Back to Front Page


Share This Article!
Share
የአንድነቱ መንገድ

የአንድነቱ መንገድ

 

ከብርሃኑ ተሰማ(ኢዜአ)

12-27-18

 

ስምሪቱ

 

ባለፈው ወር አጋማሸ ወደ ተባበሩት መግሥታት ስብሰባ ማዕከል የተላክሁበት ጉዳይ ለእኔ ለየት ያለ ነበር። በተለምዶ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን (ኢ ሲ ኤ)በውስጡ በመያዙ በዚሁ ተቋም ወደሚጠራው አዳራሽ ማለት ነው።ሥፍራውን በተደጋጋሚ ለሥራ ሄጄበት ሙያዊ ግዴታዬን ተወጥቼበታለሁና አዲሴ አልነበረም።

 

ኃላፊዬ ወደዚህ ቦታ እንድሄድ ሲነግረኝ ስብሰባውን ተሳትፌ ጠቃሚ ነገር ይዤ እንድመጣ መሆኑ አያጠያይቅም። ቢያንስ በተላክሁበት ርዕሰ ጉዳይ ያለኝን ዕውቀት ለማዳበር ወደ ሥፍራው አቀናሁ።ለዘገባው ተጨማሪ ባልደረቦች እንዳሉኝ በማወቅ ወደዚያው አመራሁ።

 

ወደ ጉባዔው አዳራሽ የሚያስገባኝ ባጅ ተዘጋጅቶልኝ ገባሁ።አስቸኳይ ከመሆኑ የተነሳ ሊሆን ይችላል ፎቶ አላነሱኝም።የትኛውን ተቋም ወክዬ እንደምሳተፍ የጠየቀኝ ባለመኖሩ በባጁ ላይ የሰፈረ ነገር የለም።ነገር ግን አገሬን ወክዬ እንደምገባ አውቃለሁና። አልተቸገርኩበትም። የአፍሪካን አህጉር የሚወክሉ ተሳታፊዎች ይሳተፉበታል በተባለው አዳራሽ በኢትዮጵያ ወንበር የተቀመጠ የለም።ደፍሬ ሄጄ አንዳልቀመጥ ዜግነት እንጂ፤ውክልና የለኝም።የመወያያ አጀንዳው ከሙያዬ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያልነበረው መሆኑም የራሱ ተጽዕኖ ነበረው።ምንም እንኳን ጋዜጠኝነት ከሁሉም ሙያዎች ልምድ የሚቀሰምበትና የሚዘገብበት ሙያ ቢሆንም።ከሴኔጋል ልዑካን ቡድን ጀርባ ከገባሁበት በር ብዙም ሳልርቅ ተቀመጥኩኝ።

Videos From Around The World

 

የስብሰባው መክፈቻ ንግግሮች ተራ በተራ እየተካሄዱ ነው።የስብሰባውን ምንነትና አጀንዳዎችን ከያዙት ዶኩመንቶች ጋር የተሰጠኝ መርሐ ግብር በፈረንሳይኛ ቋንቋ በመዘጋጀቱ የተናጋሪዎችን ማንነት ለመለየት አልተቸርኩም።ማዕረግ፣ኃላፊነትና የሚወክሏቸውን ተቋማት ስሞች መለየት ግን ግራ ሲያጋባኝ ቆየ።

 

ኢትዮጵያን አገኘኋት

 

በመድረኩ መካከል የአገሬ ተወካይ በክብር ስምና ኃላፊነታቸው እየተጠሩ ንግግሮች መካሄድ ቀጥለዋል።ኋላም ራሳቸው ተናጋሪ ሆነው የመንግሥታቸውን መልዕክትና በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም ያብራሩ ገቡ።የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር የስብሰባው የክብር እንግዳና የአስተናጋጇ አገር ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው።በአንድ ጎናቸው የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ኮንፍረንስ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሚስተር ሙክሂሳ ኪታዪ፣በሌላው ጎናቸው ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ቶማስ ኪዌሲ ኳርቴ ይገኛሉ። የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ቬራ ሴንጋዌም በመድረኩ ከተሰየሙት ባለሥልጣናት መካከል ናቸው።

