Back to Front Page


Share This Article!
Share
መደመር እንዴትና በምን መልኩ?

መደመር እንዴትና በምን መልኩ?

ይዲድያ ብፁእ 07-28-18

ሰሞኑ እንደ ትኩስ ኬክ አየተገመጠና ስሙ ጣራ ነክቶ ያለ ቃል መደመር ነው። እንደ ዕድሜ ጠገብ የሂሳብ ተማሪ፤ አስተማሪና አፍቃሪ መደመርን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። በሂሳብ መደመር ምን እንደሆነ በጨረፍታ አቀርብና፤ በሌሎች ሦስት ዘርፎችም ምንነቱን ገረፍ ገርፍ አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

መደመር ሲወሳ በግንባር ቀደምትነት ብቅ የሚሉት ተደማሪ ቁጥሮቹ ናቸው። እነዚህ ቁጥሮች የራሳቸው ህልውናና መጠን ያላቸው ሲሆኑ፤ የድምሩ መጠን የሚወስኑትም እነርሱ ናቸው። ድምሩ ከተደማሪዎቹ የሚመነጭና ከተደማሪዎቹ ውጭ ትርጉም የለሽ ነው። ድምርና ተደማሪዎች የማይነጣጠሉ ናቸው። ስለሆነም ለመደመር የሚያስብ ሰው ተደማሪዎቹን ቁጥር ውስጥ ማስገባት ግድ የሚለውና ተደማሪዎችም በድምሩ ተጠቃለው እንዳሉ ማወቅ የሚገባው ነው።

ሁለተኛው ስለ መደመር ሲነሣ እንደ ክርሰቲያንነቴ አያሌ አብነቶች ከሕያው ቃሉ መጥቀስ ብቻልም፤ መድረኩ ሁሉን ለማቅረብ ስለማይፈቅድልኝ በጣም በጥቂቱ ለማቅርብ እሞክራለሁ። ከእነዚህ አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስትያን ራስ እንደ ሆነና፤ ቤተክርስትያንም አካሉ እንደሆነች ያወሳል። ምእመናኑም የአካሉ ብልቶች እንደሆኑና፤ አካሉም የእንዳንዱ ጥምረት ወይም ድምር እንደሆነ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ቤት ወይም ህንጻ የሚሰራው ከትናንሽ ድንጋይ እንደሆነ፤ ምእመናኑም ሕያው ድንጋይ ተብለው ተጠርቷል። በዚህ ድምሩ ማለትም አካሉ ወይም ህንጻው ከብልቶች ወይም ከድንጋይ እንደተሰራ በግልጽ የሚታይ ነው።

ሦስተኛው በተፈጥሮ ሳይንስ የሚታይ የተቀነባበረ፤ የተቀናጀና የተዋሃሃደ ድምር ክስተት ነው። ከሊሂቃኑና ከግዝፎቹ ከከዋክብት ጀምሮ በማይክሮስኮፕ ጭምር እንኳን ሊታዩ እስከማይችሉት ደቃቃና አናሣ ቁስ አካላት የተዋቀሩት ወይም የተገነቡት፤ የሁሉም ቁስ አካላት የመገንቢያ ድንጋይ ከሆኑት (building blocks of all things) አቶም (Atom) የተባሉ ደቃቃ ነገሮች ናቸው። ሁሉም ቁስ አካል በተለያዩ አሰደናቂ አወቃቀር፤ አደረጃጀትና፤ ቅንብር ከእነዚህ አቶሞች የተሰራ ወይም የተገነባ ነው። ከዚህ አኳያም መደመር ብዥታ የሌለው ግልጽ ክስተት ነው። ለምሣሌ ስለ ከዋክበት ሊያጠና የተነሣ ጠበብት ግብዴዎቹን ቁስ አካላትን ማጥናትና መመርመር የሚጀምረው ከምን እንደተዋቀሩና እንደተደራጁ በማጥናት ነው። ስለ ግዙፍ አካል ለማወቅ ሰሪዎቹ ትናንሽ ነገሮች ማወቅ ግድ የሚል ነው።

አራተኛው ዘርፍ የማሕበረ-ሰብ ሣይንስ ጥናትና ምርምር ነው። በማሕበረ-ሰብ ሳይንስ ስለ ሃገር ሲታሰብ መነሻው ግለሰብ ነው፤ ግለ ሰብ ቤተሰብን ይፈጥራል፤ ወይም ቤተሰብ የሚገነባው ከግለሶቦች ነው። በመሆኑም ቤተሰብ ግለ ሰቦች በተወሰነ ግኑኙነት የተጣመሩበት ነው። የቤተ ሰብ ጥንቅር ህዝብን ወይም ህዝቦችን የሚፈጥር ሲሆን፤ ሃገር ደግሞ እንደ ሁኔታው የአንድ ህዝብ ወይም የብዝሃ ሕዝብ ጥንቅር ወይም ድምር ናት። ይህ መሰረታዊ አወቃቀር በአግባቡ ማወቅ በሕዝቦች መካከል ጤናማ የሆነ አንድነት የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር በመፈቃቀድና በእኩልነት ለምትመሰረት አገር የጀርባ አጥንት ነው።

Videos From Around The World

በዚህ የማሕበረ ሰብ የመደመር ቀመር አያሌ ጉዳዮች በሰከነ መንፈስ በጥናት፤ በምርምር፤ በውውይትና በምክክር ሊቀርቡ የተገባቸው ሲሆኑ፤ ለዚህ ሥራ ብቃት ያላቸው በሞያው የተካኑ ሰዎች መሰባሰብ የሚጠይቅ ነው። እንደ ችግኝ ዘወትር ክትትልና እንክብካቤ የሚያሻው ነው። በርካታ በዝርዝርና በጥልቀት የሚቀርቡ ሰነዶች፤ እንዲሁም ክትትልና ጥበቃ የሚያደርጉለት መዋቅሮችም የሚጠይቅ ነው። በሂደት አንድነቱን ሊያናጉ፤ ሊያፈርሱና ሕብረቱን ለያደፈርሱ ይቻላሉ የሚባሉት ተግዳሮቶች ለይቶ ምን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ቀድሞ መጦቆመን የሚያካትት ነው። መደመር

