Back to Front Page


Share This Article!
Share
የትግራይ ህዝብና ድርጅቱ ህወሓትን ለመነጠል የሚደረግ ሴራ እናትና ልጅ ለመነጠል የሚደረግ ከንቱ ጥረት ነው፡፡

 

የትግራይ ህዝብና ድርጅቱ ህወሓትን ለመነጠል የሚደረግ ሴራ እናትና ልጅ ለመነጠል የሚደረግ ከንቱ ጥረት ነው፡፡

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ሰኔ 12፣ 2010 ዓ.ም.


 

መግብያ

የጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ ሰኔ 11፣ 2010 ዓ.ም. ለበፓርላማ ላይ ካደረጉት ንግግር መነሻበማድረግ ይህንን ፅሁፍ ለማዘጋጀት ያነሳሱኝ ብዙ ነጥቦች ስላሉ ነው፡፡ በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብዪ ያደረጉት ንግግር በጣም ሳቢና ብዙ ብዥታዎች ያጠሩ በጣም ጥሩ ማብራርያ እንደነበር ከልብ ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ ይሁንና ከተናገሩትና ማስተላለፍ ከፈለጉት ብዙ-ያልተመቹኝ አንድ ሁለት ነጥቦች ስላሉ ግን ነፃ ሁኜ ልንወያይባቸውና በህዳሴ ጉዛችን ለሁላችን ይጠቅሙናል ብየ የማስባቸው፣ ወይም መታረም ኣለባቸው ብየ የማስባቸውን ነጥቦች ለማንሳት በማሰብ ነው፡፡

በዋናነት ያልተመቹኝ ብየ የማነሳቸው ነጥቦች

1.  በህወሓት እና በትግራይ ህዝብ ያለውን ግንኝነት በማስመልከት ጣል ያደረጉትን ንግግር

2.  በኪራት ሰብሳቢነት ትግል ላይ ጠ/ሚ እየተከተሉት ያለውን አካሄድና፣ በሚመለከቱ ላይ ነው፡፡

እኔ እንደ ፀሃፊው በህወሓት ስር ተደራጅቼ በአገራችን ላይ በሚደረገው የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግል ውስጥ የራሴን አዎንታዊ ሚና እየተጫወትኩ ነው ብየ የማምን ዜጋ፡፡ ይህ ፅሁፍ ራሴን ወክየ የፃፍኩት እንጂ የማንም ውክልና የሌለው መሆኑ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ እኔ ለራሴ በአብዮታዊ ዴክራሲ ጠንካራ እምነት ኣለኝ ብየ የማምንና የምታገል እንደመሆኔ መጠን በራሴ እምነት ይምፅፋቸው ሁሉም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነትን ያንፀባርቃሉ ብየ አምናለሁ፡፡ ይህ ፅሁፍ ስፅፍም የጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ እንደመነሻነት በመውሰድ ካለኝ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነት ጋር በማያያዝ የፃፍኩት መሀኑን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ምንና ምናቸው?

በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ትግራይ ህዝብ የገለፁት በጣም የተመቸኝና ትክክለኛ በሳል አነጋገር የተናገሩት በማመስገን ለመጀመር እፈልጋለሁ፡፡እሱም ግልፅነታቸውና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ውሳኔዎችም ቢሆኑ ከህዝቡ መደበቅ የለበትም የመደበቅ ወይም የማቆየት ባህል መቀየር አለበት በማለት የተናገሩት በጣም የሚመች ሲሆን ስለ ትግራይ ህዝብ ሲያነሱም፣ የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ለዚህ ያበቃ እንደሆነ፤ ነገርግን በዚህ ስርዓት ከሌላው የላቀ ጥቅም እንዳልተጠቀመ፣ ጥቂቶች በስሙ ነግደው እንደሆኑ እንጂ የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ አልነበረም፡፡ በሌሎች የሚታዩ ችግሮች በትግራይም እንዳሉ፣ የውሃ ችግር፣ የመልካም ኣስተዳደር ችግር ጎልተው እንደሚታዩ፡፡ ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ እንደነበር ተደርጎ የሚነዛው ወሬ አጥፊና ትክክል እንዳልሆነ መግለፃቸው ነው፡፡ በእውነትም በጥሩ አነጋገር ብለውታል፡፡

