቴር በመሾም የኣመራር ለውጡ ከመጀመሩም በላይ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ በስልጣን ርክክቡ ጊዜ ያደረጉት ንግግርና የሰጡት የተስፋ ቃላት የኢትዮጵያ ህዝብን በእጅጉ እንዳስደሰተ የተከታተልነው ጉዳይ ነው፡፡የዚሁ ቀጣይ ስራ ሆኖም እስረኞችን መፍታት ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ኣጀነዳቸውን ይዘው በሰላም እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ ፣ በፀረ ሽብርተኝነት የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ኣዋጁን እንዲነሳላቸው ማድረግና ከኤረትራ ጋር የነበረው የ20 ዓመታት ችግር የመፈታት ሂደት መጀመር ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በዚሁ ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ የለም ማለት ይቻላል፡፡

Videos From Around The World

በሌላ በኩል በኣንዳንድ ኣፈፃፀም ላይ ከተቋማዊነት ወደ ግላውነት ያዘነበለ ከመሆኑም በላይ የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ እየገባ መምጣቱ የብዙዎች ስጋት መሆኑን በቀላሉ የሚታይ ችግር ኣልነበረም፡፡ይኸውም ኣፈፃፀሙ ተቋማዊ ከሆነ ከላይ እስከ ታች ያሉትን የመንግስትና የፓርቲ መዋቅሮች በኃላፊነት ስለሚያሳትፍ የበለጠ ወጤታማ ከመሆኑም በላይ የህግ የበላይነት ለማስፈን ስለሚበጅ እንጂ እየተወሰዱ ያሉ ለውጦች (reforms) ኣስፈላጊነታቸው ኣለመቀበል ኣይመስለኝም፡፡

እንዲሁም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ይቅርታ ፣ ፍቅር ፣ መደመር የሚሉት መሪ ቃላት ሲናገሩ በአገራችን የስርዓት ለውጥ ሲደረጉ በተለይ ከዘውዱ ስርዓት ወደ ደርግ ፣ ከደርግ ወደ ኢሕኣዴግ የተደረጉ ሽግግሮች የተለያዩ ችግሮችን ያስተናገዱ ሲሆኑ የኣሁኑ ለውጥ ግን የህዝቡ ግፊት በከፍተኛ ደረጃ የታከለበት ቢሆንም ከውስጥ መፍለቁ ቢያንስ የተለያዩ የመንግስትና የህዝብ ተቛማት ማኖቆቻቸውን በማስወገድ ተጠናክረው የሚቀጥሉበትና ማፍረስ የሚባለው ኣደገኛ ኣካሄድ ቦታ እንደማይኖረው ለብዙዎች ተስፋ ያሰነቀ ነው፡፡

በተጨማሪም እንደ ስርዓት ለተፈፀሙ ስህተቶች ኢህአዴግ ይቅርታ የጠየቀበት ሲሆን የሰዎችን ኣስተሳሰብ በመለወጥ ህብረተሰቡ ወደ ሚፈልገው በሰላም እንዲቀጥል መንገድ ይከፍታል ተበሎ ተሰፋው የተጠናከረበት ታላቅ ጉዳይ ነበር፡፡በተለይ ሁሉም የዜግነት ድርሻውን ለአገሪቱ ዕድገት ማበርከት እንዲችል ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰቱ በጥላቻ የመጠማመድና የመጠላለፍ ፖለቲካ አብቅተው በቀል የሚባል ኣደገኛ ኣካሄድ በይቅርታና በምህረት ተዘግቶ ጥላቻና መወነጃጀል ለኣንዴና ለመጨረሻ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ በህዝቡ ያሳደረ ሲሆን ኣሁንም ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