ከማሕበረ ሰብ ሳይንስ አኳያ በትንሹ ጨልፈን ለማየት የሞከርን ሲሆን፤ አገር ከየት እንደሚጀምርና መደመር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትንሽ ብርሃን የሚፈነጥቅ ነው።

ይህን መጣጥፍ እንዳቀርብ ያነሳሳኝ ወቅቱ እንዲሁ መደመር፤ እንደመር፤ ተደምረሃል ወይ? እና የመሳሰሉት ቃላቶች እያስተጋባ ስላለ፤ ከምቀርባቸው በርካታ ወዳጆቼ ተደምረሃል ወይ? የሚል ጥያቄ አዘል ጥሪ አብዝቶ ስለደረሰኝ ነው። ጥሪው በመጀመሪያ ግራ አጋብቶኝ ተደማሪዎቹና ድምሩን ስቀምር የኖርኩ ሰው፤ አሁን እንዴት ራሴ እደመራለሁ አሰኝቶኝ ነበር። ደግነቱ ተደማሪ እንጂ ድምር እንድሆን ያለመጠራቴ ነው። ለካስ የኔ ተደማሪነትም በድምሩ ላይ ስፍራ አለው። ነገር ግን ስደመር እንዴትና በምን መልኩ ልደመር? ይህ ቆም ብዩ እንዳስብበት አደረገኝ።

ከወዳጆቼ ስንወያይ ሆነ ስንሟገት አንድ የሚገዛን ሕግ (House Rule) እናስቀምጣለን። ይህም በመለያየት መስማማት የሚል ሲሆን፤ በአንድ ጉዳይ ላይ የግድ መስማማት እንደሌለብን የሚገልጽና፤ ካልተስማማን ደግሞ ነገሩን ባለመስማማት ቋጭተን ያለ አንዳች ጥል መዝጋት ነው። ከዚህ ጋር የሚመሣሰል አንድ የትግሪኛ ምሣሌ አቀርብና ትርጉሙ በአማርኛ አቀርባለሁ። ምሣሌው ካብያ መርዓ ደቂ ኽፉኣትስ፤ ፍትሕ ደቂ ጭዋታት የሚል ሲሆን፤ በአማርኛ ከክፉ ሰዎች ልጆች ሰርግ፤ የጭዋ ሰዎ ልጆች ፍች የሚል ነው። ልዩነትን በልዩነት ያለ መደባደብና መጠላላት መዝጋት ብልህነት ነው።

ሰው በቤተሰቡ፤በማህበረ ሰቡና በመጨረሻም በአገሩ ሊደመር እንዲመገባው ለመገንዘብ ጊዜ ባይወስድብኝም የአደማመሩ ስልት ግን ቀላል ሆኖ አላገኘሁትም። የማሕበረ ሰብ የመደመር ቀመር እንደ ሂሳቡ ቀመር ቀላል ሆኖ አላገኘሁትም። ነገሩ እንዲሁ በዋዛና በቸልታ ሊደምሩት የሚችሉት አይደለም። የተጨነቅኩበት ነገር ይህ ቀመር እንደ ሂሳቡ ቀመር ቀላል ሆኖ ስላላገኘሁት ነው። የማሕበረሰቡ ድምር ከሂሳቡ ድምር ቢመሳሰልም አያሌ ልዮነት ግን አለው። ቁጥሮች በቁጥሮች ላይ ደምረህና ቆልለህ በቀላሉ የምታገኘው መልስ ከቶ አይደለም።

ከወዳጆቼ የደረሰኝ የተደምረሃልን ጥሪ የቀረበው፡ 98% የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንም ሳይገፋፋውና ሳይጫነው በገዛ ፈቃዱ ተደምረዋልና አንተም ተደመር በሚል ቀና ምልከታ ታጅቦ የቀረበ ግብዣ ነው። ነገር ግን ለዚህ ስታትስቲካዊ መረጃ ማሥረጃ የማቅረብ ሸክም (burden of proof) በእነርሱ ጫንቃ ላይ የሚጣል ነው።

በዚህ ርእስ ስለ መደመር የጻፍኩት አጠቃላይ ተክለ ሰውነቱን ማለትም (General frame work) ወይም (Skeleton) ምን መሆን እንዳለበት ለመጠቆም ያክል እንጂ አሁን ዶ/ር አብይ መደመር በሚሉት ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም። እዚህ ላይ የእርሷቸው መደመርም በዚህ ተክለ ሰውነት (ፍሬም ወርክ) የሚሰካካና የሚገጣጠም መሆን እንደሚገባው ከወዲሁ ለመቀበል ዝግጁ መሆን የሚጠይቅ ነው።

በእርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ መደመርን ይፈልጋል፤ ይናፍቃልም። ይህ አጠቃላዩና ድፍን ስእሉ ነው። ዳሩ ግን ወደ ዘርዛራ ጉዳይ ሲገባ ልዩነቱና ውስብስብነቱ ወዲያውኑ ብቅ ይላል። ለምሣሌ በአንዳንዶቹ ወገኖቻችንና የአንድነት አጋሮቻችን ሰሞኑን በተካሄደ የእኛም ተደምረናል ድጋፍ ሰልፍ፤ ተደምረናል ከሚሉት መደመሩ በምን መልኩ መሆን እንዳለበት በግልጽ አሳይተዋል፤ አንፀባርቀዋልም፤ ይህም የሌሎች ሕዝቦች መብትና እኩልነት በመቃወምና በመጋፋት ነው።

እኚህ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች ወይም ግለሰዎች፤ እንዲህ ዓይነቱን መደመር ወይም አንድነት የማስተጋበት መብታቸው የተጠበቀ ነው፤ይሁንና ሌላው በዚህ አመለካከት የሚጎዳ ክፍልም ሊቃወመውና አልደመርም ሊልም መብቱ ነው። ከሚጎዱት፤መብቱን ከሚገድቡትና ከማይጠቅሙት ማህበራትና ድርጅቶች አልፎም ግለሰቦች እንዴት ይደመራል? እንዴትሰ ይተባበራል?