Videos From Around The World

በንግግራቸው ያልተዋጠልኝ

በህወሓት ላይ የሰነዘሩት ግን ወጥነት የሌለው ለትምክህተኞችና ጠባቦች ለማስደሰት ተብሎ ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ የሚነጥል አነጋገር በመሆኑ እኔም ኣብዛኛው ህዝብም ያስከፋ ሆኖ ኣግኝቸዋለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብና ህወሓት የተለያዩ እንደሆኑአገላለፅ ማለቴ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ ታግሎና ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለው በህወሓትና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመራር ስር ተሰልፎ ነው፡፡ ህወሓት የዚህ ስርዓትም የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝቦችም ባለውለታ ነው፡፡ህወሓት ኢህአዴግም ዶ/ር አብዪም ለዚህ በማብቃት ከፍተኛ ባለውለታ ነው፡፡ ህወሓት ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በመሆን ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ ስልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲተላለፍ ያደረገ ድርጅት ነው፡፡ ህወሓት ገና ከጅምሩ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሆኖ፣ ተገዶ ወደ ትጥቅ ትግል ከገባና ትግሉ በድል ከተጠናቀቀ ቦኋላም ስልጣን በጦርነትና በመሳሪያ ጋጋታ ነው ያመጣሁት ስለዚ ማንም እንዳይጠጋኝ ኣላለም በዴሞክራሲያዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡ በመሆኑን በ1997 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ቅንጅት ባሸነፈበት ቦታ ሁሉ ስልጣን ለማስረከብ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር ግንባር ቀደም ተሰልፏል፡፡ የአንድ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የዴሞክራሲያዊነት መለኪያ አንድን የማያምንበት አቋምምም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እስከተወሰነ ድረስ ተቀብሎ ለማስፈፀም ግንባር ቀደም መሆን ነው፡፡ህወሓትም በዚህ የሚገለፅ ድርጅትና አሁንም ከባህሪው ያልወጣ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ላይ ፅኑ እምነት ያለው ድርጅት ነው፡፡ ህወሓት ከነፈሰ ንፋስ የማይነፍስ የዓላማ ፅናት ያለው፣ በህዝበኝነትና በጊዝያዊ ሆይ ሆይ የማይመራ ድርጅት፣ ለቆመለት ዓላማ መስዋእት የሚከፍል ብርቅየ የህዝብ ድርጅት ነው፡፡

ይህ ሲባል ግን ህወሓት ውስጥ ችግር የለም ማለት ኣይደለም፡፡ በተለይ በድርጅታችን ኢህአዴግ ላይ የታየውን የዝቕጠት ችግር በህወሓት ጎልቶ ታይቷል፡፡ ችግሮቹ ህዝብ እስኪያማርር ድረስ ተንፀባርቋል፡፡ ይህ ችግር ግን የአመራር ችግር እንጂ የድርጅቱ ወይም የአብየዮታዊ ዴሞክራሲ ችግር ኣልነበረም፡፡

ህወሓት የትግራይ ህዝብን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሰለፈ፣ ትክክለኛ የህዝብን ጥቅም ማረጋገጥ የመሚችልና በተግባርም የህዝብንን ጥቅም ማረጋገጥ ያስቻለ መስመር ያነገበ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የአገራችን ጭቁን ህዝቦች ባለውለታ የሆነ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ ህወሓት በውስጥም በውጭም ጠባብነትና ትምክህተኝነት መታገል የሚያስችለው ብቃትና ችሎታ ያለው፣ ከገጠሙት ችግሮችም በራሱ ጊዜ በመውጣት ላይና በመታደስ ላይ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ስለዚ ይህንን እየታወቀ በጠ/ሚ ድርጅቱን ኣሳንሶ ማየትና ከትግራይ ህዝብ ነጥሎ እንዲታይ ማድረጉ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡

ትግራይ ህዝብ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለ ቢሆንም ልዩ ጥቅም ግን ኣላገኘም፤ በስሙ የነገዱ ይኖራሉ እንጂ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ የተጠቀመው ነገር የለም ብለዋል በጣም ትክክል ነው፡፡ በህወሓት ላይም ተመሳሳይ ኣቋም መያዝ ነበረባቸው፡፡ ህወሓት ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለ፣ ህዝብን ኣስተባብሮ ለድል የበቃ ብቃት ያለው ውጤታማ የህዝብ ድርጅት ነው፡፡ ጥቂት በህወሓት ስም የሚነግዱ ኪራይ ሰብሳቢዎች ኣባላትና አመራር ካልሆነ በስተቀር አሁንም ህወሓት ትክክለኛው የህዝብ ድርጅት ነው፡፡

አሁንም የትግራይ ህዝብና ድርጅቱ ህወሓት የማይለያዩ አንድና ያው ናቸው፡፡ ህወሓት ማለት ከትግራይ ህዝብ ብሶት የወለደው የህዝቡ አድን ድርጅት ነው፡፡ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ በደም፣ በአጥንት፣ በከፍተኛ መስዋእትነት የተሳሰሩ ህዝብና ድርጅት ናቸው፡፡ ህወሓት የትግራይ ህዝብን ከሰውበላ ደርግ መንጋጋ ያዳነ የህዝብ የቁርጥ ቀን ድርጅት ነው፡፡ ህወሓት የትግራይ ህዝብን ከድህነት አረንቋ ወጥቶ በአገሩ እንደማንኛውም ህዝብ እኩል እንዲሰለፍ ያደረገና ከድህነት እንዲወጣ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረገ ድርጅት ነው፡፡

