Back to Front Page


Share This Article!
Share
እውነት ይዘገያል እንጅ አይጠፋም የሚለው ዶ/ር አብይ ሊገነዘቡት የሚገባ ትልቁ የአበው ብሂል

እውነት ይዘገያል እንጅ አይጠፋም የሚለው ዶ/ር አብይ ሊገነዘቡት የሚገባ ትልቁ የአበው ብሂል

ከእውነቱ ይታያል 09-30-18

ዶ/ር አብይ አህመድን ለመደገፍ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. መስቀል አደባባይ ተደርጎ በነበረው ሰልፍ ላይ አረመኔያዊ የሆነ የቦምብ ጥቃት ተፈፅሞ የነበረ መሆኑ ለሁላችንም የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ ትዝታ ነው። በዚህ ጥቃት ወቅትም ሁለት ንፁሃን ዜጎች እንደተገደሉና ከአንድ መቶ ሃምሳ በላይ የሚሆኑ ደግሞ እንደቆሰሉ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል። ይህ የቦምብ ጥቃት እንደተፈፀመ ዶ/ር አብይ በብርሃን ፍጥነት በሚያስብል ደረጃ ጣታቸውን ማን ላይ ቀስረው እንደነበረ ሁላችንም የምንክደው አይመስለኝም። እርሳቸው መልእክት ሊያስተላልፉ የፈለጉት ድርጊቱን የፈፀሙት ሙያቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው አገር ለማተራምሰ በፈለጉ በህወሃት ዙሪያ ያሉ ሰዎች እንደሆኑ በሚያስመስል ሁኔታ ነበር። እንዲያውም የህወሃትን ሰዎች ለማጥቃት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረለኝ በሚል ይመስላል ኤፍ ቢ አይ (FBI) ገብቶ ምርምራውን እንዲያደርግ አስቸኳይ ፈቃድ የሰጡት። በተጓዳኝም የቀን ጅቦች፣ ፀጉረ ልውጦች፣ ሌቦች፣ ሆዳሞች፣ ቁማርተኞችና የመሳሰሉ ቃላትንና ሃረጎችን በመጠቀም ጣት መቀሰራቸውን ገፉበት። ይባስ ብለውም ባንድ ወቅት ሰብስበው ላወያዩዋቸው ምሁራን የኤርትራውን የአምባገነን ቁንጮ (በርሳቸው አባባል ኢሱን ውይም ወዲ አፎምን) ትግራይ ያልወሰድኩት እንደ አዲስ አበባ አይነት የቦምብ ፍንዳታ ቢያጋጥም ህዝብ ለህዝብ ያለው ግንኙነት ይሻክራል ብየ ፈርቸ ነው ብለው እንደተናግሩ ደጋፊዎቻቸው ሳት ብሏቸውም ቢሆን ሲያራግቡት ሰማን።

Videos From Around The World

ይህ በንዲህ እንዳለ ከጊዚያት በኋላ የተጠርጣሪዎቹ ስም ይፋ እየሆነ ሲሄድና ብዙዎቹ ከሌላ አከባቢ እንደሆኑ ይፋ እየሆነ ሲመጣ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው የዶ/ር አብይን ሃሳብ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ማስገባት ጀመረ። በዚህ መሰረትም ዶ/ር አብይ አሜሪካን አገር በነበራቸው ቆይታ በተለይም የትግራይ ተወላጆች ለምን ስለቦምብ ፍንዳታው ዝርዝር ጉዳይ አይገለፅም፤ መዘግየቱስ አግባብ ነው ወይ? የሚል መንፈስ ያለው ጥያቄ ይጠይቋቸዋል። ዶ/ር አብይም የሰጡት መልስ ሽብር የሚከናወነው ድርጊቱን በአካል በሚፈፅመው ሰው ብቻ ሳይሆን ከኋላ ሆኖ በሚጠነስሰው፣ በሚያቅደውና በሚያሳተባብረው ሰውም ጭምር ነው የሚል ነበር። በርግጥም ዶ/ር አብይ እንዳሉት አንድን ወንጀል በተለያየ ደረጃ በሚሳተፉ ሰዎች ሊፈፀም ይችላል። ዶ/ር አብይ ትክክል ያልነበሩት ግን ማስረጃ ሳይኖራቸው በስሜት ብቻ ተነሳስተው አንድን አካል ተጠያቂ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸው ነው።