ዶ/ር አብይና አንድነትን የሚፈልጉና የሚደግፉ የተባሉት 98% የሕብረተሰቡ ክፍሎች፤ አደማመራቸው የማሕበረ ሰብ የመደመርን ሕግና ደንብ የተከተለና ያገናዘበ ከሆነ እሰዮው የሚያሰኝና ተቀባይነት ያለው ነው።ነገር ግን በደምሣሣው፤በጥቅሉና በድፍኑ እንደመር ወይም አንድ እንሁን የሚባለው፤ ዝርዝር ጉዳዮች በሚገባ ሳይመረመሩና ሳይጠኑ በስሜት የሚደረጉ ከሆነ፤ ጠላልፎ የሚጥል መሰናክልና ወጥመድ ከፊት ለፊቱ የተደቀነበትና የተጠመደበት ነው። ይህም በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ በስሜት ሲጋልቡ ክፉኛ የሚወድቅበት እንቅፋት ነው። ሁሌም በስሜት ኮሮቻ ተቀምጦ መጋለብና፤ በስሜት የሚደረግ ሁሉ ለአፍታ ቆይቶ የሚፈራርስና የሚናድ ነው።

ብረት ብረትን እንደሚስልና እንደሚሞርድ፤ ሰከንና ረጋ ተብሎ የጠለቀና የመጠቀ እውቀት ባላቸው ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያት ጭንቅላቶች ከየማእዝናቱ ተሰባስበው በሚያደርጉት የሃሳብ ፍጭትና ፍትጊያ የሚወጣና የሚፈልቅ የጠራና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትና ተአማኒነት ያለው ሕገ መንግሥት ግን መሥረታዊ፤ አስተማማኝና ዘለቄታ ያለው ነው። ይህ በዓለት ላይ እንደተገነባ ሕንፃ ጽኑና የማይነቃነቅ ደልዳላ መሠረት ያለው ነው።

እንዲህ ዓይነቱ የበለጸገ ሕገ መንግሥት የሚፈልቀው ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ወይም ነባራዊ ሁኔታ ነው። ብቃትና ተቀባይነት ያለው ሕገ መንግሥት ማውጣት የሚቻለው የኢትዮጵያን ነበራዊ ሁኔታ በሚገባ በማገናዘብና በመረዳት ብቻና ብቻ ነው። ይህ በማስተዋል፤ በማጥናት፤ በመወያየትና በመደማመጥ በምድሪቱ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመንደርደር የሚወጣ ነው።ይህ አታላዮች፤ሙሶኞችና የራስ ጥቀም አጋባሾች እንዳሻቸው እንዳይመዘብሩና እንዳይሰርቁ ቀዳዳዎቹን ሁሉ የሚደፍንና መፈናፈኛ የሚያሳጣ ነው።

ኢትዮጵያ የብዝሃ ሕዝቦች ወይም ብሔሮች አገር እንደ መሆንዋ መጠን፤ አንድነቱ ወይም መደመሩ ከዚህ የሚነሣና የሚፈልቅ እንደሚሆን ለመገንዘብ አያዳግትም። ተደማሪዎቹ የተለያዩ ሕዝቦች ሲሆኑ፤ ድምርዋ ውድ እናት አገራችን ኢትዮጵያ ነች። ኢትዮጵያ የሁሉም ሕዝቦች ድምር እንደሆንች፤ ለሁሉም እኩል የምታቅፍና የምታሰተናግድ እናት መሆን ይኖርባታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከብልጥግናዋና ከጸጋዋ በምታሰናዳው ማእድ ዙሩያ ሁሉም ልጆችዋ ተቀምጠው ሊቋደሱና ሊመገቡ ይገባቸዋል። እናት አገራችን ሁሉንም በእናትነት ፍቅርዋ የምታቅፍ ደግ እናት መሆን ይገባታል እንጂ፤ ላንዳንዶቹ የእንጀራ እናት መሆን አይኖርባትም።

ይህ ማእድ አግባብነት ባለው አያያዝና አሰራር ተቀምሞና ተከሽኖ፤ተቀነባብሮና ተቀናጅቶ የሚቀርብ ፌዴራላዊ የመንግሥት ስርዓት አወቃቀር ሲሆን፤የሁሉም ሕዝቦችና ዜጎች መብት ሳይሸራርፍና ሳይቆራረጥ የሚጠብቅና የሁሉም ይሁንታና አሜኔታ ያገኘ መሆን አለበት። ሕገ መንግሥቱ ለማሻሻል፤ ለመለወጥና ለመስተካከል ሁሉ ጊዜ እድል የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል።

ለምሣሌ አንድ ሰው ቋንቋና ባህል አባል ወይም ተደማሪ ከሆነበት ማሕበረ ሰብ ጋር የሚጋራው እሴት ነው። ይህ ተዘንግቶና ቸል ተብሎ አጠቃላይ መብቱ በግለሰብ መብቱ ሊያገኘው ይችላል ከተባለ ትክክል አይደለም። በመሆኑም ሊዋቀርና ሊመሰረት የተገባው ፈዴራላዊ የመንግሥት ስርዓት አወቃቀር ይሄንን መሰረትና ታሣቢ ያደረገ ይሆን ዘንድ የተገባ ነው።

የራሴ ወይም የግሌ ሁኔታ እንደ ምሣሌ አድርጌ ላቅርብ። በአጼ ሃይለሥላሴ መንግሥት በትግራይ ተወልጄ ያደግሁ ትግራዋይ ኢትዮጵያዊ ነኝ። የአፍ መፍቻ ቋንቋዩ ትግሪኛ፤ ባህሌና ስነ-አእምሮዩ ትግራዋይነትን የለበሰ ነው። ዳሩ ግን ቋንቋዩ ልጽፍበት፤ ለማርበትና በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ልገለገልበት አልችልም ነበር። ይህ ወድጄና መርጨ ያደረግሁት ሳይሆን እድሉ ስለተነፈግሁ ነው። በሌላ ብሔሮች በቋንቋቸው እንዳይጠቀሙና ባህላቸው ባንድም በሌላም መንገድ እንዳይጠቀሙና እንዳያጣጥሙ የተደረጉ የኔ ብጤ ምስኪኖች በቁጥር በርካታ ናቸው።