ስለዚ አሁንም የትግራይ ህዝብና ድርጅቱ ህወሓትን ለመነጠል የሚደረግ ሴራ እናትና ልጅ ለመነጠል የሚደረግ ከንቱ ጥረት ነው፡፡ህወሓትና የትግራይ ህዝብ እንኳን አሁን የሰላሙ፣ የዴሞክራሲው፣ የልማቱ ቱርፏት በያንዳንዱ ዜጋ ማጣጣም በጀመረበት ጊዜ፤ በ17 ዓመት የትግልና የእልቂት ጊዜም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አልተለያዩም፡፡ጠላትም ወዳጅም ማወቅ ያለበት ነገር ካለ አንዱ የትግራይ ህዝብ በብርቅየ ልጁ በህወሓት የሚመጣበት አይወድም ህወሓትም እንደዚሁ፡፡

 

ዶ/ር አብዪእና የኪራይ ሰብሳቢነት ትግል

ከጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብዪ ንግግር ካልተመቹኝ ውስጥ ሁለተኛው ነጥብ በኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳይ ዳርዳር ማለታቸው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስተር ዳር ዳር ከመሄድ የሚያውቁትና በርግጠኝነት አፋቸው ሞልተው የሚናገሩበት ሁኔታ ካለ በግልፅ ይንገሩን፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና የማንኛውም ህዝብ ፀር ነው፡፡ በልማታዊ መንግስታችን የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዟችን ላይ ሊገጥመን የሚችል ትልቁ ስጋት ይህ ኪራይ ሰብሳቢነት እንደሆነ በግልፅ በማስቀመጥ የትግል ስልት በመንደፍ ላለፉት 17 ዓመታት ስንጓዝ እዚህ ደርሰናል፡፡ ካለው ነባራዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ /ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸ ከመሆኑ ኣንፃር/ ሲታይ ቀላል የማይባል ውጤትም ተመዝግቧል፡፡ ይሁንና ከምንፈልገውና የደረስንበትን የልማት ደረጃ ከሚመጥን ኣኳያ ሲታይ የኪራይ ሰብሳቢነትን ሁኔታ ገና ብዙ የሚቀረው እንደሆነ ሁሉም የገመገመው ጉዳይ ነው፡፡ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቻቸውንና የተደላደለውን መንገድ በማፍረስ በምትኩ ለልማታዊነት የተመቻቸ ለማድረግ ባለፉት 17 የተሃድሶ ዓመታት ከፍተኛ ትግል ተካሂዷል፡፡

እንደ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸ ነው የሚባለው ለውድድር የሚመች ሁኔታ ያለመኖር፣ ባለሃብቱ በኣጠቃላይ ዜጋው በእውቀቱና በብቃቱ ተወዳድሮ እንዳያድግ በአገራችን ከፍተኛ የገበያ ክፍተት መኖሩ ይህ ማለት የትምህርትና ስልጠና ያለማዳረስ፣ የመሰረተልማት ዝርጋታ ችግር፣ የኣሰራር፣ የኣደረጃጀት፣ የፋይናንስ፣ በኣጠቃላይ የመሰረተ-ልማት ወዘተ ጉድለቶችን በመኖራቸው ነው አገራችን ለኪራይ ሰብሳቢነት እንጂ ለልማታዊነት፣ ጥራት ያለው ምርት በማምረት በገበያ ተወዳድሮ ለመክበር ኣይመችም የሚባለው፡፡

ከዚ ኣንፃር ሲታይ ለኪራይ ሰብሳቢነትን የተመቻቸ ሁኔታ ማፍረስ የሚቻለው ልማቱ ማፋጠን፣ ወደ ውድድር ማስገባት፣ የልማት ኣሰራርና ኣደረጃጀት መገንባት መሰረተልማቶች መዘርጋት፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ፋይናንስና ድጋፎችን በማመቻቸት ባለፉት 17 ዓመታት ከፍተኛ ጥረት በማድረጋችን ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡በኣጠቃላይ ሲታይ ባለፉት 17 የተሃድሶ ዓመታት የተመዘገበው ድል ሲመዘን ለኪራይ ሰብሳቢነትን የተመቻቸው አስፋልት መንገድ ዶዘር የገባበት/የታረሰበት/ እንጂ በበለጠ እንዲ መቻች የተደረገበት ሁኔታ ኣይደለም የነበረው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የኪራይ ሰብሳቡኔት ቪ-8 ማስኬድ የሚያስችል የተመቸ መንገድ የለም፣ ምናልባት ለመጓዝ የሚሞክር ካለ ይቅር ረጅም ርቀት ሊጓዝ በሜትሮች ርቀት ከተጓዘ ቦኋላ ተሰሰብሮ እንደሚወልቅ በተtግባር እያየነው ነው፡፡

