<

Back to Front Page

br>Share This Article!
Share
በብሄር መሰባሰብ ችግሩ ያለው የት ላይ ነው?

በብሄር መሰባሰብ ችግሩ ያለው የት ላይ ነው?

ዶ/ር ዮሃንስ አበራ አየለ 09-20-18

ኢትዮጵያ ውስጥ ወገን ለይቶ መቀራረብና መጠቃቀም መረዳዳት ለዘመናት የኖረና የተለመደ ነው። ሰዎች በእለት ተእለት ኑሯቸው በቋንቋ፣ በባህል፣ በስነልቦና ከሚመሳሰሏቸው ሰዎች ጋር ቢመቻቹ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ይህ መቧደን የብሄር፣ የጎሳ፣ የወረዳ፣የአውራጃ፣ የጎጥ፣ ወዘተ ቅርፅ ሊይዝ ይችላል። በአብዛኛውም ስብስቡ ከጎጥ ጀምሮ እስከ ብሄር ድረስ የሚደርስ፣ ከሌላው የስብስብ ደረጃ አኳያ እየታየ የሚፈጠር ይሆናል።  የጉሎ መኸዳ ወረዳ ስብስቡ እንዳለ ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ ወይንም የሌላው መሰባሰብ ደረጃ እያዩ ወደ ዓጋመ አውራጃ ደረጃ መሰባሰብ አስፈላጊ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ይህ በሌላውም አካባቢ የሚታይ የስብስብ ደረጃ ነው። ማርቆስ ብሎ ጎጃም፣ ደብረታቦር ብሎ ጎንደር፣ ደምቢደሎ ብሎ ወለጋ፣ ማይምሻም ብሎ ዓድዋ፣ ራያ ቆቦ ብሎ ወሎ የመሳሰሉ ስብስቦች እንደአስፈላጊነቱ ወደ ክልላዊ ማንነት ስብስብም ሊያድጉ ይችላሉ። በውጪው አለም የስደት ኑሮ ውስጥ ስብስቡ ወደ ሃገር ደረጃ አድጎ ኢትዮጵያዊነት የመሰባሰብያ መመዘኛ ይሆናል።

Videos From Around The World

በወገን፣ ማለት በብሄር፣ በጎሳ፣ በወረዳ፣በአውራጃ፣ በጎጥ መሰባስብ የአገር ትልቅ ፈተና የሚሆነው ስብስቡ እርስ በርሱ የሚረዳዳውና የሚጠቃቀመው ከሃገር ሃብት ከድርሻው በላይ በመውሰድ ለቡድኑ አባላት የተለየ ጥቅም ሲያስገኝ፤ ባጋጣሚ ይሁን በጉልበት፣ በብልጠት ይሁን በእውቀት ባገኝው ስልጣንና ሃላፊነት ወገኔ ነው ለሚለው በአድልዎ ሲሰራ፤ ለቡድኖቹ መሪዎች የኢኮኖሚና የፓለቲካ ጥቅም ወይንም የግል ዝና ሲባል "ሌላ" የሚሉትን ስብስብና አባላቱን ሲያራክሱ፣ ሲያሳድዱ፣ ሲገድሉ፣ሲያቆስሉና ንብረቱን ሲዘርፉ፤ "አለቦታው" ተገኝቷል በሚል (አለም ትንሽ መንደር በሆነችበት ዘመን) በጥንታዊ ጋርዮሽ አስተሳሰብ ደረጃ የሰው ልጆችን መሠረታዊ ሰብአዊና ህገ መንግስታዊ መብት ሲጥሱ ነው።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በየዘመኑ ጊዜ ያነሳቸው ወይንም የዘር ሃረግ መዘው የወረዳ፣ የአውራጃ፣ የጠቅላይ ግዛት፣ ወዘተ ገዢዎች በማድረግ ራሳቸውን የሰየሙ ግለሰቦች ህዝቡን በወረዳ፣ በአውራጃ፣ በጠቅላይ ግዛት አለያይተው አንዱ በሌላው ላይ አለኝ የሚለውን ብልጫ በማጋነን የስድብና የሙገሳ ተረትና ምሳሌዎችና ቀልዶች እየፈበረኩ እርስ በርሱ ሲያጋድሉት መኖራቸው ሳይበቃ እስካሁን ድረስ የልዮነትና የጥላቻ መነሻ ሆኖ ቀርቷል። በክልል ማንነት ተሸፍነው የሚጋጋሙት የአውራጃ/ ዞን ልዩነቶች አንዳንድ ደካማ ፓትቲከኞች የሚጠቀሙባቸው ያለፉት ዘመናት አስቀያሚ ቅሪቶች ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ ይህን ከሃገራዊነት በታች ያለው መሰባሰብ ምን ብለን እንደምንጠራው ተችግረናል። ብሄር? ብሄረሰብ? ህዝብ?፣ ጎሳ?፣ ክልልኛ? በንጉሱ ዘመን ጎሳ ሲባል (አሁንም የሚሉ አሉ)፣ በደርግ ዘመን ብሄረሰብ ሲባል፣ በኢህአዲግ ዘመን ደግሞ ብሄር/ ብሄረሰብ/ ህዝብ ሲባል የማያሻማና ለአፈፃፀም የሚመች ትርጉም አልተሰጠውም። በአሁኑ ወቅት ሁሉም "ብሄሮች" እየተባሉ ስለሆኑና የስያሜው ትርጉም አሻሚነት ለጊዜው ችላ በማለት በፅሁፌ ርእስነት ተጠቅሜበታለሁ።

