Back to Front Page


Share This Article!
Share
የኢትዮጵያ መንግስት በ2011 ምን ቢያስብ ጥሩ ነው?

የኢትዮጵያ መንግስት በ2011 ምን ቢያስብ ጥሩ ነው?

ዮሃንስ አበራ አየለ (ዶ/ር፣ ተባባሪ ፕሮፌሰር) 09-12-18

ከነገረ ቀደም እኔ ተደምሬያለሁ!! "ድምሩ ከይዘቱ የላቀ ነው" በሚለው ሃይለቃል መሠረት። ስውየውንም (ጠቅላሊ ምኒስትሩ) ስብእናውን ሳየው "ኢትዮጵያዊ" ለሚለው ቃል ስጋ የለበሰ የመዝገበ ቃላት ትርጉም ሆኖ ታይቶኛል። እድሜ ይስጥህ ልጄ!! ታላቅ ወንድምህንም (ኢሱ) ወደ እናቱ ቤት እንዲመለስ ስለረዳኸው ሁለታችሁም ተባረኩ ታሪክ ስርታችኃል ብያለሁ፡፡

እሁን ክቡርነትህን የምለምንህ የሚከተሉትን እንድታስብባቸው ነው። ከተሳሳትኩ አርመኝ።   

1. ተፈጥሮ ሃብትን የማይጎዳ የኢኮኖሚ እድገት (ወርቅ እንቁላል የምትወልደውን ደሮ አለማረድ)። ጣና ሃይቅን ያንን ያገር አድባር ዝም ብሎ ማየት ምን ይባላል? አገር አቀፍ ኮሚቴ ቢመሰረት እኔ በአራት እጄ በነፃ አገለግላለሁ፡፡ የአቢጃታና የሃዋሳ ሃይቅም ነገር ይታሰብበት። አንዱ እንደ ውቡ ሃረማያ አይናችን ስር ሆኖ እየጠፋ ነው፤ ሌላውም የ ላቦራቶሪ ብልቃጥ እየሆነ ነው። ሀሮ ደምበልም ጤና ርቆታል። በየቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ከመናገር ተግባር ላይ ጊዜያችንን ብናውለው። አንድ ቶን ግንዛቤ መፍጠር አንድ እፍኝ ተግባር አይሞላም። የአበባ እርሻዎች ከርሰ ምድር ውሃ ያለ ገደብ እየቀዱም እፈርና ውሃውን እየመረዙብን ነገ የ አዋሽና የሰምጥ ሽለቆ ትውልድ መርዝ ሊጠጣ ነው ወይስ አበባ ሊበላ? ዶላርና የትውልድ የወደፊት እጣ ሚዛን ይጠበቅ። ያካባቢ ጥበቃ ምሁር ነኝና ያመኛል።

Videos From Around The World

2. የሚጨማለቁ ሀብታሞችን የሚያበዛ ሳይሆን የድሀን ቁጥር የሚቀንስ የኢኮኖሚ እድገት ማጠናከር።

3. ከላይ እስከታች ድረስ ሹመትና ምደባ በጎጥና በጎሳ ሳይሆን በችሎታና በግልፅነት ይሁን።

4. ለአገልግሎት ሰጪዎችና አሽከርካሪዎች ሁሉ የግብረ ገብነት ትምህርት ይሰጥ።

5. በዩኒቨርሲቲዎች የመሽጉት ዘረኞች ይመንጠሩ።

6. ዩኒቨርሲቲዎች የፌደራል እንጂ የክልልና የዞን መደረጋቸው በህግ ይከልከል።

7. የህፃናትን አይምሮ የሚያበላሹ ቻናሎች ቁጥጥር ይደረግባቸው።

8. ፊልሞችና የሽቀጥ ማስታወቂያወች በህብረተሰቡ ስነአይምሮ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ትኩረት ይሰጠው። የፓለቲካ ሳይሆን የባሕል ሳንሱር መኖር አለበት።