ነገር ግን በሂደት እየታየ ያለው በተለይ በየመድረኩና በድጋፍ ሰልፎች ላይ እንደ ተገነዘብነው በአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች አስተባባሪነት ትግራይን ያገለለና ህወሓትን የማስወገድ ዓለማ መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ በግልፅ የታየ ሲሆን ይህ ከሆነ ደግሞ ኣሁንም ከቂም በቀል እየወጣን ኣይደለም፡፡ እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ይቅርታውና ለውጡ ለምን ዓላማ እንደ ሆነና ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት ቁልጭ ኣድርጎ የሚያሳይ ኣቅጣጫ ወይ ፍኖተ ካርታ ስላልተሰራለት እንኳን ለህዝቡ በከፍተኛ ኣመራር ላሉ ብዙዎችም ግልፅ ካለ መሆኑም በላይ የተንኮል ፖለቲካ ለተጠናወታችው ፓርቲዎችና ግለሰዎች የፈለጉትን ቀዳዳ የተፈጠረላቸው ይመስላል፡፡

ለምሳሌ እንደ የጊዜውና እንደየ አገሩ ነባራዊ ሁኔታ የኣፈፃፀም ስልቱ ሊለያይ የሚችል ቢሆንም ደቡብ ኣፍሪካ ከኣፓርታይድ ነፃ በምትወጣበት ጊዜ ለይቅርታ ሂደቱ የወጣለት ማዕቀፍ እንደ ነበረ ይታወቃል፡፡በኣገራችንም ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሊጣጣም የሚችል ፍኖተ ካርታ መንደፍ አስፈላጊ ነበር ባይ ነኝ፡፡ይቅርታው ለሁሉም ዜጋ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚመለከት ቢሆንም እየታየ ያለው ግን ከዚሁ የተለየ ነው፡፡ይኸውም ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያና የንብረት ዝርፍያ በብዙ ክልሎች እየተባበሰ ሲሆን በተለይ በኣማራ ክልል ዓይን ያወጣና የባሰበት ዝርፊያና ግድያ አልበቃ ብሎ ወሰንን ሰበብ በማድረግ በትግራይና አማራ አዋሳኝ ወረዳዎች እየተደረገ ያለው ትንኮሳ ወዴት እያመራ እንደሆነ የኣማራ ክልል መንግስትና መንግስቱን የሚመራ አዴፓ ቆም ብለው ማሰብ ነበረባቸው፡፡

አዴፓ በክልሉ ያለውን ህገ ወጥ ወይም ስርዓት ኣልበኝነት መቆጣጠርና ማረጋጋት ሲሳነው በአማራ ቴሌቪዥን ፣ በአብን መሪዎች ፣ በወሎ ዩንቨርሲቲ ፣ በደብረታቦር ዩንቨርሲቲ ፣ በኢንጅባራ ዩንቨርሲቲ ወዘተ በሚያስተምሩ ጥቂት የዘር ሐረግ የሚያወራርዱ ወጣት መምህራንና በጥቂት የአማራ ሊሂቃን አዝማችነት ውስጣዊ ይዘቱ ህወሓትን ለማስወገድ ሆኖ በወሰን ሰበብ የትግራይ ክልል ሰላም የማወክ ተግባር ቀጥሎበታል፡፡

የወሰን ችግር ከሆነ በየአከባቢው የሚኖር ህዝብና የአገራችን ህገ መንግስት ጉዳይ ስለሆነ አሰራርን ተከትሎ ለሁለቱ አዋሳኝ ህዝቦች የሚበጅ እልባት ማድረግ እንጂ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ፣ ባህርዳርና ሌሎች ታላላቅ የአማራ ክልል ከተሞች ሆኖ ጊዜ ያለፈበት የእኛ እናወቅልሃለን ጋጋታ የትም እንደማያደርስ መታወቅ ነበረበት፡፡

