Back to Front Page


Share This Article!
Share
አንድ ሥንሆን ዓለም ያከብረናል!

አንድ ሥንሆን ዓለም ያከብረናል!

ወንድይራድ ሃብተየስ 08-05-18

አንድ እንሁን ማለት አንድአይነትነት ማለት አይደለም። አንድ እንሁን ሲባል ብዝሃነት ይጥፋና አንድቋንቋ፣ አንድሃይማኖት አንድአስተሳሰብ ይኑረን ማለት አይደለም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንድ እንሁን ሲሉ አገራዊ መገባባት ይጎልብት፤ የጋራ አገራችንን በጋራ እንገንባ፤ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ እናራምድ፣ ፍትሃዊነት ይንገስ ማለታቸው ነው። በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶስት የአሜሪካ ከተሞች ያደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያዊያኑንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን አንድያደረገ በመሆኑ በዲሲ፣ ሎስ አንጅለስና በኒኖሶታ የኢትዮጵያዊያን ቀን አስብለው እስከማስወሰን ደርሰዋል። አያችሁ እኛ አንድ ስንሆን መፍጠር የምንችለውን ሃይል! ይህ ነው የመደመር ፖለቲካ ትርፉ!

ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፖለቲካ አንዳንዶች ለርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ ሲያውሉት ይስተዋላሉ። ለመናኛ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ነገሮችን ማጣመም፤ በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር ወይም ጥርጣሬ ለመንዛት መሯሯጥ ለማንም የሚበጅ አይሆንም። ከባለፈው 27 ዓመታት በአገራችን የነበረው የመጠላለፍ ፖለቲካ ሄዶ ሄዶ የት እንዳደረሰን መዘንጋት የለብንም። ባለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት በርካታ መልካምና መጥፎ ሁኔታዎችን ማሳለፋችን ትምህርት ሊሆነን ይገባል። ዛሬ ከትላንት ስህተታችን ልንማር ይገባል፤ እኔ ብቻ ከሚል የፖለቲካ አካሄድ መላቀቅ መቻል አለብን። አግላይ የፖለቲካ አካሄድ ከ27 ዓመታት ብኋላ ምን ላይ እንዳደረሰን ምን ዋጋ እንዳስከፈለን መገንዘብ ይኖርብናል።

እውነት እንነጋገር ከተባለ ከዛሬ አራትና አምስት ወራት በፊት በአገራችን የነበረው ሁኔታን ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ከነበረው የ1983 ዓ.ም ጋር ብናነጻጽረው በቅርቡ የነበረው ሁኔታ የከፋ ይመስለኛል። በ1983 ዓ.ም በአገራችን የታጠቁ ሃይሎች ይኑሩ እንጂ ህብረተሰቡ በብሄርና ሃይማኖት የተከፋፈለ አልነበረም። በ1983 ዓ.ም መንግስት አልባ ሆነን ሳለ እንኳን በህዝቦች መካከል በብሄርና በሃይማኖት ተቧድኖ ግጭት አልነበረም፤ በእርግጥ እየዋለ ሲያድር አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች መርዛማ ፖለቲካ መረጨት ሲጀምሩ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭት አልነበረም ማለት ባይቻልም እንደአሁኑ የገነገነ አልነበረም። በ1983 ዓ.ም እንደዳሁኑ የከፋ ጎጠኝነት፣ ዘረኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት በአገራችን አልነበሩም። በዚህ ሳቢያ የህዝቦች አብሮነት ከአሁኑ እጅግ የተሻለ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

Videos From Around The World

ይሁንና ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በአገራችን የነበረው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነበር። ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በአገራችን መንግስት እያለ ዜጎች በብሄራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ወይም በሚያራምዱት ሃሳብ ሳቢያ በጠራራ ጸሃይ ተገድለዋል፣ ከበርካታ አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ እነርሱ ተገርፈዋል፣ ተሰደደዋል፣ ወዘተ። በአጭሩ ህዝቦች በብሄር፣ ሃይማኖትና በጎጥ ተከፋፍለው ዕርስ በርሳቸው መበላላት ደረጃ ላይ ደደርሰው ነበር። አገራችን ልትፈርስ አንድ ሃሙስ የቀራት መስላ ነበር።

እንግዲህ ለክቡር ጠቅላይ ዶ/ር አብይ ያስረከብናቸው አገር እንዲህ ያለች ልትፈርስ አፋፍ ላይ የደረሰችና የተውገረገረች አገርን ነው። ዶ/ር አብይ በተከተሉት ብልሃት የተሞላበት አካሄድ አገሪቱን ከመበተን አደጋ ታድረዋታል። የእኚህ ሰው የመደመር ፖለቲካ አገራችንን ከመበተን ታድጓታል፤ የህዝብን ስቃይ አስወግዷል፤ አብሮነትን አጠናክሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከተሉት የመደመር የፖለቲካ አካሄድ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን ባህር ማዶም ተሻግሮ ውጤት አምጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ አገራት ያካሄዷቸው ጉብኝቶች ለአገራችን እና ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም መሰረት መሆን ችለዋል። ዛሬ ላይ አገራችን ከሁሉም የጎረቤት አገራት ጋር ጥሩ ግብብነት መስርታለች። በቅርቡ በሶስት የአሜሪካ ከተሞች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ያደረጉት ውይይት እጅግ ስኬታማ ነበር። በእርሳቸው የአቀባበል ስነስርዓት ላይ ኢትዮጵያዊያኖችና ትውለደ ኢትዮጵያዊያኖች ብቻ ሳይሆኑ ኤርትራዊያኖችም ጭምር ተሳትፈዋል። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዲሲ፣ ሎሳንጅለስና ሚኒሶታ ባካሄዱት ጉብኝት በዳያስፖራው የነበረውን የጥላቻ ፖለቲካ ከማስወገዱም ባሻገር ለአገራችን የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እጅግ ከፍ ያለ ነው።