ያለፉት መንግሥታትና ስርአቶች ሰብአዊ መብቴ እንዳላከበሩልኝ ለመረዳት አዳጋች አይደለም። ቋንቋዩ በመንግሥት ተቋሞች እንዳልጠቀምበት ስለተደረግኩ፤ በቋንቋዩ እንዳልማር እድሉ ስለተነፈገኝና በቋንቋዩ እንዳልጽፍና እንዳላነብ ስለተደረግኩ መብቴ ተጥሰዋል ወይም ተሸራርፏል ለማለት በቂ ምክንያት አለኝ።

በቋንቋዩ ልማር፤ ልጽፍና በመንግሥት መዋቅሮች ልገለገልበት እመርጥና እፈልግ ነበር፤ እድሉ ቢሰጠኝ ኖሮ የምፈልገው በትግርኛ ብጠቀም ነበር። ይሁንና መብቴ ተጥሶ የአፍ መፍቻ ቋንቋዩ እንዳልጠቀምበት ተደረግኩኝ። ሁሌ በትግርኛ የማናግራቸው ወላጆቼ ቤተሶቦቼ ጓዶኞቼና ማሕበረሰቤ በሌላ ቋንቋ መልእክት እንድጽፍ ተገድጃለሁ። እነርሱም ሊጽፉ ሆነ ሊያጽፍ በሌላ ቋንቋ ሊጠቀሙ ይገደዳሉ።ይህ ሁሉ ጣጣና መዘዝ የመጣው ለምን ይሆን? ስብአዊ መብቴ ያለመከበሩስ የሚያሳይ አይደለን? ማንስ ይሆን ይሄ እኮ የመብት መጣስ ጉዳይ አይደለም፤አንተ ነገሮችን ስለምታካብድና ዘረኛ ስለሆንክ እንጂ ሌሎች ሲያማርሩ አንሰማቸውም ሊለኝ የሚዳዳው?

እንዲህ ዓይነት አመለካከትና ባህሪ ያላቸውን በድምር ስሌቱ ማካተት፤በቁጥር ላይ ነጌቲቭ ቁጥርን እንደመደመር ነው። ቁጥሮች ከነጌቲቭ ቁጥር ጋር ሲደመሩ ድምሩ ቁልቁል ይወርዳል እንጂ ከፍ አይልም። በዚህ ትውልድ በየክልሉ ያሉ ወጣት ዜጎች እኔ እንደጨለጥኩት እንደሚጎመዝዝና እንደሚመር ጽዋ እንዲጎነጩና እንዲጠጡ አልሻም፤ ይህ ለመፈጸም ከሚፍጨረጨሩና ከሚጥሩ ጋርም ሕብረት አይኖረኝም፤ ለመደመርም አይቃጣኝም። በቋንቋህ ያለመጠቀምና ያለመገልገል፤ በቋንቋህ ያለመማር፤ ያለመጻፍና ያለማንበብ፤ ባህልህ እንዳይድግ መገደብና እንዲቀጭጭ ማድረግ የሰብአዊ መብት ጥሰት ካልሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምን ሊባል ነው?

እናማ ከሰሞኑ ጆሮአችንን ጭው የሚያደረግ ዘመንኛ የመደመር መረዋ በጆሮአችን እየጮኸብን ነው። በጥምረት ይሁን በተናጠል በጠራራ ፀሐይ እንዲህ ዓይነቱ ግራ የሚያጋባ አንድነትና መደመር ሲያውጁብን መቃወም እንዴት ይብዛብን? አንተ ላይ የሆነው ለወደፊቱም በልጆችህና በእድሜ እኩዮቻቸው ሁሉ ይሆንባቸዋል ሲባል እንዴት አይሰቅቀኝም። እየሰማነውና እያየነው ያለው የዘመኑ የመደመር መርህ ሶቆቃ እንዳያመጣብን በትክክል እየተደመርን እንዳለን መረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ሁሉም እንዴትና በምን መልኩ እየተደመረ እንዳለ ቆም ብሎ ቢያስብ በጎ ነው።

በእውንስ አገሪቱ የምትዳደርበት ሕገ መንግሥት ይህን ዓለማ አድርጎ የተቀረጸ ነውን? በቋንቋዩ ልጠቀም፤ ልማር፤ ልጻፍና ልገልገል የሚለን፤ የራስህ ጉዳይ ብሎ ገሸሽና ገለል የሚያደርግ ይሆንን? ደግሞስ ቋንቋዩ ልጠቅምበት ካልቻልኩ፤ ባህሌም እንዲቀጭጭ ከተደረገብኝ፤ ለሚለውስ የግለ ሰብ መብትህ እስከተከበረ ድረስ ሁሉም ታገኘዋለህ የሚል መልስ የሚያገኝበት ሕገ መንግሥት ይሆንን? ከህገ መንግሥቱ የሚወጣውና የእርሱ ማረጋጋጫና ማሳያ የሆነው ባንዴራስ የሚውለበለበውና የሚንበለበለው ለእንዲህ ዓይነቱ ሕገ መንግሥት ማሳያና መግለጫ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነውን?