ከላይ የተገለፁ ስሜታዊና ሃላፊነት የጎደላቸው ካንድ ያገር መሪ አፍ ቀርቶ ከተራ ሰው ሊወጡ የማይገባቸው መግለጫዎችና ንግግሮች ደግሞ ያስከተሉት ጉዳቶች በቀላሉ የሚገመቱ አይደሉም። በነዚህ መግለጫዎችና ንግግሮች የተነሳ ንፁሃን ተገድለዋል፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል እንዲሁም ብዙ ንብረቶች ወድመዋል። ከዚህ ባሻገርም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳይተማመኑ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በተጨማሪም እነዚህ መግለጫዎችና ንግግሮች ከደርግ ጋ በነበረው እልህ አስጨራሽ ትግል ወቅት ከልጅነት እስከውቀት ከፍተኛ ሚና የነበራቸውን የህወሃትና ለህወሃት የቀረቡ ናቸው የሚባሉ የኢህዴን ነባር ታጋዮችና አመራሮች ነጻ እንቅስቃሴን ገድበዋል። በነገራችን ላይ እነዚህ ነባር የህወሓትና የኢህዴን ነባር አመራሮች ባሳለፏቸው የትግል ጊዚያት የፈፀሟቸው በርካታ ጥፋቶች ቢኖሩም እንደዚህ አይነት አገር ሊያፈራርስ የሚችል እኩይ ተግባር ውስጥ ይገባሉ ብሎ ማሰብና እሱንም ሃሳብ በተለያየ መንገድ መግለፅ መነሻው አለመብሰል ብቻ ሳይሆን እኩይ አላማን ለማስፈፀም መደላድል ለመፍጠርም የታለመ ይመስላል። የነዚህ ሰዎች ህልም እንደዚህ የወረደ ቢሆን ኖሮ ወታደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ስልጣኑ በጃቸው ውስጥ በነበረ ጊዜ ሊፈፅሙት ይችሉ ነበር። ከዚህ አንፃር ሲታይ የዶ/ር አብይ መግለጫዎችና ንግግሮች ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ አይነት እንደነበሩ ከወትሮውም ግልፅ ነበሩ።

ከነዚህ የዶ/ር አቢይና ደቀመዝሙሮቻቸው መግለጫዎችና ንግግሮች በተጉዳኝ የህወሃት እንዲሁም የነሱን ሃሳቦችና እንቅስቃሴዎች የሚደግፉ ሰዎች በበኩላቸው ውንጀላዎቹ መሰረት የሌላቸው በማስረጃ ያልትደገፉ ናቸው በሚል ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል። ይልቁንም በዶ/ር አብይና በደጋፊዎቻቸው የሚሰነዘሩ ሃሳቦችና አስተያየቶች ከፋፋይና ለዴሞክራሲያዊ አንድነት የማይጠቅሙ ናቸው በሚል ያጣጥሏቸው ነበር። እነዚህ አካላት ይጎተጉቱ የነበረው ማንኛውም ጥርጣሬ መመርመር ያለበት የአገሪቱን ህገመንግስትና ሌሎች ህጎችን ተከትሎና ሁሉንም ባካተተ መሆን እንዳለበት ነበር። ይህ አቋም ደግሞ ወርቅና ምንም የማይወጣለት የተቀደሰ አቋም ነው። ይህ ሲባል ግን እነዚህ የህወሃት ሰዎች ችግር አያውቃቸውም ለማለት አደለም፤ አሁን ላይ የያዙት አቋም ትክክል ነው ለማለት እንጅ። ችግሮችን በተመለከተማ ቢዛቅ ቢዛቅ ሊያልቅ የማይችል ችሮች እንደፈፀሙ መካድ አይንን በጨው ታጥቦ እንደመዋሸት ያስቆጥራል። እንዲያውም እነዚህ የህወሃት ሰዎች ስግብግብነታችውና አልጠግብ ባይነታቸው በግር ቆሞ ይሄድ የነበረ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ባጠቃላይና የትግራይ ህዝብ ደግሞ በተለይ በገሃድ የሚያቀው ጉዳይ ነው። ከዚህ አልጠግብ ባይነታቸው የሚብሰው ችግራቸው ደግሞ ሌላው ሰው አያውቅብንም ብለው የራሳቸውን ቂልነትና ጀብደኝነት ሲያስመሰክሩ የነበሩ መሆኑ ነው። ይህም ቢሆን ግን የነዚህ ሰዎች ተጠያቂነት መወሰን ያለበት በስማ በለው፣ በስሜትና በመንጋ ፍርድ ሳይሆን በህግና በህግ አግባብ ብቻ መሆን እንደሚገባው ለአንድ ሰከንድም ቢሆን ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችል ጉዳይ መሆን የለበትም።