 

ሚኒስትሯ የወጪ ንግዷን ለማቀላጠፍ እያደረገች ያለችውን እንቅስቃሴ በስፋት የዳሰሱበትን ንግግር አደረጉ።ከጅቡቲ በተጨማሪ ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው የሰላም ስምመነት ወደቦቿን ለመጠቀም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አንዱ ነጥብ ሲሆን፤የደረቅ ወደቦች ጉዳይ ሌላኛው ማጠንጠኛቸው ነበር።አህጉራዊ ስብሰባ በተጠራበት ጉዳይም አገሪቱ ቁርጠኛ አቋም የያዘችበትና ንግድ በተቀላጠፈ መንገድ ለማካሄድ የሚደረገውን ጥረት እንደምትገፋበት አረጋገጡ።

 

ሁሉም በአንድ ጉዳይ ለአንድ ዓላማ የመጡበትን ጉዳይ ይናገራሉ።በተለይ ዛሬን ከነገ ከማገናኘት።ትናንትን በአላፊነቱ ያወሳሉ።ወደፊት ዛሬን ሳይነጥል ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል።እንዴት አብረን እንስራ ዓቢዩ የመነጋገሪያ ነጥብ ሆኗል።

 

አፍሪካን ከሌሎች አህጉሮች

 

ዓለማችን እንደ መንደር እየጠበበች መምጣቷን ለማመልከት በይነ መረብን መመልከትብቻ በቂ ነው።በእርግጥም በይነ መረብ በዕለት በዕለት ሕይወታችን በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ያለውን ድርሻ ስንመለከት እውነትነቱ አያጠያይቅም።በይነ መረብን ላይ ማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሲታከሉበት ልማቱንም ጥፋቱንም እያየነው ነውና ምድሪቱን የሚያገናኘው መሣሪያ ያለውን ኃይል እንገነዘባለን።

 

 

ፕላኔታችን በምታከናውነው እንቅስቃሴ የጋራነትን ታሳቢ ማድረጋቸው እሰየው የሚያሰኝ ቢሆንም፤አንዱ በፍጥነት፤ሌላው ዘግየት የሚሉባቸው ሁኔታዎች ያጋጥማሉ።ሁለቱንም ለማጣጣም ደግሞ የሚከናወኑ ተግባራት አሉ።እንድሳተፍበት የተላክሁበት ስብሰባ ይህንን ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ አህጉራዊ መድረክ ነበር።የአፍሪካ የመጀመሪያው የንግድ አቀላጣፊ ኮሚቴዎች መድረክ የተሰኘ።

 

ንግድን ማቀላጠፍ ሲባል

 

ንግድ ማቀላጠፍ በመሠረቱ የንግድና የልውውጭ ሂደትን ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ ማከናወን ነው።በዚህም ለሸቀጦች እንቅስቃሴ ሂደቶችንና ተያያዥነት ያላቸውን አገልግሎቶች በሰመረ መንገድ ማካሄድንና አገልግሎቶችን ከሻጭ ወደ ገዢ ማስተላለፍና ክፍያዎችን መፈጸምን ይጨምራል።መሠረታዊ ዓላማው የአገር ውስጥ ወይም ዓለም አቀፍ ንግድን ማቅለል ነው።የንግድ ልውውጥ ያለ ምንም እንቅፋትና ጫና ሳይደናቀፉ እንዲካሄዱ ማድረግ ነው።

 

ንግድ ማቀላጠፍ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ያካትታል

 

ማቅለል-የንግድ አካሄዶች ድግግሞሽ ያሉባቸውን አሰራሮች እንዲያስወግዱ ማድረግ-ወጪና ጫናን መቀነስ።

 

ማስማማት- በአገር ውስጥ ገበያ ወይም በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የሸቀጦችና የምርቶች እንቅስቃሴ በመረጃ ታግዞ ማከናወን።

 

ደረጃ መጠበቅ (ስታዳንዳርዳይዜሽን)-ተፈላጊው መረጃ በአግባቡ መቅረቡ፣መግባባትና ትግበራው በተገቢው ሁኔታ መከናወኑን ማረጋገጥ ።