በድሮው ሕገ መንግሥትና የሱ ነጸብራቅ ሆኖ በተዘጋጀው ባንዴራ ሥር ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰብአዊ መብታቸው ያልተከበረላቸው መሆኑ ለመገንዘብ አዳጋች አይደለም። ምንም እንኳን ባንዴራው ከኢትዮጽያ ታሪክ ጋራ በአያሌው ትስስር ይኑሮው እንጂ፤ ሕገ መንግሥቱ የሁሉም ዜጎች ሰብአዊ መብቶች የሚያከብር ሆኖ ሲወጣ በነበሩት ህብረ ቀለማት ማለትም ቀይ፤ ብጫና አረንጓዴ ላይ አዲሱን የሕዝቦች ውል፤ ኪዳንና ስምምነት የሚያስረግጥ ምልክት ሊኖሮው ይገባል፤ ይህ ተጨማሪ ምልክት ቃል ኪዳን፤ ውልና ስምምነት በሚያደርጉት ሕዝቦች ምርጫና ፍላጎት የሚወሰን ነው። ሕብረ ቀለማቱ የታላቂቱን አገር ድንቅ ታሪክ የሚገልጥ ሲሆን፤ ምልክቱ ደግሞ ሁሉም በእኩልነትና በመፈቃቀድ የመሰረትዋትን አገርና የሁሉም ሰብአዊ መብቶችን የሚያሰከብረው አዲሱ ሕገ መንግሥት የሚያንጸባርቅ ይሆናል።

ኢትዮጵያ አንድ ሆናና ዜጎችዋም ተደምረው ለመኖር የሚወጣው ሕገ መንግሥትና ከእርሱም ተያይዞ የሚወጣው ሰንደቅላማ የመአዝን ድንጋይ ነው። ሌላው ተጨማሪና በዚህ ተክለ ሰውነት ማለትም በሕገ መንግስቱና በባንዴራው ላይ የሚሰካካና የሚገጣጠም ነው። ሕገ መንግሥቱና ተያያዥ ሆኖ የሚዘጋጀው ባንዴራ ሁለተኛ የሌላቸው ብቸኛ ምርጫዎች ናቸው።በርካታ ዜጎች አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። እውነት ከሆነና በሁሉም ዘንድ ተአማኒነትና ተቀባይነት ካገኘ፤ መሻሻል የሚገባውን አሻሽሎ፤ መለወጥ የሚገባውን ለውጦ፤ መሰረዝ ያለበትን ሰርዞና፤ መጨመር ያለበትን ጨምሮ እንዲቀጥል ማድረግ አንደ አማራጭ ቢወሰድ መልካም ነው። ነገር ግን ከዚህ የተሻለና የበለጠ የዜጎችን አጠቃላይ ስብአዊ መብት የሚያከብር ሕገ መንግሥት የሚቀርብ ከሆነ፤ የሕዝቡ አጠቃላይ ስብአዊ መብቶች እስካከበረ ድረስ ያለውን ለውጦ ተግባራዊ የሚደረግበት አግባብ ቢኖር ጥሩ ነው። ነገር ግን በጥንቃቄ ዘጎችና ሕዝቦች ተወያይተውበትና ተማምነውበት፤ በሚገባ ተመዝኖና ተስፍሮ አዎንታና ይሁንታ እስካገኘ ድረስ ተቀባይነት ቢያገኝ ይመረጣል።

ተቀባይነት የማይኖሮው አንድ ነን እና ተደምረናል በሚል ጭፍን አስተሳሰብ ከለላ ሥር ከዚህ በፊት ስብአዊ መብቶቻቸው ያልተከበረላቸውን ዜጎችና ሕዝቦች፤ አሁንም ለወደፊቱም በድሮው ሕገ መንግሥት ሰብአዊ መብታቸው ተገፍፎ እንዲቀጥሉና እንዲኖሩ ለማድረግ መከጀልና መጣር ነው። ይህ ፈፅሞ ተቀባይነት የማይኖረው ነው፤ የሁሉም ዜጎችና ሕዝቦች መብት አያከብርምና።

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ወይም ነባራዊ ሁኔታ ቋንቋንና ባህልን መሰረት ያደረገ ፌዴራላዊ አወቃቀር ቢሆን በቋንቋና በባህል ጠንቅ ሊከሰት የሚችለውን የወል ወይም የሕዝቦች ሰብአዊ መብት መቅረፍ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፤ ይሁንና ፌዴራልዝሙ የማያስፈልግ የብረት ግድግዳ ወይም አጥር ፈጥሮ እንዳይለያይና እንዳይጋርድ የጠበቀ ክትትል፤ ቁጥጥርና ጥበቃ ሊደረግልት ይገባል። በተሞክሮ እንዳየነው ብሔረተኝነት ጠንክሮና ፈርጥሞ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላና እንዳይደክም በየወቅቱ ክትትል የሚያደርጉ ማቋቋምና መዘርጋት ያስፈልጋል። ከዚህ የተለየና የተሻለ የሁሉም ዜጎች አጠቃላይ ሰብአዊ መብት የሚያሟላና የሚያከብር አማራጭ ካለ ግን አማራጩ እስከነ ምክንያቶቹ ለህዝብ ውይይት ቀርቦ ተቀባይነት ካገኘ መልካም ነው።

አንዳንድ ወገኖች ሕገ መንግሥቱ ጥሩ ነው እያሉ ከዚህ ጋር በሚጻረር መልኩ ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌዴራልዝም ወይም ሕገ መንግሥት ለ27 ዓመት ተጠቅመንበት ምን አተረፍን? ስለዚህ መሻር ወይም መወገድ አለበት ይላሉ። የመጣው ውጤት መጥፎ መሆኑ የሚካድ አይደለም። ዳሩ ግን ውጤቱ መጥፎ እንዲሆን ያደረገው ፌደራላዊው ሕገ መንግሥቱ ያይደለ አተገባበሩ ነው። አተገባበሩ ላይም ችግር የፈጠረው በስልጣን ያሉት ገዢዎችና መሪዎች በመንቀዛቸው ጠንቅ ነው። የእነርሱ መንቀዝ መላ ተክለ ሰውነት ወይም ፍሬም ወርክ ቦሮቦረው አነቀዘውም።

አለቆቻችን ነቅዘዋል፤ በዘመድ አዝማድ፤ በዘር፤ በጎጠኝነት፤ በወገንተኝነት በጥቅማ ጥቅም፤ በልከከልህ እከክልኝ ተለክፏል። ሁሉም ለወገኔ ይጠቅማል የሚል አባዜ ተጠናውቶአቸዋል፤ በስብሰዋልም። የበሰበሰ ብርቱኳን ትጥለው እንደሆነ እንጂ አሻሻሎ ለመብል የማቅረብ እድል እንደማይኖርና፤ የነቀዘ እህልም ተፈጭቶ እንጀራ ወይም ዳቦ እንደማይሆን ሁሉ፤ የእነዚህ ንቅዘትም ከጥገና በላይ (beyond maintenance) በመሆኑ የሚኖረው እድል ፈንታ ማስወገድና ላደረሱት ከፍተኛ ጥፋትና በደልም አግባብ ባለው ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢው ብይን ማግኘት ነው።