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በውስጥም ይሁን በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የአብሮነት መንፈስ አነቃቅቷል፣ ዲያስፖራው በአገሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በቀጥታ ተሳትፎ እንዲኖረው ዕድል ፈጥሯል። ዳያስፖራው ቀድሞ በነበረው የመንግስት ሁኔታ መገለልና አድልዖ ይደርስበት ስለነበር በታሪክ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለኢትዮጵያ መንግስት መልካም እይታና ድጋፍ ኖሮት አያውቅም። በተመሳሳይ መንግስትም ዳያስፖራውን ቀርቦ በማነጋገር ችግሩን መፍታት ሲገባው፤ ማዶ ለማዶ የሚያስኬድ የፖለቲካ አካሄድን ከመከተሉ ባሻገር የተለያዩ ተቀጽላዎችን ለዳያስፖራው በመስጠት አገር ከዳያስፖራው ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ እንድትቀር አድርጓታል። ዛሬ ይህ ሁኔታ ተቀይሯል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ እኛ ስንደመር እኛ አንድ ስንሆን ዓለም ያከብረናል ያሉት የአሁኑ የአሜሪካ ጉብኝት ጥሩ ማሳያው ነው። የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የዓለም ባንክ እና የአይ ኤም ኤፍ ፕሬዝዳንቶች በኢትዮጵያ ለተጀመረው ለውጥ በማድነቅም በአገራችን እየተካሄዱ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች በሁሉም መንገድ ድጋፍ እንደሚሰጡ አሳውቀዋል። እንዲሁም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩበት የስደት አገር ዕውቅና እንዲያገኙ ሆነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀደዱት የአንድነትና የመደመር የፖለቲካ አካሄድ ምን እያሰገኘ እንደሆን ማየት የሚከብድ አይደለም።

ባለፉት 27 ዓመታት በአገራችን ይስተዋል የነበረው የፖለቲካና ማህበራዊ መዛነፎች ሳቢያ በቤተ ዕምነት ሳይቀር መቆራቆስና መለያየትን እንደፈጠረ የአደባባይ ሚሲጢር ነው። ዛሬ ላይ አንዳንድ ወገኖች ህገመንግስት ተጣሰ እያሉ ሲጮሁ እናደምጣለን። እውነት ነው ህገመንግስት ተጥሶ ከሆነ መስተካከል አለበት ባይ ነኝ። ይሁንና ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ እውነት በኢትዮጵያ ህገመንግስት አለ የሚያሰኝ አልነበረምን? በእውኑ ህገመንግስት ሰው ግረፉ ሰው አሰቃዩ ይላልን? ህገመንግስት ሰው አኮላሹ ይላልን? ህገመንግስት ሰው ቶርች አርጉ ይላልን? ህገመንግስት ተጣሰ ማለት የነበረብን ዛሬ ላይ ሳይሆን ቀድሞ በዚያን የስቃይ ወቅት መሆን ነበረበት። ዛሬ በእኛ ላይ ስለመጣ ጥቅማችን ይነካል ብለን ስናስብ መሆን የለበትም። ዕውነት እንናገር ከተባለ ባለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ህገመንግስት ሲጨፈለቅና ሲደፈለቅ አባት ነኝ የሚል አካል ነበረን?

መንግስትና ሃይማኖት አንዱ በአንዱ አሰራር ጣልቃ እንዳይገባ በህገመንግስታዊ ገደብ ቢበጅላቸውም፤ መንግስት በተለይ በሁለቱ ሃይማኖቶች እንዳሻው ጣልቃ በመግባት የማይፈልገውን አካል ከሚያጠቃበትና የሚያስጠቃበት መንገድ እንደነበር እማኝ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ከመንግስት ጋር ቅርበት አለን የሚሉ አካላት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እንደፈለጉት በመግባት ዘረኛ ፖለቲካዊ አስተሳሰብን ዘርተዋል፤ ሌብነተን አስፋፍተዋል። ይህ የአደባባይ ሚሲጢር ነው። ዛሬ ላይ እኮ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ለመሾም እጅ መንሻ እስከማቅረብ እንዲሁም የሙዳይ ምጽዋት ሳይቀር የሚመዘበርበት ሁኔታ መኖሩን ከምዕመን የተደበቀ ነገር አይደለም። ይህን የተቋወመ አካል እስከቅርብ ጊዜ አልተመለከትንም ነበር። እድሜ ለዶ/ር አብይ ሁኔታዎችን ቀይረዋቸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ወደአገር መመለሱ ቤተክርስቲያኗ በአንድ ሴኖዶስ መመራት መቻሏ የሁለቱንም አባቶች ቅንነት የሚያሳይ ነው። ፓትሪያርኩ አቡነ ማትያስ እውነት መንፈሳዊ አባት ናቸው። በእርሳቸው ጊዜ ነው ቤተክርስቲያናችን ወደ አንድነት የመጣችው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የሰሩት ታላቅ ስራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለዘለዓለሙ ሲዘከሩ የሚኖሩ ታላቅ መሪ እንዲሆኑ አርድጓቸዋል። እውነት ነው ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ባይመጡ እነዚህ ሁለት ሴኖዶሶች ምንአልባት ለዘለዓለሙ ተለያይተው ይኖሩ ነበር። አገራችን የተያያዘችው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ በሁሉም መስክ አገራዊ መግባባት እንዲጎለብት እርቅ እንዲወረድ ዶ/ር አብይ እየተከተሉ ያሉት ስትራቴጂ ስኬታማ ሆኗል።

 

Back to Front Page