የህወሓት ህልውና በተመለከተ ደግሞ የትግራይ ህዝብና የራሱ የህወሓት ጉዳይ እንጂ ሌላ የሚመለከተው ኣካል አለ ብዬ አላምንም፡፡ይኸውም የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ የደረሰበትን ድምዳሜ እስከ ታች ድረስ እንዲወርድ ህዝቡ የሚጠብቅ ሲሆን በተጨማሪም የኢህኣዴግ ምክር ቤት ገምግሞ ያስቀመጣቸውን የመፍትሄ ኣቅጠጫዎችና የተጀመሩ ለውጦች ተቋማዊ ይዘት ተላበሰው ከቀጠሉና የተገባው ቃል ይተገበራል ተብሎ ስለሚታመን ግራም ነፈሰ ቀኝ ህወሓት እስከ ምርጫ 2012 ድረስ የሀዘቡ ውክልና ይዞ ይቀጥላል፡፡

በተጨማሪም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የህዝቡን ልብ ትርታ በማዳመጥ ከሰራና ምርጨው ግልፅና ዴሞከሲያዊ ሆኖ ህዝቡ በሙሉ ነፃነት የፈለገውን እንዲመርጥ ከምርጫ ቦርድ ጀምሮ ሌሎች የሲቭል ተቋማት የሚፈለገውን ነፃ አደረጃጀት ተላብሰው ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረለት የትግራይ ህዝብ ይጠቅመኛል ብሎ ያመነበትን ፓርቲ ይመርጣል፡፡

ህወሓትም ይሁን ሌላ በተሟላ ቁመና መምራት ኣይችልም ብሎ ካመነም በካርድ ቀጥቶ ለሌላ ጊዜ ምርጫ እንዲዘጋጅ ያደርጋል እንጂ በግርግር የሚፈታው ችግር አይኖርም፡፡ትክክለኛ ምርጫ ተካሂዶ ህወሓት ካሸነፈም የመቀጠል ዕድሉ ክፍት ስለሆነ ለመመረጥ የሚያበቃው ስራ ያከናውናል ብለን እንጠብቃለን፡፡በሌላ በኵል ያለ መሪ የፖለቲካ ድርጀት እንዲቀርና ሹም የሌለው ንብ እንዲሆን የትግራይ ህዝብ ስለማይፈቅድ በስመ አማራ የተደራጁ ፓርቲዎች ፣ ጥቂት ሊሂቃንና የአማራ ቴሌቪዥን ቁርጣቸውን ኣውቆው ልዩነትን በማጥበብ ለትግራይና ለአማራ ወንድማማች ህዝቦች በሚጠቅም ስራ ላይ እንዲጠመዱ ይመከራል፡፡    

ይሁን እንጂ ከመስከረም ወር 2011 አጋማሽ ጀምሮ እየታዩ ያሉ ክስተቶች መጥፎ አዝማሚያ ብቻ ሳይሆን በዓብደራፊዕ ፣ በዳንሻና በአላማጣ የሰውን ህይወት እስከ ማጥፋት የደረሱ ትንኮሳዎች የተስተናግዱ ሲሆን የአማራ ቴለቪዥን ፣ ጥቂት የአማራ ሊሂቀንና ፖለቲከኞች ነገሮችን እያጣመሙ ህዝቡን ለባሰ ጥፋት እንዲዳረግ በማነሳሳት ላይ ናቸው፡፡

ስለዚህ የኣማራና የትግራይ ክልሎች መንግስታትና የፌደራል መንግስት ጉዳዩ ወደ ባሰ ጥፋት ከማምራቱ በፊት ሓላፍነት ወስደው አለ የሚባለውን ችግር በሰላም የሚፈታበት ሁኔታ እንዲያመቻቹና ከተጠያቂነት የሚድኑበት ታሪካዊ አደራቸውን እንዲወጡ ህብረተሰቡ ይጠብቃል፡፡በሌላ በኵል በትግራይና በአማራ ክልሎች ያሉ የሃይማኖት መሪዎች ፣ ታዋቂ ግለሰዎችና የአገር ሽማግሌዎች የጉዳዩ ባለቤትነት ወስደው በሁለቱም ክልል መግሰታት ላይ ሰላማዊና ሃይማኖታዊ ጫና በማሳደር ድርሻቸውን እንዲወጡ በፈጣሪ ስም እማፀናሎህ፡፡

 

Back to Front Page