እዚህ ላይ በጥንቃቄ መለየት የሚገባው በሕገ መንግሥቱና በተግባሪዎቹ መካከል ያለው ልዮነት ነው። ለውድቀቱ ጠንቅ የሆነው ማን ነው? ጥሩ ነው የተባለው ሕገ መንግሥት ወይስ እርሱን የሚተገብሩት በሥልጣን ላይ ያሉት መሪዎች? ይህ በተገቢ ሁኔታ ማጤን የተገባ ነው። ይሁንና ጥሩ ነው የተባለው ሕገ መንግሥት በአጠቃቀም ጉድለት ሳቢያ አብሮ ከተጣለ፤ እርምጃው ልከኛ አይደለም። ገላው የቆሸሸ ህጻን ገንዳ ውስጥ በውሃ ካጠቡ በሃላ፤ ህጻኑን አቅፎ የቆሸሸውን ውሃ መድፋት እንጂ ህጻኑንም ከውሃው ጋር መድፋት የተገባ እንዳይደለ፤ ሕገ መንግሥቱና አስፈጻሚዎችም እንዲሁ ለታዩ ይገባል። የነቀዙት

 

መሪዎች ማግለልና መስወገድ፤ ሕገ መንግሥቱ ግን አሻሽሎ፤ ጨምሮና ቀንሦ ማስተካከል፤ ለትግበራው በሞያው የተካኑና ታማኝ የሆኑ ሰዎች መሾም፤ ተገቢ መዋቅሮች ማቋቋም፤ እለት ተእለት የሚከሰቱ እንግዳ ክስቶቶች ትኩረት ሰጥቶ ሲከሰቱ ወደያዊኑ አስተውሎ የእርምት እርምጃ መውስድ፤ የመብት ጥሰት እንዲፈጸሙ ጠንቅ ሊሆኑ የሚችሉትን መለየትና መፍትሄ መስጠት ወዘተ ናቸው።

ከዚህ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አንድ ንጽጽር ብናይ የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረን ሊያደርግ ይችላል። አንድ ባለንጀራዩ በአንድ ትልቅ ዳቦ ቤት ይሰራ በነበረበት ወቅት የዳቦው ቤት አወቃቀር የሥራ ክፍፍል፤ የሥራ ሃላፊነትና ተጠያቂነት፤ ለዳቦ መጋገሪያው ዕቃ የሚደረግለት ክትትልና ጥበቃ፤ በመጨረሻም ዳቦው ሲወጣ እንከን ከተገኘበት ችግሩ የት እንደተከሰተ የማጣራቱ ሂደትና የሚወሰደው እርምጃ ነግሮኝ ከዚህ ጋር በንጽጽር ላማቅረብ ፈለግኩኝ። በዚህ ዳቦን ለተጣቂመው የማቅረብ ሂደት፤ ለዳቦው ጥሩነት ዱቄት የሚገዛ፤ የተገዛው የሚያቦካ ሌላ ፤ ተቦክቶ የተዘጋጀው በዳቦው ዕቃ መንኮራኩር የሚጥድ ሌላ፤ በስሎ የወጣው ዳቦ የሚያወጣ፤ የወጣው ዳቦ ጥሩ መሆኑ የሚያረጋግጥ፤ የዕቃው መካኒካዊና ኤሌክትርካዊ ደህንነት ወይም ጤንነት የሚከታተል፤ ዕቃው ሲያመርት ጠቅላላ የእቃው ሁኔታ የሚያሳይ ግራፍ የሚያነብ ቡዱን አሉት። እነዚህ የየራሳቸው የሥራ ድርሻና ሃላፊነት ያለቸው ሲሆን፤ እርስ በርስ መናበብና መረዳዳት የሚጠበቅባቸው ናቸው፤ በመጨረሻ ዳቦው ከተበላሸ ብልሽቱ የት ጋር እንደሆነ ለማጣራት እያንዳንድዋ እንቅስቃሴ ትፈተሻለች።

አብዛኛው ጊዜ ብልሽቱ የሚፈጠረው በሰዎች እንጂ በዕቃው እንዳይደለ ነግሮኝ፤የዳቦ ቤቱ ማናጀር ጎበዝ ከሆነ ተከታትሎ ጥፋቱ የት ጋር እንደሆነ በመለየት ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል፤ ብዙ መዋእለ ንዋይ አፍስሶ አዲስ የመጋገሪያ ዕቃ ከመግዛትና የነበረውን ከመጣል ይታደጋል ያድንማል። ማናጀሩ ቸልተኛና ገራገር ከሆነ ግን፤ ኦፕሬቶሮቹ የገዛ ጥፋታቸውን ሸፍነው ዕቃው ተበላሽተዋልና መለወጥ አለበት ሲሉት በርካታ ንዋይ አፍስሶ ሌላ ውድ የመጋገሪያ ዕቃ ለመግዛት ይውተረተራል።ይህ ትርፍን ዓላማ አድርጎ ለሚሰራ አንድ ዳቦ አምራች ተቋም በጤንነት ሥራውን ለማካሄድ የሚደረግ ጥርት ያለ ክንውን ነው።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን እንየው፤ በተቋሚዎች ዘንድ ጥሩ ነው የተባለለት ነው። ይህ ከአንድ መቶ ሚልዮን ሕዝብ በላይ የሚያገለግል ትልቅ፤ ውድ፤ ውስብስብና በጣም ጠቃሚ የሆነ ዕቃ ነው፤ ለዳቦው ማምረቻ ይኼ ሁሉ ክትትልና ቁጥጥር ከተደረገለት፤ ለዚህማ ምንኛ የጠበቀና የበለጠ እንዴት ሊደረግለት አይገባም? ጥፋት ሲፈጠር ኦፕሬቶሮቹ በእቃው ላይ እንደሚያላክኩና እንደሚያመኻኙ፤ በሕገ መንግሥቱ የሚላካኩ ኦፕሮቶሮች በርካታ እንደሆኑ ከንጽጽሩ ለመረዳት አዳጋች አይደለም።እዚህ ላይ የእቃው አንዳንድ ክፍሎች ሊያረጁና ሊበላሹ ስለሚችሉ፤ በሌላ ስፔር ፓርት ቀይሮ እንዲሰራና እንዲስተካከል የማድረግ ሂደትና አሰራር እንዳለ ሁሉ፤ በሕገ መንግሥቱም እንዲሁ፤ ሊሻሻሉና ሊለወጡ፤ ሊጨመርበትና ለቀንስበት የተገባ ነገር ይኖራል።