 

መንግሥታት የንግዱ ሂደት እንዲቀላጠፍ ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ዘመናዊነትን በጠበቀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል።

 

መድረኩ የዓለም ንግድ ድርጅት የንግድ ማቀላጠፊያና የአፍሪካ ነፃ የነገድ ቀጣና ስምምነቶች ከተደረሱ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተደረገ መድረክ ሆኗል።የዓለም ንግድ ድርጅት ስምምነትን 31፣ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ደግሞ 10 አገሮች በፓርላማዎቻቸው አጽድቀዋል።

 

የግሉንና የሕዝብን ዘርፎች በማቀናጀት በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮችን በተለይም የአፍሪካን ሕዝብ ሕይወት ለማሻሻል የሚጥረው ድርጅት ከሰባት አጋሮቹ ጋር ያዘጋጀው ስብሰባ ለሦስት ቀናት ተካሂዷል።ወጪ፣ጊዜና በዓለምና በአፍሪካ ነገድ የሚታዩትን ውስብስብ ሂደቶች መቀነስ ዋነኛው ዒላማው አድርጎ መነሳቱ ተገልጿል።ለዚህም አገሮች ብሄራዊ ኮሚቴዎችን አቋቁመው ለተቀላጠፈ የንግድ ሂደት ተቀናጅተው ለመሥራት ተስማምተዋል።

 

 

የዓለም ንግድ ድርጅት ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው አሁን በምድራችን እየተካሄደ ባለው ንግድ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮችን በዓለም አቀፍ ንግድ ዝውውር 219 በመቶ ታሪፍ በመጣል ጉዳት እያደረሰባቸው ነው።የአፍሪካ መንግሥታት በየአገሮቻቸው በመሰረቷቸው ብሔራዊ ኮሚቴዎች አማካይነት የንግድ ሂደቱንና የአገር ውስጥ ንግድ ሥራቸውን ለማቀላጠፍ ስምምነቶቹን በመተግበር ጫናውን ወደ 15 በመቶ ማውረድ ይችላሉ።ይህም አገሮች የታክስ አሰባሰባቸውን ያሻሽላቸዋል። የጸጥታና ደህንነት ተግባራት የተሻለ ደረጃ ላይ ይሆናሉ።በተለይ የምግብ ደህንነት ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎም ይገመታል።

 

ለዓለም ገበያ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶችን ለማቅረብና ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ እንደ ድንበር ላይ ንግድ፣ሴቶችን በንግድ ሥራዎች በማብቃት ንግድ ተጠያቂነት ግልጽነት በተሞላበት ሁኔታ ይካሄዳል ተብሎም እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

 

መልካም አስተዳደርን ለማራመድ፣ጥራት ያላቸው ሠራተኞች ለማፍራት፣የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብቃትን ለማሻሻልና አስተዳደራዊ ብቃትን የተላበሰ ዘመናዊ ኅበረተሰብ በመገንባት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታምኖበታል።

 

የንግዱን ሂደት ማቀላጠፍ ሰብዓዊና ተቋማዊ ልማትን ለማምጣት አዎንታዊ ዕድገት የሚመዘገብበት ሁኔታ ይፈጥራል።ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ይረዳል ተብሎም ተስፋ ተደርጎበታል።

 

መወያያዎቹ

 

የክፍለ አህጉራዊ ንግድ ድርጅቶች ሚና፣ብሔራዊ ኮሚቴዎችና የአፍሪካ የነፃ ንግድ ስምምነት ያላቸው ድርሻ፣ወረቀት አልባ ተግባራት ንግድ ማቀላጠፊያ ሂደት፣የግሉ ዘርፍ በብሔራዊ ኮሚቴዎች ያላቸው ተሳትፎ፣የድንበር ላይ ተቋማት እንቅስቃሴ በማቀናጀትና የትራንዚት ኮረደሮች ሚና የጉባዔው መወያያ አጀንዳዎች ነበሩ።በተጨማሪም የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በወደፊቱ ዓለም አቀፍ የንግድ ልወውጥ ያለው ሚና አንደኛው መነገጋገሪያ ሆኖ አልፏል።

 

ምን እንውሰድ?