በዚህም አለ በዚያ የዶ/ር አብይ ደቀመዝሙሮች ከረጅም ጊዚያት ማመንታት በኋላ እየመረራቸውም ቢሆን በቦምብ ጥቃቱ ፈፃሚዎች ላይ ክስ የመሰረቱ መሆኑን ሪፖርተር የተሰኝው የአማርኛ ጋዜጣ በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል።

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በተፈመው የቦምብ ጥቃት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች የሽብርተኝነት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ክስ እንደገለው፣ ተከሳሾቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ላይ ግድያ ለመፈም ያነሳሳቸው በእሳቸው የሚመራ መንግሥት መኖር ስለሌለበት ነው፡፡ የአገሪቱ መንግሥት መመራት ያለበት ቀድሞ በተመሠረተው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ነው የሚል ዓላማ ተከሳሾቹ እንዳላቸው ዓቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ ጠቁሟል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም በማለትም፣ ተጠርጣሪዎቹ ለግድያ መነሳሳታቸውን ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡

አሁን ቁም ነገሩ ያለው ዶ/ር አብይ የተፈፀመውን የሽብር ድርጊት እንዴት አድርገው ከህወሃት ሰዎች ጋ በማያያዝ ይቀጥላሉ የሚለው ጉዳይ ነው። መቸም የኦነግን አመራሮች ያደራጇቸው የህወሃት ሰዎች ናቸው በሚል ከንቱ የመከራከሪያ ሃሳብ ይዘው ብቅ አይሉም። ምክንያቱም ያሁኑን አያድርገውና በወቅቱ ከህወሃት ሰዎች ይልቅ በግልፅ ጦርነት አውጆ ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦነግ ሃይል እንደነበረ ማንኛውም ንፁህ አምሮ ያለው ሰው ሊረዳ ይችልላልና። ከዚህ ስንንነሳ ታዲያ የቀን ጅቦቹ እነማን ናቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ካሁን የበለጠ ጊዜ የለም የሚል አቋም ላይ ደርሻለሁ።? በእኔ እምነት "የቀን ጅቦቹ" ሽብሩን የፈፀሙት በኦነግ ዙሪያ ያሉ ሰዎችና ሌሎች ሁኔታውን ሳያጣሩ ሌላውን ለመብላት በማሰብ ጣታቸውን የቀሰሩ ሃይሎች መሆናቸው አጠያያቂ አይደለም። እዚህ ላይ ተረት አበዛህ እንዳትሉኝ እንጅ አያ ጅቦ ሳታመሃኝ ብላኝ የሚለው አባባልም ሁኔታውን ሳይገልፀው አይቀርም። ለማንኛውም ይህ ክስተት "እውነት ይዘገያል እንጂ አይጠፋም" የሚለውን የአበው አገላለፅ ህያውነት በግልፅ ያሳየ ገሃድ ማስረጃ ሆኖአል። ወደፊትም ቢሆን ሌሎች ውንጀላዎችን በተመለከተ እውነታው ሲገለፅ ወንጃዮቹ እርቃናቸውን ይቀራሉ ብሎ ለመናገር "ጠንቋይ" መቀለብ አያስፈልግም። ከዚህ ይልቅ ሂደቱ የሚያሳየን ሽህ አመት ላማይኖርበት ጊዚያዊና ከንቱ አለም "እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር ይሻላል" የሚለውን ብሂል እንደ ህይወት መመሪያ አድርጎ መያዝ ጠቃሚ መሆኑን ነው።

Back to Front Page