ኪረራይ ሰብሳቢነት ለማፍረስ በሰራነው ስራ ኪራይ ሰብሳቢነት ባናጠፋውም ግን ዕድሜው አጭር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ገዜ የመንግስት ቦታዎች በኣማካይ ከ2 ዓመት በላይ የማይቆይበት ቦታ ሆኖዋል ይህም ገሚሱ በድርጅት ግምገማ፣ ገሚሱ በህዝብ ቅሬታ፣ በብቃት ችግር፣ በሙስና ችግር ሲቀያየር ማየት የትግሉ ውጤት ነው፡፡ሁሉም ክልሉ ሰከን ብሎ ቢፈትሽ ምን ለውጥ እንዳመጣ ማየት ይቻላል፡፡ በኦሮምያ ክልል በኣማራ ክልል፣ በትግራይ ክልል በደቡብ ክልል የሚታይ ሃቅ ነው፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግ በድርጅቱ እምነት ይሁን በህዝቡ ግፊት በየመዋቅሩ ሙሰኞችን እየመነጠረ፣ ኣመራሮችን እየተካ መጥቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው በኪራይ ሰብሳቢነት ትግል የሄድነው ርቀት ያሳያል፡፡ በአንድ ወቅት ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ በሚመሩት ድርጅት እስከ 80% የወረዳና የዞን ኣመራር ማሸጋሸጋቸው የቅርብ ቀን ትውስታ ነው፡፡ ይሁንና በኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ለውጦች ቢኖሩትም ገና ብዙ የሚቀረውና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ቢያንስ ግን ሙስናን የሚቃወም ህብረተሰብ ከመፍጠር ኣኳያ ቀላል የማይባል ስራ እየተሰራ ነው፡፡

ምናልባት ከጊዜ ወደ ጊዜ ኪራይ ሰብሳቢነት እየጨመረ ነው የመጣው የሚል ካለ፣ እሱ ምናልባት የአገራችን ሁኔታ የት ነበረች ምንጋ ኣለች የሚል በደንብ ያልተገነዘበ ኣርቆ ማየት የተሳነው ፖለቲከኛ ብቻ ነው፡፡የአንድን ፖለቲከኛ ብቃት የሚመዘነው ከህዝቡ አንድ እርምጃ ቀድሞ ማየት፣ ማሰብ፣ መምራት የሚችል እንጂ ህዝቡን የሚለው የሚደግም፣ ህዝቡ ከሚያየው ኣርቆ የማያይ፣ ህዝቡን ቀድሞ መሄድ የማይችል ከሆነ ችግር አለው ማለት ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ከማንም በላይ ቀድሞ መረዳት ያለበት ኣመራሩ ነው፣ ለችግሮች ኣስቀድሞ መፍትሄ ማስቀመጥ ያለበት ኣመራሩ ነው፡፡በአንዳንድ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት/ክስተቶችን የሚደናገጥ አመራር ሩቅ ሊጓዝ አይችልም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በአጭር ጊዘ የሚቀረፍ ችግር አይደለም፡፡ ዘርፈ ብዙ ችግር ነው፡፡ የሁሉም ችግሮቻችን መገለጫ ሃውልት ነው፡፡ ስለዚ ለኪራይ ሰብሳቢነት ችግር መወገድ ስትራቴጂካሊ ኣርቆ በማየት መሰራት ያለበት እንጂ በሆይ ሆይ፣ በማሰርና በመፍታት፣ የሚቀረፍ ኣይደለም፡፡ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመቅረፍ ኣንድ እርምጃ በተጓዝን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትም በዛው መልክ መልኩን ቀይሮ መጓዝ እንደሚችልና ብቃትም እንዳለው ካልተገነዘብን ችግር ነው፡፡ አሁን እያየነው ያለ ነገርም ይህ ነው፡፡