አህጉረ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ዘመናት በኋላ ፖለቲካዊ ነፃነቷን ተቀዳጅታለች።ከነችግሮቿና ከዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎች ጋር።ኢኮኖሚው በአምባገነንና ጨቋኝ መሪዎች ቁጥጥር ፣በሙሰኞችና በውጭ ኃይሎች ተይዞ ሕዝቦቿን ከድህነት ሳያወጣ ባለበት አለ።ያልተመጣጠነ የንግድ ልውወጥም ሲጎዳው ኖሯል።

 

አህጉሪቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2063 ልትደርስበት የያዘችው ራዕይ አላት።የተዋሃደች፣የበለጸገች፣ሰላሟና ደህንነቷ የተጠበቀ አህጉር ሆና መገኘት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ12 ዓመታት በኋላ ሊያሳካ ያቀደውን

የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካትም ቀና ጎንበስ እያለች ነው።

 

ኢኮኖሚ የደም ሥር፤ንግድ ደግሞ መሠረቱ እንደመሆኑ መጠን ቀልጣፋና ሕዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምምነቶች ትግበራ በአግባቡ ከተከናወነ፤ዓለም አቀፍ ንግዷን ሥርዓት ባለው መልኩ ለመምራት አያዳግታትም።

 

ኢትዮጵያ

የዓለምም ሆነ የአፍሪካ ንግድ ቅልጥፍናዋን ለማራመድ የጀመረችው ጥረት በጅምር ላይ እንደሆነ ከሚኒስትሯ በስተቀር ማንም ያልነበረበት ወንበሯ አመልክቷል። ካቢኔው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ከመሆኑ አኳያና ስምምነቶቹ ወደ ተግባር መለወጥ ከጀመሩ ገና አንድ ዓመት ካለመሙላቱ አንጻር መንግሥትን ለማማት እንኳ ያስቸግራል።ስምምነቶቹ የተፈረሙበት ቀለም ገና ያደረቀና በኢትዮጵያ መንግሥትንና ካቢኔው ተዋቅሮ ሥራ ለመጀመር ጊዜ መውሰዱ አልቀረም።ስለዚህም ብሔራዊ ኮሚቴው ገና በመመስረት ላይ በመሆኑ ሚኒስትሯ በክብር መቀመጫቸው ላይ ሲሆኑ በተሳታፊዎች ወንበር ላይ ያለው መቀመጫ ለጊዜው ባዶ ነበር።

 

አህጉሩ ንግዱን ሲያቀላጥፍ፤ሕዝቦቿን የተሻለ ሕይወት እንዲመሩና ከሌሎች አህጉሮች ጋር ለመስተካከል ተግቶ መሥራትን ይዞ ነው።የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ ኢትዮጵያን አስመልከተው አንድ ነገር ጣል አደረጉ።''ኢትዮጵያ በየቀኑ ተዓምር የሚነግሩን መሪ አግኝታለች'' አሉ። ሚስተር

ኳርቴ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን አመራርና ለውጥ አራማጅነት ለመግለጽ ከነዚህ ቃላት በላይ አልተናገሩም።በአገር ውስጥና በአካበቢው አገሮች ብሎም ለእህጉሪቱ ያላቸውን ራዕይ በአግባቡ የተረዱ ይመስላሉ።

 

አዎን።ምክትል ሊቀመንበሩ ጥሩ አይተውናል።አገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለች።ከራሷ አልፎ ጎረቤቶቿንም ወደ ውህደት የሚያመጣ እንቅስቃሴ እያደረገች ለመሆኑ እኛው ለራሳችን በምንሰጠው ምስክርነት ሳይሆን፤አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚመሰክሩላት ጉዳይ ሆኗል።

 

 

ከኤርትራና ከሶማሊያ ጋር በዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተጀመረው ግንኙነት ወደ ጅቡቲ፣ሱዳን፣ደቡብ ሱዳንና ኬንያ መስፋት ይችላል።በጊዜ ሂደትም ወደ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ዑጋንዳና ቡሩንዲ ሥር ሰዶ ኢኮኖሚያዊ ውህደት መፍጠር አያዳግተውም።