የኢትዮጵያውያን ሁለተኛ ማንነት የአገሪቱ የውስጣዊ አስተዳደር ካርታ በተቀየረ ቁጥር አብሮ ሲቀየር ኖሯል። ሸዌው ኢጆሌ ስላሌ በአዲሱ የቋንቋ ካርታ ኦሮሞ ሆኗል፤ ወሎየ ነኝ ሲል የኖረው የአያሌው መስፍኑ ላሌ ጉማም ትግራዋይ ሆኗል፤ የአባዩ ልጅ ጎጃሜም ከሽዌው ጋር በሚያገናኘው ድልድይ ሲቆጭ ኖሮ ከሽዋ ጋር አማራ ሆኖ አረፈው። ይህ የሚያሳየው ሰው ከመሆናችን ውጪ ያለው ማንነት እንደ አፍኝጫችን ፊታችን ላይ ተለጥፎ እንዳልተፈጠረ ነው።

በእርግጠኛነት  በ"ውክልና" ሳይሆን ቀጥተኛ ይሁንታ መሠረት ያደረገና የሌላውን መብት የሚያከብር መሰባሰብ ተቀባይነት አለው:: የዲሞክራሲ ዋናው ምሶሶም የህዝቡ ቀጥተኛ ይሁንታ ነው። እንኳንና በብሄር መካለል ይቅርና ለታዛቢው የመረረ ለቅሶ ያስለቅሳል እንጂ አንድ ህዝብ በሙሉ ድምፅ ራሱን ለማጥፋት ቢወስን ውሳኔውን አክብሮ ከመቀበል ውጪ ምን ምርጫ ይኖራል?  ይህ የህዝብ ውሳኔ ግን እንደ ሳይንሳዊ መርህ ተቆጥሮ ሌላው ህዝብ ያለ ፍላጎቱ እንዲተገብረው ሊገድድ አይችልም። ብሄርተኝነት መያዣ እጀታ ስለሌለው ለራሳችን እስካልደከመን ድረስ ትከሻችን ላይ ይዘነው ብንዞር ማንም ላይ የሚያስከትለው ችግር የለም። ትልቅ ችግር የሚሆነው አሽካከሙን አላውቅበት ብለን እንጥለውና ሌላውን ሲጨፈልቅ ነው።

 

Back to Front Page