አንድ መሪ ተቀይሮ በመጣ ቁጥር ያለፈውን መሪ ጉዞ ማብጠልጠል ነው፡፡ይህ ደግሞ የአገራችን የልማት ጉዞ በተረጋጋና ፍጥነቱን አቅቦ በመሄድ የራሱ አሉታዊ ጫና ያሳድራል፡፡ ስለዚህ የተመዘገበው ልማት እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢነት ያለው ደረጃ ሁሉም በልኩ ካልታየ የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡ ዶ/ር አብዪ ወደፊት ሊጓዙ ከሆነ ከፊታቸው የነበረ መሪ ያስመዘገበው ውጤት በመርገጥ /ረግጦ-በማለፍ/ ሳይሆን ተገቢዉን እውቅና በመስጠት የጎደለውን መሙላት ሲሆን ነው ተቀባይነት የሚኖረው፡፡ አሁን እያየነው ያለው ግን ረግጦ ማለፍ የሚመስል አካሄድ ነው፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በማፍረስ በምትኩ ልማታዊነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመተካት በተደረገው ጥረት ባለፉት 17 ዓመታት አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ምክንያቱም ኪራይ ሰብሳቢነትና ልማታዊነት በእኩል ሊያድጉ ፈፅመው ኣይችሉም፡፡ ልማት አለ ከተባለ በሌላ አነጋገር የተወሰነ የኪራይ ሰብሳቢነት ቦታ በልማት ተተክቷል ማለት ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲካል ኢኮኖሚ እየተቀየረ ነው፡፡ በልማቱ የህዝቡ ተሳትፎ ተጣጥፎ የቀጠለበት ሁኔታ ነው ያለው፣ የህዝቡ ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚነትም የተረጋገጠበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሞጓች ህብረተሰብ ተፈጥሯል ስንል የልማት የዴሞክራሲ ምንነት የገባው በተግባር ማጣጣም የጀመረ፣ ጠያቂ ህብረተሰብ ተፈጠረ ማለታችን ነው፡፡ ይህም ማንም የሚያየው ጉዳይ ነው፡፡ እያንዳንዷን የልማት እንቅስቃሴ፣ እያንዳንዷን የህዝብ ተሰሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንቅስቃሴ የኪራይ ሰብሳቢነትን ምቸ ሁኔታ የምትቀይርና ይምታፈርስ አንድ እርምጃ ናት፡፡ስለዚ ያለፉት የ17 የተሃድሶ ጉዛችን ኪራይ ሰብሳቢነትን እየጨመረ የሄደብትና ለልማታዊነት እየተደናቀፈ የመጣበት ሁኔታ ኣይደለም ያለው፡፡ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸውን ሁኔታ እየፈራረሰ፣ ልማቱም የብዙሃኑ ሂይወት እየለወጠ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህ ሲባል ግን ኪራይ ሰብሳቢነት እየተደፈቀ ነው ሲባል ግን ከገዢነቱ ለቋል ማለት ኣይደለም፣ አስፋፍቶ የነበረውን እየተሸረሸረ ሲሄድ እሳት ላይ እንደ ገባ ፕላስቲክ እየተሸመረረ ሃይሉን ወደ ጥቂት የሚያሰባስብበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ያለው፤ ስለዚ ሙቀቱ እየበረታ ሲሄድ ቀልጦ ይጠፋል፡፡ሙቀቱ ግን በአንድ ጀንበር ወይም በአንድ የስልጣን ዘመን የሚፈጠር ኣይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር የልማቱ ጉዞ ይወስነዋል፡፡ ስለዚ የከኪራይ ሰብሳቢነnት ትግል ከድህነት ትግልና ከልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ኣጣምሮ ማየት ኣለበት፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ነጥሎ በማየት አንዳንድ የኪራይ ሰብሳቢነት ክስተቶችን እያዮ መደናገጥ ወይም መደነቅ ማለትም ብዙ ብር ተሰረቀ ሲባል ወይም ዘራፊ ተያዘ ሰሲባል ትልቅ ተአምር እንደተሰራ መደናገጥ ወይም ሆይሆይ ማለት ህዝበኝነት ነው፡፡

ይህ ሲባል ግን ኪራይ ሰብሳቢነት የለም ማለት ወይም ያለውን ሁኔታ ኣሳንሶ ከማየት ኣንፃር ኣይደለም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትን በተለይ በሙሰኝነት በመንግስት ኣገልግሎት ኣሰጣጥ ላይ ከላይ እስከታች /ከቀበሌ እስከ ፌደራል/ በጥቂት ቁልፍ የመንግስት ቦታዎች በመጠኑም እየጨመረ የሚሄድበት ለመከላከሉም ውስብስብ እየሆነ የሚመጣበት ሁኔታ መኖሩ የሚካድ ኣይደለም፡፡ ኣሁንም ይህ ትግል ኣሳንሶ ማየት የለብንም፡፡ ከማንም በላይ እዚህ ላይ ካልተረባረብን ለአንድነታችን ትልቅ ፈተና ነው የሚሆነው፡፡ ይሁንና የተደረገው ትግል ወደኋላ የሚመልስ ግን መሆን የለበትም፡፡ ያለፈውን ትግል ላይ በመደመር እንጂ ወደኋላ በመመለስ መሆን የለበትም፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል የሁሉም ጠላት ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ብሄር የለውም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በተለየ የመንግስት መዋቅር ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛው የፌደራል መዋቅር ተንሰራፍቶ ይታያል፡፡ ነገር ግን የኪራይ ሰብሳቢነትን ትግል በሚያደናቅፍ መልኩ የሚደረግ እንቅስቃሴ ግን በጣም ትክክል ኣይደለም፡፡ ለምሳሌ አሁን አሁን ኮንትሮባንዲስቶች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች ሙሰኞች እየተባለ የሚሰማው ነገር በጣም ኣሳፋሪ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል ከአንድ ድርጅት ብቻ ማያያዝ፣ ከአንድ ብሄር ብቻ ማያያዝ፣ አደገኛ ኣካሄድ ነው እየታየ ያለው፡፡ በኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መተማመን እየታጣ ነው ያለው፡፡ ይህም ለአንድነታችን በጣም ትልቅ ፈተና ነው፡፡