ከዚህ ንጽጽር (analogy) በርካታ ጠቃሚ ሁኔታዎችን መቀሰምና መቃረም ይቻላል። ዕቃው ጥሩ እያለ በአፕሬቶሮቹ ጥፋት ሳቢያ ዕቃውን መጣል ተገቢ አይደለም፤ ጥፋቱ የት ጋር እንዳለ በተገቢው የቁጥጥር አሰራር መሰረት ተገቢ እርምጃ መውስድ የተገባ ነው። ዳሩ ግን ዕቃው ምንም ችግር ሳይኖረው ሳያጣሩ ጥሩ ዳቦ ማምረት አልቻለምና መጣል አለበት ከተባለ ኪሳራው የትም የለሌ ነው።

ከዚህ አኳያ አማርኛ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በስፋት የሚጠቀሙበት ብሔራዊ ምግባቢያ ቋንቋ ስለሆነ የሌሎች የአፍ መፍቻ ቋንቆች ላይ ምንም አሉታዊ ተጽእኖ እስካላደረስ ሁላችንም ብንጠቀምበት በጎ ነው። አፋን ኦሮሞም እንዲሁ ኦፌሴላዊ የአገሪቱ ቋንቋ ቢሆን ይበጃል እንጂ ክፋት የለውም።የአናሣ ብሔር ቋንቆች በአበይት ክልሎች እንዲጠቀሙባቸው በፈቀድላቸው በዚያው ለሚኖሩ ሰዎች መብታቸው እንዲከበር እድል የሚሰጥ ነው። ከክልላቸው ውጭ በሌላ ክልል የሚኖሩ ዜጎች የሚኖሩበት ክልል ቋንቋ መጠቀም ከቻሉ የበለጠ ጠቃሚ ከመሆኑ ባሻገር፤ ለጽኑ ማሕበራዊ ትስስርና ቁርኝት (social integrity) አይነተኛ መፍትሄ ነው።

 

ፌዴራላዊ ቅርጽ ያለው ሕገ መንግሥት አያስፈልገንም፤ ከፈደራልዝሙ ጋር ተዛምዶ የወጣው ባንዴራም አንሻውም፤ የምንፈልገው በድሮው ሕገ መንግሥት ይውለበለብ የነበረ ባንዴራ ነው የሚለው አስተሳሰብ የሚያራምዱ እንደ መብት ሃሳባቸው በአደባባይ ለመገለጽ፤ በሰላማዊ ሰልፍ ለማንጸባረቅ፤ በጹሑፍ ለማቅረብና በአደባባይ ለመናገር ሊፈቀድላቸው የተገባ ቢሆንም፤ በሌላ ገጽ ይህን ያለ በቂና አሳማኝ ምክንያት በማቅረብ ለመቃወም የክል የሚቀርብ ተቃውሞ ባይሆን ይመረጣል። ይሁንና ሌላው ክፍል ተቃውመውን ሰከን ብሎ በምክንያት መስረዳትና ማሳመን ይጠበቅበታል። እነዚህ ብቃት ባለው አመክንዮና ትንተና ወደ መረዳዳት መድረስ ከቻሉ ይደመራሉ እንጂ መናቆርና፤ መጠላለት የለባቸውም። ዳሩ ግን መንግሥት መፍትሔ ያመጣል የተባለ በሣይንሳዊ ጥናት የተደገፈና የሁሉም የጋራ አካፋይ የሆነ ሕገ መንግሥትና ባንዴራ ማውጣት ግዴታው ነው።

በድሮው ሕገ መንግሥትና ባንዴራ እንቀጥል በሚለው አመለካከትና እንቅስቃሴ ዙሩያ ከበርካታ ዜጎች የሚነሱ አያሌ ጥያቄዎች ወደያውኑ ብቅ ማለታቸው አይቀርም። ከነዚህ ጥቂቶቹ፦

1. ሕገ መንግሥቱና ባንዴራው የሚመነጩት ከአገሪቱ ተጨባጭ ወይም ነበራዊ ሁኔታ እስከሆነ ድረስ በምድሪቱ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚል ይሆናል። ለዚህ ተገቢና አርኪ መልስ መስጠት ሕገ መንግሥቱና ባንዴራው ለማዘጋጀች ቀላል የሚያደርገው ነው። ኢትዮጵያ የአንድ ወጥ ህዝብ አገር ነች ወይስ የተላያዩ ሕዝቦች ድምርና ጥምረት? ይህ ወሳኝ ጥያቄ በጥንቃቄ መመለስ ያለበት ነው። የሚዘጋጀው ሕገ መንግሥትና የሚወጣው ባንዴራም የዚህ ተገዥ ናቸው። ባንዴራውና ሕገ መንግሥቱ በዚህ ዙሩያ የሚሽከረከሩ ናቸው። 2. ኢትዮጵያ በድሮው ሕገ መንግሥታና ባንዴራ ሥር ትተዳደር በነበረበት ወቅት ሕዝቡ ሁሉም ስብአዊ መብቶቹ ሳይሸራረፉ በእውን ተከብረውለት ነበር ወይ? መልሱ አለተከበሩለትም ከሆነ፤ ሁሉንም የሚያቅፍና የሚደምር ሕገ መንግሥትና ባንዴራ የመኖር ጉዳይ አጠያያቂ አይሆንም። እዚህ ላይ ሕዝቡ ባለው ሕገ መንግሥትና ባንዴራ የማይረካና የማይስማማ ከሆነ፤ በሚፈልገውና በሚስማማበት ለመቀየር በሩ ክፍት መሆን አለበት።ሕገ መንግሥቱ እንደ ሕንፃና እንደ አውራ ጎዳና ነው፤ በየወቅቱ እየተከታተሉ፤ ማደስ፤ መለወጥ፤ መስተካከልና መጠገን የሚሻ ነው። አስፈላጊ ከሆነም ያለው ግንብ ወይም ጎዳና አፍርሶ በአዲስ መለወጥም ይቻላል።