9. በዩኒቨርሲቲዎች ለሚያስተምሩዋቸው የትምህርት አይነቶች የሚመጥን እዉቀት የሌላችው በርካታ ናቸው። ተማሪዎች በፍርሃትም በይሉኝታም ዝም ስለሚሉ ጎደሎ እውቀት ይዘው አገር ሊመሩ እየተመረቁ ነው።

10. የዩኒቨርሲቲ መምህራን ቅጥር መረን የለቀቀ ነው። በጉዋደኝነት፣ በጎጥ፣ ወዘተ ሲመለመል ነው የተኖረው።  ይህ ጥብቅ የሆነ የፌደራል ክትትል ያስፈልገዋል።

11. የዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የመምህራን እድገት አለአግባብ እየዘገየ የመጠቃቂያ መሳሪያ ቢሆንም በብዛት የሚገባቸው ያገኛሉ። አለ አግባብ በስልጣናቸው የሚያገኙም አሉ። መንግስት ይህን ጉዳይ ለዮኒቨሲቲዎች ባይተወው ይመከራል።

12. በየ ዪኒበርሲቲዎች ሰፍኖ ባህርያዊ እስከሚሆን ደረጃ የደረሰው ሙስናና አድልዎ ዝም ብሎ ማየት አገርን ይጎዳል። መንግስትና ህብረተሰብ በነዚህ ርካሽ አገር አፍራሾች ላይ ይዝመት።

13. ቁዋንቁዋና ባህልን ለማክበርና ለማዳበር የግዴታ በአንድ ክልል መሰባሰብ አያስፈልገውም። የትም እስተዳደር ውስጥ ሆኖ ቁዋንቁዋንና ባህሉን ለማክበርና ለማዳበር ህጋዊና ሞራላዊ መብት እለው። ነፃነት ማለት በተፈጥሮው ቡድን ሳይሆን ግለሰብ ስለሆነ። ስለዚህ ለዚህ ብቻ ተብሎ የቁዋንቁዋ ክልል መፍጠር ኪሳራ ነው። ይህን ተገን ያደረጉ ኪራይ ሰብሳቢ ከበርቴዎች ከመፍጠር በስተቀር። የኛ የሚሉት "ከብሄር ጭቆና ነፃ የወጣው" ድሃ ህዝብ ግን ስጋ የሌለው የብሄር አጥንት ቀቅሎ ይበላል። መንግስት ለሁሉም የሚበጅና ህዝብን አስተሳስሮ ለጋራ ብልፅግና የሚበጀውን የኢኮኖሚ እከላለል ቢጠቀም በሚልዮን እጅ ይሻላል።

14. የሃይማኖት ፓርቲዎች ከልክሎ  የቁዋንቁዋ ፓርቲዎች መፍቀድ ምን የሚሉት ነው?    ከቁዋንቁዋ ይልቅ ሃይማኖት ሚዛን አያነሳም? የሃይማኖቱም ይከልከል የቁዋንቁዋውም ይከልከል። ህዝብ የሚያተርፈው ነገር ቢኖር ቁዋንቁዋውን የሚናገር ገዢ ብቻ ነው። ያገሬ ጅብ ይብላኝ አይነት አስገራሚ ምኞት!! መልካም አስተዳዳሪ ከሆነ ኦሮሞው የመቀለ ከንቲባ ቢሆን፣ ትግሬውም የአዳማ ቢሆን ችግሩ ምንድነው? አገር ቀና መንገድ ትሄዳለች እንጂ። ስለዚህ መንግስት የብሄር ፓርቲዎችን አግዶ በህግ የሚወሰን በቂ ተዋፅኦ ያላቸው አገር አቀፍ ፓርቲዎችን ብቻ ህጋዊ ያድርግ።