በደርግ ጊዜ አንዱን ብሄር በማንነቱ ሲብጠለጠል፣ ቋንቋው ሲዋረድ፣ ማንነቱ ሲንቋሸሽ፣ ራስን ኣሳንሶ እንዲያይ የሚያደርጉ ከፍተኛ ጭቆና ነበር፡፡ ይህም ሂዶ ሂዶ አገራችን ለብተና ዷርጓት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ኣሁን ደግሞ ይህን መልኩ ቀይሮ አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር የሚጋጭበት፣ አንዱን ብሄር እንደ ብሄር ኮንትሮባንዲስት ኪራይ ሰብሳቢና ሙሰኛ እየተባለ በገዛ አገሩ እንደ ሌላ ዜጋ የሚታይበት ሁኔታ ሲያጋጥም ለአንድነት ሳይሆን ለብተና የሚዳርግ ነው፡፡ኣንድን ብሄር በብሄር ማንነቱ ካልተከበረ ማንነቱ ከተዋረደ ለምን ብሎ አንድነትን ይመርጣል፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ኮንትሮባንዲስት፣ ሙሰኛ እያለ አንዱን ብሄር ለይቶ የሚሳደበው ራሱ በኪራይ ሰብሳቢነት የተዘፈቀ የኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች ኣመራር ነው፡፡ዛሬ በአንዱ ብሄር ዘመቻ የገባው ነገ በሌላውና በኣጠቃላይ በህዝቦች መካከል ጥላቻ እንዲፈጠርና ብሎም ወደ ፋሽዝም የሚያመራ ሂዶ ሂዶ በከፍተኛ እልቂት የታጀበ ፍቺ የሚያመራ እንጂ እንደ ድሮው በፀረዴሞክራሲ፣ ማንነቱ እየተዋረደ ዝም ብሎ የሚገዛ አንድም ህዝብ አይኖርም፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር እየዳረገን ያለው በጣም ጥቂት ግለሰቦች፣ ብሄርም፣ ድርጅትም የማይወክሉ ሙሰኞች ተግባር ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን ሙሰኞች በጥቂት ብሄሮች ወይም በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ብቻ የታጠሩ ናቸው ማለት ኣይደለም፡፡ ሙስና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ከታቹ የአስተዳደር እርከን እስከ ከፍተኛው የፌደራል ስልጣን ተንሰራፍቷል ሲባል በዚህ ያለ አመራር ባለመታገል ወይም ራስን እጅ በማስገባት ተጠያቂ ነው ማለት ነው፡፡ይህ ሁኔታ ከክልል ክልል እንደየ ስፋቱ፣ ባጀቱ፣ የልማት እንቅስቃሴው ሊለያይ የሚችል ቢሆንም ከደሙ ንፁህ ነው የሚባል ግን ሊኖር ኣይችልም ምክንያቱ ህዝቡ እያማረረ ያለው ከጫፍ ጫፍ እንጂ በተወሰነ ኣከባቢ ብቻ ስላልሆነ፡፡ ህዝቡ በመልካም ኣስተዳደር ችግር እያማረረ ያለው በመረጣቸው መሪዎቹ እንጂ በእህት ድርጅቶች ኣይደለም፡፡ ነገር ግን ሙሰኞች ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት እጃቸውን ወደ እህት ድርጅቶች፣ ወደ አንድ ብሄር ሲቀስሩ ይታያል፡፡