ይሁንና በድሮው ምልከት በህብረ ቀለማቱ በሌለው ባንዴራና ህገ መንግሥት እንቀጥል ከተባለ፤ ሕገ መንግሥቱና ባንዴራው በሥራ እያሉ ለምን በምድሪቱ የብሔር ጥያቄ ያነገቡ ድርጅቶች እንደ አሸን ፈሉ? አገራዊ አጀንዳ ይዘው ከወጡ ጥቂት አንጋፋ ድርጅቶች በቀር አብዛኞቹ በብሔር ጥያቄ ማዕድ ዙሩያ የተሰለፉ አልነበሩምን? አሁንም ቢሆን ሃገራዊ አጀንዳ ካላቸው በብሔር ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱት እንደሚበዙ መገንዘብ ይቻላል።

ይህ ምን የፈጠረው ነው? ጠባብነት ይባል ይሆንን? አይመስለኝም! ብሔራዊ ድርጅቶች ጠባቦች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በብሔር መደራጀት ጠባብነት ብሎ ማጠቃለል አይቻልም። የብሔር ጥያቄ እንዲበዛ ያደረገው ነባራዊው ሁኔታ እንዲያ እንደሆን ስለሚያስገድደው ነው። ሰው በወል ከማሕበረሰቡ የሚጋራው ብሔራዊ መብቱ የግለ ሰብአዊ መብቱ ሲከበርለት ይቀዳጃዋል ማለት ዘበትና ቀልድ ነው። ተወደደም ተጠላ የሰው ጠቅላላ ሰብአዊ መብት ማለት የወልና የግል መብቶቹ መከበር ድምር ነው። እነዚህን ድምሮች የሚያሟላ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀትና ይህንን እውነታ የሚያንጸባርቅ ባንዴራ መኖር ግድ የሚል ነው። ዴሞክራሲ ማለት እነዚህን በሙላት አጠቃልሎ የሚይዝ ነው።

ዴሞክራሲ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ስለሆነ፤ የራስ መብት እንዲከበር የሚፈልግ ከዚያ ባልተነነሰ የሌላውን መብት ያለመንካት ግዴታ እንዳለበት ማወቅ ያስፈልጋል። ግዴታ

ያለ መብት ባርነት፤ መብት ያለ ግዴታ ደግሞ ስድነት ወይም ስርዓተ አልበኝነት ነውና ዴሞክራሲ በእነዚህ መካከል ሚዛኑ የጠበቀ እንጂ ወደ አንደኛው ፅንፍ ወይም ጫፍ ያዘነበለ ወይም ያጋደለ መሆን አይገባውም።

የሚዘጋጀው ሕገ መንግሥትና የሚወጣው ባንዴራ የማይነጣጠሉ ናቸው። ባንዴራው ሕገ መንግሥቱን መስሎ የሚወጣ ነው።ባንዴራው በሚወጣው በሕገ መንግሥት መሰረት የሚወሰንና ሁሉንም ህዝቦች የሚወክል መሆን ያለበት ነው። እዚህ ላይ በግንባር ቀደምትነት ለኢትዮጵያ ለታሪክ አብይ ሥፍራ መስጠት የሚያስፈልግ እንደሆነ አጽንኦት ሳይሰጠው ማለፍ ተገቢ አይሆንም።

ወደ ማጠቃለያው ሲኬድ ተደምረናል ከሚሉት ጥቂቶቹ ፌዴራልዝምን መሰረት ያደረገው ሕገ መንግሥት ባንድም በሌላም መንገድ ሲቃወሙት ይስተዋላሉ። መቃወማቸው አይከፋም፤ ዳሩ ግን የሚቃወሙበት ምክንያት እስከነ መፍትሄው አቅርበው የማሳመን ግዴታ ደግሞ አለባቸው። ያለበለዚያ በጭፍን አመለካከት የሌሎችን መብት የማስከበር ግዴታ ሳይወጡ በሌላው ጫንቃ ላይ ቀንበርን የመጣል አባዜ ከዴሚክራሲ ሕግጋትና ደንቦች የሚጣረስና የሚቃረን ስለሆነ ተቀባይነት አይኖረውም።

በድሮው ሕገ መንግሥትና ባንዴራ መቀጠል አለብን ከሚሉት አብዛኛዎቹ፤ በስሜት ተገፋፍተው በየዋህነት የሚጓዙ ሲሆን፤ ዓላማ አድርገው የተነሱ ጥቂት ብልጦች የጦር ዕቃዎቻቸው ወይም የመጠቀሚያ መሣሪያዎቸቸው አድርገው የሚጠቀሙባቸው ምስኪኖች ናቸው።እንዲህ ላሉት ወገኖች አቅም በፈቀደ መጠን ሳይታክቱ የመደመርና የአንድነት ምንነት እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል። ዜጋ እንዴትና በምን መልኩ መደመር እንዳለበት ማወቁ ከብዙ ጉዳትና አደጋ ሊታደግና ሊያድን ይችላል።

ዓላማው በመደመርና በአንድነት አስታክኮና አስብቦ እያወቁ በሌሎች መብት ላይ ችግር መፍጠር ግን ገና ከእንጭጩ ሊቃወሙት የተገባና ሊጠራ፤ ሊነጻና ሊንገዋለል የተገባ ነው።ይህን በነጻ መድረክ በሚገኝ እድል ሃሳባቸውን በበቂና በአሳማኝ መንገድ በመማረክና በማስበርከክ የሚገኝ ሰለማዊ ድል ነው።

Back to Front Page