15. የሃገር ሀብት/ቅርስ ሆነው ተመዝግበው በማእከላዊ መንግስት እጅ መሆን ያለባቸው እንደነ አክሱም ሃውልት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያን፣ የአባጅፋር ቤተ መንግስት፣ የአንኮበር የሚኒሊክ ቤተመንግስት፣ የአፄ ዮሃንስ ቤተ መንግስት፣ የሃረር ጀጎልና መስጂድ፤ የንጉስ ሚካኤል ቤተ መንግስት፣ የንጉስ ተክለሃይማኖት ቤተመንግስት፣ የመቅደላ አምባ፣ የደአማት መቅደስ፣ የግእዝ ፊደል፣ የቀን መቁጠርያ፣ የጣና ሃይቅ፣ የስሜን ተራሮች፣ ሶፍ ኦማር ዋሻ፣ የኮንሶ አርከኖች፣ የዲሬ ሼክ ሁሴን፣ የዳሎል ድንቅ ተፈጥሮ፣ መልካ ቆንጡሬ፣ የጢያ ቁም ድንጋዩች፣ ወዘተ የክልል ንብረቶች ሆነው የአርማቸው ማድመቅያ ሆነዋል። ይህ የጋራ ታሪክንና የተፈጥሮ ሃብትን የመዝረፍ ህገወጥ ተግባር ነውና መንግስት ክልሎችን አደብ ያስገዛ። የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው ቢባልም ሃውልቱን ከሮም ያስመጣው ወላይታው አልነበር? ሀብቱ ቢሆን ንው እንጂ!!

16. ላጭር ጊዜ ቢሆንም መቀለ፣ ለረዥም አመታት ደግሞ ጎንደር የኢትዮጵያ ዋና ከተሞች ነበሩ። አክሱምም ክርስትና የጀመረባት፣ እስልምናም ብቅ ያለባት ኢትዮጵያውያን 3000 አመት የሚቆጥሩባት በአለምም ከጥቂቶቹ የስልጣኔ ማእከላት አንድዋ የነበረችው፣ ሃረር የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሙስሊም እሚሬትና የፍቅር ዘፈን ውሎ ማደርያ። እነዚህ ከተሞች ደረጃቸው ወርዶ የክልል ከተሞች ሆነው ቀርተዋል። ማእከላዊ መንግስት እነዚህን ከተሞች የሃገር ደረጃ ክብራቸውን መልሶ በማላበስ የፌደራል ቻርተር ከተሞች አድርጎ በመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ስም እንክብካቤና ልማት ማከናወን ይጠበቅበታል።

17. ከኤሪትርያ ጋር በፌዴሬሽንና ከሱማልያ፣ ጁቡቲ፣ ሱዳንና፣ ደቡብ ሱዳን ጋር በኮንፌዴሬሽን ብንዋሃድ።

18. የመጨረሻ አስተያየቴ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ሲባሉ ቶሎ ብለው አንዱ ብቻ ጨቁዋኝ የሚሆንበት አድርጎ የመተርጎም አባዜ ላይ ነው። እንዴ! ስንትና ስንት ዲሞክራሲያዊ አገሮች አሉኮ አገራዊ አንድነትን ማእከል ያደረገ አስተዳደራዊ አወቃቀር ያላቸው። በቁዋንቁዋ የክልል አወቃቀር ለዲሞክራሲ ዋስትና እንደማይሆን እኮ የሱማሌ ክልል አሳይቶናል፤ የሌሎችን ለጊዜው እንተወውና ። ሱማሊኛ የሚናገር ጅብ አማርኛ ከሚናገር እርግብ ይሻላል ካልተባለ በስተቀር።

ወፍራም ነው ድርብ ነው ያገርኛ ግንቡ፣

...........ነጠላ ነው ፈራሽ ብሄርኛ ካቡ::

 

ስላም፣ ፍቅር፣ ለሁላችን፤ መልካም አዲስ አመት!!

ይህ የግል አስተያየት ነውና አርሙኝ እንጂ እርግማናችሁን አትከምሩብኝ።

 

 

Back to Front Page