የሚያሳዝነው ነገር ግን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተጠምቄአለሁ የሚለው አመራር/ኪራይ ሰብሳቢው/ የህዝቡን ቅሬታ ተገን በማድረግ እውነትህ እኮ ነው ችግሩ የአንዱን ብሄር የበላይነት ስላለ ነው፣ የአንዱን ድርጅት የበላይነት ስላለ ነው፣ ኮንትሮባንዲስቶች የአንዱን ብሄር ተወላጆች ብቻ ናቸው፣ የሚያጣሉን እነሱ ብቻ ናቸው፣ እኛ ማ ምን እናድርግ ኣልቻልንም በማለት ሙሰኞቹ ችግሩን ፈጣሪና ኣድራጊው አንዱን ብሄረሰብ እንደሆነ ኣድርገው ስለሚሰብኩ በጣም ኣሳፋሪ ወቅት ላይ ሆነን እንገኛለን፡፡ በተለይ በብአዴንና በኦህዴድ የሚመሩ በመንግስት ሚድያዎች እየታዘብን ያለነው ነገር የኣመራሩ ችግር ጎልቶ እስከ መውጣትና ሻምፒዮን እስከ መሆን ደርሷል፡፡

 

ሙሰኞቹ ለህጉ የተሰወሩ ቢሆኑም ከህዝቡ ግን በምንም ተኣምር ሊሰወሩ ኣይችሉም፡፡ ሙሰኞቹ ሁሉም ያውቃቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሙሰኞቹ በቤታቸው በአከባቢያቸው፣ በሚኖሩበት ኣከባቢ ሃውልት ኣቁመዋልና፡፡ አንድን የ4 ወይም 5 ሺ ደሞዝተኛ ሃውልት ሲሰራ ፣ ለህጉና ለፍትህ እና ለፀረሙስና መዋቅራችን የተሰወሩ ቢሆኑም፤ለህዝቡ ግን የተሰወሩ አይደሉም፣ ወለል ብሎ ይታየዋል፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስተሩ በቢሆኑም፣ ከዚህ ጣጣ ነፃ ኣይደሉም፡፡ ቃል በገቡት መሰረት ለኪረይ ሰብሳበቢነት ኣጥብቀው እንደሚታገሉ፤ለሁሉም ህዝበች እኩል አተየይ እንዳላቸው ነበር የነገሩን፡፡ ነገር ግን በተግባር እየታየ ያለው ከዚህ በተለየ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በፅናትና በቆራጥነት በመታገል ፋንታ ኪራይ ሰብሳቢነትን እንደ ማስፈራሪያነት መጠቀማቸው በጣም ኣሰልችቶናል፡፡ በእውነት ኪራይ ሰብሳቢነት የሚታገሉ ከሆነ በትክክል መታገል እንጂ እንደ ማስፈራሪያ፣ እረፍ ኣለበለዚያ እንዲህ ኣደርጋሎማለት የትክክለኛ መሪ ኣካሄድ ተደርጎ ኣይወሰድም፡፡ ህዝቡ በትክክል ሓቁን ማወቅ ኣለበት፡፡የትግራይ ተወላጅ ሙሰኛ ከማንም በላይ የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው፡፡የኣመማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ የሌለላው ብሄር እንደዛው፡፡ለዚህ ምስክር ከተፈለገ አሁን ያለውን ሁኔታ ማየቱ ቀላል ያደርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዳሉት በትግራዋይነት የሚነግዱ ጥቂት ኪራይ ሰብሳቢ እንደሆነ እንጂ የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የበለጠ የተጠቀመበት ሁኔታ የለም፤ ነገር ግን ትግራዋይ እየተሰደበ በገዛ አገሩ እንደ ኮንትሮባንዲስት እየተቆጠረ ነው፤ እንደ ኪራይ ሰብሳቢ እየተቆጠረ ነው፡፡ በዚህ አገር በትክክል እንየው ከተባለ ኪራይ ሰብሳቢነት ከላይ እስከ ታች አለ ከተባለ፤ ኪራይ ሰብሳቢው ቢቆጠር ለሁሉም ክልል እንደየ ህዝብ ብዛቱ እንደሚደርሰው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡አሁን እያየነው ያለው ነገር ግን አንዱን ብሄር ላይ ያነጣጠረ ፕሮፖጋንዳና እርምጃ ነው፡፡ ይህም ከፍየሏ በላይ ነውእንደተባለው ሆን ተብሎ ኪራይ ሰብሳቢነትን ትግል ለማደናቀፍና ትግሉን መልኩን ቀይሮ ወደ ለየለት ፋሽዝም እንዲያመራ የሚደረግ የጅቦች ሴራ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ ኪራይ ሰብሳቢ ነው፡፡ የፈለገው ብሄር ቢሆን ኪራይ ሰብሳቢ ከሆነ የሁሉም ብሄር ጠላት ነው፡፡ ሌባ ሌባ ነው፡፡