 

በውጭ በስደት ይኖሩ የነበሩትን ፖለቲከኞች፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞችን ለአገራቸው አፈር የበቃው ለውጥ፣ይቅርታና ምህረትን አንግቦ የተንቀሳቀሰው አዲሱ አመራር እያስመዘገባቸው ባሉ ለውጦች የኢትዮጵያውያንና የትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው የታሪክ አጋጣሚ ነው።

 

ይህቺ አገር በታሪኳ ለውጭ ዜጎች ጥገኝነትን በመስጠት ተወዳዳሪ ያላት አትመስልም።በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እያስተናገዷቸው ያሉትን የሶሪያና የየመን ስደተኞችን ማየት በራሱ ከየትም ይምጡ የተቸገሩና የተፈናቀሉ ሰዎችን ዛሬም ከአፋችን ነጥለን ለማስተናገድ የማንሳሳ መሆናችን ማሳያ ነው።ቀደም ሲል የገቡትን የጎረቤት አገሮች ስደተኞች መስተንግዶዎችን ያተረፈልን ስምና ክብር ሳይዘነጋ።

 

ታዲያ ኢትዮጵያዊ ብሄር ለይቶ ሲተነኳከስ ማየት አያሳፍርም በገዛ አገሩ? የውስጥ ተፈናቃዮች መበርከትስ ፈጣን ምላሽ አያስፈልገውም?

 

ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታና ለአፍሪካ ኅብረት በጽናት የታገለችው አገር ውስጣዊ ሰላሟ የተናጋና ዘረኝነት እየበቀለባት መሆኑ ሲታይ መሥመር ስተናልና ወዲህ በል ለማለት ነገን መጠበቅ የግድ አይልም።በዓለም አቀፍ መድረኮች በሰላም ማስከበር ተልዕኮዋ የምትመረጥና የምትጠቀስ አገር ባለቤት ሆነን መከላከያ ሠራዊት የውስጥ ሰላማችንን ለማስከበር ግዳጅ ሲቀበል ከማየት በላይ አሳፋሪ ነገር ያለ አይመስልም። ምክንያቱንም ስለማይመጥነን።

 

በፈጣን ልማትና ዕድገት ዓለም ባወቃት አገር ሙስናና ሌብነት የገነነባት ሆኖ መገኘቷም አስገራሚ፣ብሎም አሳዛኝ ሆኗል።እምነት የት ገብቶ? በዜጎች ላይ መጨከንስ ወዴት ተረስቶ ተብሎ ያሳምማል።ለአፍሪካውያን ነፃነት የታገለቸው ኩሩዋና የአፍሪካና የተጨቆኑ አገሮች ሕዝቦች መመኪያና መኩሪያዋን አገር ታሪኳንና ማንነቷን ካለማወቅ አልያም አውቆ ከማጥፋት ይቆጠራልና ወደ ቀልብ መመለስ ይበጃል።

 

ኢትዮጵያውያን ዓለምን ያስደመመ ለውጥ ጀምረናል።ድጋፉንም እያገኘን ነው። ዛሬ 1953 ወይም 1966 አይደለም።ዳግም የማይቀለበስ ለውጥ በማምጣት ሕይወታችንን ለማሻሻልና ወደተሻለ ከፍታ ለመውጣት አኮብኩበናል።ማረፊያው ትልቁ ማማ ነው።የኋሊዮሽ ጉዞ አይታሰብምም። አፍሪካ እርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ተነስቷል።በሂደትም አንድ አህጉር አንድ አገር ይሆናል።ቢያንስ መንገዱን ጀምሮታል።ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሞዴል ሆና ኖራለች።በአሁኑ አያያዟ ደግሞ መሪነቱን ልክ እንደ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷ መያዟ አይቀሬ ነው።የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር እንዳሉት ''ተዓምር'' የሚቀጥለው አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነን በጋራ ስንሰራ ነው።ችግሮቻችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት እየፈታን ለውጡን እናራምድ።ያለበለዚያ መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን ባለፈ፤መጨረሻችን ሳያምር ይቀራል።ሰላም !!!!

 

 

Back to Front Page