ሁሉም በአንድላይ ኪራይ ሰብሳቢን መዋጋት አለበት፡፡ ለኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል ድንበር ማበጀት የለብንም፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት ትግል እንደ ኢህአዴግ የተለያየ አቋም መኖር የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ከማንም በላይ የውስጥ ችግር ነው፡፡ መገለጫውም ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡ ይህም ምሽጉ አንድ ብሄር ወይም አንድ የፖለቲካ ድርጅት ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም በመንፀባረቅ ላይ ያለ ነው፡፡ኦህዴድ ወደ ሌሎች እህት ድርጅቶች እጅ ከመቀሰሩ በፊት የውስጡን ኪራይ ሰብሳቢ ማፅዳት አለበት፣ ብአዴን፣ ህወሓትም ደኢህዴንም እንደዚሁ፡፡

እነዚህ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ድርጅቶች በኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በየ ድርጅታቸው ብቻ ይታጠሩ ማለትም አይደለም፣ ደርግን ያሸነፍነው በየፊናችን በመሯሯጥ አይደለም በጋራ በመዝመት ነው፡፡ስለዚ ለኪራይ ሰብሳቢነት ትግልም በጋራም የምንዘምትበት ስትራቴጂ መኖር ኣለበት፡፡ ይህ ሲባል ግን የውስጣችን የማጥራት ስራ የያንዳንዱ ብሄራዊ ድርጅት ስራ ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለው የጣት ቅሰራ እየታዘብን ነው፡፡ ኦህዴድ የውስጡን ኪራይ ሰብሳቢ ሳይታገል ህወሓት ላይ ሲያነጣጥር ይታያል፣ ብአዴን የውስጡን ኪራይ ሰብሳቢነትን ሳይታገል እጁን ህወሓት ላይ ሲቀስር ይታያል፡፡ ይህ የተጀመረውን ይህዳሴ ጉዛችን ሊያደናቅፍና ሊያዘገይ ካልሆነ በቀር ሌላ እሚረባ ውጤት የለውም፡፡ እንደአብዮታዊ ዴሞክራቶች ከዚህ በፍጥነት ካልወጣን ነገ ወደማንወጣው ችግር እንገባለን፡፡

ሙሰኛ የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ የደኢህዴን ኣባል ወይም ኣመራር ከማንም በላይ የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ የደኢህዴን ጠላት ነው፡፡ የቆመለት ዓለላማ ፀር ነው፣ ኣደናቃፊ ነው፣ ፀረ ልማት ፀረ ህዝብ ነው፡፡ኢህአዴግ ኣባላቱ ኣመራሩ የማይበላሹበት የብፁኣን ስብስብ ኣይደለም፡፡ በየጊዜው ችግር የሚፈጥሩ ኣባላትና ኣመራር ሲያጋጥሙ እየገመገመ እያሸጋሸገ የመጣ ድርጅት ነው፡፡ ባካሄዳቸው የተለያዩ ተሃድሶዎች በኮር ኣመራሩ ችግር ሲፈጠር የተበላሸው ኮር ኣመራር ቆርጦ የሚጥል ድርጅት ነው፡፡ ኢህአዴግ በ1993 ዓ.ም. በተደረገው ተሃድሶ ሁሉንም እንደሚያስታውሰው፣ ኣሉ የሚባሉ፣ ተተኪ የላቸውም የሚባሉ የነበሩትን ሳይቀር ቆርጦ የሚጥልና መስመሩን የሚመርጥ ድርጅት ነው፡፡

ታድያ ለምንድን ነው ኣሁን ይህ ሁኔታ የማይታየው?

በሙሰኝነት የተዘፈቀ ኣመራር ለምን ይዘን እንጓዛለን?

በሙሰኝነት መዘፈቃቸው የሚያውቅ ኣመራር ለምን ዝምብሎ ያያል?

ለምን ኣይታገልም? ችግሩ /ሙስናው/ ለምን እንደማስፈራሪያ ይጠቀምበታል? ያልተመለሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ስለዚ ኣብዮታዊ ዴሞክራቶች ምን እያደረግን ነው? ምንድነው ይህ ሁሉ ዝምታ? ድርጅታችን ኢህአዴግ እየበሰበሰ ነው? ዝምታው ይሰበር?የኢህአዴግ ሊቀመንበርም መምራት ካለባቸው በደንብ ይምሩን፡፡ ሊቀመንበሩ በኪራይ ሰብሳቢነት ትክክለኛ ትግል የሚያደርጉ ከሆነ መጀመሪያ ኦህዴድ ላይ ያለውን ኪራይ ሰብሳቢነት ታግለው ያሳዩን፣ በሌሎች እህት ድርጅቶች የሚያውቁት ነገር ካለም ለየድርጅቶቻችን ይስጡንና መታገያ እናድርገው፤ ያግዙን፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት መረጃ እንደ ባንክ ቁጠባ አድርጎ መጠቀም ግን ትክክል አይደለም፡፡ ይውጣና ይመንዘር መታገያ እናድርገው!!!!!

ቸር እንሰንብት

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ሰኔ 12፣ 2010 ዓ.ም.


Back to Front Page